ኢዮብ እሸቱ

ኢዮብ እሸቱ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የሚድያ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ስራ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ የነበራቸውን ሰዎች ታሪክ እያሰባሰበ በመሰነድ ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህ በመረጃ እና በመዝናኛ ማቀበል ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በሀገረቱ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ላይ የሚኖራቸው እና የነበራቸው ሚና ከታሪክ መዝገብ ላይ መስፈር ይኖርበታል፡፡ ይህን ቀዳሚ መነሻ በማድረግ ብዙም ያልተነገረላቸው ግን የጎላ አሻራ የነበራቸውን ሰዎች ማስታወሱና ይህን ሰርተው ነበር ብሎ ሰነድ ማስቀመጡ አዲሱን ትውልድ እፎይ የሚያስብል ተግባር ነው፡፡ ድርጅታችንም በቅርቡ የ130 የመዝናኛ እና የመረጃ ስራ ላይ ጉልህ ስራ ሰርተዋል ብለን እኛ ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ ደረጃውን በጠበቀ መጽሀፍ እናሳትማለን፡፡

ይህ መዝገበ-አእምሮ የሚል ስያሜ የሰጠነው መጽሀፍ ከአመት በፊት በሀምሌ 30 2014 ያሳተምነው ተከታይ 2ኛ ቅጽ መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም በመጽሀፉ ላይ የሚወጡትን ሰዎች አልፎ አልፎ በተወዳጅ ሚድያ የዲጂታል እና የማህበራዊ አማራጮች ስለምናቀርብ ይከታተሉ ዘንድ እንጋብዛለን፡፡ አሁን በዚህ ጽሁፍ የህይወት እና የስራ ታሪኩ የሚዳሰስለት ሰው ኢዮብ እሸቱ ሲባል በሚድያ ስራ 25 አመት ቆይቷል፡፡ በተለይም ዘጋቢ ፊልሞችን ሲሰራ ይዋጣለታል፡፡ በህትመት ውጤቶች ላይ በሚያወጣቸው ጽሁፎችም ይታወቃል፡፡ ኢዮብ በኢትዮጵያ ብሮድስቲንግ ኮርፖሬሽን ለ23 አመት የሰራ ሲሆን አሁንም ሙያውን ወዶት እየሰራ ይገኛል፡፡ ኢዮብ ለተወዳጅ ሚድያ የሰጠውን መረጃ መሰረት በማድረግ እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው አጠናክሮታል፡፡

ትውልድ እና ዕድገት

የትውልድ ቦታው ምስራቅ ሐረርጌ፣ ከሐረር ከተማ 94 ኪ.ሜትር ርቃ በምትገኘው በደኖ ከተማ ነው፡፡ አሁን 47ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ የ1ኛ ደረጃ ትምህርቱን በተወለደባት ከተማ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሐረር ከተማ መድሃኒያለም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምሯል፡፡ ለሥነ- ፅሑፍ የነበረው ዝንባሌ ከታዳጊነቱ ይጀምራል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ የሥነ- ፅሁፍ ስልጠና ወስዶ በሐረር ከተማ ኋላ ላይ የብራና ስነ-ጥበባት ማዕከል የሆነውን የሥነ ፅሁፍ ክለብ፣ አሰልጣኙ ከነበረው ካሳ ርጥብነህ እና ከሌሎች ወጣቶች ጋር ሆኖ በመመስረት በስነ- ፅሁፍ ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡ ማዕከሉ ሐረርን ጨምሮ በድሬዳዋ፣ በጉርሱም፣ በጅግጅጋ እንዲሁም በተለያዩ ከተሞች የተለያዩ ይዘት ያላቸውን የኪነ -ጥበብ ሥራዎችን ያቀርብ ነበር፡፡ (ማዕከሉ ጋዜጠኛ፣ ተዋናይ እና የአይ ቲ ባለሞያ አበበ ፈለቀ፣ ድምፃዊት ሐይማኖት ግርማ፣ ተዋናይት ፍሬሕይወት አሰፋን ጨምሮ ጥሩ ደረጃ የደረሱ በርካታ አባላት ነበሩበት፡፡) በአፋን ኦሮሞ ፕሮግራሞቹ ተወዳጅ በነበረው በሐረር ሬዲዮ ጣቢያ በሳምንታዊ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን የጥበብ ስራዎችን ያቀርብ ነበር፡፡

በብራና የኪነ-ጥበብ ማዕከል ሳለ በርከት ያሉ መጣጥፎችን፣ አጫጭር ልብ ወለዶችን፣ ግጥሞችን፣ መካከለኛ ርዝመት ያላቸው የቴአትር ድርሰቶችን ይፅፍ ነበር፡፡ አልፎ አልፎም የፅሁፍ ሥራዎቹን አዲስ አበባ እየላከ ሕብር፣ አዲስ ዘመን፣ የብራና ማህደር…የተሰኙ መፅሔት እና ጋዜጦች ላይ የሕትመት ውጤቶች ላይ ይወጡለት ነበር፡፡

የሥራ ዓለም

1990 ኢዮብ ወደ ሥራ ዓለም ገባ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ማስተባበሪያ ከመላው የኦሮሚያ ዞኖች ሪፖርተር ለመቅጠር ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ ኢዮብም በወዳጁ አበበ ፈለቀ ጎትጓችነት ተመዝግቦ፣ ተወዳድሮ ያልፋል፡፡ ሐረር ከተማን ለቆም የetv አፋን ኦሮሞ ማስተባበሪያ ጀማሪ ሪፖርተር ሆኖ ተቀጥሮ አዲስ አበባ ገባ፡፡ በአፋን ኦሮሞ ማስተባበሪያ ክፍል፣ በዜና ክፍል ለተወሰነ ጊዜ፣ በፕሮግራም ክፍል ደግሞ የተለያዩ ፕሮግራሞች አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል፡፡ Dargaggootaaf (የወጣቶች ፕሮግራም)፣ AADAA (የባህል ፕሮግራም)፣ ከፓርላማ፣ Tibbanaa (ወቅታዊ ዝግጅት)፣ Itoophiyaa Quba Qabdu (በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ- ኢትዮጵያዊያን ይዘጋጅ የነበረ ሳምንታዊ ፕሮግራም) ፕሮግራሞችን ያዘጋጅ ነበር፡፡

የኢቴቪ አፋን ኦሮሞ ማስተባበሪያ ጋዜጠኛ ሳለ፣ አቡነ ጴጥሮስ ከሚገኘው የጋዜጠኝነት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምሽት ፕሮግራም ለሁለት ግዜያት ያህል ትምህርት ጀምሮ በራሱ አባባል ’በገዛራሴ ስንፍናና እና ከሥራ ጋርም አልጣጣም ስላለኝ’ የመጀመሪያውን ዓመት እንኳን ሳያጠናቅቅ አቋርጧል፡፡ ከአይረሴ የአፋን ኦሮሞ ጋዜጠኝነት ዘመኑ ለመጥቀስ፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ቡሬ ግንባር ዘምቶ ዘገባዎችን ሰርቷል፡፡ ለ97 ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የጉጂ ኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ሲጀመር በሥፍራው ተገኝቶ ተከታታይ ክፍል ያላቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ሰርቷል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰፊ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ (15 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ) የተራቡበትን አስከፊ ድርቅ እና ርሀብ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ተዘዋውሮ በዜናና እና በፕሮግራም ዘግቧል፡፡ አገሪቷ በግብርና የተትረፈረፈ ምርት አገኘች በተባለበት ዘመንም በየክልሎች በመዞር ዘገባ ሰርቷል፡፡ የታሪክ፣ የተፈጥሮ፣ የባሕል…ቅርሶችን በኢትዮጵያ ምድር በመዞር ለኢትዮጵያዊያን መልሶ አቅርቧል፡፡

በአፋን ኦሮሞ ማስተባበሪያ ለስምንት ዓመታት ያህል የሰራው ኢዮብ፣ ወደ አማርኛ ክፍል ተዛወረ፡፡ እዛም በወጣቶች ፕሮግራም፣ መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲ በሚባል ወቅታዊ ዝግጅት ክፍል ብሎም ኮርፖሬሽኑ ለመጀመሪያ ግዜ የዶክመንታሪ ዲፓርትመንት ሲያቋቁም ወደ ክፍሉ በመመደብ እስከዛሬ ድረስ በርካታ ርዕሰ -ጉዳዮችን የዳሰሱ ዘጋቢ ፊልሞችን እያዘጋጀ ይገኛል። ዲፓርትመንቱ ሲቋቋም አዲስ እንደመሆኑ፣ ክፍሉ የላቁ ሥራዎች እንዲሰራ ትኩረት በመስጠትና እንደ ተቋሙ አቅም መሟላት የሚገባቸው ማቴሪያሎች እና የሰው ኃል እንዲሟላ ከፍተኛ ጥረት በማድረጉ በምክትል ሥራ አስኪያጅ ደረጃ ኃላፊ የነበረውን ተሻለ በቀለን ሳላመሰግነው ማለፍ አልፈልግም ይላል፡፡

ትልቁ ምኞቴ ደረጃቸው ከፍ ያለ፣ ጥልቅ ይዘት ያላቸው፣ ዓይን የሚገልጡ ዘጋቢ ፊልሞችን መስራት ነው የሚለው ኢዮብ እስከዛሬ ባይሳካልኝም ወደፊት አሳካዋለሁ ይላል፡፡ እስከዛሬ የሰራቸውን በሱ ሚዛን ዘጋቢ ፊልም የሚመስሉ እንጂ አፍ ሞልቶ ዶኩመንተሪ ፊልም ናቸው የሚያስብሉ አይደሉም ይላል፡፡ ባለሁበት ተቋምም ሆነ እንደ አገር በኢትዮጵያ ደረጃ ለመስራት ጥረቶች ተደርገዋል እንጂ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ዘጋቢ ፊልሞች ብዙ ተሰርተዋል የሚል እምነት የለውም፡፡ እነ ግርማ ያኒ እና አበራ ሳህሌን የመሳሰሉ ጥልቅ ይዘት ያላቸው ዘጋቢ ፊልሞችን የሚሰሩ ጋዜጠኞችን ግን ሳያደንቃቸው አያልፍም፡፡ ኢዮብ በኢቢሲ ዶኩመንተሪ ዲፓርትመንት ሆኖ በአዘጋጅነት ከሰራቸው ዘጋቢ ፊልሞች ውስጥ፡

  • ኢትዮጵያ ነገ፣
  • ቀናነት፣
  • የብርሐን ዘመን፣
  • አንቀፅ 88፣
  • ኢትዮጵያን ለመቀራመት፣
  • ጥርስ የገባች ኢትዮጵያ፣
  • የአፈ ጉባኤው ውሎ፣
  • የሕዳሴ ውል፣
  • …መቼም ላይደገም፣
  • የኢትዮጵያ ክንድ፣
  • 1 ቢሊዮን ጣቶች፣
  • አብሮነት፣
  • አዲስን በ24 ሰዓት፣
  • የገዳ አስተዳደር፣
  • የኢትዮጵያ ፈርጦች፣
  • የትስስር ማህተም፣
  • ስደት-ተስፋ-ሞት፣
  • ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም፣
  • ዓለም- ሠላም- ኢትዮጵያ፣
  • ይህ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ነው፣
  • ቤት ለምቦሳ፣
  • የጥልቅ አስተሳሰብ ባለቤት፣
  • የሕዝቦች ልደት፣
  • ኢትዮጵያ፣
  • ባለፈርጥ ኮከብ፣
  • የዘመን ጅረት፣
  • ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም…. ይጠቀሳሉ፡፡

በ EBC በቆየባቸው ዓመታት ከጋምቤላ ክልል በስተቀረ ሁሉንም የኢትዮጵያ ክልሎች ተዘዋውሮ አይቷቸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ እስራኤል፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሱዳን(ሰሜን)፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዱባይ፣ ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ባይድዋ-ሶማሊያ እና ቻይናን በሥራ ምክንያት ተጉዞ የማየት ዕድሉ ገጥሞታል፡፡በጋዜጠኝነት ህይወቱ ከሚደሰትባቸው ነገሮች አንዱ በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ ግለሰቦችን አግኝቶ ከነሱ ጋር ማውራት እና ቃለ መጠይቅ ማድረግ መቻሉ ነው፡፡ በርካታ ምሁራንንና እና ታዋቂ ግለሰቦችን ብሎም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡ በስም ከሚታወቁቱ መሀከል የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፣ ፕሮፌሰር አየለ በከሬ፣ ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ፣ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ገ/እግዚአብሔር፣ ድምፃዊ ዘለቀ ገሰሰ፣ ድምፃዊት ማሕሌት ገ/ጊዮርጊስ፣ አቶ ካህሳይ ገ/እግዚአብሔር፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ ፕሮፌሰር አደም ካሚል፣ አባ ገዳ አጋ ጠንጠኖ፣ አቶ ልደቱ አያሌው፣ ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ፣ ፕሮፌሰር ለገሰ ነጋሽ፣ ዶ/ር ኤሊዛቤጥ ወ/ጊዮርጊስ፣ አርኪቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ፣ አቶ ካሳ ተክለብርሐን፣ አቶ ተሾመ ቶጋ፣ ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል፣ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ፣ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ፣ አምባሳደር መሐመድ ድሪር፣ ፕሮፌሰር ጆን አቢንክ፣ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፣ ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ፣ ዶ/ር ጌታቸው ካሳ፣ ዶ/ር ሳሙኤል ተፈራ፣ ዶ/ር ኢዮብ ተስፋዬ፣ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ፣ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሀ፣ ፕሮፌሰር አሰፋ እንደሻው፣ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ፣ ወ/ሮ ፍሬዓለም ሺባባው፣ ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ፣ አቶ አማረ አረጋዊ፣ አቶ ሽፈራው ጃርሶ፣ ከአቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተስፋዩ፣ ሌ/ጀነራል ታደሰ ወረደ፣ ሜ/ጀነራል ባጫ ደበሌ፣ ሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ፣ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ አምባሳደር ህላዌ ዮሴፍ፣ ዶ/ር ሳሙኤል አሰፋ፣ አቶ ክቡር ነጋ፣ አቶ ልደቱ አያሌው፣ ዶ/ር ብርሐኑ ሌንጂሶ፣ ኢንጂነር ጌታሁን ሔራሞ፣ አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ፣ ፕሮፌሰር መድሀኔ ታደሰ፣ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማሪያም፣ ፕ/ር መሳይ ከበደ፣ አቶ ዳዊት ዮሐንስ፣ አቶ ግርማ ብሩ፣ አቡነ ማቲያስ፣ አቶ ሳሙኤል ታፈሰ፣ አቶ ያረጋል አይሸሹም፣ ዶ/ር ካሱ ኢላላ፣ …እና ሌሎች በርካታ የሕይወት እይታውን ያሰፉለት ግለሰቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሌሎች ሥራዎች

ኢዮብ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሆኖ በተቀጠረበት ዘመን፣ የሆነ ወቅት ላይ (ማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት ብርሀን ኃይሉ የድርጅታችን ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት)፣ የጥቅም ግጭት ስለሚያመጣ፣ ጋዜጠኞች ማስታወቂያ መስራት አይችሉም ተብሎ እስከተከለከለበት ጊዜ ድረስ፣ ለሌሎች ድርጅቶች ማስታወቂያ መስራትን የሚከለከል ስላልነበረ፣ ኢዮብም ለሰራዊት ፍቅሬ የማስታወቂያ ድርጅት፣ ለካክተስእና ከሌሎችም ማስታወቂያ የሚያሰሩ ተቋማት ጋር በኮንትራት መልክ የተለያዩ የሕትመት፣ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ሥራዎችን በአፋን ኦሮሞ ሰርቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ፣ የተለያዩ መፅሄቶች ላይም በአምደኝነት ፅፏል፡፡ በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ታዋቂ እና ተወዳጅ ብሎም አወዛጋቢ ስብዕናና አስተምህሮ ያለውን የሽሬ ራጅኔሽ ባግዋን(ኦሾ) ረቂቅ ፍልስፍናዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሳይንሳዊ፣ ስነፅሁፋዊ፣ ስነ ልቦናዊና የመገለጥ ሀሳቦቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መፅሔት በማምጣትና ለአስር ዓመታት ያህል ማክዳ እና ላይፍ የተሰኙ መፅሔቶች ላይ በመተርጎም ኦሾን ከአንባቢያን ጋር አስተዋውቆታል። ከማክዳና ላይፍ መፅሔቶች ባሻገር ቃልኪዳን፣ እቴጌ፣ ሮዳስ የተሰኙ መፅሔቶች እና ጋዜጦች ላይም የተለያዩ የስነልቦና፣ የእውነተኛ ታሪክ፣ የኪነጥበብ፣ የፍልስፍና፣ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች፣ ስነ ክዋክብት…ወዘተ ፅሁፎችን (በአብዛኛው ትርጉም) ያቀርብ ነበር።

አንዳንድ ነገሮች

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን) ለ23 ዓመታት (ከጀማሪ ሪፖርተርነት እስከ ከፍተኛ ኤዲተርነት) ያገለገለው ኢዮብ ኢቢሲ ስለ ህይወት፣ ስለ ፖለቲካ፣ ስለ ታሪክ፣ ስለ አገር…ወዘተ ብዙ እንድረዳ የረዳኝ፣ መስሪያ ቤቴ ብቻ ሳይሆን ትምህርት ተቋሜም ነው ይላል፡፡ ጋዜጠኝነት ንፁህ መረጃ ብቻ ማቅረብ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ-ይሄ ስህተት ነው፡፡ ጋዜጠኝነት የተዛባ መረጃም ማቅረብ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ-ይሄም የተሳሳተ ነው፡፡ ጋዜጠኝነት እንደየተቋሙ ኤዲቶሪያል ፖሊሲና እንደየሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም ለሀገርም ለዞጎችም የማይጎዳ፣ ተጠርቦና ተቀርጾ የሚሰጥ መረጃ ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ህይወቱ ብዙ አስደሳች እና አንዳንዴም ግርም የሚሉ ነገሮች ገጥመውት የሚያውቁት ኢዮብ የተወሰኑትን ጠቅሶልናል፡

የአማርኛ ክፍል የወጣቶች ፕሮግራም አዘጋጅ ሳለ፣ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን (ወጣት ሳለሁ በሚል ፕሮግራም) እንግዳ አድርጎ የወጣትነት ዘመናቸውን ዘና በሚያደርግ መልኩ የሚያስታውስ ቃለ መጠይቅ ካደረገላቸው በኋላ በመጨረሻ ዘፈን ምረጡ ሲባሉ የራሔል ዮሐንስን ማንኛውንም ዘፈን ወይንም የቴዲ አፍሮን ‘አቦጊዳ’ መረጡ፡፡ ኢዮብም ለወጣቶች ፕሮግራም ትክክለኛ ይሆናል ያለውን የቴዲ አፍሮን አቡጊዳ ከቃለመጠይቁ በኋላ አስገብቶ ለኤዲተሩ ይሰጣል፡፡ በወቅቱ ታዲያ ቴዲ አነጋጋሪ ድምፃዊ ስለነበር (ምንም እንኳ የቴዲ አፍሮ ዘፈን መተላለፍ የለበትም የሚል መመሪያ ባይቀመጥም) አርታኢዎቹ ‘ይሄ ነገር ዘፈኑ ቢቀር ይሻላል’ በሚል አርታኢው፣ የአርታኢው ኃላፊ፣ ከዛም ከፍ ያለ አለቃ ተጨቃጭቀው ’ጎመን በጤና’ በሚል ርዕሰ ብሔሩ የመረጡት ሙዚቃ ተቆርጦ ቃለ መጠይቁ ብቻ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡

ሌላኛው ኢዮብ ከቀድሞው ጠ/ሚ/ር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አራት ግዜ ያህል ቃለመጠይቅ አድርጓል። ጠ/ሚ/ር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እያሉ በዛ ቦታ ሆነው የመጨረሻውን ቃለ መጠይቅ ሰርቷቸዋል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታቸውን ሊለቁ የሁለት ወር ዕድሜ ሲቀራቸው የመጨረሻውንና የተደመምኩበትን፣ ጠንከር ብለው ያወሩበትን አንድ ሰዓት ተኩል የፈጀና በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰ ቃለ መጠይቅ አድርጌ ነበር። ቃለ መጠይቁ አንድም የአንድ ለአንድ ቃለ መጠይቁ እንዳለ አየር ላይ እንዲውል ብሎም የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሕይወት ታሪክ ተሰርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን ሲለቁ ዓየር ላይ ለሚውል ዘጋቢ ፊልም ግብዓት እንዲሆን የተደረገ ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የፖለቲካው ሁኔታ ጡዘት ላይ የደረሰበት እና ነገሮች ያልለዩበት በመሆኑ ሊተላለፍ ዝግጅት ላይ እንዳለ ‘ይቆይ ተብሏል’ በሚል ሳይተላለፍ ቀርቷል።

እኒህን የመሳሰሉ በርካታ የሥራው ዓለም ገጠመኞች አሉት፡፡ ኢዮብ ዕድሜያቸው 13 እና 11 የሆኑ የሁለት ልጆች (ሴት እና ወንድ) አባት ነው፡፡ ጓደኞቹ “ከሠው ተለይቶ መኖር የሚቻል የማይመስለው፣ ሠው ይወዳል፡፡” ይሉታል፡፡ ኢዮብ ደግሞ “አሁን ላይ ’ሠው ይፈራል’ ተብሎ ይስተካከልልኝ፡፡” ሲል ይመልሳል፡፡ ማህበራዊ ግንኙነቱ ሰፊ ነው፡፡ ከልጆቹ እና ጓደኞቹ ቀጥሎ የሚደሰትባቸው ነገሮች መፅሐፍት፣ ሙዚቃ እና ዶኩመንተሪ ፊልሞችን መሥራት ናቸው፡፡ “መፅሐፍትን እወዳለሁ እንጂ ያን ያህል አንባቢ የምባል ዓይነት ሰው አይደለሁም፤ ጃፓኖች Tsundoku የሚሉት ዓይነት ሰው ነኝ፡፡” ይላል ኢዮብ፡፡ እንዲያም ሆኖ የሚያስደስተው ነገር ግን ሙዚቃና ንባብ ነው፡፡

ኢዮብ እሸቱ በአበበ ፈለቀ አንደበት ሲታወስ

ትውውቃቸው በ1983 ዓ.ም ሐረር እንደሚጀምርና ከኢዮብ እሼቴ ጋር ጠበቅ ያለ ወዳጅነት እንዳላቸው የሚናገረው አበበ ፈለቀ በጓደኝነት ወደ 32 አመት እንዳሳለፉና አብረው እንደቆዩ ይገልጻል። በወቅቱ ሐረር ውስጥ የሚሰጠውን የሥነ ፅሁፍ ትምህርት አብረው መውሰዳቸውን እና በስምንት ሰዎች መስራችነት የተመሰረተውን ብራና የሥነ ፅሁፍ ማህበርን ከዛም ብራና የኪነ ጥበብ ማዕከልን ማቋቋማቸውን ገልጿል።
መድረክ ትወናን ጨምሮ ከኢዮብ ጋር በርካታ ስራዎች አብረን ሰርተናል የሚለው አበበ፥ ኢዮብ የሚደነቅ የሥነ ፅሁፍ ችሎታ ያለውና ድርሰት እንደሚጽፍም ነው የሚገልጸው፤ ኢዮብን ሲገልጸው ‘ሃሳብ የማያልቅበት ሰው’ ይለዋል። “ከምንም በላይ ግን ኢዮብን ለንባብ ባለው ፍቅር አደንቀዋለሁ፤ አከብረዋለሁም” ነው የሚለው።

ኢዮብ የእውቀትና የንባብ ማዕከል እና ከምንም በላይ ማንበብ የሚያስደስተው ሰው እና ንባብ እንደሚወድም ነው የሚናገረው። በዚህ በኩል (በማንበብ ማለቱ ነው) እረፍት የሌለውና የማከብረው ሰው ነው ሲልም ይገልዋል ኢዮብ ከንባብ ጋር ያለውን ቁርኝት ሲገልጽ። ስለ ባህሪው ሲናገርም “በባህሪ ደረጃ ሰው አፍቃሪ፣ ሰው ወዳድ እና ለራሱ የማያደላ የሚወደድ ተፈጥሮ ያለው፤ ከራሱ የበለጠ ለሰው የሚኖር፣ የዋህና የማይታበይ ሲልም ነው የሚገልጸው። ሁልጊዜም ቢሆን አዲስ ነገር ለማወቅና ለመለማመድ ዝግጁ የሆነ፤ ለሰው መስጠትንና ለሰው ማድረግን ተፈጥሯዊ ስጦታው ያደረገ መልካም ሰው ስለመሆኑም ይናገራል።

ሐረር በትምህርትም በስራም የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ መዛወራቸውን የሚያነሳው አበበ፥ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም በአዲስ አበባ የብራናን ቅርንጫፍ በማቋቋም አብረው መስራት መቀጠላቸውን ነው የሚያስረዳው። እርሱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ በጋራ “ዘጋቢ ፊልሞች፣ ቪዲዮዎች እና ድራማዎችን ከመስራት ባለፈ የሥነ ፅሁፍ ዝግጅቶችን አብረን እናቀርብ” ነበር ሲልም የአዲስ አበባ ቆይታቸውን ያብራራል። ኢዮብ እንደ ሐረር ልጅነቱ መኖሪያ ቤቱ ከሐረር የመጣ ሰው የሚውል የሚያድርበት ከመሆኑ አንጻር ‘የሐረር ኤምባሲ’ ነበር የሚባለው ሲልም መልካምነቱንና እንግዳ ተቀባይነቱን ያስታውሳል። “ወደ ቴሌቪዥን ከገባም በኋላ በተለይም ዘጋቢ ፊልሞችን ይሰራ ነበር” የሚለው አበበ “ኢዮብ ምናልባትም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አሉኝ ከሚላቸው ምርጥ ፕሮዲውሰሮች አንዱ” መሆኑን ይጠቅሳል። ስለ ኢዮብ የስራ ብቃት ሲያስታውስም “በፈጠራ ደረጃ ኢዮብ ጎበዝና የላቀ ችሎታ ያለው” ነው ይላል። ከሁሉም በላይ ግን ከኢዮብ ጋር ቁጭ ብሎ ጊዜ ያሳለፈ ሰው አትራፊ ነው፤ “ምክንያቱም ከእርሱ ጋር ጊዜ ካሳለፍክ አንድ ነገር አውቀህ ነውና የምትሄደው” የጓደኛውን የእውቀት ደረጃ ያስረዳል። ኢዮብ በጣት ከሚቆጠሩና ጥቂት ግሩም ጓደኞቸ መካከል አንደኛው ነው በማለት ስለ እርሱ መልካምነት የሚገልጸው አበበ፥ “ኢዮብ የማደደንቀው፣ የማከብረው እና የምወደው ጓደኛየ ነው” ሲል ለእርሱ ያለውን ስሜት ይገልጻል።

ኢዮብ እሸቱ በሀብቱ ግርማ

በአገራችን ብሒል እውቀት ትሑት ያደርጋል ይላሉ፡፡ የማወቅ ትልቁ እርካብም ሰውን ለመውደድ ክፍት መሆን ይሰጣል ብለው ይገልጹታል፡፡ እዮብ እሸት የትሕትና እና ሰውን የመውደድ መልክ ነው፡፡ ሰውንም ሲቀበል ያለውን በጎ ፍሬ ለማድመጥ የሚቀድም ፣ ተፃራሪ ስሜት ያላቸው ልጆች እንኳን እርሱ ካለ ክፉ ስሜታቸውን ጥለው የሚሰባሰቡበት ዋርካ ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ሕይወቱም በኢትዮጵያ የፓለቲካ ተሳትፎ ንቁ እና አይገኜ የሆኑትን ሰዎች ቃለመጠይቅ አድርጓል፡፡ አንደኛው እንድርያስ እሸቴ ነው፡፡

እዮብ እሸቱ በተለይም በጎላ ሚካኤል አካባቢ በነበረው ቤቱ ብዙ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሚሰባሰቡበት ታዛቸው ነበር፡፡ ብዙ ጽሑፎች ፣ ድራማዎች እና የጋዜጠኝነት ፕሮግራሞች ታስበውበታል ፤ ተዘጋጅተውበታል፡፡ አንደበቱ ለበጎ እሴት የቀደመ ፣ እጆቹ ለቸርነት የቀደሙ ፣ በሙያው ከትልልቆቹ ሕያውያን አንዱ ቢሆንም አንገቱን ደፍቶ ፤ ልቡን በትሕትና አጥምቆ ሙያ እና ሰውነትን የታረቁበት ሰው ነው፡፡

የኢዮብን የቲቪ ሥራዎች የተወሰኑትን ከዩቲዩብ እንድትመለከቷቸው ሊንካቸውን እነሆ፡

https://www.youtube.com/watch?v=NmYvwJelZqw&t=249s&pp=ygUW4Yqi4Ym14Yuu4Yy14YurIOGKkOGMiA%3D%3D
https://www.youtube.com/watch?v=-hCSglNaXx8&pp=ygUM4YmA4YqT4YqQ4Ym1
https://www.youtube.com/watch?v=AOy5PsawoKg&pp=ygUP4Yqg4YqV4YmA4Y2FIDg4
https://www.youtube.com/watch?v=zblQbHfaQrw&t=120s&pp=ygUnbwnhiqLhibXhi67hjLXhi6vhipUg4YiI4YiY4YmA4Yir4YiY4Ym1
https://www.youtube.com/watch?v=-1UZB4Rk300&pp=ygUm4Yyl4Yit4Yi1IOGLqOGMiOGJo-GJvSDhiqLhibXhi67hjLXhi6s%3D
https://www.youtube.com/watch?v=E_qRSPbpY6g&pp=ygUc4Yuo4Yqi4Ym14Yuu4Yy14YurIOGKreGKleGLtQ%3D%3D
https://www.youtube.com/watch?v=xaJzraLdU4c&t=1631s&pp=ygUabwkxIOGJouGIiuGLruGKlSDhjKPhibbhib0%3D
https://www.youtube.com/watch?v=UtQi5osnkkA&t=247s&pp=ygUh4Yuo4YyI4YuzIOGKoOGIteGJsOGLs-GLsOGIreGNoyAg
https://www.youtube.com/watch?v=D2PtUTnEXcQ&t=1310s&pp=ygUa4Yi14Yuw4Ym1LeGJsOGIteGNiy3hiJ7hibU%3D

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *