ኢየሩሳሌም ነጋ
የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል የስነ-ጽሁፍ ባለሙያ ኢየሩሳሌም ነጋ ትገኝበታለች፡፡ ኢየሩሳሌም በህጻናት ስነ-ጽሁፍ ላይ አንድ አሻራ ለማኖር የሰራች ሲሆን የህይወት ታሪኳም እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
ኢየሩሳሌም ነጋ ከእናቷ አስካለ ቸርነት እና ከአባቷ ከሰዓሊ ነጋ ገብረመድህን በአዲስ አበባ ቤላ ተብላ በምትጠራ መንደር በ1967 ዓ.ም ሰኔ 10 ቀን ተወለደች፡፡ በሕብረት ፍሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአንደኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ፣ በከፍተኛ አስራ ሁለት (ካራማራ) ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቀቀች፡፡ በኢትዮጲያ ስነ-ጽሑፍ እና ፎከሎር የመጀመሪያ ዲግሪና የማስተርስ ድግሪ ተመርቃለች፡፡ በተጨማሪም ክህሎቷን ለማዳበር በርካታ አይነት ኮርሶችንና ጉባኤዎችን በመካፈል የምስክር ወረቀቶችን አግኝታለች፡፡
ኢየሩሳሌም የስነ-ጽሑፍ እና የክዋኔ ተሰጥኦ እንዳላት ያወቀችው በቤተክርስቲያን ውስጥ በምታደርገው አገልግሎት ነበር፡፡ ከዚያም በከፍተኛ አስራ ሁለት ትምህርት ቤት ውስጥ በትምህርት ቤቱ ሚዲያ በመሳተፍ፣ ትምህርት ቤቱ ከሌሎች ትምህርት ቤቶች ጋር በሚያደረጋቸው ውድድሮች አንደኛ በመውጣት መጻፍና ማሸነፍ እንደምትችል አወቀች፡፡ ኢየሩሳሌም በልጅነቷ ታጋሽ፣ አዳማጭ፣ ዝምተኛ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ብቻ የምታወራ፣ የልጆች ጨዋታ የማታዘወትርና ጓደቿ ሲጫወቱ ደብተራቸውን እየጠበቀች መጽሐፍ የምታነብ፣ በተጨማሪም እጅስራ የምትወድና ቤተሰብን በወጪ ላለማስወጣት ካገለገሉ ውድቅዳቂ ክሮች ሹራቦችና ቦርሳዎችን፣ ከጫማ ሶሎች ጫማዎችን በክር በመስራት ትገለገል እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ የልጅነት ህልሟ ደራሲ፣ ተመራማሪና ሳይንቲስት መሆን ነበር፡፡
ኢየሩሳሌም ነጋ በመጀመሪያ ወደ ስራው ዓለም የተቀላቀለችው በ”ዘገየ የህትመትና ማስተወቂያ አገልግሎት”፣ በሚታተሙ የተለያዩ ጋዜጦች አምድ ላይ፣ አጫጭር ልቦለዶች፣ ወጎች እና ግጥሞችን በመጻፍ፣ British Council ይታተም በነበረው Woman to woman በተሰኘው መጽሔት ላይ የጤና እና አጫጫር ልብወለዶች ዓምድ ላይ በመጻፍ እና በማዘጋጀት ወደ ጥበቡ ዓለም ተቀላቀለች፡፡ ወደ መደበኛ ስራ ስትገባ ደግሞ በመጀመሪያ መካኒሳ ይገኝ በነበረው ማዘር ትሬዛ ወላጅ አልባ ልጆች ማሳደጊያ የትምህርት አካዳሚ በመምህርነት እና በምክር አገልሎት 1988-1994 ድረስ ሰርታለች፣ Organization for Social Services for Aids (OSSA) ቀጣሪነት፣ “ጤናማ ወጣትነት” በሚል ስም በተሰየመ የራዲዮ ዝግጅት፣ F.M 97.1 እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ፕሮግራም በአዘጋጅና አቅራቢነት ከ1994-1996፣ ድረስ ቆይታለች፡፡ በትውልድህን አድን ኢትዮጲያ Save your generation (SUGA) የመድረክ ድራማዎችን በመጻፍ በማዘጋጀት እና በመተወን ከ1984-1994 ጀምሮ በትጋት ሰርታለች፡፡
ከስራዎቿ በተጓዳኛ ደግሞ፣ በፋና ብሮድካስት የጉም ጅቦች እና ሌሎች የሬዲዮ ድራማዎች፣ በPopulation Media Center የረገቡ ፈትሎች እና ሌሎች ድራማዎች፣ በኢትዮጲያ ቴሌቪዥን “መንታልብ”፣ “የጨቅላው ጣር”፣ “ዓይን” “የተሸጡ ልጆች”፣ “የጎዳናዋ ሙሽራ”፣ ሄሌውያ፣ “ንጋት” እና ሌሎች ድራማዎች ላይ ተሳትፋለች፡፡
በነበራት ከፍተኛ የሆነ የትረካ ፍላጎት 2005-2006 ከደራሲና ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን ጋር በ97.1 የሬዲዮ ፕሮግራም ብርቅርቅታ፣ ሕይወት በክር ጫፍ፣ ፕሮፌሰሩ፣ ኬ ሳራሳራ፣ እምቢባዮቹ፣ ቆንጂቷ፣ ገጠሬዋ ልጅ፣ ሾላ ገበያ ሌሎችንም ረጃጅምና አጫጭር መጻሐፍትን በራዲዮ ተርካለች፡፡ ሜሎን እና ሌሎች አጫጭር ልብ-ወለድ ታሪኮች የሚሉ ድርሰቶቿ በኦዲዮ ቡክስ በራሷ ድምጽ ተተርኮ በአሁኑ ወቅት ለአድማጭ ተዘጋጅቷል፡፡ ውስጡ ከያዛቸውም ጥቂቶቹን ብንገልጽ ልጅና ቡቃያ፣ ሜሎን፣ ከባንኮኒው ጀርባ፣ ጓደኛዬ፣ አረቡ ደላላውና ወራሿ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ካሳተመቻቸው መጽሐፍት ውስጥ፣ በራሷ ተጽፈው የታተሙ የድብልቅልቅ ሰፈር ሰዎች አጫጭር ልብ-ወለድ፣ ከአለማችን ድንቅ የህጻናት ጸሀፊ እና ስነ-ምግባር አስተማሪ ከሆኑት የFolk Tales ተረት ጸሐፊዎች ውስጥ Jon setapetu, Dong-il Park፣ Nora Brook፣ Dick Gackenbach፣ Sherry Litwack፣ Adelaide Holl፣ Mirra Ginsburg ከመሳሰሉ ጸሐፊዎች የተረጎመቻቸው አገዘኑና እንጨት ቆራጩ፣ የአይጥና የድመት ማሰሮ፣ የገጠሯ አይጥ፣ የንጉሱ ቆንጆ ልጅ እንዲሁም የራሷ ፈጠራ ብልጧ በለጡ የተሰኙት ያሳተመቻቸው ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ባሳተመው “የሕይወት ገጾች” የኢትዮጲያ ሴት ደራሲያን ማህበር ባሳተመው “እኛ” የግጥም መድብል ውሰጥም ግጥሞቿ ተወዳድረው በማሸነፋቸው ታትመዋል፡፡
እንዲሁም በPopulation Media Center “ታጋቾቹ” እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ስራዋች ተካቶ ለህትመት በቅቷል፡፡ “ዶን የፊልምና የማስታወቂያ ድርጅት” የሚገለገልባቸው የተለያዩ ማስታወቂያዎችና የቴሌቪዥን ድራማዎች ጽፋለች፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዋሽቶኛል፣ በቃኝ፣ ማነው የተጋባው፣ የተፈታ ጥርስ፣ የመካኗ ሴት ክስ፣ ሽማግሌዎቹ የተሰኙት ይገኙበታል፡፡ ኢየሩሳሌም ነጋ ከደራሲዎች ጋር ለመገናኘት እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ባላት ከፍተኛ ጉጉት ወደ ድርሰት ማህበራት ጎራ ካለችበት ጊዜ አንስቶ፣ በኢትዮጵያ ሴቶች ደራሲያን ማህበር በዋና ፀሐፊነት ለአምስት ዓመት፣ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ደግሞ በተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥ በመግባት እያገለገለች ትገኛለች፡፡
በተጨማሪም በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የተነሳም፣ ውጤታማ ሴቶች በሚወሱበት በSynergy Habesha የግል ማህበር በሚዘጋጀው “እኔ ምጠይቀው” በሚል ፕሮግራም ሙሉ የሕይወት ታሪኳ ላይ በመመስረት ዶክመንተሪ ተሰርቶ በኢትዮጲያ ቴሌቪዥን በ2006 ቀርቧል፡፡ በዚሁ ድርጅት ውስጥም ከየተለያዩ ስራዎችን በመተርጎምና በማቅረብ ሰርታለች፡፡ ከነዚህም ውስጥ የቻይናዊቷን እውቅ ጋዜጠኛና የሌሎችን ዶክመንተሪ በመተርጎምና በመተረክ፣ International Rescue Committee (IRC) ከSynergy Habesha ጋር በመተባበር ዱንጋ በተሰኘው ተከታታይ የድምጽ አጫጭር የህጻናት ተረትና አስተማሪ ሙዚቃዎች ከእንግሊዘኛ ወደ አማረኛ በመተርጎም በድርጅቱ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ተተርጉመው በቪዲዮ እንዲሰሩ አስተዋጽኦ ያደረገችባቸው ከፊል ስራዎቿ ናቸው፡፡
በግጥምና በልብ-ወለድ እንዲሁም በወግ የሚካሔዱ ውድድሮችን በማሸነፍ በርከት ላሉ ጊዜያት ሸልማቶችን አግኝታለች፡፡ ከነዚህም መካከከል ለአብነት የሚጠቀሱት፣ በጸረ-ሙስና ኮሚሽን በሚዘጋጁ ተከታታይ ውድድሮች፣ ዳሸን ቢራ ባዘጋጀው ታላቅ የስነ-ጽሑፍ ውድድር የሰባ አምስት ሺህ ብር ተሸላሚ ሆናለች፡፡ የአባይን ግድብ ለማጠናቀቅ ማህበረሰቡን ለማንቃት በተደረገው የደራሲያን የስነ-ጽሑፍ ውድድር በተደጋጋሚ አንደኝነትን በመያዝ ሽልማትን አግኝታለች፡፡
ኢየሩሳሌም ነጋ የተለያዩ የጥናት ስራዎችንና ስነ-ጽሐፍ ከመወዳደር ባለፈ በዳኝነት ስራ ተሳትፋለች፤ ከሰራችባቸው ድርጅቶች ውስጥ በኢትዮጵያ ቴሌቨዝን በሚዘጋጀው ሐገርና ጥበብ ዝግጅት፣ Consortium of Christian Relife and Development Association (CCRDA) በሚያወደድራቸው የስነ-ፅሑፍ ስራዎች በተጨማሪም አባይ ግድብ ጽሕፈት ቤት በሚያደርገው የጻሑፍ ውድድር፣ በጎንደር ፋሲለደስ በ2015 በተደረገው ወይዘሪት አማራ የቁንጅና ውድድር በዳኝነት የተሳተፈችባቸው ስራዎች ናቸው፡፡
ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ በወመዘክር ቤተመጻሕፍት በሚያዘጋጇቸው የደራሲያን ትውውቅ በተለያየ ወቅት በመቀሌ፣ በጎንደር፣ በባህርዳር፣ በደብረብርሃን፣ በአዲስ አበባ፣ በኤግዚቢሽን መአከል በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በሚደረጉ የንባብ ማነቃቂያዎች፣ የሕይወት ልምድ ተሞክሮዋን ለተደራሲያን እና ለደራሲያን አቅርባለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በደራሲን ማህበር በስራ አስፈፃሚ ኮመቴ አባል በመሆን ማህበሩን በማገልገል የምትገኝ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ሶስተኛ ዲግሪ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ ኢየሩሳሌም ፍቅር አንማው እና ፍጹም አንማው የተባሉ የወንድና ሴት ልጆች እናት ናት፡፡
ደራሲዋ ሁልጊዜም ከታሪኳ መጨረሻ “ይህንን ሁሉ እንዳደርግ መነሻ የሆነችኝ አፌን የፈታሁባት፣ ብእር ያነሳሁባት፣ ከሰው ፊት መቅረብን የለመድኩባት፣ ታላቁን መጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩባትና በዚህ ሁሉ መካከል እንዳልፍ መሰረቴ የሆነች ውለታዋ የማይረሳ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፈረንሳይ ለጋሲዮን የምትገኘው መካነ ሕይወት አቡነገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ-ክርስቲያን የላቀ ክብር ይገባታል ትላለች፡፡
ተወዳጅ እውነትም ተወዳጅ ናችሁ። በጣም ጥሩ ሰው መርጣችሁ አቅርባችኋል። እየሩስ ከሰው ጋር ተግባቢ ባለቀና ልብ ድንቅ ዘርፈ ብዙ የጥበብ ባለቤት ነች። በማራኪ ድምጿ የምታቀርባቸው የራዲዮ ፕሮግራሞችም በሳል፣ ውብና ተወዳጅ ናቸው።