ኢትዮጵያዊቷ መስከረም ገስጥ ተጫኔ የአፍሪካ ምርጥ 78 የህግ ባለሙያዎች ዝርዝር ውስጥ ገባች ከዕዝራ እጅጉ

ይህ ዲጂታል መጽሔት በአፍሪካ የታወቀ ሲሆን 100 ሴት ጀግኒት የህግ ባለሙያዎችን እውቅና እየሰጠ መዝለቁ የበለጠ ከበሬታን አስገኝቶለታል፡፡

‹‹ኮርትሩም ሜል›› የተሰኘ የህግ ባለሙያዎችን ሥራ የሚያስተዋውቅ ዲጂታል መጽሔት ከሰሞኑ የ78 ሴት አፍሪካውያን የህግ ባለሙያዎችን ዝርዝር ከእነ ግለ ታሪካቸው አውጥቷል፡፡

የሕይወት ታሪካቸው በዲጂታል መጽሔቱ ላይ ከተሰነደላቸው መካከል ኢትዮጵያዊቷ መስከረም ገስጥ ትገኝበታለች፡፡ በህግ ሙያ ላይ ዓለም አቀፍ ተጽእኖ የፈጠሩ ሴት ባለሙያዎችን ወደ አንባቢያን የሚያደርሰው ይህ ተቋም በይፋ ከተመሠረተ 5 ዓመቱን ያስቆጠረ ሲሆን መሥራቹም አንቶኒ አታታ የተባለ ታዋቂ አፍሪካዊ የህግ ባለሙያ ነው፡፡
መሥፈርቱን የሚያሟሉ ሴት የህግ ባለሙያዎችን በመምረጡ በኩል ሙያዊ ድርሻቸውን ለመወጣት የፈቀዱ 23 ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ኬንያዊቷ እውቅ የህግ ባለሙያ ማሪያ ቤኔካ የዳኞቹ ሰብሳቢ ናቸው፡፡

ዳኞቹ፣የመምረጥ ተግባሩንም በጥንቃቄ እንደተወጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዘጋጅ ኮሚቴው 100 ባለሙያዎችን ለይቶ የማውጣት እቅድ ቢኖረውም ከሁሉም ሀገራት መስፈርቱን የሚያሟሉ በቂ ዕጬዎች ባለመገኘታቸው 78ቱን ብቻ ይፋ አድርጓል፡፡ አምና ከነበረው የባለሙያዎች ቁጥርም የዘንድሮው መጨመሩንም ዝግጅት ክፍሉ በዲጂታል መጽሄቱ ላይ አስታውቋል፡፡

የዓለም የሴቶችን ቀን ማርች 8 ትን ምክንያት በማድረግ ይፋ የሆነው ይህ ዝርዝር በዲጂታል መጽሔቱ ላይ የባለሙያዎቹን ታሪክ ያወጣው በያዝነው መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ነበር፡፡
78ቱ ሴት የህግ ባለሙያዎች ልምድና እውቀት ያካበቱ በመሆናቸው በዝርዘር ውስጥ ስማቸው መካተቱ ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል ሲልም ኮሚቴው ሀሳቡን አስፍሯል፡፡

የህይወት ታሪካቸው ከሰፈረላቸው አፍሪካዊያን መካከል ኢትዮጵያዊቷ መስከረም ገስጥ ተጫኔ ባለፉት 20 ዓመታት በአገር አቀፍ ፤በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰብአዊ መብት ላይ ጉልህ ሚና ያበረከተች በሳል ባለሙያ ናት፡፡

በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ከፍተኛ ባለሙያ ወይም ልዩ ልዑክ፣ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር፣ ዳኛ፣ ጠበቃ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት መሪ፣ የህግ መምህር በመሆን ያገለገለች ሲሆን ለዚህም በቂ ዕውቅና ተቸሯታል፡፡

መስከረም ገስጥ፣በተለይም በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና መድሎዎች እንዲወገዱ ጉልህ ሚና ተጫውታለች።
ከ2 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር ሆና ባገለገለችበት ወቅትም የሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ ምርመራ እና ስነዳ ሥራዎችን መርታለች። በተለይም በሀገሪቱ አለመረጋጋት እና ግጭቶች በተበራከቱበት አስቸጋሪ ወቅት ከጦርነት ጋር በተያያዘ በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን አስመልክቶ አስፈላጊውን መረጃ የማጠናቀር እንዲሁም ይፋ የማድረግ ኃላፊነቷን ለመወጣት የቻለች ባለሙያ ናት።

ይህች ኢትዮጵያዊት የህግ ባለሙያ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ባለሙያነት የስድስት ዓመታት የአገልግሎት ዘመኗ የባለሙያዎች ቡድኑ ሰብሳቢም ሆና የሠራች ሲሆን በተለያዩ አህጉራት የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከታተል ፣ ለመዘገብና በሚመለከታቸው አካላትና በተመድ ምላሸ‍ እንዲያገኙ ጥረት ለማድረግ ችላለች ። በአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ መብቶች ተቋማትም ጋር በባለሙያነት በቅርበት ሠርታለች። ለበርካታ የአፍሪካ የሕግ ባለሙያዎችና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ስልጠናና ድጋፍ በማድረግም አህጉራዊ አስተዋጽኦዋን አበርክታለች።

መስከረም የመጀመሪያ ዲግሪዋን በህግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ሁለተኛ ዲግሪዋን ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ በሰብአዊ መብቶችና ዲሞክራሲ ያገኘች ሲሆን ፣ የፒኤችዲ ዲግሪዋን ደግሞ በፓዶቫ ዩኒቨርሲቲ በመከታተል ላይ ትገኛለች።

በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ በተለይም በሴቶችና በሕፃናት መብቶች ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መብቶች፣ የልማት መብቶችና ግቦች፣ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን ያሳተመችው መስከረም በአፍሪካ፣በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ተጋባዥ መምህር በመሆን አገልግላለች፡፡

መስከረም ገስጥ ተጫኔ በዚህ አስተዋጽኦዋ እንደምትቀጥል ትናገራች፡፡https://www.courtroommail.com/breaking-news-2025-courtroom-mail-100-released-kenya-south-africa-dominate-list/

One thought on “ኢትዮጵያዊቷ መስከረም ገስጥ ተጫኔ የአፍሪካ ምርጥ 78 የህግ ባለሙያዎች ዝርዝር ውስጥ ገባች ከዕዝራ እጅጉ

  1. ይህን በብስራት የተሞላ ዜና እንደሰማሁ ያደረኩት ወደ ወላጆችሽ መደወል ነበር እናም ሁሌም የምኮራበትን አቶ ገስጥን ደስ ብሎኛል አልኩት::የሁለታችንም ደስታ የሚጋባ አይነት ስለሆነ በቃለ ምልልሳችን እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ጀግና እንዳለችን አረጋገጥን::
    መስከረም ሆይ ድካምሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ስላስገኘልሽ ደስ ይበልሽ በርቺልን::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *