ኢሳያስ መኩሪያ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡
ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ኢሳያስ መኩሪያ አንዱ ነው፡፡ ኢሳያስ በፎርቹን ጋዜጣ ላይ ለፊት ለፊት ገጽ የሚሆኑ አነጋጋሪ ዜና በማውጣት ይታወቃል፡፡ ስራ ከጀመረ 30 አመት የሞላው ሲሆን የህይወት ታሪኩን ቤርሳቤህ ጌቴ አጠናክራዋለች፡፡
ትውልድ እና ልጅነት
ትውልዱ አዲስ አበባ ላይ ነው በጥቅምት 7 ቀን 1960 ዓ.ም። ወላጅ አባቱ አቶ መኩሪያ አሠፋ እና እናቱ ወ/ሮ ከበቡሽ መኮንን ከገጠር እንደመጡ ማረፊያቸውን ጉለሌ አካባቢ ይኖሩ ከነበሩ የአባቱ አጎት ፊታውራሪ አሰፋ ነጋሽ ቤት አደርገው ነበርና ኢሳያስም ጉለሌ ፊታውራሪ አሰፋ ቤት ተወለደ። እድሜው ለትምህርት እንደደረሰ ወላጆቹ ከጉለሌ ወደ አዋሬ ቀበና ሞሪስ ጋሌም መኖሪያቸውን ቀይረው ስለነበር ኢሳያስ ሞሪስ ጋሌም አጠገብ የፊደል ገበታ ዘርግተው ፊደል ያስቆጥሩ ከነበሩት ከየኔታ አካሉጋ የቄስ ትምህርቱን ተከታተለ (ፊደል ቆጠረ)፡፡ ከእዚያም ወላጆቹ መኖሪያቸውን ከቀበና ወደ ካዛንቺስ አካባቢ ዘነበወርቅ ተብሎ ይጠራ ወደነበረው ሰፈር ሲቀይሩ ኢሳያስም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ቀድሞ ልዕልት ዘነበወርቅ አሁን የካቲት 6 ሚስ ፎርድ ተብሎ በሚጠራው የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት መማር ጀመረ።
የንባብ ፍቅር እና የጽሁፍ ዝንባሌ
ኢሳያስ በልጅነቱ ረባሽ ስለነበረ በተለያዩ ት/ቤቶች ሊማር ግድ ነበር። ስለዚህም በትንሳኤ ብርሃን እና በምስራቅ ጎህ (በቀድሞው አስፋወሰን) ትምህርት ቤት ተማረ። የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በኮከበ ፅባህ እና በምስራቅ አጠቃላይ ተማረ። የቤተሰቡ 3ኛ ልጅ የሆነው ኢሳያስ መኩሪያ ወላጅ አባቱን በእጅጉ ያደንቃቸዋል። ከገጠር መጥተው፣ እራሳቸውን አስተምረው ለቁም ነገር ያበቁ ከመሆናቸም በላይ በተማሩት የህግ ሙያ የህግ አንቀፆችን ሁሉ በቃላቸው የሚያውቁ ጎበዝ የህግ ባለሙያ ነበሩ። ኢሳያስ የንባብ እና የመፃፍ ባህልን አባቱ እንዳስተማሩት ይናገራል። አባቱ ከስራ ይዘውት የሚመጡትን ትላልቅ የህግ ሰነዶች እያገላበጠ በቃሉ የሚነግሩትን የህግ አንቀፅ እያጣቀሰ በቀን እስከ 20 ገፅ ፅሁፍ በእጁ እንዲፅፍ ያደርጉት ነበርና ይህም ከጽሁፍ ጋር አወዳጀው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ጋደም ብለው ደግሞ በግዜው ታላላቅ የተባሉ የታሪክ እና የስለላ መፅሀፍትን ጮክ ብሎ እንዲያነብላቸው ያደርጉ ነበር፡፡ ይህም የማንበብ ፍላጎቱን አዳበረለት፡፡ ሬድዮ ማድመጡም አልቀረለት። እነዚህ ሁሉ የአባቱ ድርጊቶች ወደ ጽሁፍ አለም መሩት፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ቆይታ
ኢሳያስ በምስራቅ አጠቃላይ ት/ቤት የ2ኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ሁለት አይነት ክበቦች ውስጥ ይሳተፍ ነበር። 1, በስነ-ፅሁፍና ቲያትር ክበብ 2, በጋዜጠኝነት እና በቀይ መስቀል የደም ለጋሾች ክበብ፡፡ በእነዚህ ክበባት ውስጥ በተለይም የ10ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ዝግጅቶችን በመድረክ እያቀረበ ከጥበብ ጋር ያለውን ቁርኝት አጠናከረ። ኢሳያስ ጧት ጧት በትምህርት ቤቱ የባንዲራ መስቀል ሥነ-ስርዓት ጊዜ ለተማሪ የሚያቀርበው ዝግጅት ፈጽሞ የማይዘነጋው ነው፡፡ በአንድ ወቅት እውቁ ጋዜጠኛና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ በትምህርት ቤቱ ክበባት በተዘጋጀ መርሃ-ግብር ላይ ተጋብዞ ጳውሎስን አስፈርሞታል፡፡የጋዜጠኝነት መሻቱንም የቆሰቆሰለት እለት ያ ሳይሆን አይቀርም።
ብሄራዊ ውትድርና
በ1981 ዓ.ም ወጣቱ ኢሳያስ በጊዜው የመጨረሻ የነበረውን ብሄራዊ ውትድርና በ5ኛው ዙር በግዳጅ ተቀላቅሎ ወደ ወለጋ ደዴሳ አቀና። ደዴሳ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በነበረው የ6 ወራት የወታደራዊ ሥልጠና ቆይታ በልጅነቱ በክበባት ውስጥ እንደነበረው እንቅስቃሴ ሁሉ ለ5 ብርጌዶች በተዘረጋ የድምጽ ማጉያ ይቀርብ የነበረ የማነቃቂያና የማጀገኛ ፅሁፎችና ሪፓርቶችን የሚያቀርቡበት ሚኒሚዲያ ላይ ሲሳተፍ ቆየ፡፡ በዚህም ተግባሩ የተማረኩት ኃላፊዎች እዚያው ማሰልጠኛ ውስጥ እንዲቆይ ወሰኑ፡፡ ሆኖም ግን ጊዜው ከፍተኛ ውጥረት የነገሰበትና ኢ.ህ.አ.ዴ.ግም ወደ መሃል አገር እየገፋ የመጣበት ሁኔታ ላይ በመገኘታቸው እዚያው ማሰልጠኛ የመቅረቱ ውሳኔ ቀርቶ ሠልጣኙ በጠቅላላ ለግዳጅ ወደ ደብረ ዘይት እንዲጓጓዝ ተደረገ፤ ኢሳያስም አብሮ መምጣቱ ግድ ሆነ። በዚያን ወቅት የማይረሳው ነገር ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ያመለጡበትን ዕለት ነው፡፡
ሠራዊቱን ከደብረ ዘይት የአየር ኃይል ግቢ ወደ ጦር ግንባር የማጓጓዙ ሥራ ቀናት መጨመሩን ምክንያት አድርገው ኢሳያስን ጨምሮ 8 ጓደኞቹ በአጥር ሾልከው በመውጣት ፋሲካን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር ወስነው፣ ካምፑን በእኩለ ለሊት ለቀው በእግር ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመሩ፡፡ እስከ ዱከም ድረስ በእግር ከዚያም በባቡርና በአውቶቡስ ተጉዘው እንዳሰቡት ቤተሰቦቻቸውጋ ደረሱ፡፡ ለቤተሰቦቻቸው አስገራሚም አስደሳችም ነገር ነበር። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በታላቅ ደስታ ደማቅ ፋሲካን አከበሩ። ታዲያ ጓደኛሞቹ ሲጠፉ የተስማሙት ፋሲካን ከቤተሠብ ጋር አሳልፈው ከ3 ቀናት በኃላ ለገሃር አውቶብስ ተራ በማለዳ ተገናኝተው ወደ ደብረዘይት ለመመለስ ቢሆንም 4ቱ ቃላቸውን አክብረው ሲገኙ 4ቱ ሳይመጡ ቀሩ፡፡ የተገናኙት 4ቱ ወደ ደብረዘይት በዕለቱ ተመለሱ፡፡
በአገባባቸው ላይ ግን ሁለት ለሁለት ተከፈሉ። ሁለቱ እንደአወጣጣቸው በአጥር ሾልኮ መግባትን መረጡ፡፡ ኢሳያስና አንደኛው ጓዳቸው ግን በበር ገብተው የመጣባቸውን ቅጣት ሊቀበሉ ወሰኑ፡፡ ይህንን የወሰኑት ኢሳያስና ጓደኛው ሁለቱን ጓደኞቻቸውን ተለይተው በበሩ እንደገቡ መያዛቸው የሚያጠራጥር አልነበረም፡፡ ሆኖም በአጥር እንደሾለኩት ሁለቱ ጓደኞቻቸው የከፋ ቅጣት ሳይደርስባቸው ቀረ፡፡ ይልቁንም በወቅቱ ከደብረ ዘይት ዘማቹን ወደ ግንባር ያዘምት የነበረው ሻላቃ በሻ ግርማ የሚባል ሰው ‹‹ወታደር ገንዘብ ይዞ ግንባር አይዘምትም›› ሲል ኢሳያስና ጓደኛው በኪሳቸው ይዘውት የነበረውን ጠቀም ያለ ገንዘብ ከተማ ወጥተው ጨርሰው እንዲመለሱ ፈቅዶ አስወጣቸው፡፡ ኢሳያስና ጓደኛው ምሽቱን በደብረዘይት ከተማ በነበሩ መሸታ ቤቶች ሲዝናኑ አመሹ እና በዚያው አደሩ፡፡ በማግስቱ ጓደኛው ገንዘባችንን ከጨረስን በል ወደ ካምፕ እንግባ ቢል ኢሳያስ አልመለስም ብሎ እንደወጣ ቀረና ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።
ከውትድርና ወደ ቤተሰብ መመለስ
ኢሳያስ ወደ ቤተሰቡ ዘንድ ከተመለሰ ወዲህ ወደ ጥበብ የሚያደላው ልቡን ለማስተንፈስ ውሎ እና ምሽቱ ሁሉ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲአትር አካባቢ ሆነ። አንድ ቀን ‹‹ትዕይንተ ጥበባት›› የተሰኘ የሙዚቃና የተውኔት ዝግጅት ለመታደም ከፊት ተሰልፎ ሳለ አንድ ሰው ከአንዲት ሴት ጋር ሆኖ ወረፋ ያስቀድመው ዘንድ ጠየቀው፡፡ ኢሳያስም መልካም ፈቃዱን ሰጥቶ አስቀደመው፡፡ ወደ አዳራሹ እንደገቡም ከዚያ የተራ ቅድሚያ ከሰጠው ሰው ጋር ጎን ለጎን ተቀምጠው ጭውውታቸውን ቀጠሉ። ኢሳያስ እና ሰውየው ለጥበብ ያላቸውን ፍቅር እየተጨዋወቱ ሳለ ኢሳያስ እጁ ላይ ያለውን አጭር መጣጥፍ የተመለከተው ግለሰብ ስራውን አድንቆ እሱም የሥነ-ጽሁፍ ሰው መሆኑን ለኢሳያስ ገለፀለት፡፡ ያ ሠው እውቁ የእፀ-በለስ መጽሐፍ ደራሲ፣ የማስታወቂያ እና የሚዲያ ሠው የሆነው ዝነኛው ተስፋዬ ማሞ ነበር፡፡ ተስፋዬ ማሞ ኢሳያስ የጽሑፍ ሥራዎቹን ይዞ ኢትዮጵያ ሬዲዮ እንዲመጣ ቀጠሮ ሰጠው፡፡ ኢሳያስም በቀጠሮው ዕለት በቲያትር ቤት በተዋወቀው ተስፋዬ ማሞ አማካኝነት የኢትዮጵያ ሬድዮን ለመጀመሪያ ጊዜ ረገጠ።
በጊዜው የመዝናኛ ክፍል ኃላፊ የነበረውን ታምራት አሰፋን ተዋውቆ ይዞት የመጣውን አጭር ፅሁፍ እንዲያቀርብ ጀርመን ስቱድዮ በመባል የምትታወቅ ስቱዲዮ ያስገባዋል። በዚያች እለት ይዞት የመጣው ፅሁፍ ከቄራ እስከ ምኒሊክ አደባባይ በ6 ቁጥር አውቶብስ የሚሄድን ሰው ታሪክ በልብ-ወለድ ቅርፅ ፅፎ ነበር የቀረበው። ይሄንን ፅሁፍ ጀርመን ስቱዲዮ ገብቶ እንዲያነብ አድርገውት ወደራሳቸው ወግ የገቡት ታምራት አሰፋና ቴክኒሺያኑ ከመስታወቱ ወዲያ ሆነው እየተሳሳቁ ሲታዩ ኢሳያስ ላይ እያሾፉ የሚሳሳቁበት አስመስሏቸው ነበርና ኢሳያስ ዜና እንኳን በማይቀርብበት የንባብ ፍጥነት ልክ ፅሁፉን አዋክቦ ይወጣል። ታምራት ቶሎ መጨረሱ ደንቆት ሲሰማው ፍጥነቱ ለከት አልነበረውምና ተረጋግቶ እንዲያነብ ይነግረዋል፡፡
እንደታዘዘውም ኢሳያስ ስቱዲዮ ገብቶ በታምራት አሰፋ አመራር ደግሞ አነበበ፤ ውጤቱም ጥሩ ነበር። ‹‹አንተ ለሬድዮ የሚሆን ጥሩ ድምፅ አለህ ስለዚህ ስራህ እሁድ ይቀርብልሀል›› ተባለ። ፅሁፉ በሬድዮ እንደሚቀርብለት የተነገረው ኢሳያስ ከእለተ ማክሰኞ እስከ እሁድ ቀኑ በእጅጉ ራቀበት፡፡ ለቤተሰቡና ለሚያውቁት ሁሉ ነገራቸው፡፡ ‹‹እሁድ ድምፄ በሬድዮ ይሰማልና ጠብቁ›› ብሎም ቀጠራቸው። እሁድ እንዳይደርስ የለ ደረሰ፤ ዝግጅቱም አየር ላይ ዋለለት። ከዛች እለት ጀምሮ አለሙ ሁሉ ኢሳያስን የሚያውቀው ያህል እየተሰማው መጣ፤ ኮራ ብሎ መራመድ ጀመረ። ስራው በዚህ ብቻ አላቆመም በየሳምንቱ ይቀርብለት ጀመር ጥሩ ልምድንም አዳበረበት። ‹‹ከኢትዮጵያ ሬድዮ የተማርኩት ነገር ለራስ እና ለሙያው ትልቅ ክብር እንዲኖረኝ ማድረጉን ነው›› ይላል ኢሳያስ።
የዜና ፋይሉ ፈጣሪ ጌታቸው ኃ/ማርያም ጋዜጠኛ ጥንቅቅ ያለ አለባበስ ሊኖረው ይገባል ብሎ ያምን ነበርና ሁሉንም ጋዜጠኛ ያስጠነቅቅ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሬድዮ እያለ ኮልፌ ልብስ መግዣ እና ጭድ ተራ በትዕዛዝ የሚሰራ ጫማ በመረጡት ዲዛይን ከ2 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ አሰርተው በገበያ የማይገኝ ጫማ ከ15-25 ብር ከፍለው ዘንጠው አቡነ ጴጥሮስ አካባቢ ይገኝ ወደ ነበረው ኢትዮጵያ ሬዲዮ ስቱዲዮ ይሄዱ እንደ ነበር ኢሳያስ ያስታውሳል፡፡ ታደሰ ሙሉነህ የኢሳያስ መኩሪያ ሞዴል ነበር። እሱ ብቻ ግን አልነበረም ታምራት አሰፋ እና አምባዬ አማረም ጭምር እንጂ። የጌታቸውን አነባበብና አለባበስ፣ የእነ ታምራት አሰፋንና ታደሰ ሙሉነህን ደግሞ አተራረክ በጣም ይወደው ነበር። በተለይ የእሁድ ማለዳ ዝግጅቶቻቸውን በእጅጉ ጓግቶ ይጠብቀው እንደነበር አይዘነጋውም።
ከ1983 -1993
በ1983 ዓ.ም የኢ.ህ.አ.ዴ.ግን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የኢሳያስ የሬዲዮ ተሳትፎም አከተመ። በመሆኑም ኢሳያስ ፊቱን ወደ ግል ጋዜጦች አዞረ። እርሱ እንደሚያስበው በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነችው የግል ጋዜጣ ብስራት የተባለች ጃንሜዳ፣ ምኒሊክ ሆስፒታል አካባቢ መኖሪያ ቤታቸውን ቢሯቸውን ባደረጉ አንድ ግለሰብ አሳታሚነት የምትታተም የግል ጋዜጣ ነበረች። በዚህች ጋዜጣ ላይ ዜና መፃፍን ‹ሀ› ብሎ የጀመረው ኢሳያስ በጊዜው ዜና መፃፍ ማለት ገዢውን መንግስት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግን ማንቋሸሽ እና ደርግን ማሞካሸት ስለነበር ፕሮፌሽናሊዝም አልነበረም ብሎ ያምናል።
ከብስራት በኃላም በተለያዩ በወቅቱ ይታተሙ በነበሩ በርካታ የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ሲሰራ ቆይቷል። ‹ሕብር› መጽሄት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራው ዘገባ የ‹አንድ ብር ለአንድ ወገን› ዝግጅትን የተመለከተው ሪፖርት ሲሆን አብሮ አደግ ጓደኛው ከነበረውና አሁን የፎርቹን ጋዜጣ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ከሆነው ታምራት ገ/ጊዮርጊስ ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘትና ከወዳጃቸው ታማኝ በየነ ያገኙትን መረጃ በማጠናቀር የሰሩት ዘገባ እንደነበር አይዘነጋውም። በኋላ ግን በ1987 ዓ.ም በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የደላላው አምድ ፀሀፊ የነበረው ከበደ ደበሌ ወዳጁ ስለነበርና በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ይፅፍ የነበረውን ያውቅ ስለነበር ወደ ሪፖርተር እንዲመጣ ይጋብዘውና አማረ አረጋዊጋ ሄዶ መስራት ይጀምራል። ኢሳያስ እንደሚለው ከሆነ ለመጀመሪያ ግዜ ፕሮፌሽናል ዜናን መስራት የጀመርኩት ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሪፖርተር በነበርኩበት ወቅት ነው ይላል።
ከሪፖርተር በኋላ ወደ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ያመራው ኢሳያስ መኩሪያ አዲስ አድማስ ምንም እንኳን ወደ መዝናኛው የሚያደላ ጋዜጣ ቢሆንም ዜናዎችን በፊት ገፅም ጭምር በማውጣት ሲሰራ ቆይቷል። በአዲስ አድማስ ከሰራቸው ስራዎች መካከል የጥላሁን ገሰሰን 60ኛ ዓመት የልደት ክብረበዓልን በመዘገብና መጣጥፍ በመፃፍ የሰራው የሚጠቀስ ነው። ነገር ግን ኢሳያስ እና አዲስ አድማስ ብዙ ሳይዘልቁ ተለያዩ።
ፎርቹን ከ1993-2000
ኢሳያስ በምንም ስራ ላይ ባልነበረበት ወቅት ከአብሮ አደጉ ታምራት ገ/ጊዮርጊሥ ጋር ከጦማር ጋዜጣ በኋላ አሜሪካ ደርሶ እንደተመለሰ በአንዱ ቀን በሂልተን ሆቴል ይገናኛሉ፡፡ ኢሳያስ በወቅቱ ስራ ላይ ባለመሆኑ ፎርቹን ገና መከፈቱ ነበርና ለምን እኔጋ አትሰራም? የሚል ጥያቄ ከታምራት ይቀርብለታል። ቅዳሜ ማታ ተገናኝተው ሰኞ ማለዳ አትላስ ሆቴል አካባቢ ወደሚገኘው የጊዜው የፎርቹን ጋዜጣ ቢሮ ያመራል ኢሳያስ። ታምራትም እጅህ ከምን? ይለዋል እቅድ እሱ ከሰጠው ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ለታምራት ነገረው። ታምራትም አንድ ድንቅ ዕቅድ ያቀብለዋል፡፡ ይኸውም በዚያን ወቅት ከአየር ጤና ወደ ቃሊቲ የተዘረጋው የቀለበት መንገድ አዲስ የተሰራና ብዙ ቤተሰብና ጎረቤትን የለያየ፣ አገልግሎቶችን ያቋረጠ እንደመሆኑ ይሄንኑ ችግር ማህበረሰቡን አነጋግሮ ዜና እንዲሰራ ይነግረዋል፡፡ እንዳለውም ዕቅዱን ተቀብሎ ዜና በመስራት ኢሳያስ ፎርቹንን ተቀላቀለ።
የፎርቹን ስራው ‹‹ለካ ጋዜጠኝነት ማለት ይህ ነው የሚለውን የተረዳሁበት ሆነ›› የሚለው ኢሳያስ ‹‹አንድ ዜና ዜና ለመሆን የሚያልፈው መመዘኛም ሆነ የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ላይ ጠንካራ ባህልን ያዳበርኩበት፣ ብዙ የሰራሁበትም የተሰራሁበትም ቤት ነው›› ሲል ይመሰክራል። የፎርቹን ጋዜጠኛ ዜና ከመስራቱ በፊት መመዘኛ ላይ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡ ደግሞም የግል አስተያየቱን ዜና ውስጥ መክተት ፈፅሞ የተከለከለ ነው። ጋዜጠኛ ሆኖ የማርኬቲንግ ስራን ደርቦ መስራትም ሆነ በግል ውል የመዋዋል አዝማሚያ ፈፅሞ አይፈቀድለትም፡፡ እንዲያውም ለዘገባ የወጣ ጋዜጠኛ የሻይ ሰዓት ተቋሙ ከሚበጅትለት በጀት ይጠቀማል እንጂ ዜና ሊሰራ በሄደበት ስፍራ ሻይ ቡና ማለት ፈፅሞ የማይፈቀድበት ጥብቅ ስነ-ምግባር የሰፈነበት ቤት ነው ፎርቹን።
ኢሳያስ ፎርቹን የተቀጠረው በፍሪላንስ ጋዜጠኝነት ነበር፡፡
የሚከፈለው ደግሞ በጋዜጣው ለመታተም የበቁ ዜናዎቹ ቃላት መጠን ተቆጥረው በአንድ ቃል 15 ሣንቲም ሂሳብ ተሰልቶ ነበር፡፡ ኢሳያስ በየሣምንቱ የሚሰራቸው ዜናዎች ብዛት ከሣምንት ወደ ሣምንት በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ይከፈለው የነበረው ክፍያም በዜናዎቹ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የሚያገኘው ገቢ ከእሱ ቀድመው ከተቀጠሩ መደበኛ ጋዜጠኞች በላይ እየሆነ መጣ፡፡ ነገር ግን ይሄ ከፍተኛ ክፍያ የማግኘት ነገር አንዳንድ የጋዜጣውን ሰዎች አላስደሰተም ነበር፡፡
በመሆኑም ከሠራተኞቹ በተነሱ ጥያቄዎች መደበኛ ጋዜጠኛ ሆኖ በሙሉ ሰዓት እንዲቀጠር ተጠይቆ ወደ ሙሉ ቅጥር ሊዛወር ቻለ፡፡ በቆይታውም እስከ ከፍተኛው መደብ ድረስ በደረሰ ኃላፊነት በርካታ አነጋጋሪ ዘገባዎችን ይበልጡኑ በፊት ገፅም ጭምር በማስነበብ ስኬታማ የስራ ላይ ቆይታ እንደነበረው ያስታውሳል ኢሳያስ፡፡ ከፎርቹን ያገኘው ሙያዊ ስነ-ምግባርም እንደተጠበቀ። ፎርቹን ላይ የሙሉጊዜ ተቀጣሪ እስከሚሆን ድረስ በሚሰራው የዜና መጠን ስሌት በወር በሺዎች የሚቆጠር ገቢ ያገኝ የነበረ ሲሆን ለዘገባ ይወጣ በነበረ ግዜ የሚያገኘው አበልም ተጨማሪ ይሆንለት ነበር።
በህግ ዘገባ እና በምርመራ ዜናዎች ላይ የሠለጠነውና በብዛት የሰራው ኢሳያስ የፊት ገፅ ከሚሰጠው 3 ጉዳይ በአብዛኛው ከ3 እስከ 2 የሆኑት ዜናዎቹ የፊት ገፁን የሚያገኘው የኢሳያስ ሥራ ነበር። በቪኦኤ ማክሰኞ ማክሰኞ የንግድና ምጣኔ ሀብት መሰናዷቸው ላይ የፎርቹንን ዘገባ በስልክ ያቀርብም ነበር። ፎርቹን ላይ ምክትል ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሲሰራ ጋዜጣውን እንደተቀጣሪ ሆኖ ሳይሆን እንደባለቤት በልዩ ተቆርቋሪነት እያደረም ጭምር ሲሰራ መቆየቱ የማይካድ እውነት ነው። ሀሙስ ከቤቱ ወጥቶ እስከ እሁድ ጋዜጣው ለህትመት እስኪበቃ ድረስ ወደ ቤቱ ሳይገባ መስራቱ አንዱ ማሳያው ነበር።
ዜና የማግኘት ስልት
ኢሳያስ ዜና በማነፍነፍ አቅሙ የታወቀ ነው። የእውቀቱ ምንጭም ታምራት መሆኑን ይናገራል። ኢሳያስ ዜና ለማግኘት ጋዜጣ ገልጦ ከማስታወቂያ እስከ ልዩ ልዩ ዘገባዎች እያነበበ ለምን ብሎ ሲጠይቅ ብዙ ታሪክ ማግኘት ይችልበታል፡፡ የህግ መዝገቦችን ማንበብ፣ ከፍተኛ ሀላፊዎችንና የቢዝነስ ባለቤቶችን ቀርቦ ወዳጅ ማድረግና ቢሯቸውም ከተገኘ አካባቢውን በሚገባ በመቃኘት ዜና ይፈለፍላል። የኃላፊዎችን ፀሀፊዎችና ተላላኪዎችንም በወዳጅነት ያቀርባል፡፡ የእርሱ አላማ ግን ያው ዜና ማግኘቱ ላይ ብቻ ነበር። ‹‹ጸሃፊዎችና ተላላኪዎች ከፍተኛ የዜና ምንጮች ናቸው›› ይላል ኢሳያስ፡፡
አንድ ቀን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኃላፊ ቢሮ ውስጥ ካለች ፀሀፊ ጋር ወዳጅነቱን አጠናክሮ ባለበት እርሷ ቢሮ ጎራ ሲል አንድ ጥብቅ መረጃ ያገኛል፡፡ ለግዜው ስማቸውን መጥቀስ ባያስፈልግም ግለሰቦቹ አንድ ኩባንያ ለመመስረት ውል የሚፈራረሙበት ዕለት መሆኑን ፀሀፊዋ ታጫውተዋለች፡፡ ይሄ ግን ለኢሳያስ ጮማ ወሬ ሆነለት። ከዛ ቦታ እንደወጣም ነገሩን መመርመር ሲጀምር ከተዋዋዩ አንደኛው ለካስ በህግ የማያስኬደውን ውል ነበር በድብቅ ፈፅሞ ትልቁን የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያ ለማቋቋም ደፋ ቀና በማለት ላይ የሚገኘው።
ይህ ሰው በድብቅ እራሱ ይመራው ከነበረ ኩባንያ በተጻራሪ ተፎካካሪ የሚሆን ኩባንያ ለማቋቋም እየሞከረ ያለውን ተግባር በዜና ይፋ ለማድረግ ኢሳያስ ሲጥር ብዙ ዛቻ ቢቀርብበትም ዜናውን ከመስራት ግን ወደ ኋላ አላለም ነበር። ሌላው የደንበል ሲቲ ሴንተር በባንክ እዳ በሀራጅ ሊሸጥ መሆኑን ከቅርብ ወዳጁ በሰማበት ወቅት ዜናውን ሲሰራ ለስማችን አይመጥንም በሚል ቅድሚያ የገንዘብ ማታለያ ብሎም ዛቻ የቀረበበት ኢሳያስ አሁንም ዜናውን ከመስራት ወደ ኋላ አላለም ነበር። በጋዜጠኛነት ህይወቱ ዛቻን የጠገበ ሰው ነው። እንደውም የእርሱን ድፍረት እያዩ ‹የሚወዳጁትን ሰዎች ተማምኖ ነው እንዲህ የሚዳፈረው› እስከማለት አስተያየት የሚሰጡ ብዙዎች ነበሩ።
ደግሞ በሌላ ዘገባው አንድ ኩባንያ በ800ሺ ብር ደረቅ ቼክ የተከሰሰበትን ሰነድ የፍርድ ቤት ዶሴን ሲያገላብጥ ያገኛል። ኢሳያስን የሳበው ጉዳይ በጥራጥሬና በቡና ኤክስፖርት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጭምር የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ሰው እንዴት በደረቅ ቼክ ሊከሰስ ቻለ? የሚለው ነበር። ይሄንን ከፍርድ ቤት መዝገብ ላይ አንብቦ ዜና ለመስራት ሲነሳ የታወቀ የተባለው ዝነኛ ግለሰብ በእጅ በስልኩ ደውሎ ዜናውን ከሰራ የሞት ጽዋን እንደሚጎነጭ በመዛት ሊያስፈራራው ይሞክራል፡፡ ኢሳያስ ግን በዚህ የሚበገር አልሆነም፡፡ ይልቁንም መረጃውን በሚገባ አጠናቅሮ ለህዝብ ያስነብበዋል። ዜናው እንደወጣ ከወጋገን ባንክ ወደ 24 ሚሊየን ብር እዳ እንዳለበት ከዛም ከንብ ባንክ ወደ 42 ሚሊየን ብር አካባቢ ብድር ጠይቆ ለብድሩ ማስያዣ ዋስትና በመጋዘን የተከማቸ ቡና አለ በሚል አጭበርብሮ ገንዘብ ሊወስድ፣ ባንኩ በመደባቸው አጣሪ ቡድኖች አማካኝነት የተከማቸ ቡና መኖሩን አስመስክሮ እንዲፈቀድለት ከሆነ በኋላ ብድሩን ለመውሰድ የኃላፊው ፊርማ ብቻ ሲቀረው የእሁዱ የኢሳያስ የፎርቹን ላይ ዘገባ መዘዝ አስከትሎ የባንክ ኃላፊውን ያጠራጥራል። በእርግጥም የባንኩ ኃላፊ የኢሳያስን ዘገባ አንብበው ነገሩ የበለጠ እንዲጣራ ሲያደርጉ ግለሰቡ የቡና ገለባ ከምሮ እንደተከማቸ የቡና ክምችት አጭበርብሮ ገንዘብ ሊበደር ከዳር የደረሰ ሰው መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ በእዚህም ምክንያት ብድሩ ሳይፈቀድ ይቀራል። በጊዜው ባንኮች በኔትወርክ አለመናበባቸው ደግሞ ለአጭበርባሪዎች በር መክፈቱ አልቀረም ነበር።
ይሄ ግለሰብ ከኢሳያስ ጋር የከፈተውን የዛቻ ዘመቻ ሳይቋጭ እግሬ አውጪኝ ብሎ ወደ የመን ይፈረጥጣል። ነገር ግን በባንኮቹ ያላሰለሰ ክትትል በኢንተርፖል ተይዞ ወደ ሀገር ቤት በእስር ሊመለስ ችሏል። ይህ አንግዲህ የኢሳያስ የስራ ውጤት ማሳያ ነው። ኢሳያስ መኩሪያ ከወዳጆቹ በሚያገኘው መረጃ ላይ ተመርኩዞ የሚሰራው ዜና ቅሬታ ማጫሩ አልቀረምና ብዙዎች አኩርፈውት ቀርተዋል። እርሱ ግን የሚያረካው ዜና ፈልፍሎ ማግኘቱ ብቻ ነው።
የራሱን ጋዜጣ ኢኮኖሚን መሰረተ 2000-2002
ፎርቹን ጋዜጣ ላይ ለ8 ዓመታት ከሰራ በኋላ ራሱ ወደ ሚያሳትመው የግል ጋዜጣው ያመራው ኢሳያስ ‹‹ኢኮኖሚ›› የተባለ በቢዝነስ እና በንግድ ላይ ያተኮረ ጋዜጣ በ2000 ዓ.ም መሠረተ። ይህንን ጋዜጣ ለማቋቋም ከ1 ዓመት በላይ ነበር የፈጀበት፡፡ ለ1 ዓመትም በህትመት ከተሰራጨ በኋላ የ2002 ዓ.ም የምርጫ ወቅት ላይ በጋዜጣው ገጽ 5 ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በኢኮኖሚው ረገድ ያላቸውን ሀሳብ የሚያቀርቡበት ዕድል ፈጠረላቸው፡፡ እናም የሰዎችን አስተያየት እያቀረቡ በመስራት ላይ እያሉ ታዲያ የፓለቲካ አመራሮችን ያስቆጣ ሀሳብ ሳይሰነዘር አይቀርም፡፡
ብቻ ባልታሰበ ግዜ ድንገት ጋዜጣውን ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ስፖንሰሮች ማለትም አንደ አንበሳ ባንክ እና የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አይነቶቹ አድቨርታይዘሮች በስጋት ይመስላል በጋዜጣው ላይ ይወጣ የነበረውን ማስታወቂያቸውን አቋረጡ። የጋዜጣው የህትመት ዋጋም በድንገት በእጥፍ አሻቀበ፡፡ በመሆኑም ኢኮኖሚ ጋዜጣም በበጀት እጥረት መቀጠል አልቻለችምና በዚሁ ቆመች። ኢሳያስ ከፎርቹን የ8 ዓመት አገልግሎት በኋላ ወጥቶ በመሠረተው ሳምንታዊው ‹‹ኢኮኖሚ›› ጋዜጣው ላይ የስራ እድልም ጭምር ፈጥሮ ከአንድ ዓመት በላይ በጥሩ ሁኔታ ሲሰራ መቆየቱን አብረውት የሰሩት ሁሉ ያስታውሳሉ።
‹‹ኢኮኖሚ›› ጋዜጣ ከተዘጋች በኋላ ግን ኢሳያስ ለተወሰነ ጊዜ ያለስራ መቆየቱ የግድ ነበር። በመቶ ሺዎች ገንዘብ ለጋዜጣው ማቋቋሚያ አፍስሶ በመጨረሻ በኪሱ 65 ሳንቲም ይዞ የወጣ እንደመሆኑና የስራ ብድር የነበረበት ጋዜጣውን ዘግቶ መውጣቱ ተስፋ ያስቆረጠው ኢሳያስ የማንንም ስልክ እስካለመመለስ የደረሰ የዝምታ ግዜ ውስጥ ገብቶ ነበር። እሱ ያንን ጊዜ ‹‹የጥሞና ጊዜ›› ይለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከቪኦኤ ጋር በነበረው ስራ በሚሰጣቸው አስተያየቶች ምክንያት በግዜው ቪኦኤ ሊያስተናግዳቸው የማይገቡ ሰዎች ተብሎ በመንግስት ከተዘረዘሩ 48 ስሞች ውስጥ የኢሳያስ ስም በመገኘቱ የቪኦኤ ሰዎችም ለኢሳያስ በማሰብ ከቪኦኤ ጋር የነበረው ግንኙነት ተቋረጠ።
ሌላ የስራ እድል
አንድ እለት ግን ተደጋጋሚ የሚደወል ስልክን ምላሽ እንዲሰጥ ባለቤቱ ስትጠይቀው በእሺታ ለደዋዩ ምላሽ ይሰጣል፡፡ የደወለለት የውጭ አገር ሰው መልካም የስራ በር ነበር ይዞለት የመጣው። ስራው መረጃዎችን አጠናቅሮ መቀመጫውን እንግሊዝ አገር ለንደን ከተማ ላደረገ ‹‹ኮንትሮል ሪስክስ›› ለተሰኘ አማካሪ ድርጅት መላክ ነበር፤ ክፍያው ደግሞ በፓውንድ ነበር። ኢሳያስ እቤቱ ድረስ አንኳኩቶ የመጣለትን የስራ እድል ደስ ብሎት ተቀብሎ እስከ አሁን ድረስ እየሰራ ይገኛል። ግን ደግሞ የጋዜጠኝነት ሙያ ልክፍት የሚለቅ ባለመሆኑ አሁን ላይ ለመንፈሱ እርካታ ሲል በአራዳ ኤፍ ኤም 95.1 ሬድዮ ላይ ፕሮፖዛል ቀርፆ በልጁ ስም በከፈተው ቃል መልቲ ሚድያ አማካኝነት ‹‹መሃለቅ›› የተሰኘ የቢዝነስ ሬዲዮ ፕሮግራም እያስተላለፈ ይገኛል። በዚህ ስራውም አንድ አመት ሊሞላው ጥቂት ግዜያት ቀርተውታል።
ቤተሰብ
ኢሳያስ ከወ/ሮ እድላዊት አሻግሬ ጋር በመሰረተው ትዳር ለ21 ዓመት የዘለቀ ሲሆን 2 ሴትና 1 ወንድ ልጆች በጋራ አፍርተዋል። ደግሞ ከትዳር በፊት በአፍላ የወጣትነት ዘመን ከውትድርና ህይወት መልስ የወለዳት አንድ ሴት ልጅም አባት ነው ኢሳያስ፡፡ በባህሪው ቁጡ እንደሆነ ወዳጆቹ የሚናገሩለት ኢሳያስ ‹‹የማይነካ›› የሚለውን ድንበር ከነካ ሰው ጋር አብሮ ለመዝለቅ ትዕግስት የሌለው ቆራጥና ቁጡ መሆኑን እርሱም አይክደውም፡፡ ነገር ግን እድሜን ተከትሎ ትዕግስትን ማዳበሩ ደግሞ የተፈጥሮ ህግ ነውና አሁን ‹‹ቀዝቅዣለሁ›› ይላል ኢሳያስ።
ውድነህ ዘነበ ስለ ኢሳያስ መኩሪያ
ውድነህ ከኢሳያስ ጋር ፎርቹን ውስጥ መስራትየጀመረው ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ስለኢሳያስ ሲመሰክር እንዲህ ብሏል። ኢሳያስ በይበልጥ በምርምር ጋዜጠኝነት ላይ ያተኮሩ ዜናዎችን የሚሰራ ሲሆን በሳምንት ውስጥ ብዙ ዜናዎችን ፕሮዲውስ እያደረገ ሲስራ እንደነበር አስታውሳለሁ። ዜናዎቹም አንድ ዜና ሊያሟላቸው የሚገባቸውን መረጃዎች ያካተቱ ናቸው ። ኢሳያስ ልክ እንደ ነብር ጭራ የያዘውን የማይለቅ ፣ ጎበዝ የሚባል ጋዜጠኛ ነው። በኢትዮጵያ በህትመትም በኤሌክትሮኒክስ ሚድያ ነፃ ሆኖ ለመስራት አስቸጋሪ በነበረበት ሰዓት ኢሳያስ ሙያዊ አደራውን የተወጣ ሰው ነው።
በፎርቹን ውስጥ ኢሳያስ በሚሠራቸው ዜናዎችየግል ኩባንያዎች እና የመንግስት ተቋማት ጫና በሚያሳድሩባቸው ጊዜያት ወጀቡን ተቋቁሞ ማለፍ ፈተና በሆነበት ጊዜ አነጋጋሪ የሆኑ ርዕሶችን የሚያዘጋጅ ሰው ነው።ኢሳያስ ። በአብዛኛው የፍርድ ቤት ጉዳዮችን ፣ ከገቢዎች እና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ፣ በግል መስሪያ ቤት የማጭበርበር ሂደቶችን ፣ ሲዘግብ ነበር ። ለዚህም ዜናዎችን ከሰዎች ጋር መነጋገሩ እንዲሁም ከቢዝነስ ኮምዮኒቲ መስሪያ ቤቶች ጋር መገናኘቱ ከፍርድ ቤት ሰዎች ጋር መነጋገሩ ለዜናው ትልቅ ምንጭ ሆኖት ነበር ።
ኢሳያስ ትልቅ የመምራት አቅም ያለው ሲሆን የሚያቅዳቸው ዕቅዶችም በአብዛኛው በኤዲቶሪያሉ በኩል የሚያልፉለት ዜናዎች ነበሩ።በስራው ወቅት እራሱን የሚያከብር ስለሆነ ለቃለመጠይቅ ለሚሄድባቸው ቦታዎች በሙሉ እራሱን ጠብቆ እና ተጠንቅቆ ይሄድም ነበር። በዚህ አጋጣሚ ለኢሳያስ ጥንካሬ አድናቆት መስጠት እፈልጋለሁ።
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላትን አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ኢሳያስ የዜና ሰው ነው፡፡ ለዜና ሲል ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ በተለይ የፎርቹን ባልደረባ ከሆነ በኋላ የዜና ችሎታው ማዳበሩን ይናገራል፡፡ መረጃ ወይም ዜና እንደልብ መቃረም በማይቻልበት ሀገራችን ኢሳያስ ወገቡን ታጥቆ ዜናን አነፍንፏል፡፡ ከ17 አመት በፊት በፎርቹን ጋዜጣ የሚወጡ የፊት ዜናዎችን ብናይ ብዙዎቹ በኢሳያስ ጥረት የተገኙ ናቸው፡፡ ይህንን የፎርቹን ጋዜጣ መስራች አቶ ታምራትን ጨምሮ ሁሉም በሙሉ አንደበት የሚመሰክሩት ነው፤፡ ኢሳያስ የዜና ምንጭ ያለው ሰው ነበር፡፡ ዜናን በመግለጫና በሚታወቅ መንገድ ከማግኘት ይልቅ በራሱ ምንጭ 2 ወይሞ 3 ዜዎችን በአንድ ጊዜ ያገኝ ነበር፡፡ ህዝብ የማወቅ መብት አለው ከተባለ ጋዜጠኛም የማነፍነፍ ግዴታ አለበት፡፡ ኢሳያስም ይህንኑ ግዴታውን ነበር ሲወጣ የነበረው፡፡ በዚህ በፎርቹን ጋዜጣ ላይ ከፍተኛ አፈጻጸም ስለነበር ሁሌም አድናቆት ይቸረው ነበር፡፡ እውነተኛ የጋዜጠኝነት አሰራር በሚፈለግበት በአሁኑ ጊዜ የኢሳያስ መኩሪያ አይነት የሚድያ ሰዎች የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ ኢሳያስ ያኖረው አሻራ ትልቅ ሲሆን ትውልድም ይህን ልዩ አሻራውን እንዲያውቅለት እንሻለን፡፡
ኢሳያስ በሚድያ ስራ ከ30 አመት በላይ የዘለቀ በመሆኑ ባለፉትአመታት የነበሩ የታሪክ ሂደቶችን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ሌላው የኢሳያስ ችሎታ ዜና ለመስራት አስፈላጊ ሰዎችን አጠገቡ ይዞ ነበር፡፡ ይህም ከጋዜጠኝነት መሰረታውያን ቀዳሚው ነው፡፡ ሁል ጊዜም ታዋቂ ሰዎች መድረኩን ስለያዙት እንጂ ብዙ ሚድያ ወይም ፌስ ቡክ ላይ ያልሰፈሩ ባለታሪኮች አሉ፡፡ ከእነዚያ አንዱ ኢሳያስ መኩሪያ ነው፡፡ በእጁ ያሉትን የፎቶ እና የሰነድ ማስረጃዎች ስናይ ዘመንን የማሳየት ልዩ አቅም እንዳላቸው እንገነዘባለን፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እንዲህ አይነት የተደበቁ ሰዎች ወደ መድረኩ እንዲመጡ መዝገበ-አእምሮን እነሆ አቅርበናል፡፡ በየቦታው አሊያ በስርቻው ወይም ካጠገባችን ስንት ባለታሪክ ተቀምጦ ይሆን? መስፈርቱን እንዳሟላችሁ ከነገርናችሁ ታሪካችሁን ለማካፈል ወደ ኋላ አትበሉ፡፡ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ የተሰናዳ ሲሆን የአርትኦት ስራው ደግሞ በእዝራ እጅጉ የተሰራ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች ዛሬ ነሀሴ 8 2015 ተሰነደ፡፡ በቅርቡም በመዝገበ-አእምሮ ላይ ከሚወጡ ታሪኮች አንዱ ነው፡፡