አቶ ያዕቆብ ወልደማሪያም ዛሬ ህይወታቸው አለፈ

ቤተሰቦቻቸው ዛሬ ለተወዳጅ ሚድያ እንደነገሩት አቶ ያዕቆብ ትናንት ነሀሴ 15 2015 ሌሊት ነበር በ 94 ዓመታቸው ያረፉት። የቀበር ስነ-ስርዓታቸውም ነገ ነሀሴ 17 2015 ከቀኑ 8 ሰዐት በስላሴ መንበረ ጸባኦት ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል ። አቶ ያዕቆብ ወልደ ማርያም የኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ ናቸው ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ የእንግሊዝኛ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ለ56 ዓመታት ያለማቋረጥ በመሥራት ይታወቃሉ::

እርሳቸው የዛሬ 64 ዓመት በኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ሲቀጠሩ ደሞዛቸው 300 ብር አይደርስም ነበር፡፡ በጊዜው ሄራልድን ሲቀላቀሉ 30 አመት የሞላቸው አቶ ያዕቆብ በዓመቱ በ1952 የሄራልድ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ ለመሆን ችለዋል፡፡ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን በበላይነት የሚመሩት አቶ ዓምደ ሚካኤል ደሳለኝ ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ እንዲሠራ ይመኙ ስለነበር አቶ ያዕቆብ በሄራልድ ዐቅማቸውን እንዲያወጡ ዕድል ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ርእሰ አንቀጽና መጣጥፎችን በመጻፍ ችሎታቸውን ያሳዩት አቶ ያዕቆብ ጥረታቸውን በማጠናከር ቀጠሉበት፡፡ ያኔ እርሳቸው ዋና አዘጋጅ ከመሆናቸው አስቀድሞ ዶክተር ዴቪድ ታልቦት የሄራልድ ዋና አዘጋጅ ነበሩ፡፡

አቶ ያዕቆብ በሄራልድ በሠሩበት ዓመት ጠንካራ አገራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ሙያዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ነዋሪዎች ገንዘብ ቆጥበው የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ሲሉ በርእሰ አንቀጻቸው ሙግት ገጥመዋል፡፡ ያን ጊዜ ለንጉሡ ቀረቤታ ያላቸው ብቻ ቤት ያገኙ ስለነበር ደሃውም የቤት ባለቤት ይሁን ሲሉ አቶ ያእቆብ በርእስ አንቀጻቸው ላይ አስፈረዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ሠራተኛው የጡረታ መብቱ ሊከበርለት ይገባል ሲሉ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል፡፡

ከሄራልድ ከለቀቁ በኋላ በመነን መጽሔት፤ በቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ፤ በአዲስ ሪፖርተር በኤዲተርነት የሠሩ ሲሆን በሚሠሩትም ሥራ ደስተኛ ነበሩ፡፡ በንጉሡ ዘመን ለ15 ዓመታት፤ በደርግ ዘመን ለ17 ዓመታት፤ ከዚያ በኋላ ላለፉት 24 ዓመታት በጠቅላላ ለ56 ዓመታት በሙያቸው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ አቶ ያዕቆብ ከ1983 በኋላ ዘሰን፤ ዘሪፖርተር፤ ፎከስ ለተሰኙ የኅትመት ውጤቶች ሠርተዋል፡፡ በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ማሳተም ለሚፈልጉ ሰዎችም ሙያዊ ምክር በመስጠት ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡

አቶ ያዕቆብ ሄራልድ ከመግባታቸው በፊት አምኃ ደስታ ትምህርት ቤት የሳይንስ መምህር ሳሉ የትምህርት ቤት ጋዜጣ እንዲጀመር አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አቶ ያዕቆብ አልፎ አልፎ የጋዜጠኝነት ኮርስ ከመውሰዳቸው ሌላ በመደበኛነት ጋዜጠኝነትን አልተማሩም፡፡ ይልቁንም በእንግሊዝ ስኩል ኦፍ ለንደን ምሕንድስናን ለተወሰነ ዓመት አጥንተዋል፡፡ በለንደን እያሉ ጋዜጦችን በማንበብ ራሳቸውን በራሳቸው ጋዜጠኝነት ማስተማር ችለዋል፡፡
አቶ ያዕቆብ የራሳቸውን ግለ ታሪክ በ1995 ያሳተሙ ሲሆን አሁን ዕድሜያቸው 94 ነው፡፡ አንድ ዓይናቸው ማየት ያቆመው አቶ ያዕቆብ ባለትዳርና የ ልጆች አባት ናቸው፡፡ የትውልድ ቦታቸውም ወለጋ ነቀምት ሲሆን አዲስ አበባ መጥተው በኮተቤ ተምረዋል፡፡ ለአገራችን የእንግሊዘኛ ጋዜጦችና መጽሔቶች እድገት ከወጣትነት እስከ አረጋዊነት እድሜያቸው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አስተዋጽኦ ያደረጉትና እያደረጉ ያሉት እኚህ አንጋፋ ጋዜጠኛ በ2007 የበጎ ሰው ሽልማትን ወስደዋል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *