አቶ ተድላ ተሾመ
በአጼ ሀይለስላሴ ዘመን ሀገራቸውን በልዩ ልዩ ኃላፊነት ያገለገሉት አቶ ተድላ ተሾመ ‹‹የእኔ መንገድ›› በሚል ርእስ የህይወት ታሪካቸውን ጽፈው ያስመርቃሉ፡፡
ቅዳሜ እለት ከቀኑ 8 ሰአት በሚደረገው የምረቃ ስነ-ስርአት የባለታሪኩ የቅርብ ሰዎች ይታደማሉ፡፡ በእንጦጦ አጠቃላይ ወይም በቀድሞው ስሙ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት በሚደረገው መርሀ ግብር ታዋቂ ምሁራን ንግግር ያቀርባሉ፡፡
አቶ ተድላ ተሾመ ፣ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ1950 የዛሬ 66 አመት በ23 አመታቸው በዲግሪ የተመረቁ ሰው ሲሆኑ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በኢኮኖሚክስ ከእንግሊዝ ሀገር ከማንችስተር ዩኒቨርሲቲ በ1954 አ.ም ለማግኘት የቻሉ ናቸው፡፡ አቶ ተድላ በኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኦፍ አፍሪካ በ1954 ለመቀጠር ከበቁ የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ኢትዮጵያውያን አንዱም ናቸው፡፡
አቶ ተድላ ተሾመ በኢሲኤ ለ 4 አመት በማገልገል ላይ ሳሉ ከልጅ ይልማ ዴሬሳ በቀረበላቸው የሀገር ጥሪ መሰረት የገንዘብ ሚንስቴር መስሪያ ቤትን በመቀላቀል በበጀት ዝግጅት እና በፖሊሲ ስራዎች ላይ የጎላ ሚና አበርክተዋል፡፡
እኒህ ታላቅ ባለውለታ፣ ሀገራቸውን በንቃት ሲያገለግሉ በባህር ማዶ ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ አደራቸውን በሚገባ ተወጥተዋል፡፡
አቶ ተድላ ‹‹የእኔ መንገድ›› በሚለው የህይወት ታሪካቸው ላይ እንዳሰፈሩት በንጉሱ ዘመን በገንዘብ ሚኒስቴር በረዳት ሚኒስትር ማእረግ የገቢዎች መስሪያ ቤት የበላይ ሃላፊ በመቀጠልም በምክትል ሚኒሥትር ማእረግ የግሙሩክ የበላይ ኃላፊ በመሆን ሙያዊ ተግባራቸውን የተወጡ ሰው ናቸው፡፡
አቶ ተድላ ተሾመ በተባበሩት መንግስታትና የልማት ፕሮግራም ውስጥም ለ 20 አመታት በዋናው መሥሪያ ቤትና በአፍሪካ አገራት በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በመወከል ጭምር ያገለገሉ ናቸው። ካገለገሉባቸው ሀገራት መካከልም ኒዮርክና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ይገኙበታል።
በአሁኑ ሰአት የ88 አመት የእድሜ ባለጸጋ ናቸው፡፡ አቶ ተድላ ተሾመ ከተባበሩት መንግስት ጡረታ ከወጡም በኋላ የተባበሩት መንግስታት የቀድሞ ሰራተኞች ማህበርን በመመስረት በመሪነት ጉልህ ሚና አበርክተዋል፡፡
የ5 ልጆች አባት እና የ 9 የልጅ ልጆች አያት ለመሆን የበቁት አቶ ተድላ በሮታሪ ክለብም ውስጥ በብዙዎች የማይዘነጋ ተግባር ያከናወኑ ሰው ስለመሆናቸው በብዙዎች ይመሰከርላቸዋል፡፡
‹‹የእኔ መንገድ›› የሚለው መጽሀፋቸው በሚመረቅበት እለትም ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ፤ አቶ አያልነህ ሙላቱ እና ረዳት ፕሮፌሰር ደረጀ ገብሬ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
መድረኩን በመምራት እና በማዘጋጀት ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የተለመደ ተግባሩን የሚለወጣ ሲሆን የባለታሪኩ የቅርብ ወዳጆች እና ጥሪ የተደረገላቸው ይታደማሉ፡፡