አብይ ኤፍሬም ታላቅ ሰው አጣን

አብይ ኤፍሬምን ለመጀመርያ ጊዜ የተዋወቅኩት በሀምሌ 2004 የዛሬ 10 አመት መሆኑ ነው፡፡ ያኔ የሴቶች እና የህጻናት ጉዳይሚኒስትር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ፋና እሰራ በነበረበት ሰአት ሀዋሳ ለዘገባ ተልኬ ያኔ ነው ለመጀመርያ ጊዜ ያወቅኩት፡፡ ከዚያ በኋላ በሩቅ ካልሆነ በቅርበት ያገኘሁበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ ድርጅቴ ተወዳጅ ሚድያ የባለሙያዎችን ታሪክ በመዝገበ-አእምሮ ፣በዊኪፒዲያ እየሰነደ ባለበት ሰአት አብይ የፌስ ቡክ ጉዋደኛዬ ስለነበር ስለምሰራው ጉዳይ ተጨዋወትን፡፡ በአሁኑ ሰአት የመንግስት የስራ ሃላፊ መሆኑን ስለማውቅ እንዲህ ቀለል ብሎት የሚያወራኝ አልመሰለኝም፡፡

እርሱ ግን ጥሩ ስራ እየሰራን መሆኑን አጫወተኝ ፡፡ አስታውሳለሁ ጊዜው ጥቅምት 14 2014 ከሌሊቱ 7 ሰአት ነበር፡፡ በቴክስት ማውራት ጀመርን፡፡ አብይ ዳግም በድምጽ ራሱን ቀርጾ ላከልኝ፡፡ በንግግራችን የእርሱን ታሪክ ብንሰራ ሙሉ ፈቃደኛ መሆኑን ገለጸ፡፡ ከዚያም በህይወት እያሉ ታሪክን ማስቀመጥ ያለው ትልቅ ፋይዳ መሆኑን አስረድቶኝ የህይወት ታሪኩን እንድንሰራ ሙሉ ፈቃደኝነቱን አሳየ፡፡ የተወዳጅ ሚድያ የቦርድ አባላትም ታሪኩ ቢሰራ ሊያስተምር እንደሚችል አመኑበት፡፡ እናም የአብይ እፍሬምን ታሪክ ለመሰነድ እኔና ወዳጄ ጸጋ ታሪኩ መስራት ጀመርን፡፡ አብይ ስራ ይበዛበታል-ቢሆንም ግን ማታ ማታ መደዋወላችን እንደቀጠለ ነበር፡፡ በጣም ትሁት አበረታች እና ብሩህ አእምሮ ያለው ሰው መሆኑን ለማወቅ ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡ እና ስለ እርሱ የሚመሰክሩ ሰዎችን ቃለ-ምልልስ አደረግን፡፡ የህይወት ታሪኩ በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ታህሳስ 20 2014 ወጣ፡፡ የነበረው ግብረ መልስ አብይ ጠንካራ ሰው መሆኑን የሚገልጽ ነበር፡፡ አብይም ታሪኩ በመሰነዱ ደስ ብሎት ታሪኩን ለብዙዎች አጋራው፡፡ በተወዳጅ ሚድያ ጥረት ታሪኬ ተሰነደ ብሎ ጽሁፉን አጋራው፡፡ ከዚያም ጽሁፉ ከወጣ በኋላ ማድረግ ያሉብንን ማስተካከያዎች ሲነግረን ነበር፡፡ አጠቃላይ የሰራችን ደጋፊ እና አማካሪ ሆነ፡፡

መዝገበ-አእምሮ የ180 የሚድያ ሰዎች ታሪክ ታትሞ ሊወጣ መሆኑን ስነግረው አብይ ላይ ያየሁት የሀሴት ስሜት አሁን ድረስ ትውስ ይለኛል፡፡ ልብ በሉ ከአቢይ ጋር ከ10 አመት በፊት ለ4 ደቂቃ ሀዋሳ ከማግኘቴ በፊት በአካል ተገናኝተን አናውቅም፡፡ ቢሆንም ግን እኛ ለምንሰራው የስነዳ ስራ የቀድሞ ወዳጅነትና ትውውቅ አላስፈለገውም፡፡ አብይ በቃ በስልክ ይደውላል-ሀሳብ ይለግሳል፡፡ መዝገበ-አእምሮ ገና ማተሚያ ቤት ሳይገባ የ10 መጽሀፍ ዋጋ 10000 ብር ከፍሎ ያበረታታን ሰው ነው፡፡ አሁንም አብይ የምንሰራው ስራ ላይ አዎንታዊ እሳቤ በመያዝ ለሰዎች ስለ እኛ መልካም ጅምር ይናገራል-ይህ ሰው እንዴት ቀና ቢሆን ነው እል ነበር፡፡ መዝገበ-አእምሮ ሀምሌ 15 2014 ከማተሚያ ቤት ስትወጣ 10 መጽሀፍ ላኩለት፡፡

‹‹ አብይ መቼ ነው በአካል ተገናኝተን የምናወራው ? የመዝገበ-አእምሮ ምረቃ ላይ እንገናኛለን ብዮ ሳንገኛኝ ›› አልኩት እንዳልቻለ ነገረኝ፡፡ ይህ በእድሜ 3 አመት ከእኔ የሚያንስ ባለሙያ አንድ ቀን በአካል ተገናኝተን ሻይ ቡና ብንባባል ደስ ይለኝ ነበር፡፡ እርሱም ቆይ ነገ ቆይ ዛሬ ሲል እኔም በዚህ ቀን ስል የአብይን የህልፈት መርዶ ዛሬ ዿግሜን 3 2014 ሰማሁ፡፡ እንዴት ይቆጫል፡፡ ማግኘት እየፈለጋችሁ እንደናፈቃችሁ የሚያመልጣችሁ ሰው ታውቃላችሁ? የዛ አይነት ስሜት ወረረኝ፡፡ እርግጥ ነው አብይ የሰራውን ስራ በሙሉ ነግሮኛል፡፡ ታሪኩ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን አደራውን ተወጥቷል፡፡ ሁሌም ከአርሱ ጋር የምናወራው ሰው ህይወቱ ቢያልፍ ታሪኩ ግን ይቀመጣል እያልን ነበር፡፡ የሰው ልጅ መቼ ወደ አምላኩ እንደሚሄድ ባያውቅም በኖረበት ዘመን ግን ያከናወነውን ጽፎ ማስቀመጥ አለበት፡፡ አብይ….. አብይ ወዳጄ …. አበረታቼ ………… ሀዘኑ ቢያመኝም …….. ታሪክህን ለትውልዱ በማኖሬ ግን አይቆጨኝም፡፡ አንተ ባትኖርም በወጉ የተሰናዳው ታሪክህ ግን ይኖራል፡፡ ነፍስህን በገነት ያኖር ……. ለወዳጅ ዘመድ ሁሉ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

እዝራ እጅጉ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *