አብርሃም ረታ አለሙ

አብርሃም ረታ አለሙ(1950-2000)

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡

በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ የ200የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ደራሲና ጋዜጠኛ አብርሃም ረታ አለሙ አንዱ ሲሆን እርሱም በ2000 አ.ም ህይወቱ ማለፉ ይታወቃል ።አብርሃም ረታ በሚድያ እና በድርሰት ሥራ ለ 20 አመታት ያገለገለ ሲሆን የቆዩ ካሴቶችን በመሰብሰብ ፣ሰነዶችን በመያዝ የተመሠከረለት ነው። ይህን የአብርሃምን ታሪክ ስንሠራ ትልቁን ትብብር ላደረገልን ለብርሃኑ ሰሙ ምስጋናን ማቅረብ እንወዳለን ። የህይወት ታሪኩንም ዕዝራ እጅጉ እንደሚከተለው ሰንዶታል።

የአባቱ ወገኖች ከሰሜን የእናቱ ቤተሰቦች ከደቡብ ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ በይርጋለም ከተማ ነው የተወለደው፤ በሕፃንነቱ ወደ ባህር ዳር በሄደበት አጋጣሚ፣ በቄስ ትምህርት ቤት ከፊደል ገበታ ጋር የመተዋወቅ ዕድል አገኘ፡፡ በባሕር ዳር ብዙ አልቆየም፤ እናቱ ወደ ይርጋለም ከመለሱት በኋላ ቀጣይ ኑሮው እዚያ ሆነ፡፡ አባቱ በይርጋለም ከተማ በፍርድ ቤት የሚሠሩ ዳኛ ስለነበሩ፣ ለአባቱ በራፖርት ፀሐፊነትና አንባቢነት ማገልገል የጀመረው በልጅነቱ ዕድሜው ነበር፡፡ ለሥነ ጽሑፍ ሙያ የመጀመሪያው የሆነውንና ‹‹ዣንጥላ›› የሚል ርዕስ የቴአትር ጽሑፍ በልጅነቱ እንዲጽፍ ምክንያት የሆነውም፣ በፍርድ አደባባይ ያየው ታሪክ አስደምሞት እንደነበር ቤተሰቦቹ ያስታውሳሉ፡፡ የቴአትሩ ጭበጥ፤ ምንም ዓይነት ትምህርት ያልነበራቸው ሰው (ዋናው ገጸ ባሕሪ) የሀገሪቱን ወንጀለኛ መቅጫ እና የፍትሐ ብሔር ሕጎችን እያጣቀሱ፣ በፍርድ አደባባይ ሕብረተሰቡን ሲያገለግሉ የሚያስቃኝ ነው፡፡

አብርሃም ረታ ዓለሙ በቀበሌ የኪነት ቡድን ታቅፎ በድምፃዊነት መድረክ ላይ ሲወጣ የ5ኛ ክፍል ተማሪ የነበረ ሲሆን፤ በአብዮቱ ዘመን ‹‹ኢሕአፖን በመደገፍ ድንጋይ ወርውረሃል›› ተብሎ ታስሯል፡፡ በልጅነቱ በእግር ኳስ ተጫዋችነቱ ብቻ ሳይሆን በተለይ አብዶ (ፍጥር) በመሥራት ይታወቅ እንደነበር አብሮ አደጉ ጋዜጠኛ አሳምሬ ሳህሉ ያስታውሳል፡፡ ከሙዚቃ መሣሪያዎች አርሞኒካና ጊታር ከመቻሉም ባሻገር የራሱን ግጥምና ዜማ በራሱ ድምጽ ይጫወታል፡፡ በዚህም ችሎታው ተወልዶ ካደገበት ይርጋለም ከተማ ከቀበሌ ኪነት ቡድን አልፎ ሶሻሊስት ወደነበረችው ጀርመን ድረስ የተጓዘበት አጋጣሚ ነበር፡፡

አብርሃም ረታ ዓለሙ አንባቢና መጻሕፍት አፍቃሪ እንዲሆን የመጀመሪያውን በጎ ተጽእኖ ያሳረፉበት ታላላቅ ወንድሞቹ ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ ወንድሞቹ ወደ ይርጋለም ሲሄዱ ለታናሽ ወንድማቸው ይመጥነዋል የሚሉትን መጽሐፍ ገዝተው እየወሰዱ ያበረክቱለት ነበር፤ በዕውቀትና በዕድሜ እያደገ ሲመጣ የራሱን መጻሕፍት ማሰባሰብ ጀመረ፡፡ አብርሃም በመምህራን ማሰልጠኛ ተመርቆ፣ በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለ13 ዓመታት ያህል በመምህርነት ማገልገሉም በኋላ ለታወቀበት የሥነ ጽሑፍ ችሎታው ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎለታል፡፡ በመምህርነት ዘመኑ በይርጋለም፣ በሐዋሳ፣ በድሬደዋና በዝዋይ ሕፃናት አምባ አገልግሏል፡፡ ለመምህርነት ሙያው ልዩ ፍቅርና ትዝታ ነበረው፡፡

ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በአምደኛነት ጽሑፍ በመላክ የጀመረው ተሳትፎ ወደጋዜጠኝነት ካሸጋገረው በኋላ ጋዜጠኞች ማስተማሪያ ሆኖ በ1990ዎቹ መጀመሪያ በተቋቋመው ‹‹የመገናኛ ብዙኃን ማሰልጠኛ›› በመጀመሪያው ዙር ገብተው እንዲማሩ መንግሥት ዕድሉን ካመቻቸላቸው አንዱ ሆኖ ተምሮ ተመርቋል፡፡ በሚያዘጋጀው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የኪነ ጥበባት ዐምድ የተዘነጉ ታሪክና ባለታሪኮችን እየጋበዘ ለአንባቢያን ማቅረቡ እውቅና እያስገኘለት መጣ፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የጀመረው የጋዜጠኝነትን ሥራ ‹‹ሩሕ››፣ ‹‹ዕለታዊ አዲስ››፣ ‹‹አዲስ አድማስ›› በመሳሰሉ ጋዜጣና መጽሔቶች በተለያየ ኃላፊነትና ደረጃዎች እያለፈ ከዕለት ዕለት በሙያው እያደገና እየታወቀ የመጣው አብርሃም ረታ ዓለሙ፤ በተለያዩ የሬዲዮ መዝናኛ ዝግጅቶች የወግና የድራማ ጽሑፎችን በመላክ ይሳተፍ ነበር፡፡ መጻሕፍትን አንብቦ፣ የሙዚቃ ሲዲና ካሴቶች አዳምጦ በመጽሔትና ጋዜጦች ለአንባቢያኑ ያቀርባቸው የነበሩ የዳሰሳ ጽሑፎች፤ አብርሃምን (ሞት ባያስቆመው) ከጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ወግ ፀሐፊ፣ ተርጓሚ፣ የድራማና የፊልም ፀሐፊነት ባሻገር ወደ ሐያሲነት የሚያሸጋግረው መስመር መያዙን አመላካች ነበር፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየቱም ቀደም ብሎ አምስት መጻሕፍትን አሳትሞ ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡ ስድስተኛውን የትርጉም መጽሐፍ (አባቶችና ልጆች) ለ7ኛ ሙት ዓመቱ መታሰቢያ እንዲሆንለት ብቸኛ ልጁ (ቃልኪዳን አብርሃም) ነው ያሳተመለት፡፡

አብርሃም ረታ ዓለሙ በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦና ችሎታ እንደነበረው ብዙዎች ምስክርነት ይሰጡለታል፡፡ በአንድ መድረክ ጋሽ አስፋው ዳምጤ የአብርሃም ረታ ዓለሙን ሕልፈት በተመለከተ ሲናገሩ ‹‹ባለ አእምሮ ልጅ ነበር›› በሚል በአድናቆት መስክረውለታል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ መሥራችና ባለቤት የነበረው አቶ አሰፋ ጎሳዬ (ዐፈሩ ይቅለለው) በአብርሃም ረታ ዓለሙ የፀሐፊነት ፍጥነትና የሀሳብ ስፋት ተገርሞ ‹‹ጎርፉ›› የሚል ቅጽል ሥም አውጥቶለት ነበር ይባላል፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹ዕውቀትና ትጋት አሰፋ ጎሳዬ መታሰቢያ ቤተ መጻሕፍት›› ሲቋቋም ለቤተ መጻሕፍቱ አደራጆቹ በሺህ የሚቆጠር መጽሐፍ በውሰት ከሰጡት መሐል አብርሃም ረታ ዓለሙ አንዱ ነበር፤ በኋላ መጻሕፍቱ ለአብርሃም ቤተሰቦቹ ተመላሽ ተደርገዋል፡፡

አብርሃም ረታ ዓለሙ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ ለመታሰቢያ ከተዘጋጀለት መድረክ አንዱ በሐዋሳ ከተማ ነበር የተከናወነው፡፡ ‹‹60 ሻማዎች›› በሚል ርዕስ በኪነ ጥበብ ዙሪያ የተለያዩ መድረኮችን ማሰናዳት ዓላማው አድርጎ ይንቀሳቀስ የነበረው የሥነ ጽሑፍ አድናቂ ወጣቶች ማኅበር፣ ኅዳር 7 ቀን 2001 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ባዘጋጀው መርሐ ግብር ገጣሚ ፊርማዬ ዓለሙ፣ መምህር ደበበ ሰይፋ፣ ዶ/ር አብርሃም ፈለቀ እና ጋዜጠኛ አብርሃም ረታ ዓለሙን በጋራ የሚዘክር ነበር፡፡

ከዕለቱ ተዘካሪዎች አንዱ በነበረው አብርሃም ረታ ዓለሙን በተመለከተ ታላቅ ወንድሙ መምህር ሙሉጌታ ረታ ዓለሙ በሰጡት ምስክርነት ‹‹አብርሃም በቤተሰቦቹም ሆነ በጓደኞቹ ማን እንደሆነ በደንብ ሳይታወቅ፣ በመጻሕፍቱ ውስጥ እንደመሸገ በድንገት ያለፈብን ፀፀታችን ነው›› በማለት ነበር የገለጹት፡፡ በዕለቱ ከአብርሃም ረታ ዓለሙ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች፣ በተለይ ተዘካሪው ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየቱ ከአንድ ወር በፊት ‹‹እችክችክ›› በሚል ርዕስ ያሳተመው የግጥም መጽሐፍን ማዕከል አድርገው ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የዲላ ዩኒቨርስቲ መምህር ቴዎድሮስ ቦጋለ፤ ‹‹የአብርሃም አንድ ወግና ሁለት አጫጭር ልቦለድ ጽሑፎቹ የሩሲያ ባህል ማዕከል ወደ ሩሲያ ቋንቋ አስተርጉሞለታል›› የሚል መረጃ ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡ አብርሃም ረታ ዓለሙ በእስር ሕይወቱ በጣም መመረሩን ከገለጸባቸው ስንኞቹ አንዱ ነው በማለት፤ መምህር ቴዎድሮስ ቦጋለ ከ‹‹እችክችክ›› መጽሐፋ የሚከተለውን ግጥም በንባብ ለታዳሚው አቅርበው ነበር፡፡
ድንገት ዕድሜ ባገኝ
ተጨማሪ ዘመን ባለም ላይ ለመኖር
እኔኑ ለማሰር ሌላኛው ምክንያት
አገሬ ምን ይሆን ?
አብርሃም ረታ ዓለሙ በሕይወት ዘመኑ 3 ጊዜ ታስሮ ተፈትቷል ‹‹ድንጋይ ወረወርክ አስወረወርክ እና ሕዝብን ለአመጽ አነሳሳ ብላ ሀገሬ 3 ጊዜ ለእስር ዳርጋኛለች›› ይል የነበረው አብርሃም፤ በክስተቱ የተሰማውን ምሬትና ስሜቱን ከላይ በተመለከተው መልኩ በግጥም ቢገልጽም በተቃራኒው ደግሞ ‹‹የታሰርኩት አፈሳ በሚካሄድበት ስፍራ በድንገት ስለተገኘሁ ነው›› በማለት በችግርና በመከራው የመቀለድ ልዩ ተሰጥኦም ነበረው፡፡

አብርሃም የየዕለት ውሎና እንቅስቃሴውን የመመዝገብ ልማድ ነበረው፡፡ ‹‹አልን ተባልን አስባልን›› እና ‹‹አከራይ ተከራይ አካከራይ›› መጻሕፍቱ ላይ ያሰፈራቸው ታሪካዊ መረጃዎች በዚህ መልኩ ያሰባሰባቸው ነበሩ፡፡ አብርሃም ስምንት የሚደርሱ የብዕር ስሞች ነበሩት፡፡ በብዕር ሥምነት ይጠቀማቸው የነበሩት በአብዛኛው የኢሕአፓ ዘመን ጓደኞቹን መጠሪያ ነበር፡፡ ጎበዝ ፀሐፊና አድማጭ ብቻ ሳይሆን ንግግር አዋቂም ነበር፡፡ ከተቆጣም ኃይለኛ ነው፡፡ ቀልድና ጨዋታ አዋቂ ናቸው ከሚባሉት የሚመደብ ሰው ነበር፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት በስሜት ከመቀመጫው ተነስቶ ድራማዊ በሆነ እንቅስቃሴ ሊገልጽ ሁሉ ይሞክራል፡፡ ጊታር እየተጫወተ የግሉንና የሚወዳቸውን ድምፃዊያን ዘፈን እያንጎራጎረ ራሱንና ወዳጆቹን ያዝናናል፡፡

እርቦት ይሁን ጠምቶት ደክሞት የተኛ ሰው፣
አይቀርም መንቃቱ ጠኔው ‹ተነስ› ሲለው፡፡
የሞተስ ? የሞተስ ? …

የሚወዱት ንጉሥ፣ ጌጥ፣ ምልክት፣ ግርማ፣
የሞተስ ያለፈስ ነፍሱን የተቀማ ?
ይህ ግጥም ጋዜጠኛ አብርሃም ረታ ዓለሙ የቅርብ ወዳጁ በሞት ሲለየው የጻፈው ነው፡፡ ሐኪም ብቻ ሳይሆን ሥነ ጽሑፍ አፍቃሪና ገጣሚ የነበረው ዶ/ር አብርሃም ፈለቀ በሐምሌ ወር 1996 ዓ.ም ነበር በሞት የተለየው፡፡ አብርሃም ረታ ዓለሙ የሟች ጓደኛውን የግጥም ሥራዎች በማሰባሰብ ለ40 ቀን መታሰቢያ እንዲሆንለት ‹‹ቢላዋ እና ብዕር›› በሚል ርዕስ አሳትሞለታል፡፡ ከላይ የቀረበው ግጥም በጥራዙ በገጽ 32 ይገኛል፡፡

አብርሃም ረታ ዓለሙ ሞትን በተመለከተ (በንግግሩም በጽሑፉም) በቀልድና ቁም ነገር የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች ልብና አእምሮ ላይ ታትመው የሚቀሩ ነበሩ፡፡ ‹‹እያንዳንዳችን መጠሪያችን ስለማይታወቅ ምኞትና እቅዳችንን ቶሎ እንተግብር›› እያለ ይመክራል፡፡ እናቱ ከዚህ ዓለም ድካም (በሞት) የተለዩበትን ዕለት ሻማ እያበራ የማስታወስ የዓመታት ልምድም ነበረው፡፡ ‹‹ሞት››ን ርዕሰ ጉዳይ ያደረጉ ጥቂት የማይባሉ የግጥም ሥራዎችም አሉት፡፡

በሥነ ጽሑፉ ዘርፍ በሁለገብ ሙያ ተሳታፊ በመሆኑ ይታወቅ የነበረው አብርሃም ረታ ዓለሙን በቅርበት ያውቁት የነበሩ ወዳጆቹ አእምሮ ውስጥ ሊጠፋ የማይችሉ በርካታ ትዝታዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መሐል በተመራጭነታቸውም ሆነ በብዛታቸው ‹‹ልዩ›› ሊባሉ የሚችሉት የመጻሕፍት ስብስብ እና ከተለያዩ የሬዲዮ ዝግጅቶች ለዓመታት እየቀዳ ያስቀመጣቸው የቴፕ ካሴቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አብርሃም ዕውቀቱን፣ ጊዜውን፣ ገንዘቡን … ሳይሰስት አውጥቶ ያሰባሰባቸው እነዚህ ‹‹ቅርሶች›› እንዳይባክኑ ቤተሰቦቹ ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ እና በይርጋለም የተለያዩ ቦታዎችን በማቀያየር ቀላል የማይባል መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ እነዚህን ስብስቦች በጥንቃቄ በማቆየቱ ረገድ በተለያ የልጁ የቃልኪዳን አብርሃም ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ አባቱ ‹‹ማሙሽ›› እያለ ይጠራው የነበረው ቃልኪዳን አብርሃም ስለዚህ ጥረቱ፣ ቀጣይ እቅድና ምኞቱን በተመለከት ሲናገር ፡-

‹‹አባቴ አብርሃም የተቀደደ ሸሚዝ አየለበሰ ለመጽሐፍ ግን ገንዘቡን ሳይሰስት ያከማቻቸው ውድ የጽሑፍ ስብስቦች ናቸው እጄ ላይ የወደቁት፡፡ ስብስቦቹ በሺ የሚቆጠሩ መጻሕፍንና የቴፕ ካሴቶችን ጨምሮ የተለያዩ ታዋቂ ደራስያን የእጅ ጽሑፎችን ያካተተ ነው፡፡ እኔ ባለፉት 15 ዓመታት ‹እሱ ሊገዛቸው ይችል ነበር› ብዬ የገመትኳቸውን መጻሕፍትንም እየገዛሁ የስብስቡ አካል ለማድረግ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ አባቴ በይርጋለም ከተማ ከእናቱ የወረሰው መኖሪያ ቤት አለው፡፡ የእኔም ምኞትና ግብ የአብርሃምን የተለያዩ ስብስቦች በዚህ ቤት፣ ቤተ መጻሕፍት በማቋቋም የአባቴን ሥም ማስጠራት ነው›› ይላል፡፡

የአብርሃም ብቸኛ ልጁ (ቃልኪዳን) ለአባቱ መታሰቢያ እንዲሆን ያስቀመጠው ምኞትና እቅድ ተግባራዊነቱ ከፈጠነ፣ አብርሃምን ከመዘከሪያነት ባለፈ በተለይ የይርጋለም ከተማና ነዋሪ በብዙ እንደሚማሩበትና እንደሚጠቀሙበት ከወዲሁ አስረግጦ መመስከር አይከብድም፡፡ በብዙ የሙያ ዘርፎች የ‹‹እሳት ልጅ ዐመድ›› እየሆኑ በምንቸገርባት ሀገራችን የ‹‹የጎበዝ ልጅ ጎበዝ ›› መሆን እንደሚችል በተግባር ለማሳየት ጥረት እያደረገ ያለው ወጣት ቃልኪዳን አብርሃምን መተባበር የሚችል ሁሉ ከጎኑ ቢቆም፤ የአባቶቻቸውን ታሪክና ሥራ ለሀገርና ለትውልድ የማስተላለፍ ፍላጎት ላላቸው ወጣቶች አንዱ ማሳያና ምሳሌ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *