አብርሀም ገዛኸኝ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡
ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል የፊልም ዳይሬክተር አብርሀም ገዛኸኝ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የፊልም ታሪክ ውስጥ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ብቅ ካሉ የፊልም ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡ አብርሀም ገዛኸኝ፡፡ በብዙዎች ከሚመሰከርላቸውና በሙያቸው ከበሬታን ካተረፉ የፊልም ደራሲ እና ዳይሬክተሮች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ስራዎቹ ተጀምሮ እስኪጨረስ የብዙዎችን ስሜት ገዝቶ የመያዝ አቅም አላቸው፡፡ ሚዜዎቹ፤ የእግር እሳት፤ ሎሚ ሽታ፤ የነገን አልወልድም እና በስንቱ ከሰራቸው ስራዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ቀረፃ፣ተዋንያን መረጣ፣ዳይሬክቲንግ፣ፕሮዳክሽን በሁሉም ዘርፍ የተዋጣለት ሰው ሆኗል። በአገር ውስጥ ካለው ከፍተኛ ተወዳጅነት በተጨማሪ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የፊልም ሽልማቶችን አግኝቷል። አብረሃም ገዛኸኝ። ባለፉት 20 አመታት በፊልም ኢንዱስትሪ ላይ ተሰማርተው በጎ ለውጥ ለማምጣት እየተጣጣሩ ካሉት አብርሀም ተጠቃሹ ነው፡፡ ዘቢባ ሁሴን እና ዕዝራ እጅጉ የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው ሰንደውታል፡፡
ውልደትና እድገት
አብርሃም ገዛኸኝ በ1973 ዓ.ም መጋቢት ወር ነበር የተወለደው፡፡ እናቱ እታፈራሁ አክሊሉ ሲባሉ አባቱ አቶ ገዛኸኝ አሰፋ ናቸው፡፡ አብርሀም በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ አካባቢ ነበር የተወለደው። አብርሃም ከታላቅ እህቱ እና ታናሽ ወንድሙ ጋር ሁለተኛ ልጅ ሲሆን አስተዳደጉ ባብዛኛው ከቤት እስከ ቤተክርስቲያን ብቻ የተገደበ ነበር። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በቦሌ ህብረተሰብ ትምህርት ቤት እና በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። አባቱ እና ታላቅ እህቱ የፊልም አድናቂና ተከታታይ በመሆናቸው በጊዜው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይተላለፍ የነበረውን ታላቅ ፊልም አብሮ መመልከት መጀመሩ የመጀመሪያው የልጅነት የፊልም ምልከታ ትውውቁ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በዚህ የተጀመረው የፊልም ምልከታ ቀስ በቀስ በዘመኑ በነበረው የዴክ ካሴት ፊልም ማጫወቻ ምልከታ አድጎ አብርሃምን ዛሬ ለደረሰበት የፊልም አዘጋጅና ዳይሬክተርነት መሠረት አደረሰው፡፡
ፊልም ከመመልከት በተጨማሪ አብርሃምን የፊልም ፍቅር እንዲኖርበት ያደረገው መጽሀፍ ማንበብ ነው፡፡ በዚህም በልጅነቱ ያነበባቸው ልብወለድና ኢ-ልብ ወለድ መጽሀፍቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሲገባ በተለይ በአሁን ወቅት ገበያው ላይ የበዙት አነቃቂ መልእክት ያላቸው መፅሀፎች ይበልጥ ያተኩርባቸው ነበር፡፡ ከነሱም ውስጥ የዶ/ር ማይልስ ሞንሮ እና ስቲቭን ኮቬይ መጽሃፎች የህይወት ግቦቹን፣ አላማዎቹን እና እውነተኛ ፍላጎቱን እንዲረዳ አግዘውታል፡፡ በ1990 የማትሪክ ውጤት በማምጣት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ከተቀላቀለ በኋላ ከልጅነት የፊልም ስራ ህልሙ ጋር ተቀራራቢ ሆኖ ያገኘውን የትያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል በ1992 ዓ.ም ተቀላቀለ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ጆርናሊዝም እና ኮሚኒኬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ተመረቀ፡፡
አብርሃምና የቲያትር ትምህርት
የትምህርቱ አቅጣጫ ትያትር ተኮር እንደመሆኑ አብርሃምን ከጠበቀው ውጭ ሆኖበት የመጀመሪያው አመትን ትምህርቱ ላይ አሉታዊ ስሜት አሳድሮበት ነበር፡፡ ነገርግን ዓመታት በተጨመሩ ቁጥር የሚሰጡትን የትያትር ኮርሶች ለፊልም ህልሙ እንዴት ሊስማሙ እንደሚችሉ እያዛመደ ይማር ነበር፡፡ በ4 አመት ከሚሰጡ ኮርሶች ውስጥ አንደኛው ብቻ ፊልም ላይ ብቻ አትኩሮቱን የሚያደርገውን ኮርስ ውጤቱ ከሌሎች ኮርሶች በተለየ ከፍተኛ ውጤት ነበር ፡፡ አብርሀም ለአንድ ፊልም ሰሪ ስኬት ትያትር ትምህርት ትልቁን ቦታ ይይዛል ብሎ ያምን ነበር፡፡
በዘመኑ ከነበሩ የቲያትር ጥበባት መምህሮቹ ሁሉ እጅግ የሚያደንቀውና ላሁን ህይወቱ ቀርፆኛል ብሎ አፉን ሞልቶ የሚመሰክርለት ፋንታሁን እንግዳን ነበር። ቁርጠኝነትን : የጀመሩትን ከግብ ሳያደርሱ አለመተኛትንና ለሰዓት ክብር መስጠትን አብርሀም ከአስተማሪዎቹ ተምሯል፡፤
አብርሃም ገዛኸኝ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቲያትሪካል አርት የ3ኛ አመት ተማሪ በነበረበት ወቅት ለኮርስ ማሟያ የሰራውን የአሜሪካን ዲቪ የተሰኘ የሙሉ ጊዜ ትያትር ስክሪፕት በአንድ ወቅት ወደ ባህር ዳር ሙሉአለም ቲያትር ልኮት ነበርና በእርሱ ተወዳድሮ አሸንፎ በዘመኑ ለተማሪ ከፍ ያለ ገንዘብ(2500) ብር ማግኘት ችሎ ነበር፡፡
አብርሃምና ሜጋ
አብርሀም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ በወጣበት ዓመት ሜጋ ኪነጥበባት በ1,200 ብር ተቀጠሮ መስራት ጀመረ፡፡ ወደ ሜጋ እንዲገባ ያደረገው ደግሞ ተማሪ በነበረበት ወቅት ያስገባው አንድ የቴሌቭዥን ድራማ ስክሪፕት በጊዜው የፕሮዳክሽን መምሪያ የነበረውን ሰለሞን በላይን ትኩረት በመሳቡ በዚሁ ግለሰብ ጫና ፈጣሪነት በተመረቀበት አመት እንዲቀጠር አስተዋፅኦ አደረገ፡፡ በሜጋ ቆይታውም በተቀጠረ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተመራቂ ተማሪ ሆኖ ድራማ ዳይሬክት እንዲያደርግ ተፈቀደለት፡፡ በጊዜው አዲስ ለሆኑ ባልደረቦች ይህ አይነቱ እድል አይሰጥም ነበር፡፡ how she lies to her husband የተሰኘ የእንግሊዛዊው Bernaned showን አጭር ልብወለድ “ግጥሙ” በማለት ወደ አማርኛ ተርጎሞ ስክሪብትን ራሱ ፅፎ ራሱ ዳይሬክት አደረገ። ምንም እንኳ ስራው የተወደደለትና ቆንጆ የነበረ ቢሆንም ከቴሌቪዠን ቅርፅ ይልቅ ወደ ፊቸር ፊልም ያደላ በመሆኑ በቴሌቭዥን የመታየት እድል ሳያገኝ ቀረ።
አብርሀም ሜጋ በሰራበት ሁለት አመት ከሶስት ወር ውስጥ ማስታወቂያዎችንና ድራማዎችን ዳይሬክት አድርጓል። በፕሮዳክሽን ማናጀርነት ፤ በቪዲዩ ሙዚቃ ክሊፖች የተለያዩ የሙዚቃ ስራዎችን ዳይሬክት አድርጓል። በወቅቱ የነበረውን ሰርቶ ያለመጥገብ ስሜት ሁሌም አዲስ ነገርን የመሞከር አቅሙን አብርሀም ዛሬም ድረስ ይደነቅበታል። በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ የመስራት እቅድ የነበረው ለሁለት አመታት ብቻ እንደነበረ የሚያስታውሰው አብርሃም ሁለት አመት ሲሞላው ግን ስራ የመልቀቅ ፍርሃት ውስጡ በማደሩ አላደረገውም፡፡ ከሁለት አመት በላይ የሰራበት የሶስት ወር ጊዜያት በጣም ደስተኛ እንዳልነበር እና ሚዜዎቹ የተሰኘው ፊልም ስክሪፕት ግን ከሜጋ እንዲለቅ ድፍረት ሰጠውና በስተመጨረሻ ከሜጋ ለቀቀ።
አብርሃምና አዳዲስ ስራዎቹ
‹‹ሚዜዎቹ›› ሮማንቲክ ኮሜዲ ፊልም ሲሆን የአብርሀም የመጀመሪያ ፊቸር ፊልም ሆኖ እ.አ.አ በ2001 ተሰርቷል። ስራው በስክሪፕትና በዳይሬክቲንግ ዘርፍ አሸናፊ በመሆኑ በር ከፋች ሆነለት ። አብርሃም ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ እና ከብዙዎች ጋር ያስተዋወቀው ስራው ነበር። በኋላም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይተላለፍ የነበረውን “ገመና” የተሰኘ ተከታታይ ድራማ ወደ 52 ያህል ክፍል ዳይሬክት ማድረግ ቻለ። በዚህ መሀል በአንድ የውጭ ድርጅት በፕሮዳክሽን ማኔጅመንት የስራ ዘርፍ ቅጥር ፈፀመ። በዚህ ድርጅት በነበረው ቆይታ የጤና ኮሚዩኒኬሽን ስራ ላይ የፎቶ ኮሚክ መፅሄቶችን ፕሮዲዩስ ማድረግ መሆኑ በተለይ በአንድ ስእል እንዴት ሃሳብን መግለፅ ይቻላል የሚለውን የሲኒማቶግራፊ ምሰሶ እሳቤ ላይ ያለውን መረዳት አሳደገለት። በዚህ ድርጅት ቆይታውም “አትሌቱ” የተሰኘ ፊልም መመልከቱ ከተኛበት እንደቀሰቀሰው ይናገራል፡፡ አብርሃም አትሌቱ የተሰኘውን ፊልም በፊልም የመቀጠሉን ህልም በመቀስቀስ አኳያ ትልቁን ሚና እንደተጫወተ ይናገራል፡፡
ሎሚ ሽታ
ሎሚ ሽታ የአብርሃም ገዛኸኝ ሁለተኛ ፊቸር ፊልሙ ነው። ታሪኩ ገና በለጋ እድሜው በእናቱ ላይ ማህበረሰቡ ያደረሰውን ግፍ የተመለከተ የህግ ባለሙያ ላይ ያጠነጠነ ነው ። ፊልሙ ጉማ አዋርድ የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል እና የምስራቅ አፍሪካ የፊልም ፌስቲቫልን ጨምሮ በሀገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ከ10 በላይ ሽልማቶችን አስገኝቷል። ሎሚ ሽታ ፊልም አብርሀም “የአዳም ረታ መፅሃፍን ሲያነብ የመጣለት ሀሳብ ሲሆን የደራሲ አዳም ረታን ፍቃድ ያገኘና እርሱን እያማከረ በ2004 ዓ.ም የሰራው ተመራጭ ስራው ነው፡፡
የነገን አልወልድም
መነሻውን በገነነ መኩሪያ ሊብሮ ኢህአፓ እና ስፖርት ላይ ባደረገውና ጓድ እርገጤ የተሰኘውን ንኡስ ታሪክ ላይ መነሻው ያደረገው የስክሪፕት ፅሁፍ በሰለሞን ጋሻውና በአብርሃም የተፃፈ ሲሆን በ1969 የአንድ ስፖርት አሰልጣኝ ታሪክ የሚተርክ ስራ ነው፡፡ የነገን አልወልድም ፊልም በለንደን የሮያል አፍሪካ ፌስቲቫል ላይ የመመረጥ እድል አግኝቷል። ከኬንያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በፕሮዳክሽን፣ በሲኒማቶግራፊና በኤዲቲንግ ሶስት ዋንጫዎችን አምጥቷል፤እንዲሁም በጉማ አዋርድ ስድስት ዋንጫዎች ተሸላሚ ነበር፡፡
የአብረሃም ስራዎች ተጀምሮ እስኪጨረስ የብዙዎችን ስሜት ገዝቶ የመያዝ አቅም ያላቸው ቀረፃ፣ተዋንያን መረጣ፣ዳይሬክቲንግ፣ፕሮዳክሽን …ከላይ እስከ ታች ይህ ነው የሚባል እንከን የማይወጣላቸውና አጨራረሳቸው ከተለመደው ዉጪ የሆኑ ከዚህ ቀደም ለታዩት መማሪያ ወደ ፊት ለሚሰሩትም አጋዥ መነሻ የሚሆኑም ናቸው።
ተወዳጁ የእግር እሳት ተከታታይ ድራማ
የእግር እሳት ተከታታይ ድራማ አብርሃም በ2008 ዓ.ም ለ አራት ወራት ያክል የቢቢሲ ሰራተኛ ሆኖ በኬንያ ናይሮቢ በነበረ ጊዜ ያበሰለው ስራ ነበር፡፡ ይህም ስራውን አቋርጦ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ የሠራው የተዋጣለት ስራው ነበር። የእግር እሳት የስክሪፕት ፈጠራ በራሱ ድርጅት በሆነውና በ2008 በተቋቋመው ከፅንሰ-ሃሳቡ ጀምሮ ጎበዝ ዳይሬክተሮች፣ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች :ሲኒማቶግራፈሮች እና ፀሃፊዎች እንዲወጡበት ታስቦ በተቋቋመው “በአብሪኮም መልቲሚዲያ “የተሰራ ተወዳጅ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ነው። በእግር እሳት ተከታታይ ድራማ አብርሃም በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ኢ-ፍትሃዊነት ነቅፏል። ዛሬ የምንሰራው ኢ-ፍትሃዊነት ቀን ቆጥሮ ፤ጊዜ መንዝሮ ተመልሶ ወደ እኛው ላይ ተመልሶ እንደሚደርስ እና በማናቸውም ሁኔታዎች ውስጥ ተሆኖ ኢ-ፍትሀዊነትን ከዘርና ከውግንና በላይ እንድንታገለው ሞግቶበታል፡፡ በዚህም ሰውን ለመረዳት ከመሞከር ይልቅ ማውገዝ፣ማጭበርበር ሰውን እንደ ድንጋይ መወጣጫ መጠቀም እና በቀልን ማውገዝን በዚህ የቴሌቭዥን ድራማው አሳይቶናል።
በስንቱ
የሲትኮም ዘውግን ሙሉ ለሙሉ ጠብቆ የተሰራ ድንቅ ስራ ነው ይባልለታል። በሃገራችን ኢትዮጵያ በአጥጋቢ ሁኔታ አልተሰራም ብሎ ያሰበውን ክፍተት ለመሙላት ታላቁ ዳይሬክተር አብርሀም ገዝኸኝ ለህዝብ ያበረከተው ተወዳጅ ስራ ነው። ” በስንቱ” የኢትዮጵያውያንን ህይወት በሶስት ትውልድ ወክሎ በተለየ ጥበባዊ ለዛ የሚያቀርብ ምርጥ ሲትኮም ሲሆን ስመጥሮቹ ተዋንያን አለማየሁ ታደሰ – ስዩም ተፈራ – ፍቅርተ ጌታሁን – መስከረም አበራ – ዮሐንስ ተፈራ እና ሌሎችም ዝነኞች ተሳታፊ ሆነውበታል። በስንቱ ከይዘትና ጭብጡ የቀረፃ ቦታው በ 200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ መጋዝን ውስጥ እያንዳንዱን መቼት በመገንባት እጅግ በሚያምር ዲዛይን በመስራት ለአይን ግቡ በመሆኑ የህፃናትን የሴቶችና የሁሉም እድሜ ክልል ተመልካቾችን ቀልብ ለመያዝ የቻለ እንዲሆን አድርጎታል። በስንቱ አሁንም ዘወትር ሀሙስ ምሽት በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ተመልካችን እያስደነቀና እያሳቀ መታየቱን ቀጥሏል።
ቤተሰባዊ ህይወት
ተወዳጁ የፊልም ሰው አብርሃም ገዛኸኝ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን ትዳር የመሠረተውም እኢአ በ2005 ዓም ነው። ከትዳር አጋሩ ሃና ታዬ የ8 ዓመት ወንድ ልጅና የ5 ዓመት ሴት ልጅ አለው። አብርሃም ተከታታይ ድራማዎቹን ስክሪፕት መጻፍ ከመጀመሩ በፊት መረጃን ሰብስቦ በታላሚ ታዳሚዎቹ ላይ ጥናት አድርጎ እንደሚሰራ ይናገራል። ይህም የታዳሚዎቹን ፍላጎት እንዲያውቅ እና መልእክቶቹን በፈለገው ልክ እንዲያስተላልፍ ረድቶታል። በ”ሚዜዎቹ” በ”ሎሚሽታ” በ”የነገን አልወልድም” ፊልሞች “የእግር እሳት” እና በስንቱ የተሰኙ ልዩ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ አሳይቶን ያስገረመን ትውልዳችን ያገኘው ግዙፍ ፈርጥ አብርሃም ገዛኸኝ አሁን ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጅ “መሀል ሰፋሪ” የተሰኘ በ2024 የሚጠናቀቅ አዲስ ፕሮጀክትን በመስራት ላይ ይገኛል። አብርሃም በመሀል ሰፋሪ ምን ያሳየን ይሆን ? አብርሀም ወደ አውሮፓ በማቅናትም የአውሮፓ የፊልም ገበያ እንደምን እንደሆነ ቅኝት አድርጓል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚሰሩ የፊልም ስክሪፕት ጸሀፊዎችም ልምድ መቅሰም ችሏል፡፡በዶሀ የፊልም ተቋምም ውስጥ ተጋባዥ በመሆን ለስራው የሚጠቅመውን እውቀት ቀስሞ ተመልሷል፡፡
አብርሃም የመጀመሪያ የትያትር ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ሜጋ ኪነ ጥበባት ውስጥ የተለያዩ ተከታታይ ድራማዎችን በማስተባበር እንዲሁም አጫጭር ድራማዎችን ይሰራ ነበር። የመጀመሪያው ወደ ህዝብ የቀረበበት ፊልሙ ሚዜዎቹ የተሰኘ ሲሆን ሽልማቶችንም ያስገኘለት ድንቅ ስራውም ነው። በማስቀጠል ሎሚ ሽታ የተሰኘውን የአዳም ረታን ፅሁፍ ወደ ፊልም የቀየረ ሲሆን በስክሪፕትም ሆነ በዳይሬክተርነት ተሸልሞበታል። የገነነ መኩሪያን መፅሃፍት በመንተራስ የነገን አልወልድም የተሰኘ ፊልምም ሰርቷል። በዳይሬክተርነት ሙያውም በገመና ድራማ የተወሰኑትን ክፍሎች በዳይሬክቲንግ፣ ሞጋቾች ድራማን ላይ እንዲሁ ተሳትፏል። በማስቀጠልም በሙሉ አዘጋጅነት ሆኖ እና የራሱን ስራ የእግር እሳት በተሰኘው ተከታታይ ድራማም ለህዝብ መድረስ ችሏል፡፡ ከመጀመሪያው ፊልሙ ማለትም ከሚዜዎቹ ፊልም ውጪ እምብዛም ወደ ኮሜዲው ባያቀናም አሁን ላይ እየታየ ያለው በስንቱ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ይበልጥ ጠንክሮ መጥቶበታል። ይህም በባለሙያውም ሆነ በተመልካች ዘንድ ከበሬታን ያስገኘለት ነው፡፡
ስለ አብርሀም ገዛኸኝ የተሰጡ አስተያየቶች
አብርሃም ወደፊት ከነ ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ እኩል መጠራት የሚችል ትልቅ የፊልም እና የዳይሬክቲንግ ጥበብ ያለው ሰው ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከውጪም ሆነ ከሃገር ውስጥ በስራው ዙሪያ እንደሚያስጠራ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አብርሃም ትልቁ ጠንካራ ጎኑ ስራዎቹን ወረቀት ላይ የመጨረስ ትልቅ አቅም አለው፡፡ ይህም ለብዙ ዳይሬክተሮች ትምህርት የሚሆን ነው፡፡ አብርሀም የሚፈልጋቸውን ምስሎች አሊያ ቀረጻ ወረቀት ላይ ከማስፈሩ ባሻገር ወቀ ለስራው ትልቅ ቦታ ስለሚሰጥ ትጋቱን ያለአንዳች ስስት ያሳያል፡፡ በእርሱ ስራ ላይ የተሳተፉ አርቲስቶች እና ስራዎች ሁሌም በሽልማት መድረክ መጠራታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው። ከሩቅ በሌሎች እይታ ኮስታራ የሚመስለው አብርሃም ለሚቀርቡት ሰዎች ግን ጨዋታ ወዳጅ ፣ሳቂታ ፣ ቀልደኛ ሰው ነው። ለስራው ያለው ትጋት እና ፍላጎት ገና ከመጀመሪያው ወደ ፊልሙ አለም ሲገባ በሽልማት መጀመሩ ፈጣንነቱን እና ለስራው መሰጠቱን ያሳያል። በባለሙያዎች እና በህዝብ የመወደድ እድል ያለውም ሰው ነው። ለዚህም ምስክር በስንቱ ድራማ ያሳያል። በፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ለውጥ ከሚያመጡ ባለሙያዎች አብርሀም አንዱ ነው፡፡ደግሞም ይሳካለታል፡፡
አማኑኤል መሀሪ /ደራሲ /
አብረሀም ገዘሀኝ ስራውን የሚያከብር፣ በዕውቀት እና በዕቅድ የሚሰራ ጊዜውን በአግባቡ የሚጠቀም ሰው ነው። አብርሀም በስራ ላይ ሰርቶ የሚያሰራ፣ ያወቀውን ለማሳወቅ የማይታክት ሙያተኛን የሚያከብር ባለሞያ ነው። አብርሀም በጓደኝነት ተጫዋች፣ ሳቂታ ፣የዋህ በመከባበር እና በፅኑ ጓደኝነት ግንኙነት የሚያምን ደግ፣ ወጀብ የማይነዳው በጣም አቋም ያለው ህይወትን የተረዳ መልካም ስብዕና ያለው ቀና ጓደኛ ነው።
አብርሀም ለቤተሰባዊ ህይወቱ ቅድሚያ የሚሰጥ ባለቤቱን ልጆቹን የሚወድ የሚያከብር ምሳሌ የሆነ አስተዋይ የቤተሰብ ሰው ነው። ለአብርሀም የስኬታማነት ጉዞ ደስተኛ ቤተሰብ ከመመስረቱ፣ ጊዜውን በአግባቡ እና ስራውን በዕቅድ እና በዕውቀት ከመስራቱ ባሻገር ህይወትን የተረዳበት መንገድ እና በአቋም እና በማስተዋል የታነፀው ቀና ስብዕናው አስተዋፅኦ አድርጓል ብዬ አምናለሁ።
ቴዎድሮስ ታደሰ( ጋዜጠኛ)
መዝጊያ
ይህ የመዝጊያ ሀሳብ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላትን አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ አብርሀም በፊልሙ ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዙዎች ዘንድ መደነቅ የቻሉ ስራዎችን የሰራ ነው፡፡ አለምአቀፍ ልምድንም ለማካበት የቻለ ሲሆን በየጊዜው ራሱን ለማሳደግ በመጣሩ ጥሩ ውጤትን ማግኘት ችሏል፡፡ የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ገና ሀ ብሎ በጀመረበት በ1990ዎቹ አጋማሽ ወደ ኢንደስትሪው ብቅ ያለው አብርሀም የውስጥ መሻቱን እውን ለማድረግ የሞከረው ሙከራ ተሳክቶለታል፡፡ እንዲህ አይነት ስኬቶች ደግሞ ለትውልዱ የሚነግሩት አንድ መልእክት አለ፡፡ የሰው ልጅ ህልሙን ለመኖር ውሳኔ ካደረገ እንደሚችል የአብርሀም የህይወት እና የስራ ተሞክሮ ጥሩ ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ አብርሀም የማስተማር ስራ ቢጀምር ሌሎች ወጣቶች ብዙ ልምድ ይቀስማሉ፡፡ ምስክርነት የሰጡት ብዙዎቹ ያነጋገርናቸው ሰዎች እንደነገሩን ነገሮችን ወረቀት ላይ መጨረስ የአብርሀም ልማድ ነው፡፡ ይህ ልማድ ደግሞ ስራው በጥንቃቄ እና በቀላሉ እንዲሰራ አስችሎታል፡፡ በሀገራችን ፊልም ላይ አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪክ መሰነድ አለበት፡፡ የፊልም ዝንባሌ ያለው ይህን ሰነድ ሲያገላብጥ ብዙ ሊማር ይችላል፡፡ አንድ ሰው ታሪኩን ካካፈለ ሁነኛ መፍትሄ እንዳካፈለ ይቆጠራል፡፡ አብርሀምም የስራ ታሪኩን ለማካፈል የፈቀደው ሌሎች ከእርሱ ይማሩ ዘንድ ነው፡፡ የእኛም ግብ በየዘመናቱ ብቅ ያሉ የሀገር ከዋክብቶችን እያፈላለግን እና በመስፈርቱ መሰረት ሚዛን የሚደፉትን ወደፊት እያመጣን እናስተዋውቃለን፡፡ በዚህ ስራችን ደግሞ ተጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተዘጋጀ እና በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች የሚሰነድ በመዝገበ-አእምሮ ቅጽ 2 መጽሀፍ ላይ ታትሞ የሚወጣ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ሀምሌ 26 2015 ተሰነደ፡፡