አባይነሽ ብሩ ሺበሺ
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1970ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡
ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ይህ አጭር ግለ-ታሪክ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ ከ43 አመት በላይ በሚድያ ሙያ ከሰሩት መሀል ታሪካቸው የሚዘከርላቸው ጋዜጠኛ አባይነሽ ብሩ ሺበሺ ናቸው፡፡
ትውልድ ዕድገትና ትምህርት
አባይነሽ ብሩ በ1946 ዓ.ም በቢሾፍቱ/ ደብረ ዘይት ከተማ ተወለደች፡፡ በአራት ዓመት ከአራት ወር አራት ቀኗ ወደ ቄስ ትምህርት ቤት ተወስዳ ከፊደል እስከ ዳዊት መድገም ተምራለች፡፡ የአንደኛ ደረጃንና ከሁለተኛ ደረጃም ግማሹን በአፄ ልብነ ድንግል ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃን በልዕልት ተናኘ ወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምራ የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን በአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ስር በነበረው የልዑል በዕደ ማርያም ት/ቤት አጠናቃለች፡፡
ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በአማርኛ ቋንቋ አግኝታለች፡፡ አባይነሽ የነበራትን የትምህርት ጥማት ለማርካት ጡረታ ከወጣች በኋላ እንደገና ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በሶሻል ሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪዋን በ2011 ዓ.ም አግኝታለች፡፡ በሥራ ቆይታዋም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በርካታ ሥልጠናዎችን ወስዳለች፡፡
የጋዜጠኝነት ሥራና ህይወት
አባይነሽ ሥራ የጀመረችው በዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሆና በፍሪላንሰርነት በ1970 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ ነው፡፡ በሬዲዮ ጋዜጠኝነቷ በሪፖርተርነት ፤ በአዘጋጅነት ፤ እንዲሁም የአማርኛው ዘርፍ የመዝናኛና ትምህርታዊ ፕሮግራሞችና የአማርኛ ፕሮገራም ክፍል ኃላፊ በመሆን አገልግላለች ፡፡ “የጋዜጠኝነት ሥራዬ ህይወቴ ነበር፡፡ ባለቤቴ የሚረዳኝ ጥሩ ሰው ባይሆን ኖሮ ትዳሬንና ልጆቼን አጣቸው ነበር” ትላለች አባይነሽ፡፡ሁሉም ቀናቶቿ የሬዲዮ ሥራዎቿን የምታከናውንባቸው ነበሩ፡፡
የእረፍትና የበዐላት ቀናት አልነበሯትም፡፡ የሬዲዮ መጽሔት፣ በራስ መተማመን፣ ከአድማስ ባሻገር፣ የሴቶች ፐሮግራም፣ የማለዳ ፕሮግራም ፣ የተሰኙ ፕሮግራሞችን ትሰራ ነበር፡ ፡ ከመዝናኛ ውጭ በምትሰራቸው ፕሮግራሞች ትኩረቷ በተለይ ጤናን፣ ሴቶችን፣ ህፃናትን የሚመለከቱ ነበሩ፡፡ ማህበራዊ እሴቶቻችን፣ የልጆች አስተዳደጋችን፣ የትዳር ህይወታችን፣ የትምህርት ቤት ቆይታችን፣ የሀገር ፍቅርና ታሪካችን እና ሌሎች ብዙ ብዙ ጉዳዮቻችን በአባይነሽ ዝግጅቶች ተዳሰዋል፡፡
አባይነሽና የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም
በኢትዮጵያ ሬዲዮ ፕሮግራም ታሪክ የሬድዮ ፕሮግራሞች አቀራረብ ላይ ከፍተኛ ለውጥን ያስተዋወቀው የእሁድ ጠዋት የመዝናኛ ፕሮግራም ከ40 ዓመታት በፊት በ1973 ዓ.ም ሲጀመር ከመስራቾቹ መካከል ብቸኛዋ ሴት ጋዜጠኛ አባይነሽ ብሩ ነበረች፡፡
በዚያ ለመዝናኛ የሚደመጡ አማራጭ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ባልነበሩበት ዘመን አባይነሽ በታዋቂው የሬዲዮ ሰው በታደሰ ሙሉነህ ተኮትኩታ ያደገች ጋዜጠኛ ነበረችና ከሙያ ባልደረቦቿ ከንጉሤ አክሊሉ፣ አዲሱ አበበና ታምራት አሰፋ ጋር በመሆን የእሁድ ጠዋት ፕሮግራምን ለአድማጮቿ በጣፈጠ ሁኔታ የምታቀርብ የዚያን ጊዜ ታታሪ ፈርጥ ነበረች፡፡ በዚያ የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም ቃለ-መጠይቅ ያደረገቻቸውን ባለሙያዎች፣ አንስታ ያወያየችባቸውን ጉዳዮች ብዙ ነበሩና ዛሬ ዝርዝራቸውን አታስታውስም፡፡
አባይነሽና የሙያ እናትነቷ
የሬዲዮ ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኞች ክብር በሚሰጥበት የ2013 የዓለም ሬዲዮ ቀን እንደተገለጸችው አንጋፋና ድምፀ ሸጋዋ አባይነሽ ብሩ የበርካታ ግለሰቦች የሙያ እናት ናት ፡፡ ብዙዎች አዲስ ለሚቀጠሩና በሥራ ላይ ለሚገኙ ጋዜጠኞች ሙያዊ ሥልጠናን በመስጠት ብቁ እንዲሆኑ አድርጋለች፡፡ በሥራው ላይ ልምዷን በማካፈል ለብዙዎች ምሳሌ ሆናለች፡፡ የተደበቀ ችሎታና ዕውቀት ጎልቶ እንዲወጣ ተሰጥዖ ያላቸውን የሬዲዮ እንግዶቿን በማበረታታት ወደ መድረክ እንዲወጡና ዕውቅናና ክብር እንዲያገኙ ረድታለች፡፡
አባይነሽና የማህበረሰብ ልማት ሥራዎቿ
ከ19 ዓመት የጋዜጠኝነት ቆይታዋ በኋላ አባይነሽ በሙያዋ ወደ ማህበረሰብ ልማት ሥራ ውስጥ ገብታ በሰራቻቸው የሬዲዮ ፕሮግራሞችና ሌሎች የኮምዩኒኬሽን ሥራዎች የሚያኮሩኝን ውጤቶች አግኝቼባቸዋለሁ ትላለች፡፡ በዚህ ተግባር ውስጥ ኤችአይቪን በመከላከል ሥራ በጥናት ላይ በመመስረት የተሰሩትን “ማለባበስ ይቅር፣ መሊ ሃራ፣ ና ማመን መታመን ” የተሰኙ 3 የሙዚቃ ሥራዎችን ያስተባበረች መሆኑን ትጠቅሳለች፡፡
በርካታ ዶክዩመንተሪዎችንና የሬዲዮ ፕሮግራሞችንም በመቀየስና በማቀድ ሰርታ አሰርታለች፡፡ በሬዲዮ ሥራ ላይ የነበራትን ልምድ በጤና ኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ካገኘችው ዕውቀት ጋር በማጣመር ለበርካታ በጤናው ዘርፍ ለተሰማሩ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች በባህሪይ ለውጥ ኮሚዩኒኬሽን ሥራ ላይ ሥልጠናዎችን ሰጥታለች፡፡
“ብዙውን ጊዜ በመድረክ ላይ ስገኝ በጋዜጠኝነት ወይ በባህርይ ለውጥ ኮሚዩኒኬሽን ያሰለጠንኩት ወይም ደግሞ በሬዲዮ ቆይታዬ ቃለመጠይቅ ያደረኩለት አንድ ሰው አላጣም ”
አባይነሽ
አባይነሽና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር
አባይነሽ “የሴቶች ጉዳዮች በመገናኛ ብዙሃን” በሚለው አንድ የጥናት ወረቀቷ “በሁሉም የሚዲያ ዘርፎች የተሰማሩ ሴቶች የሥራቸው ሁኔታና ፀባይ የሚያስከትሉባቸውን የተለያዩ ሙያዊም ሆነ ማህበራዊ ችግሮች ሊቋቋሙ የሚችሉበትና የሚረዳቸው የሚዲያ ሴቶች ማህበር ቢያቋቁሙና የጋራ ችግሮቻቸውን በመፍታት በኩል ብቻ ሳይሆን ለመጭዎቹ ወጣት ሴቶች ትምህርት ሊሰጡ የሚችሉ ሥራዎችን ሊያዘጋጁ የሚችሉበትን መንገድ ቢቀይሱ መልካም ነው” ብላ ያቀረበችው ሐሳብ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በኢትዮጵያ በጊዜው በነበሩ ሴቶች ጋዜጠኞች ተጋድሎ እውን ሆኖ ማየቷ ትልቅ ደስታን እንደሚሰጣት ትናገራለች፡፡ በመሆኑም ማህበሩ ከምስረታ እስከ አሁን በነበሩት 20 ዓመታት ውስጥ በነበረውና ባለው ውጣ ውረዱ ውስጥ ተካፋይ ናት፡፡ አሁንም በማህበሩ ውስጥ ትሰራለች ትሳተፋለችም፡፡
አባይነሽና የትዳር ህይወት
አባይነሽ ከአቶ ሲሳይ ቱሉ ጋር በ1971 ዓ.ም በፍቅር ትዳር መስርታ ትርሲት ሲሳይና ልዩ ሲሳይ የሚባሉ ሁለት መልካም ልጆችን አፍርታ፣ 5 የልጅ ልጆችንም አይታለች፡፡ ትዳርና ጋዜጠኝነትን አስማምቶ ለመሄድ የባለቤቷ መልካምነትና የቤተሰብ አባሎቿ ድጋፍ በጣም እንደረዳት የምትገልጸው አባይነሽ ባለቤቷ በህይወት ቢያልፍም ዛሬ እግዚአብሔር ጥላ መከታ ሆኗት፣ ልጆቿ አይዞሽ እያሏት ህይወትን እንድትቀጥል እንዳደረጓት ትናገራለች፡፡
አባይነሽና ሽልማቶች
አባይነሽ በሰራቻቸው የተለያዩ ሥራዎች ከተለያዩ ድርጅቶች የምስጋና የምስክር ወረቀቶችን አግኝታለች፡፡ ከ “ ሴቶች ይችላሉ” ድርጅት “ጣዝሙት” ተብላ ተሸልማለች፡፡ በ2013 ዓ.ም የዓለም ሬዲዮ ቀን ጋዜጠኛ አባይነሽ ብሩ በሬድዮ ጋዜጠኝነት ላደረገችው ከፍ ያለ አስተዋፅዖ የህይወት ዘመን ምርጥ ጋዜጠኛ ተሸላሚ ሆናለች፡፡
አባይነሽና ዛሬ
አባይነሽ ዛሬ ከቅጥር ሥራ ጡረታ ወጥታለች፡፡ በጡረታ ጊዜዋ ተምራ ሁለተኛ ዲግሪዋን አግኝታለች፡፡ ዛሬም በማማከርና በማሰልጠን ሥራ እየሰራች ነው፡፡ አባይነሽ ሁሌም በመማር ታምናለች በማንበብ ትደሰታለች፡፡ ሥራ መድኃኒት ነው ትላለች፡፡ “ ሰው ማንበብ ሲተውና፣ መስራት ሲያቆም የህይወት ምዕራፉን የመዝጋት ጉዞውን ይጀምራል” ትላለች፡፡