የመዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢ
አስፋው መሸሻ
ይህን ጽሁፍ ፖስት ሲያደርጉ የጽሁፉን ባለቤት ተወዳጅ ሚድያን በምንጭነት እንዲጠቅሱ ይገደዳሉ፡፡
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በመዝናኛው ዘርፍ ያሉ የሚድያ ሰዎችን የህይወት ታሪክ ሲሰንድ ነበር፡፡ በ2014 የ180 የሚድያ ሰዎች ታሪክ በመጽሀፍ መውጣቱ አይዘነጋም፡፡ በቅርቡ ደግሞ ቅጽ 2 መጽሀፍ ለማውጣት እየተዘጋጀን ነው፡፡ በዚህ ስብስብ ውስጥ ታሪካቸው ከሚካተትላቸው አንዱ አስፋው መሸሻ ነው፡፡ አስፋው ባለፈው ቅዳሜ ጥር 4 2016 ህይወቱ ያለፈ ሲሆን እዝራ እጅጉ የቤተሰቡን ፈቃድ በማግኘት የህይወት ታሪኩን ሰንዶታል፡፡
የመዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢ አስፋው መሸሻ አባቱ ክቡር አቶ መሸሻ አስፋው ሲባሉ እናቱ ደግሞ ክብርት ወይዘሮ ዘነበወርቅ አሻግሬ በመባል ይታወቃሉ፡፡ አስፋው መሸሻ ሀምሌ 19 1959አ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ‹‹ሰሜን ማዘጋጃ ችሎት ሰፈር›› በሚባለው አካባቢ ተወለደ፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በቤተልሄም ት/ቤት ከ 1-8ኛ የተማረ ሲሆን በልጅነቱም ከሁሉም የተማሪ ቤት ጓደኞቹ ጋር ተግባቢና ለኪነ-ጥበብም ታላቅ ፍቅር ያሳደረ ታዳጊ ነበር፡፡ ለወላጆቹ 5ኛ ልጅ የሆነው አስፋው መሸሻ ገና በልጅነቱ የሰው ጥቃት የማይወድ ለብዙዎች አሳቢ እንደነበር የእናቱ እህት አክስቱ ወይዘሮ ደብረወርቅ አሻግሬ ለተወዳጅ ሚድያ ግለ-ታሪክ አዘጋጅ ነግረውታል፡፡
የእነ አስፋው ሰፈር በተለይ በልዩ ስሙ የሚታወቀወ ‹‹ጉቶ ሜዳ›› እግርኳስን ለመጫወት የተመቸ ሜዳ ነበር፡፡ በርካታ ስመ-ጥር ተጫዋቾችንም ያፈራ ነበር፡፡ ታዳጊው አስፋው ግን ከኳስ ይልቅ ጥበባዊ ነገሮች የበለጠ ይስቡት ስለነበር ወደ ኳሱ ብዙም ትኩረት አላደረገም ነበር፡፡
አስፋው፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ አባቱ ክቡር አቶ መሸሻ አስፋው በአፍሪካ ህብረት የሚያገለግሉ ከፍተኛ ዲፕሎማት ስለነበሩ እርሳቸው ለአፍሪካ ህብረት ተልእኮ ታንዛንያ በመሄዳቸው በ1972 አ.ም ቤተሰቡ ኑሮውን በዚያው አድርጎ ነበር፡፡ አስፋውም በታንዛንያ የሁለተኛ ደረጃ እና የኮሌጅ ትምህርቱን በመማር በኮምፒውተር ሳይንስ ሊመረቅ ችሏል፡፡
አስፋው በመቀጠል፣ ከቤተሰቡ ጋር በናይሮቢ ኬንያ መኖሪያውን ያደረገ ሲሆን በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በሀረርም ለተወሰኑ ጊዜያት ከታላቅ ወንድሙ ከአቶ በለጠ መሸሻ ጋር ኖሯል፡፡
አስፋው መሸሻ፣ አዲስ አበባ እንደተመለሰ አቶ ግርማ በሻህ በጀመሩት ‹‹ፕሬስ ዳይጀስት›‹ መጽሄት ላይ ለተወሰኑ ጊዜያት ይሰራ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ይህች የህትመት ውጤት በሳምንቱ የወጡ ዜናዎችን በአጭሩ ጨምቃ የምታወጣ ነበረች፡፡ አስፋውም ከአቶ ግርማ በሻህ ጋር የአቅሙን ያህል የሚድያ ፍቅሩን ሊወጣ ሞክሯል፡፡
አስፋው፣ ከ1992 አ.ም በኋላ የኤፍ ኤም ሬድዮ በሀገራችን አንድ ተብሎ ሲጀመር ከነበሩ ግንባር ቀደም አቅራቢዎች አንዱ ነበር፡፡ በተለይም ‹‹አይሬ›› በተሰኘው የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ በ 97ነጥብ አንድ ከጓደኛው ከዳንኤል ግዛው ጋር በመሆን ብዙዎችን ሲያዝናና ቆይቷል፡፡
ዳንኤል ግዛው እና አስፋው መሸሻ ላለፉት 30 አመታት የሚተዋወቁ ጓደኛማቾች ስለነበሩ ዳንኤል አይሬ ዲጂታል ኢንተርቴይመንትን እንደጀመረ አስፋውን ወደ ሚድያው የመዝናኛ አለም እንዳመጣው ይናገራል፡፡ በተለይም የአይሬ ፕሮግራም ሲጀመር አስፋው ፕሮግራሙን በማድመቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ በይበልጥም ድምጹ በጣም ለሬድዮ የሚሆን ስለነበር ብዙ አድማጮችን ለመማረክ ችሎ ነበር፡፡ ‹‹ ሞቅ ደመቅ ሸብረቅ፡›› በሚለው አነጋገሩ ከአድማጭ ጆሮ ያልጠፋው አስፋው መሸሻ የበለጠ ፕሮግራሙን ተናፋቂ ለማድረግ ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ ይህ ጥረቱ እንደተሳካለትም ወዳጁ ዳንኤል ግዛው ይመሰክራል፡፡ ዳንኤል ግዛው አስፋውን ሲገልጸው ለመዝናኛ የተፈጠረ ድንቅ ሰው ይለዋል፡፡ አስፋው ባለበት ቦታ ሁሉ ሳቅ እና ጨዋታ ከእነ ሙሉ ክብራቸው ይኖራሉ፡፡ ዳንኤል ግዛው ይህን የልብ ወዳጁን ማጣቱ ትልቅ ሀዘን ውስጥ ከቶታል፡፡ ነገር ግን ከፈጣሪ ጋር ማንም አይጣላምና ነፍሱን በገነት እንዲያኖራት እመኛለሁ ሲል ዳንኤል ሀሳቡን ሰጥቷል፡፡
አስፋው መሸሻ በአይሬ የመዝናኛ ፕሮግራም ለ6 አመታት ቆይታ ካደረገ በኋላ መሰናዶው ሲቋረጥ ለተወሰኑ ጊዜያት በዛሚ ኤፍ ኤም ሰርቶ ነበር፡፡
ጥር ወር ሲነሳ ለአስፋው እጅግ አሳዛኝ ወቅት ነበር፡፡ ጥር 8 1999አ.ም በአንድ ቀን የሚወዳቸው አባቱን ክቡር አቶ መሸሻ አስፋው እና የሚያከብራት ባለቤቱን ወይዘሮ ሱዛን አስመላሽን በሞት ያጣበት ቀን ነበር፡፡ ያ ቀን ለአስፋው ፈጽሞ የማይረሳ የሀዘን ጥላ ጥሎ ያለፈ ሲሆን ለአስፋውም በጊዜው መጽናናት ከባድ ነበር፡፡ ቢሆንም አጠገቡ ባሉ ሰዎች አበረታችነት አስፋው ፈጣሪ ያመጣውን ከመቀበል ውጭ አማራጭ አልነበረውምና ተጽናና፡፡ በወቅቱ የ12 አመት ታዳጊ የነበረውን ልጁን ጃፒን ወይም ሳምሶን አስፋውን በጥንቃቄ ለማሳደግ የተቻለውን አድርጓል፡፡ በእርግጥም አንድ ልጁ ነበርና በልጁ ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳይገጥመው የተቻለውን አድርጎ ነበር፡፡
አስፋው መሸሻን በ1992 በአይሬ ፕሮግራም ያውቀው እንደነበር ዲጄ ፋትሱ / ሱራፌል ግዛቸው ይናገራል፡፡
የመዝናኛ አዘጋጅ እና አቅራቢ ዳንኤል ግዛው ሙዚቃው ላይ ባለው እውቀት አስፋው መሸሻ ደግሞ ፕሮግራሙን ከአድማጮች ጋር በስልክ እንዲሁም በአየር አድማጭን በሚይዝ መልኩ አዋዝተው ያቀርቡ ነበር ። ያኔ አይሬን አየር ላይ በሚያውሉበት ሰአት አስፋው ያቀርባቸው የነበሩት ቀልዶች የማይዘነጉና የማዝናናት አቅም ነበራቸው ሲል ፋትሱ 20 ወደ ኋላ ተመልሶ ያስታውሳል፡፡
ፋትሱ ሲቀጥልም ” አስፋው ለመዝናኛው ኢንዱስትሪ ያሳየው አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡ እንደእርሱ አይነት ሰው ናቸው ፕሮግራሙን ማቅረብ የሚችሉት ። ፈጣን የሆነ አይምሮ ያላቸው ለማዝናናት እንዲሁም አየር ሰአቱንም ጣፋጭ እንዲሆን ያደርጋሉ” ይላል።
‹‹ከአይሬ በመቀጠል በዛሚ የሬዲዮ ጣቢያ አብረን እንሰራ ነበር፡፡አስፋው ህይወትን ቀለል አድርጎ ይመለከት የነበረ ፈታ ያለ ሰው ነው፡፡ ፣ መሳቅ ፣ መጫወት፣ ታሪክ ማውራት የሚወድ ከትልቅም ከትንሽም ሰው ጋር የጓደኛ ያህል የሚቀርብ ፣ ከተማረውም ካልተማረውም ከሁሉም ጋር በየደረጃው የሚግባባ ፣ ሰውን የሚያከብር ሰው ነበር፡፡›› በማለት ዲጄ ፋትሱ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
አስፋው መሸሻ ከዛሬ 30 አመት በፊት አሁን በህይወት የሌለችውን ባለቤቱን ከወይዘሮ ሱዛን አስመላሽ ጋር ጋብቻ መስርቶ ሳምሶን አስፋውን ወይም ጃፒን ወልዷል፡፡ ጃፒ በአሁኑ ሰአት የ29 አመት ወጣት እና ኑሮውንም በባህር ማዶ ያደረገ ነው፡፡
አስፋው የዛሬ 14 አመት ግድም ወደ አሜሪካን ሀገር በማቅናት ኢቢኤስ ቲቪ ሲጀመር ከመስራች የሚድያ ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ በተለይም ‹‹ኑሮ በአሜሪካ›› በተሰኘ መሰናዶው በተመልካቾች ዘንድ ከበሬታን አግኝቷል፡፡ ይህ ፕሮግራም በተለይ በባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚያሳልፉትን የህይወት ውጣውረድ ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነበር፡፡
አስፋው መሸሻ ሙሉ ለሙሉ ኑሮውን አዲስ አበባ ካደረገ በኋላ በእሁድን በኢቢኤስ ፕሮግራም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ያገለገለ ባለሙያ ነበር፡፡ ይህ ፕሮግራም በተመልካች ዘንድ ተናፋቂ እንዲሆን ካደረጉት በሳል ሰዎችም አስፋው ይጠቀሳል፡፡ አስፋው መሸሻ በመዝናኛው አለም በጠቅላላ ከ27 አመት በላይ በኢቢኤስ ደግሞ ለ 14 አመት በንቃት እና በትጋት አገልግሏል፡፡
ለሰዎች በጎ ነገር ማድረግ ከፍ ያለ ደስታን የሚያጎናጽፈው አስፋው መሸሻ አባቱ የሰጡትን ቪታራ መኪና ለበጎ አድራጎት ስራ ያበረከተ ቸር እና በጎ አሳቢ ታላቅ ሰው ነበር፡፡ አስፋው መሸሻ በኢ.ቢ.ኤስ ቲቪ አብረውት በሚሰሩ ባልደረቦቹ ዘንድ የሚወደድ በመሆኑ ለብዙዎችም እንደ ታላቅ ወንድም በመሆን የሚገስጽ እና የሚመክር ነበር፡፡
አስፋው መሸሻ ባለፈው ጥቅምት 2016 በገጠመው የጤና መታወክ በሀገር ውስጥ የተወሰነ ህክምና ሲከታተል ነበር፡፡ ለበለጠ ህክምና ወደ ባህር ማዶ አቅንቶ ባለፉት ወራት ህክምናውን ሲከታተል ነበር፡፡ በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ሲታከም ነበር፡፡ ነገር ግን ሊድን ስላልቻለ ቅዳሜ ጥር 4 2016 በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከለሊቱ 9 ሰአት ከዚህ አለም ድካም አርፏል፡፡
መዝጊያ፤ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የዊኪፒዲያ ወይም የአማርኛ መዝገበ አእምሮ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
ድርጅታችን ተወዳጅ የሚድያ ሰዎችን ታሪክ መሰነድ ከጀመረ 3 አመት ሊሞላው ነው፡፡ ሰዎች በህይወት ሳሉ ታሪካቸውን ሰንደው ወይም አሰንደው ማስቀመጥ እንዳለባቸው ስንናገር ቆይተናል፡፡ ህይወታቸው ካለፈው በኋላ ስለ ባለታሪኮቹ የሚናገሩ ሰዎች ተባባሪ ሆነው የሰው ስም ከመቃብር በላይ መዋል አለበት፡፡
አስፋው መሸሻን በህይወት ሳለ ልናነጋግረው ሀሳብ ነበረን፡፡ ስለ እርሱም አንዳንድ መረጃዎችን እያሰባሰብ ህምሙ ቀደመ፡፡ ህይወቱ ካለፈ በኋላም የዚህን ታላቅ ሰው ታሪክ ከእኛ ትልቅ የመረጃ ቋት ወይም መዝገብ ላይ ለማስፈር ሞክረን በ1 ቀን ተሳክቶልናል፡፡ ማህበራዊ ድረ-ገጽ ላይ አስፋውን የሚመጥን ትክክለኛ መረጃ ወይም የህይወት ታሪክ ያስፈልጋልና ይህንኑ አድርገናል፡፡ ከወንድሙ ከአቶ በለጠ መሸሻ ለዳንኤል ግዛው እንዲሁም ከአክስቱ ከወይዘሮ ደብረወርቅ አሻግሬ ከወንድሙ ልጅ ከአይዳ በለጠ ባገኘነው ማረጋገጫ እና መረጃ ተገቢውን ፈቃድ አግኝተን ይህን የህይወት ታሪክ በራሳችን ተነሳሽነት በዲጂታል ሚድያዎች ላይ አስቀምጠናል፡፡ እውነተኛ እና ትክክለኛ መረጃ በቅርብ ሰዎች መፈቀድ እና መነገር አለበት ብለን ስለምናምን ይህንኑ ፕሮፌሽናል አካሄድ ተከትለን ሙያዊ ተግባራችንን ተወጥተናል፡፡ ይህን አጭር ታሪክ ስንሰራ መረጃ በመስጠት ተባባሪ ለነበሩት ለዲጄ ፋትሱ ፤ ለሳምሶን ሺፈራው እና ለዲጄ ያሬድ የከበረ ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን፡፡
ይህ ጽሁፍ የቃለ-መጠይቅ የምርምር እና የአርትኦት ስራው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተከናወነ ሲሆን ዛሬ ጥር 6 2016 በድረ-ገጾች ላይ የተቀመጠ ነው፡፡ አስፈላጊው ማሻሻያ ታክሎበት የሚነበብ ይሆናል፡፡ ስለ አስፋው መረጃ እና ምስል ያላችሁ በ0911416678 በቴሌግራም መላክ ትችላላችሁ፡፡