አስናቀች ደምሴ ወልደሚካኤል
ከ23 አመት በላይ በጋዜጠኝነት የዘለቀችው አስናቀች ደምሴ ከአስመራ ሬድዮ እስከ ኢትዮጵያ ሬድዮ ብዙ ገጠመኝ አስተናግዳለች፡፡ ብዙ ልምድም አካብታለች፡፡ የግንቦት 1981 መፈንቅለ መንግስት በተደረገ ጊዜም አስመራ የነበረችው አስናቀች የምታስታውሰው አላት፡፡ በመስክ ጉዞ በርካታ የኢትዮጵያን ክፍል መጎብኘት የቻለችው አስናቀች ታሪኳ ብዙ አስተማሪ በመሆኑ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡
ትውልድ
ጋዜጠኛ አስናቀች ደምሴ ሰኔ 21 1957 ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ወረዳ ወዴሳ ቀበሌ ነበር የተወለደችው፡፡ እድገቷ ከ2 ዓመት እድሜዋ ጀምሮ አያቶቿ ዘንድ አምቦ ከተማ ነው፡፡ ትምህርቷን ከፊደል ቆጠራ እስከ ዳዊት መድገም አምቦ በመንፈሳዊ ጉባኤ የቄስ ት/ቤት ፤ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በማዕረገ- ህይወት ቀ/ኃ/ሥ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ፣በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ፣ በተጨማሪም አስመራ ከተማ በሚገኘው ባርካ (ካምበኒ) አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትላለች፡፡
የጋዜጠኝነት መሠረት ከየት መነጨ?
የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ነበር ከአብሮ አደግ እኩዮቿ ጋር በመሆን ከታላላቆቿ ስር ስለማትጠፋ የተማሪዎች መማክርት አባላት እገዛና ድጋፍ ተቋቁሞ በነበረው የሙዚቃና የትያትር ክበብ ሥር እስክስታ ፣ ዳንስ ፣ ተዋናይ ለመሆን ተመዘገበች፡፡ በትያትሩ ዘርፍ ባትዘልቅበትም “ ‹‹ወይ የምድር ሠው” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ትያትር በወቅቱ መድረክ ተዋናይ ሆና ሰርታለች(ተውናለች)፡፡ ይኸው ትያትር ባኮ ከተማ እና ኢጃጂ ከተማ ለዕይታ መብቃቱን ታስታውሳለች፡፡
የጋዜጠኝነት ሙያ እያደገ የመጣው እንዴት ይሆን?
ቤተሰብ የመሰረተችው ገና በአፍላ ዕድሜዋ ቢሆንም ሥራ ይዞ ቤተሰብ የማገዝ ውጥን ነበራት፡፡ አንድ የሥራ ማስታወቂያ ለፖሊስ ሠራዊት ጠቅላይ ሆስፒታል የመዝናኛ ክበብ የሠራተኞች ኃላፊና የሂሳብ ሠራተኛ የሚል ተመለከተች፡፡ ተመዝግባም በውድድሩ በማለፍ ዕድሉን አገኘች፡፡ እዛው እየሠራች ነበር ሀገር አቀፍ የፖሊስ ሠራዊት ስፖርት ውድድር ላይ በምትችላቸው የስፖርት ዓይነት የተመዘገበችው የዱላ ቅብብል ፣ 4×4 (ሪሌ) ሩጫ በገመድ ጉተታ ፣ መረብ ኳስ ተሳትፋለች፡፡ በዚሁ የስፖርት ውድድር ላይ ግጥም ይቀርብ ነበርና የራሷ የሆነውን ግጥም በንባብ አቀረበች፡፡ በዚሁ በፖሊስ ሠራዊት አባልነት ወታደራዊ ሙያ እንድታገኝ ታጨች፤ እርሷም ሳታቅማማ በ1977 ወርሃ ጥር ላይ ኮልፌ 4ተኛ ኮርስ (ቴኳንዶ ኮርስ) ተቀላቀለች፡፡ የውትድርና ሙያ ሥልጠና በመውሰድ ላይ ሳለች ነበር ለፖሊስ ሬድዮ ጋዜጠኝነት ተወዳድራ በድምፅም በፅሁፍም እድሉን ያገኘችው፡፡
ከዚያስ ጋዜጠኝነት ሙያው እንዴት ተጀመረ?
ጊዜው 1978 ወርሃ የካቲት 2 ወታደራዊ ሥልጠናዋን ሳታጠናቅቅ ትመደባለች፡፡ ወደ ተባለው ፖሊስ ሠራዊት ጠቅላይ መምሪያ የሬድዮ ዝግጅት ክፍል ሳይሆን ጉዞ ወደ ኤርትራ ክ/ሃገር ሆነ፡፡ እዛም እንደደረሰች አስመራ ከተማ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ባልደረባ ሆና በአስመራ ቤተመንግስት ለጋዜጠኝነት ሙያ የሚያግዛትን የስልጠና እድል ወሠደች፡፡ ወንጀል ነክ ዜናዎችንም በማጠናቀር ለፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መላክ ጀመረች፡፡
አስመራ ከተማ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ድምፅ ሬድዮ መቼና እንዴት ተቀላቀለች?
ዘመኑ 1980 ዓ.ም ሻዕቢያና ወያኔ ከደርግ ጋር ጦር የሰበቁበት ከአ/አበባ የመንግስት ጋዜጠኞች በተለይ አንጋፋዎቹን ለመቀላቀል ዕድል አገኘች፡፡ አስመራ ከሁለተኛ አብዮታዊ ሠራዊት ፣ ከባህር ኃይልና ከፖሊስ ሠራዊት ጋዜጠኞች ጥሪ ተደርጎላቸው ሊወዳደሩ የማለፍ ዕድሉን ማግኘቷን አጫወተችን፡፡
ከዚያም ጊዜው ጦርነቱ እየተፋፋመ የመጣበት ወቅት ነበርና የጀግናው ሁለተኛ አብዮታዊ ሠራዊት የሚበረታታበት ዝግጅት ማቅረብ ዜና ማንበብ በጊዜው ፕሮግራም ለመምራት ጠንከር ያለ ፅሁፍ ፣ የማጀቢያ ሙዚቃውም የጀግንነት ወኔን የሚቀሰቅስ በመለየት በጥንቃቄ መስራትን የሚጠይቅ እንደነበር ትናገራለች፡፡
በዚህ ወቅት ጌታቸው ኃ/ማርያም
ሙሉጌታ ሉሌ
ሙሉጌታ ዘውዴ
ተክሉ ታቦር
ደራሲና ጋዜጠኛ ኃይሉ ፀጋዬ
ብርሀኑ ሀረገወይን እና ሌሎችም ስማቸው ያልተጠቀሱ ጋዜጠኞች መካከል ሆና መስራቷ ለጋዜጠኝነት መሠረት የጣሉላት ናቸው፡፡ በህይወት ላሉት ሠላም ጤና እረጅም እድሜ ተመኝታ በህይወት ለሌሉት ፈጣሪ በአፀደ ገነት ያኑራቸው ብላለች፡፡
የ1981 የግንቦቱ መፈንቅለ-መንግስት ገጠመኟስ?
ጋዜጠኛ መሆን እውቀትን ፣ ድፍረትን እና ልበ-ሙሉነትን ያላብሳል አለችና የተለመደ ሥራዋን ለማከናወን ዜና ለማደራጀት ወደ ኢትዮጵያ ድምፅ አስመራ ሬድዮ ስቱዲዮ ስትደርስ በሁለተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ- ጦር በታንክ ተከቧል፡፡ ከተማው ፀጥ እረጭ ያለ ነው፡፡ ተጠግታ መታወቂያዋን በማሳየት ተረኛ መሆኗን ስትናገር “የሚያነብልሽ ሠው ስላለ ወደቤትሽ መሄድ ትችያለሽ” በዚያ ምሽት የተሰጣት መልስ ነበር- ምክንያቱ ምን እንደሆነ አልተረዳችም፡፡
ድንገት በሬድዮ ሲተላለፍ የባልደረባዋን ሙሉ ብርሀን ሰይፉን ድምፅ ሰማች ለካስ “የመፈንቅለ-መንግስቱ ሙከራ ነበር” ፡፡ ግንቦት 8/1981 ዕለተ ማክሰኞ ምሽት ላይ በተደጋጋሚ በቀጥታ ሥርጭት መተላለፍ ቀጠለ አይነጋ ነገር የለ ሚሊቴሪዋን ለብሳ ወደ ስቱዲዮ ስትሄድ ምሽት ሲተላለፍ የነበረው በጥቁር ማርከር የተፃፈ የእጅ ፅሁፍ መንግስቱ ኃ/ማርያምን በመግደል የሚለው ሀረግ ተሰርዞ ተመለከተች፡፡ በነገራችን ላይ ይህች ፅሁፍ መፈንቅለ መንግስቱን ያነበበው ፍርድ ቤት ለምስክርነት ይዟት መቅረቡን ጠቆም አረገችን፡፡
መፈንቅለ-መንግስቱ ሲከሽፍ ምን ገጠማት?
ዳኘው አርአያ የተባለ የሬድዮ ጣቢያው ቴክኒሽያን በወታደር ታጅቦ እጁን ወደላይ አድርጎ ሲሄድ ተመለከተች፡፡ ጥቂት እንደተጓዘች እሷም አልቀረላትም ተያዘችና በተጠመደ ጅፕ ላይ ከወታደሮች መሃል ተቀምጣ ወደ ስቱዲዮ ታመራለች ሌሎች ባልደረቦቿ ጎይቶም ቢሆን እና አበበ ዘውዴ ተይዘው መጡ አስመራ የከተሙ ጋዜጠኞችም ከማረፊያቸው ተፈልገው ተገኙ የዚያን ሰዓት የሚያስተባብሩት አንጋፋው ጋዜጠኛ አቶ የወንድወሰን አለሙ ነበሩ፡፡
እርምጃ የተወሰደባቸው ጀነራሎችና ሌሎች መኮንኖችን ዝርዝር የያዙና ከጀግናው ሁለተኛ አብዮታዊ ሠራዊት የተለያዩ የጦር ክፍሎች የተላኩ የደስታ መግለጫዎች ጉረፉ የተያዝነው ጋዜጠኞች በቀጥታ ሥርጭት ከጀርባችን መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች አጅበውን ማንበቡን ቀጠልን፡፡ ከዚያም የኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ንግግር በሪል ቴፕ የተቀረፀውን እያዳመጠች ወደፅሁፍ እንድትቀይር ታዘዘች፡፡ ለሊቱን ሰርታ ከዚያም በስቱዲዮ ጠረጴዛ ላይ አድራለች፡፡ የኮለኔል መንግስቱ ንግግር በጋዜጠኛ ጎይቶም ቢሆን ድምፅ ተላለፈ፡፡ ውሎ አዳራቸውን በስቱዲዮ ያደረጉት ጋዜጠኞች ሥራቸውን አጠናቀው ወደ የመኖሪያቸው ዘለቁ፡፡
ግንቦት ወር 1983 ምን ገጠማት ይሆን?
አሥመራ በሻዕቢያ እጅ ወደቀች ለደስታ የሚተኮሰው አብሪ ጥይት ሠማዩን አድምቆታል፡፡ ለሊቱን የስደት ጉዞ ተጀመረ፡፡ የፖሊስ ባልደረቦቿ ይዘዋት ወጡ፡፡ በእግር እየተጓዘች የ16ኛው ሠንጥቅ ሜካናይዝድ ታንክ ላይ መሣፈር ጥቂት ተጉዛ በእግር መጓዝ ፤ ረሃብ ጥሙ አልበገራትም፡፡ ወገን በየመንገዱ ይረግፋል፤ የETV ባልደረባ የነበረው (ካሜራ ባለሙያ) ዘካሪያ ሴካ አቆርዳት አካባቢ ቁጥቋጦ ስር አሸልቧል፡፡ ሀዘን ቢገጥማትም በጠላት እንዳልማረክ ጥሎ ማለፍ የግድ ነበር አለች፡፡
ሙዱ አሊ ፣ አስፋው ገረመው ፣ በህጉ መሠረት ፣ ብርሀኑ ሀረገወይን (የካሜራ ባለሙያ) ታምራት ሰንበቶ ሌሎችም ጋዜጠኞች በስደት ላይ ተገናኙ፡፡ ስደት ሲባል እንደ ሀገሬ ኢትዮጵያ እንዳይመስላችሁ ሠሃራ በረሃ አሸዋ ላይ ተኝቶ መዋል ማደር ፣ ለመንቀሳቀስ በወታደር መታጀብ ፣ ሕይወትን ለማቆየት ነጭ ሽንኩርት ከማሽላ ንፍሮ ጋር ቀላቅሎ መመገብ ወባን ለመከላከል እርዳታ ሲመጣም የናፈቃትን እንጀራ ከፍርኖ ዱቄት አዘጋጅታ በቆርቆሮ ላይ በመጋገር አጠገቧ የነበሩ ስደተኞችን አቃምሳለች፡፡
እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ሬድዮ ብሄራዊ አገልግሎት ተቀላቀለች?
ጥቅምት 1984 ዓ.ም በፍሪላንስ በሪፖርተርነት ተመደበች፡፡ የደመወዝ መጠን 184 ብር ነበር ወደ መስክ ሲወጣ አበሉ 18 ብር አንጋፋዎቹ ጥሩነህ ማሞና አበራ ማሞ አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና የማያውቃቸው አልነበረም፡፡ የዘፈን ምርጫ ፕሮግራም አዘጋጆች ናቸው፡፡ እሷም በዚህ ዝግጅት አብራቸው መሥራት ጀመረች፡፡ በትምህርታዊ ፕሮግራም ዝግጅት ክፍል ሴቶች ፣ አውደ ገጠር (ግብርና) ፣ ኢኮኖሚያችን ፣ ህግና ህብረተሰብ ፣ ጤናችን ፣ የክልሎች ዜና ወቅታዊ ሪፖርት ፣ የአድማጮች አስተያየት ፣ ከመዝናኛው ወጣቶች ፕሮግራም ላይም ሰርታለች፡፡ አብዛኛው ዝግጅቶቿ ከመስክ ጋር የተገናኘ በመሆኑ ቤተሰቧን ሳታስቀድም ከ20 -25 ቀናት በአርሶአደሩና በአርብቶ አደሩ መንደር ታዘወትራለች፡፡ ዜናም ትዘግባለች፡፡
የመስክ ነገር ከተነሳ አጋጣሚዎቿ በርካታ ናቸው፡፡ መጓጓዣው አውሮፕላን ፣ ላንድሮቨር ፣ አውቶብስ ፣ አይሱዙ ፣ የጋማ ከብት ፣ ታንኳ (አዋሽንና ኦሞን ለመሻገር) የእግር ጉዞም ያጋጥማታል አርሲ ፣ ባሌና ሐረርን የሚያገናኘው መንገድ በንጉሱና በደርግ ዘመን ህዝቡ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቶ ችግሩ ሊፈታ ጊዜው ደረሰና ከኢህአዴግ የፓርላማ አባላት ጋር ክብደቱ ከ20 ኪሎ በላይ የሚመዝን መቅረፀ ድምፅ ተሸክማ ሀገሬው እያገዛት ከETV ጋዜጠኛና የካሜራ ባለሙያዎች ጋር በእግር በመጓዝ የሸንኮራ አገዳ ተንተርሰው ድንኳን ያደሩበትን ታስታውሳለች፡፡
ሲመለሱ በጋማ ከብት የአራት ሰዓት መንገድ ተጉዘው ፍሬያማ ሥራ በመሰራቱ ዛሬ ሀገሬው መንገድ አግኝቷል፡፡ ምርቱን በደጁ ለገበያ ያቀርባል ሕዝብ ማገልገል እንዲህም አይደል፡፡ የኔ ገጠመኝ ማብቂያ የለውም አለችና ምስራቅ ሀረርጌ የጋዜጠኞች ቡድን በደኖ በጋራ ገቡ በወቅቱ የፀጥታ ችግር ነበር ፤ በወረዳው አስተዳዳሪ መኖሪያ ቤት ሁለት ሾፌሮች ተደምረው ዘጠኝ ጋዜጠኞች ሴት እሷ ብቻ ነበረች፡፡ በለበሰችው ልብስ መሬት በኬሻ ላይ ተኝታ አደረች፡፡ ባሌ ጎባ በርበሬ ወረዳም ለጤና ጣቢያ በመገንባት ላይ ያለ ቤት ኩራዝ እያበሩ ማደር ፤ በ1997 ምርጫ ወቅት በደዴሳ ያሳለፈችውን አጫውታናለች፡፡ ጋዜጠኛና ወታደር ተልዕኮው ይገናኛልና እዚህም እዚያም ገጠመኟ ብዙ ነው፡፡ ውጤቱም እንደዚያው ስኬታማ ነበር፡፡
የአድማጮች አስተያየት ፕሮግራም አዘጋጅ ሆና ካዛንቺስ ችሎት ቀርባለች ፤ ከቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ ከ50 በላይ ቤተሰብ በድንገት በግለሰብ ተፈናቅለው ለአየር ከበቃ በኋላ መጉላላት ቢደርስባትም እውነትን ይዛ በመዘገብዋ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት አግዘዋት ቅሬታ አቅራቢዎቹን ከመበተን ታድጋለች፡፡ በበዓል ከቤተሰብ ተለይቶ ያውም ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ህፃናትን ትቶ መዋል ፤ ከስቱዲዮ ወጥቶ መውለድ ፣ የአምስት ወር አራስ ልጅ ጥላ ጡቷ እየፈሰሰ ከከረዩና ከአፋር አርብቶ አደሮች መንደር ውላ አድራ ስትሰራ አንድ የግብርና ሚኒስቴር የካሜራ ባለሙያ የማትታለብ ላም ነው እንዴ ያመጣነው ?ያለውን አጋርታናለች፡፡
የማህበራዊ ኑሮ በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት
የሠራተኛውን እድር በፀሐፊነት በማናቸውም ዝግጅቶች የኮሚቴ አባል በመሆን አገልግላለች፡፡ በተለይ አለም አቀፍ ሬድዮ ጣቢያ (ዘነበወርቅ) በመባል በሚጠራው በዘመናዊ የንብ ቀፎ ንብ በባለሞያ በማነብ የተገኘውን ምርት ተጣርቶ ለጋዜጠኞችና ለሌሎችም ሠራተኞች ማከፋፈል ያስደስታት ነበር፡፡ ዋልታና ሚዲያ በሚል በተመሰረተ የቤት ሥራ ማህበር በኮሚቴነት በማገልገል የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች፡፡ በርካታ ጋዜጠኞች ለተሰባሰቡበት መንደር መሰረት ጥላለች፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን አንድ ላይ ሲዋሃዱ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ማለቷና አሁን በመተላለፍ ላይ በሚገኘው “ጤናዎ በቤትዎ” ፕሮግራም በአዘጋጅነት ተሳትፋለች፡፡ በመጨረሻ የመስክ ጉዞ ያደረገችው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከተንቤን እስከ ሁመራ የወባ በሽታ ያለበትን ደረጃ ዘግባለች፡፡
የምትወደውን የጋዜጠኝነት ሙያ እንዴት አቋረጠች?
የጋዜጠኝነት ሙያ ሚሊዮኖችን ማገልገል ቢሆንም ወርሃ ታህሳስ 2001 በመንግስት መልካም ፈቃድ ቂርቆስ ክ/ከተማ በሴቶችና ህፃናት አማካሪነት ፣ በልደታ ክ/ከተማ የህዝብ አቤቱታና ቅሬታ ማስተናገጃ የሥራ ሂደት ተመድባ ስታገለግል ቆይታለች፡፡ በአመራርነት ከ8 ኣመት በላይ ሠርታለች፡፡
የሹመት ጊዜዋን በቅንነት በታማኝነት ስታጠናቅቅ ወደ ኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን እንደምትመለስ የሚገልጽ የፅሁፍ ደብዳቤ ብትይዝም ያለሙያቸው ወንበር ላይ በተቀመጡ ግለሰቦች ምክንያት ከ20 ዓመት በላይ የቆየችበትን የጋዜጠኝነት ሙያ እንድታቋርጥ እንቅፋት እንደሆኑባት ትገልፃለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በልደታ ክ/ከተማ በመሬት ልማት ማኔጅመንት በፈጻሚ ሠራተኝነት በማገልገል ላይ ነች፡፡
ምስጋና የምትቸራቸው
ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ እድሜና ጤና አብዝቶ ለሰጣት ለልዑል እግዚአብሄርና ለድንግል ማርያም ፣ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለቀድሞ ባልደረቦቿ ጋዜጠኞችና ቴክኒሽያኖች፣ በሹመት በሠራችባቸው የቂርቆስና የልደታ ክ/ከተሞች ለሚገኙ ማህበረሰቦች፤ ባለቤቷ በሞት ቢለያትም በብቸኝነት ላሳደገቻቸው የአብራኳ ክፋዮች ሶስት ወንዶች ልጆቿና ለሥራ በየክልሉ መስክ ስትሠማራ እንደ እናትና አባት ሆና የቤቱን ኃላፊነት በመውሰድ እገዛ ላደረገችላት ለሴት ልጇ ትልቅ ክብር አላት፡፡
በመጨረሻ የኔ ሀብቴም ዕውቀቴም ሁለመናዬ ናቸው የምትለው አራት ልጆቿንና ስምንት የልጅ ልጆቿ ታሪኳን ሰንደው እንደሚያቆዩላት ተስፋ አለኝ ብላለች፡፡ ግለ-ታሪኳን እንድታካፍል ለረዳት ለጋዜጠኛ ብርሃኑ ገ/ማርያምና ለናንተም ለአዘጋጆቹ የሀገሯን ክልሎች ከጋምቤላ በስተቀር አዳርሳለች፡፡ በየትኛውም ሥፍራ እገዛ ያደረጉላትን ሁሉ በዚህ አጋጣሚ አመስግናለች፡፡