አለማየሁ ገበየሁ አስፋው

አለማየሁ ገበየሁ አስፋው

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፣ በማስታወቂያ ዘርፍ ፣ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፣ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸውን ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡

በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ አሁን በድርሰትና ወጎችና ስነ-ጽሁፍ ዘርፍ ታሪኩ የሚሰነደው አለማየሁ ገበየሁ አስፋው ይሆናል፡፡

እድገትና ትምህርት

አለማየሁ ገበየሁ የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ ባልቻ ሰፈር ሲሆን እድገቱ ሰላም ሰፈር / ልደታ ክፍለከተማ ቀበሌ 02/03 / ነው ። ለአቶ ገበየሁ አስፋውና ለወ/ሮ የብርጓል ዘውዴ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን አንድ ወንድምና ሶስት እህቶችም አሉት ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቀራንዮ መድሃኒያለም ፣ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ  በባልቻ አባነፍሶ የ2ኛ ደረጃን ደግሞ በአየር ጤና ተከታትሏል ። በ1994 ዓም በ ቋንቋና ስነጽሁፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ አግኝቷል ። 

የማለዳ ተሳትፎ

አለማየሁ ንባብና ግጥም የጀመረው በወጣትነቱ ነው ። በደራሲ ሃይለመኮት መዋእል በሚመራው ‹ ‹‹እንቡጥ›› የስነጽሁፍ ክበብ  ውስጥ የአባላቱን ስራ በማድመጥና በመተቸት እንዲሁም  የራሱን ሙከራዎች በማንበብና ትችትን በመቀበል ስነ-ጽሁፋዊ ትውውቅን ማዳበር ችሏል ። ስነጽሁፋዊው ውይይት የተጀመረው ደራሲ ሃይለመለኮት በሚያስተምሩበት መሰረተ እድገት ትምህርት ቤት ቢሆንም ብዙ ርቆ መጓዝ የቻለ አልነበረም ። ከአያሌ አመታት ቆይታ በኋላ ደግሞ አለማየሁን ጨምሮ ስድስት ጸሐፊያን በደራሲ ሃይለመለኮት ቤት እየተገናኙ በጠንካራ ስራዎችና ሀሳቦች ላይ ይወያዩ ነበር ። በዚህ አፍላ ወቅት ኩራዝና ኢትዮጽያ መጽሐፍት ድርጅት የሚያሳትሟቸውን ግጥሞችና አጫጭር ልቦለዶች እያሳደደ ያነብ እንደነበር ያስታውሳል ። 

የጋዜጠኝነት ህይወት

አለማየሁ ወደ ጋዜጠኝነቱ የስራ አለም  የተቀላቀለው ባላሰበው መንገድ ነበር ። ከንባብ ጋር የቀደመና በእጅጉ የጠበቀ ግንኙነት ስለነበረው የሚታዘባቸውንና እንዲህ ቢሆኑ ጥሩ ነበር የሚላቸውን መጣጥፎችና ሀሳቦች በአምስት አቅጣጫ ይልካቸው ነበር ። ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፣ ለዛሬይቱ ኢትዮጽያ ፣ ለብስራተ ወንጌል የአማርኛው ድምጽ ፣ ለለገዳዲ  እንዲሁም ለኢትዮጽያ ሬዲዮ አድማጮች አስተያየት ፕሮግራም ።

ብስራተ ወንጌል በአዘጋጆቹም ሆነ በራሱ ድምጽ የሚያነበው ግጥሞቹን ነበር ። ለገዳዲ ላይ አጫጭር ልቦለዶች ሲሆኑ በጊዜው ብቸኛ ለነበሩት ትላልቅ ጋዜጦች ለአዲስ ዘመንና የዛሬይቱ አትዮጽያ ደግሞ ማህበራዊና ጥበባዊ አስተያየቶችን ነበር ።

በተለይም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጠንካራ ተሳትፎ ስለነበረው አንድ ቀን ዋና አዘጋጁ ደምሴ ጽጌ « ከእኛ ጋ በፍሪላንስ ጋዜጠኝነት እንድትሰራ እንፈልጋለን » የሚል አስተያየት አቀረበለት ። የሚጽፈው ስሜቱን ለመግለጽና ለርካታ እንጂ ስራ ያስገኝልኛል ብሎ ስላልነበረ ጥያቄውን እየገረመው ነበር የተቀበለው ። በአንጋፋ ጋዜጠኞች / መስፍን ሀብተማርያም ፣ የሺጥላ ኮኮብ ፣ ሐዲስ እንግዳ ፤ ጸጋዬ ሃይሉ ፤ ደምሴ ጽጌ ና በሌሎች / የተዘጋጀውን የአርባ ቀናት መሰረታዊ የጋዜጠኝነት ሙያና የአርቲክል አጻጻፍ ስልጠና ተቀብሎ በሪፓርተርነት መደብ ስራ  ጀመረ ። ይህ የሆነው በ 1986 ዓም ነበር ።

በነገራችን ላይ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተቀጥሮ የሰራው በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ነው ። የመጀመሪያው ድርጅቱ  ጥሩ ጸህፊ ስለሆንክ እፈልግሃለሁ ብሎ የጠራው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አለማየሁ ራሱ አዲስ ዘመንን በከፍተኛ የስራ መደብ እቀላቀላለሁ ብሎ በ1995 ዓም መቀጠሩ ነው ። ልዩነቱ ሁለተኛው ቅጥር የአዘጋጅነት ቦታ መሆኑና ከበርካታ ተወዳዳሪዎች ጋር ሰላማዊ ፍልሚያ ስለነበረው ነው ። በመጀመሪያው የሪፖርተርነት ቅጥር ከእለታዊ ዜና በተጨማሪ ‹ መዲናችን › የተሰኘ ገጽ ያዘጋጅ ነበር ። በሁለተኛው የአዘጋጅነት ቅጥር ‹ ማህደረ ህግ › የተባለውን አምድ ከማዘጋጀት በተጨማሪ ጥበብና ባህልን  ጨምሮ ሌሎች አምዶችን አርትኦት የማድረግ ሃላፊነት ነበረበት ። ‹ አጀንዳ › በተባለው ወቅታዊ አምድ ላይም የሚያቀርባቸው ትኩረት ሳቢና ተነባቢ መጣጥፎች በኢትዮጽያ ሬዲዮ እየተጠቀሱ ይነበቡለት ነበር ።

አለማየሁ በበርካታ መንግስታዊና የግል ጋዜጦች ተቀጥሮ በመስራት ንቁ ተሳትፎ አበርክቷል ። ለአብነት ያህል ከ 1999 እስከ 2002 በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን / አዲስ ልሳንና ኤፍ ኤም 96.3 / ላይ በዋና አዘጋጅነትና በሃላፊነት ደረጃ ሰርቷል ። በግሉ ዘርፍ ደረጃ በ1992 በእለታዊ አዲስ ጋዜጣ የማህበራዊ አምድ አዘጋጅ በመሆን የሰራ ሲሆን በ1994 ዘ ፕሬስ የተባለ ጋዜጣን በከፍተኛ አዘጋጅነት በመቀላቀል ‹ ከአለማችን › የተሰኘ አምድ አዘጋጅቷል ።

ሙያውን በእውቀት ለማገልገል ጥሩ የዜና አድማጭነት ፣ ንባብና ነባራዊውን ሁኔታ ከመጪው እውነት ጋር አዛምዶ የመተንተን ክህሎት ያስፈልጋል የሚለው አለማየሁ አንጋፋዎቹን መስማትና በእነሱም መሰልጠን ስል እንደሚያደርግ ያምናል ። በዚህ ረገድ የትየለሌ ስልጠናዎችን ቢወስድም በተለይም በአሜሪካ መረጃ ማእከል / United states information service / ለአራት ግዜ ያህል የወሰዳቸው ስልጠናዎች / Basic journalism training , Journalism and the law , Investigative Journalism and the law እና Writing for the mass media / አይን ከፋቾች እንደነበሩ ያስታውሳል ።

አለማየሁ በ ኤፍኤም 96.3 ሬዲዮ ላይ በሃላፊነት መስራት ከጀመረ በኋላ ሬዲዮው እንዲነቃቃና የተደማጭነቱ አቅም በተቻለ መጠን ከፍ እንዲል የሚያደርጉ ስራዎች ተሰርተዋል ። በዋናነት የሬዲዮው ፕሮግራሞች ለምን አላማ እና በምን መልኩ መሰራት እንደሚኖርባቸው የሚገልጽ የአሰራር ብልሃትና አቅጣጫ አልነበረውም ። በመሆኑም ‹ የፕሮግራሞች ይዘት አሰራር ማንዋል › አጥንቶ በመቅረጽ ስራ ላይ እንዲውል አድርጓል ። በሬዲዮው ጋዜጠኞች ትክሻ ላይ የወደቁትን ፕሮግራሞች ለውጭ ተባባሪ አካላትም ማጋራት ያስፈልጋል በሚል ከበላይ አለቆቹ ጋር በመተባበር በጣቢያው የአውትሶርስ/አየር ሰአት ወስደው የሚሰሩ/ ስራዎች እንዲበራከቱ ትልቁን ሚና ተጫውቷል ። 

በከተማው አስተዳዳሪዎችም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን የበላይ ሃላፊዎች ትኩረት የተነፈገው የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ይዘት ለማሻሻል በቅድሚያ ችግሮችን አጥንቶ መለየት ያስፈልጋል በሚል ‹ የጋዜጠኞች ፎረም  እንዲቋቋም አድርጓል ። ሁሉም ጋዜጠኛ በየተራ ርእስ ወስዶ ጥናት እንዲያቀርብ ይደረጋል ። በቀረበው ጥናት ላይ ሞቅ ያለ ውይይትና ክርክር ይደረጋል ። በፎረሙ ጋዜጠኞች ችግሮቹን ነቅሰው በማውጣት የመፍትሄ ሀሳቦችን ይወረውራሉ ። በመጨረሻም ጥናቱ እንዲጸድቅና እንዲሰነድ ይደረጋል ። በዚህ መልኩ በርካታ ጥናቶች ተከውነዋል ።  

በ1994 ዓም የኢትዮጽያ ስነጥበባትና መገናኛ ብዙሃን ሽልማት ድርጅት አገር አቀፍ ፕሮግራም ማከናወኑ ይታወቃል ። አለማየሁ የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉን ሊዳኙ ከተመረጡ አምስት ጋዜጠኞች አንዱ ነበር ። ሀገሪቱ ካላት ጋዜጠኞች ጥቂት ምርጦችን ለሽልማት ፈልፍሎ ለማውጣት በርካታ ጥናት ፣ ምርምርና ልፋት የሚጠይቅ ነበር ። ለበርካታ ወራት በተደረገው ልፋት ውድድሩ መቋጫ ቢያገኝም ዳኞች ለሽልማት ያቀረቧችው ጋዜጠኞች በሽልማቱ ቀን ተሰርዘው ሌሎች ክብሩን እንዲወስዱ በመደረጉ ሁሌም ያፍርበታል ። የዳኝነት ጉዳይ ከተነሳ ለሚሊኒየም በአል በተዘጋጀ የስነ-ጽሑፍ ውድድር በደራሲያን ማህበር ታጭቶ መዳኘቱንና ሽልማት ማግኘቱን ያስታውሳል ።

በ2005 ዓም አይሲኤፍጂ የተባለው ዝነኛ የጋዜጠኞች ተቋም ጋዜጣ ላይ የታተሙ ምርጥ ‹ የክትባት ታሪኮች ›ን ያወዳድር ነበር ። አለማየሁ ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ « የተሰቀለው ሪፖርትና የተደፈጠጠው እውነት » በሚል ርእስ ያሳተመውን ግሩም መጣጥፍ አቅርቦ ማሸነፍ ችሏል ።

ሙያዊ መጽሐፍ

የሀገራችን የጋዜጠኝነት ሙያ ከ 130 ዓመታት በላይ የዘለቀ ቢሆንም ሙያው ላይ ተመስርተው የተጻፉ የአማርኛ መጽሐፍት ከስድስት አይበልጡም ። ይህ ጉዳይ ያሳሰበው አለማየሁ ከ 14 አመታት የጋዜጠኝነት ቆይታ በኋላ አንድ በይዘቱ ለየት ያለ መጽሐፍ ማበርከት እንዳለበት አሰበ ። ቀድሞ የተሰነዱት መጽሐፍት በአብዛኛው  ዜና ፣ ዜና ትንታኔ ፣ ፊቸር ፣ ቃለምልልስ እና የልማት ጋዜጠኝነት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው ። በመሆኑም የጦር ዘገባ  ፣ የሰላም ጋዜጠኝነት ፣ ሚዲያና የፕሮፓጋንዳ ዝምድና ፣ የምርጫ አዘጋገብና ሌሎችንም ትኩረት ያላገኙ ርእሰ- ጉዳዮችን በጥልቀት መርምሮና ፈትሾ « የጋዜጠኝነት ፈታኝ አጀንዳዎች » በሚል ርእስ ደጎስ ያለ መጽሐፍ  በ2003 ዓም ለንባብ አብቅቷል ። ይህም ዘርፉን ለሚቀላቀሉ ሙያተኞች ትልቅ ግብዓት ይፈጥራል ።

ስነ-ጽሁፋዊ ህትመቶች

አለማየሁ በአጠቃላይ አምስት መጽሐፍትን ለንባብ አብቅቷል ። ከአንባቢ ጋር የተዋወቀበት የመጀመሪያው የግጥምና የአጭር ልቦለድ መጽሀፍ « ያላወቅኳት ቆንጆ » ትሰኛለች ። የ 36 ግጥሞችና የ 6 አጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ናት ። እሱ ድንቅ የሚለው ሁለተኛ ስራው « የአበሻ ፊት » የሚሰኝ ሲሆን የምናባዊ ወጎችና የአጫጭር ልቦለዶችን ታሪክ አሰባስቦ በ 1998 ዓም ለብርሃን የበቃ ነው ።

የዚህ መጽሀፍ የተወሰኑ ወጎችና ታሪኮች በሸገር ሬድዮ ለመተረክ በቅተዋል፡፡ ሶስተኛው ስራው « የጋዜጠኝነት ፈታኝ አጀንዳዎች » ሲሆን ለህትመት የበቃው በ 2003 ዓም ነው ። « ወንዶች ለምን ይዋሻሉ ሴቶች ለምን ያለቅሳሉ ?» የተሰኘው ስነ ልቦና ላይ  መሰረት ያደረገ የትርጉም ስራው ደግሞ በ 2006 ዓም የታተመ ሲሆን አራተኛ መጽሐፍ ሆኖ ተመዝግቦለታል ። በ 2007 ዓም « የረከሰ ፍርድ በኢትዮጽያ » የሚል የወግ ስራው በሊትማን አሳታሚ ድርጅት በኩል ታትሞለታል ።

አለማየሁና የአሊጎሪ አጻዳፍ ስልት

በ « አበሻ ፊት » መጽሐፍ ውስጥ የቀረበው « አስችኳይ ጉባኤ » የተሰኘ አጭር ልቦለድ በዩኒቨርስቲ የስነጽሑፍ መምህራንና ተማሪዎች ዘንድ መወያያና ማጣቀሻ ነው ። ታዋቂው የስነጽሑፍ መምህር ረዳት ፐሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በሚሰጡት የስነ-ጹሑፍ ስልጠና ላይ የአበሻ ፊቱን ‹ አስችኳይ ጉባኤ › በአስረጅነት ሲጠቅሱ ደራሲው ራሱ ሰምቷል ። የኢትዮጽያ ደራሲያን ማህበር ባሳተመው የደራሲያን አጀንዳ ላይም የአበሻ ፊት በምርጥ መጽሐፍነቱ ጠቅሶ አትሞታል ። የስነጽሑፍ ተማሪዎች ለጥናት መዘውታል ።

ለምሳሌ ያህል ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያውን የሰራው ‹ አሊጎሪ በአማርኛ ዘመናዊ አጫጭር ልቦለዶች › በሚል ርእስ ነው ። ለዚህ ስራው የመረጣቸው ደራሲዎች ደግሞ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ፣ አዳም ረታ ፣ ሚካአኤል ሽፈራው ፣ አሳምነው ባረጋ እና አለማየሁ ገበየሁ ናቸው ። እንዳለጌታ ከበደ የአለማየሁ ገበየሁን ‹ አስቸኳይ ጉባኤ › የተባለውን አጭር ልቦለድ ከአሊጎሪ ስነጽሑፍ ብልሃት አንጻር በሚጥምና በሚያስደምም መልኩ ተንትኖ በፋክት መጽሄት ቁጥር 14 ላይም በድጋሚ አቅርቦታል ።

በሀገራችን የአሊጎሪ አጻጻፍ ይትበሃልን እንደ ቋሚ መለያ እያቀረበ የሚገኘውም ደራሲ አለማየሁ ገበየሁ ነው ። በ 2007 ዓም የረከሰ ፍርድ በኢትዮጽያ በሚል ርእስ በቀረበው የወግ ስራው ላይ አንድ ብችኛ ልቦለድ አለ ። ‹ አንሳርማ › የሚል ። ይህ ልቦለድ ብዙ ያልተባለለት ድንቅ የአሊጎሪ ስራ ውጤት ነው ። ድንገት ሀገሪቱን የማስተዳደር ሃላፊነት በእጃቸው የወደቀባቸው ‹አሳማዎች › የተቀሩት እንስሣት ድብቅ አላማቸውን ሳይቃወሟቸው ባንዲራ ፣ ብሄራዊ መዝሙር እና የሀገሪቱን ስያሜ  ለመቀየር በብልጠት ቢተጉም ያልጠበቁት መራራ ትግል ይገጥማቸዋል ። ለምሳሌ ያህል የከተማችንን ስያሜ ‹ አንሳርማ › ያልነው ‹ አን › – አንድነትን ፣ ‹ ሳር › – ምግባችንን ‹ ማ › ደግሞ ማህተማችንን እንዲወክሉ ነው ቢሉም እንደ ፍየል ባሉ አርቆ አሳቢዎች ድብቅ አላማቸው ሲጋለጥ እናያለን ። ፍየል አንድነት ፣ ሳር እና ማህተም የሚሉ ቃላትን ቁልቁል አሰልፈን የመጀመሪያ ፊደላቱን ብናነብ « አሳማ » የሚል ቃል እናገኛለን በማለት ሀገሪቷን የአንድ ጨቋኝ እንስሳ ፍላጎት ማራመጃ ለማድረግ የተወጠነውን ሴራ አክሽፋለች – የጨካኞች ካራ ሰለባ ብትሆንም ። በመጨረሻም ሲወጋገዱ የምናያቸው ሶስት ግዙፍ አሳማዎች / ራዞር ፣ ብሌስ እና ቡፋሎ /የኢሃዴግን ሶስት ቁልፍ ሰዎችን የሚወክሉ ናቸው ። በቅርቡ ለህትመት በሚበቃው የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ውስጥም « የቀዌ ሃሳብ » በሚል ርእስ የሜዳ አህዮች ህይወትና ትግልን የሚተርክ አሊጎራዊ ስራ ቀርቧል ።

አምደኝነትና ብሎገር

የአለማየሁ ገበየሁ መጣጥፎች ሳቢና አስተማሪ በመሆናቸው አሳታሚዎች አብሯቸው እንዲሰራ ይጋብዙታል ። በዚህ ረገድ በቁም ነገር መጽሄት ላይ በቋሚ አምደኝነት ተሳትፏል ። በትላልቅ ጸሀፊዎች በሚታውቀው ታዛ መጽሄትም ቋሚ አምደኛ በመሆን ስራውን እያበረከተ ነው ። 

አለማየሁ በ2004 ዓም የአሌክሶ ገጽ / alexopage.blogspot.com / የሚል ብሎግ በመክፈት ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ስነጥበባዊ መጣጥፎችን ለተከታዮቹ እያቀረበ ነው ። እስካሁንም ከ 112 በላይ መጣጥፎች ተስተናግደውበታል ። የሰሉ የመጽሃፍት ሂሶችና ፖለቲካዊ እይታዎች  የብሎገሩ ልዩ መለያዎች ናቸው ። ሀገር ውስጥ የሚታተሙ መጽሄቶችም ብሎጉን በመጥቀስ ጽሑፎቹን በስፋት ይጠቀሙባቸዋል ።

የቤተሰብ ሁኔታ

ከወ/ሮ ሃይማኖት ቢሆነኝ ጋር ትዳር መስርቶ የሚኖረው አለማየሁ የሁለት ወንዶችና የአንዲት ሴት ልጆች አባት ነው ። በአሁኑ ወቅት የኑሮውን መሰረትበሀገረ እንግሊዝ  አድርጓል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *