ንጉስ ወዳጅነው ማሙዬ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በቅርቡ ደረጃውን የጠበቀ ለቤተ-መጽሀፍቶች አገልግሎት የሚውል በጠንካራ ሽፋን የተጠረዘ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ አሳትሞ ያቀርባል፡፡ እስካሁን በዚህ ገጽ ያወጣናቸውን በጥራዝ መልክ አድርገን ለታሪክ የምናስቀምጥ ሲሆን ታሪካቸው በዚህ መልክ በክብር ከሚሰነድላቸው አንዱ ንጉስ ወዳጅነው ይሆናል፡፡ ንጉስ ወዳጅነው አዲስ ዘመን ጋዜጣን በዋና አዘጋጅነት የመራ ነው፡፡ እስከዛሬ ስለጉዳዮች ወይም በመሪነት ሲሰራ ቆይቶ እንደሆነ እንጂ ንጉስ ማነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ አልነበረም፡፡ አሁን ግን መልስ አለ፡፡
ንጉስ ማነው?
ባለፉት 19 አመታት ውስጥ አዲስ ዘመን ፣ሪፖርተር ፣ በኩር፣ አዲስ ልሳን ፣አዲስ አድማስ፣ ሪፖርተርና ለአጭር ጊዜ በቆየችው ዲያጉ ጋዜጣ ፣ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በድሬቲዩብ በርካታ መጣጥፎችን ለንባብ አብቅቷል ፡፡ ከራሱ ስም ባሻገር፣ በተለያዩ የብእር ስሞች የሚያቀርባቸው ፅሁፎቹ የፖለቲካና ኢኮኖሚ አስተያያት ፣ የማህበራዊ ሂስና መፃሃፍት ዳሰሳ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው ፡፡ የፓርላማ ዘገባና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ምሁራን ቃለምልልሶች፣ እለታዊ ዜናዎችንና ትንታኔዎችንም ሲሰራ ነው የቆየው ፡፡
ንጉሥ በሙሉ ጋዜጠኝነት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልን የተቀላቀለው 1998 ዓ.ም መስከረም ላይ ነበር ፡፡ በዚሁ ክፍል ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ለ9 አመታት ሰርቷል፡፡ እነበአሉ ግርማ ፣ ብርሀኑ ዘሪሁን ፣ ጳወሎስ ኞኞ፣ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄርና ሌሎችም … የነበሩበትን አንጋፋ ጋዜጣ ሲቀላቀል ደስታው ከፍ ያለ እንደሆነ የሚያስታውሱ አሉ ፡፡
ያምሆኖ ፈጥነው ወደስራው ከገቡ ጀማሪዎች አንዱ ሆነ ፡፡ ለዚህም ቀደም ባሉት አመታት ያካበታቸው ልምዶች ፣ የማንበብ ፍላጎቱና የመፃፍ ጥረቱ ፣ እንዲሁም በቄስ ትምሀርት ቤት ማለፉ አግዞታል ፡፡ በሂደትም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመጀመሪያው የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ዘጋቢ (ቢት ሪፖርተር)ና የፖለቲካ አርታኢ መሆን የቻለ ሲሆን ፣ በኋላም ለአምስት አመታት ገደማ ለጋዜጣው በዋና አዘጋጅነት አገልግሏል ፡፡ በጠንካራ የፅሁፍ ዝግጅት ልምዱ እየተመረጠም የመጀመሪያው የብሄር ብሄረሰቦች መፅሄት ዝግጅት (2000ዓ . ም) የፅሁፍ አዘጋጅ ኮሜቴ አባል፣ በዋፋ ማርኬቲንግ የሚዘጋጁ ሶስት መፅሄቶችንም በዋና አዘጋጅነት አሰናድቷል ፡፡
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት
ንጉሥ ወዳጅነው ከጥር 2005 እስከ ሀምሌ 30 ፣ 2009 አዲስ ዘመን ጋዜጣን በዋና አዘጋጅነት መርቷል ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በዝግጅት ክፍሉ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ሞክሯል ፡፡ ቀዳሚው ፈፃሚዎችን በቡድን ከፋፍሎ አንድ አንድ ቀን በመስጠት በእቅድና በትንታኔ ወደ መስራት የተገባባት ነው ፡፡ ሌላኛው የ“ኦፔድ“ ገፅን ጠንከር ባሉ ሂሶችና ገንቢ አመላካቾች ለማጉላትም ሞክሯል ፡፡ በጋዜጣው ቅርፅና ከለር በኩል ለመጡ መሻሻሎች ከባልደረቦቹ ጋር ሆኖ ብዙ ጥረት አድርጎል፡፡
ንጉሥ ለጋዜጠኞችና ለምክትል አዘጋጆች ሙሉ ሃላፊነት በመስጠት፣ በፍትሃዊነት በማሰማራት ፣ሰራተኞችን በቅንነት በመደገፍና ነፃ በማድረግ ይታወቃል ፡፡ ያም ሆኖ በወቅቱ ዋና አዘጋጁ (ማኔጂንግ ኤዲተር የሌለው ጋዜጣ ስለነበር ) የሙያውን ስራ ብቻ ሳይሆን ፣ የአስተዳዳርና የሎጂስቲክ ጉዳይ ሁሉ የወደቀበት ስለነበር የስሜቱን ያህል ለመፃፍ እድል አላገኘም ነበር ፡፡ ለዚህም ነው በራሱ ፍቃድ ስራዉን ለቆ ወደግል ስራ ቢገባም ፣ በተነሳሽነቱ በአራት አመታት ብቻ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ከ312 በላይ አርቲክሎችን ማቅረብ የቻለው ፡፡ ይህ እንግዲህ በግል ፌስቡክ ገፁ ከሚከትባቸው አጫጭር ማስታወሻዎች ሌላ ነው፡፡
አዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን
በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ተጨማሪ ዘውግ ላይ ለመስራት እድል የተፈጠረለት ንጉሥ ፣ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ 2001ዓ. አጋማሽ ላይ ወደአዲስ አባባ አስተዳዳር መገናኛ ብዙሃን አጄንሲ በመዘዋዋር የETV2 አርታኢና አስተባባሪ ሆኖ ተመድቧል ፡፡ በዚህ መደብ ለአንድ አመት ከመንፈቅ በተሻለ ትጋት ካገለገለ በኋላ፣ በኤጀንሲው ስር የሚተዳደሩትን ኤፍ.ኤም ሬዲዮ 96.3ና አዲስ ልሰን ጋዜጣን ጨምሮ የሁሉንም የይዘት ስራዎች በስራ ሂደት መሪነት ለአንድ አመት መርቷል ፡፡
በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በነበረው ቆይታ ልዩ ልዩ የቴሌቭዥንና የሬዲዩ ፕሮግራሞችን ፎርማት በማዘጋጀት፣ መመሪያዎችና ማንዋሎችን በማሰናዳት ብቻ ሳይሆን “ መስኮት“ የተሰኘው ተወዳጅ የቲቪ ድራማ ከገጠመው መቀዛቀዝ ተላቆ ፣ በታዋቂ አርቲስቶች ተጠናክሮ እየተዘጋጀ እንዲተላላፍ አድርጎል ፡፡በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ተመድቦ አገሩንም አገልግሏል ፡፡
በኋላ ከሚዲያ ስራ ጋር በተገናኛ ፣ በአዲስ አባባ ደረጃ የሴክተር መስሪያ ቤቶችን መረጃ አሰጣጥና አደረጃጃት በማስተካካል አዋጅ 590 /2000ን ለማስተግበር የመንግስት መረጃ አቅርቦት ፅህፈት ቤት ተቋቁሞ ነበር ፡፡ ለዚህ ስራ ከተመደቡት ጠንካራ ባለሙያዎች አንዱ ደግሞ ንጉሥ ሲሆን በምክትል ስራ አስኪያጅነት ፅህፈት ቤቱን መርቷል ፡፡
በዚህ ጊዜም 36 የአስተዳዳሩ መስሪያ ቤቶች ራሳቸው ድረገፅና ፖርታል እንዲኖራቸው ፣ብዙዎቹ መስሪያ ቤቶች የመረጃ ዴስክ እንዲያደራጁ የተደረገ ሲሆን 400 ገፅ ያለው ከተማ አቀፍ የአገልግሎት አሰጣጥ መድብል ( ዳይሬክተር ) እንዲታተም ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ስራ እንደተጠናቀቀም መልሶ ወደ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ነበር የተመለሰው ፡፡
መምህርነትና ህዝብ ግንኙነት
ንጉስ ጎበዝ የቋንቋ መምህርም ነበር፡፡ ስራ የጀመረው ገና በለጋነት እድሜው በ1994 ሲሆን ፤ ደቡብ ወሎ ዞን ፣ቦረና ወረዳ መካነሰላም ( ዋለልኝ መኮንን) ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር ፡፡ በዚያም ከማስተማር ስራ ባሻገር ፣ የፀረ ኤች አይ..ቪ ኤድስና ሚኒሚዲያ ክበባትን በማጠናከር በዞን ደረጃ ተሸላሚ የነበረ ሲሆን ፣ ተወዳጅ ከነበሩት መምህራን አንዱ እንደሆነ ነው የያኔ ተማሪዎቹ የሚናገሩት ፡፡
በዚህ መልካም ጅምሩ ለሁለት አመት ከሰራበት የመምህርነት ሙያ ወደ ወረዳው ማስታወቂያና ህዝብ ግንኙነት ፅህፈት ቤት ተዘዋውሯል ፡፡ በወቅቱ ክልሉ የወረዳዎችን ሴክተር መስሪያ ቤቶች በሰው ሃይል ያጠናክር ስለነበር ፣ ንጉስ በጋዜጠኝነት፣ በቪዲዮና ፎቶ ካሜራ ሙያዎች አጫጭር ስልጠናዎችን ለማግኘትና በተግባር ለማሳየት ችሏል ፡፡ በደብረሲና ወረዳ ህዝብ ግንኙነት ኤክስፐርት ሙያ በቆየባቸው ሁለት አመታት ፣ እንደወረዳ ክበባትንና የወጣት አንባቢዎች ንቅናቄን ከመጀመር አንስቶ፣ “ልሳነ ደብረሲና“ የተሰኘች የህትመት ቡክሌት በየወሩ እየታተመች ለአንባቢ እንድትደርስ ሲያደርግ ነበር ፡፡
እንዲሁም በአካባቢው ያለውን ” የደንቆሮ ጫካ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን” ከክልሉ ማስታወቂያ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ፣ ወደፓርክነት ለማሳደግ የሚረዱ የማስተዋወቅ ስራዎች በህትመትና በቲቪ ዶክመንተሪ አዘጋጅቷል ፡፡ ሙከራው ውጤት አምጥቶም ጥብቅ ደኑ ከአመታት በኋላ ዛሬ ወደ ፓርክነት አድጎል ፡፡
የውጭ አገር ተሞክሮ
ንጉሥ ለአጫጭር ጉብኝት ፣ስልጠናና የዘገባ ስራ ወደተለያዩ አገሮች የመጓዝ እድል ገጥሞታል ፡፡ እንደ ቻይና ፣ግብፅ ፣ደቡብ አፍሪካ ፣ ደቡብ ኮሪያ ፣ ጅቡቲ.. ያሉትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል ፡፡ በእነዚህ አገሮችም በርካታ ልምዶችና የታዋቂ ሰዎችን ተሞክሮ ለመቅሰም የቻለ ሲሆን፣ ያገኛቸውን ልምዶችና የጉዞ ማስታወሻዎች በተለይ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በማቅረብ ለአንባቢ አካፍሏል ፡፡
ውልደትና አስተዳዳግ
የዩኒቨርስቲ ትምህርት ቆይታ
ንጉስ የአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ሶሻል ሳይንስ ካምፓስ (6ኪሎን) የረገጠው መስከረም 1989 ዓ.ም ነበር፡፡ በዚያም በቋንቋና ስነፅሁፍ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል ፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታው ከጊዜ ወደጊዜ አቅሙን እያሻሻለ ፣ በተለይ በፅህፈት ኮርሶችና የግል ሙከራዎቹም እያበሰለ መሄዱን በመመረቂያ ፅሁፉና የመጨረሻ ኮርሶች ውጤቱ አረጋግጦል ፡፡
የሁለተኛ ዲግሪውንም የሰራዉ፣ ምንም እንኳን ለ6 አመታት ገደማ በስራዉ አለም ከቆየ በኋላ ቢሆንም፣በዚያው በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ፣ በፎክሎር ትምህርት ክፍል ነው ፡፡ 2001 ዓ.ም ላይ የተመረቀበት “ የበርታ ህዝብ የአመጋገብና የአኗኗር ማቴሪያል ካልቸር ” ከአንድ ወር ላላነሰ ጊዜ የመስክ ጥናት የተደረገበትና “ Excellent” ማርክ ያገኘበት ነው ፡፡ አሁን ላይ ቢዘገይም ጥናቱ በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሊታተም የብሄረሰብ ምክር ቤት ግምገማን አልፏል ፡፡
የቤተሰብ- ሁኔታ
ንጉሥ፣ ባለትዳርና የ3 ሴት ልጆች አባት ነው ፡፡ ከጋዜጠኛ ሸዋርካብሽ ቦጋለ ጋር ትዳር ከመሰረተ 13 አመታት የተቆጠሩ ሲሆን ሜላት ፣ዳግማዊትና መክሊት የሚባሉ ብርቅዬዎችን አፍርተዋል ፡፡ በትዳራቸው ህይወትን ለማቅናት ተደማምጦ ከመስራት ባሻገር በስራዉ አለም ተመሳሳይ ሙያ ውስጥ ያሉ እማና አባዎራዎች እንደመሆናቸው በመደጋገፍ አግዟቸዋል ፡፡
መዝጊያ
ንጉስ ወዳጅነው ፣ አዲስ ዘመንን የመሰለ 80 አመት የሞላው ፣ ከአፍሪካ ባለረጅም እድሜ ጋዜጣን በዋና አዘጋጅነት ሲመራ ባገኘው እድል አቅሙን ሳይቆጥብ ለማውጣት ሙከራ አድርጓል፡፡ አብረውት የሰሩ ጠንካራ ሰው መሆኑን በይፋ መስክረዋል፡፡ ለለውጥ ያለውን ተነሳሽነት አድንቀዋል፡፡ አጠቃላይ መምህርነት እንዲሁም የህዝብ ግንኙነትን ስራ ጨምሮ በሚድያው አለም ከ19 አመት በላይ የቆየው ንጉስ ወዳጅነው በሄደበት ቦታ ሁሉ አንድ ነገር ለማበርከት ይጥራል፡፡ ከአሁን በኋላ ደግሞ ለሀገሩ ከዚህ በላይ ጨምሮ በመስራት አዲስ ታሪክ መስራቱ የማይቀር ነው፡፡ ንጉስ ዛሬ በግሉ መስራት የጀመረ ሲሆን ብእር ከወረቀት ማቆራኘት ያረካዋል፡፡ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሲጽፍ ደግሞ የደስታ ባህር ውስጥ ይገባል-ይህ ለእርሱ አርኪ ስራ ነው፡፡ ትልቁ ሚድያ ላይ በዋና መሪነት በመስራቱ የሰራባቸው ስፍራዎች ሰፊ እውቀት እንዲያከማችረድተውታል፡፡
ስለ ንጉስ ጽሁፎች ለማወቅ ሪፖርተር ላይ የወጡትን ጽሁፎች ማንበብ በቂ ነው፡፡ ንጉስ ለማህበራዊ ድረ-ገጽ ሩቅ አይደለም፡፡ ፌስ ቡክ ላይ ፕሮፌሽናሊዝምን በጠበቀ መልኩ ይጽፋል፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች ንጉስ በኢትዮጵያ የህትመት ሚድያ የራሱን አሻራ ማኖሩን ያምናሉ ፡፡ በመሆኑም ታሪኩ ለትውልድ እንዲተላለፍ በዚህ መልኩ ሰንደነዋል፡፡ / ይህ ጽሁፍ የተገኘው ከዋናው ባለታሪክ ከጋዜጠኛ ንጉስ ወዳጅነው ሲሆን ከ15 በላይ አስረጂ ምስሎችን ልኮአል፡፡ ታሪኩ እንዲሰራ በመጠቆምና ጽሁፉ በዚህ መልኩ እንዲወጣ ያደረገው ደግሞ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ሀምሌ 1 2013 ተጻፈ፡፤