ኃይለመለኮት መዋዕል መሐሪ

ኃይለመለኮት መዋዕል መሐሪ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ደራሲ ኃይለመለኮት መዋእል አንዱ ነው፡፡ ይህ ደራሲ ባለፉት 30 አመታት በድርሰት ስራ ላይ የተሰማራ ሲሆን በርካታ መጽሀፍትንም ለህትመት ሊያበቃ ችሏል፡፡ እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪኩን ሰንዶታል፡፡

ኃይለ መለኮት፣ ሰኔ 16 ቀን 1943 ዓ.ም. ከእናቱ ከወይዘሮ ሙላቷ ሀብተ ሚካኤል ከተማ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ይፋትና ጥሙጋ አውራጃ፣ ገምዛ ወረዳ፣ ማጀቴ ከተማ፣ ደይ ምድር ተወለደ፡፡ አባቱ አቶ መዋዕል መሐሪ ፖስታና ቴ.ቴ. ሚኒስቴር (ቴሌፎንና ቴሌግራፍ) በኋላ ቴሌኮሙኒኬሽን በስልከኝነት ተቀጥረው ይሠሩ ነበር፡፡ ወላጆቹ ገና በልጅነቱ በመለያየታቸው፣ እነዚያን ዓመታት ያሳለፈው መሶቢት ሚካኤል ይኖር ከነበረው አርሶ አደር አጎቱና፣ ማጀቴ ከነበሩት አያቶቹ ዘንድ ነው፡፡ አባቱ ከካራቆሬ ወደ ኮምቦልቻ ተዛውረው ገና ኑሮአቸው ባለመደላደሉ ልጃቸውን በወቅቱ መውሰድ አልቻሉም ነበር፡፡ የኃላ ኃላ ግን ወደ ኮምቦልቻ ወስደውት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ፊደል ቆጥሮ ዳዊት ደገመ፡፡ ኮምቦልቻ ከተማ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ስለተከፈተ የቤተ ክህነት ትምህርቱን አቋርጦ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገባ፡፡

“የልጅነት ሕይወቴ” ይላል ኃይለ መለኮት፣ “በዚያን ጊዜዋ ኮምቦልቻ ከተማና በዙሪያዋ ባለው ተፈጥሮና ሕዝብ፣ በቦርከና እና በበርበሬ ወንዝ ትዝታዎች የተሞላ ነው፡፡ ኮምቦልቻ እስከ አራተኛ ክፍል እንደተማረ፣ ከአባቱ ጋር ወደ ኤርትራ ሄደ፡፡ በዚያ ዘመን ኤርትራ ውስጥ ትምህርት የሚሰጠው በትግርኛ ስለነበር፣ ቋንቋውን የማይችለው ኃይለ መለኮት ትምህርት ቤት መግባት አልቻለም፡፡

አንድ ዓመት ያህል ገጠር ከእህት ወንድሞቹና (በአባቱ በኩል ከተወለዱት) ዘመዶቹ ጋር እንደቆየ፣ ትግርኛን አሳምሮ መስማትና መናገር ቻለ፡፡ አሥመራ ሐዲሽ ዓዲ ሠፈር የሚኖሩት የአባቱ ታላቅ እህት ወይዘሮ ማመት መሐሪ፣ እርሳቸው ዘንድ ተቀምጦ እንዲማር ስለፈቀዱ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል አክሪያ፣ ሁለተኛ ደረጃን ልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ትምህርት ቤት ተማረ፡፡ “የሰባተኛ ክፍል ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ” ይላል ኃይለ መለኮት “የሥነ ጽሑፍ ዝንባሌ የነበራቸው የአማርኛ ቋንቋ መምህሬ፣ ስለ ንባብ ጥቅም በሰጡኝ ምክርና ጮርቃ ጽሑፎቼን እያነበቡ ባደረጉልኝ ማበረታታት ምንጊዜም አልረሳቸውም” እያለ ያመስግናቸዋል፡፡

በእነዚያ ዓመታት ለክፍል ውስጥ በአማርኛ፣ ከክፍል ውጪ በትግርኛ የጻፋቸውን ግጥሞችና ዝርው ጽሑፎች የቤተ ክህነት ትምህርት ለነበራቸው አባቱ ስለሚያነብላቸው ያደንቁለት ነበር፡፡ ወደ ቀጣዩ ትምህርት እርከን ያልገባው ኃይለመለኮት፣ የገጠር ነዋሪ አባቱን በልዩ ልዩ ሥራ እየረዳ ከቆየ በኋላ፣ በሕፃንነቱ የተለያቸውን እናቱን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ወሰነ፡፡ በአካል ለይቶ የማያስታውሳቸውን እናቱን ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ፣ አባቱ የሰጡት የቀድሞ ጓደኛቸውን አድራሻ ብቻ ነበር፡፡ በሰውየው አማካኝነት ወላጅ እናቱን ፊት በር፣ ቀድሞው ቄራ ሠፈር አገኛቸው፡፡ ከጥቂት ወራት በስተቀር እናቱ ዘንድ መኖር ባለመቻሉ “ቅኗ፣ ደጓና ሩኅሩኋ” እያለ ወደሚጠራቸው አክስቱ የሺ ተፈራ ቤት ገባ፡፡

በ1962 ዓ.ም. አዲስ አበባ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ በሚገኘው በዓለም ማያ የግል (በኋላ የሕዝብ) ትምህርት ቤት በቀጥታ መምህርነት /ያለ ሥልጠና/ ተቀጥሮ እስከ 1969 ዓ.ም. ሠራ፡፡

“የንባብ ልምዱን ያዳበረው ለዓመታት ባነበበበት በሕዝብ ቤተ- መጻሕፍት ወመዘክር ነው፡፡ የታተሙትንም ሆነ ገና ያልታተሙትን መጻሕፍቱን በከፊልም ሆነ ከሞላ-ጎደል እዚያ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ እንደጻፋቸው ይገልጻል፡፡ “እንኳንስ ለንባብ ተቀምጬ፣ ገና ወደ ግቢው ስገባ ልዩ የመንፈስ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ሆኖም ያ በዕፅዋት ተውቦ የኖረው ግርማ ሞገሳም ግቢ፣ ከሞላ ጎደል ነበር ሆኗል፡፡

በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው በሚሠሩ መምህራንና ሠራተኞች ላይ ይፈጸም የነበረውን ከፍተኛ የአዕምሮና የጉልበት ብዝበዛ ለመከላከልና ለመቋቋም ሲባል፣ በ1965 ዓ.ም. የግል ትምህርት ቤቶች መምህራንና ሠራተኞች አንድነት ማኅበር በተመሠረተ በአራተኛው ወር፣ ኃይለመለኮት የማኅበሩ አባል ሆነ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የማኅበሩ ሊቀ መንበርና ዋና ጸሐፊ ሥራቸውን በመልቀቃቸው፣ እነርሱን ለመተካት በተካሄደው ምርጫ የማኅበሩ ፕሬዚደንት እንዲሆን ተመረጠ፡፡ ሁኔታውን ሲገልፀው “ከተመረጥኩበት ዕለት አንስቶ እስር ቤት እስከገባሁበት ዕለት ድረስ እልህ አስጨራሽና ወኔ ካቢ ትግል አድርጌአለሁ፡፡ መምህራኑና ሠራተኞቹ ትግላቸው እንዲሳካ ያላሠለሰ ጥረትና ተጋድሎ በማድረጋቸው፣ የማታ ማታ ትግሉ በከፊል ተሳክቶ ነበር፡፡ እኔን በሚመለት ግን በእነዚያ የትግል ዓመታት ያገኘሁት የሕይወት ተሞክሮና ያነበብኳቸው መጻሕፍት የርዕዮተ ዓለም ይዘትና አቅጣጫ እጅግ የተለየ በመሆኑ የአመለካከቴ መንገድ ተቀየረ” ይላል፡፡

የመምህራኑ ማኅበር የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር አባል ስለነበር “የሠራተኛ ድምፅ” በተባለ ጋዜጣ ላይ በስሙ እና በብዕር ስም ስለ ሠራተኞች አስቸጋሪ ሕይወትና ኑሮ መጻፍ ጀመረ፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች መምህራንና የሠራተኞችን ማኅበር ለማጠናከርና ትግሉንም ለማፋፋም “መምህር ይናገር” በሚል ርዕስ ይዘጋጅ በነበረው የቅስቀሳ እና የሥነ ጽሑፍ መጽሔት ላይ በምክትል አዘጋጅነትና አርታኢነት ይሳተፍ ነበር፡፡

ከዕለት ወደ ዕለት እየፋመና እየጋመ የመጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍትሕና የመብት ጥያቄ፣ ለግል ትምህርት ቤቶች መምህራንና ሠራተኞች ፀረ ጭቆናና ፀረ-ምዝበራ ትግል እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ያንን ጊዜ በትውስታው ሲዳስሰው “በሕዝቡ ትግል እየተናጠና እየተፍረከረከ የሄደው የገዢ መደብ ጎራ፣ በ1966 ዓ.ም. ለየለትና የካቲት 28 ቀን 1966 ዓ.ም. ኢ.ሠ.አ.ማ. ጠቅላላ የሥራ ማቆም አድማ ጠራ፣ በከፍተኛ የአሠሪዎች ምዝበራና ጭቆና ውስጥ የነበርነው መምህራንና ሠራተኞች፣ የዚያ ታላቅ ሕዝባዊ ተጋድሎ አካል እንሆን ዘንድ፣ ከማኅበሩ አመራር አባላት ጋር እየተዘዋወርን የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ስንቀሳቀስ በአንድ የግል ትምህርት ቤት ባለቤትና አጋር ዘመዶቹ ጠቋሚነት በፖሊስ ተይዤ እስር ቤት ገባሁ፡፡ ከአራት ቀን በኋላ በኢ.ሠ.አ.ማ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት፣ መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች የታሠሩ የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎችን ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ተጠይቆ፣ ሳይወድ በግድ በመስማማቱ ተፈታን፡፡ ያቺ የእስራት ቅምሻና የተካሄደው የሠራተኞች ትግል፣ የመታገል መንፈሴን አጠናክሮ ወኔዬን ይበለጥ አሰላው፡፡

በንባብም ረገድ ወደ ማርክሳዊ ርዕዮት ጎራ ይበለጥ ገፋሁ፡፡ በእጅጉ ተስማማኝ፡፡ የኢ.ሕ.አ.ፓ. እና የሠራተኛው ክንፍ የኢ.ላ.አ.ማ. /የኢትዮጵያ ላብ አደሮች ማኅበር/ አባል የሆንኩት በነዚያ ዓመታት ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ከደርግ ጋር በተፈጠረው የፖለቲካ መሥመር አቅጣጫ ልዩነት የተነሳ እንደሌሎቹ የኢሕአፓ አባላት /ከሠራተኛ ማኅበር ቢሮ/ ተይዤ፣ ከ1969 እስከ 1971 ዓ.ም. ድረስ በሕሊናም በአካልም ክፍ ያለ የሰቆቃ ጊዜያት አሳለፍኩ” ይላል በምሬት፡

አባቱ /የእንጀራ አባቱ/ ቢጠፋ በኃላፊነት ሊጠየቁ፣ የት አለ ሲባሉ አድራሻውን ሊያሳውቁ፣ ደርግ ጽሕፈት ቤት ድረስ ቀርበው በመፈረማቸው ከእስር ተፈታ፡: ቀደም ሲል 8 ዓመታት ወዳስተማረበት ትምህርት ቤት ሄዶ ከእስር ቤት የተለቀቀበትን ማስረጃ በማሳየት ወደ ሥራ እንዲመልሱት ጥያቄ አቀረበ፡፡ “አይቻልም” ብለው፣ ዳግመኛም እንዳይመለስ አስጠንቅቀው አባረሩት፡፡ በቤተሰቦቹ የእህል ወፍጮ ቤት አስፈጪ ሆኖ ሲሠራ ቆየና ወደ ሁለተኛዋ አክስቱ የብረት አልጋ መሥሪያ ጋራዥ ገብቶ ዓመት ያህል ከሠራ በኋላ፣ የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ እጅግ አስጊ ስለሆነበት ከአካባቢው “ገለል” ለማለት ወደ ማጀቴ ሄዶ ከአያቱና ከአክስቱ ጋር /ሄድ መለስ እያለ/ አራት ዓመት ያህል ኖረ፡፡

“ከሕይወት ዘመኔ ላይ…” ይላል ኃይለመለኮት፣ “…ከ1969 እስከ 1976 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ የነበሩትን 7 ዓመታት በመብትና ነፃነት እጦት በግፍ ተዘርፌአለሁ፡፡ ሆኖም ከምወዳት ማጀቴ እና በአካባቢው ካሳለፍኩት መቼም አይረሴ ኑሮዬ “ጉንጉን” የተሰኘውን ልብ ወለድ መጽሐፌን አፍርቼበታለሁ” በማለት ያንን ጊዜ ያስታውሰዋል፡፡

ከማጀቴ መልስ ጥቂት ወራት በሥራ አጥነት እንደቆየ፣ በ1976 ዓ.ም አጋማሽ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ ኮልፌ፣ “ጅማ ሠፈር” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሠረተ ዕድገት የሕዝብ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተቀጥሮ እስከ 1986 ዓ.ም. ሠራ፡፡ በእነዚያ ዓመታት በትምህርት ቤት ደረጃ፣ ሁለት ጊዜ በ“ምስጉን መምህርነት”፣ በ1979 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ደረጃ “ምስጉን የትምህርት ባለሙያ” ተብሎ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልሟል፡፡ በ1986 /87 ዓ.ም. እፎይታ መጽሔት በሠራበት ጊዜ ከሥራ ባልደረቦቹ “ከፍ ያለ የሙያ ዕውቀትና የሥራ ተመክሮ” እንደቀሰመ ይገልፃል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ውስጥ የምክር ቤት አባል ሆኖ በማኅበራዊ ዘርፍ ውስጥ አንድ ዓመት ተኩል ሠርቷል፡፡

በሜጋ አንፊ ቴአትር ባለቤትነት ታትተም በነበረችው የ“ፈርጥ” መጽሔት፣ (ከመምህርነቱ በተደራቢ) በአርታኢነት አገልግሏል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ መገናኛ አካባቢ 1990-2002 ዓ.ም. ድረስ ተከፍቶ በነበረው በዕድገት የጎልማሶች አዳሪ ትምህርት ቤት (ከጋምቤላ፣ ከአፋር፣ ከሱማሌ፣ ከቤኒሻንጉልና ጉሙዝ በክልሎቹ ተመርጠው የመጡ ጎልማሶች ከ5ተኛ እስከ 12ተኛ ክፍል የሚማሩበት) 12 ዓመታት አስተምሮ፣ በአጠቃላይ 33 ዓመታት በመምህርት ካገለገለ በኋላ እጅግ ከሚያከብረውና ከሚወደው የመምህርነት ሙያው በ2003 ዓ.ም. በጡረታ ተገለለ፡፡

የጽሑፍ ሙከራው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ ከመምህርነት ሥራው ጎን ለጎን፡-

1. ፀላም መቐነት፣ 2. ጋህሲ ስቓይ፣ 3. መገሻ ዓሻ፣ የራሱ ሥራ የሆኑ የትግርኛ ተውኔቶች፣ 4. የደንከል ዱቄት፣ 5. የሩፋኤል ጠበል (ባለ 1 ገቢር ትርጉም ተውኔት በአማርኛ)፣ 6. በሶቭየት ኅብረት ደራስያን ተጽፈው ከእንግሊዝኛ ወደ ትግርኛ የተረጎማቸው 7 አጫጭር ታሪኮች (በትግርኛ) ከመታሰሩ በፊት የጻፋቸው ሲሆኑ፣ ከጡረታ በኋላ በአርትኦት አቃንቶና አርሞ ለኅትመት አዘጋጅቷቸዋል፡፡

7/ ኦቴሎ የተሰኘውን የዊልያም ሼክስፒር ዝነኛ ተውኔት ከ40 ዓመት በፊት በትግርኛ ተርጉሞት ስለነበር በ2006 ዓ.ም. በበረከት ማተሚያ ቤት አሳትሞታል፡፡ ይህ ተውኔት በ2007 ዓ.ም. በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ሥነ ጥበባት ተማሪዎች ለመድረክ በቅቷል፡፡

8/ የትምህርት ሚኒስቴር በ1995 ዓ.ም. በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ5ተኛ እስከ 8ተኛ ክፍል ለማስተማሪያነት የሚውል የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መጻሕፍት ባዘጋጀበት ወቅት፣ በአስተባባሪነት፣ በአራቱም መጻሕፍት ውሰጥ በጽሑፍ አቅራቢነትና አርታኢነት ጉልህ ተሳትፎ አድርጓል፡፡

9/ ሀገራዊውን የእንካስላንቲያ ትውፊት መሠረት አድርጎ ከ750 በላይ አዳዲስ እንካስላቲያዎችን በ110 ገጽ ባለው መጽሐፍ አዘጋጅቶ 2005 ዓ.ም. በበረከት ማተሚያ ቤት በማሳተም ለንባብ አብቅቷል፡፡

10/ ግለ ታሪኩን የምትገልፅ “አንዲት ነፍስ” የተሰኘች ጽሑፍ በፈርጥ መጽሔት ላይ ታትማ ነበር፡፡ ይህችው አጭር ታሪክ ትምህርት ሚኒስቴር ለ12ተኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ ማስተማሪያነት ባዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ ተካትታ ታትማለች፡፡

11/ ኢትዮጵያውያን ደራስያን ያዘጋጁትን “ደንሺ ሳሮን ደንሺ” የተባለ የሕፃናት መጽሐፍ (በጎተ የባሕል ማዕከል አስተርጓሚነት) “ሳዕስዒ፣ ሳሮን ሳዕስዒ” በሚል ርዕስ ወደ ትግርኛ ተርጉሞት በ2010 ዓ.ም. ለንባብ በቅቷል፡፡

12/ በ1970 ዓ.ም አቶ ዮሐንስ ክፍሌ ዳዲ የማክሲም ጎርኪን “እናት” የተሰኘች ገናና ልብ ወለድ” መጽሐፍ እስር ቤት ውስጥ ወደ አማርኛ በተረጎመበት ወቅት፣ ኃይለ መለኮት ትርጉሙን እያነፃፀረ በማረጋገጥ በአርታኢነት አግዟል፡፡ በዚያው ዓመት ይህንኑ ትርጉም ወደ ተውኔት ለውጦት ለኅትመት ዝግጁ ሆኗል፡፡

13/ በ1978 ዓ.ም. በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አሳታሚነት በቦሌ ማተሚያ ድርጅት በ2002 ዓ.ም. በንግድ ማተሚያ ቤት በ2007 ዓ.ም. በግራፊክ አታሚዎች የታተመችው “የወዲያነሽ” 356 ገፅ ያላት ልብ ወለድ ናት፡፡ በአጠቃላይ በ40 ሺህ ኮፒዎች ያህል 4 ጊዜ ታትማለች፡፡

14/ 462 ገጾች ያሉት “ጉንጉን” የተሰኘው ልብ ወለድ መጽሐፉ በ1982 ዓ.ም. በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አሳታሚነት በቦሌ ማተሚያ ቤት በ40 ሺህ ኮፒዎች የታተመ ሲሆን፣ በ2007 ዓ.ም. ደግሞ 3 ሺህ ኮፒዎች በግራፊክ አታሚዎች ታትሟል፡፡ በተጨማሪም በ2012 የገብረክርስቶስ ገብረእግዚአብሄርን የ100 አመታት የህይወት ታሪክ በአማርኛ ጽፏል፡፡ መጽሀፉም ወደትግርኛ ተተርጉሞ በሻማ ቡክስ ታትሟል፡፡ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እስከ 2015አ.ም ባሉት አመታት በተለያዩ ደራሲያን እና የተተረጎሙ ከ80 በላይ መጽሀፍትን አርትኦት አድርጓል፡፡ኃይለመለኮት መዋዕል ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነው፡፡

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ የቦርድ አባላት አቋምን የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ይህ የህይወት ታሪክ በተወዳጅ ሚድያ ሲሰነድ 72 አመቱን ያከበረው ጋሽ ሀይለመለኮት ዛሬም ከጽሁፍ ስራው ላይ ይገኛል፡፡ እርሱ ብእሩ እናም ፈጽሞ የሚነጠሉ አይደሉም፡፡ እነ ጉንጉን እና የወዲያነሽ የዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ለመሆን የቻሉ ሲሆኑ በዚህም ጋሽ ሀይለመለኮት ስሙ በደማቁ የሚጻፍ የብእር ሰው ነው፡፡ ሁሌም ሊነገርለት የሚገባ ጎምቱ የስነ-ጽሁፍ ሰው፡፡ ይህ ደራሲ ከአማርኛ በዘለለ በትግርኛ ቋንቋ የድርሰት ስራዎችን ማቅረቡ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ልምዱን ለማካፈል እኔ ምን ገዶኝ የሚለው ይህ ቅን ደራሲ የብዙዎችን ጽሁፍ አቃንቷል፡፡

በዚህም ብዙዎች ምስጋናቸውን ይቸሩታል ፡፡ እኛም የጋሽ ሀይለመለኮትን ታሪክ ስንሰንድ ከድርሰት ስራዎቹ ባሻገር ሰው ለማገዝ ያለውን ተነሳሽነት በማጤን ነው፡፡ ይህ ደራሲ የሚጠበቅ ነው፡፡ ደራሲ ወደ መልካም መንገድ የሚመራ እንደመሆኑ ጋሽ ሀይለመለኮትም ይህን አደራውን በአግባቡ ተወጥቷል እንላለን፡፡ ለዚህ ትልቅ ውለታውም እናመሰግነዋለን፡፡