ትዕግስት ካሳ ሚልኮ
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸውን ሰዎች ጠቁሙን ፤ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪካቸዎን እናወጣለን፡፡
በ tewedajemedia@gmail.com ጥቆማዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡
ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ በተለይም ከሬድዮ ጋዜጠኝነት ጀምራ በአለም ኣቀፍ ተቋማት ከፍተኛ የኮሚኒኬሽን አማካሪ እስከመሆን የደረሰችው ትእግስት ካሳ ብዙ የሚነገር ታሪክ አላት፡፡ ከሬድዮ እስከ ከፍተኛ የኮሚኒኬሽን ባለሙያነት የሄደችበት መንገድ ከታሪክ መዝገብ ላይ ሲሰፍር የሚከተለውን ቅርጽ ይዞ ይነበባል፡፡
በልጅነት ዕድሜዋ ትምህርት
ትዕግስት ካሳ ሚልኮ በአዲስ አበባ በቀድሞው የብስራተ ወንጌል አለምዓቀፍ አገልግሎት በአሁኑ የኢትዮጵያ ሬድዮ አገልግሎት ግቢ ውስጥ ነበር ከአባቷ ከአቶ ካሳ ሚልኮ ከእናቷ ከወ/ሮ ፈቃደ በዛብህ የተወለደችው፡፡ ከስድስት ልጆች አምስተኛዋ፤ ሶስት ወንድሞች እና ሁለት እህቶች ያሏት ቢሆንም ሰው ሁሉ ቤተሰቧ እንዲሆን የመፈለጓ ጉዳይ በቤተሰብ ቤት ያደገች አያስመስላትም፡፡ የእድሜዋን ሀሁ በትምህርት መጀመሯ ዛሬ ለደረሰችበት ማመላከቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የእናቷ ለትምህርት ያላቸው ፍቅርና መቆጨት ፤ የአባቷ ያለ ትምህርት መኖር ባዶነት ይሉት ፍልስፍና በልጅነት ዕድሜዋ ትምህርት እንድትጀምር አስገድዷት ነበር፡፡ በወራት እድሜ ላይ እንዳለች አፍ በጊዜ መፍታቷ ለእናቷ ጥሩ አጋጣሚ ሆነላቸው፡፡
በ3 አመቷ ተማሪ ቤት ገባች-የእናት ጽናት
በሁለት ዓመቷ ከብስራተ ወንጌል አለምዓቀፍ አገልግሎት አቅራቢያ ካለው የቄስ ት/ቤት ለየኔታ ወልደ ሚካኤል ተሰጠች፡፡ በአንድ ዓመት የቄስ ት/ቤት ቆይታዋ ፊደልን ጠንቅቃ በመለየቷ ወደ አንደኛ ክፍል እንድትገባ በመወሰኑ በሶስት ዓመቷ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን እንድትቀጥል ሆነ፡፡የአባቷ ሰው የምትሆኑት በትምህርት ነው የሚለው ውትወታ ፤ የእናቷ ልፋት እንዲሁ በከንቱ አልነበረም፡፡ የእራሳቸውን የትምህርት ናፍቆት ለመወጣት ፤በአንድ በኩል ትንሽዬዋን ትዕግስት በሶስት ዓመቷ ወደ ትምህርት ቤት ብቻዋን ላለመላክ ትምህርት ካቆሙበት መቀጠልን በማሰብ የማነ ብርሃንን ት/ቤትን ተቀላቀሉ፡፡ ከአምስት እስከ ስድስት ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዞ መማር ፤ያውም በልጅ እግር ከብስራተ ወንጌል እስከ የማነብርሃን ት/ቤት መጓዝ የመፈተን ብሎም የመጠንከር ጅማሮ ነበር፡፡
የማነ ብርሃን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በልጅነቷ የተሰራችበት ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ከእናቷ ቀጥሎ እንደወላጅ ያነፅዋት መምህር ተማም ከማል ፣ መምህር ግርማ፣ መምህር ገዙ ብላቴ፣ መምህር ገዙ ከበደ መምህር አስፋው ወሰን እና ሌሎቹም በልጅነቷ መሠረት ላይ አሻራቸውን ያኖሩ የዕውቀት አባቶቿ ናቸው፡፡ ከ1ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የደረጃ ተማሪ በመሆን ብታጠናቅቅም የስምንተኛ ክፍል የሚኒስትሪ ውጤቷ አመርቂ ሆኖ ወደ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ለመሻገር የእድሜዋ ነገር ማነቆ ሆነ፡፡ በ13 ዓመቷ 9ኛ ክፍልን ማስጀመር ከባድ ነው የሚል ትግል፡፡ ‘ልጄን ወደ ኋላ አልመልስም …የደረጃ ተማሪ ናት’ የሚለው የእናት ክርክር መዝጋቢዎችን ስሜታዊ በማድረጉ አየር ጤና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትን በመቀላቀል ሁለተኛው የትምህርት ምዕራፍ ቀጠለ፡፡ ከእናቷም ጋር የተጀመረው የትምህርት ጉዞ በተለይ ወላጅ እናቷ በመሃል የተወለደውን ታናሽ ወንድሟን ለማሳደግ መታጎል ቢገጥመውም የ12ኛ ክፍል ማጠቃሊያ ፈተና (ማትሪክ) ላይ እንዲገናኙ ግን አድርጓል፡፡ እናትና ልጅ በአንድ ጠረጴዛ ላይ ለማትሪክ መቀመጥ በትዕግስት ህይወት ውስጥ የዓላማ ጽናትን ከምንም በላይ የትምህርትን ዋጋ ያየችበት እንደሆነ ትናገራለች፡፡
የሚድያ ፍቅር ጥንስስ
ከትምህርቱ ጎን ለጎን የጋዜጠኝነት ፍቅሩ ተዳፍኖ እንዳይቀር በአየር ጤና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚኒ ሚድያ ከማቋቋም ጀምሮ በትጋት በመስራት በህፃን አዕምሮዋ የተቀረጸው ፍላጎት መጎልመስ ጀመረ፡፡ ለዚህ ሌላው አጋዡ ነገር የአባቷ የሬድዮው ጣቢያው የቴክኒክ ባለሙያ መሆናቸው በተለይም የጌጃ ጀዌ ማሰራጫ ጣቢያ ኃላፊም በመሆናቸው ሬድዮ ጣቢያውን በልጅነት ዕድሜ የማየት ፤ የመከታተል ዕድል ነበራት፡፡ ያኔ በልጅ ዕድሜ የተፈጠረው ጋዜጠኛ የመሆን ፍላጎት በቀላሉ የሚገደብ ባለመሆኑ የመጀመሪያው የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ተወልዳ ባደገችበት የብስራተ ወንጌል አለምዓቀፍ አገልግሎት በመከፈቱ ዕድሉን አግኝተው ወደ ሙያው ከተቀላቀሉት ጓደኞቿ ጋር የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች በመሆን ሙያውን ልትኖረው መንገዱን ጀመረች፡፡ ትውልዷም እድገቷም ትምህርቷም ብሎም የመጀመሪያ የጋዜጠኝነት የሙከራ ጊዜዋም በብስራተ ወንጌል አለምዓቀፍ አገልግሎት መሆኑ ለሙያው የበለጠ መትጋት እንድትችል ያገዛት ይመስላል፡፡ አጋጣሚውም ከፍላጎቷ ጋር መጣጣም መቻሉ የስኬት የመጀመሪያ ምዕራፍ አድርጋ እንድታየው ሆነ፡፡
የመጀመሪያ ምዕራፍ -ሬድዮ ፋና
ሬድዮ ፋናን በ1989 ዓ.ም ስትቀላቀል በመገናኛ ብዙሃን ታሪክ አዲስ ተጫማሪ የሬድዮ አማራጭ የተገኘበትና የጅምሮቹ መንደርደሪያ ከመሆኑ አንፃር አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር ዕድል የሚሰጥ ነበር፡፡ ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት በሰራችባቸው የመዝናኛ ፕሮግራሞች ውስጥ እጅግ ተወዳጅ የነበሩ ዝግጅቶችን በማቅረብ ሬድዮ ጣቢያው ተወዳጅ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር ያልተነኩ ማኅበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት ለውጥ እንዲመጣ ትልቅ ሚና ተጫውታለች፡፡ የኢትዮ -ኤርትራ ጦርነትን በተመለከተ ፤ግለ-ታሪኮችን መሠረት ያደረጉ ዘጋቢ የሬድዮ ታሪኮችን በመስራት እንዲሁም ትላልቅ መድረኮችን በመምራት ኃላፊነቷን ተወጥታለች፡፡
ሬድዮ ፋና ሌላው ዩኒቨርሲቲ ነው የምትለው ትዕግስት ሙያን ከማዳበርና ከማበልጸግ ባሻገር የህይወት ልምድ የቀሰመችበት ከተለመደው አኗኗር በተለየ ሌላውን የኢትዮጵያ ክፍል ለማየት ዕድል የፈጠረላት ትልቅ ትምህርት ቤትም ነበር፡፡ የመኖር ትርጉም የተጀመረበት የህይወት ማዕከል፡፡
ትእግስት ፋና በሰራችባቸው አመታት አብረዋት ያገለገሉ ባለሙያዎችን አትዘነጋም፡፡ በተለይ በመዝናኛ ክፍሉ የነበሩ ባልደረቦች ወርቃማውን ዘመን ወደ ህሊናዋ እንድታመጣ የሚጋብዙ ናቸው፡፡ እሸቱ ዱብ ፤ ደግአረገ ነቅአጥበብ ፤ መስፍን አሸብር ፤ ነቢዩ ግርማ ፤ ዮናስ አብርሀም ፤ ማህደር በቀለ ፤ ሳሙኤል እንዳለ፤ እማዋይሽ ዘውዱ የመሳሰሉት አይረሱዋትም፡፡ ይህ የህይወት ማዕከል እንደተጀመረ 1993 ዓ.ም ላይ ሬድዮ ፋናን በመሰናበት ወደ ሌላ ምዕራፍ ለመሻገር መንደርደሪያ ሆነ፡፡
ሙያ ከጎረቤት – ኬንያ
የሲቪል ማኅበራት የመነቃቃት ጉዳይ የመገናኛ ብዙሃኑን አቅም ለማጎልበት አግዟልና በተለይም የሴት ጋዜጠኞች ማኅበር መቋቋም ሌላው እይታ ነበር፡፡ ትዕግስት በኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማኅበር ውስጥ ከተመሠረተ ጀምሮ አባል የነበረች ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ከኖርዌይ መንግስት በተገኘ ድጋፍ የFredskorpset (FK Norway)Exchange Program ተሳታፊ የመሆን ዕድልን አገኘች፡፡ ፍሬድስኮርፕሴት በኖርዌይ እና በታዳጊ ሀገሮች (በሰሜን-ደቡብ) እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች (ደቡብ-ደቡብ) መካከል የወጣት ባለሙያዎችን እና በጎ ፈቃደኞችን ልውውጥ በማድረግ የልምድ ፣ የክህሎትና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር የሚያደርግ ሲሆን የተሣታፊ ድርጅቶችን አፈፃፀም የሚያሻሽል ከመሆኑም በላይ በሕይወት ላይ ለውጥ የሚያመጣ ተሞክሮ እዲኖር በስልጠናና በገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ፕሮግራም ነው፡፡
በዚህም መሠረት በአምስት የአፍሪካ ሀገራት በሚገኙ የሴት ጋዜጠኞች ማኅበራት መካከል በተዘጋጀ ፕሮግራም ትዕግስት ከመጀመሪያዎቹ ተሳታፊዎች አንዷ በመሆን የመጀመሪያውን ስልጠናና ስለ ፕሮግራሙ ማስገንዘቢያ በዑጋንዳ ልዌዛ በመከታተል የአንድ ዓመት የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሙን በኬንያ ናይሮቢ ተከታትላለች፡፡ በኬንያ ናይሮቢ በሚገኘው የሴት ጋዜጠኛች ማኅበር (Association of Media Women in Kenya- AMWIK) በኩል በኔሽን ሚድያ (Nation TV –NTV እና Eazy FM) ላይ በፕሮግራሙ መሠረት ለአንድ ዓመት የመስራት ዕድል አጋጥሟታል፡፡ ትእግስት ከ1994-1995 በኬንያ የነበራትን ቆይታ አዲስ አለም ስትል ትጠራዋለች፡፡
በምርመራ ያጋለጠችው ዘገባ
በኔሽን ቴሌቪዥንና ሬድዮ ትልቅ ልምድ ያገኘችበት ብሎም ሀገሯንም ያስጠራችበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በተለይ በኬንያ የማኡ ማኡ ታጋይ በነበሩት ጄነራል ስታንሊይ ማቴንጌ ዙሪያ በተካሄደ የማጭበርበር ዘገባ ላይ ከፍተኛ ሚና በመጫወት የሙያና የሀገር ግዴታዋን መወጣት ችላለች፡፡ ይህ ዘገባ በህይወት የሌሉትን የማኡ ማኡ ታጋይ ጄነራል ስታንሊይ ማቴንጌን በህይወት እንዳሉ ፤ ኑሯቸውንም በኢትዮጵያ እንዳደረጉ ከሃምሳ ዓመት በኋላም ከአገቧቸው ኢትዮጵያዊ ሚስታቸው ጋር ቤተሰብ መስረተው ልጆች አፍርተው እንደሚኖሩ የሚያትት ዘገባ ምድረ ኬንያን ቢንጣትም ታሪኩ ግን ትክክል ያልሆነ ብሎም በአንድ ንጹህ ኢትዮጵያዊ አቶ ለማ አያኖ በተባሉ ግለሰብ ላይ የተሰራ ታሪክ መሆኑን በማጋለጥ በምርምር ዘገባ ሰፊ ድርሻ ተወጥታለች፡፡ ይህ ታሪክ አስቸጋሪ ፤ፈታኝና ውስብስብ ከመሆኑ አንፃር ከአምስት ወራት በላይ የፈጀ ፤የታሪኩ መጨረሻ አጓጊ እንዲሆን ያደረገ በኬንያ ብቻም ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ብሎም በCNN የአፍሪካ ጋዜጠኞች የሽልማት ውድድር ላይ እጩ ታሪክ የነበረ በመሆኑ የምርምር ጋዜጠኝነቱን አክብዶት ነበር፡፡
ይሁንና በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ (በተለይም በወቅቱ ካውንስለር በነበሩት ዲፕሎማት አቶ መንግሰቱ አያሌው ከፍተኛ ድጋፍ) እና በሙያ አጋሮቿ ማበረታቻ ውጤቱ ያማረ እንዲሆን ሆኗል፡፡ ባለታሪኩ ኬንያዊው የማኡ ማኡ ታጋይ ጄነራል ስታንሊይ ማቴንጌ ሳይሆኑ ኢትዮጵያዊው ለማ አያኖ መሆናቸውን በማረጋገጥ ታሪኩን ማስቀየር ችላለች፡፡ ለዚህም ስራዋ በኬንያ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም ከኔሽን ሚድያ የምስጋና ደብዳቤ ተችሯታል፡፡
የሀገሯን ባህል ማሳወቅ እና የሀገር ልጅን መርዳት
በኬንያ ኔሽን ሚድያ ቆይታዋ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን በጣቢያው መተላለፍ እንዲችሉና እንዲሁም የኢትዮጵያን ባህልና ኃይማኖት የሚያንጸባርቁ ዝግጅቶችን ናይሮቢ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዙሪያ እንዲዘገብ አድርጋለች፡፡ በተለየ አጋጣሚ ከኬንያ ወደ ታንዛንያ ድንበር አቋርጣ በምትጓዝበት ወቅት በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው በሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ፣ መከራ እንዲሁም ናማንጋ በተባለው ድንበር በእስር ላይ እንዳሉ የሚደረስባቸውን ፈተና ለሚመለከተው በማሳወቅ እንዲሁም ለኔሽን ሚድያም የዘገባ አቅጣጫ እንዲሆን አግዛለች፡፡ ትልቁ የህይወት ተሞክሮ በዚሁ ሁሉ የተገደበም አልነበረም፡፡
በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ አስመልክቶ ከምርጫ ቅስቀሳ እስከ ምርጫ ዘገባ ድረስ ብሎም የምርጫውን ውጤት ተከትሎ የተፈጠረውን ግጭት የመዘገብ ዕድል አጋጥሟታል፡፡ ይህን ተከትሎ የተፈጠረውን የመንግስት ለውጥና የስልጣን ሽግግርን ለመዘገብም አስችሏታል፡፡ በተለይም በኬንያ ያለው የመገናኛ ብዝሃነት ብዙ ልምድ ለመቅሰም ዕድል መፍጠሩም ብቻም ሳይሆን ፖለቲካዊ ዘገባዎች ላይ እንድታዘነብል አግዟታል፡፡ ይህ ጊዜ የትዕግስትን ህይወት ወደ አንድ አቅጣጫ ያሳደገ ነበር፡፡
ከኬንያ መልስ … ቁጭትና ጋዜጠኝነት
ከኬንያ የተገኘው ልምድ በቀላል የሚነገር ባይሆንም ወደ ሀገር በፍጥነት ተመልሶ በተግባር ለመቀየር እንደታሰበው መሆን አልቻለም፡፡ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በጥምረት የመስራቱ ነገር ቀድሞ ፓኖስ ኢትዮጵያን በመቀላቀል ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ድምጽ በሚያደርገውና በፆታ ጉዳይም የመጀመሪያ ሆነውን የሬድዮ ፕሮግራምን ከ1995-1997 ባሉት ጊዜያት ማዘጋጀት ጀመረች፡፡ ጎን ለጎንም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የመዘገብ ፍላጎትዋ እንዳይገደብ በሞኒተር የአማርኛ ጋዜጣ ላይም መፃፏን ቀጠለች፡፡ ቁጭቷ እረፍት ቢያጣ የግሏን ጊሸን ሚድያና ኮሙዪኒኬሽንን በማቋቋም የጋዜጠኝነት ፍላጎቷን ለማርካት የተለያዩ የሬድዮ ፕሮግራሞችን በመስራት እንዲሁም የኮሙዩኒኬሽን ስራዎችን መስራቷን ቀጠለች፡፡
ጋዜጠኝነት እና ትምህርት
እምቅ ፍላጎት በትምህርት መታገዝ እንዳለበት የምታምነው ትዕግስት ከመጀመሪያው የጋዜጠኝነት ትምህርት በኋላ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ለመዘገብ ያስችላት ዘንድ በሉላዊነት ጥናት እና አለምዓቀፍ ግኑኝነት የመጀመሪያ ዲግሪዋን በማህበረሰብ ጥናት ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪዋን የሰራች ሲሆን የጋዜጠኝነት ሙያዋን የበለጠ ለማዘመን ተጨማሪ ስልጠናዎችን ወስዳለች፡፡ በሚድያ አስተዳደር በተለይም የህዝብ ብዙሃን መገናኛ PBS ማጠናከር በስዊድን ሀገር፣ በstorytelling, Youtubing እና ፊልም አዘጋጅነት በኔዘርላንድ ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡
ጋዜጠኝነትና ሽልማቶች ከነፃ የትምህርት ዕድሎች ጋር
- Broadcast Journalist of the Year, FAWE Media Excellence Award 2005
- Ethiopian Journalist Fellow, Stop TB Media Fellowship, Global AIDS Fund, Lusaka, Zambia 2005
- Ethiopian Journalist Fellow, Panos G8 Summit, Heligendamm Germany, 2007
- National Coach on Women’s Empowerment, Washington D.C. 2012
- Woman Champions of RH/FP, CEDPA, Washington D.C. 2011
ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ስልጣናዎችን በጋዜጠኝነት፣ በኮሙዩኒኬሽን ፣ በአመራርነት ዙሪያ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ተከታትላለች፡፡ እንዲሁም ከሌሎች የአፍሪካ ጋዜጠኞች ጋር በመሆን ስራዎቿ በስፓኒሽ ቋንቋ ታትሟል፡፡
በኮሙኒኬሽን/በተግባቦት ሙያ ድንገት መጠለፍ
ትዕግስት ጋዜጠኛነቱን በልቧ አስቀምጣ በኮሙኒኬሽን/ተግባቦት ሙያ ድንገት መጠለፏ በሌላ ሙያ ራሷን የምታይበት ሆነ… ለዚህም የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶችን መቀላቀል ችላለች፡፡ በተለይም በጤናው ዘርፍ ያለውን የተግባቦት ስራ ከማገዝ ባሻገር እስከ ሀገርአቀፍ ሰነዶችን እስከማዘጋጀት ደርሳለች፡፡ የተግባቦት ስራውንም ከአድቮኬሲ እና ሀገራዊ ንቅናቄዎች (Campaigns) ጋር በማቀናጀት ትላልቅ መድረኮችን በማዘጋጀት ድርሻዋን ተወጥታለች፡፡ እነዚህን የተቀናጁ ስራዎችን የመንግስት አካላትን ፣ የፓርላማ አባላትን እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችን በማካተት ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክታለች፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለችግር የተጋለጡ እና ተደራሽ መሆን ያልቻሉ ማኅበረሰብን አርብቶ አደሩን ጨምሮ ሰፊ ስራን የሰራች ሲሆን በተለይም የተግባቦትና የአድቮኬሲ ስራዎች ለእነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተገቢው መንገድ ተቀርጸው እንዲቀርቡና የተለያዩ የጤናና ተያያዥ ፕሮግራሞችም አካታች የሆነ ስልት ማስቀመጥ እንዲችሉ ስታግዝ ቆይታለች፤ አሁንም በማገዝ ላይ ትገኛለች፡፡ በሚሰሩ ሀገር አቀፍ ሰነዶች ላይም ይህንን ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ አድርጋለች፡፡ የስርዓተ- ጾታ ጉዳይም አንዱ ትኩረት ሰጥታ የምትሰራበት ከመሆኑ አንፃር ስልጠናዎችንም በማዘጋጀት የስርዓተ- ጾታው እይታውና ተግባራዊነቱ ላይ ለውጥ እንዲመጣ በተለይም የሴቶችን ተሳትፎ ከመጨመር/በቁጥር የሚገለጽ ተሳትፎን/ አንፃር ብቻ ሳይሆን የውሳኔ ሰጪነትና የአመራር ብቃታቸው ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ በማገዝ ላይ ትገኛለች፡፡
የማህበረሰብ አመራር እና ተሳትፎ
ሙያዊ ድጋፍ ከመስጠትና ከማገዝ አንፃር በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ በቦርድ ኃላፊነትና አባልነት እየሰራች ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት ሴት ተማሪዎችን የህይወት ልምድ በማካፈል የማማከር ስራንም ትሰራለች፡፡ ከዚህም ባሻገር ስራቸው ላይ እገዛ ለሚፈልጉ ሴት ባለሙያዎችም የማማከር ስልጠና የመስጠት ስራን ደርባ ትሰራለች፡፡ ይህም ከፍተኛ እርካታ የሚሰጣት በመሆኑ ወደፊትም አጠናክራ ትቀጥልበታለች፡፡
ሀገራችን ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚደርሱ አደጋዎች እና የእርስ በርስ ግጭቶች ለሚፈናቀሉ ወገኖች እገዛ በማድረግ ስራ ውስጥም ሰፊ ድርሻ እንዲኖራት ማድረግ ችላለች፡፡ ከአለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውን መብት ግብረ-ሰናይ ድርጅትጋር በመሆን በተለምዶ ‹‹ቆሼ›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰው የቆሻሻ መናድ ለተጎዱና ቤተሰባቸውን ላጡ ወገኖች በመድረስ እንዲሁም በጌድዮና ጉጂ አካባቢ በተነሳው ግጭት ከሌሎች አባላት ጋር በመሆን ጥናት በማድረግ ሰፊ እገዛ እንዲኖር የማስተባበር ስራን ሰርታለች፡፡ በጣፎ፤ በሻሸመኔ ፣ በአጣዬና አካባቢው በመተከል በተነሱ ግጭቶች ለተጎዱ ፣ ለተፈናቀሉ እና ቤተሰባቸውን ላጡ ወገኖች ለማገዝ በሚደረገው የተቀናጀ ስራ ላይ አስተባብራለች፡፡ ይህንኑ ስራ ከተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲሁም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር እየሰራች ትገኛለች፡፡
ያገረሸው ጋዜጠኝነት እና ዋርካ መልቲ ሚድያ
ጋዜጠኝነት ሱስ ነው ፤ በቀላሉ አይላቀቅም … ግርሻም አለው የምትለው ትዕግስት በተግባቦት ስራ ውስጥ ተሸፍና እንዳትቀር የግል መገናኛ ብዙሃን መስፋፋትን ተከትሎ የአሃዱ ሬድዮ መከፈት መልካም አጋጣሚ ሆነላት፡፡ ከሬድዮ ጣቢያው ጋር በአንድ የጀመረውን የሰርክ ጨዋታን ይዛ ብቅ አለች፡፡ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተለይ ነቅሶ በሳምንቱ ሰርክ የሚቀርበው መሰናዶ አዲስ ጅማሮን ያሳየ ከመሆኑም ባሻገር ሀገራዊ ጉዳዮችን ከዲያስፖራው ጋር በማገናኘትና ትስስር በመፍጠር የሚሰራ የሬድዮ መሰናዶ ነበር፡፡
ፕሮግራሙ ለሀገር ከማዋጣት አንጸር ሚና እንዲኖረው ተደርጎ የተቀረጸ ሲሆን በየአህጉራቱ ዘጋቢ ባለሙያዎችን በማካተት በቦታው ላይ ሆኖ ዜናውን የማስተላለፍ ሁኔታዎችንም የፈጠረ ነበር፡፡ ይኸው ጉዞ መልክ ይዞ ከሌሎች የሙያ አጋሮቿ ጋር በመሆን ዋርካ መልቲ ሚድያን የመፍጠር እሳቤ ተነስቶ ከሰፊ ጉዞ በኋላ በ105 ጋዜጠኞች መስራችነት ዋርካ ህያው ሆኗል፡፡ ዋርካ 104.1 በመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በኩል ህጋዊነት አግኝቶ ስራውን ለመጀመር እንቅስቃሴው ተጀምሯል፡፡
ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ተተኪ ጋዜጠኞችን የማፍራት ዓላማዋን የበለጠ የምታሳካበት ከመሆኑ አንፃር ከመደበኛው የጋዜጠኝነት ስልጠና ጀምሮ Health Reporting, Conflict Sensitive Journalism, Gender Sensitive Reporting and election Reporting ላይ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ትገኛለች፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ቲንክ-ታንክ ቡድኖች ላይ በውጭ ጉዳይ እንዲሁም በህዳሴው ግድብና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ በመስጠት እየሰራች ትገኛለች፡፡
እናትነት ከባድ ኃላፊነት ቢሆንም በዚህ ትግል ውስጥ ለ3 ልጆችዋ አርአያ ሆኖ ለማለፍ እና የታሪኮቿ አካል እንዲሆኑ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በተለይም ሀገር ወዳድነት፣ የሀገር ፍቅር ስሜት እና ሰው ሆኖ መገኘትን አጥብቀው እንዲይዙና የህይወታቸው ቁልፍ እንዲሆን ምናልባትም ለአባቷ የገባችላቸውን ቃል የምትፈጽምበት እንደሆነ ትናገራለች፡፡
በመጨረሻም…
ያልተነገሩ ታሪኮች
- ሩጫ ከመውደዷ የተነሳ በትምህርት ቤት ደረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ደርሳ ለትምህርቷ ስትል አቋርጣዋለች፡፡
- ኪነ-ጥበብ አንዱ መደበቂያዋ አሊያም መገለጫዋ ነው፡፡ ቴአትርን ተስፋዬ ሲማ ጋር ተምራ በማዘጋጃ ቤት ቴአትርና ባህል አዳራሽ ሮሚዮና ጁልየት እና ጁሊየስ ቄሳርን በኮርስነት፤ ዕድል ሃያን በተዋናይነት ፣ እንዲሁም ‹‹ደም›› የተሰኘውን ቴአትር በቀንዲል ቤተ ተውኔት ተውናለች፤ የተከበሩ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅንን በዚህ መድረክ በክብር እንግድነት ተጋብዘው የነበረ ሲሆን ምክርንና ማበረታቻን ከሌሎች ሙያተኞች ጋር ተቀብላለች፡፡
- መድረክን በብቃት መምራት በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እያለች የጀመረች ቢሆንም በሬድዮ ፋና የተለያዩ በዓላት በነበሩ ዝግጅቶች ላይ መድረክ መምራትን አጎልብታ ዛሬም መድረክ መምራቱን ቀጥላለች፡፡
- ግጥም መተንፈሸዋ ነው፡፡ ያልታተመ መድብል ያላት ሲሆን ወደፊት ለህመት እንዲበቃ ዕቅድ ተይዞለታል፤
- ስለ ኢትዮጵያ ብሎም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ኃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት ማድረግ አንዱ ስራዋ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከ1000 በላይ ኃይማኖታዊ መጽሃፍትን ሰብስባለች፡፡
- ጉዞ ማድረግ ህይወቷ ነው፡፡ ሀገሯን የማየት የመጎብኘት ዕቅዷ ፳ ዓመታትን ቢፈጅም ማሳካት ችላለች፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ሀገሯን ጠንቅቃ መረዳት ችላለች… ኤርትራን ጨምሮ፡፡ ይህ የጉዞ ህይወት በሀገር ውስጥ ብቻ የተገደበ አይደለም አፍሪካንም ያካተተ ጭምር ነው፡፡
ማጠቃለያ
ትእግስት ካሳ በልጅነት የጀመረችው የሚድያ እና የስነ-ጽሁፍ አለም አሁን ላይ አድርሷታል፡፡ ባለፉት 24 አመታት ያሳለፈችው ድንቅ ጊዜ አልጋ ባልጋ ነው ባይባልም ሁሉንም ፈተናዎች በጽናት ተጋፍጣ አሁን ካለችበት ስፍራ ደርሳለች፡፡ ይህን የትእግስትን የዊኪፒዲያ ታሪክ ባዘጋጁት ሰዎች እምነት ትእግስት እውቀትን መደበኛ ትምህርትን መሰረት ያደረገ ዘመናዊ የሚድያ ስራን በማራመድ የበኩሏን አደራ ተወጥታለች፡፡ በሬድዮ እያስደመጠች ፤ ህትመት ሚድያ ላይ ብእሯን እያሳየች፤ በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ድምጹዋን እያሳማች በተለይ በኮሚኒኬሽን ዘርፍ ላይ ገጠር ከተማ እያካለለች ርካታን የሚፈጥር ታላቅ ተግባር አከናውናለች፡፡ በሚድያ ስራ ላይ ለተሰማሩ አዳዲስ ሴትና ወንድ የሚድያ ባለሙያዎች ትእግስት አርአያ ናት፡፡ ይህ በስኬትና በአርአያነት የታገዘ ጉዞ ጅማሮ እንደሆነ የምታምነው ትእግስት የቤተሰብ ሃላፊ ሆና ጥረቷን ትቀጥላለች፡፡ ነገ ደግሞ ተጨማሪ ታሪክ ስታክል ይጻፍላታል፡፡ ታሪክ ይህን በጽናት የተሞላ የትእግስትን የስኬት ጉዞ እነሆ መጪው ትውልድ እንዲያውቀው መዝግበነዋል፡፡