ታዬ አሰፋ (ዶ/ር)

ታዬ አሰፋ (ዶ/ር)

በመኖሪያ ቤቱ ከልጆቹ ቤዛዬ እና ጽዮን ጋራ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡

ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ዶክተር ታዬ አሰፋ ናቸው፡፡ ዶክተር ታዬ በስነ-ጽሁፍ መምህርነት ፤ በበሳል ተመራማሪነት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በአመራርነት ጉልህ ሚና የተወጡ ናቸው፡፡ በተለይ የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ ላይ ያገኙ በመሆኑ በሀገራችን የድርሰት ስራዎች ላይ ብዙዎችን ያስደነቁ የጥናት ወረቀቶችን ለህትመት አብቅተዋል፡፡ ዶክተር ታዬ የዛሬ 30 አመት ከ 5 ወር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በግፍ ከተባረሩ 41 ምሁራን መካከል አንዱ ሲሆኑ ከዚያም በኋላ ቤተሰብ ለማስተዳደር ኑሮ አስቸጋሪ ቢሆንባቸው በግብረ-ሰናይ ድርጅት ውስጥ የአርትኦት ስራዎችን ማከናወን ችለዋል፡፡ ዶክተር ታዬ ብዙ ሊነገርላቸው የሚገባቸው ባለሙያ ሲሆኑ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ያቀረበላቸውን ጥያቄ በአክብሮት በመቀበል የህይወት ታሪካቸውን በዚህ መልኩ እንድንሰንደው ፈቅደውልናል፡፡ ለዚህም የአክብሮት ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ የህይወት ታሪካቸውን ራሳቸው ፅፈው ሰጥተውናል።ቀሪ ታሪካቸውን በማንበብ ማን መሆናቸውን መገንዘብ ይችላሉ፡፡ እዝራ እጅጉ የህይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡

ታዬ አሰፋ (ዶ/ር)

አጭር የሕይወት ታሪክ

(ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ/ም)

ከገጠር ወደ ከተማ ሽግግር

እሱን ያጋጠሙት አስተማሪዎች (አንዱ ሩፋኡል ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ ዛፍ ሥር የሚያስተምር፣ ሌላው በአንድ ጉሮኖ መሳይ ክፍል ውስጥ የመንደር ልጆች ሰብስቦ የሚስተምር) ገበታ ሐዋሪያን በቃል እንዲደጋግሙ ከማድረግ ውጪ ጽሕፈት ለልጆቹ ስለማያስተምሩና ለንባብም ከዳዊት የተለየ መጽሐፍ ስለማያስነብቡ፣ ተማሪ ከዓመት ዓመት እዚያ ቆይቶ የነሱ የኑሮ መደጎምያ እንዲሆን የሚፈልጉ ይመስሉ ነበር፡፡ ስለዚህ ታዬ ዘመናዊ ትምህርት ወደሚሰጥበት እንዲስያስገባው አባቱን ስለወተወተ “ከታ” በሚባል ከከተማው ወጣ ባለ ሰፈር አዲስ በተከፈተው የሕዝብ ትምህርት ቤት አስገባው፡፡ የከታ አካባቢ ሜዳማና ድንጋያማ ቦታ ሲሆን ቀትር ላይ እባብ ይበዛባታል፡፡ ታዬ በባዶ እግሩ ወደ አራት ኪሎ ሜትር የሚሆነውን መንገድ ነጋ ጠባ ሲጓዝበት የአንድ እግሩ ጣት በተደጋጋሚ በእንቅፋት እየጓነች ጥፍሯ ወለቀና አልተካም አለ፡፡ አባቱን ያጠራቀመውን ገንዘብ መሬት በመግዛት ስለተጠመደ ለልጆቹ ልብስ መቀያየርና ጫማ መግዛትን እንደ አጉል ቅንጦት ነበረ የሚቆጥረው፡፡ ስለዚህ የሌሎችም ጣቶቹ ዕጣቸው ያው እንደሚሆን የተረዳው ታዬ ከሦስት ዓመት ትምህርት በኋላ ከታን እርም ብሎ ጓደኞቹ የሚማሩበት የመንግሥት ትምህርት ቤት ካልገባሁ አልማርም ብሎ ስላመፀ በ12 ዓመቱ ዐፄ ልብ ድንግል ወናግ ሰገድ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አራተኛ ክፍል ገባ፡፡ በንባብ ፍቅር የተጠመደው ዐፄ ልብነ ድንግል ትምህርት ቤት ከገባ በኋላ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ያኔ ፋሽን የነበረው የቻይና ሸራ ጫማ የተገዛለት በዚሁ ትምሀርት ቤት የ6ኛ ክፍል አገራዊ ፈተናን በጥሩ ውጤት ሲያልፍ ነበረ፡፡ ቦላሌ ሱሪም መልበስ የጀመረው ያኔ ነው፡፡

አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት

ያኔ የእንግሊዝኛ ትምህርት የሚሰጠው በደረቁ ሰዋስውና ቃላትን በማስተማር አልነበረም፡፡ በዚያን ጊዜ Green Primer, Red Primer, Reader I, Reader II, Reader III የሚባሉትን በማንበብ ሰዋስውንም ሆነ ቃላትን በዐውድ ውስጥ በማስገባት ተማሪዎች በተዘዋዋሪ እንዲማሩ ነበር የሚደረገው፡፡ የምንባብና አሳጥሮ የመጻፍ (précis) መልመጃዎችም ስለተካተቱ በትርክት የጣፈጠው ንባብ የጽሕፈትና አንብቦ የመረዳት ክሂሎትን ያዳብራል፡፡ በሰባተኛና ስምንተኛ ክፍሎች ደግሞ የአውሮፓ የወሸነኔ (romance) ልቦለዶች እንደ She, King Solomon’s Mines, Round the World in Eighty Days, Gulliver’s Travels, እንዲሁም የቻርለስ ዲከንስ A Tale of Two Cities እና የሼክስፒር ኦቴሎ፣ ሮሜዎና ዡልየት የመሳሰሉት ተውኔቶች ለተማሪዎች ዕድሜ በሚመጥን ደረጃ አጠርና ቀለል ተደርገው ስለተዘጋጁ በብዛት ያስነብቡ ነበር፡፡ በአማርኛም ከእንቅልፍ ለምኔ እና ታሪክና ምሳሌ ጀምሮ ጦቢያ፣ ልጅነት ተመልሶ አይመጣም፣ አርአያ፣ እንደ ወጣች ቀረች፣ ራስ ሤላስ (ትርጉም)፣ እንዲሁም ፍቅር እስከ መቃብር የመሳሰሉትን ልቦለዶች ሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ተካተው ተማሪው እንዲያነብ ይደረጋል፡፡

መምህራኑ ሌሎችንም መጻሕፍት ተማሪዎች ከቤተ መጻሕፍት ወይም ከግምጃ ቤት ተውሰው እንዲያነቡ ይገፋፉ ስለነበረ ያኔ የነበረው ሥርዓተ ትምህርት የተማሪዎችን የንባብ ፍቅርና ልምድ አብልጽጎ ነው ያለፈው፡፡ ንባቡ ደግሞ በሥነ ጽሑፍ መጻሕፍት የተወሰነ ሳይሆን ታሪክ፣ ጂዎግራፊና በተወሰነ ደረጃ ሳይንስንም ስለሚያካትት ዓላማው የቋንቋ ክሂሎትን ከማዳበር ባለፈ ሰፋ ያለ ጠቅላላ ዕውቀት ያለው አንባቢ ትውልድ መፍጠር ነበር፡፡ ያኔ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያስተምሩ የነበሩት የአሜሪካ የሰላም ጓድ መምህራንና እነሱም ሲሄዱ የተኳቸው ሕንዶቹ የተማሪን ችሎታ ከዚህ አንጻር በመኮትኮት ረገድ የራሳቸው በጎ ተጽዕኖ ነበራቸው፡፡ መምህራኑ ለልህቀት በሚሰጡት ትኩረት ተማሪን እርስ በርሱ በማወዳደር የተሻለ ውጤት ያመጣውንም ተማሪዎች በተሰበሰቡበት በማስሸለም ያበረታቱ ነበር፡፡ ታዬም በዚያ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ስላለፈ ዐፄ ልብነ ድንግል ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሮ አዲስ በተከፈተው ልዕልት ተናኘ ወርቅ ኃይለ ሥላሴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘጠነኛ ክፍል ሲገባ ጥሩ መሠረት ይዞ ስለነበረ በክፍሉ ውስጥ የላቀ ውጤት ከሚያስዘግቡት ተማሪዎች ተርታ ለመሰለፍ አላዳገተውም፡፡ በተለያየ ጊዜም የአካዳሚያዊ ክብር (Academic Honour) ባጅ፣ የምስክር ወረቀት እና መጻሕፍት ከትምህርት ቤቱ ለመሸለም በቅቷል፡፡

አሥራ አንደኛን ክፍል ከጨረሰ በኋላ ግን ስለ አዲስ አበባ የሚወራው ሁሉ ስላማለለው የት/ቤት ዲሬክተሩንና የመምራኑን ምክር ችላ ብሎ የልዑል በዕደ ማርያም ላቦራቶሪ ትምህርት ቤት የመግቢያ ፈተናን ተፈትኖ አለፈ፡፡ መምህራኑ የሚቃወሙት በሌላ ሙያ ለመሰማራት ዕድል ያላቸው ወጣቶች በመምህርነት ተወስነው እንዳይቀሩ ሲሆን፣ ዲሬክተሩ ደግሞ ብዙ ተማሪዎችን በ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና አሳልፎ ወደ ዩኒቨርሲቲ በማስገባት እሱም በአውራጃ ት/ቤቶች ሥራ አስኪያጅነት የመሾም ዕድል ስለሚኖረው ነበረ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር የበዕደ ማርያም ት/ቤትን በዩኔስኮ ድጋፍ የከፈተው ከአገሪቱ ትምህርት ቤቶች የተሻለ ውጤት ካላቸው የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች መርጦ በመውሰድ አንድ ዓመት አስተምሮ በትምህርት ፋከልቲ ውስጥ በመምህርነት ሙያ በዲግሪ ካሠለጠነ በኋላ በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመደልደል የትምህርት ጥራቱን ከፍ ለማድረግ በማለም ነበረ፡፡ ታዬ 12ኛን ክፍል በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ውስጥ በነበረውና በዘልማድ ላብ ስኩል በሚባለው ውስጥ አንድ ዓመት ተምሮ በ1965 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ፋከልቲ የ1ኛ ዓመት ተማሪ ሆነ፡፡

የዩኒቨርሲቲ ትምህርት

መሥሪያ ቤቱ በሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ በሚመራው በእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ሥር ሲጠቃለል ታዬም በ1968 ዓ/ም መደበኛ የመንግሥት ሠራተኛ ሆነ፡፡ በ1969 ዓ/ም ዩኒቨርሲቲው ሲከፈት ግን ሥራውን ትቶ ወደ ተማሪነቱ ተመለሰ፡፡ አንድ ሰሚስተር ከተማረ በኋላ ግን ሌላ ችግር ተከሠተ፡፡ ሠራተኛም ሆኖ ቢሾፍቱ እየተመላለሰ የኢኮፓን የፖለቲካ ሥራ ያካሂድ ስለነበረ በቀይ ሽብር ዋዜማ የመንግሥት ካድሬ ክትትል እየበረታ ቢመጣም የኢሕአፓ የከተማ የትጥቅ እንቅስቃሴና በድርጅቱ ሥር ያልታቀፉትን ሌሎች ታጋዮች ያለምንም መረጃ በመንግሥት ወይም በመኢሶን ደጋፊነት የመፈረጅ አባዜ ኹኔታውን ይበልጥ አወሳሰበው፡፡

ስደት ወደ ጂቡቲ

በቢሾፍቱ ውስጥ የኢኮፓ አባላት በመንግሥት ደኅንነትና ካድሬዎች ቅኝት ውስጥ እንዳይወድቁ በመጣር ላይ እያሉ ካላሰቡት አቅጣጫ ለጥቃት ተጋለጡ፡፡ የኢሕአፓና የወጣት ክንፉ አባላት የኢኮፓ አባላት ናቸው ብለው የጠረጠሯቸውን ታጋዮች የስም ዝርዝር በየአውራ መንገዱ በኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ላይ በመለጠፍ ለመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አጋለጧቸው፡፡ ጥቂት ቆይቶም በታዬ ሥር ሆኖ የሚንቀሳቀስ አንድ ብርቱ የኢኮፓ አባል በመንግሥት የጸጥታ አባላት ተይዞ ታሠረ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪና በጣም የሚቀርበው ሌላው ጓዱም በድንገት ደብዛው ጠፋ፡፡ መረቡ እየጠበበ መምጣቱን የጠረጠረው ታዬም ከሁለት ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ጓዶቹ ጋራ በመምከር ወደ ጂቡቱ ለመሰደድ መጀመሪያ ወደ ድሬ ደዋ አቀኑ፡፡ እዚያም ቀይ ሽብር መፋፋም ጀምሮ ስለነበረ በነሱ ዘመዶች ቤት ለጥቂት ጊዜ ተደብቀው ቆይተው ወደ ጅቡቲ የሚያደርሳቸው መንገድ መሪ ሲገኝ የተወሰነ መንገድ በባቡር ከተጓዙ በኋላ በመሀሉ ወርደው በረኻውን በእግር በማቋረጥ አንዲት አነስተኛ የጂቡቲ ከተማ ገቡ፡፡

ሁለቱ ጓዶቹ የተሰጣቸው የዘመድ አድራሻ ስለነበረ ፈልገው አገኙት፡፡ ሰውየው ጥቂት ቀናት ቤቱ ካሳደራቸው በኋላ የድንበር ከተማዋ ወታደራዊ አዛዥ ጽ/ቤት ቀርበው ካልተመዘገቡ እሱም እነሱም እንደሚታሠሩ ስለነገራቸው በማሳሰቢያው መሠረት በማግሥቱ የፈረንሳይ መኮንኑ ዘንድ ቀርበው ጥገኝነት ጠየቁ፡፡ መኮንኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪነታቸውን ካጣራ በኋላ በተደጋጋሚ የሚጠይቃቸው፤ 1ኛ/ ለምን የኢዲሕን ድርጅት ተቀላቅለው እንደማይታገሉ፣ 2ኛ/ የኢትዮጵያ ወይም ሌላ ወታደራዊ እንቅስቃሴን በመንገዳቸው ላይ አይተው እንደሆነ በዝርዝር እንዲነግሩት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ጅቡቲ ከፈረንሳይ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነበረች፡፡ የቀረቡላት ዐቢይ አማራጮችም፣ በፈረንሳይ አስተዳደር ሥር መቆየት፣ ነፃ ሀገር መሆን፣ ወይም ከሶማሊያ ጋራ መዋሐድ ነበረ፡፡ የደርግ መንግሥት የጂቡቲ ሕዝብ ከሶማሊያ ጋራ ለመዋሐድ ቢወስን በኃይል ጣልቃ በመግባት ለመቀልበስ በማቀድ፣ የአፋር ወጣቶችን መልምሎ በሽምቅ ውጊያ ያሠለጥን ስለነበረ ነው ፈረንሳዩ መኮንን በተደጋጋሚ ከነታዬ ስለ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መረጃ ለማግኘት የሞከረው፡፡

ነገር ግን አሉታዊ መልስ ሲሰጡት የናንተ ጉዳይ የሚወሰነው በጂቡቲ ነው በማለት ወዲያው በሚኒባስ አሳፍሮ ከፖሊስ አጃቢ ጋራ ወደ ጂቡቲ ዋና ከተማ ላካቸውና ለአንድ ተለቅ ላለ ፖሊስ ጣቢያ አስረከባቸው፡፡ እዚያም የቀረበላቸው ተመሳሳይ ጥያቄና እንዲሁም ጂቡቲ የሚያውቁት ሰው ይኖር እንደሆን ነበረ፡፡ ለመሰደድ የወሰኑት በችኮላ ስለ ነበረ ስለ ጂቡቲ በቂ መረጃ ባለማሰባሰባቸውና የሚቀበላቸው ሰውም ባለማዘጋጀታቸው የፈረንሳይ ፖሊሶች የሚፈልጉትን መረጃ ሊሰጡ ስላልቻሉ ምድር ቤት ባለ አንድ የእስረኛ ማቆያ ክፍል አስገብተው ከሌሎች ከከተማው ከተለቃቀሙ ስደተኞች ጋራ ዘጉባቸው፡፡ ክፍሉ ከአንድ ውሃ መያዣ ቆርቆሮ በስተቀር ምንም ዕቃ የሌለበት፣ በቂ ብርሃን የሌለውና ጠባብ ቢሆንም ብዙ ታሳሪ አልነበረውም፡፡ ነገር ግን ሕንፃው ፎቅ ላይ ካሉት ቢሮዎችና መኖሪያ ቤቶች የሚወጣው ፍሳሽ ወደ ክፍሉ ስለሚገባ ለመቆም ወይም ቁጢጥ ለማለት ካልሆነ በስተቀር ለመቀመጥ አያስችልም፡፡

የዚህ ዓላማው ታሳሪዎች ሁለተኛ ወደ ጂቡቲ ለመምጣት እንዳያስቡ ለማማረር ይመስላል፡፡ ያንን በየጊዜው የሚለቀቀውን ፍሳሽ በዚያ ቆርቆሮ እየቀዱ ወደ አንድ ቦይ ማፍሰስ የታሳሪዎቹ ፋንታ ነው፡፡ የፈረንሳይ ፖሊሶቹ ያንኑ ቆርቆሮ ታሳሪዎች በውሃ እንዲያለቀልቁት አድርገው ምንም ጣዕም የሌለው የተቀቀለ ሩዝ በሱ አድርገው ለታሳሪዎቹ ይሰጣሉ፡፡ የተጠየፈ ሆዱን ሲሞረሙረው ይውላል፣ ያድራል፡፡ ደግነቱ አንዲት ባለሆቴል ኤርትራዊ አዲስ ስደተኞች መምጣታቸውን ሰምተው ሳንድዊች አሠርተው ስደተኞቹ ኤርትራውያን እንደሆኑ ለማጣራትና ምናልባትም በዋስ ለማስለቀቅ፣ እስር ቤቱን ሲጎበኙ ያሰቡት ባይሳካም ሳንድዊቹን ለነታዬ አብልተው ስለሄዱ ለጊዜው ረኻቡን በሳንድዊቹ ትዝታ ለማስታገስ ተችሎ ነበር፡፡ እንድምንም ከታደረ በኋላ ፖሊሶቹ ታዬና ጓደኞቹን ከአንድ ሶማልኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊ ጋራ አዳብለው እያንዳንዱን ሰው እጆቹን በካቴና በማሰር በፖሊስ አሳጅበው በባቡር ካሳፈሩ በኋላ ኢትዮጵያ ድንበር ላይ በምትገኘው የደወሌ ጣቢያ ላሉ ፖሊሶች አስረከቧቸው፡፡ ሐበሾቹ የድንበር ፖሊሶችም ከነታዬ ይልቅ ያን ወጣት የሱማሌ ወጣት በየምክንያቱ ማዋከብና መጎሻሸም አበዙ፡፡

ምናልባትም የሶማሊያ ሰላይ ሊሆን ይችላል በማለት ፖሊሶቹ ጠርጥረውት ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜ የዚያድ ባሬ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመውረር እየተዘጋጀ ስለነበረና የምዕራብ ሶማሊያ ነፃ አውጪ ድርጅትና ሶማሊያ አቦ የሚባሉ ሸማቂዎችን በማደራጀት፣ በማሠልጠንና አሥርጎ በማስገባት ክርስቲያኑን ማኅበረሰብና የድንበር ጠባቂዎችን ያስጠቃ ስለነበረም ይሆናል ፖሊሶቹ በወጣቱ ላይ ያመረሩት፡፡ ወጣቱ ግን ተግባቢና መዝፈን የሚወድ፣ ስለ ፖለቲካ ደንታ የሌለው ነበረ፡፡ በሶማሊያ ወረራ ሥጋት ምክንያትም የደወሌ ጣቢያ ፖሊሶች እነታዬን ወደ መጡበት አገራቸው በጊዜ እንዲመለሱ መክረው፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ባቡር ሲመጣ አሳፍረው ያለአጃቢ ወደ ድሬ ደዋ ላኳቸው፡፡ ድሬ ደዋ በሶማሊያ ወረራ ሥጋትና በቀይ ሽብር ውጥረት ላይ ስለነበረች ታዬና ጓዶቹ ብዙም ሳይቆዩ ነው በባቡር ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት፡፡

የድኅረ ምረቃ ትምህርትና የዩኒቨርሲቲ መምህርነት

ከመጋቢት አጋማሽ 1969 ዓ/ም ጀምሮ አዲስ አበባ በመንጥር ዘመቻ ስትታመስና በኋላም የቀይ ሽብር አውድማ ስትሆን የዩኒቨርሲቲው ግቢዎች፣ በተለይ ከኢሕአፓና ከመኢሶን የልደት አዳራሽ ግርግር በኋላ፣ የድንጉጦች አምባ በመሆን አንጻራዊ ሰላም ነበራቸው፡፡ ያ ግርግርና ተኩስ ብዙ ተማሪዎች የኖኅ መርከብ በሚል የዳቦ ስም በወጣለት ፍልሰት ትምህርት አቋርጠው በየክፍለ ሀገሩ በመምህርነት የትምሀርት ሚኒስቴር ተቀጣሪ አደረገ፡፡ ያን አማራጭ ያልወሰደው የቀረው ተማሪ አንገቱን ደፍቶ በሚማርበት ጊዜ ታዬም አደብ ገዝቶ ትምህርቱ ላይ በማተኮር በ1969 ዓ/ም ሦስት ሰሚስተር ተምሮ የሦስተኛ ዓመት ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡ 1970 ዓ/ም ደርግ ኢሕአፓንና መኢሶንን በማሳደድ ብቻ ሳይሆን በሶማሊያና በሰሜን ጦርነትም የተወጠረበት ጊዜ ስለነበረ ትኩረቱን ወደ ዩኒቨርሲቲ አዙሮ በስፋት ለመመንጠር ብዙም ፋታ አላገኘም፡፡ የኢኮፓ ዋና ዋና መሪ ጓዶች ከፊሉ በእስር፣ ከፊሉም በስደት ስለተበታተኑ የተቀናጀ ትግል ለማካሄድ አዳጋች በመሆኑ ታዬም ትምህርቱን በትጋት ተያያዘው፡፡

በዓመቱ መጨረሻም በማዕረግ ተመርቆ የመጀመሪያ ዲግሪውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ አገኘ፡፡ በ1971 መጀመሪያ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በምሩቅ ረዳት መምህርነት ተቀጥሮ እንግሊዝኛ ማስተማር ሲጀምር በዚያው ጊዜም ዩኒቨርሲቲው በከፈተው አዲስ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ለ2ኛ ዲግሪው መማር ጀመረ፡፡ በአብዮቱ ምክንያት በርካታ የውጭ ሀገርና የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን መምህራን አገሪቱን ለቀው በመውጣታቸው ከፍተኛ የመምህራን እጥረት ተፈጠረ፡፡ የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብሩ እንዲጀመር ካስገደዱት ምክንያቶች ውስጥ አንዱም ይኸው የመምህራን እጥረት ሲሆን፣ ሌላው የውጭ ዜጎችን በኢትዮጵያውያን መምህራን የመተካት ፍላጎት (Ethiopianization) ነበረ፡፡

ስለዚህም ታዬ እንደ ማንኛውም የሙሉ ጊዜ አስተማሪ እያስተማረም፣ በተደራቢ ደግሞ እየተማረም በ1972 ዓ/ም መጨረሻ በሥነ ጽሑፍ የማስተርስ ዲግሪውን በማግኘት ተመረቀ፡፡ ኅዳር 1976 ዓ/ም ከብሪቲሽ ካውንስል በተገኘ ነጻ የትምህርት ዕድል ወደ እንግሊዝ አቅንቶ የመካከለኛው ምሥራቅና የአፍሪካ ጥናት ትምህርት ቤት (School of Oriental and African Studies/SOAS) በተባለ ስመ ጥር የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሎንዶን ተቋም ውስጥ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ የፒ.ኤች.ዲ. ጥናቱን ጀመረ፡፡ በሦስተኛው ዓመት ጥናቱን አጠናቆ በጥቅምት 1978 ዓ/ም የፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪውን አገኘ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመመለስም መደበኛ ሥራውን በቅድመ እና በድኅረ ምረቃ ትምህርት መርሐ ግብሮች በማስተማር ጀመረ፡፡

ከማስተማር ሥራው ጎን ለጎንም በአስተዳደርና በምርምር ሥራዎች በንቃት ይሳተፍ ነበረ፡፡ ለምሳሌ ከተለያዩ የኮሚቴ ሥራዎች በተጨማሪ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ረዳት ዲን፣ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት አባልና የትምህርት ምርምር ተቋም የቦርድ አባል ሆኖ አገልግሏል፡፡ እሱ የተማረበትን የማስተርስ ዲግሪ የሥነ ጽሑፍ መርሐ ግብር እንዲከልስ በዲኑ ታዞም ከበፊቱ የተሻለ ይዘት ያለውና ከሌሎች አገሮች ጋራ ተመጣጣኝ የሆነ መርሐ ግብር በማዘጋጀት አቀረበ፡፡ ይኸም በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ አካላት ከተመረመረ በኋላ ጸድቆ ለአራት ለአምስት ዓመታት በርካታ ተማሪዎች ተምረውበት በስተኋላ በተወሰነ ደረጃ እንዲከለስ ሆኗል፡፡ በምርምር ረገድም የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር ሆኖ ለአራት ዓመታት ከማገልገሉም በላይ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ላይ ጥናቶች በማድረግ በአገር ውስጥና በውጭ ታዋቂ የምርምር መጽሔቶች በማሳተም፣ በኢትዮጵያ ጥናት ዓለም ዐቀፍ ጉባኤዎችና ሌሎች ሲምፖዚየሞች ላይ በማቅረብና በመዋዕለ ጉባኤዎች በማሳተም በመስኩ ያለው ዕውቀት እንዲበለጽግ የራሱን አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ለዚህም ዕውቅና የዶክትሬት ዲግሪውን ባገኘ በአራተኛው ዓመት ማለቂያ ላይ ዩኒቨርሲቲው የተባባሪ ፕሮፌሰርነት የማዕረግ ዕድገት ሰጥቶታል፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በ1984 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበር እንደ አዲስ እንዲቋቋም ሲፈቅድ ታዬ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባልና ውይይት/Dialogue የተባለው የመምህራን ማኅበሩ የምርምር መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆኖ በመምህራን ጠቅላላ ስብሰባ ተመረጠ፡፡ ውይይት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበር መጽሔት ሆኖ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 1967 የተመሠረተ ሲሆን ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ተቋርጦ ቆይቶ እንደገና ለጥቂት ጊዜያት በሚምዎግራፍ መልክ ተባዝቶ ይሠራጭ ነበረ፡፡ 3ኛው ዙር የመጽሔት ኅትመት “አብሳሪ” ዕትም በማኅበሩ ምረቃ ላይ እንዲቀርብ በተወሰነው መሠረት ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የጥናታዊ ጽሑፍ ጥሪ ተደረገ፡፡ በቂ ምላሽ ስላልተገኘ ታዬና የአርትዖት ቦርዱ ያቀረቡትን አማራጭ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውም ስለተቀበለው በወቅታዊና አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳቦች እንዲንሸራሸሩ ዕውቅ ምሁራን ጽሑፍ እንዲያቀርቡ በቀጥታ እንዲጠየቁ ተወሰነ፡፡ ታዬም ታዋቂ ተመራማሪዎችን ቀርቦ በማነጋገር እሺታቸውን ገለጹለት፡፡

በዚሁ መሠረት “የሦስት ሺሕ ወይስ የመቶ ዓመት ታሪክ?” በሚል ርእስ ፕሮፌሰር (ያኔ ዶ/ር) ባሕሩ ዘውዴ፣ “ሥርዓተ ጽሕፈት” በሚል ርእስ ፕሮፌሰር ባዬ ይማም (ያኔ ዶ/ር)፣ “The Land Question and Reform Policy” በሚል ርእስ አቶ ደሳለኝ ራኅመቶ፣ እንዲሁም “Ethiopia at the Crossroads: Reflections on the Economics of the Transition Period” በሚል ርእስ ዶ/ር እሸቱ ጮሌ ጥናታዊ ጽሑፍ ሲያቀርቡ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘና አቶ ሰይፉ መታፈሪያም ወቅቱን የዋጀ ፖለቲካዊ ግጥሞችን አበረከቱ፡፡ እነዚህን ምርጥ ጽሑፎች በማካተት መጽሔቱ ተዘጋጅቶ መጋቢት 1984 ዓ/ም ለንባብ ሲቀርብ የብዙዎችን ትኩረት ሳበ፤ አፍቃሪ ኢሕዴጎችን ደግሞ የጽሑፎቹ ሒሳዊ አቀራረበ አበሳጨ፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደ ምሁር የጥናታዊ ጽሑፎቹን ፍሬ ነገሮችና ምክረ ሐሳቦች በጥሞና ቢመረምሩ ኖሮ ጥብቅና የቆሙለት ድርጅት ብዙ ከመሳሳቱ በፊት መስመሩን እንዲያስተካክል የሚረዱት ነበሩ፡፡ ከነሱ በተቃራኒ ግን በሕዝቡ ዘንድ በይዘቱ ወቅታዊነት ምክንያት ስለተወደደ የመጽሔቱ ዕትም ሦስት ጊዜ ቢታተምም ለሁሉም ማዳረስ ስላልተቻለ አንዳንዶቹ ጽሑፎች ከማኅበሩ ዕውቅና ውጪ በከተማው ውስጥ እየተባዙ በውድ ዋጋ መቸብቸብ ጀመሩ፡፡ በማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ያሉ በመጽሔቱ ይዘት የተከፉ አፍቃሪ ኢሕአዴጎችም የማኅበሩን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሰበብ አስባቡ በማመስ አሽመደመዱት፡፡ ዳግም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ሲደረግ በተፈጠረው ክስተት የተከፋው የአካዳሚው ማኅበረሰብ አዋኪዎቹን ሳይመርጥ ቢቀርም ታዬ ያለምንም ተወዳዳሪ ዳግመኛ ተመረጠ፡፡ መጽሔቱንም በጀመረው መልክ በመቀጠል ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ዕትሞችን አዘጋጅቶ ለንባብ አበቃ፡፡ ሆኖም ታዬና የመጽሔቱ አርትዖት ቦርድ አባላት የአፍቃሪ ኢሕአዴጎች ጥቁር በግ ሆኑ፡፡ ከአፎቱ የወጣው ስለትም ግዳዩን የሚጥልበትን ቀን አድብቶ መጠበቅ ጀመረ፡፡

ከዩኒቨርሲቲ መባረር

ሰላማዊና ሕጋዊ የነበረው የተማሪዎች ተቃውሞ በኃይል ከተዳፈነ በኋላ የመምህራን ማኅበሩ አባላት ተሰብስበው በተማሪዎች ላይ የተወሰደውን ከልክ ያለፈና አላስፈላጊ የኃይል እርምጃ በጽኑ አወገዙ፡፡ ለዚህም የውሳኔ ሐሳቡን አርቅቀው እንዲያቀርቡ ከተመረጡት አራት መምህራን አንዱ ታዬ አሰፋ ስለነበረ ይኼንኑ ለጠቅላላ ጉባኤው በንባብ አሰማ፡፡ የውሳኔ ሐሳቡ ከጸደቀ በኋላ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ፣ ለብዙኃን መገናኛና ለሌሎች በአገር ውስጥና በውጪ ላሉ ባለድርሻዎች በሰፊው ተሠራጨ፡፡ ይህን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲው ለአንድ ወር ከተዘጋ በኋላ በአዲስ ቦርድ ሥር እንዲተዳደር ተወሰነ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሲከፈት ግን ቦርዱ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ 41 የዩኒቨርሲቲ መምህራን እንዲባረሩ መወሰን ነበረ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ታዬ አሰፋ ነበረ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት የተፈረመው የስንብት ደብዳቤያቸው ለመባረራቸው ምንም ምክንያት አይገልጽም፡፡

ከተባረሩት መምህራን 24 የሚሆኑት ተሰባስበው ዩኒቨርሲቲው ያላግባብ ከሥራ እንዳባረራቸው በመግለጽ ዩኒቨርስቲውን በአዲስ አበባ የዞን ፍርድ ቤት ከሰው አስፈረዱበት፡፡ ዩኒቨርሲቲውም የተባረሩት መምህራን ከዩኒቨርሲቲው ጋራ በሕግ ፊት የሚጸና ምንም የሥራ ግንኙነት የላቸውም የሚል አሳፋሪ ሙግት በማቅረብ ይግባኝ አለ፡፡ ሆኖም የአ.አ. ክልል ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማጽናት የሥራ ውልን ያላግባብ በማፍረስ የስድስት ወር ደሞዝ፣ እንደዚሁም መምህራኑን ለእንግልት በመዳረግ የሦስት ወር ደሞዝ ካሳ እንዲከፍል ስለወሰነበት በዚሁ መሠረት ተፈጽሞ መምህራኑና ዩኒቨርሲቲው ተለያዩ፡፡ በነዚህ መምህራን መውጣት በርካታ በነሱ ይሸፈኑ የነበሩ ኮርሶች በወቅቱ ሳይሰጡ ቀሩ፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብም በፍርሃት ተዋጠ፡፡ ያልተባረሩ ጥቂት የማኅበሩ አመራሮች ስለተባረሩት መምህራን ለመነጋገር ካንዴም ሦስቴ ጠቅላላ ስብሰባ ቢጠሩም ምልዓተ ጉባኤ ሳይሞላ ቀርቶ ተበተነ፡፡ ለጋው ማኅበርም ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጸመ፡፡

ሕይወት መንግሥታዊ ባልሆኑ የምርምር ተቋማት ውስጥ

ታዬ ያገኘው ለኑሮው የተሻለ አማራጭ መንግሥታዊ ላልሆኑ ለውጭ ደርጅቶች በግል የማማከር አገልግሎት መስጠት ነበረ፡፡ በዚህ ረገድ አገልግሎት ከሰጣቸው አህጉራዊ ተቋማት ውስጥ የአፍሪካ ሕብረት፣ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት ልዑካን ጽሕፈት ቤትና በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ጽ/ቤት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ታዬ በብዛት ለአገር ውስጥና ለዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች የምክር አገልግሎት የሰጠው በአርትዖትና በትርጉም ዘርፍ ነበር፡፡ በገቢ ረገድ ይህ ከዩኒቨርሲቲውም እጅግ በጣም የተሻለ በመሆኑ በባንክ ዕዳ ቤቱ እንዲይሸጥበት የነበረበትን የዘወትር ሥጋት በአጭር ጊዜ አስወገደለት፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የአርትዖት ሥራ ከብዙ ጽሑፎችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሥራ ባህል፣ እሴትና የትኩረት ዘርፎች ጋራ ስላስተዋወቀው የዩኒቨርሲቲ ተማሪም ሆነ መምህር ሆኖ ያላገኘውን ዕወቀትና ክሂሎት አስጨበጠው፡፡

ይህም ትልቅ እርካታ ሰጠው፡፡ ሥራው በተለይ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በስፋት እንዲያነብና ስለ አገሩ ተጨባጭ ችግሮች በየጊዜው ከሚቀርቡለት የጽሑፍ ሰነዶች እንዲማር ዕድል የሚሰጥ ስለሆነ በዚህ ዘርፍ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ተቋሞች ተቀጥሮ መሥራትን እንደ ጸጋ ቆጠረው፡፡ የአርትዖት ተመክሮው በየጊዜው መበልጸግና የማኅበራዊ ዘርፍ ግንዘቤው መሻሻልም በዚህ መስክ ተቀጥሮ ለመሥራት በር ከፈተለት፡፡ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የማኅበራዊ ሳይንስ የምርምር ድርጅት (OSSREA) በተባለውና ጽ/ቤቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ውስጥ በሚገኘው የውጭ ድርጅት ውስጥ መጀመሪያ በተናጠል በአርትዖት የምክር አገልግሎት፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላም የድርጅቱ የኅትመትና የዶኩመንቴሽን ኃላፊ ሆኖ ለመቀጠር ቻለ፡፡ የድርጅቱን ለበርካታ ዓመታት ሳይታተሙ የተጠራቀሙ የምርምር ጽሑፎችን በማስገምገምና አርትዖት በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኅትመት አበቃቸው፡፡ የድርጅቱን የምርምር መጽሔትም (EASSRR) ወቅቱን ጠብቆ እንዲታተም አደረገ፡፡ አዳዲስ የምርምር ሥራዎች ሳይዘገዩ እንዲታተሙ በማድረግና የሥርጭት አድማሳቸው ከምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የድርጅቱ አባል አገራት ባሻገር ዓለም ዐቀፍ ተደራሽነት እንዲኖረው አመቻቸ፡፡ የድርጅቱ አፈጻጸም በለጋሾች ቡድን ሲገመገምም የኅትመት ውጤቶቹ ጥራትና የሥርጭት አድማስ ያረካቸው በመሆኑ ድጋፋቸውን አጥናክረው ለመለገስ ወሰኑ፡፡ ነገር ግን ጥቂት ቆይቶ የድርጅቱን ከፍተኛ አመራር ቦርዱ ሲለውጥ ይህን ተከትሎ የመጣው የሥራ ሁኔታ ስላላረካው ለአራት ዓመታት የሠራበትን ድርጅት በራሱ ፈቃድ ለቆ ወጣ፡፡

ለጥቂት ጊዜ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ውስጥ ሆኖ በሚንቀሳቀስ “የልማት ፖሊሲ ማኔጅምነት መድረክ” (DPMF) የተባለ የአድቮኬሲ ድርጅት ውስጥ ለመንፈቅ ያህል በኅትመትና ምርምር ዲሬክተርነት ከሠራ በኋላ የተሻለ ዓለም ዐቀፍ ተመክሮ አገኛለሁ በሚል ተስፋ ዋና መሥሪያ ቤቱ በአክራ (ጋና) ውስጥ የሆነው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ማኅበር ውስጥ ለኮሙኒኬሽንና አገልግሎት መምሪያ ኃላፊነት ተወዳድሮ ስለተመረጠ ተቀጠረ፡፡ ነገር ግን ከወቅት ወቅት የማይሻሻለውን የአክራን ሙቀትና ወበቅ ደገኛው ታዬ በቀላሉ ሊለማመደው አልቻለም፡፡ ደሞዙ ከመቼውም የተሻለ ቢሆንም ሥራው ግን እንዳሰበው ሠርቶ ልዩነት የሚያመጣበት ወይም አዳዲስ ነገር የሚማርበት ዓይነት ሆኖ ስላላገኘው በራሱ ፈቃድ ሥራውን ትቶ ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡

ከተመለሰ ብዙም ሳይቆይ የማኅበራዊ ሳይንስ መድረክ (Forum for Social Studies) ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ አብሮት እንዲሠራ ስለጠየቀው የድርጅቱ የኅትመትና ምርምር ዲሬክተር ሆኖ ማገልገል ጀመረ፡፡ ለአራት ዓመታት በዚህ ድርጅት ውስጥ በሠራበት ጊዜ በርካታ መጻሕፍት ታትመው በአገር ውስጥና በውጭ አገራት እንዲሠራጩ፣ ድርጅቱ ለአውሮፓ ሕብረት ተወካይ ጽ/ቤት ሁለት ፕሮጀክቶችን አቅርቦ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኝ፤ በከፍተኛ ት/ቤቶች ያለውን የአካዳሚ ነጻነት በሚመለከት ጥናት ተደርጎ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ጉባኤ እንዲያካሂድና የኢትዮጵያ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ጥንቅር እንዲዘጋጅና ታትሞ እንዲሠራጭ ቁልፍ አስተዋጽዖ አደርጓል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያና በተመረጡ የአፍሪካ አገራት የሲቪል ማኅበረሰቦች ያሉበትን ሁኔታ የሚቃኝ ጥናት ተደርጎ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የሲቪል ማኅበረሰቦች ጉባኤ አዘጋጀ፡፡ በዚሁ መድረክም የኢትዮጵያ መንግሥት የሲቪል ማኅበራት መተዳደሪያ ሕግ ሲነደፍ ዋና ባለድርሻ የሆኑትን የሲቪል ማኅበራት እንዲያሳትፍ ጥያቄ እንዲቀርብ፣ ይህንንም የሚከታተል አስተባባሪ ኮሚቴ እንዲመሠረት በማስወሰን ፎረሙ የማይተካ የማሳለጥ ሚና እንዲጫወት ጥረት አድርጓል፡፡

የዚህ ጥረቱ ውጤትም ሲቪል ማኅበረሰቡ ከወቅቱ የፍትሕ ሚኒስትር ጋራ በመተዳደሪያ ሕጉ ጉዳይ እንዲወያዩና ረቂቅ ሕጉ ሲወጣም በሲቪል ማኅበረሰቡ ሒሳዊ አስተያየት እንዲሰጥበት ከማስቻሉም በላይ የንቅናቄው መጠናከር ያሳሰበው ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ዜናዊ የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮችን ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ሰብስቦ ለማነጋገር ተገደደ፡፡ ውይይቱ በረቂቅ ሕጉ ላይ የነበሩት ተደራራቢ ቅጣቶችና ማነቆዎች እንዲቀንሱ እና ሕጉ ተፈጻሚ ከመሆኑ በፊት የአንድ ዓመት የመዘጋጃ ጊዜ እንዲሰጥ አስችሏል፡፡ ሆኖም አቶ መለስ በስብሰባው ላይ “የኢሕአዴግ የፈንጂ ቀጣና” በሚል የገለጻቸውን የሕጉን ሌሎች አፋኝና ኢዴሞክራሲያዊ ድንጋጌዎች በውይይት ማስቀረት አልተቻለም፡፡ ምክንያቱም በ1997 ዓ/ም አገራዊ ምርጫ ተቃዋሚዎች ሊያሸንፉ የቻሉት በሲቪል ማኅበረሰቡ ተሳትፎና ድጋፍ ነው የሚል ግምገማ ገዢው ፓርቲ ስለነበረው ያ ሁኔታ እንዳይገም የሲቪል ማኅበረሰቡን እንቃስቃሴ መጠርነፍ እንደ ስልታዊ አማራጭ ስለተወሰደ ነበረ፡፡ የፎረሙ ጥረት ግን ሲቪል ማኅበረሰቡ ተሰባስቦ ለጋራ ጥቅሙ በአንድነት እንዲታገል ፈር ቀዷል፡፡ ነገር ግን ሕጉ ተፈጻሚ ከሆነ በኋላ የተከሠተው ዐውድ ብዙም የሚያንቀሳቅስ ባለመሆኑ ታዬ ድርጅቱን ለቆ ወጣ፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ የፒ.ኤች.ዲ. መርሐ ግብር ለመጀመር ስለሚፈልግ አብረው ኮርሶቹን እንዲነድፉ በዶ/ር ዮናስ አድማሱ አማካይነት ጥያቄ ስለቀረበለት በበጎ ፈቃድ የሙያ አገልግሎት ለመስጠት ተስማማ፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ሳህለ ማርያምም ቡድኑን ተቀላቀለ፡፡ ለመነሻ የሚሆን የኮርሶቹን ዓይነት፣ የክሬዲት መጠን፣ የይዘት መግለጫና የጊዜ ርዝመት የሚያሳይ ረቂቅ በታዬ አዘጋጅነት ቀርቦ ሦስቱ ከተወያዩበት በኋላ ማሻሻያ ሐሰቦችን አቀረቡ፡፡ በግብረ መልሱ መሠረት የተሻሻለ መርሐ ግብር ረቂቅ ታዬ እንደገና አቀረበ፡፡ ይህን ከተቀበሉ በኋላ ዶ/ር ዮናስ የመርሐ ግብሩን ዳራና መግቢያ እንዲጽፍ ተደርጎ ይኸው በኮሚቴው ተቀባይነት ካገኘ በኋላ የመርሐ ግብሩ ፋይዳና የሚጠበቀው ውጤት ምንነት እንደገና በታዬ ተዘጋጀ፡፡ ከዚያም የመርሐ ግብሩ ባለቤት በሆነው የአማርኛ ቋንቋ፣ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት አማካይነት በተለያዩ የዩኒቨርሲቲው አካላት ውይይት ከተደረገበት በኋላ መርሐ ግብሩ ጸደቀ፡፡ የታዬ ሐሳብ የነበረው ለመርሐ ግብሩ ስኬት አስፈላጊው መጻሕፍት፣ የምርምር መጽሔቶችና በቂ የምርምርና ኅትመት ተመክሮ ያላቸው መምህራን ሳይዘጋጁ መርሐ ግብሩ እንዳይጀመር ቢሆንም እነዚህ በሂደት ይሟላሉ በማለት ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ጀመረ፡፡

ታዬም በትርፍ ጊዜ መምህርነት እንዲያስተምር በዚያው ባባረረው ዩኒቨርሲቲ ተጠይቆ ቅድሚያ ለመስኩ ዕድገት በሚል ማስተማር ጀመረ፡፡ ነገር ግን እንደተፈራው የተመራማሪ መምህራን እጥረት ብቻ ሳይሆን ከሚቀበላቸው ተማሪዎች ውስጥ የከፊሉ ለደረጃው የሚመጥን ቀዳሚ ሥልጠናና ዝግጅት ማነስም ከጊዜ ወደ ጊዜ በመርሐ ግብሩ ጥራት ላይ አሳሳቢ ተግዳሮት ደቀነበት፡፡ በመጨረሻም የሁኔታው እያደር አለመሻሻል ኅሊናው ከሚቀበለው በላይ ሲሆን ታዬ በፒ.ኤች.ዲ መርሐ ግብሩ ማስተማሩን አቆመ፡፡

ታዬ ከመደበኛ ሥራው በተደራቢ በምርምር አድማስ የራሱን አሻራ ለማኖር የቦዘነበት ጊዜ የለም፡፡ መጀመሪያ ከዩኒቨርሲቲው ከተሰናበተበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ በተለይም በልቦለድ ዘውግ በግሉ ጥናት እያካሄደ ውጤቱን በተለያየ የምርምር መጽሔቶች ላይ አሳትሟል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣ በኋላ ያሳተማቸው ምርምራዊ ሥራዎች ቋሚ የዩኒቨርሲቲ መምህር ከነበረበት ጊዜ እጅጉን ይበዛል፤ አሁንም ድረስ የምርምር ተሳትፎውን አላቆመም፡፡ እንደዚሁም በኢትዮጵያ ጥናት ዓለም ዐቀፍ ጉባኤና የሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ዓመታዊ ሲምፖዚየሞች (ለምሳሌ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ) ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርቧል፡፡ በሠለጠነበት መስክ ነጻ አገልግሎት በመስጠት ረገድም የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር መጽሔት የሆነው ብሌን ዋና አርታዒ በመሆን አራት ከወትሮው ለየት ያሉ ምርምራዊ ዕትሞች ለኅትመት እንዲበቁ ከአርታዒ ቦርዱ ጋራ ጥሯል፡፡

በአካዳሚያዊና ሌሎች የሙያ አስተዋጽዖዎቹ መነሻም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ መሥራች አባልና ም/ሊቀ መንበር በመሆን ለሦስት ዓመታት ለማገልገል ችሏል፡፡ በዚህ አካዳሚ ውስጥ በነፃ ሲያገለግል ካበረከታቸው ውስጥ አንዱ ቁልፍ አገራዊ አስተዋጽዖ ከሌሎች አምስት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ጋራ የኢትዮጵያን የቋንቋ ፖሊሲ ማርቀቅ ነበረ፡፡ ሐሳቡ የመነጨው ከአካዳሚው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሲሆን በኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ክትትልና ድጋፍ ፖሊሲውን የማርቀቅ ሥራ ከሐምሌ 2003 እስከ 2006 ዓ/ም ድረስ ተከናውኗል፡፡ ይህን ያህል ጊዜ የፈጀው ለፖሊሲው ግብአት እንዲሆን በየክልሉ ያለውን የቋንቋ አጠቃቀምና ዕቀዳ ደረጃ የዳሰሳ ጥናት ማድረግ፣ ዓለም ዐቀፍ ተመክሮን መቃኘትና በረቂቁ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት ግብረ መልስ በማሳባሰብ ረቂቁን ማበልጸግ ስላስፈለገ ነበረ፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊ አካላትና ምሁራን ተገምግሞ ይሁንታ ያገኘው ረቂቅ ፖሊሲ በመጀመሪያ ላይ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አማካይነት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሚመራው የኢፌዲሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ የቀረበ ቢሆንም በተለያያ ምክንያት ይሄ በወቅቱ ሊሳካ አልቻለም፡፡

ዓመታት ቆይቶም መለስተኛ ክለሳ ከተደረገበት በኋላ በመጨረሻ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሚመራው የኢፌዲሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ/ም ጸድቋል፡፡ በፖሊሲው ከተካተቱት ዋና ዋና ድንጋጌዎች ውስጥ በአንቀጽ 6 (1) (ሀ) “የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋዎች አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ፣ አፋርኛ ናቸው፡፡ ልሳነብዙ የፌዴራል ቋንቋ ሥርዓት ሕጋዊነት ወደ ፊት በሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ይረጋገጣል፡፡” የሚልና የአተገባበሩን ስትራቴጂ በሚመለከትም በቁ. (1) ላይ “ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የፌዴራል የሥራ ቋንቋ የሚሆኑበት የሕግ አግባብ በሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ይወሰናል፡፡ በፌዴራል ደረጃ የቋንቋዎቹ አጠቃቀም በሕገ መንግሥቱ ማእቀፍ በሚዘጋጁ ዝርዝር ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ይወሰናል፡፡” የሚል ይገኝበታል፡፡ ፖሊሲው በአንቀጽ 5 (3) ደግሞ “አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የተናጋሪዎቹ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በአፍ መፍቻ ቋንቋው ወይም በመረጠው የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ልጆቹን ቢያንስ ከአፀደ ሕጻናት እስከ 1ኛ ደረጃ ትምህርት መጨረሻ ድረስ የማስተማር፣ አፍ መፍቻ ቋንቋውን ልጆቹ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲማሩለት የመወሰን፣ ልጆቹ በመረጠው ቋንቋ የሚማሩበትን ትምህርት ቤት የመምረጥ ወይም ደረጃውን ጠብቆ በራሱ የማቋቋም መብት አለው፡፡” በማለት ዕውቅና ይሰጣል፡፡ ለፖሊሲው ስኬታማ አፈጻጸም የቋንቋ ጉዳዮች ምክር ቤት፣ የቋንቋ ጥናትና ምርምር ተቋምና የትርጉም ተቋም በሀገር ዐቀፍ ደረጃ እንደሚቋቋሙም በፖሊሲው ተደንግጓል፡፡

ሌላው የታዬ ሙያዊ አስተዋጽዖ የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ሲቋቋም አንዱ መሥራች አባልና የዚሁ ተቋም የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብአት ዘርፍ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ማገልገል ነበር፡፡ ኮሚቴው የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ጥራትን በሚመለከት፣ እንዲሁም በተመረጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ውስጥ የምርምር መካርነትን (research mentorship) ሁኔታ በሚመለከት የዳሰሳ ጥናቶችን እንዲካሄዱ በማድረግ ግኝቱን ለባለድርሻ አካላት አቅርቧል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የምርምር መጽሔቶች የጥራት ምዘናና ዕውቅና አሠራር (journal evaluation and accreditation practice) ጥናት እንዲካሄድ በአካዳሚው ዋና ዲሬክተር የተቋቋመው ሦስት አባላት ያሉት ዐጥኚ ቡድን አባልና ሰብሳቢ በመሆንም ታዬ በጥናቱ በትጋት ተሳትፏል፡፡ በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያን፣ የሌሎች የአፍሪካ አገሮችንና የዓለም ዐቀፍ ተመክሮዎችን መሠረት በማድረግ የተደረገው ጥናት ግኝትና የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ ለተለያዩ ባለድርሻዎች ከቀረበ በኋላ ታትሞ ለንባብ በቅቷል፡፡ ታዬ የአካዳሚው ምክትል ዲሬክተር ሆኖ ከተቀጠረ በኋላም የጥናቱ የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ አዲስ ለተቋቋመው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በአካዳሚው ዋና ዲሬክተርና በሱ አስረጂነት ቀርቦ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

በዚሁ መሠረትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማስፈጸሚያ መመሪያውን ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋሞች በማሠራጨት የምርምር መጽሔቶቻቸው እንዲገመገሙና የጥራት መስፈርቱን ያሟሉት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዕውቅና እንዲሰጣቸው ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡ አካዳሚውም የግምገማ ሥራውን እንዲያካሂድ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተወክሏል፡፡ ይኼን የግምገማ ሥራ የመምራት ኃላፊነትም አካዳሚው ለታዬ ስለሰጠ በዚሁ መሠረት ባለሙያዎችን አሰማርቶ ግምገማውን በማስፈጸም በመጀመሪያው ዙር ለዕውቅና ያመለከቱ 35 መጽሔቶች ተመዝነው 16ቱ መስፈርቱን ስላሟሉ ዕውቅና እንዲያገኙ ተደርገዋል፡፡ ከዚሁ ሥራ በተጓዳኝ በታዬ ይመራ በነበረው የእንግሊዝኛ-አማርኛ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት ዝግጅት ፕሮጀክት 97 ያህል በተለያየ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችን በማሰማራት 11,755 ሙያዊ ቃላት ተመርጠው ተተርጉመዋል፡፡ የአካዳሚውን ሥራ በራሱ ጥያቄ ከለቀቀ በኋላም መዝገበ ቃላቱን ለኅትመት በማዘጋጀት ሥራ ታዬ ዋናው ተሳታፊ ነው፡፡

ከአካዳሚያዊ ጉዳዮች ውጭም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ታዬ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ከሆኑት አንዱ ዘርፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ነው፡፡ በመጋቢት 30 ቀን 1985 ዓ/ም ከዩኒቨርሲቲው 41 መምህራን ሲባረሩ የተቃውሞ ድምፃቸውን ካሰሙት ድርጅቶች አንዱ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም ሲመራ የነበረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ነው፡፡ ታዬ በዚሁ ዓመት የድርጅቱ አባል በመሆን የመጀመሪያ ተግባሩ ስለ ሰብአዊ መብቶች ምንነት፣ መርሖች፣ አገራዊ ሕጎች፣ ዓለም አቀፍ ደንቦችና የትግል ተመክሮዎች በራሱ ንባብም ሆነ ከሌሎች መማር ነበር፡፡ ቀጥሎም የትምህርት ኮሚቴ አባል ሆኖ ሌሎች አባላትን ማንቃትና፣ ከዚያም በኢሰመጉ የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ውስጥ በአባልነት ተመርጦ ማገልገል ነበር፡፡ ኢሰመጉ የሚያወጣቸውን የሰብአዊ መብቶች ዘገባዎችና መግለጫዎች ማረምና ወደ እንግሊዝኛ መተርጎም አንዱ ሥራው ነበረ፡፡ በዚህ ረገድ ከሌላ አባል ጋራ በመሆን የተመረጡ ዓለም ዐቀፍ የሰብአዊ መብት ሰነዶችን (international human rights instruments) ወደ አማርኛ የተረጎመ ሲሆን ኢሰመጉ መጽሐፉን ካሳተመው በኋላ የኢፌዲሪ የፍትሕ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ዳጎስ ያለ ተመሳሳይ ትርጉም በርካቶቹን ክፍሎች በማካተት ታትሞ ለሕዝብ ተሠራጭቷል፡፡ በ1997 ዓ/ም የተደረገው አገራዊ ምርጫ ውጤት ተጭበርብሯል በሚል የተደረጉትን ተቃውሞዎች ለመግታት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት ከልክ ያለፈ የኃይል እርምጃ ግድያን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡ ታዬ ኢሰመጉን በመወከል ወደ ጄኔቫ (ስዊዘርላንድ) በመጓዝ እዚያ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን (በኋላ ምክር ቤት) ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚካሄደው መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰት ካንዴም ሁለቴ ዘገባ አቀርቧል፡፡

የኢሰመጉ ምክትል ሊቀ መንበር በነበረበት ጊዜም መንግሥት አዲስ ያወጣው አፋኝ የሆነ የሲቪል ማኅበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ዐዋጅ ስለሚያስከትለው ጉዳት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ላሉ የኢትዮጵያ የልማት አጋሮችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ማበራሪያዎችን አቅርቧል፡፡ ኢሰመጉ አዲስ በተፈጠረው የዐፈና ማሕቀፍ ውስጥ ህልውናውን አስጠብቆ እንዴት መቀጠል እንዳለበት ስትራቴጂ ነድፎ ለሥራ አስኪያጅ ኮሚቴና ለአባላት እንዲሁም ለአጋሮች በማቅረብና በማሳመን እንዲተገበር አድርጓል፡፡ በዚህ ጥረትም ኢሰመጉ ከአገር ውስጥ ቀጣይነት ያለው የገቢ ምንጭ እንዲኖረው በማቀድ ባለሁለት ፎቅ ቤት እንዲገዛ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከኢሰመጉ ደጋፊዎችም ገንዘብ በማሰባሰብ በባንክ የታገደበትን ገንዘብ ለማስለቀቅ በፍርድ ቤት ክስ እንዲመሠረት በማድረግ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ክርክር እንዲካሄድ አድርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ታዬ የኢሰመጉ የዕድሜ ልክ አባል ነው፡፡

ታዬ በ2012 ዓ/ም

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ዶክተር ታዬ አሰፋ በስም የሚታወቁ ነገር ግን ታሪካቸው ብዙም ያልተነገረ ለመሆኑ ብዙዎችን የሚያስማማ ነው፡፡ ባለፉት 44 አመታት በመምህርነት እና በተመራማሪነት ለዚህች ሀገር ያበረከቱት ጎልቶ ሊጻፍ ይገባል እንላለን፡፡ ምሁሩ ስነ-ጽሀፍን ማጥናታቸው ብቻ ሳይሆን ምሁራዊ ቅኝት ያለው ፤ በንባብ የሚያምን የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተቻላቸውን አድርገዋል፡፡ አካዳሚያዊ ነጻነት በዩኒቨርሲቲ እንዲሰፍን ብዙ የጣሩ ናቸው፡፡ ምሁርነትን ለንድፈ-ሀሳብ በዘለለ በተግባር ያሳዩ ናቸው ሲሉ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡ ዶክተሩ በህይወታቸው ብዙ ውጣ ውረድ ቢገጥማቸውም ዛሬም ከነፍሳቸው አስበልተጠው የሚወዱት የምርምር ስራ ቀልባቸውን ይገዛዋል፡፡ ዛሬም ለምርምር ንቁ ናቸው፡፡ የእኛ የስነዳ ፕሮጀክት አባላት የህይወት ታሪካቸው እንዲሰነድ ሲጠይቋቸው በሀሳቡ ትክክለኛነት ላይ ብዙም አላንገራገሩም፡፡ ፈቃደኝነታቸውንም ለመግለጽ እንደ ሌሎች አላስቸገሩንም፡፡ እንዲህ አይነት ያለፉበትን መንገድ ለታናናሾች ለማካፈል በር የሚከፍቱ መምህራን እንዲበዙ ብቻ ሳይሆን ሁሉም በራቸውን ወለል እንዲያደርጉ እንሻለን፡፡ የእኛ ትልቁ ግብ ለሀገሩ አንድ ጡብ ያኖረ በህይወት እያለ ታሪኩን ያካፍል የሚል ነው፤፡ ይህን ህልማችንን ለማሳካት ደግሞ ብዙዎች ከጎናችን እየሆኑ ነው፡፡ የዶክተር ታዬን ታሪክ እንዳነበብነው እርሳቸው ትልቅ የኢትዮጵያ ልጅ ናቸው፡፡ ወደፊት ሙሉ የህይወት ታሪካቸውን እንደሚጽፉ ባለሙሉ ተስፋ ነን፡፡ ለዛሬው ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ላሳዩት ትብብር አክብሮታችን ይድረሳቸው፡፡ ይህ ጽሁፍ በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ዛሬ መስከረም 9 2016 ከሌሊቱ 6 ሰአት ተኩል ተጫነ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *