ተፈሪ ለገሠ

ተፈሪ ለገሠ

ትሑቱ ጋዜጠኛ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ በስነጽሁፍ በቴአትርና በፊልም ዘርፍ ያሉ የተወሰኑ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የስነዳው ስራ ተጠናክሮ እየቀጠለ ሲሆን ይህም 2ኛው ዙር መሆኑ ነው፡፡ እኛ በአቅማችን የሰሩ ሰዎችን እያፈላለግን ያኖሩትን አሻራ ለምርምር ግብአት እንዲሆን አድርገን እያስቀመጥን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ባህር ማዶ ቢሄዱ እንኳን አሻራ እስካኖሩ ድረስ በህዝብ ዘንድ እንዲታወሱ እናደርጋለን፡፡

በዚህ ስራችን እንቀጥላለን፡፡ በተወዳጅ ሚድያ ቦርድ አጽዳቂነት የህይወት እና የስራ ታሪካቸው ሊሰራ ይገባል ያልናቸውን በተወዳጅ ሚድያ የዲጂታል መገኛዎችና በማህበራዊ ድረ-ገጽ ላይ እያስቀመጥን እንገኛለን፡፡ ትልቁ አላማችን በመረጃ እና በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ላይ እነማን አሉ እነማንስ ነበሩ? ብለን በጨረፍታ ለማሳየት ነው ትልቁ ሙከራችን፡፡ ያለቀለት ወይም የሁሉንም አሊያ የአብዛኛውን በዘርፉ ላይ ያለን ሰው ታሪክ ለማካተት ብንሞክር እንኳን ስራውን ከባድ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ አመት በ2015 መጨረሻ በምናሳትመው መዝገበ-አእምሮ ከ120 በላይ የመረጃ እና የመዝናኛ ዘርፍ ላይ ያሉ ሰዎችን ታሪክ ጠብቁ ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ተፈሪ ለገሰ ሲሆን በሚድያው አለም 30 አመት አገልግሏል፡፡ ተፈሪ በአሁኑ ሰአት መኖሪያውን ያደረገው በባህር ማዶ ሲሆን ይህ ታሪክ ፖስት ሲደረግ ተፈሪ የ57ኛ አመት ልደቱን ያከብራል፡፡ ተፈሪ በተለይ በዜና ፋይል የማይረሳ አሻራ ካኖሩት አንዱ ነበር፡፡ የህይወት ታሪኩ እንደሚከተለው ተጠናክሯል፡፡

አያ ተፈሪ

ሰውን ሲያከብር ኖር ብሎ ከወንበሩ የሚነሳ ፣ ከቁጥብ አንደበቱ በጎ ነገር የሚያሰማ ፣ ብእሩ አጫጭር ቃላትን የሚወዱ ፣ ከእኩዮቹ ሆነ ከታናናሾቹ ጋር ጓደኛ የሆነ የሰውነት ባለቤት ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ውስጥ ሰላሳ ዓመት አሳልፏል፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ራዲዮ ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና በመጀመሪያው የኤፍ ኤም ራዲዮ 97.1 ውስጥ ከዘጋቢነት እስከ ኃላፊነት ድረስ ሰርቷል፡፡

ሙያ እና ሰውነት የተጣመሩበት ÷ ሰውን በፍቅር ሰንደቅ የሚያነሆልል ÷ ራሱንም በትሕትና ዝቅ አድርጎ የሚኖረው ሕያው ሰው ተፈሪ ለገሰ ይባላል፡፡ ለስላሳ ድምጹ ለትረካ የተመቸ ፣ ዜናዎቹ በአጫጭሩ የሚፃፉ ፣ ለስፓርት ጥንቅሮች ልቡ የተከፈተ ፣ በተለያዩ አገሮች በመጓዝ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኝነት ድንበር ተሻግሮ እንዲከወን የልምድ ገጽ ሁኖ ሰርቶበታል፡፡ አገሩን እና የአገሬውን ነዋሪ የሚወድ ፣ ከሰው ጋር በሕብረት ለመኖር በምግባር የሚቀድም ፣ ሁልጊዜም ሰው ለመውደድ ወደ ኃላ አትበሉ የሚለው ተፈሪ ለገሠ የሙያ እና የሰውነት አርአያ መሆን የሚቻለው ነው፡፡

የመሰዋዕቱ ልጅ

የሶማሌ የመጨረሻው ፕሬዝዳንት የሆነው ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የእናት አገር ጥሪውን ተቀብለው ከዘመቱት ውስጥ አንዱ ናቸው የተፈሪ አባት፡፡ መጋቢ ሃምሳ አለቃ ለገሠ ገ/ሥላሴ ስለ አገራቸው በጦርነቱ ተሰው፡፡ በጎንደር ክ/ሃገር ጎርጎራ የተወለደው ተፈሪ ለገሠ እናቱ ወ/ሮ በተሃ መንግስቱ ይባላሉ፡፡ ለወላጆቹ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ተፈሪ ለገሠ እስከ ሶስተኛ ክፍል ትምህርቱን በጣና ኃይቅ ዳርቻ በጎርጎራ ነው የተማረው፡፡ አባቱ ከወታደርነት ወጥተው ወደ ሹፍርና ሲገቡ ወደ ጎንደር በመጓዝ ፃድቁ ዮሐንስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡ ከስድስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን አንዴ ጎንደር ሌላ ጊዜ ጎርጎራ እየለዋወጠ ተምሯል፡፡በዚህ መሃል ነበር ስምንተኛ ክፍል እያለ ወላጅ አባቱ በሶማሊያ ጦርነት ምክንያት ተሰዉ፡፡

ወደ ኩባ

ለአገራቸው ሲታገሉ ወላጆቻቸውን ላጡ ተማሪዎች የኩባ መንግስት የትምህርት ዕድል በመስጠቱ ያንን እድል ካገኙ አንዱ ኾነ፡፡ ከጎንደር ወደ ታጠቅ ጦር ሰፈር ከዛም በአሰብ ወደብ በኩል ቀይ ባህርን÷ ሜዲትራንያ ባህርን እና አትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጠው ወደ ኩባ ካመሩት አንዱ ተፈሪ ለገሠ ነበር፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኩባ ሰኔ 21 እና መንግስቱ ኃ/ማርያም ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ የ12ኛ ክፍል ሲያጠናቅቁ የተለያዩ የሙያ መስኮች ለመማር እንዲመርጡ ሲጠየቅ ተፈሪ ለገሠ የሚፈልገውን ጋዜጠኝነትን መረጠ፡፡

ተፈሪ ለገሠ ጋዜጠኝነትን ከመምረጡ በፊት ግን ከወጣቶች ደሴትና ሃቫና ከሚገኙ ሬዲዮ ጣቢያዎች ጋር መፃፃፍ ÷ ከጓደኞቹ ብር አሰባስቦ ሬዲዮ መግዛትና ሬዲዮ ሲያዳምጥ መዋል ÷ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት በየቀኑ ከትምህርት በኃላ አልጋቸው ላይ የሚጠብቋቸውን ጋዜጦች ማንበብ በጋዜጠኝነት ሙያ ሕይወቱን ለመቃኘት ተፅእኖ አድርጎበታል፡፡

ጋዜጠኝነትን የመማር ምርጫው ተቀባይነት አግኝቶ ከኩባ ርዕሰ ከተማ ሃቫና በአንድ ሺ ኪሎ ሜትር ርቀት ወደ ሳንቲያጎ ደ ኩባ በመጓዝ Universidad de oriente በተባለው ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ተምሯል፡፡ ከአምስት አመት በኃላ Licenciado en periodsimo በጋዜጠኝነት የማስተርስ ዲግሪውን ሰርቷል፡፡ በኩባ ትምህርትን ከስነ-ምግባር ጋር አጣምሮ አውቋል፡፡ ተፈሪ ከ 12 አመት የኩባ ቆይታ በኃላ በ 1983 ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል፡፡

በኢትዮጵያ ራዲዮ

የኩባ ትምህርቱን አጠናቆ መጋቢት 1983 ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ በግንቦት 9 ÷ 1983 ደግሞ በኢትዮጵያ ራዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት ሥራ ጀመረ፡፡ በ1983 ከደርግ ውድቀት እና ከኢህአዴግ መምጣት ጋር በነበረው ወቅት ዝናው በገነነው በኢትዮጵያ ራዲዮ ዜና ፋይል ቡድንን ተቀላቀለ፡፡ በአቶ ዳሪዮስ ሞዲ አለቅነት የሚተዳደረው ዜና ፋይል በዛን ወቅት ስማቸው የገነነው እነ ነጋሽ ማሃመድ፣ ንግስት ሰይፋ፣ አለምነህ ዋሴ፣ ዳንኤል ወልደሚካኤል (የክፍሉ ዜና ኤዲተር) ሌሎችንም ለመተዋወቅና አብሮ ለመስራት እድሉን አገኘ፡፡ ጋዜጠኝነትን በዩኒቨርስቲ ደረጃ ከኩባው Universidad de oriente ተምሮ ቢመጣም ÷ በተግባር የተማረው በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና ፋይል ነው ይላል ተፈሪ ለገሠ፡፡

በዜና ፋይል ከሪፓርተርነት እስከ አዘጋጅነት በዘለቀው የአመታት ቆይታው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ዜና እና ፕሮግራሞችን አቅርቧል፡፡ በለስላሳ ድምጹም በዜና አንባቢነት በኢትዮጵያ ራዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት ለአመታት አገልግሏል፡፡ የዜና ዘገባን በዜና ፋይል አዘጋጅ ሆኖ በቆየባቸው አመታት ከተለያዩ ቦታዎች ዘግቧል፡፡ የኦሎምፒክ ቡድናችን የዓለም ሻምፒዮና በድል የተመለሰው ራጮቻችንን አቀባበል በቀጥታ ፕሮግራም ሸፍኗል፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ዘገባዎችን ከጦር ሜዳ ጭምር በመስራት ሙያዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡

የቤተ – መንግስት የዜና ዘጋቢነት

ተፈሪ ለገሰ ሰላሳ አመት በቆየው የጋዜጠኝነት ሕይወቱ ውስጥ ለአስራ ሰባት ፤ ለአስራ ስምንት አመት የቤተ መንግስት የዜና ዘጋቢ ሆኖ ሰርቷል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ አብሮ በመጓዝ ለኢትዮጵያ ራዲዮ አልፎ አልፎም ለኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና ለአዲስ ዘመን ጋዜጣም ሽፋን ሰጥቶአል፡፡ በጋዜጠኝነት ሕይወቱም ለዘገባ ከአገር ቤት የምክር ቤት ዘገባዎች ፣ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባዎች ፣ ከተባበሩት መንግስታት ስብሰባዎችን ከቦታው በቀጥታ ለሕዝብ አድርሷል፡፡ በስራው አማካኝነት ከሃያ አምስት በላይ አገሮች መጓዝ ችሏል፡፡

በቤተ መንግስት የዜና አዘጋጅነት ውስጥ ከዜና ጥንቅር በተጨማሪ አገርን እና ተቋምን ወክሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ መንቀሳቀስን ስለሚጠይቅ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡ ሙያ እና ስነምግባር አስፈላጊዎቹ ግብዐት ናቸውም ይላል፡፡ በኢትዮጵያ ራዲዮ የስራ ቆይታው በስራ ወደ ጀርመን በመጓዝ ለስድስት ወራት የስራ ስልጠና በመውሰድ በጀርመን ራዲዮ ዶቸቨሌ አማርኛ ክፍል ዜና እና ፕሮግራሞችን በመስራት ለአድማጭ አቅርቧል፡፡ ተፈሪ ለገሠ በዜና ፋይል ከሪፓርተርነት እስከ አዘጋጅነት በቆየባቸው አመታት ዜና ከማጠናቀር ከማዘጋጀት በተጨማሪ አሁንም ድረስ በራዲዮ ጣቢያው ተደማጭ በሆኑት የሳምንቱ ታላቅ ዜና፣ ዓለም እንዴት ሰነበተች ፕሮግራሞች ላይ ሰርቷል፡፡

በፕሮግራም ክፍል ኃላፊነት

ተፈሪ ለገሰ በኢትዮጵያ ራዲዮ ጣቢያ የትምህርታዊ ፕሮግራም ክፍል ለሶስት ዓመት ኃላፊ በመሆን ለህፃናት ወጣቶች ሴቶች፣ ፓለቲካዊ እና ምጣኔ ኃብታዊ ፕሮግራሞችን፣ ከአድማስ ባሻገር እና ኢትዮጵያን እንቃኛት የመሳሰሉ ፕሮግራሞችን በስሩ ያቀፈውን ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን በተቻለው መጠን ለማሻሻል የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ተፈሪ ለገሠ በዜና ክፍል ሆነ በፕሮግራም ክፍል ኃላፊነት ቦታ እያለ ልዩ ፍቅር በነበረው ስፓርት መደበኛ ፕሮግራሞችን በመስራትም ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቭዥን ድርጅት በአንድ ላይ ሲዋቀር ወደ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በመዘዋወር አገልግሏል፡፡ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ቆይታው የዜና ክፍሉን አቀራረብ ለማሻሻል በተደረጉ ጥናቶች ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን የድርሻውን ተወጥቶአል፡፡ የ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 “አዲስ መረጃ” በሚል የዜና እወጃ ሲጀመርም በአዘጋጅነት አገልግሏል፡፡

ሰው ለመውደድ የተፈጠረው አያ ተፈሪ

ተፈሪ ለገሠ በትሕትና በሚኖርበት የሕይወት እና የሙያ ገጹ ውስጥ ሰውን መውደድ ዋነኛው ዓላማው ነው ፡፡ ለሙያው አጋዥ የሆኑ የአማርኛ ፣ የእንግሊዝኛ እና የስፓኒሽ ቋንቋ መረዳቱ ጥሩ ናቸው፡፡ ጣልያንኛ እና ፓርቹጊዝም እውቀቱም ደሕና የሚባል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬሽን በሰራባቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት አመት በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የስፓርት ክፍል ኤዲተር ሆኖ አገልግሏል፡፡ ተፈሪ ለገሠ ከ 1983 ግንቦት 13 እስከ 2013 ግንቦት 13 ድረስ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬሽን ለ 30 አመት በጋዜጠኝነት እና በአመራርነት አገልግሏል፡፡
ዳግም ብወለድ ጋዜጠኝነትን በተለይም ደግሞ ለሬዲዮ ፍቅሬ አይቆምም የሚለው ተፈሪ ለገሠ ከሁለት አመት በፊት ወደ አሜሪካ አቅንቷል ÷ ከባለቤቱ ወ/ሮ ገሊላ አፈወርቅ ጋርም ይኖራል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *