ብርሃኑ ገ/ማርያም ሙሳ

ብርሃኑ ገ/ማርያም ሙሳ

ብርሀኑ  ገብረማሪያም በወጣቶች ፕሮግራምና በከልጆች አለም ይታወቃል፡፡ ሌላም ብዙ ሰርቶአል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን  አሻራ ላኖሩ ሰዎች ክብር ስላለው ታሪካቸው እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ እነሆ ብርሀኑ ገብረማሪያም ማነው ብለናል፡፡

ትውልድ 

እናቱ ወይዘሮ ፋናዬ ገ/ማርያም ሲባሉ አባቱ ደግሞ  አቶ ደበበ ወ/ማርያም ይባላሉ፡፡ ብርሀኑ በመጋቢት 28 1969 ነበር የተወለደው፡፡  በአዲስ አበባ ከተማ ከልደታ ቤተ ክርስቲያን በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ልዩ ስሙ ጌጃ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነበር የተወለደው ፡፡  ወላጅ አባቱ በልጅነቱ በሞት በመለየታቸው ምክንያት በአባታዊ ፍቅርና እንክብካቤ አንድም ነገር ሳይጓድልበት ብርሃኑን ያሳደጉት አያቱ በመሆናቸው ስሙን ተከትሎ  የሚጠራው በአቶ ገ/ማርያም ሙሳ  ነው ፡፡ 

ገና የአምስት አመት ህፃን እያለ ቤተሰቦቹ በቀድሞ አጠራር በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በስራ ምክንያት አድራሻ በመቀየራቸው ብርሃኑም የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በኮተቤው ደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤት  ነበር ፡፡  በልጅነቱ በመኖሪያ ቤቱ ሁሌም የሚከፈትና የሚያደምጠው ሬዲዮ ብላቴናዊውን የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ምኞትና ፍላጎት ገና በአፍላነት ዕድሜው በውስጡ እንዲቀጣጠል ምክንያት ሆነው ፡፡

ልጅነትና ስነ ፅሁፍ

ብርሃኑ በኮተቤው ደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤት ቆይታው ግጥም እና አጫጭር ምክሮችን እየፃፈ በሬዲዮ እንደሚሰማቸው ጋዜጠኞች ለክፍል ጓደኞቹ ያነባል ፡፡ ይህን ጅምር አቅሙን ያጤኑ የአማርኛ መምህራኖቹ ደግሞ ርዕስ እየሰጡት መደበኛ የትምህርት መርሃ ግብር ከመጀመሩ በፊት ግጥም እያዘጋጀ ለተማሪዎች እንዲያነብ በማድረግ ያበረታቱት ነበር ፡፡  በዚያን ወቅት ብርሃኑ በሬዲዮ ከሚከታተላቸው ፕሮግራሞች ቀዳሚው ቅዳሜ ጠዋት የሚተላለፈው ከልጆች ዓለም የተሰኘው ፕሮግራም በመሆኑ በ 1020 የፖስታ አድራሻ  ግጥምና ለህጻናት ምክሮችን ይልካል ፡፡ የሚልካቸው የደብዳቤ መልእክቶች በተደጋጋሚ በሬዲዮ ይቀርቡለት ጀመር ፡፡

በሬዲዮ ስምህን ሰማነው የሚሉቱ ተበራከቱ ፡፡ የልጅነት ልቡ በሀሴት ተናጠች ፡፡ በመሆኑም ከልጅነት ጀምሮ በሬዲዮ ፍቅር የወደቀው ይህ ጋዜጠኛ፤ ጋዜጠኝነትን “ሀ” ብሎ የጀመረው ሀገር ተረካቢን ትውልድ በሚቀርጸው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ከልጆች ዓለም ለተሰኘው ፕሮግራም ፅሁፍ ከመላክ ባሻገር የራሱን ጽሁፍ በድምፁ ማቅረብ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

የልጆች ፕሮግራም ጅምር ተሳትፎና ቀጣይ ሽግግር

የልጆች ፕሮግራም ዝግጅት ክፍል ቢሮ የሚገኘው ባምቢስ የቀድሞው መካነ እየሱስ ግቢ ውስጥ ነበር ፡፡ ይህን ቢሮ ለማግኘት ደግሞ ብርሃኑ ብዙ ተንከራቷል ፡፡ ብዙም ድክሟል ፡፡ ቆይቶ ግን ያሰበው ተሳካ ፡፡ አዘጋጆቹንም አገኛቸው ፡፡ ፕሮግራሙ የሚቀረፀው አርብ አርብ ስለነበርም ከትምህርት እስከ መቅረት የደረሰበት አጋጣሚን ያስታውሳል ፡፡ በወቅቱ የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋሽ ሰለሞን ገ/ ስላሴ ብላቴናው ብርሃኑ  ከትምህርቱ ሳይዘናጋ  በፕሮግራሙ ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ  አሁን ላለበት የጋዜጠኝነት ሙያ እንዲበቃ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከተለት የሙያ አባቱ መሆኑን ተናግሮ አይጠግብም ፡፡

ከጋሽ ሰለሞን ጋር በህፃናት ፕሮግራም  ባሳለፋቸው ዓመታት ለሬዲዮ መፃፍ ምን ማለት እንደሆነ ፤ ቴክኒክና መርሁን በተከተለ መንገድ በተለይም አጭር ቀላል ግልፅ እና ቁጥብ  ቃላት ተመራጭ መሆናቸውን መረዳት እንዲችል ፤ በሬዲዮ ምስል ከስቶ እንዴት እንደሚፃፍ  በተግባር የመገንዘብ ዕድል አግኝቷል ፡፡  በልጅነቱም ግጥም ፤ ጭውውት  ፤ መነባነብ ፤ አጫጭር አስተማሪ ምክርና አስተያየቶችን  በየሳምንቱ ለማቅረብ የቻለበት ጅምር የጋዜጠኝነት ተሳትፎው መገለጫ ነው ፡፡ በወቅቱ አብረውት በፕሮግራሙ ውስጥ ይሰሩ ከነበሩት ህፃናት መካከል ዓለም አንተ አፋርደው ፤ አያልቅበት አደም ፤ ጥላሁን ሲዳ ፤ ስንታየሁ መለሰ ፤ ሉሊት ታፈሰ ፤ ቅድስት በላይ ፤ አስካለ ተስፋዬ ፤ እመቤት ወልደ ገብርኤል ፤ ትርሲት ተስፋዬ  ወ.ዘ.ተ ይጠቀሳሉ ፡፡  ብርሃኑ ከእነኚህ ተባባሪ አዘጋጆች ጋር የወንድምና እህት ያህል የሚቀራረቡ ሳምንት አልፎ ሳምንት እስኪመጣ የሚነፋፈቁ ፤ በሙያው በትብብር መስራት እንደሚቻል እና የመደጋገፍ ተምሳሌትነትን የተገነዘበበት የማይረሳ የእድሜው ምዕራፍ እንደሆነ ይመሰክራል ፡፡ በከልጆች ዓለም ቆይታውም ድምፁ ጎርምሶ ለማቆም እስከበቃበት ጊዜ የቀጠለ ሲሆን የጋዜጠኝነት ህይወቱ ግን ከልጆች ወደ ቅዳሜ ቀኑ የወጣቶች ፕግራም ተሸጋገረ ፡፡

ከባንቢስ ስቱዲዮ ወደ አቡነ ጴጥሮስየተሻገረው ጋዜጠኝነት ግቢ

ብርሃኑ ገ/ ማርያም ይበልጥ ደምቆ የወጣው በቅዳሜ ከሰዓት በሚተላለፈው የወጣቶች ፕሮግራም ነው ፡፡ የወጣቶች ፕሮግራም አዘጋጅ ሆኖ ክፍሉን ሲቀላቀል በወቅቱ የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅና ሃላፊ የነበረው በአሁኑ ወቅት በህይወት የሌለው ገጣሚና ጋዜጠኛ በቀለ ተሾመ ከጋሽ ሰለሞን ገ/ ስላሴ ብርሃኑን ተቀብሎ ይበልጥ በሙያው ሰርቶ የማሰራት አቅሙን እንዲያዳብር ገርቶታል ፡፡ አሁን ድረስ ከበቀለ በተቀበለው ልምድ  ሰርቶ በማሰራት ያምናል ፡፡ በቀለ ደግሞ የሬዲዮ ፕሮዳክሽን ላይ  ብርሃኑ አቅሙን እንዲያሳድግ ፤ በሬዲዮ ፕሮግራሞች ኤዲቲንግ ላይ ብቃት እንዲላበስ ፤ ለመስክ ስራ ወደ ክልሎች ወጥቶ ፕሮግራም ለመስራት የሚያስችል የጠራ የስራ እቅድ በማዘጋጀት ውጤታማ  ስራ እንዲያከናውን በማገዝ ፡ ላይቭ ፕሮግራም መስራት እንዲችል አቅሙን ገንብቶለታል ፡፡ ጀሚል ከፍልውሃ ፤ ሰለሞን በርሄ ፤ ሀይለ ዘ በቅሎ ቤትና የውቤው ልሳን ብርሃኑ ወጣቶች ፕሮግራምን በተቀላቀለበት ወቅት በብዕር ተሳትፎ ያደርጉ የነበሩ ተወዳጅ ፀሀፍት ነበሩ ፡፡ ከቆይታ በኃላ የቅርብ ጓደኛው ከነበረው አብዱራህማን አህመዲን ማለትም በብዕር ስሙ የቦሌው ሻሾ ጋር ቀስቱ ከኮተቤ በሚል የብዕር ስም የተለያዩ መጣጥፎችን ለማቅረብ መሰረት የሆኑት ከላይ የተጠቀሱት ጸሀፍት ናቸው ፡፡ በተለይ ከጋዜጠኛ ደረጀ ሃይሌ ጋር የቅዳሜ ከሰአት ወጣቶች ፕሮግራምን አብረው በመቀባበል ሲመሩ የነበረበትን ወቅት ብርሃኑ ሁሌም ያስታውሳል ፡፡ ከመላው ኢትዮጵያ በአቡነ ጴጥሮስ የስቱዲዮ ስልክ ቁጥር 12 88 10 የሚቀርቡላቸውን የአድናቆት አስተያየቶች አይዘነጋውም ፡፡

አሁን ድረስ አስገምጋሚ ድምጹ ሲሰማ “ይህ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ነው፤” በማለት በድፍረት መናገር የሚቻልለት ብርሃኑ በተለይ በወጣቶች ፕሮግራም ላይ ለበርካታ ታዋቂ ሰዎች አሁን ለደረሱበት ደረጃ የወጣቶች እንግዳ በማድረግ ልምዳቸውን በማካፈል ደረጃ ድምፃቸው እንዲሰማ የድርሻውን ተወጥቷል ። በጣም የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል አርቲስት ሱራፌል ተካ ፤ ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ ፤ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ ፤ ሰለሞን አለሙና የአፍለኛ ቴአትር ቡድን አባላት ፤ ባህር ዳር አንድ ምሽት ክለብ ውስጥ ገና ታዋቂ ሳይሆን ኢንተርቪው ያደረገው ማዲንጎ አፈወርቅ ፤ በርካቶች በካሴት ስራውና ተቀበል በሚል ተከታታይ ሙዚቃው የምናውቀው ድምፃዊ ጌትሽ ማሞ ካሴት ሳያሳትም  የሀገር መከላከያ ድምፃዊ በነበረበት ወቅት ሽሬ እንዳስላሴ ላይ ቃለ ምልልስ በማድረጉ ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ጌጡ ተመስገን የበኩር ስራውን እንዲያቀርብ የዕድል መስኮቱን የከፈተለት ብርሃኑ ነው ፡፡

 

ደራሲ እና ሀያሲ አንዷ አለም አባተ ( በአንድ ወቅት በትምህርቷ በጣም ሰነፍ የነበረች መክሊት የተባለች ተማሪ ራሷን በጥረቷና በእልህ አስጨራሽ ትግል ቀይራ የ12 ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤቷን አሻሽላ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ የመጀመሪያዋ የወርቅ ተሸላሚ መሆኗን በተመለከተ ብርሃኑ የሰራውን ፕሮግራም አዳምጦ በተፈጠረበት የመነቃቃት ስሜት በትምህርቱ ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ አስከ የሁለት ማስተርስ ባለቤት ለመሆን የበቃው በጋዜጠኛው ተፅዕኖ ፈጣሪ የሬዲዮ ፕሮግራም አማካኝነት ነበር ) እነኚህና ሌሎችም ገና ከመነሻቸው ብርሃኑ ከስራዎቻቸው ጋር ዕድል ሰጥቶ በበጎነት በሚዲያው ድምፃቸው እንዲሰማ በማድረጉ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ምስክርነታቸውን ሲሰጡለት ተሰምቷል ፡፡

አማተር የጋዜጠኞች ማህበራት፤ የስነ ፅሁፍና የቴአትር ክበባት በሀገራችን በስፋት በሚንቀሳቀሱበት የ 1980 እና 90ዎቹ ዓመታት ችሎታና አቅሙ ኖሯቸው የሚዲያ አማራጩን ላላገኙ ወጣቶች ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ከማድረግ አኳያ በበጎነት ብዙዎችን ታድጓል ፡፡ በሀገራችን ውስጥ በሁሉም ክልሎች በመንቀሳቀስ የተለየ አቅምና ችሎታ ያላቸው ወጣቶች ድምፅ እንዲሰማና ዝንባሌና ተሰጥዖ ያላቸውን ወጣቶች በማቅረብ ከስራና ህይወታቸው ጋር ከህዝብ ጋር እንዲታወቁ አድርጓል ፡፡ ቅዳሜ ከሰአት ወጣቶች ፕሮግራምን ነፍስ የዘራበትና ፕሮግራሙን ላይቭ ሲመራም በበርካታ አድማጮች ዘንድ ተወዳጅ የነበረበት ወቅት በተለይም የእርሱን ድምፅ ለመስማት በርካቶች ይጓጉ እንደነበር ይታወሳል ፡፡ በቆይታውም እጅግ አስቸጋሪና ርቀት ያላቸው ቦታዎች ላይ በህዝብ ትራንስፖርትና በጋማ ከብት ሳይቀር በመጓዝ  ሙያዊ ሃላፊነቱን ለመወጣትም ጥረት አድርጓል ፡፡

ከወጣቶች ፕሮግራም ውጭ በአዘጋጅነት የሰራባቸው ፕሮግራሞች

በቀጥታ ከስራው ጋር ተያያዥ በሆነ መንገድ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ዘርፍ ተመራቂ የሆነው ብርሃኑ ገ/ማርያም በወቅታዊ ፕሮግራም ፤ በሰኞ ምሽት የመዝናኛ ሙዚቃ ክፍለ ጊዜ በአዘጋጅና አቅራቢነት  ፤ ከአድማስ ባሻገር ፡ ከሳይንስ ማህደር ፤ በአንድ ወቅት እጅግ ተወዳጅና በርካታ አድማጭ የነበረው ዘወትር እሁድ ከ 10 እስከ 12 ሰአት ከወይን አሸት አስፋው ጋር ብርሃኑ  ያቀርብ የነበረው የዘፈን ምርጫና ልዩ የመዝናኛ ፕሮግራም በብዙዎች ልብ ውስጥ ያለና የሚታወስ ተወዳጅ ፕሮግራሙ ነበር ፡፡

የኢትዮጵያ ሬዲዮ ከኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ጋር በትብብር ያዘጋጅ የነበረው ፍጥጫ የተባለውን ፕሮግራም ባልደረባው ከነበረው ዳንኤል አያሌው ጋር ለፕሮግራሙ ፎርማት በመቅረፅ በአዘጋጅነት ለአመታት በስነ ተዋልዶና ጤና ላይ አዝናኝ አስተማሪ እና አሳታፊ ፕሮግራም በመላ ሀገራችን በሚገኙ የወጣቶች ማዕከላት በመገኘት አዘጋጅቷል ፡፡ የሬዲዮ መድረክ በኃላ ላይ ስሙ ተቀይሮ ኢቢሲ መድረክ ተብሏል ፡፡ የዚህ ፕሮግራም አዘጋጅ በመሆን በጥናት ላይ የተመሰረተ ዳሰሳ በማድረግ ምኒስትሮች ፤ ዲያሬክተሮች ፤ ኮምሽነሮች ፤የቢሮ ሀላፊዎች ፤ የፖሊስና የፀጥታ ክፍል ሃላፊዎችን እንደሚመሯቸው ተቋማት ስራና ተግባር በጥንካሬና ጉድለታቸው ላይ በማተኮር በቀጥታ ላይቭ ውይይት አድማጮች በስልክ ጥያቄ በማቅረብ እንዲሞግቷቸው አድርጓል ፡፡

ከሶስት አመት በፊት በኢትዮጵያ ሬዲዮ የፎርማት ማሻሻያ ሲደረግ ምክንያታቸው በማይታወቅ ምክንያት  አድማጮች እየወደዷቸው የተቋረጡ እንደ ኪነጥበባት ምሽት  ፤ መንገደኛው ጋዜጠኛ ፤ የብዕር ምልልስ ፕሮግራሞች ዳግም እንዲጀመሩ አድርጓል ፡፡ በሬዲዮ ጣቢያው ታሪክ የምሽት መዝናኛ ፕሮግራም መጀመር አለበት በሚል ዘወትር ቅዳሜ ከምሽቱ 3 እስከ 6 ሰአት የሚተላለፍ 180 መዝናኛ የተባለ ተወዳጅና አድማጭን አሳታፊ  የፕሮግራም ፎርማት በመቅረፅ ሰርቶ በማሰራት ላይ ይገኛል  ፡፡

ሰለቸኝ ደከመኝ የማያውቀውና በጋዜጠኝነት ፍቅር የወደቀው ብርሃኑ በሴቶችና በቤተሰብ ጉዳይ ላይ በአዘጋጅነትና አቅራቢነት ተሳትፏል። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም በባድመ ሽራሮ ግንባር ለወራት ቆይታ በማድረግ  በሞትና በህይወት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መረጃዎችን ለአድማጭ ጆሮ አድርሷል። በኢትዮጵያ በተካሄዱት ሀገራዊ ምርጫዎች ላይ በዘገባ ስራው በአንፃራዊነት ትክክለኛ መረጃን ለህዝብ ለማድረስ ታትሯል ። ብዙውን ጊዜ እንዳለመታደል ሆኖ የቴሌቪዢን ዘገባ ብቻ ጎልቶ ስለሚጠቀስ እንጂ በምርጫ 97 ወቅት ኢህአዴግ እና ተተፎካካሪ ፓርቲዎች ያደርጉት የነበረው ክርክር በኢትዮጵያ ሬዲዮ በቀጥታ ስርጭት ሁሉም ውይይት ሽፋን እንዲያገኝ ላይቭ ስርጭቱን ከስፍራው በመምራትና በማስተባበር ብርሃኑ ሚናው ከፍተኛ ነበር ፡፡

በተያያዘ በሀገራችን ውስጥ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን በተከናወነባቸው ትላልቅ ሀገራዊ ክንውኖች ላይ እንዲሁም የበአል የመዝናኛ የመድረክ ዝግጅቶችን በማስተባበርና ላይቭ ስርጭቶችን HOST በማድረግ ተሳትፎ ነበረው ፡፡ የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ መተላለፍ የጀመረውና በተማሪዎች መካከል በሚካሄደው ” የሊቀ ናይል ” የጥያቄና መልስ ውድድር ፕሮግራም ተማሪዎች በኢትዮጵያ የውሀ ሀብቶችና የተፋሰስ ሀገራቱ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በተለያዩ ክልሎች የተጓዘበት ርቀት መገለጫ አድርገው በርካቶች ይወስዱለታል ፡፡ በሬዲዮ እንግዳ ፕግራምም በርካቶችን እየጋበዘ ስራና ህይወታቸውን በጥናት ላይ ተመስርቶ ከማሳወቅ ባሻገር በቀጥታ ስርጭት አድማጮች ከሚወዷቸውና ከሚያደንቋቸው ጋር በማገናኘት አድናቆትና ጥያቄያቸውን  እንዲያቀርቡ አድርጓል ፡፡                            

ጋዜጠኛ ብርሃኑ ገ/ማርያም በኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ምን ሰራ ?

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዢን ድርጅት በአንድ መዋቅር በተዋሀዱበት ወቅት በቴሌቪዢን ዘርፍ ብርሃኑ የተለያዩ ሳምንታዊና መደበኛ ፕሮግራሞች አዘጋጅና አቅራቢ ሆኖ ሰርቷል ፡፡ በእሁድ መዝናኛ ፕሮግራም የሳምንቱ የመዝናኛው ዘርፍ ድንቃ ድንቅ ዜናዎችን በተከታታይ ይሰራ ነበር  ፡፡ በጥበብ ሰዎች የህይወት ሰብዕና ላይ ያተኮሩ አዝናኝ ሚኒ ዶክመንታሪ ፕሮግራሞችና የበአል እንግዶችን ያቀርብ ነበር ፡፡  ለአመታት ዘወትር እሁድ ከ2 ዜና ቀጥሎ ሲተተላፍ ቆይቶ የተቋረጠው ” ተሞክሮ ” የተሰኘ ሚኒ ዶክመንታሪ ፕሮግራም አዘጋጅ በመሆን በሀገራችን ብዙ ሰርተው ያልተዘመረላቸውን ግለሰቦች ስራና ህይወት በተመለከተ ያቀርብ የነበረው ፕሮግራም ለአጭር ጊዜም ቢሆን በተመልካች ዘንድ የሚወደድለት ፕሮግራሙ እንደነበር ይታወሳል ፡፡

በወቅቱ የብርሃኑ እንግዶች ከነበሩት መካከል የተወሰኑትን ለመጥቀስ ፕሮፌሸሸሰር ዝናቡ ገ/ ማርያም ፤ የአክሱም ሀውልት አስመላሽ ኮሚቴ አባልና የደራሲ ከበደ ሚካኤልን የህይወት ታሪክና ድርሰቶቻቸውን ያሳተሙላቸው ኢንጂነር ታደለ ብጡል ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር እሸቱ ወንጨቆ ፡  የሴቶች ግርዘትን የተመለከተ አንቀፅ በተ.መ.ድ ደንብ ውስጥ እንዲገባ ብርቱ ትግል አድርገው የተሳካላቸው ወይዘሮ ብርሃኔ ራስወርቅ ፤ የበግና የበሬ ቆዳ ቤት ለቤት ሰብስበው በመሸጥ ሆስፒታል ያሰሩት የቡታጅራው የልማት አባት አቶ በቀለ  አየለ ወ.ዘ.ተ ተጠቃሽ ናቸው ፡፡ በ 2002 ዓ.ም በሀገራችን በተካሄደው ምርጫ ወቅትም በኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ከነቀምት ላይቭ ዜናዎችን በመስራቱም እናስታውሰዋለን ፡፡ እ.አ.አ በ2017 በዱባይ የተካሄደውን ዓለም ዓቀፍ የገልፍ ፉድ የንግድ ትርኢትና ባዛር ከስፍራው የዜናና ፕሮግራም ሽፋን ከመስጠት ባሻገር በዱባይና አቡዳቢ በስደት ህይወት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ህይወት በተመለከተ መንግስት ትኩረት ማድረግ ያለበትን የህገ ወጥ ደላሎች ደባ ያጋለጡ ዘገባዎችን ሰርቷል ፡፡ በዩናይትድ አርብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያውያንን ህይወት የሚዳስሱ ፕሮግራሞችንም በቴሌቪዢን አዘጋጅቶ አቅርቧል ፡፡

መጠቀስ ያለባቸው ተሞክሮው

ጎምቱው ጋዜጠኛ ብርሃኑ ገ/ማርያም “ብርቆቻችን” እና “እንጎቻ” የተባሉ ሁለት መጽሄችንም በዋና አዘጋጅነት ለአንባቢ አብቅቷል። በየካቲት መፅኄት ፤ አዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በግል ጋዜጦች ላይ በብዕር ስም የተለያዩ ፅሁፎችን በማዘጋጀት ንቁ ተሳታፊ  እንደነበር ያስታውሷል ፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ለወጣቶችና በእሁድ ጠዋት ፕሮግራም መንግስትና ማህበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ዕፀፆችን በመንቀስ ፤ በማህበራዊ ኑሯችን ውስጥ የሚስተዋሉ ውሱንነቶች  ቀስቱ ከኮተቤ በሚለው የብዕር ስሙ አማካኝነት በበሳል ብዕሩ ከትቦ ከአድማጭ ጆሮ መልዕክት ለማድረስም የቻለ ጋዜጠኛ ነው ፡፡ 

ጋዜጠኛ በሁሉ ጉዳይ ላይ መሰረታዊ ዕውቀት ሊኖረው እንደሚገባ በጽንሰ ሀሳብ የሚቀመጠውን መርህ በተግባር መፈተሽ የሚወደው ይህ ጋዜጠኛ ሁሉንም ሞክሮ የነፍሱ ጥሪ ወደሆነችውና የጥበብ መገለጫ የመዝናኛ ፕሮግራም በማድላት በአዘጋጅነትና በአቅራቢነት እንዲሁም ሰርቶ በማሰራት ምሳሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም የመዝናኛ ዘርፍ ከፍተኛ ኤዲተርና ኃላፊ በመሆን ሁለተኛ ቤቴ የሚለውን የኢትዮጵያ ሬዲዮን በማገልገል ላይ ነው ።

ከኢትዮጵያ ውጭ በታንዛኒያ የአንድ ሳምንት ፤ እንዲሁም በቻይና ቤጂንግ እና የተለያዩ ግዛቶች ለ16 ቀናት ሙያዊ ስልጠና ከመቅሰም ባለፈ  ከአፍሪካና ላቲን አሜሪካ በወርክ ሾፑ ላይ ከተሳተፉ ጋዜጠኞች ጋር የልምድ ልውውጥ አድርጓል ፡፡ በቻይና የሚገኙትን ታላላቅ የሚዲያ ተቋማትንም የመጎብኘት ዕድል አጋጥሞታል ፡፡ የቻይናውን የዜና ወኪል XIN HUA ፤ CCTV እና CGTN እንዲሁም በቻይና የባህልና ሳይንስ ሙዚየም ውስጥ  የሚገኙትን በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሚዲያ ዘመን ላይ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩትን የሬዲዮ፤ የቴሌቪዢን የድምፅና ምስል መቅረጫ መሳሪያዎችን የመጎብኘትና የልምድ ልውውጥ በስፍራው ተገኝቶ አከናውኗል ፡፡

ብርሃኑ ገ/ማርያም  ከልጅነት እስከ አንጋፋነት በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ጥሪ ውስጥ ከነጻ አገልግሎት እስከ ፍሪላንሰርነት ከዚያም በቋሚ ሰራተኝነት በኢትዮጵያ ሬዲዮ የ30 ኣመት የሙያ ልምድ ያለው ጋዜጠኛ ነው ፡፡ ብርሃኑ ከልጅነት እስከ ጎልማሳነት አንድ ለእናቱ በነበረው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ለሶስት አስርት አመታት በማገልገል  ከሬዲዮ ስራ ባለመውጣት ለሚዲየሙ ያለውን ተአማኒነት አስመስክሯል  ፡፡ በጥሩ ሙያዊ ስነምግባሩና በስብእናው ለበርካቶች ምሳሌ መሆን የቻለ ጋዜጠኛም ነው ፡፡

የኢትዮጵያ ሬዲዮ በተዳከመበት ወቅት እንኳን እኛ የድርሻችንን ከተወጣን ኢትዮጵያ ሬዲዮ ከቀደመውም በላይ እንደስሙ የሀገር ኩራት ሆኖ ይቀጥላል በሚል ጽኑ እምነት በመያዝ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን የይዘትና አቀራረብ ማሻሻያ እንዲደረግ የራሱን አሻራ አሳርፏል ። በኢትዮጵያ ሬዲዮ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ውስጥ ዛሬም ድረስ ድምፁን የማናጣው ከወጣትነት ወደ አንጋፋነት በዘመን ቅብብል እየተሻገረ ያለው ብርሃኑ ገ / ማርያም የአለም የሬዲዮ ቀን ለሁለተኛ ጊዜ በሀገራችን በተከበረበትና  ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኞች ክብር በተሰጠበት የ2013 ዓ.ም የዓለም የሬዲዮ ቀን የህይወት ዘመን ምርጥ ጋዜጠኛ ተብሎ ተሸልሟል ፡፡

ማጠቃለያ 

ብርሀኑ ገብረማሪያም ጋዜጠኝነት ገና በልጅነት አሃዱ ብሎ ጀምሮት ዛሬ ላይ አድርሶታል፡፡ ሙያውን ወዶት እንደሚሰራ  ከታሪኩ መረዳት ይቻላል፡፡ ብርሀኑ በተለይ በቅዳሜ ለወጣቶች መሰናዶ  ላይ ሲሰራ  ከልብና በፍቅር  ስለሚሰራ ሊዋጣለት ችሎአል፡፡  ብርሀኑ ሙያውን ከልቡ ስለሚሰራ በክቡራን አድማጮች በቀላሉ የሚረሳ አይሆንም፡፡  በሀገራችን ከ1985 ጀምሮ ስላለው ወርቃማው የመዝናኛ የሬድዮ  ዝግጅት ስናነሳ በቀዳሚነት ብርሀኑ ከፊታችን ድቅን ይላል፡፡ እርሱና ባልደረቦቹ በዘመናቸው ብዙ ለፍተዋል፡፡ እውቅና አገኙ አላገኙ ሌት ተቀን ስራቸው ላይ ብቻ ትኩረት በመስጠት ዛሬ ታላቅ ከበሬታን ማግኘት ችለዋል፡፡ ያኔ የዘሩትን ዛሬ እያጨዱት  ይገኛሉ፡፡ ታላላቆቻቸውን እየሰሙ መልካም  ልምድን እያቃረሙ  የጋዜጠኝነት ጉዞአቸውን አሳምረውታል፡፡  ኢትዮጵያ ልጆቿን የማመስገን ፤ የልጆቿን ታሪክ የመሰነድ ፤ ያልተነገረላቸው ሰዎችን ታሪክ ከፊት ለማምጣት እነሆ የብርሀኑን ታሪክ በዚህ መልኩ አቅርበናል፡፡ ብርሀኑ ለወጣቱና ለልጆች  ሲሰራ ሲመክር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ አዲሱ ትውልድ  ብርሀኑን እንዲያውቀው አድርገናል፡፡ / ይህ ጽሁፍ ከብርሀኑ ገብረማሪያም የተገኘ ሲሆን  ዛሬ ሀምሌ 14 2013 ዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *