የአለም የፎቶግራፍ ድርጅት ያዘጋጀው የሶኒ አመታዊ የፎቶግራፍ አዋርድ በመጪው ሚያዝያ ወር ላይ ይካሄዳል ፡፡ ለዛ ውድድርም ከ 200 ሀገራት የተውጣጡ የፎቶ ባለሙያዎች የውድድር ስራቸውን ያቀርባሉ፡፡ ይህ ውድድር አመታዊ ሲሆን በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡ ለዚህ ውድድር ከመላ አለም 320000 የፎቶ ስራዎች ተልከዋል፡፡
አወዳዳሪው አካልም የውድድሩን አሸናፊ የሚያሳውቀው ኤፕሪል 19 2018 በሚደረገው ስነ -ስርአት ላይ ሲሆን በውድድሩ ምርጥ የተባለውን ፎቶ ያቀረበው የ 5000 ዶላር ሽልማት የሚያገኝ መሆኑ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም አሸናፊው ‹‹የአመቱ ምርጥ ›› የሚል ማእረግ የሚቀዳጅ ሲሆን የሶኒ ዲጂታል መሳሪያዎችንም ይሸለማል፡፡ ወደ ለንደንም ሄዶ እንዲዝናና እድሉ ይመቻችለታል፡፡ የውድድሩ ዳኞች አሸናፊውን ከማሳወቃቸው ቀደም ብሎ ወደ 15 የሚጠጉ ምርጥ ያሏቸውን ምስሎች አሳውቀዋል፡፡ እነዚህ ምስሎች https://www.worldphoto.org/ በሚለው – ገጽ ላይ የተጫኑ ሲሆን እንዲመለከቱ ተጋብዘዋል፡፡
ለውድድር ከቀረቡት 320,000 ምስሎች ውስጥ በዳኞች ምርጫ ምርጥ ከተባሉት አንዱ የክሪስ ሽሚድ የፎቶ ስራ ነው፡፡ ይህ ባለሙያ ያቀረበው አንድ በዱር የሚኖርን የዝንጀሮ ዝርያ ሲሆን ዝንጀሮው በኡጋንዳ የሚገኝና በግዙፍነቱም የሚታወቅ ነው፡፡ሌላዋ የውድድር አቅራቢ ቲና ስትሆን ቲና በኖርዌይ በተደረገው ውድድር ላይ አሸናፊ ለመሆን የቻለች ናት፡፡ ቲና በምስሉ ላይ ያነሳችው የ12 አመቷን ሊና ነው፡፡ ፎቶግራፈርዋ ስለ ሊና ስትናገር ‹‹ሊና ለእኔ ምቹ ናት፡፡ በፎቶግራፈርነት ባሳለፍኩት ዘመን ለእኔ ጥሩ ሞዴል ሆናለች፡፡ በቀላሉም መግባባት እንችላለን፡፡›› በማለት የፎቶ ባለሙያዋ ተናግራለች፡፡ በማስከተልም ‹‹ይህ ስራ እንደሚያሸንፍ እምነቴ ነው›› ስትል ሀሳብዋን ሰጥታለች፡፡
አቦሸማኔ በፎቶ አስቀርቶ ወደ ውድድሩ የተቀላቀለው ብሬንደር ክሬመር ይባላል፡፡ ብሬንደር ይህን አቦሸማኔ ለማግኘት ወራት እንደወሰደበት ይናገራል፡፡ በተለይ ከወንዝ ውሃ ፉት ሲል በካሜራ መውሰድ ፈታኝ ሆኖበታል፡፡ ቢሆንም ግን ሊሳካለት ቻለ፡፡ የፎቶ ግራፉ ርእስ ‹‹ አይን ለአይን ›› የሚል ሲሆን አቦሸማኔው ካሜራማኑን ፊት ለፊት ሲያየው ይታያል፡፡
ሌላው የፎቶ ባለሙያ ለፈረስ የተለየ ፍቅር እንዳለው ይናገራል፡፡ ዊቤክ አስ ይባላል፡፡ ‹‹ ብዙ ጊዜ ሰዎች ለምን ፈረስ ታነሳለህ ይሉኛል፡፡የምሰጠው ቁርጥ ያለና አንድ መልስ ነው፡፡ፈረስ ስለምወድ ነው ›› ሲል ይናገራል፡፡ በተለይ በመልካቸው የተለዩ ፈረሶች ይማርኩኛል›› ሲል ፎቶግራፈሩ ሰዎች ያነሳውን ምስል እንዲያዩለት ጋብዟል፡፡
ልጆች የቴክኖሎጂ ሱስ ውስጥ የሚገቡበት ጊዜ አለ፡፡በተለይ የአይፓድ ጌሞችን በመጫወት ጊዜአቸውን ያሳልፋሉ፡፡ በምስሉ ላይ ያለው ልጅ ከእንዲህ አይነቶቹ ተርታ ይመደባል፡፡ በምሽት ከበረንዳው ዳር ወጥቶ ጌሙን ሲጫወት እንመለከተዋለን፡፡
የዚህ ፎቶ አቅራቢ ቺን ቦንግ ሌንግ ይባላል፡፡ስፍራው ሰሜን ምእራብ ቻይና ሲሆን ጸሀይ ስትገባ በሚገባ ይታያል፡፡ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒክሽን ሚያዝያ 2018 የሚደረገውን የሶኒ ምርጥ ውድድር በተመለከተ አሸናፊው ከታወቀ በኋላ ሰፊ ዘገባ ያቀርባል፡፡