ስዩም ወልዴ
ውልደትና እድገት
ስዩም ወልዴ ጥር 7 ቀን 1935 ዓመተ ምህረት በመዲናችን አዲስ አበባ አራዳ አካባቢ ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ጎን ባለው ትልቅ ግቢ ውስጥ ተወለደ። ስዩም ከአምስት ወንድሞችና ከአንድ ብቸኛ እህቱ ጋር አድጓል። ለሀይማኖት እጅግ ቅርብ ከሆኑ ቤተሰቦች የተገኘ ነበርና ትምህርትን የጀመረው በቄስ ትምህርት ቤት ነበር።
የሃይማኖት ትምህርት
ስዩም ከ1946 ዓም ጀምሮ በጊዮርጊስ የዳዊት ትምህርት ይማር ነበር፡፡ በተወለደበት ግቢ የነበሩ የእድሜ እኩዮቹ ዘመናዊ ትምህርትን የሚማሩ ሆነው ሳለ እርሱ ግን በወቅቱ ለዚህ ሳይታደል በቄስ ትምህርት ቤት ውስጥ ህይወትን ሲገፋ ቆይቷል። ከዚህ ህይወት ወጥቶ እንደ ሰፈሩ ልጆች ፤ እንደ እድሜ እኩዮቹ ሁሉ ዘመናዊ ትምህርት መማርም የዘወትር ምኞቱ ነበርና ቶሎ የዳዊት ትምህርቱን አጠናቅቆ ዘመናዊውን ለመቀጠል ከጉጉት ጋር ዳዊቱን መድገም ቀጠለ።
ምንም እንኳን ዳዊት የሚያስደግሙት መምህሩ ብሩህ ጭንቅላት ያለው ልጅ በመሆኑ ዳዊትን ሲጨርስ ወደ ድቁናው እንዲገባ ቢፈልጉም ፤ ቤተሰብም ከዘመናዊው ትምህርት ይልቅ የሃይማኖት ትምህርቱን ብቻ አጥብቆ እንዲይዝ ቢመኙም ስዩም ግን አሻፈረኝ በማለት የዳዊት ትምህርቱን እንደጨረሰ ወደ ዘመናዊ ትምህርት ተቀላቅሏል።
ዘመናዊ ትምህርት
ስዩም ወልዴ ብሩህ አእምሮ የተቸረው ተማሪ ነበር። በተለይ ለታሪክ ትምህርት የነበረው ዝንባሌ ልዩ ነው። በታሪክ ፈተናዎቹ ውጤት ሁሌም ቀዳሚ ነበር። የታሪክ መምህሩ አቶ ምንውዬለት ሁንዴ እጅግ ይወዱትና ያቀርቡት ነበር ። ሁሌም ግን ፍጥነቱንና ችኩልነቱን አይወዱለትም።
አንድ ቀን እኚሁ መምህር የታሪክ ፈተናን እየፈተኑ ሳለ ፈጣኑ ስዩም እንደለመደው ሁሉ አፍታም ሳይቆይ ጨርሻለሁ ብሎ ወረቀቱን ለማስረከብ እጁን ሲዘረጋ በከፍተኛ ጩኸት ደግሞ ደጋግሞ አስቦበት እንዲሰራ አሳስበው ያስቀምጡታል። ስዩም ደግሞ ደጋግሞ ወረቀቱን ቢመለከተውም ምንም ሳይጨምር ሳይቀንስ መልሶ ወረቀቱን ሰጥቷቸው ከክፍል ወጥቶ ኳስ ጨዋታውን ይቀጥላል።
ሁሌም መቸኮሉን የማይወዱለት መምህሩ ጠርተውት የፈተና ወረቀቱን በደንብ አንብበው ብዬህ አልነበር ? ይሉታል እርሱም አንብቤዋለሁ ብሎ ይመልሳል። በኋላም ከጥያቄዎቹ አንዱን መዘው ሳራ በስንት ዓመቷ ሞተች ይሉታል ? (የመፀሃፍ ቅዱሷን የአብርሃምን ሚስት ነበር የጠየቁት) ። ስዩምም በ127 ብሎ መለሠ ። የፈተና ወረቀቱ ላይ የፃፈው ግን በ107 ብሎ እንደሆነ ሲያሳዩት ስዩም እጅግ ይደነግጣል። መልሱን እያወቀው በመቸኮል ብቻ 4 ማርክ እንደሚቀንሱበት 100 እንደማይደፍን ሲያውቅ እጅግ ይፀፀታል። ይህ ለትንሹ ስዩም ከባድ ግዜ ነበር። ምንም ይሁን ምን ግን ስዩም በትክክልም የታሪክ አዋቂ ነበር።
በጓደኞቹ ሲገለፅ
የስዩም ወልዴ አብሮ አደግ ጓደኛ አቶ ፍቅረማርያም ይፍሩ እንዲህ ይላሉ:- “ስዩም ታላቅ የስነጥበብ ሰው ነበር። የሚሰማውን የሚናገር ፤ የሚያየውን የሚተነትን ለጋስ ሰውም ነበር ። ያኔ ስነፅሁፍ ፣ ስነ ስእል ፣ ጋዜጠኝነት የሚባለው ጥበብ ሳይኖር የምንማረው ሳይንስን ፣ ታሪክንና ሂሳብን ነበር ስዩም ግን ከየት እንዳመጣው እንኳን ሳናውቀው ወደ ስነ ስእሉ ያደላ ነበር።
ስዩም ባገኘው ወረቀት ሁሉ መሳል የሚወድ ፤ መማሪያ ክፍላችን ውስጥ ባለ ጥቁር ሰሌዳ ላይ የእኛን የጓደኞቹን ወይ የመምህራንን ምስል በካርቱን መልክ የመሳል ችሎታ ያለው ልጅ ነበር። በተለይ ደግሞ ለታሪክ ቅርብ የሆኑ ጉዳዮች በዘመኑ የነበሩ የአፍሪካን ቀኝ ተገዢነት እና ነፃነት ፤ የጥቁር ህዝብ ተጋድሎ ሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች የስዩምን ቀልብ የሚገዙ ነበሩ።”
ገና በልጅነቱ የኪነ-ጥበብ አፍቃሪ የነበረው ስዩም ወልዴ ያገኘውን መፅሃፍ ማንበብ፤ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይትን ማድረግ ያስደስተው ነበር። ስዩም ስፖርተኛም ነበር፡፡ ቀንደኛ የእግር ኳስ ተጫዋች። ለባስኬት ኳስ እና ለእጅ ኳስም ቅርብ ነበር ። ይወዳቸዋል ። ይጫወታቸዋል። እኚህ መስካሪ ጓደኛው አቶ ፍቅረማርያምም በዚህ ሁሉ መሀል አብረውት ነበሩና እንዲህ ይገልፁታል።
” ትዝ ከሚለኝ ውስጥ አንድ ጊዜ የትምህርት ቤት መፅሄት እንድናዘጋጅ እድሉ ተሰጥቶን ብዙዎቻችን በርካታ የርዕስ ስሞችን ሰጠን። የአብዛኞቹ ስሞች ለፈረንጆች የቀረቡ ነበሩ ። ስዩም የሠጠው በኋላም በአንደኝነት የተመረጠው ርዕስ ግን ከሁሉ የተለየ ነበር ” የተማሪዎቹ ድምፅ” ይሰኛል፡፡ መምህራን እጅግ ወደዱት፡፡ አንደኛም ወጣ። እኔም ያየበትን መንገድ ዛሬም ድረስ አደንቀዋለሁ።”
አንዱን ካንዱ ጋር ማቀራረብ፤ ሰዎች ተሰባስበው ተወያይተው ቁም ነገር እንዲሰሩ ማድረግ የስዩም ባህሪያት ነበሩ። ስዩም ላመነበት ሁሉ የሚታገል ፣ የማይወላውል ስህተት ሲመለከት ፊት ለፊት የሚናገር፤ በሰው እኩልነት የሚያምንና ሰዎች በሃገራቸው እንዲመኩ ሀገራቸውንም እንዲወዱ የሚመክር ፣ የሚዘክር መልካም ጓደኛችን ነበር የሚሉት ደግሞ በትምህርት ቤት አብረዋቸው የተማሩና ከ1957 ጀምሮ እስከ ህልፈቱ ድረስ ጥሩ ወዳጅነት የነበራቸው ወይዘሮ ቀለመወርቅ ታምራት ናቸው።
ጋዜጠኝነት
ስዩም 12ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቅ በመለስተኛ የስዕል ኤግዚቢሽን የሳላቸውን ስዕሎች አሳይቶም በጣም ተወዶለት ነበር።
በ1958 ዓም ልክ በ22 ዓመቱ የስዩም ወልዴ አዲስ ምዕራፍ ተጀመረ። ይህንንም ወቅት ጓደኛው አቶ ፍቅረማርያም እንዲህ ያስታውሱታል። “12ኛ ክፍልን እንደጨረስን ክረምት ላይ በሚወዱትና በሚያደንቁት ሰዎች ጋባዠነት “በብስራት ወንጌል” ራዲዮ ጣቢያ ውስጥ በፍሊራንስ ጋዜጠኝነት መስራት ጀመረ።በኋላም ከፍሊራንስነት ወደ ቋሚነት ተሸጋግሮ ሰርቷል።
ስዩም ወልዴ ብስራት ወንጌል ራዲዮ ላይ በሚያቀርባቸው ዝግጅቶች በአጭር ግዜ ውስጥ በአድማጭ ዘንድ ተወዳጅ ሆነ።እንደብዙዎቹ እምነትም ስዩም በአጭር ጊዜ ውስጥ በእጁ ያለን ብረት ወደ ወርቅነት የመቀየር ያህል ጥበብ ነበረው።
ስዩም ከራዲዮ ጋዜጠኝነቱ ባሻገር ለጋዜጦችም ይፅፍ ነበረ። ጥልቅ አንባቢው ስዩም የሚፅፋቸውን ፅሁፎች ታላላቅ ደራሲያን ሳይቀር አሳደው ያነቡለት ነበር። በብስራት ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ አራት አመታት ያህል ያገለገለ ሲሆን በነዚህ አመታት የነበረውን ጊዜ እጅግ አስደሳች እንደነበረ ” ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ” በሚለው ፅሁፉ ላይ አስፍሮት ነበር።
ሃያሲነት
ስዩም ወልዴ ከብስራተ ወንጌል ቆይታው በኋላ ያቀናው ወደ ራሺያ ነበር። በሩሲያም ለስድሰት ዓመታት ያክል በትምህርት አሳልፏል። ከራሺያ ከተመለሠ በኋላ የስነ-ጥበብ ሃያሲነቱ እና ለስእል የነበረው እውቀት በትምህርት ታግዞ እጅግ ከፍ ብሎም ነበር።
ከ1968 በኋላ በሃገሪቱ አለ የተባለ ሀያሲም ነበር ስዩም። በተለይ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ለተከታታይ ስድስት ወራት ያቀረባቸው ፅሁፎች ይህንኑ ያስመሰከሩና ታላቅ ከበሬታን ያስቸሩት ነበሩ። በነዚህ የኪነጥበብ ስራዎቹም ከበርካታ ሰዎች ጋር ሊተዋወቅ ችሏል። ከነዚህ አንዱ ደግሞ ሰአሊ እሸቱ ጥሩነህ አንዱ ነበርና ስዩምን እንዲህ ይገልፀዋል።
” ስዩም በዘመኑ የነበርን ሰአሊያንና ደራሲያን ሙዚቀኞች በአጠቃላይ የኪነ-ጥበብ ሰዎች አንድ አካባቢ ቤት ሰርተን ሰብሰብ ብለን እንድንኖር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። በተለይ ለሰአሊያን ያለው ፍቅር ልዩ ነበር። እባካችሁ ስዕል ስሩና እኔም ሂስ ልስጥበት ሞያውም ይደግ እያለ ይለምነን ነበር። በኋላም እኔ በ1982 ዓም መጋቢት አምስት ቀን አንድ የስዕል ኤግዚቢሽን ስከፍት ለዚያ መግቢያ አንድ ፅሁፍም ፅፎልኝ ነበር። ስዩም የዚህን ያህል ሙያውን ወዳድ ነበር።
መምህርነት
ስዩም ወልዴ ከጋዜጠኝነት፣ ከሰዓሊነትና ከሀያሲነት በዘለለ ጎበዝ መምህርም ነበር። በመምህርነት ዘመን አብረውት የነበሩት አቶ ታደሰ በላይነህ ያን ዘመን እንዲህ ያስታውሱናል። ” በሞያዬ ቀራፂ ነኝ ከ1962 ዓመተ ምህረት ጀምሬ በስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት መምህርም የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተርም ነበርኩ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነበር ከስዩም ወልዴ ጋር የምንተዋወቀው፡፡ ስዩም ትምህርቱን ፈፅሞ ከውጭ ሲመለስ በዚህ ትምህርት ቤት መምህር ሆኖ ሲቀጠር ያኔ ለእኛ ትልቅ እድል ነበር። ምክንያቱም በሙያው የሰለጠነ በሀያሲነት ትምህርት የሚሰጥልን አልነበረንምና። ስዩም በጣም ጎበዝ መምህር ነበር ። ብዙ ያድጋል ለሀገርም ይጠቅመናል ባልንበት ዘመን በህይወት አጣነው።”
ዳግማዊ ስዩም የስዩም ወልዴ ሁለተኛ ልጅ ሲሆን አሁን ላይ የ42 ዓመት ወጣት ነው። ዳግም አባቱን በህይወት ሲያጣው ገና 13 ዓመቱ የነበረ ቢሆንም አባቱ በውስጡ የነበረውን የስዕል አቅም እያየ የሚያበረታታው ፣ የሚያግዘው ፣ እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ትልቅ ሰው የሚያዋየውና ነገሮችን በትኩረት እንዲረዳ መንገዱን የሚያሳየው እንደሆነ ይናገራል።
ስዩም ወልዴ ጎበዝ አንባቢ ነበር ። ሲያነብ ደግሞ ሙዚቃን ያደምጣል። አዘውትሮ የሚያደምጠው ሙዚቃ ኦፔራን ሲሆን ከሃገራችን ደግሞ የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደን” ባለዋሽንቱ እረኛን” በጣም ይወደዋል።
በልጆቹ ሲገለፅ
ስዩም ወልዴ በብዙ ኃላፊነቶች ተወጥሮ እንኳን ለቤተሰቦቹ ፣ ለባለቤቱ ፣ለልጆቹ፣ ለወዳጆቹና ለተማሪዎቹ የሚሰጠው ጊዜ ነበረው። የስዩም ወልዴ የበኩር ልጅ መካኒካል ኢንጂነሩ ራምሴ ስዩምም ስለአባቱ እንዲህ ይላል። ” በርካታ የጥናት ስራዎችን በመስራቱ የረዳት ፕሮፌሰርነት ማእረግን በሚያገኝበት ወቅት ላይ ነበር አባቴን ያጣነው። አሁን ላይ እኔ ያለሁበትን ዘመን ሳስበው በትንሹ የምንደክም ራሳችንን ቢዚ የምናደርግና የማንጠያየቅበት ደረጃ ደርሰናል። አባቴ ግን አይደክመውም ።የሰፈሩ እድር ሰብሳቢእና ምርጥ ጎረቤት፤ ለኛም ጥሩ አባት ፤ ለጓደኞቹም መልካም ጓደኛ ፤ ለዘመድ ወዳጅ አለኝታ ነበር። ለእናቴም ምርጥ ባል እና የህይወት አጋሯ ሆኖ አልፏል። ሁሌም አደንቀዋለሁ።”
ስዩም ወልዴ ከውልደቱ ጀምሮ አስር አመት እስኪሞላው ድረስ ከኖረበት ከሃገር ፍቅር ትያትር ቤት ጎን በተጨማሪ ታች ግቢ ፣ ስርቆሽ በር፣ስድስት ኪሎ፣ መርካቶ ፣ ሰፊ ሰፈር ፣ ራስ መኮንን ድልድይ እና አቧሬ አካባቢም ኖሯል። በመጨረሻም እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ድረስ በቦሌ መድሃኒያለም አካባቢ በሰራው መኖሪያ ቤቱ ነበር።
ስዩም በኖረባቸው ሰፈሮች ሁሉ ከትልቁ ግቢ ጋር ሲነፃፀር የነበረው ማህበራዊ ህይወት እጅግ የላላ ነበር። ምንም እንኳ በቤተሰቦቹ የተከበበ ቢሆንም ስዩም ግን አንድም ቀን ምቾት ተሰምቶት አያውቅም። በሰው መሀል ሆኖ ብቸኝነት ያጎሳቆለው ይመስልም ነበር።
ቤተሰብ ምስረታ
ስዩም ምኞቱን ሲያሳካ ከወይዘሮ መሠረት ባልቻ ጋር ትዳር ሲመሠርትና ልጆች ሲወልድ ግዜ አልፈጀበትም ። ትዳሩን የሚወድ፤ ቤቱ የሚናፍቀው ፤ ልጆቹ ጋር አብዝቶ መሆንን የሚመርጥ ሰውም ነበር።
ወይዘሮ ቀለመወርቅ ታምራት ከስዩም ወልዴ ቤተሰቦች ጋር ጥብቅ ቅርርብ አላቸው በዘመኑ የነበረውን የጥንዶቹን ሰርግ እንዲህ ያስታውሱታል። “የስዩምና ባለቤቱ ሰርግ በጣም ደማቅ ነበር። ቀን በሆቴል ማታ ደግሞ በመኖሪያ ቤቱ የእራት ግብዣ የነበረው ደስ የሚል ሰርግ ነበር። ስዩም በዚያን ዘመን በጣም ቆንጆ ቤት ሰርቶም ነበር።”
ስዩም ወልዴ በህይወት ሳለ ‹‹ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ›› በሚል በፃፈው ግለ – ታሪኩ ላይ ባለቤቱን ወይዘሮ መሠረት ባልቻን አመስግኗል። በህይወቱ እጅግ ደስተኛ እንደሆነ እና ባለቤቱ የህይወቱ ጣዕም እንደሆነችም አንስቷል።
የስዩም ወልዴ ሁለተኛ ልጅ ዳግማዊ እንዲህም ይላል።,”አባቴ ትቶልኝ ያለፈው መፀሃፍቶች እና የስእል መሳያ ቁሳቁሶች አጋዦቼ ናቸው። እኔን ሰአሊ እንድሆን ያደረገችኝ ግን እናቴ ነች።” ታላቅ ወንድሙ ራምሴ ስዩምም ዳግማዊ ወደአባቱ ሞያ መቅረቡን ያምናል። ነገር ግን አባቱን ባይተካም እርሱም በራሱ ዘመን በራሱ መንገድ የተሻለ ስራን ይሰራል ብሎ ያምናል።
በተማሪዎቹ ሲገለፅ
በቀለ መኮንን ፤ በትምህርት ቤቱ ቅርፅና ንድፍን ያስተምራል። ከስነ-ጥበብ ተመራማሪው ስዩም ወልዴ የቀድሞ ተማሪዎችም አንዱ ነበር ። አሁን ለደረሰበት ደረጃ የመምህሩ ስዩም አስተዋፅኦ የጎላም ነበር። ስዩም ያኔ እነ በቀለን ሲያስተምር ላመኑበት ሁሉ ተሟጋች እንዲሆኑ ይመክራቸው ነበር።
“ስዩም ወልዴ ብቁ መምህር ነበር። ወደ ማስተማሪያ ክፍል ሲገባ ተዘጋጅቶ በፍፁም ራስ መተማመን ያስተምር ነበር። መምህር ስዩም ሲያስተምረን ብዙ ፅሁፍ ያፅፈን ነበር። የፈላስፋዎችን ታሪክ እጃችንን እስኪያመን ድረስ ያፅፈን ነበር። አሁን ላይ ሳስበው ሰው የፃፈውን አይረሳምና እንድናስታውሰው አድርጎናል። ስዩም በስራ ላይ ደራርቦ እየሰጠ ያጠነክረን ነበር” ይላል ተማሪው በቀለ መኮንን።
ጠንካራው መምህር ስዩም ወልዴ ተማሪዎቹ ለሃገራቸው አንዳች ረብ ያለው አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚመኝ የሃገርም ተስፋ ሆነው እንዲቀረፁ አጥብቆ የሚሻ ለዚህም የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ወደ ኋላ የማይል ሰው ነበር። ያን ግዜም ተስፋ ከጣለባቸው የሀገራችን ሰዓሊዎች መካከል ታደሰ መስፍንና እሸቱ ጥሩነህ ይገኙበታል።
የስዕል ሂስን በመስጠት ይታወቅ የነበረው ስዩም ወልዴ በየካቲት መፅሄት ህዳር 1976 ላይ በሰዓሊ ወርቁ ማሞ ላይ ያቀረበው ሂስ ሰዓሊውን ከማሳደግ ባሻገር ለጀማሪ ሰዓሊያንም በር ከፋች ነበር።
ስዩም ወልዴ ሃሳቡን በጥልቀት ከገለፀባቸው መንገዶች አንዱ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ነው። ከራሽያ በተመለሰ ማግስት ቅዳሜ ሰኔ አምስት ቀን 1968 ዓም ለመጀመሪያ ጊዜ የፃፈው ስለ ስነ-ጥበብ ትግል ሲሆን ፅሁፉ ሲነበብ የስዩምን ምሁራዊ አተያይ ያንፀባረቁ በሳልና ዝርዝሮች ነበሩ። በዚህም በዘመኑ ለነበሩ የኪነ-ጥበብ አፍቃሪያንና ተመራማሪዎች ጥሩ የመረጃ ምንጭም ነበር።
ስዩም ወልዴ ከሌሎች የስዕል ሀያሲያን ለየት የሚያደርገው ሁለገብ ሃያሲ መሆኑ ነው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ስለሙዚቃ ገፅ፣ ስለ ባህል ፣ ሰለ ጥበብ ትልም ፣ ስለ ቅርፃቅርፅ የመድረክ ጭፈራ ጥበብና የሲኒማ ጥበብ ሁሉ ይሄስ ነበር።
በተመራማሪዎች ሲገለፅ
የጥበብ ታሪክ ምሁሩ ስዩም ወልዴ በ1967 ዓም የራሺያ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ የመመረቂያ ወረቀቱን የፃፈው በሩሲያ ቋንቋ ሲሆን የጥናቱም ትኩረት የጎንደር የብራና ስዕሎች ላይ ነበር። ወደ ሃገሩ ሲመለስም ወደ አማረኛ ቋንቋ ተርጉሞ ለሌሎች ተመራማሪዎች እንዲተርፍ አድርጓል።
በስዩም የምርምር ስራ ከሚኮሩትና ከሚደሰቱት መካከል አንዱ ጥበቡ በለጠ ነው። ጥበቡ አሁንም ድረስ ለሚሰራቸው ኪናዊ የምርምር ስራዎች የስዩምን የጥናት ወረቀቶች በጥልቀት ያነባል። እንዲህም ሲል ይመሰክራል። ” እኔ የጎንደርን ታሪክ በተለይም የ17ኛ 18ኛውን ዘመን ታሪክ በምሰራበት ወቅት በርካታ ወረቀቶችን አገላብጥ ነበር ከነዚህ መካከል አንዱ የስዩም ወልዴ ስራዎች ናቸው። የስዩምን ሌሎች መጣጥፎችና አርቲክሎችንም አነብለት ነበር።”
ጃፓኖች የትም ይማሩ የት ወደ ትውልድ ሃገራቸው ሲመለሱ የተማሩትን በሃገራቸው ቋንቋ ካልመለሱ ሀገራቸው አይገቡም። በዚህ አለም ያወቃቸው ጃፓኖች ስልጣኔን ወደ ሃገራቸው በማምጣትም የበኩላቸውን አበርክቶ አድርገዋል ። የኛው ስዩምም እንዲሁ ነበር። ይህንኑ ሲተገብር የኖረ።
ስዩም ያኔ ከዛሬ 42 አመታት በፊት የብራና ፅሁፎቻችን አስፈላጊነት ላይ ጥናት አቅርቦ ነበር። ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላም ዛሬ እነዚህ የብራና ፅሁፎች የአለም ታላላቅ ቅርሶች ተብለው ተመዝግበዋል። ዛሬም በወመዘክር ውስጥ ይጎበኛሉ። ዛሬ እርሱ በህይወት ባይኖርም ስራዎቹ ግን ሁሌም ህያው ናቸው።
ጥበቡ በለጠ የስዩምን አቅም እንዲህ ያደንቀዋል። ” እኔን የሚገርመኝ አንዳንዴ በሳምንት ውስጥ ወይም ወርሃዊ ሆነው በሚወጡ ሁለት መፅሄቶች ላይ እንዲሁም በዛሬይቱ ኢትዮጵያና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የተለያየ ይዘት ያላቸውን ፅሁፎች በአንድ ቀን ያስነብበናል። መቼ ነው የፃፈው? መቼ ነው ያጠናው? ሁሌም ያስገርመኝ ነበር።”
አቶ ደረጀ ገብሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው ። “ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ” የተሰኘ የስዩም ወልዴ መፅሀፍ ለህትመት እንዲበቃ ጉልህ ሚና ካበረከቱ ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ለአቶ ደረጀ ስዩም ወልዴ ማለት ብዙ መስራት ሲችል በአጭሩ የተቀጨ ምሁር ነው። ” ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ የተሰኘው የስዩምን መፅሃፍ የቅርብ ወዳጆቹ ሰጥተውኝ ሳነበው ብዙ ቁምነገሮችን የያዘ ሆኖ ስላገኘሁት መታተም እንዳለበት ተገንዝቤ በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ታትሞለታል ። ሲሉ አቶ ደረጄ ይገልፃሉ።
ስዩም ወልዴ በባህል እና በስነ ጥበብ ምክንያት ወደ 32 የሚሆኑ ሀገሮችን ለመጎብኘት እድል ያጋጠመው ነበር፡፡እና ከነዚም ብዙ የሆኑ ልምዶችን ለሀገራችን የባህል ፖሊሲ እንዲኖራት ብዙ የጎተጎተ እና ረቂቃ የሆኑ ለፖሊሲ የሚያግዙ ጽሁፎችን ያበረከተ ታላቅ የሀገር ባለውለታ ነበር፡፡
በ1980 ዓ.ም በጸደቀው ህገ- መንግስት በረቂቅ ጥናቱ ውስጥ ከነበሩት የቡድን መሪዎች በዚሁ የባህል እና ስነ -ጥበብ ቡድን መሪ የነበረ ሲሆን ለህገ-መንግስቱ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማበርከቱ ከወቅቱ የሀገራችን መሪ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያም የከፍተኛ ሽልማት እና የእውቅና የምስክር ወረቀት አግኝቷል።
ስዩም ወልዴ በህይወቱ ያሳለፈውን ውጣ ውረድ ‹‹ኩርፊያ የሸፈነው ፈገግታ›› በሚል ግለ ታሪኩ ላይ በጥሩ ቋንቋ ይግለፀው እንጂ የእርሱ ታሪክ ይህ ብቻ አልነበረም። በመፀሀፉ ላይ እንዳለው ከህመሙ የሚያገግም ከሆነ ወደፊት ጥሩ ስራን ሰርቶ ለህዝብ እንደሚያደርስ ቃል ነበረው። ይሁንና ስዩም እንደፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ በህይወት ሳይቆይ ቀርቷል።
ሞት የሰው ልጅ እጣ ፈንታ ነው። ሁሉም የሚቀምሰው ፤ ሁሉም የሚደርሰው ። ስዩም ወልዴም ለሃገሩ በርካታ ስራዎችን ቢሰራም አንድም ቀን እንደሰራ ሳይሰማውና ሳይረካ በ51 ዓመቱ ህዳር 14 ቀን 1986 ዓም ከዚህች አለም ተሰናበተ። ፅሁፎቹ ግን ዛሬም ህያው ናቸው። ዛሬም ብናነባቸው፤ ዛሬም ብንመራመርባቸው እናተርፍባቸዋለን። ነፍስ ይማርልን ።ለቤተሰቦቹና ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን ይስጥልን ።
መዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ስዩም ወልዴ በሀገራችን በስነ-ሂስ ቀደምት ከሚባሉት የሚጠቀስ ነው፡፡ በተለይ በ1970ዎቹ ብእር ከወረቀት አቆራኝቶ የሚጽፋቸው የሂስ መጣጥፎች ከፍተኛ ከበሬታ አስገኝተውለታል፡፡ ከስዩም በኋላ ሂሳዊ ጽሁፎችን በየህትመት ውጤቱ ላይ የሚያወጡ ባለሙያዎች የሉም ባይባልም የስዩም ግን በጥልቀት የተሞሎ ነበሩ፡፡ ስዩም ይዘት ላይ አተኩሮ ከበቂ እውቀት ጋር የሚጽፍ በመሆኑም መጣጥፎቹ ዛሬም ሲነበቡ ብስለታቸው ሀያል ነው፡፡
ይህን ድንቅ ጋዜጠኛ ፤ መምህርና ሀያሲ ካጣነው ድፍን 30 አመት ሊሞላው ነው፡፡ በእነዚህ 30 አመት ወይም ሩብ ክፍለ-ዘመን ስዩምን የሚተካ አሊያ የሚከተል ልቡ የበራለት ሀያሲ አፍርተናል ወይ? ይህን ያነበበ ሁሉ በልቡ ይጠይቅ፡፡ እኛ ግን የስዩም ወልዴን ታሪክ ስንሰንድ ልዩ አበርክቶው በጊዜ መራቅ ምክንያት እንዳይረሳ ስለሚያሳስበን ነው-ታሪኩን ማቅረባችን፡፡ ደግሞም ስዩም የሕይወት ታሪኩን በህይወት ሳለ ጽፎ ያጠናቀቀ በመሆኑ ልናከብረው ወደናል፡፡ ስዩም ያልተዘመረለት ጀግና ሲሆን እኛም ከእነዚህ ጀግኖች ጎን መቆማችን ይቀጥላል፡፡ ይህ የስዩም ወልዴን ታሪክ እንድንሰራ ተገቢውን ትብብር ያደረጉልንን ወዳጆቻችንን ራምሴ ስዩምን ዳግማዊ ስዩምን ሳልሳዊ ስዩምን ከልብ ልናመሰግን እንፈልጋለን፡፡