ስለ ሙሉጌታ ገሰሰ

ክፍል 3

 ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን  ሙሉጌታ ገሰሰ  በተመለከተ ፅሁፎችን ሲያወጣ እንደነበር አይዘነጋም። የሕይወት ታሪኩም በዝርዝር ቀርቦ ማንነቱ እና አበርክቶው እንዲታወቅ አድርገናል፡፡ በዚህ ክፍል 3 ላይ ደግሞ ሙሉጌታን ከዛሬ 49 ዐመት በፊት አንስቶ የሚያውቀው አቶ ብርሀኑ አባዲ የነገረንን ትዝታ እና ምስክርነት እናቀርባለን፡፡  

 ክፍል 3ቱን ፅሑፍ ዕዝራ እጅጉ እና ቤርሳቤህ ጌቴ እንደሚከተለው አጠናክረውታል፡፡

            ብርሀኑ አባዲ የሰጠው ምስክርነት

ከሙሉጌታ ጋር  በአንድ ከተማ ነው ተወልደን ያደግነው። ኩዊሃ ከተማ ይባላል፡፡ ከመቐለ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ አሁን ያለው አሉላ አባ ነጋ ኤርፖርት የሚገኝበት ።እዛ ነው ሁለታችንም ተወልደን ያደግነው፡፡ እና እኔ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ነው የማውቀው።  መቐለ አጼ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ነው የተማረው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን።  1968 ያኔ እንግዲህ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ስለነበረ ፀረ ደርግ የትምህርት እንቅስቃሴ ስለነበረ ያው… ደርግ… ሁሉንም የዲሞክራሲያዊ መብቶች አፍኖ የመደራጀትን፣ የመናገር ፣የመጻፍን መብቶች  በአዋጅ ስላፈነ   ወይም መታገል አለብን ብለን ለወቅቱ ወጣቶች በየመሰለን ድርጅት የምንደራጅበት ጊዜ ነበር። ያኔ ተወልደን ያደግነው ኩዊሃ እና መቐለ  ድርጅት ነበረ የትህነግ እንቅስቃሴ ነበረ፡፡ እኔም ሙሉጌታም  በትህነግ የከተማ ውስጥ ሴል ተደራጅተን እንታገል ነበረ። ስለዚህ በፖለቲካ ትግልም  አብረን ነበርን። በከተማው የህወሓት አደረጃጀት ገብተን ፀረ ደርግ እንቅስቃሴ ውስጥ ነበርን፡፡  በኋላ   ትግራይ የቀይ ሽብር ዘመቻ ሲጀምር በ 1970 ዓ.ም. ጥር አካባቢ አጋጣሚ እኔ እና ሙልጌታ በተለያየ ቦታ ግን በአንድ ቀን ታሰርን። በ 1970 ዓ.ም. የካቲት ወር  ታሰርን። እዛ መቐለ የቀይ ሽብር እስር ቤት የሚባል ነበር።   የህዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት የነበረበት ሰፊ ግቢ ስላለ እዛው ውስጥ ማሰሪያ፣ መግረፊያና መመርመሪያ ነበረ። ሁለታችንም እዛ ታሰርን። በጊዜው  ከ500 በላይ የምንሆን ወጣቶች ተማሪዎች አስተማሪዎች የመንግስት ሠራተኞች ነጋዴዎች ነበር የታሰርነው ፡፡ሁለታችን ስንታሰር ዝም ብለው በግምት ነው ያሰሩን፡፡  ማስረጃ አግኝተው ሳይሆን ያው ያኔ እንዲሁ አይተው ነበር ወጣቱን የሚያስሩት፡፡

ሙልጌታ የኮሌጅ ትምህርት በዛ ደረጃ የሚካሄደው እርሻ ስልጠና ወስዶ ከዛ አጋርፋ የገበሬዎችን ማሰልጠኛ ውስጥ ባለሙያ ሆኖ ሠራ።    

ሙሉጌታ በ 1951 ዓ.ም. ነው የተወለደው። ፖለቲካውን ትቶ በ 1976 ዓ.ም. ያው ሁላችንም እንደምናስታውሰው ሰፊ የሆነ የትግራይ ተወላጆች የሚታሰሩበት ዘመቻ ነበረ። ያኔ  በደርግ መንግስት በኩል ምን አይነት ድምዳሜ ተደረሰ መሰለ? በየትኛውም የመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙት እና ነጋዴዎች የትግራይ ተወላጆች የህወሓት አባላት ናቸው የሚል ግምገማ ነበረ፡፡ እና ስለዚህ ሁሉም መታሰር አለባቸው። በኢሰፓኮ መዋቅር ውስጥ ያሉት ጭምር ይታሠሩ ነበር፡፡ ለደርግ ሥርአት ብዙ ያገለገሉ በቀይ ሽብር ውስጥ ተሳትፈው ብዙ ወጣቶችን ያስሩ ነበር። የትግራይ ተወላጆች ጭምር የማይታመኑበት ደረጃ ተደረሰ። ምናልባት በታሪክም እንደምታውቀው ያኔ የኢሰፓኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የአዲስ አበባ የፖለቲካ ኃላፊ የነበረው ታደሰ ገብረ እግዚአብሔር የሚባል  የ66 የፖለቲካ ትምህርት ቤት የሚባል ዋና ዳይሬክተር ነበረ፡፡ ታደሰ  ገብረ እግዚአብሔር ያኔ ከነበሩት የተማሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ  በደርግ ውስጥ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ ነበሩ። እሱ ጭምር የታሰረበት የክፍለ ሃገር የኢሰፓኮ ተወዳዳሪዎች የነበሩ ጭምር በሙሉ እየተለቀሙ የሚታሠሩበትም የነበረ እና በጣም አሰቃቂ ምርመራ እና የዘረፋ ሁኔታ ይካሄድ ስለነበረ ሁሉም የሚያውቁትን እንዲጠሩ ምንም የህወሓት አደረጃጀት እና ግልጽ ግንኙነት ሳይኖራቸው ግን በነበረው አስከፊ ምርመራ አዎ ነን ብለው የሚያምኑበት እና ማንኛውንም በማህበራዊ ግንኙነት የሚያውቁትን ሰዎች ጭምር እየጠሩ የሚታሰርበት ሁኔታ ነበረ። ያኔም ሙልጌታ እዛ የትግራይ ተወላጅ በመሆኑ ብቻ ከአጋርፋ ተነስቶ አዲስ አበባ መጣ። አዲስ አበባ ብዙ ስቃይ ደረሰበት ፡፡ከዚያ ወደ መቐለ አብዛኞቹ ወደ ትግራይ ዋናው የምርመራ ቦታ ማዕከላዊ ምርመራ የሚባለው ትግራይ ውስጥ ተቋቁሞ  ሲካሄድ ነበረ። በዘመቻ መልክ ሲካሄድ ስለነበረ ወደ መቐለ እንደገና ለምርመራ መጣ። እኔ ከእርሱ ቀደም ብዬ በ1972 ነበረ የፖለቲካውን ትግል የጀመርኩትና የታሰርኩት። ኋላ እሱም ታስሮ መቐለ መጣ እዛ ተገናኘን መቐለ ወህኒ ቤት እና አብሮ አደጎች ስለሆንን፣ ጓደኞች ስለሆንን፣  የተለያየ ክፍል እንኳን ብንሆን ምግባችንን አብረን ነበር የምንመገበው። አስራ ሶስት ወጣቶች በጣም እንደሚተዋወቅ ጓደኛሞች አብረን እንበላና እንጠጣ ነበር። የመጣውን ምግብ ከቤተሰብ ነው የሚመጣው። 13 ከሆንን ለምሳሌ ሦስት ሰዎች እንኳን ቢመጣ ከቤተሰብ የሦስቱን አብረን ነው የምንመገበው። ማህበራዊ ሁኔታችን በጣም ጠንካራ ነበር ።እና በጣም የቅርብ ነበርን። 13 ሆነን ለምግብ እንገናኛለን። በሌሎች ውይይቶችም አብረን እንሆን ነበር።  ወህኒ ቤትም እስከ 1978 ዓ.ም አብረን ነበር ያሳለፍነው። ከዛ በ1978 ዓ.ም በጥር 8:30 ምሽት ለየካቲት አንድ አጥቢያ የአጋዕዚ ኦፕሬሽን ተካሂዶ በዛ ኦፕሬሽን መሰረት ነው ሁለታችንም ከእስር ቤት የወጣነው። ከእስር ቤት ወጥተንም የተለያዩ የትግራይ ቦታዎች እየተጓዝን ቆይተን የተለያዩ የፖለቲካ ትምህርት ሲሰጠን ቆይቶ ወልቃይት አካባቢ አንድ ወር ስልጣን ከወሰድን በኋላ ምርጫ ተሰጠን መታገል የሚፈልግ የትጥቁ ትግሉን መቀላቀል የሚፈልግ የትጥቁ ትግሉን እንዲቀላቀል ወደ ውጪ ሀገር መሄድ የሚፈልግ ወደ ውጪ ሀገር እንዲሄድ እዛው የነጻ መሬት የሚባሉት ቦታዎች ላይ በሙያው ማገልገል የሚፈልግ ማገልገል እንደሚችል ምርጫ ተሰጠን።

 እኔና ሙልጌታ ግን የትጥቅ ትግሉን ለመቀላቀል ሁለታችንም መረጥን። ስለዚህ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ሁለታችንም ደግሞ አንድ ክፍል ውስጥ ተመደብን። እዛ ስልጣን ወሰድን፡፡ ወታደራዊ ፖለቲካዊ ስልጠና ተሰጠን፡፡ ወታደር ሆነን ሚሊተሪን ስልጠና የፖለቲካም ስልጣና አብረን ወሰድን።

 እኛ የተሰለጥንበት ሥልጠና የአጋዕዚ ስልጠና ይባል ነበር። ከዚያ በፊት ከ ምርጫ  በፊት የፖለቲካ ትምህርት ሲሰጠን 2 ወር ያህል በተለያዩ ኃይሎች ተሰድረን ነበር ስልጠናውን የምንወስደው እና ስልጠና ስንወስድ የኃይል ጋዜጣ እንድናዘጋጅ ተመረጥን። ስለዚህ እሱ የአንድ ኃይል አዛዥ ነበረ። የጋዜጣውም ዋና አዘጋጅ ነበር። እኔም የሌላ ኃይል አዛዥ ነበርኩ። የጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበርኩ። እና የተለያዩ ጽሁፎች እያቀረብን በዕረፍት ሰዓት ሰልጣኞቹን የትግል  ትምህርት የሚወስዱትን የአጋዕዚ ኦፕሬሽን ነጻ ያወጡትን ወታደሮች የተለያዩ የልብ ወለዶች ግጥሞች የተለያዩ መጣጥፎች እያቀረብን እናዝናናቸው ነበረ። እና የጋዜጠኝነት ስራችንን እኔም እርሱም እዚያ ነው የጀመርነው።

ከዛ በፊት ሙልጌታ በጣም አንባቢ ነው። ከመጽሐፉ አይለይም። እኔም የንባብ ዝንባሌ ነበረኝ፡፡ ከእዚያ እስር ቤት ያገኘነው ትልቅ ቁም ነገር  መጻሕፍቶችን ማንበብ ነው፡፡ የተለያዩ ጓደኞቻችን ቤተሰቦቻችን መጽሐፎችን ይልኩልን ነበር። ትልቁ ያገኘነው ጥቅም በእስር ቤት ራሳችንን ማስተማር መቻላችን ነው። ሙልጌታ ደግሞ በጣም ጎበዝ ገጣሚ ነበር። የአማርኛ ሥነ ጽሁፍ ችሎታው በጣም ከፍተኛ ነው። እኔ በአብዛኛው በትግርኛ ነበር የማዘነብለው። በእርግጥ በአማርኛም እጽፍ ነበር። እርሱም በዋነኛው የሚጽፈው በአማርኛ ነው። በትግርኛም ጭምር ይጽፍ ነበር። ስለዚህ እዛ ጋዜጣ መጻፍ ጀመርን ፡፡ከዛ ስልጠና ስንገባን የአጋዕዚ ስልጠና ጋዜጦችን እያዘጋጀን የተለያዩ መልእክቶችን እናስተላልፍ ነበር። ከዛ ምደባ ሲካሄድ እኔም እሱም በፕሮፖጋንዳ ዲፓርትመንት ነው የተመደብነው። ሁለታችንም  የፖለቲካ  ፕሮፖጋንዳ ዲፓርትመንት የጥናትና ትርጉም እና ምርምር የሚባል ዲፓርትመንት ነበር። ሁለታችንም እዛው ተመደብን።  አማረ አረጋዊ የዚያ ዲፓርትመንት ኃላፊ ነበር። እና ያ ዲፓርትመንት  ሁለት ሥራዎችን ነበር የሚያከናውነው። አንደኛው የተለያዩ የማሌ መጻሕፍቶችን ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ወደ አማርኛ እና ትግርኛ መተርጎም ነው። እኛ  የትርጉም ክፍሎች ተመድበን እንሠራ ነበር። ሁለተኛው ሥራችን ደግሞ የድርጅቱ የፕሮፓጋንዳ ጋዜጦች ነበሩ። አንደኛው ወይን ይባላል። “ወይን” ጋዜጣ በትግርኛ ነው የሚዘጋጀው። ሁለተኛው “የካቲት” ጋዜጣ  ይባላል። ያ “የካቲት” ጋዜጣ በአማርኛ ነው የሚዘጋጀው። ስለዚህ የሁለቱም ጋዜጦች እኛ ነበር የምናዘጋጀው። ሙልጌታ የየካቲት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ይሠራ ነበር። እኔ የ”ወይን”አዘጋጅ  ሆኜ እሠራ ነበር። ግን “የካቲት” ውስጥም ኮን ፅሑፍ አቀርብ ነበር። እርሱም የወይን ውስጥም ኮንትሪቢዩት ያደርጋል። ለሁለቱም ኮንትሪቢዩት እናደርጋለን። ግን በዋነኛነት እርሱ የካቲት እኔ የወይን ጋዜጣ አብረን እንሠራ ነበር። የትርጉም ስራ እናከናውናለን፡፡ ከዛ አንድ ወር ያህል ከሠራን በኋላ በ1979 ዓ.ም እኔም እርሱም የድምጸ ወያነ ትግራይ ውስጥ ተመደብን። 

  እርሱ ድምጸ ወያነ ሬድዮ ዲፓርትመንት ውስጥ ተመደበ። ያኔ የፕሮፓጋንዳ ትግል በጣም የጦፈበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ እና ትልቁ የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ ደግሞ ሬድዮ ነበረ። ስለዚህ ሙሉጌታ በጣም ለሬድዮ የምታውቀው አንድ ትልቁ መስፈርት ድምጽ ነው። ሙሉጌታ በጣም ወርቃማ ድምጽ ነው ያለው። በድምፁ በእውነት ደግሞ የእዚህ ችሎታው የትንታኔ ብቃቱ እና የፖለቲካ እውቀቱ ጭምር ተመርጦ ነው ድምጸ ወያነ እንዲገባ የተደረገው። እኔም ተመደብኩ፡፡ ሁለታችንም እና እሱ እዛ ድምጸ ወያነ ውስጥ የአማርኛው ዲፓርትመንት ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሲሠራ ነበር።እኔ ደግሞ በትግርኛ ዲፓርትመንት እሰራ ነበር። ስለዚህ ምናልባት የድምጸ ወያነ ሬድዮ ጣቢያ ወርቃማው ዘመኑ የሚባለው ከ1979 እስከ 1983 የነበረው ዘመኑ ነው። በዛ ዘመን ውስጥ በጣም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው፣ ንቃት ያላቸው ፕሮግራሞች ነበር የሚዘጋጁት። ጥልቀት ያላቸው ትንታኔዎች እና መጣጥፎች ሀተታዎች ይዘጋጁ ነበር። ይህንን በማዘጋጀት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው ሙሉጌታ።

በተጨማሪ፣ ለድምጸ ወያነ ታሪክ ጉልህ ሆኖ የሚጠቀሰው ሬድዮን የሥነ ጥበብ መሣሪያ ማድረግ ስነ ጥበብን በሬድዮ የማቅረብ ፖለቲካን በስነ ጥበብ በኩል ለህብረተሰቡ የማቅረብ ስራ ያኔ ነው የተጀመረው፡፡ እና በዚህ ስራ በኩል ሙሉጌታ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። ግጥም አንዱ የስነ ጥበብ አካል ነው የተለያዩ ግጥሞችን እያዘጋጀ ያቀርብ ነበረ። ሁለተኛው ጭውውት ነው። ጭውውቱ በጣም የፖለቲካል ሳታየር ዓይነት ባህሪ ያለው። በዛ አማካኝነት ስርዓቱን ሬዲኩል ማድረግ እና በጣም የሚገርሙ ጭውውቶችን ያዘጋጅ ነበር። ሶስተኛው የሬድዮ ድራማ ነው። የሬድዮ ድራማ በጣም ሀይለኛ  የፕሮፓጋንዳ ሥራ ነበር፡፡

 ሙልጌታ የፖለቲካ እውቀቱ ከፍ ያለ ነበር።  ተከራክሮ፣ የማያምንበትን ነገር በግልፅ ተናግሮ፣ ህወሃት የሚያነሳቸው የፖለቲካ መስመሮች ላይ ያለው ግልፅነት ወይ ደግሞ የማይስማማበት ጉዳይ ካለ እስከመጨረሻ ተከራክሮ ነበር። እና የውይይቶቹ ፈርጥ እሱ ነበር። አስታዉሳለሁ እዚህ ቃሌ ማን የሚባለው ቦታ ላይ፣ የሶቬት ህብረት መንግስታዊ ካፒታሊዝም የሚከተል ሥርዓት ወደ መሆን ተለውጧል የሚል መነጋገሪያ ሀሳብ አንስቶ ነበር የሚያወያየን፡፡ እና አዲስ አስተሳሰብ ነበር። ምክንያቱም የሶቬየት ህብረት የሶሻሊስት ሥርዓት መሆኑ ነው የሚታወቀው። በዓለም ደረጃ እንደዚያ ነው የሚታወቀው። በህወሃት በኩል ግን የሶሻሊስት ሥርዓትነቱ ስማዊ ነው እንጂ የስርዓቱ ውስጥ መገለጫ መንግስታዊ ካፒታሊዝም ነው። ወደ መንግስታዊ ካፒታሊዝምነት ተቀይሯል። ከክላሲካል ካፒታሊስት ሀገሮች የሚለየው የሶቬት ህብረት መንግስታዊ ካፒታሊዝም መሆኑ ነው። ሌላው የግል ባለሀብቶች የበላይነት በፓርቲም በመንግስታዊ ስልጣንም ይዘው የሚያስተዳድሩት ነው። የሶቬት ህብረት ግን በመንግስት ስልጣን ያሉ ኃላፊዎች ወደ መንግስታዊ ቡርዦአ ተቀይረዋል የሚል እሳቤ ነበረና ሰፊ ክርክር አካሂዶ አወያዩ በዚህ ጉዳይ ላይ ሙሉጌታን ሊያሳምነው አልቻለም። የነበረው ፖለቲካ ብቃት ከፍ ያለና በዛ ደረጃ ሙሉጌታን ለማስረዳት የሚያስችል ስላልነበረደጀና ስንሄድ  ካድሬ ትምህርት ቤት ነበረ እና እዛ ያሉ አስተማሪዎች ያቀርባሉ፤ ” ለጊዜው ይሄንን ነጥብ እንዝጋው ” ብሎ ያላፈበት ትዝ ይለኛል። 

ሙሉጌታ ተከራክሮ የማያምንበት እስከመጨረሻ ከፍተኛ እውቀት ያላቸውንም ሰዎች ቻሌንጅ አድርጎ የሚሄድ፤ ምንም ያላመለበትን ነገር ፈፅሞ የማይቀበል እና በኋላ በሂደት ደጀና ሄደን በሰፊው ተከራክሮ የተለያዩ ሪፈረንሶች(ማጣቀሻዎች) ቀርበው ነው ያንን አቋም ሊቀበል የቻለው። በትግል ሂደቱም በየትኛውም መድረኮች ዝም ብሎ እንደወረደ ነገሮችን አይቀበልም። የማያምንበትን ፊት ለፊት ይቃወማል፣ በልዩነት ይወጣል፣ በሚያስማማው ይቀጥላል ፡፡በሚያስማማው ደግሞ እንደ ልዩነት ይዞት ይሄዳል። ይሄ አንዱ የሙሉጌታ ጠንካራ ባህሪ እንደሆነ ለመግለፅ ፈልጌ ነው።

በ1983 ዓ.ም የፕሮፓጋንዳ ሥራዎችና የሬዲዮ ሥራችን በጣም ተለዋዋጭ ነበር። ስትራቴጂክ ማጥቃት የሚባል በወሎ፣ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሰሜን ሸዋ ይካሄዱ በነበረበት ጊዜ የምንሰራቸው ፕሮግራሞች ሰርተን ሪከርድ አድርገን፣ አዳዲስ ሁኔታዎች ሲመጡ ያንን ሌሊት ሙሉ ቁጭ ብለን ሌላ አዲስ ዝግጅት አዘጋጅተን የምንለቅበት ሁኔታ ነበር ። እንቅልፍ የሚባል አልነበረም ፡፡ ሌላ ትልልቅ ቃለ መጠየቆች ሲኖሩ ያኔ ከድርጅቱ መሪዎች ኋላ መለስ ቼርማን ሆነ ከዚያ በፊት እና አባይ ፀሃዬ እና ሌሎች ነበሩ። የድርጅቱ ትልልቅ የመልዕክት ሲኖር ነበር ኢንተርቪው የሚያደርጋቸው። በጣም ፓወርፉል(አስገምጋሚ) ድምፅ፣ በጣም ተደማጭ ድምፅ ነው ያለው በጣም ርቱዕ አንደበት ነው ያለው። ይሄም ሌላው የሙሉጌታ ልዩ ክህሎት ነው፡፡

በመጨረሻ አዲስ አበባ ስንገባ ሙሉጌታ በነበረው ብቃት ተመርጦ በቀጥታ የተመደበው የኢትዮጵያ ሬድዮ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ነው፡፡ እኔ ቴሌቪዥን ውስጥ የትግርኛ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሆኜ ነው የተመደብኩት።

ከፋና ሚዲያ የወጣበት ምክንያት ከሙሉጌታ ባህሪ ጋር ይያያዛል፤ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ሙሉጌታ ያላመነበትን ነገር የመቀበል ህሊና የለውም፤ የማያምንበት ነገር አያደርግም፤ የሚያምንበትን ብቻ ነው የሚፈፅመው። የማንንም ሰው አሽከር እና ተከታይ በደፈናው መሆን የማይችል፤ የራሱ ሀሣብ ያለው፣ ከፍ ያለ  በራስ መተማመን ስሜት ያለው ሰው ነው ሙሉጌታ። በመሆኑም ያን ጊዜ የህወሓት አመራር ውስጥ መከፋፈል ተፈጠረ። ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የመለስ ቡድን እና የተወልደ ቡድን ሰፊ የውስጥ ፍጥጫ ሲያካሂዱ ቆይተው በመጨረሻ የውስጣቸው ልዩነት ፈጥጦ ወጥቶ ለሁለት ተከፈሉ። ለሁለት በሚከፈልበት ጊዜ የነበረው የቅራኔው ማኔጅመንት ትክክል ያልሆነ፤ ከትግሉ ውስጥ ከነበረን ባህል የወጣ በቡድን ተከፋፍሎ አንዱን አንዱን የሚነካ፣ አንዱን አንዱን እያባበለ የእሱን ቡድን እንዲሆን የሚያደርግ፤ በግልፅ መድረክ ወጥቶ ልዩነታቸው ታጋዩ አባሉ እንዲያውቀው ተደርጎ፣ በልዩነታቸው ዙሪያ ውይይት ተካሂዶበት፣ አብዛኛው ወደወሰነው ሃሳብ አሸናፊ የሚሆንበት ሂደት አልተከተለም ነበረ። በወቅቱ የመለስ ቡድን አጋጣሚ ሆኖ የመንግስታዊ ስልጣንንም የተቆጣጠረው ቡድን ነበረ። ደህንነቱ በሱ ስር ነበረ፤ መከላከያውም እንዲሁ። ስለዚህ ልዩነትን የሚፈታበት መንገድ በሀይል ነው። ከዚህ በፊት በረሃ እያለን ድርጅቱ ውስጡ ክፍፍል ነበረ፤ ግን በውይይት ነበር የተፈታው፤ እነ ግደይ ዘራጽዮንና አረጋዊ በርሄ የሚባሉ የፖሊት ቢሮ አባሎች፣ ሌሎችም የነሱ ደጋፊዎች፤ ሃሳባቸውን በግልጽ አቅርበው፤ መድረክ ተዘጋጅቶ መድረኩ የሚያወያይ ሰው ተመርጦ መለስና የእሱ ሃሳብ የሚደግፉ ደግሞ ለብቻቸው ሆነው፤ ሃሳባቸውን እያቀረቡ ንግግር እየተደረገ ለወራት ዉይይት ተካሂዶ በመጨረሻ በድምፅ የመለስ ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ እነ ግደይ ዜራጽዮንና አረጋዊ ወደ ዉጭ ይሄዱት።

ስለዚህ ያ የቀድሞ ባህልተጥሶ ውስጥ ለውስጥ ነበር ፍንጫ የሚያካሂዱት የነበረው፤ በመጨረሻ ደግሞ  በጉልበት ነበር ችግሩ የተፈታው። አገዷቸው የመለስና ተወልደን እኛ አናውቅም ይሄ ሁሉ ምንድነው፤  እንደ ታጋዮች እንደ አባሎቻችን ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም።

በመጨረሻ መቀሌ ሄዶ መለስ ካድሬዎችን ሰብስቦ ብቻውን የእሱን ሃሳብ አቅርቦ አጨብጭበው የእሱን ተቀበሉ፤  የነተወልደ ቡድን  በደብዳቤ ታገዱ ከድርጅቱ። ከዛ ከመቀሌ ከተመለስን በኋላ መለስ እዚህ አዲስ አበባ ካድሬዎቹን ጠርቶን ነበረ። እዚህ የድሮው ደርግ የሰራው አዳራሽ የጉባኤ አዳራሽ በሚባለው ላይ ጠርቶን ነበረ፤ ሁላችንም እዛ ተገኝተን ነበር። ሙሉጌታ ነበር ፊት ለፊት ሽንጡን ገትሮ የተከራከረው፤ “አካሄዳችሁ ትክክል አይደለም፤ ልዩነታችሁን ወደ መድረክ አቅርባችሁ የሁላችሁንም ሃሳብ ሰምተን እኛም ሰፊ እድል ተሰጥቶን ለመከራከር ስለዚህ የመሰለንን አቋም ደግፈን በዛ መሰረት ነበረ መፈታት የነበረበት፤ አሁን ግን ውስጥ ለውስጥ እንደምታካሂዱት የሴራ መንገድ ተከትላችሁ ነው የሄዳችሁት፤ ይሄ ደግሞ ትክክል አይደለም፣ የሚጎዳ ነው። የህዝቡን ጥቅም ይጎዳል፤ ትክክል አይደለም፤ ውስጡ ለውስጥ ሁለታችሁም የራሳችሁን ሰዎች እያባበላችሁ እያደራጃችሁ   ነው፤  ይሄ አካሄድ ትክክል አይደለም!!” ብሎ ግልጽ ነው ብቻውን ሽንጡን ገጥሮ የተከራከረው።

ከዛ በኋላ እዛ ድርጅት ውስጥ መቆየት ደስ አላለውም። ስለዚህ በዚህ ምክንያት ለጊዜው ከሬድዮ ፋና ወጣ። ከዛ ለጊዜው ከወጣ በኋላ ሜጋኔት ማከፋፈያ ድርጅት ውስጥ በጊዜያዊነት ቆየ፤ ከዛ ግን የስንብት ደብዳቤ ጽፎ በራሱ ፍቃድ ነው የወጣው። ያው የነበረው የፖለቲካ አካሄድ እና በድርጅት ውስጥ የነበረው መከፋፈል ማኔጅ የተደረገበት መንገድ ዲሞክራሲያዊ ነው ብሎ ስላላመነ ነበር በራሱ የለቀቀው። ከዛ በኋላ የተስፋ ጎህ የኤች.አይ.ቪ.ኤድስ ማህበር ውስጥ ከመጀመሪያው ጀምሮ ያደራጃቸው ሬድዮ ውስጥም ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ያደረጋቸው ሙሉጌታ ስለሆነ እባክህን እርዳን ብለውት የማህበራቸው ስራ አስኪያጅ ሆኖ የተወሰነ ጊዜ ሠርቷል። ከዚያም የኮንስትራክሽን ባለሃብቶች ማህበር ማኔጅ እንዲያረግላቸው ጠርተውት የእነሱ ስራ አስኪያጅ ሆኖም ሲሰራ ቆይቷል። በዚህ መሃል በቢዝነስ አድሚስትሬሽን ከእንግሊዝ ሀገር የማስተርስ ዲግሪ ሰርቷል። 

በሚዲያው ዘርፍ አንዳንድ የማማከር ስራዎች ከማከናወን ባለፈ በይፋ የሚዲያ ስራዎች አልሰራም። የፖለቲካ ሂደቱ እና አካሄዱ አልጣመውም፤ አልተመቸውሜ፡፡ከዛ በግል ይፅፍ እንደነበረ አውቃለሁ። ግጥሞችን ይፅፍ ነበረ፣ በትርፍ ጊዜው ሌሎች ጽሁፎችን ይፅፍ ነበረ ፡፡ግን ቋሚ  የሆነ የተቀጠረበት ስራ ነው ሲሰራ የነበረው፤ የዛ የኮንስትራክሽን ባለቤቶች ባለንብረቶች ማህበር ውስጥ ለረዥም ጊዜ እንደሰራ አውቃለሁ። ያም ቢሆን ግን ለሙሉጌታ የሚመጥን አልነበረም። ቢዝነስ አስተዳደር ስለተማረ በሙያው ሲሰራ ነበር።  እንደ ሙሉጌታ አይነት ትልቅ የሚዲያ ሰው፣ የአርት ሰው፣ የስነ ጥበብ ሰው በዛ ዘርፍ መስራት አልቻለም። ተጨባጩ ሃቅ እውነታ ያህንን ነው የሚያሳየው።

ሙሉጌታና እኔ በጣም የጠበቀ ማህበራዊ ግንኙነት ነበረን። በብዙ ነገር ላይ እንጨዋወታለን። የሀገሪቱን ፖለቲካ ሁኔታ እያነሳን እንጨዋወት ነበር።  እንደምታውቀው እኛ ወጣቶች ሆነን ገና የአስራ ስድስት ዓመት፣ የአስራ ሰባት ዓመት ልጆች ሆነን ነው ፖለቲካ ውስጥ የገባነው። ስንገባ የነበረን ራዕይ ህዝቡ እንዲያልፍለት የሚል ነው። ህዝባችን ካለበት በጣም አስከፊ ድህነት እና ኋላቀርነት እንዲላቀቅ፣ የበለፀገች  ሃገር እንድትኖረን፣ ታግለናል፡፡

ሙሉጌታ ከአሃዛ ጋር የተጋቡት በ አስራ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ዓመተ ምህረት ነው የተጋቡት። በትግሉ ጊዜ ማለት ነው። በትግሉ ጊዜ ከዛ በስማንያ ሁለት ዓመተ ምህረት የመጀመሪያ ልጃቸውን ወለዱ። ሚዘር ትባላለች።

 ሁለተኛ ልጁ ናሆም ይባላል፤ እዚ አዲስ አበባ ነው የተወለደው፤ እሱም በህግ ትምህርት ተመርቋል።   ሦስተኛ ልጁ ሚካኤል ይባላል፤ እርሱም የኮሌጅ ትምህርቱን ጨርሷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *