ሳምራዊት ግርማ በንቲ

ሳምራዊት ግርማ በንቲ

ለበሪሳ ጋዜጣ እድገት የተጋች ወጣት ጋዜጠኛ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-እውቀት / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዷ ጋዜጠኛ ሳምራዊት ግርማ ናት፡፡ ሳምራዊት በበሪሳ ጋዜጣ ላይ ላለፉት 13 አመታት የሰራችና የህትመት ውጤቱ እንዲቀጥል ታላቅ ጥረት ካደረጉ ባለሙያዎች አንዷ ናት፡፡ ከአፋን ኦሮም ሴት ጋዜጠኞች በተለይ 2000 ዘመንን በመወከል ብቅ ያለችው ሳምራዊት ግለ-ታሪኳን እንደሚከተለው አጠናክረነዋል፡፡

ልጅነት፣ እድገትና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት

ጋዜጠኛ ሳምራዊት ግርማ በንቲ በ1980 ዓ.ም በኦሮሚያ፣ ምስራቅ ወለጋ ዞን፣ በነቀምቴ ከተማ ከአባቷ አቶ ግርማ በንቲ እና ከእናቷ ወ/ሮ አለም መኮንን ተወለደች፡፡ እድገቷም እዚያው ነቀምቴ ሲሆን እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ ኪበ ዋቻና ጨለለቂ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት በመግባት አንደኛ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡

መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት

በ1993 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና (ሚኒስትሪ) ወስዳ በጥሩ ውጤት ወደ ዘጠነኛ ክፍል አልፋ በደርጌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብታ እስከ 10ኛ ክፍል ተምራለች፡፡

የጋዜጠኝነት ሞያና የሙያ ስልጠና

የጋዜጠኝነት ፍቅር በልጅነቷ ውስጧ ያደረዉ ሳምራዊት በኮሌጅ ቆይታዋ በሚኒ ሚዲያ ክበብ ውስጥ በንቃት በመሳተፍ ከፍተኛ አድናቆት ያገኘች ሲሆን የተሳትፎና የምስጋና ሰርተፍኬትም አግኝታለች።

የልጅነት ህልም ወደ እውን መቀየር

በልጅነቷ አብዛኛውን ጊዜ በኢትዮጵያ ሬድዮ አፋን ኦሮሞ ፕሮግራሞችን እንደምታዳምጥ የምትናገረዉ ሳምራዊት፣ በተለይም ዘውትር እሁድ ማለዳ የሚተላለፈውን ሲምቢርቱ በሪ ፕሮግራምን በጣም ታደንቅ ነበር፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘውትር ቅዳሜ ከሰኣት ሲተላለፍ የነበረዉን የDhaንጋ ፕሮግራም ትከታተል ነበረ፡፡ በዚህም ጊዜ የምተሰማቸዉ እና የምታያቸዉ ጋዜጠኞች ቀልቧን ይስቡት ነበር፡፡ በተለይም ዝናሽ ኦላኒ፣ ስመኝ ቴሶ፣ አያንቱ ጉተታ፣ ለምለምና ሌሎችንም እስከ ዛሬ እንኳ አትዘነጋችውም፡፡

ከፍተኛ ትምህርት

ከነቀምቴ መምህራን ኮሌጅ ከተመረቀች በኃላ መንግስት ወደ ስራ ቢመድባትም ቦታው ሩቅ በመሆኑ በቤተሰቦቿ ዉሳኔ ትታ ወደ አዲስ አበባ መጣች፡፡ አዲስ አበባ መምጣቷ የልጅነት ህልሟ እንዲሳካላት መንገድ ከፍቶላታል፡፡ በ1995 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በመዉሰድ ወደ መሰናዶ ት/ቤት የሚያሰገባትን ዉጤት ብታመጣም እሱን ትታ በ1996 ዓ.ም ነቀምቴ መምህራን ኮሌጅ በመግባት ለሶስት አመታት ትምህርቷን ተከታትላ በ1998 ዓ.ም በዲፕሎማ ተመርቃለች፡፡

በ1999 ዓ.ም በማታ ትምህርት አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ፋካሊቲ የመግባት እድል አግኝታ ለኣራት አመታት ትምህርቷን ከተከታተለች በኃላ በ2002 ዓ.ም በብሮድካሰት ቴሌቪዥን ቢኤ ዲግሪ ተመርቃለች፡፡ ማታ እየተማረች ሁለት አመታት ሸጎሌ አካባቢ ይባል በነበረ ፋሲል ት/ቤት አስተምራለች፡፡

በበሪሳ መቀጠርና ቆይታዋ

በ2001 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአፋን ኦሮሞ ለሚዘጋጀው የበሪሳ ጋዜጣ ለሪፖርተርነት በወጣው ማስታወቂያ በመወዳደር ጥሩ ውጤት በማምጣቷ የምትወደውን ሙያ ሀ ብላ ጀመረች ።

ትምህርቷ የህትመት ጋዜጠኝነት ስላልሆነ በሪሳ ጋዜጣ ላይ ብዙ እቆያለው ብላ ያላሰበችዉ ሳምራዊት፣ በሁኔታዎች አስገዳጅነት እስከ ዛሬ ቆይታለች፡፡ በተለይ ታሪካዊውን ጋዜጣን ህትመት ለማቆም የነበረው ፍላጎት በሪሳን ትታ እንዳትሄድ አድርጓታል።

በሪሳን የመታደግ ትግል

በሪሳ ጋዜጣ ዛሬ ላይ 45 አመታትን ብታስቆጥርም ማደግ ያለባትን ያህል አለማደጓ በተለይም በወቅቱ የነበሩት አመራሮች ጋዜጣዋ በገቢ ምክንያት እንድትዘጋ በማሰብ ወደ መፅሔት ለመቀየር አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበረ ሲሆን፣ ይህንንም ተከታትላ መረጃ በመያዝ በወቅቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ሃገር ለሚገኙ ሚዲያዎች በማጋራት እንዲሁም ለአመራሮች በማስደወል ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ጥረት አድርጋለች፡፡ በዚህም ተገምግማ እና ነገሮች ተጣርተው መረጃ ከተገኘባት እርምጃ እንደሚወሰድባት ተነግሯት ነበር፡፡

ደመወዝን የተመለከተ ትግል እስከ ፓርላማ

የዝግጅት ክፍሉ ጋዜጠኞች ተስፋ ቆርጠው ጋዜጣዋን ትተው እንዲሄዱና የሚሰራ ሰው ጠፋ ተብሎ እንዲዘጋ ተመሳሳይ የትምህርት ደረጃና የስራ ልምድ እያላቸው በደመወዝ አንድ ደረጃ ዝቅ ተደርጎ ከ3 አመታት በላይ እንዲከፈላቸው ተደርጓል፡፡ ይህንንም በመቃወም ከሌሎች ባልደረቦቿ ጋር በመሆን እስከ ፓርላማ ድረስ በመሄድና አሰራሩ ትክክል አለመሆኑን በመረጃ በማስደገፍ ተከራክራ እንዲስተካከል የበኩሏን አስተዋፅኦ አበርክታለች፡፡

ጋዜጣዋን የማሳደግ ጥረት

የበሪሳ ጋዜጣ እንዳይዘጋ ብቻ ሳይሆን ተፈላጊነትና ተነባቢነቱ እንዲጨምር በተለይ ባህል ገፅ ላይ ብዙ ስራዎችን ሰርታለች፡፡ በተጨማሪም ከቋንቋና ስነ ፅሁፍ ላይ የተለያዩ ምሁራንን በማነጋገር የምታቀርባቸው አርቲክሎች በብዙዎች የሚነበቡና በሚዲያዎችም የሚወሰዱ ናቸው፡፡ የተለያዩ ድርጅቶችም ጋዜጣዋን እንዲወስዱ፣ ማስታወቂያ እንዲያወጡባት የታተሙ ጋዜጦችን ከባልደረቦቿ ጋር ተሸክማ እስከማከፋፈል ድረስ የራሷን አስተዋፅኦ አድርጋለች፡፡

ሙያዊ ተግባራት

በቆየችባቸዉ የጋዜጠኝነት አመታት ትላልቅ ሃገራዊ ጉዳዩችን እንደ ምርጫ፣ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤዎች፣ የኢሬቻ በአል፣ መስቀል፣ ጥምቀትና የመሳሰሉትን ለመዘገብ እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ሃለፊዎች፣ ሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች እና ታዋቂ ግለሰቦችን በማነጋገር በርካታ ዜናና መጣጥፎችን ፅፋለች፡፡ ከሃገር ዉጭም የተለያዩ ታዋቂ ሰዎችን ቃለመጠይቅ አድርጋለች፡፡ ለአብነትም ታዋቂው የአለማችን ቢሊየነር ቢል ጌትን የማናገር እድሉን አግኝታለች፡፡

ለበሪሳ ያላት አቋም

በአጠቃላይ በበሪሳ ጉዳይ የማትደራደረው እና የተለያዩ ልክ የማይመስሉ ነገሮችን ስታይ የማታልፈዉ ሳምራዊት፣ በተማረችበት የትምህርት አይነት እና ካላት ልምድ አንፃር ሌሎች ሚዲያ ላይ መስራትና የራሷን ስራ ለማከናወን ብዙ እድሎች ቢኖሯትም ጋዜጣዋ ተለውጣ እስከምታይ የራሷን ጥቅም ወደ ጎን በማድረግ በሪሳን ላለመተው ወስና እየሰራች ነው፡፡

በምታደረገው እንቅስቃሴና ለበሪሳ ባላት ተቆርቋሪነት የተለያዩ ጫናዎች ሲደርሱባት ጋዜጠኛ ሳምራዊት፣ ከዚህ የተነሳም በ2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ለሴቶች የሚሰጠውን የኤምኤ የትምህርት እድል አግኝታ ስራ እየሰራች እንድትማር የድጋፍ ደብዳቤ እንዲፅፉላት ስትጠይቅ ቀደም ሲል የበሪሳ ጋዜጣ ህትመት እንዳይቆም የምታደርገውን ጥረትና ትግል ጥርስ ውስጥ አስገብቷት ነበርና በወቅቱ የነበሩት አመራሮች ሳይፈቅዱላት እድሉ ሊያመልጣት ችሏል።

የስራ ላይ ታታሪነት

በስራ ታታሪነቷ በድርጅቱ ዉሰጥ የምትታወቃውና በተለያዩ ጊዜያት ከምስክር ወረቀት ጀምሮ እስከ ገንዘብ የተሸለመችው ሳምራዊት፣ በበሪሳ ጋዜጣ ከሪፖርተርነት እስከ ከፍተኛ አዘጋጅነት እያገለገለች ትገኛለች፡፡ ከሙያ አንፃርም በተለያዩ ርእሶች ላይ በሃገር ውስጥ እንዲሁም ከሃገር ውጭ ስልጠና በመወሰድ የምስክር ወረቀቶችን አግኝታለች፡፡

ምኞት

ዛሬ ላይ ስትታገልላት የነበረችዉ በሪሳ ጋዜጣ በመጠኑም ቢሆን ተሻሽላ በማየቷ ደስተኛ መሆኗን የምትናገረዉ ጋዜጠኛ ሳምራዊት፣ በተለይ አንጋፋዋ ጋዜጣ በኦንላይን ሚዲያ አንባቢ ጋር እየደረሰችና ተመራጭ እየሆነች መምጣቷ ያስደስታታል፡፡ ለወደፊትም የእነ ጃል ሌንጮ ለታ፣ ፕሮፌሰር ማሃዲ ሃሚድ ሙዴ (አባ በሪሳ)፣ ፕሮፌስር ኩዌ ኩምሳና የሌሎች ውጤት የሆነችው በሪሳ እንደስሟ ንጋት ሆና ማየት ምኞቷ ነው፡፡

የቤተሰብ ሁኔታ

ጋዜጠኛ ሳምራዊት ግርማ በ2009 ዓ.ም ከባለቤቷ አቶ አያና ወልተጂ ጋር ትዳር በመመስረት አንድ ሴትና አንድ ወንድ ልጆችን አፍርታለች፡፡

የመዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ሳምራዊት ግርማ የጋዜጠኝነት ፍቅር ያደረባት ገና በልጅነት ነበር፡፡ ይህ የጸና ፍቅር ዛሬም አልበረደም፡፡ ሳምራዊት ወጣት ብትሆንም በተለይ በአፋን ኦሮሞ የህትመት ሚድያ ታሪክ ውስጥ አዲሱን ትውልድ በመወከል የራሷን አሻራ ማሳረፍ የቻለች ናት፡፡ የበሪሳ ጋዜጣ የህትመት ብርሀን እንዲያይ፣ በመንግስት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጠው ሳምራዊት ግላዊ ጥረቷን አድርጋለች፡፡ ሳምራዊት ሳምንታዊ በሆነው ‹‹በሪሳ›› ጋዜጣ ላይ ባለፉት 13 አመታት ከ1300 በላይ ጽሁፎች ታትመው ወጥተውላታል፡፡ ሳምራዊት ግርማ በንቲ፣ ጋዜጠኝነት ከልብ ትወዳለች፡፡ በተለይ ደግሞ በአፋን ኦሮሞ የህትመት ጋዜጠኝነት ላይ አንድ ታላቅ አስተዋጽኦ ለማድረግ አሁንም ጥረቷን ቀጥላለች፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም ላደረችው ጥረት ምን ያህል እውቅና አገኘች? ግለ-ታሪኳስ በሚገባ ይታወቃል ወይ? እኛ የዚህ ኢንሳይክሎፒዲያ አዘጋጆች የሳምራዊትን ግለ-ታሪክ ስናወጣ አዲስ እየጀመሩ ላሉ ጋዜጠኞች የምታስተምረው ነገር አለ፡፡ ጽናትን፤ ሳይፈሩ ላመኑበት ነገር መቆምን ከሳምራዊት መማር እንችላለን፡፡የእነ ሳምራዊት ታሪክ ተሰንዶ መቀመጡ ለኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ እንዲህ ነበር ለካስ ተብሎም የሚነበብ ግለ-ታሪክ ይሆናል፡፡የትጉሀንን ታሪክ አፈላልጎ ማውጣት ቀዳሚ ስራችን ሲሆን ከእነዚህ ትጉሀን መካከል ደግሞ ሳምራዊትን አቅርበናል፡፡ / ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተቀናበረ ከባለ ታሪኳ የተገኙ መረጃዎችን በመያዝ የተጻፈ ነው፡፡ ለዚህ ግለ-ታሪክ መሰናዳት የበሪሳ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ቸርነት ሁንዴሳ ላደረገው ትብብር ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ ግለ-ታሪክ ዛሬ እሁድ የካቲት 27 2014 በተወዳጅ ሚድያ ግለ-ታሪክ ገጾች ላይ ወጣ፡፡ እንደአስፈላጎነቱ ማሻሻያዎች እየታከሉበት በየጊዜው እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *