ሲሳይ ንጉሱ የዛሬ 45 አመት ለሳንሱር ክፍል የጻፈው ደብዳቤ /ከእዝራ እጅጉ/

ሲሳይ ንጉሱ

ከሰነዶቻችን ልዩ ልዩ ኦሪጅናል ሰነዶች የሚቀርብበት ነው፡፡

ያኔ ሲሳይ ንጉሱ በአዲስ ከተማ አጠቃላይ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ታዲያ ሲሳይ ብእር ከወረቀት አዋህዶ ‹‹ረጅሙ ጉዞ›› በሚል ርእስ አንድ ቤሳ ልቦለድ ጽፎ ነበር፡፡ ጊዜው 1971 አ.ም ነበር፡፡ ታዲያ ሲሳይ ሰመመንን ከማሳተሙ 6 አመት በፊት ‹‹ረጅሙ ጉዞ›› የተባለው ልቦለዱን ጽፎ ለሳንሱር ክፍል ሰጠ፡፡

ኦርጂናል ስክሪፕቱን ከእነ ደብዳቤው እንዳየሁት ሲሳይ ንጉሱ ድርሰቱ እንዲታተምለት ከፍተኛ ጉጉት አሳድሮ ነበር፡፡ እናም ከድርሰቱ በፊት ለማስታወቂያ እና መርሀ ብሄር ሚኒስቴር አያይዞ ደብዳቤ ጽፎ ነበር፡፡ የደብዳቤውን ኦርጂናል ቅጂ ማለትም ከሲሳይ የእጅ ጽሁፍ ጋር አንድ ላይ በማድረግ አብሬ ፖስት አድርጌዋለሁ፡፡ ይህን ጽሁፍ ፖስት ከማድረጌ በፊትም ሲሳይ ጠይቄዋለሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ያኔ በታዳጊነት የጻፈው ደብዳቤ ከእጁ ያለ አይመስለኝም፡፡ ለማንኛውም ሲሳይ 45 አመት ወደኋላ ተመልሶ የራሱን የእጅ ጽሁፍ እንዲያነብ ጋበዝኩት፡፡

ቀን ሀምሌ 27 1971

በህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በማስታወቂያና መርሀ ብሄር ሚኒስትር የምርመራ አገልግሎት

አዲስ አበባ

በከፍተኛ 24 ቀበሌ 17 ነዋሪ የሆንኩት እኔ ተማሪ ሲሳይ ንጉሱ ሰፋ ያለ ድርሰት በማዘጋጀቴ ወደ ህዝብ ቀርቦ እንዲነበብልኝ ጥረት በማድረግ ላይ ነኝ፡፡ የተማሪነት ደረጃዬ ለህትመት የሚወጣውን ገንዘብ መቋቋም ስለማያስችለኝና የቤተሰቦቼም የኑሮ ደረጃ ይህንኑ ፍላጎቴን እንዲያዳብሩልኝና የህትመት ወጪውን እንዲያቃልሉኝ ስለማይፈቅድላቸው ሌላ መንገድ መፈለጉ ግድ ሆነ፡፡ በዚህ መሰረት የባህል እና የስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ጽሁፌን ተመልክቶ በማሳተሙ ረገድ እንደሚረዳኝ ቃል ገብቶልኛል፡፡ ይህን ለማድረግ ጽሁፉ በመጀመሪያ ወደ ሳንሱር ክፍል መቅረብ አለበትና የሳንሱር ክፍሉም የሚመለከተው ጽሁፍ በታይፕ መተየብ እንዳለበት ብረዳውም ቅሉ የእኔ አቅም ይህን ለማድረግ አልፈቀደልኝም፡፡

ስለዚህም ከላይ የገለጽኩትን ችግሬን በመመልከት የሳንሱር ክፍሉ ድርሰቴን በእጅ ጽሁፍ / ታይፕ ሳይመታ / ተመልክቶ በማረም አብዮታዊ ትብብር ያደርግልኝ ዘንድ በማክበር አመለክታለሁ፡፡

ተማሪ ሲሳይ ንጉሱ

ፊርማ አለው

ስልክ የቀበሌ 448921

ይህ የሲሳይ ድርሰት ከ4 አመት በኋላ ጉዞው በሚል ርእስ ለማታተም በቃ፡፡

ደራሲ እና መምህር ሲሳይ ንጉሱ…..

በ1951 ዓ.ም እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ደጃች ውቤ /ውቤ በረሃ/ ነው የተወለደው፡፡ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በባልቻ አባነፍሶ ፣ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ት/ቤት ተከታትሏል፡፡ከዚያም በ1974 ዓ.ም አስመራ ዩኒቨርስቲ ገብቶ በስነ ፅሁፍ እና ቋንቋ በ1977 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ 11ኛ ክፍል እያለ “ጉዞው” የተሰኘ ኖቬላን የመጀመሪያ ስራው አድርጎ አሳትሟል፡፡ይህንን ጨምሮ 6 ያህል መፅሃፍትን እስካሁን ለአንባቢያን አድርሷል፡፡

“ሰመመን” የተሰኘው የረጅም ልብ ወለድ ድርሰቱ ከፍተኛ ተነባቢነትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያገኘለት ስራው ሲሆን በወቅቱም 60 ሺ ያህል ቅጂዎች ተሸጠውለታል፡፡በ1978 ዓ.ም የታተመው እና 378 ገፆች ያሉት “ሰመመን” በዩኒቨርስቲ ህይወት ዙሪያ እና በፍቅር ታሪክ ላይ ያተኩራል፡፡ መፅሃፉ የተፃፈው ደራሲ ሲሳይ ንጉሱ በአስመራ ዩኒቨርሰቲ የ 3ኛ አመት ተማሪ እያለ ነበር ፡፡

የደራሲው ሥራዎች፡-

1. ጉዞው ( ኖቬላ ) – 1975 ዓ.ም

2. ሰመመን ( ልብ ወለድ ) – 1977/8 ዓ.ም

3. ግርዶሽ ( ልብ ወለድ ) – 1981 ዓ.ም

4. ትንሳኤ ( ›› ›› ) – 1983 ዓ.ም

5. የቅናት ዛር ( ›› ›› ) – 1988 ዓ.ም

6. ረቂቅ አሻራ ( ›› ›› ) – 1995 ዓ.ም

“ሰመመን” የተሰኘው ድርሰቱን በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሲያሳትም፤ ግርዶሽ፣ ትንሳኤ፣ የቅናት ዛር እና ረቂቅ አሻራን በአርቲስቲክ እና ሜጋ ማተሚያ ድርጅቶች በግሉ ነው ያሳተማቸው፡፡ በ1983 ዓ.ም አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት የታተመውን “ትንሳኤ” መፅሃፍ መታሰቢያነቱን በፋሽስቶች “ቀይ ሽብር” ለወደቅው /ለሞተው/ አጎቱ ለታምሩ ተክሉ አድርጓል፡፡ በዚሁ ማተሚያ ቤት በ 1995 ዓ.ም የታተመው “ረቂቅ አሻራ” ደግሞ ማስታወሻነቱን ለባለቤቱ ብስራት አሰፋ እና ለልጁ ትንሳኤ ሲሳይ ይሁንልኝ በማለት ነው ለአባቢያን ያበረከተው፡፡

አስመራ ዩኒቨርሰቲ እያለ የስነ ፅሁፍ እና የቲያትር ክበብ መስርቶ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ የ ’’ብዕር አምባ’’ በሚል ስያሜ፡፡ የ4ኛ አመት የዩኒቨርሰቲ ተማሪ እያለም ‘’ስዊት ዲስ ኦርደር’’ የሚል ቲያትር ደርሶ ለእይታ አብቅቷል፡፡ ቲያትሩ በአሉላ አባ ነጋ አዳራሽ የታየ ሲሆን በወቅቱም በተመልካች ዘንድ ተወዳጅ ነበር፡፡ በዚህ ቲያትር ላይ ሲሳይም በተዋናይነት ተሳትፏል፡፡

አስመራ ዩኒቨርሰቲ ለ2 አመት ካስተማረ በኋላ ሙሉ ጊዜውን ለስነ ፅሁፍ በማድረግ ግርዶሽ የተሰኘውን ድርሰቱን አሳትሟል፡፡ ይህ መፅሃፍም ከ “ሰመመን” ቀጥሎ ከፍተኛ ሽያጭ ነበረው ፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥም 40 ሺ ቅጃዎች ተሸጦለታል፡፡ ደራሲና መምህር ሲሳይ ንጉሱ ለ 10 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በዋና ፀሀፊነት አገልግሏል፡፡ ካለፉት የተወሰኑ አመታት ጀምሮ ደግሞ ውጪ ከሚገኙ ወዳጆቹ እና ጓደኞቹ ጋር በመሆን አንድነት ኢነተርናሽናል ት/ቤትን ከፍተው በአመራርነት እየሰራ ይገኛል፡፡ ደራሲ ሲሳይ ንጉሱ በ1991 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ስነ ጥበባት እና መገናኛ ብዙሃን ሽልማት ድርጅት በስነ ፅሁፍ ዘርፍ ተሸላሚ ነበር፡፡በወቅቱም 20 ሺ ብር፣ የክብር ዲፕሎማ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተበርክቶለታል፡፡

በትምህርት አስተዳደር እና አመራር የማስተርስ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *