ሰለሞን ጓንጉል አበራ

ሰለሞን ጓንጉል አበራ

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡

በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡  ከሚድያ ዘርፍ አሻራ ካኖሩ መካከል ሰለሞን ጓንጉል አበራ ይጠቀሳል፡፡ የህግ ሙያን እና ጋዜጠኝነትን አጣጥሞ ያቀርባል፡፡

ትውልድ እና ልጅነት 

 ሰኔ 23 ቀን 1974 ዓ.ም ፤ በእለተ ሐሙስ እትዬ ተዋበች የተባሉ ደርባባ የጎረቤት ሴት ጎረቤቶቻቸውን አስከትለውና በአቶ ጓንጉል አበራ ቤት ተገኝተው ወ/ሮ ካሰች ፋንታሁንን “ማርያም ማርያም” እያሉ አዋለዱ፡፡ የቤቱ ሶስተኛና የመጨረሻ ልጅ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክ/ከተማ በተለምዶ አቧሬ በሚባለው አካባቢ ተወለደ ፡፡ ለቤትና ለሰፈር ውስጥ መጠሪያነት ቴዎድሮስን ለመዝገብ ስም ደግሞ ሰለሞንን አወጡለት፡፡

እትብቱ አቧሬ ይቀበር እንጂ የዛሬ ማንነቱ መሰረት የተጣለው ፤ የልጅነት ሕይወት ትዝታው ሁሉ ያለው ፈረንሳይ ለጋሲዮን ነው፡፡ አጋምና ቀጋ እየለቀመ ፤ በየሜዳው እየቦረቀ ፤ የጎበና ምንጭ ውሃን እየጠጣ ከታላቁ አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ ቤት ትንሽ ከፍሎ ብሎ ከሚገኝ ሰፈር ልጅነትን ፤ ጉርምስናንና ወጣትነቱን አሳልፏል፡፡

ትምህርት 

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በንጋት ኮከብ ፤ ቅዱስ ማርቆስና ሚያዚያ 23 ት/ቤቶች፤ የሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በከፍተኛ 12 ተከታትሏል፡፡ መምህርነትን በኮተቤ መምሕራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ፤ የሕግ ትምሕርትን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ቅድስተ-ማርያም ዩኒቨርሲቲ ተምሯል፡፡

ስራ አለምና መምህርነት

ከልጅነቱም ጀምሮ ማንጎራጎርና ዘፈንን ቢወድም ልቡ ይበልጥ ያደላው ግን ወደ ጋዜጠኝነት ነው፡፡ በእርግጥ ስራን ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረው በመምሕርነት ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቫቲካን አካባቢ በሚገኘው ተስፋ ት/ቤት ከ 1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ደረጃ ያሉ ተማሪዎችን ለአራት አመታት አስተምሯል፡፡ ቀጥሎ የእንጀራ መንገዱ አርቆ የወሰደው ወደ ቤንች ማጂ ዞን ሸዋቤንች ወረዳ ነው፡፡ እዚያ በ1997 ዓ.ም በአቃቤ ሕግነት ለአስር ወራት ገደማ ከሰራ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ በአጋር ማይክሮፋይናንስ በነገረፈጅነት ለ ሁለት ዓመታት ያሕል ሰርቷል፡፡

ትውውቅ -ከጋዜጠኝነት ጋር 

“ከፍተኛ አስራሁለት በሚገኝ ት/ቤት ውስጥ ባለ ሚኒ ሚድያ መስራት፤ ጋዜጠኛ የመሆን ስሜት በስሱ ሽው እንዲልብኝ አደረገ ፤ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ የአማርኛ ቋንቋ መምሕሬ የነበሩት መምሕር በየነ ፤ ልቦለድ መጽሐፍትን መጀመሪያ በራሴ ክፍል ከዚያ ደግሞ ወደሌሎች ክፍሎች እየሔድኩ ተማሪዎች ፊት እንዳነብ አደረጉኝ፡፡ የእርሳቸውም አብረውኝ ይማሩ የነበሩ ጓደኞቼም አድናቆት ሚኒሚድያ ስሰራ የተሰማኝ ስስ ሽውታ ወፈር ወዳለ ሞቅታ እንዲያድግ አደረገ ፡፡” ይላል ሰለሞን የጋዜጠኝነት አጀማመሩን ሲያስታውስ፡፡

በሚኒ ሚድያው ለሚያቀርበው የስፖርት ፕሮግራም ‹‹ኢንተር ስፖርት››ና ‹‹ሊብሮ›› የተሰኙ የስፖርት ጋዜጣዎችን ለመግዛት ዘወትር ቅዳሜ ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ስድስት ኪሎ ድረስ በእግር መመላለስ ነበረበት፡፡ የፈረንሳይ ለጋሲዮንን የድሮ ቀጥ ያለ ዳገት ለሚያስታውስ ሰው መመላለሱን ይህማ ጉብዝና ነው እንደሚለው አይጠረጠርም፡፡ በትምህርት ላይ አታተኩርም ሳይሉና ሳይቆጡ ለጋዜጣ መግዣ የሚሆነውን ገንዘብ ይሰጡት የነበረውን አባቱን አቶ ጓንጉል አበራንም ያመሰግናል፡፡ ነግሬያቸው ባላውቅም ጋዜጦቹን ያሳትሙ የነበሩት የኢንተር ስፖርቱ መንሱር አብዱል ቀኒና የሊብሮው ጋዜጣ ገነነ መኩሪያም ውለታቸው እንዳለብኝ ይሰማኛልም ይላል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ ያዘጋጀውን ጽሑፍ በራሱ ድምጽ በኢትዮጵያ ራዲዮ ቅዳሜ ከሰአት ፕሮግራም ላይ እንዲያቀርብ እድሉን የሰጠውን የተቋሙን ጋዜጠኛ ዳንኤል ታደሰን ያመሰግናል፡፡ እርሱ የሰጠው ዕድልና ውጤቱ ፤ የጻፈውን በራዲዮ ማንበብና እርሱንም ሰምቶ ደስ መሰኘት ብቻ አይደለም ፡፡ በውስጡ የትችላለህ መልዕክትን ለራስ ያስተላልፋል ፤ ተስፋና የወደፊት ሕይወትንም ይገነባል ፡፡ አላወቀውም እንጂ ዳንኤል ያደረገልኝ ይሄንን ነው ፡፡ እስከዛሬ በቅጡ አላመሰገንኩትምና አሁን ላመሰግነው እፈልጋለሁ ይላል ሰለሞን ፡፡ ለታዳጊዎች ፤ ለወጣቶች እንዲህ ያለ ዕድል መስጠት የወደፊት የህይወት መስመራቸውን እንዲያሰምሩ መርዳትንም የሚያካትት ትርጉመ- ብዙ መልካም ተግባር ነው ሲልም ያክላል፡፡

ጋዜጠኝነት -እንደ እንጀራ

ሸገር ኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያ ሥርጭቱን ከጀመረ ከስድስት ወራት በኋላ ገደማ የራዲዮ ጣቢያውን በመቀላቀል በሪፖርተርነት ፤ በዜና አንባቢነት ፤ በዜና ክፍል አዘጋጅነት እንዲሁም በፕሮግራም አዘጋጅነትና አቅራቢነት ለ3ዓመታት ገደማ ሰርቷል፡፡ በተለይ በፍርድ ቤትና ሕግ ነክ  ዜናዎች ዘገባ ላይ አተኩሮ ብዙ ስራዎችን የሰራ ሲሆን “ኧረ በሕግ” የተሰኘ እና የአንድ ሰአት ቆይታ የነበረው የሚወደድ የሕግ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢም ነበር፡፡ በጣቢያው በነበረው ቆይታው እንደአለቃም ፤ እንደታላቅ ወንድም እንደ ጓደኛም በመሆን ዕድልና ከበድ ያለ ሃላፊነትም ጭምር በመስጠት ያበረታኝና ምንም ያልከፈልኩት የአቶ ስለሺ ተሰማ ውለታ ብዙ ነው ይላል ፡፡

በሸገር የተጣለው የጋዜጠኛነት ህይወት መሰረት ይበልጥ እያደገ መጥቶ የራሱን ድርጅት (ሰለሞን የማስታወቂያና ሕትመት ስራ ድርጅት ) በ2002 ዓ.ም በማቋቋም ላለፉት አስር አመታት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ “የእኔ መንገድ” ሲል ስም በሰጠው የራዲዮ ፕሮግራሙ በሕግና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የአንድ ሰአት ቆይታ ያላቸው ከ አራት መቶ በላይ የተለያዩ ራዲዮ ፕሮግራሞችን በመስራት በኤፍ ኤም 96.3 እና በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 እንዲተላለፉ አድርጓል ፡፡

” ምላሽ”  በሚል ስያሜ ከኤች አይ ቪ ጋር በተገናኘ በሚነሱ የሕግና የሥነምግባር ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሃምሳ አራት ያሕል የራዲዮ ፕሮግራሞች እንዲሁም ” ብርሐን ” በሚል የፕሮግራም ስያሜ ደግሞ በአካልጉዳት በተለይ ከጊዜ በኋላ በሚመጣው ላይ በማተኮርና የመጣውን ተቀብሎ በስኬት ስለመኖር ፡ ኖረው ያዩትን ምሳሌ ያደረጉ ከሃያ በላይ ራሳቸውን የቻሉ የራዲዮ ፕሮግራሞች በፋና ኤፍ ኤም 98.1 ላይ በማዘጋጀት አቅርቧል፡፡ የሰለሞን ፕሮግራሞች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ቀድመው ታቅደው ፤ ስክሪፕት ተዘጋጅቶላቸውና ተቀርጸው የሚቀርቡ ናቸው፡፡

በማስታወቂያና የሕዝብ አገልግሎት መልዕክቶች ዝግጅትም ሰለሞን ከ 150 በላይ የራዲዮና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ፤ እንዲሁም የሕዝብ አገልግሎት መልዕክቶችና የዶክሜንታሪ ፊልም የስክሪፕት ጽሑፎችን አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡

ጠበቃው- ሰለሞን

ሰለሞን ጓንጉል ነፍሴም ደስ ብሏት ነው የምትሰራው ከሚለው የጋዜጠኝነት ስራ በተጨማሪ በጥብቅና ሙያ ሌላ ምጣድ ጥዶ እንጀራውን ይጋግራል፡፡ በማናቸውም የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃ ሲሆን ሕግ ነክ ጽሑፎችንም በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሄቶች አሳትሟል፡፡ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማሕበር ( የኢትዮጵያ ጠበቆች ማሕበር) የ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዮ መጽሄት ” ሕግና ፍትሕ ሲጣሉ ” በሚል ርእስ ያቀረበውን ትችት አትሞታል፡፡ በተጨማሪም ሴቶች ራሳቸውን በራሳቸው ወክለው በፍርድ ቤት እንዲከራከሩ የሚረዳቸውን ” የአንቺው ጠበቃ አንቺው ” በሚል ርእስ የተዘጋጀ መምሪያ አዘጋጅቷል ፡፡ ይሕም ስራው መምሪያው እንዲዘጋጅ ባደረገው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማሕበር አማካኝነት በኦሮሚፋና በትግርኛ ቋንቋ ተተርጉሟል፡፡ ለሕትመት ያልበቁ 2  ስራዎችም አሉት፡፡

  ሰለሞን ጓንጉል ከወ/ሮ ማሕሌት ለገሰ ትዳር የመሰረተ ሲሆን የሁለት ልጆችም አባት ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *