ረዳት ፕሮፌሰር አለም እሸቱ

ረዳት ፕሮፌሰር አለም እሸቱ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡

ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ረዳት ፕሮፌሰር አለምእሸቱ ይገኝበታል፡፡ ይህ በጎልማሳነት እድሜ ላይ የሚገኝ ምሁር በተለይ ለህጻናት ስነጽሁፍ ማደግ ግንባር ቀደም ሚናቸውን ከተወጡ ባለሙያዎች ቀዳሚ ተጠቃሹ ነው፡፡ ይህ ሰው ተማሪዎች ላይ በጎ ተጽእኖ መፍጠር የቻለ ጊዜውን በምርምር እና በማሳተም ያሳለፈ በመሆኑ የህይወት ታሪኩ ያስተምራል ብለን እናስባለን፡፡ ይህን የህይወት ታሪክ ስንሰራ የቁምነገር መጽሄት ባለቤት እና መስራች ታምራት ሀይሉና የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ዘላለም ጌታቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡ እዝራ እጅጉ የረዳት ፕሮፌሰር አለምን ታሪክ እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡

ትውልድ እና ትምህርት

ረዳት ፕሮፌሰር ዓለም እሸቱ በየነ፣ በ1959 ዓ.ም አዲስ አበባ ልዩ ስሙ አዲስ ከተማ በሚባለው አካባቢ ተወለደ፡፡እናቱ ወይዘሮ ወሰኔ ማሞ አባቱ ደግሞ አቶ እሸቱ በየነ ይባላሉ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው አዲስ ከተማ በሚገኘው ብርሃነ ህይወት ትምህርት ቤት ጀምሮ ቀሪውን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ፈረንሳይ አቦ በሚገኘው የመካነ ህይወት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቀ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በእንጦጦ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፈፀመ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ አቀና፡፡

ኮሌጅ እና ዩኒቨርሲቲ

በኮሌጁ ቆይታው ከኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ- ፅሁፍ ክፍል በ1979 ዓ.ም በዲፕሎማ ተመርቆ በቀድሞው ባሌ ክፍለ ሀገር በሮቤ ከተማ ለ2 ዓመት በአማርኛ ቋንቋ መምህርነት አገለገለ፡፡ በመቀጠልም ትምህርቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ- ፅሁፍ ክፍል ቀጥሎ የተቋሙ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ በመሆን በከፍተኛ ማዕረግ በ1984 ዓ.ም በባችለር ዲግሪ መመረቅ ችሏል፡፡

ከምረቃ ቀጥሎ

ከምረቃ በኋላ ወደ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በማምራት በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ፅሁፍ ክፍል በረዳት ምሩቅነት፣ በረዳት ሌክቸረርነት፣ በሌክቸረርነትና በረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ ለአሥራ አንድ ዓመታት ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 7 ዓመታቱን ያሳለፈው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ -ፅሁፍ ክፍል ሊቀመንበር ሆኖ ነው፡፡ በመቀጠልም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተሻግሮ በተለይም በድህረ- ምረቃው ትምህርት ክፍል ውስጥ ለስድስት ዓመታት ያህል አስተምሯል፡፡

ወደ ድርሰት ጉዞ

ረዳት ፕሮፌሰር አለም ወደ ድርሰት ዓለም የገባው ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ ‹‹አማርኛ ለውጭ ሀገር ዜጎች›› በሚለው መፅሀፉ ጀምሮ በቁጥር 116 የሚሆኑ መፅሀፎችን ለህትመት ሊያበቃ ችሏል፡፡ በተለይ በህፃናት መፃህፍት ላይ ማተኮር የጀመረው ግን ከዩኒቨርሲቲ ኦፎ ኬፕታውን በህፃናት መሠረታዊ ትምህርት ላይ ተመርቆ ከተመለሰበት ማግስት ጀምሮ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የህፃናት መፃህፍት መፃፍና መተርጎም ችሏል፡፡ ከእነዚሁ መካከል ሦስቱ ወደ ፊንላንድ ቋንቋ የመተርጎም ዕድል አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለህትመት የተዘጋጁ ወደ ሃያ አምስት የሚሆኑ መፃህፍት አሉት፡፡ እነዚህ መፃህፍትም በቅርቡ የህትመት ብርሃን ያያሉ ፡፡

ረዳት ፕሮፌሰሩ ከ25 ዓመት በላይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአማርኛ ትምህርት መስክ አስተምሯል፡፡ በማስተማር ሙያው ቁርጠኛ በመሆን፣ ተማሪው አቅሙን ሁሉ አሟጦ እንዲጠቀም የሚያስችል ስልት በመከተል እና ጥንካሬና ትጋትን በማሳየት በርካታ ጋዜጠኞችን፣ መምህራንን እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ማፍራት የቻለ ነው፡፡ ዛሬም ጭምር በርካታ ተማሪዎቹ የጥንካሬ እና የትጋት አብነት አድርገው ይወስዱታል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር አለም የሀገሪቱ ትምህርት መሰረታዊ ችግር የህጻናት የትምህርት አሰጣጥ መንገድ እና መሰረታዊ የትምህርት መሳሪያ የሆነው የንባብ ክህሎት ችግር እንደሆነ እና ይህንን ሳይካኑ ወደሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መሸጋገራቸው ትርጉም እንደሌለው ያምንበታል፡፡ ማመን ብቻ ሳይሆን ይህንን ችግር ከስሩ ለመፍታት በግል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡

የተሳኩ ጥረቶች

  • ደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ ተቋም ጋር በመነጋገር እና ስልጠና በመውሰድ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህጻናት ሥነጽሑፍ ትምህርት በማይነር ደረጃ እንዲሰጥና በሂደት ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲደርስ አቅዶ ሰርቷል፡፡ ለአንድ ባች በማይነር ደረጃ እንዲሰጥ ከተደረገ በኋላም በተቋሙ አስተዳደራዊ ጉዳይ ላይ በተነሳ አሳዛኝ የውስጥ ችግር ተቋርጧል፡፡
  • አሜሪካ ሀገር ከሚገኝ የንባብ ድርጅት ጋር በመተባበር ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ወደ አማርኛ የልጆች መጻሀፍትን ተርጉሞ ወደኢትዮጵያ እንዲገባና እንዲሰራጭ ትልቅ ስራ ሰርቷል፡፡
  • በልጆች መጻሀፍት ዝግጅቱም የኩራዝ አዋርድም ማግኘት ችሏል፡፡

በተጨማሪም የአማርኛ ቋንቋ የመማሪያ መጻህፍት ዘልማዳዊ አቀራረብን በመቀየር ዘመናዊ የመማሪያ መጻህፍት እንዲዘጋጅ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በተለይ የሁለተኛ ደረጃ የአማርኛ ቋንቋ የመማሪያ መጻሀፍትን እና የመምህር መምሪያን በማሰናዳት ትልቅ አሻራ ማኖር ችሏል፡፡ ይህም የትምህርት ስራውን የበለጠ ማገዝ የቻለ ነበር፡፡

ከእዚህም ባሻገር ረዳት ፕሮፌሰር አለም አጋዥ የመማሪያ መጻሀፍትን በማዘጋጀት የዝግጅት መሰረታዊ መርሆዎችን በተግባር ለማስተዋወቅ ትልቅ ሙከራ ማድረጉ ይነገርለታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የልጆች የንባብ መጻህፍት የህክምና መሳሪያ ጭምር መሆኑን በመገንዘብ፣ የላንቃ መሰንጠቅ ያጋጠማቸው ህጻናት ከህክምናው በኋላ በቀላሉ የከንፈር እና የጥርስ ድምጾችን (በእነዚህ የሚፈጠሩ) እንዲጠሯቸው ለማለማመድ የሚረዱ የንባብ መጻሀፍት በማዘጋጀት፣ ከአሜሪካ የሚመጡ የህክምና ባለሙያዎች እንዲጠቀሟቸው በማድረግና በማሰልጠን ከፍ ያለ የህይወት ዘመን የመምህርነት አበርክቶውን የተወጣ የተከበረ መምህር ነው፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር አለም የኢትዮጵያን የልጆች ስነጽሁፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቅ በማድረግ የተወሰኑ መጽሀፍት በእንግሊዝኛ እና በአይሪሽ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል፡፡ ሁሉም ለልጆች የሚዘጋጁ መጻሀፍት በጣም ዝቅ ባለ ዋጋ እንዲሸጡ ለማድረግ ሞክሯል፡፡ በእዚህም የመጽሀፎቹ ዋጋ በሁሉም ሰው ዘንድ ሊገዛ በሚችል ዋጋ የቀረበ በመሆኑ በከፍተኛ ቅጂዎች ተሸጠዋል፡፡ ልጆችም የንባብ ክህሎታቸው እንዲያድግ አስተዋጽኦ በማድረግ በግል ጥረቱ የሀገሪቱ ትምህርት ያለበትን ክፍተት ለመሙላት ጥረት አድርጓል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር አለም በአሁኑ ሰአት ኑሮውን ኒውዮርክ ላይ የመሰረተ ሲሆን፣ እዚያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አማርኛ ቋንቋን በሚመለከት ስራዎች ሲኖሩ በትርፍ ጊዜ ሰራተኛነት ይሰራል፡፡

ታምራት ሀይሉ ስለ ረዳት ፕሮፌሰር አለም እሸቱ

መምህር አለም ለማስተማር የተፈጠረ ነው፡፡ የሀገሪቱን የትምህርት ስርአት ችግሮች የተረዳ፤ የተማሪዎችን አቅም ባገናዘበ መልኩ የትምህርት መርጃ መጽሃፍትን ተጠቅሞ በማስተማር የሚታወቅ መምህር ነው፤ አለም በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በሚያስተምርበት ወቅት ከተማሪዎቹ መሀከል አንዱ ነኝ፤አለም በክፍል ውስጥ ስለ ምርምር ዘገባ አዘገጃጀት፤ስለ ስነ ልሳን ፤በአፍ መፍቻ ቋንቋ ስለ ማስተማር ወዘት ሲያስተምር በቂ ዝግጅት አድርጎ ስለሚመጣ ከሚናገራቸው ነግሮች ውስጥ ይህኛው ይጠቅማል፤ ያኛው አይጠቅምም ተብሎ የሚታለፍ ነገር የለውም፤ በአጭሩ ለተማሪዎች በማይጠቅም ነገር ጊዜውን አያጠፋም፡፡

አለም ተማሪዎቹን ጓደኛ ማድረግ የሚችል መምህርም ነው፤ ከትምህርት ሰአት ውጪ ተማሪዎቹን መምከር፤ማወያየትና ችግራችውን መረዳት የሚችል ሰው መሆኑን መመስከር ያስፈልጋል፤ የትምህርት መሰረት መጣል ያለበት በህጻናት ላይ መሆን እንዳለበት ስለሚያምን በርካታ የህጻናት መጻህፍትን አዘጋጅቷል አሳትሟል፤ የአለም የተረት መጻህፍት ብዛት ከ100 በላይ ይሆናሉ፤ መጽሃፍቱ በግልጽ እና ቀላል ቋንቋ የተጻፉ በመሆናችው ህጻናቱ በታሪኩ ውስጥ አንብቦ የመረዳትንና የቋንቋ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፤ መጽሀፍቱ ከተረቶቹና ከታሪኮቹ የወጡ ጥያቄዎችን የያዙ በመሆናቸው ወላጆችም ራሳቸውን እንዲፈትሹ እድል ይፈጥራል፤

የአለም የተረት መጽሀፍት አንዳንዶቹ ከሀገራችን ስነቃሎችና አፈታሪኮች የተቀዱ ሲሆኑ ሌሎቹ ለህጻናት ተብለው የቀረቡ ትርጉም ስራዎች ናቸው፤ በመሆኑም በእኔ አምነት በኢትዮጵያ ውስጥ በአለም ደረጃ በብዛትም ሆነ በታሪክ አማራጭነት የአለምን ያህል መጽሃፍ የጻፈ ያሳተመና ለንባብ ባህል መጎልበት የሰራ ሰው አለ ለማለት ያስቸግራል፤ እንዳለመታደል ሆኖ አለም ብዙ ሊያስተምርና ብቁ ዜጋ ሊያፈራ በሚችልበት ወቅት ከሚወደውና ከተፈጠረበት ሙያ ርቆ ለመኖር ተገዷል፤ በስደት ሀገር ሆኖም ለህጻናት የተረት መጽሀፍ መጻፉን አልተወምና ለነገው ትውልድ ተስፋ ነው፤

ታምራት ሃይሉ የቁምነገር መጽሄት ማኔጂንግ ኤዲተር የቀድሞ ተማሪ

መምህር የሻው ተሰማ ስለ ረዳት ፕሮፌሰር አለም እሸቱ

አለም እሸቱ የምወደውና የማከብረው መምህር ነው፡፡ዓለም እሸቱን የማውቀው ኮተቤ ስማር ነው፡፡ አለም መጀመሪያ አካባቢ ቁጥብ የሆነ መምህር ነው፡፡ስትቀርበው ግን በጣም የሚወደድ መምህር ነው፡፡ የተወሰኑ ታታሪ ተማሪዎችን ያቀርባል፡፡ ጥሩ ለሰራ ተማሪ ውጤት ይሰጣል-ላልሰራ ደግሞ ይነፍጋል፡፡ በጊዜ አጠቃቀም ላይ አለም ለብዙዎች አርአያ የሚሆን ሰው ነው፡፡ከአንደበቱ ክፉ ነገር አይወጣም፡፡ አለም ከሚያስተምረው ነገር ውጭ ስለ ፖለቲካ እና ተዛማጅ ነገሮች ክፍል ውስጥ አያወራም፡፡ የሚያስተምራትን ነገር አስተምሮ ይወጣል፡፡ 3 ኮርሶችን አስተምሮኛል፡፡ አለም እሸቱ እኔን ያስተማረኝ በ1988-1989 ነበር፡፡ በተጨማሪም የጥናት ወረቀቴ አማካሪ እርሱ ነበር፡፡

አለም ኮተቤ ስቀጠር ተከራክሮ ያስቀጠረኝ እርሱ ነው፡፡ በእርግጥ እኔም ኮተቤ ለማስተማር ጥሩ ውጤት ነበረኝ፡፡ ቀደም ሲልም በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የማስተማር ልምድ ነበረኝ፡፡ በጊዜው እኔ እንዳልቀጠር ሌሎች ሲጠሙ እርሱ ግን ለቦታው ይገባዋል ተከራክሮልኛል፡፡ በተጨማሪም ደግሞ ውጭ ሀገር ስልጠናዎችን እንዳገኝ የጠቆመኝ እርሱ ነው፡፡ ከመጠቆም አልፎ ጥሩ ስልጠናዎችን እንዳገኝ ረድቶኛል፡፡ አካዳሚካሊ የረዳኝ ነገሮች አሉ በግል ጉዳይም ላይ ብዙ አግዞኛል፡፡ አለም ስለሀገሩ ያለው ፍቅር ጥልቅ ነው፡፡ እንደ አለም አይነት ሰዎች ትውልድ ላይ የመስራት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ታሪኩ በመዝገበ-አእምሮም ላይ በመሰነዱ ደስ ይለኛል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር አለም እሸቱ በዶክተር ዘላለም አንደበት

ዓለም እሸቱን የማውቀው ኮተቤ ስማር ነው፡፡ ዓለም፣ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በአማርኛ ቋንቋ እና ሥነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ስማር ያስተማረኝ፣ የመጀመሪያ ዲግሪ የመመረቂያ ጥናቴን ስሰራም ያማከረኝ መምህሬ ነው፡፡ በእርግጥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ ስማርም፣ እዚያም አስተምሮኛል፤ ድጋሚም አማካሪዬ ነበር፡፡ ስለዚህ ረዘም ላለ ጊዜ በመምህርነት የማውቀው እና የማማከር አቅሙንም ከሚረዱት መካከል ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡

ዓለም እሸቱ፣ በጣም ትጉህ መምህር ነው፡፡ ለማስተማር በሚመጣበት ጊዜ በአግባቡ ተዘጋጅቶ የሚመጣ፣ በተለያየ መልኩ በንባብ እና በህይወት ተሞክሮ ያገኘውን ከትምህርት ይዘቱ ጋር እያስተሳሰረ የሚያስተምር ስለነበር ሁሉም ተማሪ ክፍለ-ጊዜውን በአግባቡ ይከታተል እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ለእያንዳንዱ ጉዳይ በጥንቃቄ እና በተሟላ ዝግጅት ቦታ ይሰጥ ስለነበር ተማሪውም የእርሱን ፈተና፣ የጥናት ወረቀት ስራ እና ማናቸውም ውጤት የያዙ ስራዎችን በጥንቃቄ ይሰራ ነበር፡፡ በግሌ በእርሱ ትምህርት የተሻለ ውጤት ለማግኘት እሞክር እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከማስተማር ችሎታው እና ሁሉም ነገር በስርአት እንዲመራ ከመፈለጉ የተነሳ ሁሉም ተማሪ ሳይዝረከረክ የቻለውን ያህል ጥረት ያደርግ ነበር፡፡

ዓለም ሁሉንም ተማሪዎቹ እኩል ይመለከታል፡፡ በአንድ ኮርስ A ያመጣ ተማሪ በቀጣይ በአግባቡ ካልሰራ D ጭምር ሊያመጣ ይችል ነበርና ከዓለም ጋር የነበረ እውቂያ ወይም ቀድሞ የመጣ ውጤት ለቀጣዩ ኮርስ የሚፈይደው ነገር አልነበረም፡፡ በእርግጥ ውጤቱ ዝቅ ማለት ብቻ ሳይሆን፣ “ምን ስትሰራ ኖረህ ነው ይህንን ውጤት ያመጣኸው?!” የሚል ቁጣም አብሮ ስለሚሰጥ፣ ካሉበት ላለመውረድ ማንበብ፣ ግልጽ ያልሆነ ነገርም ካለ መጠየቅ የግድ ነበር፡፡

ዓለም፣ ጥሩም አማካሪ ነው፡፡ አብሮኝ ይማር የነበረ የሁለተኛ ዲግሪ መርሃግብር ተማሪን ላንሳ፡፡ የጥናት ስራው አልቆ የነበረ ቢሆንም ዓለም አማካሪው ነበርና ክፍተቱን በሚገባ በማሳየት ለፈተና እንደማያቀርበው እና አንድ ሴሚስተር እንዲጨምር ይነግረዋል፡፡ ልጁ በቅሬታ ውስጥ ሆኖ ተናዶ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የሆኖ ሆኖ የዓለምን ትእዛዝ መከተል ግድ ነበርና አንድ ሴሚስተር አንብብ ያለውን እያነበበ፣ ስራ የተባለውን እየሰራ ወረቀቱን ጨርሶ ለፈተና ቀረበ፡፡ ይህንን መምህር ከአመታት በኋላ ሶስተኛ ዲግሪውን ጨርሶ ተገናኝተን ስናወራ፣ ዓለም ጥናቱን በድጋሚ እንዲሰራ በማድረጉ በህይወቱ ትልቅ እውቀት እንደቀሰመ፣ ሁለት አመት ከተማረው በላይ በእዚያ ሴሚስተር በዓለም አማካሪነት ያገኘው እውቀት እንደሚልቅ ገለጸልኝ፡፡ ያንን ውሳኔ ዓለም ስለወሰነ አሁን እጅጉን እንደሚያመሰግነው ገለጸልኝ፡፡ እውነቱን ነበር፡፡ እኔም በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃግብር ላይ ያገኘሁት ትልቁ እውቀት የጥናት ስራዬን ስሰራ በእያንዳንዱ ጥቃቅን ጉዳይ ጭምር ዓለም አንብብ ይለኝ ከነበረው፣ ባነበብኩት ላይ አስረዳኝ ይለኝ ከነበረው፣ ከቅርጽ እስከ ይዘት በጥብቅ ይከታተለው ከነበረው ያገኘሁት እውቀት ነው፡፡

ዓለምን ከመምህርነት ባሻገር በልጆች መጽሀፍ ደራሲነቱም አውቀዋለሁ፡፡ መጻሀፍቱን ለልጆቼ በማንበብ፣ ለጥናት ስራዎችም በመጠቀም በሚገባ አውቃቸዋለሁ፡፡ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ገፊ ምክንያቶች ሆነውኝም ጥቂት የልጆች መጻሀፍት እንድጽፍ መነሻ ሆነውኛል፡፡ ዓለም መጻህፍቱ ሰፊ ስርጭት እንዲኖራቸው እና ሁሉም ሰው በአቅሙ ገዝቶ እንዲጠቀማቸው የዋጋ ተመኑን ሲያወጣ የሚጨነቀውን ነገር አውቃለሁ፡፡ አንዳንዴ የህትመት ወጪውን ይሸፍኑ ይሆን የሚል ስጋት ጭምር አለኝ፡፡ ዞሮ ዞሮ ዓለም ጥሩ መምህር ነውና ዋጋውን የሚተምነው ልጆች ምን ያህል መጻሀፍቱን አንብበው ተጠቀሙ በሚለው መለኪያ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ በአጭሩ ዓለም “መምህር” ለሚለው የተከበረ ስም በሚገባ የሚመጥን እና ብዙዎቻችን አርአያነቱን ተከትለን እንደርሱ ለመሆን እንድንፍጨረጨር በጎ ተጽእኖውን ያሳረፈ ድንቅ መምህር ነው ማለቱ ሁሉንም ሀሳቤን የሚያጠቃልልልኝ ይመስለኛል፡፡

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላትን አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር አለም በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ብቅ ካሉ ጎበዝ የስነጽሁፍ መምህራን ተጠቃሹ ነው፡፡ ይህ መምህር በተለይ ኮተቤ የተማረ ሁሉ በሚገባ ያውቀዋል፡፡ ብዙዎችን እውቀት ማስጨበጥ በመቻሉ ይከበራል፡፡ መምህርነት ክቡር ሙያ እንደመሆኑ ረዳት ፕሮፌሰርም ይህን ትልቅ ሙያ ወዶ አደራውን ሲወጣ ነበር፡፡ በተለይ መሰረታዊ በሆነው የህጻናት ስነ-ጽሁፍ ላይም ደማቅ አሻራውን ለማሳረፍ የቻለ ነው፡፡ ከ116 በላይ መጽሀፎችን ለህትመት ማብቃት ትልቅ ስራ ነው፡፡ ነገር ግን መምህሩ በዚህ ሁሉ ሲያልፍ ከስር ከስር ጠንካራ ባለሙያዎችን እያፈራ ነው፡፡ በሀገራችን በየዘመናቱ ጠንካራ መምህራን አሉ፡፡ ነገር ግን ስማቸው ጎልቶ ሲወጣ አንሰማም፡፡ መምህር ከአባት ከእናት ባልተናነሰ የወደፊት መንገድን የሚያመለክት ባለውለታ እና አደራ ተቀባይ ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ የስነጽሁፍ ዘርፍ በሚለው ዘውግ ውስጥ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ መልካም ስም ያላቸውን መምህራንን መዘከር ወይም ታሪካቸውን መሰነድ ያስፈለገው መምህርነት እንዲከበር እና ባለሙያዎቹም እውቅና እንዲያገኙ ስለፈለግን ነው፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር አለም ደግሞ እውቅና የሚገባቸው ስራቸው ደግሞ በሁሉም ሰው ዘንድ የሚታይ ነው፡፡ በመሆኑም የእኒህን ሰው ታሪክ ለመጪው ሀገር ተረካቢ ስናቀብል ብዙ ሊማርባቸው እንደሚችል በመተማመን ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *