ሣሙኤል ፍቅሬ ላቂ

ሣሙኤል ፍቅሬ ላቂ

ሣሙኤል-አይናችን 

በአይናችን ፕሮግራም የምናውቀው  ሣሙኤል ፍቅሬ  ደፋር ጋዜጠኛ ነው፡፡ በ1994  የመገናኛ ብዙሀን ሽልማትን ያገኘ ነው፡፡ በምርመራ ጋዜጠኝነት ሲሰራ ታላቅ ርካታ ይሰማዋል፡፡ እንደ ሣሙኤል ፍቅሬ አይነት ወይም ከሣሙኤል የበለጡ ምርጥ ያልተነገረላቸው ግን ሳይታዩ የሚሰሩ ሰዎችን የምታውቁ ከሆነ ጠቁሙን፡፡ ተወዳጅ ሚድያ በሚድያ ዘርፍ የሣሙኤል ፍቅሬን ታሪክ እንደሚከተለው ያቀርበዋል፡፡ ክፍል አንድ በሚከተለው መልኩ ተሰናድቷል፡፡ የአሳምነው ገብረወልድ- ሁሩታ

ሣሙኤል ፍቅሬ፣ ከአባቱ ከአቶ ፍቅሬ ላቂ ከእናቱ ከወ/ሮ አማከለች ደስታ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር በአርሲ ዞን በሎዴ ሄጦሳ ወረዳ በጉዴልቻ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በ1958 ዓ.ም ነበር የተወለደው፡፡ እሱንና ሁለት ወንድሞቹን የማሳደግ ኃላፊነት የተሸከሙት ታታሪና ብርቱ እናቱ ከተወለደባት የገጠር ቀበሌ ብዙም በማትርቀው ሁሩታ ከተማ ገብተው በጠጅ ንግድ ስራ ላይ ሲሰማሩ እድገቱም ሁሩታ ከተማ ሆነ፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስም የኔታ ብርሀኔ ጋር ፊደል ቆጥሮ፣ ዳዊት ደግሞ በህፃንነት እድሜው ድቁና ተቀብሎ በሁሩታ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ቀድሷል፡፡

በ1ብር ንግድ

ሣሙኤል የድቁና ህይወቱን አልገፋበትም፡፡ የመደበኛ ትምህርቱን የጀመረው በወቅቱ ንጉስ ሀይለ መለኮት ት/ቤት በመባል ይታወቅ በነበረው የመጀመሪያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ነበር፡፡ አብዛኛው አብሮ አደግ ጓደኞቹና የአካባቢው ተወላጆች ከትምህርቱ ጎን ለጎን ከህፃንነት እድሜያቸው ጀምሮ በንግድ ወይም በእርሻ ስራ በመሰማራት በሚያገኟት ገቢ ኑሯቸውን መደጎም፤ቤተሰባቸውን መርዳት መለያቸው ነው፡፡ ሣሙኤልም እናቱ ባህሪው እንዳይበላሽ  በመስጋት ጮርናቄ፤ ፓስቲና ብስኩት ወይም ሸንኮራ መግዣ ቢከለክሉት ራሱን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ያላቅቀኛል በማለት ያሰበውን ለማሳካት የእናቱን አባት (አያቱን) ‹‹አንድ ብር አበድረኝ›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ አያቱ ‹‹ለምን ፈለግክ ?›› ቢሉት ‹‹ራሴን ለመቻል እነግዳለሁ›› ቢላቸው አንተን ብሎ ነጋዴ ብለው ሀሳቡን አጣጥለው ስለሚወዱት ብቻ የጠየቀውን አንድ ብር ሠጡት፡፡

ቅዳሜ ገበያ ወጥቶ በአንድ ብር አንድ ኪሎ ዝንጅብል ገዝቶ አስራ አምስት ቦታ በመመደብ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ሸጠ፡፡ ደግሞ ሄዶ አንድ ኪሎ ገዛና አሁንም 15 ቦታ በመመደብ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ሸጠ፡፡ አሁን የሁለት ብር ጌታ ስለሆነ ሁለት ኪሎ ገዛ፡፡ ሦስት ብር ሸጠው፡፡ የእለቱን የገበያ ውሎ በዚሁ በማጠናቀቅ አያቱ ዘንድ በመሄድ እፊታቸው በኩራት ቆሞ ሦስት ብር ቆጥሮ እያሳያቸው ‹‹ሁለት ብር አትርፌ ውያለሁ አሁን እዳዬን መክፈል እቻላለሁ›› ይላቸዋል፡፡ ‹‹ምን ነገድክ ?›› ይሉታል ‹‹ዝንጅብል›› ብሎ ይመልስላቸዋል፡፡

የዕለቱንም ውሎ ይተርክላቸዋል፡፡ የሚወዱት አያቱ ‹‹ጎበዝ›› ብለው ‹‹እንግዲያው እንዲህ ጎበዝ ከሆንክማ›› በማለት አስር ብር ሸለሙት፡፡ ሣሙኤል አያቱ የሸለሙትን አስር ብር ጨምሮ አስራ ሦስት ብር መነሻ ካፒታል በመያዝ ከ13 ዓመት እድሜው ጀምሮ እንቁላል፤ ቡና፤ ጨው ወዘተ ያልነገደው ነገር የለም፡፡ በተለይም በእንቁላል ንግድ ድሬደዋና ጅቡቲን መዳረሻው ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ የንግድ ስራው ከትምህርቱ እንዳያዘናጋው ስጋት ያደረባቸው እናቱ ግን የንግድ ስራውን አልወደዱለትም፡፡ እሱ ግን ሁለቱንም ማስኬድ እችላለሁ እያለ የእናቱንም ምክር አልሰማ አለ፡፡

በዚህ መሀል ሣሙኤል ሳይወድ በግድ በትምህርቱ ላይ ብቻ እንዲያተኩር የሚያስገድድ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ጊዜው 1973 ዓ.ም ክረምት ወቅት ነው፡፡ ሣሙኤል የ9ኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ያኔ ሁሩታ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የለም፡፡ የአካባቢው ወጣቶች ስምንተኛ ክፍልን ካጠናቀቁ በኋላ አሰላና ናዝሬት ወይም አዲስ አበባና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች ሄደው ነበር የሚማሩት፡፡ ሣሙኤል አሰላ እየተማረ ቅዳሜ ቅዳሜ ሁሩታ እየተመለሰ ይነግዳል፡፡ በትምህርቱም ጎበዝ ከሚባሉት የደረጃ ተማሪዎች ተርታ የሚመደብ  ተማሪም ነበር፡፡ 

አርፈህ  ተማር

የክረምቱ ወቅት ት/ቤት ስለሚዘጋ ለሣሙኤል አይነቶቹ የአካባቢው ወጣቶች ከትምህርት ጋር ደርበው የሚሰሩት የንግድ ስራ ላይ ለማተኮርና ጥሩ ገንዘብም ለመያዝ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ሣሙኤልም ድሬደዋና ጅቡቲ ድረስ የዘረጋውን የእንቁላል ንግድ አጠንክሮ የሰራበት አጋጣሚ ነበር፡፡፡ እንቁላል ሸጦ የሚያገኘውን ገንዘብ የኮንትሮባንድ ዕቃ ገዝቶ በማምጣትና በሚያገኘው ተጨማሪ ገንዘብ ኪሱ ሞቅ ማለት ጀመረ፡፡ሁለቴ ሦስቴ ያገኘው የግራና ቀኝ ትርፍ ሦስት መቶ ብር ድረስ መቁጠር የቻለ ሀብታም አደረገው፡፡

በአራተኛው እንቁላሉን በርከት እድርጎ ይዞ ሄደና ባገኘው ጠቀም ያለ ገንዘብ የኮንትሮባንዱንም እቃ ጠርቀም አድርጎ ገዛና ተመለሰ፡፡ አዋሽ የጉሙሩክ ጣቢያ ላይ ሲደርስ ግን የለበሰውን ጨርቅ ሣይቀር አስወልቀው ወረሱት፡፡ እያለቀሰ ባዶ እጁን አገሩ ገባ፡፡ እናቱ ግን ‹‹እሰይ ስለቴ ሰመረ›› በማለት በእልልታ ነበር የተቀበሉት፡፡ ‹‹እመቤቴ ስለቴን ሰምታ ነው፤ የምትፈልገውን እኔ እናትህ ብርሌ አጥቤ አሟላልሀለሁ አርፈህ ትምህርትህን ተማር›› ብለው መከሩት አስመከሩት፡፡ ሣሙኤልም ሌላ አማራጭ ስላልነበረው በንግዱም በእጅጉን ተስፋ ስለቆረጠ ወትሮም ያልቦዘነበትን ትምህርቱን አጠንክሮ ቀጠለ፡፡ የአስረኛ ክፍል ትምህርቱን በጥሩ ውጤት በማጠናቀቁ አዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ት/ቤት ለፈተና የሚያቀርበውን ውጤት ማስመዝገብ በመቻሉ ፈተናውን አልፎ የሬዲዮ ኤሌክትሮኒክስ የትምህርት ክፍል ተመደበ፡፡

የ1976 ቱ ቴክኒሺያን

በአዲስ አበባ ተግባረዕድ ት/ቤት ለሁለት ዓመት የሚሰጠውን መደበኛ የሙያና የቀለም ትምህርት በማጠናቀቅ በ1976 ዓ.ም በሬዲዮ ኤሌክትሮኒክስ በሁለት ዓመት መርሀ ግብር በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ ከዚያም በኢትዮጵያ ቴሌቪዝን በቴክኒሺያንነት ሙያ በመቀጠር በቅድሚያ ጎንደር ለአንድ ዓመት በኋላም ናዝሬት ሦስት ዓመት የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያ ቴክኒሻን በመሆን በድምሩ ለአራት አመታት አገልግሏል፡፡ በወቅቱ የቴሌቪዥን የስርጭት ሠዓት ከምሽቱ አንድ ሠዓት በኋላ ነበር የሚጀምረው፡፡ የሚቆየውም ቢበዛ እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ነው፡፡ ከዚያ ወደ ቤት፡፡ ለዚሁም ስራው አንድ ቀን ስራ፤ ሌላ አንድ ቀን እረፍት በመሆኑ ለሣሙኤል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቴክኒሺያንነት ቆይታው  እጅግ በጣም ሠፊ የተትረፈረፈ የእረፍት ጊዜ የበዛበት ነበር፡፡ ጎንደር እያለ በቴክኒሺያንነት ሙያው አዳዲስ ቴሌቪዥን ማስተካከልና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን መጠገንን የመሰሉ የግል ስራዎችን በመስራት ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበት እድል የተፈጠረለት ቢሆንም ካለው ሠፊ ትርፍ ሠዓት አንፃር አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፈው ከረምቡላ ቤት ነበር፡፡ እዚያው የለመደውን የከረንቡላ ጨዋታ የሚችለው ጠፋ፡፡

‹‹ንጉሱን›› ከረንቡላ ቤት

እነ ሣሙኤል የተመደቡበት የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያ ጎንደር ላይ ከመተከሉ በፊት ጎንደርና አካባቢው የቴሌቪዥን ስርጭት አልነበረም፡፡ እነ ሣሙኤል የቴሌቪዥንን በረከት ለጎንደር ያመጡ ተደርገው ስለሚታሰቡ በአካባቢው ህዝብ ዘንድ የተለየ ከበሬታ ይቸራቸው ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ ሣሙኤል በእድሜም ሆነ በማህበራዊ ቦታቸውና በስልጣን ጭምር ከሚበልጡት ትላልቅ ሰዎች ጋር የሚገናኝበትን እድል መፍጠሩ አልቀረም፡፡ አንድ ቀን በወቅቱ ትላልቅ የመንግስት ባለስልጣናትና ታዋቂ ሠዎች የሚዝናኑበት ጎንደር ተራራ ሆቴል ከረንቦላ እየተጫወተ ተጋጣሚውን በከፍተኛ ልዩነት እየመራው ባለበት ሁኔታ አንድ አጠር ያለ መልከመልካም ደልደል ያለ ወጣት መሳይ የተጋጣሚውን ድንጋይ ይቀበላል፡፡ እንዲህ ያለ አጋጣሚ በከረንቡላ ጨዋታ መሀል የተለመደ ነው፡፡

በተለይም በነጥብ የተመራ ተጋጣሚ የሌሎችን ድጋፍ በመጠየቅ ድንጋይ ሲሰጥ እጅ መግዛት ይባላል፡፡ ጎበዙ ተጋጣሚ ግን በርትቶ ድጋፍ ሠጪውንም ካሸነፈ ድርብ ድል ነው፡፡ በዚህ ላይ ቀልድና መወራረፍ የጨዋታው አንድ አካል እስኪመስል የተለመደ ነው፡፡ ሣሙኤልም በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኖ ድጋፍ ለመስጠት የተተካውን ተጋጣሚ በነገርም በጨዋታም ያዋክበው ያዘ፡፡ ‹‹አንትን ብሎ እጅ ተገዢ አቀምስሀለሁ›› እያለ በመፎከር የተጀመረውን ጨዋታ በሰፊ የነጥብ ልዩነት አሸነፈ፡፡ በአሻናፊነቱም እየተኩራራ ‹‹ትቀጥላለህ ?›› አለው፡፡ ተጋጣሚው ባልጠበቀው መልኩ የሚያዝናናው በማግኘቱ ተደስቶ ‹‹እንዴታ›› አለ፡፡

‹‹የመወራረጃው ገንዘብ ይጨመራ›› አለ ሣሙኤል በኩራት፡፡ ‹‹ሦስት እጥፍ ይጨመር›› ይላል ተጋጣሚው፤ ሽንፈቱን ላለመቀበል በተነሳሳ ስሜት ውስጥ መግባቱን በሚያሳይ ስሜት ውስጥ ሆኖ፡፡ ሣሙኤልም በከፍተኛ ልዩነት ያሸነፈው የተጋጣሚው ድፍረት ግርምት ቢፈጥርበትም ‹‹ያዝ እንግዲህ ምን ቸገረኝ›› ይልና የተረብ መናቆሩም የከረንቡላ ጨዋታው ተሟሙቆ ቀጠለ፡፡ ሣሙኤል በከፍተኛ ነጥብ መምራት ጀመረ፡፡ በከረንቡላው ጠረጴዛ ዙሪያ የተሰበሰቡትን ተመልካቾች ግን ከጨዋታው በላይ ያስደመማቸው ሣሙኤል ተጋጣሚው ላይ ያወረደበት የተረብ ዓይነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አሸናፊነቱን ባረጋገጠ ስሜት ተጋጣሚው ላይ እየፎከረ ባለበት ሁኔታ ድንገት በሰማው ድምፅ ምድር ሰማዩ እስኪዞርበት ደነገጠ፡፡ ፍርሀት አራደው ተንቀጠቀጠ ከማን ጋር እየተጫወተ እንደሆነ ሲገባው ላብ አሠመጠው፡፡ ለካስ ከፍ ዝቅ እያደረገ ሲፎክርበት የነበረው ሰው ያካባቢው ህዝብ አጠገቡ ለመቆም የማይደፍረው፤

‹‹….. የእግዜር ታናሽ ወንድም፤የዛሬን ማርልኝ ሁለተኛ አልወልድም›› የተባለለት አስፈሪ ‹‹ንጉስ›› ነበር፡፡ ሣሙኤል ይህን ሰው በአካል አግኝቶት አያውቅም፡፡ በጨዋታው መሀል ‹‹ጓድ መላኩ›› የሚለውን ድምፅ ከሰማ በኋላ በቴሌቪዥን የሚያውቀውን ምስል እያሰላሰለ ቀና ብሎ አየውና አረጋገጠ፡፡ መላኩ ተፈራ ነው፡፡ ከዚያን በፊት እንዳላወቀውና በነፃነት ሲያጫውተው ተደስቶ የነበረው ጓድ መላኩ በቤተሰባዊ አቀራረብ ‹‹አይዞህ ተጫወት›› ብሎ ሊያረጋጋው ሞከረ፡፡ ሣሙኤል ሊረጋጋ አልቻለም፡፡ አለቀልኝ አለ በሆዱ፡፡

መላኩ ድንገት ስሙን የጠራውን ሰው እየተራገመ ሣሙኤልን ለማረጋጋት ብዙ ጣረ አልሆነለትም፡፡ ጨዋታው ተቋረጠ፡፡ ‹‹በቃ ውሰዱት›› ብሎ ለአጃቢዎቹ ትእዛዝ ሲሰጥ ድንገት ሣያስበው ሱሪው ላይ በፊት በኩል አለቀሰ፡፡ የመላኩ አጃቢዎች ግን በእንክብካቤ እቤቱ ነበር ያደረሱት፡፡ ሣሙኤል አሁንም  እውነት አልመሰለውም፡፡ የአንድ ሠሞን የከተማው መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ ጎንደር ተረጋግቶ መኖር አልቻለም፡፡ ደግነቱ ናዝሬት የሚቀየርበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡

ጉዞ ወደ ዩኒቨርሲቲ

ሳሙኤል ከዓመታት በፊት አዋሽ ላይ በተፈጠረው አጋጣሚ ተስፋ ቆርጦ የተወውን ንግድ  አሁን ጀመረ፡፡ በተጓዳኝም ቴሌቪዥን፤ቴፕና የመሳሰሉት የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን በመጠገን ስራ ተጠመደ፤ የትውልድ ሀገሩ ሁሩታ ለናዝሬት ቅርብ በመሆኑ የመኸር ወቅት ሁሩታ ላይ መሬት በመኮናትር ሽንኩርትና ድንች ያመርታል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በወር የሚከፍለው ደሞዝ 305  ብር ብቻ ነበር፡፡ እሱም 285 ብር ቅጥር ከሁለት ዓመት አገልግሎት በኋላ በጭማሪ የደረሰበት ነው፡፡ ሣሙኤል ግን ሰፊውን የእረፍት ሠዓቱን በአግባቡ እየተጠቀመ በሣምንት 500 ብር እቁብ እየጣለ ቤት መስራት ቢችልም ደስተኛ አልነበረም፡፡

ምክንያቱ ደግሞ የእድሜ እኩያው፤ የልጅነት የክፍል ጓደኛው ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የፊሎሶፊ ትምህርት ከፍል ሰቃይ ተማሪ በመሆኑ በተለይም ሁሩታ አካባቢ ስሙ ገኖ ይጠራል፡፡ ይብስ ብሎ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ አንድ ዘመድ ቤት ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን የጨረሰ ልጅ ምርቃት ላይ ይጠራል፡፡ በምርቃቱ ላይ የተገኘ ዘመድ አዝማድ ተመራቂውን ሲያሽሞነሙኑት የታዘበው ሣሙኤል ወትሮም በቁጭት ይናፍቀው የነበረው የህይወት ጥሪ ህይወቱን ረበሸው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ መማርና ተመርቆ ካባ መልበስ፡፡ በዙሪያው የተሰበሰበ ዘመድ አዝማድ ከአጠገቡ ቆሞ ፎቶ ለመነሳት ሲራኮት ማየት፡፡ ይህን ህልሙን ለማሳካት ግን ሌላ ፈተና ገጠመው፡፡ መ/ቤቱ አለቅህም አለው፡፡ በዚህ ምክንያት ምንም እንኳን ዩኒቨርሲቲ የመግባት እድሉን ቢያገኝም ሥራውን መልቀቅ ግን ቀላል አልሆነም፡፡ ያገኘውን ዕድል ማበላሸት ደግሞ አልፈለገም፡፡ እናም ከናዝሬት አዲስ አበባ እየተመላለሰ ቀን ቀን ትምህርቱን እየተማረ ማታ ስራ እያመሸ አንድ ሴሚስተር ተማረ፡፡ ከአንድ ሴሚስተር በኋላ በዘመድ እርዳታ ሥራውን ለቆ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡

ቀንድለው ቀንድለው ጣሉን፡፡

ግንቦት 8 – 1981 ዓ.ም ሣሙኤል ትንሽ ልጅ አልነበረም፡፡ በታላቁ የአ.አ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ውስጥ  የመጀመሪያ ዓመት (fresh) ተማሪ ነበር፡፡ ቀደም ሲል በስራ ላይ ባሳለፈው አራት ዓመታት ምክንያት ከአብዛኛዎቹ የዚያን ዓመት ጓደኞቹ (same baches) ታላቅ ቢሆንም በወቅቱ ለዐቅመ- አዳም እንጂ ለዐቅመ- ፖለቲካ አልደረሰም ነበር፡፡ ሣሙኤል ያን ወቅት በማስታወስ ግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረው ማስታወሻ እንዲህ ብሏል– ‹‹እውነት ለመናገር እንኳንስ አንደኛ ዓመት እያለሁ አራተኛ ዓመትም ደርሼ የፖለቲካ ግንዛቤዬ ስሜት የሚነዳው እንጂ እውቀት የሚገራው አልነበረም፡፡ እንዲያም ሆኖ በዕለቱ በኮሎኔል መንግስቱ ሀ/ማርያም ላይ የተደረገው መፈንቅለ- መንግስት በመክሸፉ የተቆጩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በግቢያቸው ያደረጉትን የተቃውሞ ሰልፍ

አመሀ ……. ለምን ለምን ሞተ

መርዕድ ……. ለምን ለምን ሞተ

በሀይል በትግል ነው ነፃነት የሚገኘው እያሉ ከጮሁትና ካስጮሁት መካከል ሳሙኤል አንዱ ነበር፡፡

 ‹‹……….ድፍረት ካልሆነብኝ የመፈንቅለ-መንግስቱ መሪዎች ለምን እንደሞቱ የሰልፉ አጫፋሪ ከነበርነው መካከል የሚያውቅ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ እንዲያም ሆኖ ሰልፉን እንዲበትኑ መንግስት የላካቸው የቤተ- መንግስት ቅልብ ወታደሮች ከግቢ ውጪ ቆመው እኔንና እኔን መሰሎችን በዓይናቸው ሲመነጥሩን ቆዩና በራሳቸው ሠዓት በሀይል ግቢ ገብተው ቀንደኛ ናቸው ያሉንን በያዙት እህል ውሀ በሚያሰኝ ቆመጥ አናት አናታችንን ቀንድለው ቀንድለው ጣሉን፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ከሞት ከተረፉት መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡ በተለይም መሀል አናቴ ላይ ያረፈው የአንድ ጨካኝ ፖሊስ ቆመጥ ዛሬም ድረስ ለምልክት የኖረ ጠባሳ ያተረፈልኝ ቁስልን ቆስዬ ደሜ ባይንደቀደቅና ወደውጭ ባይፈስ ወይም ወደ ውስጥ ፈሶ ቢሆን ኖሮ የእኔ ማንነት እዚያ ላይ ባቆመ ነበር፡፡›› ሲል ሳሙኤል ትዝታውን ተርኮ ነበር፡፡

ጠዋት ስለ ሠላም ሳይረፋፍድ ለጦርነት

ሣሙኤል እንዲህ ለአደጋ አያጋልጡት እንጂ በአራት ዓመት የዩኒቨርሲቱ ቆይታው ደርግምም ሆነ ወያኔና ሻእቢያን በመቃወም በተደረጉ ሰልፎች ሁሉ የፖለቲካ ብስለትና እውቀት ሳይሆን የወጣትነት ስሜትና ግለት እየነዳው ከፊት ያልተሰለፈበት ሰልፍ አልነበረም፡፡  1983 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ኢህአዴግ ጎንደርና ጎጃምን ጨምሮ አብዛኛውን የሰሜኑን የሀገራችንን ክፍል ተቆጣጥሯል፡፡ አብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ተረጋግቶ መማር አልቻለም፡፡ በዚህ ላይ ኢህአዴግ በንፁሀን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ የሚፈፅም አረመኔ ወንበዴ ነው በማለት በወለጋ ሆስፒታል የተፈፀመ አሰቃቂ ድርጊትን ደርግ በቴሌቪዥን አስተላልፏል፡፡

ይህ ፊልም በቀረበበት ምሽት ተማሪው በፉጨት ተጠራርቶ ፕሬዚዳንቱ ቢሮ ፊት ለፊት ባለ ሜዳ ላይ ተሰባሰበ፡፡ በዚያ ምሽት በቀረበው ፊልም የተናደዱ በርካታ ተማሪዎች ምን እስኪሆን እንጠብቃለን? ታጥቀን እንዝመት አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሰላማዊ መፍትሄ ይሞከር፤ ሁሉንም የፖለቲካ ሀይሎች ያሳተፈ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም እንጠይቅ ይህን አማራጭ ደርግ ተቀብሎ ኢህአዴግ እና ሻዐቢያ አንቀበልም ካሉ እንዘምታለን የሚል ሀሳብ ቀረበ፡፡ ይህን የሠላም አማራጭ ሀያላን መንግስታት እንዲያግዙን ሠላማዊ ሰልፍ በማድረግ ኤምባሲዎቻቸው ድረስ ሄደን በደብዳቤ እንጠይቅ ተባለ፡፡ እነ ሣሙኤል የሚያስተባብሩት ከ17 ያላነሱ ወጣቶች የተሰባሰቡበት ኮሚቴ ሌሊቱን ደብዳቤ አዘጋጁ፡ ሦስት ኤምባሲዎች መረጡ ፡፡ አሜሪካ፤ እንግሊዝና ራሺያ፡፡ 

We need peace! Supper powers help us! (ሠላምን እንሻለን ሐያላኖች እርዱን) የሚል ዋና መፈክርም እንዲሆን ተመረጠ፡፡ በጠዋት ተነስተው በነ ሣሙኤል መሪነት ይህን መፈክር እያሰሙ መጀመሪያ አሜሪካ ቀጥለው እንግሊዝ በመጨረሻም ራሺያ ኤምባሲ በየኤምባሲዎቹ ደጃፍ ሄደው የተዘጋጀውን ደብዳቤ አንብበው ከጨረሱ በኋላ ድንገት የሰልፉ መልክ ተለወጠ፤ መፈክሩም ‹‹አስታጥቁን እንዘምታለን ! ›› በሚል ተቀየረ፡፡ የሰልፉ አስተባባሪ ያልነበሩ ጥቂት ወጣቶች ጉዞውን ወደ ቤተ-መንግስት አመሩት፡፡ የመጀመሪያውን መፈክር በማሰማት ሰልፉን እየመሩ ለነበሩት ወጣቶች ቀጭን ትእዛዝ ተሰጠ፡፡ ሰልፉን ወደ መንግስት ምክር ቤት እንዲመሩ፤ አስታጥቁን እንዘምታለን የሚለውን መፈክርም እንዲያሰሙ፡፡ እውነት ለመናገር ትእዛዙ ባይኖርም በስሜት እየተነዱ ሰልፉን ለሚመሩት ለእነሣሙኤል ይህን መፈክር ላለማሰማት የሚያበቃ ማመዛዘን አልነበረም፡፡ ያ ባይሆን የፈለገው ጫና ቢኖርም we need peace ያሉባት ጀንበር ሳታዘቀዝቅ ‹‹አስታጥቁን እንዘምታለን›› የሚሉበት አንዳችም አመክንዮ አልነበረም፡፡

    

ከዚያ በተረፈ ሣሙኤል በበጎ የሚያስታውሰው ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በእርሱ ዘመን እሱና ጓደኞቹ አቋቁመውት በነበረው ‹‹Arts for art sec>> የተሰኘውን የኪነጥበብ ክበብ ከዛሬው የሙያ አጋሩ ከሆነው የሸገሩ ጋዜጠኛ ዘካርያ መሀመድ ጋር በመሆን በመምራትና በመግራት ያበረከቱት አስተዋፅኦ ይጠቀሳል፡፡   ሳሙኤል ከተመረቀ በኋላ ወደየት አመራ? በዚህ ፌስ ቡክ ገጽ በክፍል 2 እንመለስበታለን፡፡

በ1984 መመረቅና ክልል 14 ማስታወቂያ ቢሮ

የአራት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነፅሁፍ በማጠናቀቅ  በ1984 ከተመረቀ በኋላ በጋዜጠኝነት ሙያ ስራ የጀመረው በወቅቱ ‹‹የክልል 14 ማስታወቂያ ቢሮ›› ይባል በነበረው የዛሬው የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ ነው፡፡ ሣሙኤል የጋዜጠኝነትን ህይወት አስቦበት የተቀላቀለው ባይሆንም በፍቅር የወደቀለት ሙያ ነው፡፡ የካቲት ወር 1985 ዓ.ም አጋማሽ ከዕለታት በአንዱ ቀን ለዜና የተሰማራበትን ስራ አጠናቅሮ ካለበት ቦታ ሁኖ ዜናውን በስልክ አስተላለፈ፡፡

ስድስት ሠዓት ላይ በጉጉት ቢጠብቅ ዜናው የለም፡፡ ደውሎ ቢጠይቅ በማታው የዜና እወጃ ሰዓት ይቀርባል ተባለ፡፡ ግን እንዴት ይምሽ የራሱን ድምፅ በሬዲዮ ለመስማትና ለማሰማት የነበረው ጉጉት ቀኑን ያራዘመበት መሠለው፡፡ በዚህ ላይ ቀን ዜናውን ጠብቁ ብሎ ድምፁን በሬዲዮ እንዲሰሙ የጋበዛቸው ሁሉ እየደወሉ ‹‹የታለ ዜናው?›› ይሉታል፡፡ ማታ ጠብቁ ብሏል- ቀኑ ግን አልመሽ አለ፡፡ የማይደርስ የለምና መሸ ፡፡ የእለቱ የዜና መሪ (anchorman) ነጋሽ መሀድ በሚስረቀረቅ ድምፁ ዜናውን ያጋፍራል፡፡

የዜና ፋይል ባልደረቦችም ለዝርዝሩ …. እየተባሉ ዜናውን ያዝጎደጉዱታል፡፡ ሣሙኤል ፍቅሬ የለም፡፡ የዜና እወጃው ከመጠናቀቁ በፊት ድንገት ለዝርዝሩ የሚለው የነጋሽ ድምፅ አንድ ከዚያ በፊት በዜና ፋይል የዜና ሠዓት ላይ ያልተጠራን ስም ጠራ፡፡ ዜናው ተነበበ፡፡ በመጨረሻም ‹‹ለክልል 14 ማስታወቂያ ቢሮ ዘገባ ሣሙኤል ፍቅሬ ነኝ ከተግባረ ዕድ አዳራሽ››፡፡ ከዚያ በኋላ ማን ይቻለው፡፡ በማስታወቂያ ቢሮው ስም በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ዘገባዎች አብዛኛዎቹ የሣሙኤል ናቸው ማለት ይቻላል፡፡በወቅቱ በቢሮው ስር ከሚታተሙት አዲስ ልሳን ጋዜጣና አዲስ መጽሄት ላይ ከሚቀርቡ የተለያዩ ዘገባዎች አናት ላይ ‹‹ከሣሙኤል ፍቅሬ›› የሚሉ መጠሪያዎች በስፋት መታየት ጀመሩ፡፡

የምርመራ ዘገባ ጅማሮ-አንድ

 በአንድ ወቅት አንዲት አራት ኪሎ አካባቢ የሆቴል ባለቤት የሆኑ ወ/ሮ ከንግድ አጋራቸው ጋር የገቡትን ውል ማፍረስ ይፈልጉና ውሉን በፈፀምኩበት ጊዜ የአእምሮ በሽተኛ ነኝ በማለት ከአማኑኤል ሆስፒታል ተገኘ የተባለ የህክምና ማስረጃን በማያያዝ የውል ይፍረስልኝ ክስ ይመሰርታሉ፡፡ ሣሙኤል መረጃ ደረሰው – ማስረጃው ሀሰተኛ (forged) ነው የሚል፡፡ ሣሙኤል የምርመራ ዘገባን የጀመረበትን ዜና ማጠናከር ጀመረ፡፡ በርግጥም ማስረጃው ሀሰተኛ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ሠነዶች ለተለያየ ጉዳይ በብዛት እንደሚዘጋጁ አረጋገጠ፡፡

ፍ/ቤት የተያዘውን ጉዳይ ወደ ጎን በመተውና በተመሳሳይ ሠነዶች ላይ በመመርኮዝ ‹‹አማኑኤል ሆስፒታል ደጁን ረግጠው ለማያውቅ ሠዎች፤በሽታም ለማያውቃቸው ጤነኞች አብደው ነበር የሚል ማስረጃ ይሰጣል የሚል ዘገባ በማጠናቀር፤  የሆስፒታሉን ማህተም፤ የሀላፊውን ቲተር አስቀርፀው በአማኑኤል ሆስፒታል ስም የሚነግዱትን ያጋለጠበትን ዜና ሠራና ኢትዮጵያ ሬዲዮ ይዞት ሄደ፡፡ የእለቱ ዜና መሪ (anchorman) አለምነህ ዋሴ ነበር፡፡ አለምነህ በዜናው ተማርኮ፤ ሣሙኤልንም አድንቆ ከዜናው ያላነሰ መሪ ዜና (lead) ሰርቶ አቀራረቡን አሳምሮና አድምቆ በመምራት ‹‹…. ዝርዝሩን ያጠናቀረው የክልል 14 ማስጣወቂያ ቢሮ ሪፖርተር ሣሙኤል ፍቅሬ ያነበዋል›› አለ፡፡ ሳሙኤል አነበበው፡፡ አገር ጉድ አለ፡፡

ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ እና ጥቁር ከረባት

በወቅቱ በክልል 14 አማካኝነት ከቀረቡትና ታሪካዊውን የአዲስ አበባ ጎርፍንና የአንዋር መስኪድን ግጭት ጨምሮ ታላላቅ የከተማዋ ኩነቶች በሣሙኤል የተዘገቡ ነበሩ፡፡ 1987 ዓ.ም በሀገራችን ለየት ያለ ፖለቲካዊ ታሪክ የተመዘገበበት ነበር፡፡ የኢፌዲሪ ህገ- መንግስት የፀደቀበት፡፡ ህገ መንግስቱ ከመፅደቁ በፊት የህገ መንግስት አፅዳቂ ጉባኤ አባላት ኮተቤ ላይ ለዚሁ ተብሎ በተሰራ ለየት ያለ ተንቀሳቃሽ አዳራሽ (አሁን ላይ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ይገኛል) ተሰብስበው ለቀናት መክረዋል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ተወካዮች በጣት ከሚቆጠሩት ጥቂቶች በስተቀር አብዛኛዎቹ የኢህአዴግ አባላት ነበሩ፡፡ የጉባኤው አባላት በሚያደርጉት ውይይት በአንዳንድ ምሁራንና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሚደመጡ የተቃውሞ ድምፆች ቢኖሩም በድምፅ ብልጫ ይወድቃሉ፡፡

ሣሙኤልን የመሰሉ ዘገባቸው ሚዛናዊ ቢሆን ለሚመርጡ ጋዜጠኞች ከኢህአዴግ አባላት በተለየ መስመር የቆሙ የጉባኤ አባላት ድምፅ ውበት ነበሩ፡፡ ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ ከክልል 14 ምክር ቤት ጀምሮ ዘወትር የሣሙኤልን የትኩረት አቅጣጫ ከሚስቡ የተለየ ድምፅ ከሚያሰሙ የዘመኑ የፖለቲካ ፈርጥ አንዱና ዋነኛው ነበሩ፡፡ አንቀፅ 39 በፀደቀ ማግስት ጥቁር ከረባት አስረው በስብሰባው አዳራሽ ተገኙ፡፡ በእለቱ ባሰሙት ንግግር ከዛሬ ጀምሮ ይህን ክረባት አላወልቅም አሉ፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በወቅቱ የክልል 14 ም/ፕሬዘዳንት ከነበሩት ባለስልጣን ጋር (ይህ ሹምባሽ በኋላ ላይ ፀረ ልማት ነኝ በማለት ከሀላፊነቱ እስኪነሳ ድረስ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባም ነበር) ጋር ሙግት ያደረጉበትን ቃለ -ምልልስ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ አቀረበ፡፡ የሪፖርተር ጋዜጣ መስራችና ዋና አዘጋጅ አማረ አረጋዊ ያኔ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ነበር፡፡ አቶ አማረ በወቅቱ ለጋዜጠኞች ስምሪት ሲሰጥ የሣሙኤልን ዘገባዎች ማጣቀሻ ያደርግ ነበር፡፡

ደሞዝ ያለስራ

ተደጋግመው በቀረቡት ዘገባዎቹ ሣሙኤል እየታወቀ ሲመጣ ግን የወቅቱ የክልል 14 ሹማምንት እውቅናውን አልወደዱለትም፡፡ በተለይም የትምህርት ደረጃቸውን ሲጠየቁ ‹‹16 ዓመት በካናዳ  የሚሉትን ጨምሮ ያለምንም የትምህርት ዝግጅት  የክልሉ ስራ አስፈፃሚ የመሆን ዕድል የተቸራቸው  ባለስልጣናት የሚሰማቸውን የበታችነት ስሜት የሚያበርዱት በተለያየ ቢሮ የሚሰሩትን ሣሙኤልን የመሰሉትን ታታሪና ጎበዝ ሠራተኞችን በማሸማቀቅ ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ለሣሙኤልም የተለየ ታፔላ በመለጠፍ በመ/ቤቱ ቆይታው ምስጉንና ታታሪ ተብሎ ለመሸለም የበቃውን ጋዜጠኛ በወቅቱ ከነበረበት የዜና ክፍል ሀላፊነት እንዲነሳ በማድረግ ያለስራ ደመወዝ እየተከፈለው እንዲቀመጥ አደረጉት፡፡

የህግ ትምህርት

 ሣሙኤል ግን አጋጣሚውን በመጠቀም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህግ ፋኩልቲ ተከታታይ የትምህርት ክፍል ህግ መማር ጀመረ፡፡ በህግ ፋኩልቲ በነበረው ቆይታ ከአንዴም ሁለት ሦስቴ የሎ ስኩል የክብር መዝገብ ‹‹Honer list›› ውስጥ ስሙን ማስመዝገብ የቻለበትን ውጤት ጭምር በማስመዝገብ ነበር ትምህርቱን ያጠናቀቀው፡፡

በጥሩ ደሞዝ -ሌላ ስራ – ጨርቃቸውን ጣሉ፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ለህዝብ ግንኙነት የስራ መደብ የሥራ ሀላፊ ለመቅጠር ሲፈልግ ሣሙኤል ተወዳድሮ በማሸነፉ ክልል 14 ማስታወቂያ ቢሮ ይከፈለው ከነበረው ደመወዝ በተሻለ ከፍያ ይቀጠራል፡፡ ያኔ ክልል 14 ያሉት  ባለስልጣናት በንዴት ጨርቃቸውን ጣሉ፡፡ ለቢሮው በጣም የሚያስፈልግ ታታሪ ሠራተኛ በመሆኑ ወደቀድሞ ስራው ይመለስ ብለው ወሰኑ፡፡ ውሳኔውን የመቃወም ህጋዊ መብት እንዳለው ቢያምንም ወደሚወደው የጋዜጠኝነት ሙያው መመለሱን እንደ ድል በመቁጠር አራት ወር ብቻ ያገለገለበትን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሚለውን የሀላፊነት ወንበርና በውድድር ያገኘውን የተሻለ ደመወዝና ጥቅማጥቅም  ትቶ ወደ ቀድሞ ስራው ተመለሰ፡፡

የባለስልጣናትን ገበና ማጋለጥ

ለስራው አስበው ሣይሆን እሱን ለማሸት እንዲመቻቸው ወደ ማስታወቂያ ቢሮ የመለሱት  ሠላም አልሰጡትም፡፡ እሱም አልተኛላቸውም፡፡ በተለይም በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በብእር ስም በሚያቀርበው ተከታታይ ዘገባ አብዛኛዎቹ የክልል 14 ስራ አስፈፃሚ አባላት ለፖለቲካው ታማኝና አሸርጋጅ ነበሩ እንጂ ለተቀመጡበት የስራ ሀላፊነት የሚመጥን የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ የሌላቸው እንደነበሩ ያጋልጥ ነበር፡፡

በተለይም አራተኛ ክፍልን ያላጠናቀቀ፤ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ በፊት የከተማው ፍ/ቤቶችን፤ የዐቃቤ ህግ መስሪያ ቤትን፤ ፖሊስ ኮሚሽንንና ባህልና ማስታወቂያ ቢሮን የመሳሰሉ ትላልቅ መ/ቤቶችን በሚመራው የአስተዳደር ዘርፍ ውስጥ ሥራ አስፈፃሚ አባል ሆኖ መቀመጡን፤ የከተማው የፋይናንስ ተቋማትን በሚመራው ትልቅ የአመራር ሚና በነበረው የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥም ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ በፊት በአንድ የመንግስት መ/ቤት በጥበቃ ሥራ ላይ የነበረ ሥራ አስፈፃሚ አባል ሆኖ መቀመጡን፤ምንም ዓይነት የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ሳይኖረው በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ተቀምጦ የትምህርት ማስረጃን በሚጠይቅ ፎርም ላይ 16 ዓመት በካናዳ እያለ ፎርም በመሙላት የሚታወቀውንና ‹‹ለበላዮቹ ድመት ለበታቾቹ አንበሳ›› የሚል የዳቦ ስም የተሰጠው የወቅቱን የክልል 14 አምባገነን ም/ፕሬዘዳንትን  እንዲሁም በስልጣን ዘመኑ ማብቂያ ላይ ፀረ- ልማት ነበርኩ ብሎ የተናዘዘውን የክልል 14 ደካማ ፕሬዚዳንት፤ እና መሰል ባለስልጣናትን ገበና የሚያጋልጥ ዘገባዎችን ያቀርብ ነበር፡፡

በዚህ መልኩ የሚገለፁ በርካታ ዘገባዎችን ሲያቀርብ በርካቶች በተለይም የፅሁፍ አጣጣሉን የሚያውቁት ወዳጆቹ ዘጋቢው እሱ ሊሆን እንደሚችል ቢጠረጥሩም እርግጠኛ አልነበሩም፡፡ ምናልባትም እስከዛሬ ድረስ ማንነቱን በትክክል የሚያውቁት የወቅቱ የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እሸቴ አሰፋና የጋዜጣው ባለቤት አማረ አረጋዊ ብቻ ነበሩ፡፡

ሣሙኤልን አትቅጠሩት!

በዚህ መሀል የኢትዮጵያ ሬዲዮ የጋዜጠኝነት የስራ ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ ለአዘጋጅነት ተወዳደረ፡፡ በከፍተኛ ውጤት አንደኛ በመውጣት አለፈ፡፡ ይህም ክልል 14 ማስታወቂያ ቢሮ ሠፈር በሰፊው ተወራ፡፡ ባለስልጣናቱ ዘንድ ሁለት የተደበላለቀ ስሜት ተፈጠረ፡፡ ከፊሎቹ ይሂድልንና እንገላገል አሉ፡፡ ከፊሎቹ እዛም ሄዶ ስለማይተኛልን እናሰናክለው ብለው አሴሩ የኋለኞቹ ሀሳብ አሸነፈ፡፡ ያኔ ታዲያ ለወቅቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ስራ አስኪያጅ ለአቶ ፈቃደ የምሩና ለዜና ክፍል ሀላፊው ለነጋሽ መሀመድ ስልክ ተደወለ፡፡

ሣሙኤል ፍቅሬን አትቅጠሩት ለማለት፡፡ አቶ ፈቃደ የምሩ ቅንና ለሰራተኞቹ መብት ጥብቅና በመቆም የሚታወቅ የስራ ሀላፊ ነበር፡፡ የክልል 14 ሰዎች በቀላሉ በስልክ የሚያስፈራሩት ዓይነት ሰው አልነበረምና ‹‹አንድን ሠራተኛ ለመቅጠርም ሆነ ላለመቅጠር የእናንተ ትእዛዝ አይደለም መስፈርቱ፡፡ ፈተና አውጥተናል- በፈተናው አንደኛ ወጥቷል፤በስራውም የሚታወቅ ጎበዝ ጋዜጠኛ ስለሆነ እኛም እንፈልገዋለን›› በማለት ዝም አሰኛቸው፡፡ በዜናና ወቅታዊ ፕሮግራም አዘጋጅነት ስራውን ቀጠለ፡፡

አለቆቹን መጋፈጥ

ኢትዮጵያ ሬዲዮን ከተቀላቀለ በኋላ አዲስ አበባ መስተዳድር ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተመለከተ የሰላ ትችት የሚቀርብበትን የምርመራ ዘገባ ባህርይ የሚታይባቸውን ፕሮግራሞችን የማቅረብ እድል አግኝቷል፡፡ ሆኖም ጊዜው የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት ስለነበር ጦርነቱ ላይ የሚያተኩር ዝግጅት ክፍል ተመደበ፡፡

በተለይም በወቅቱ በነበረው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ይዘጋጅ የነበረው የአፀፋ ፕሮፓጋንዳ (counter propaganeda) ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይዘጋጅ የነበረውን የወቅታዊ ዝግጅት ፕሮግራም በማዘጋጀት በጠላት ወረዳ ሳይቀር ‹‹ምላሱ ይቆረጥ›› እየተባለ የሚታወስ ታዋቂ ጋዜጠኛ ለመሆን በቃ፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማብቂያ ላይ ግንባር ድረስ በመሄድ በተለይም በሰሜኑ ግንባር በእያንዳንዷ የጦር ሜዳ ውሎ የተገኘውን ድል በተመለከተ ‹‹የአሸናፊነታችን ምስጢር›› የተሰኘ ተከታታይ ዘገባዎችን የመዘገብ እድል አግኝቷል፡፡

ሣሙኤል ለጦር ሜዳ ዘገባ የተመረጠው ለስራው ታስቦ አልነበረም፡፡ በሄደበት ሁሉ ለአለቆቹ የማይመች ዓይነትና አለቆቹን ለምን ብሎ የሚጋፈጥ ሠራተኛ ስለነበረ በወቅቱ ከቅርብ አለቃው ጋር ተጣልቷል፡፡ ይህቺ የቅርብ አለቃው ሣሙኤል ከመደበኛ ስራው በተጨማሪ ገጠር መሬት እየተኮናተረ እንደሚያርስና እንደሚያሳርስ እዚህም አንዳንድ የንግድ ስራዎችን እንደሚሰራና ተጨማሪ ገቢ እንደሚያገኝ፤ በኢኮኖሚ አቅሙም የተሻለ እንደሆነ ታውቃለች፡፡ በወቅቱ ጦር ሜዳ ከሚላኩ ጋዜጠኞች መካከል አንሄድም ብለው ስራ የለቀቁም እንዳሉ ይታወቃል፡፡

የጦር ሜዳ ዘጋቢው -ከሞት ተረፈ-ሰኔ 12

ሣሙኤልም ጦር ሜዳ ሂድ ቢባል አማራጭ ስላለው አይሄድም ከሚል እሳቤ በተንኮል ነበር እንዲመደብ የተደረገው፡፡ ሣሙኤል ግን በጣም ተደስቶ የሰጠው ምላሽ ማንም ያልጠበቀው ነበር፡፡  ‹‹ምነዋ ተደሰትክ ጦር ሜዳ እኮ ነው የተላከው›› ቢሉት ‹‹በጋዜጠኝነት ህይወቴ የጦር ሜዳን ውሎ የምዘግብበት የታሪክ አጋጣሚ ላይፈጠር ይችላልና ይህን ዕድል በማግኘቴ በጣም ተደስቻለሁ›› አለ፡፡ የሚያሾፍ የመሰላቸውም ነበሩ፡፡ ግን ከምሩ ነበር ሄደ፡፡

የጦር ሜዳው ቆይታው ሲታወስ በተአምር ከሞት የተረፈበት አጋጣሚን አይዘነጋውም፡፡ ጊዜው 1992 ዓ.ም ሰኔ 12 ቀን ጦርነቱ የተጠናቀቀበት ማግስት ቢሆንም ሻእቢያ እንደ አሸዋ የዘራው ፈንጂ አልተነሳም፡፡ የሰራዊቱን ተጋድሎ ገድል በተገኘበት የውጊያ ነጥብ ላይ እየተገኙ የሚዘግቡት ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ተውጣጥተው ግንባር የተገኙት ከ17 በላይ ጋዜጠኞች በዕለቱ ዛላንበሳ ግንባር ሰንዓፌ መንገድ ላይ ተገኝተዋል፡፡ እንደ አሸዋ የተዘራውን፤ የቁልቋል ተክል የመሰለውንና በሠፊ ሜዳ ላይ የተዘራውን ፈንጂ ተረማምደው አኩሪ ገድል የፈፀሙ ጀግኖችን ተጋድሎ ለመዘገብ፡፡ ከፍተኛ ገድል የተፈፀመበት የተጋድሎ ቦታ የሚገኘው ግን ከፈንጂ ወረዳው ወዲያ ማዶ ሻእቢያ  ከነበረበት ምሽግ ውስጥ ነበር፡፡

ያንን ተጋድሎ ለመዘገብ የፈንጂ ወረዳውን ማለፍ አለባቸው፡፡ መንገድ ግን የለም፣ በፈንጂ ታጥሯል፡፡ በፈንጂ አምካኝ መሀንዲሶች ፈንጂ እየተለቀመ ወይም እየመከነ ቀጭን የእግረኛ መንገድ ተከፈተ፡፡ ምድረ ጋዜጠኝ ሰለሜ ሰለሜ እንደሚጨፍሩ ሲዳማዎች ፊትና ኋላ ተያይዘው፤ ግራና ቀኝ እንደ አሸን የተዘራውን ፈንጂ ማየቱ እየዘገነናቸው በዚያች ቀጭን መንገድ ከግማሽ ኪሎ ሜትር ያላነሰ ርቀት በፈንጂ መሀል ተጉዘው የሞት ሞታቸውን ፈንጂ ወረዳውን ተሻግረው ሻእቢያ ጥሎት የሸሸው ምሽግ አፋፍ ላይ ደረሱ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ግዙፉ የፎቶ ካሜራ ባለሙያ እሱና የሙያ አጋሮቹ በአግራሞት የተሻገሩትን ያን የፈንጂ መዐት በካሜራው ለማቆየት ጉጉት ያድርበትና በቀጭኗ የእግር መንገድ ወደ መሀል ይመለሳል፡፡ ባየው ነገር ግን አይኑን ማመን አልቻለም፡፡

ከደቂቃዎች በፊት በፍርሀት ተውጠው ያለፉበት ቀጭን መንገድ ላይ አንድ የህይወት መጠበቂያ (life saver) ጃኬት የለበሰ ፈንጂ አምካኝ መሀንዲስ መሬት እየቆፈረ የተቀበረ ፈንጂ ከመሬት ለማውጣት ይታገላል፡፡ ግዙፉ የፎቶ ካሜራ ጋዜጠኛ ጠየቀ – ‹‹አንተ! ምንድነው የምታወጣው?›› በማለት፡፡ ፈንጂ አምካኙም ‹‹ፈንጂ እያወጣሁ ነው›› አለ፡፡ ‹‹አሁን ረግጠነው ያለፍንበት መንገድ አይደለም እንዴ?›› ሲል ጠየቀ የፎቶ ካሜራ ባለሙያው፡፡ ‹‹አዎ›› ሲል ምንም እንዳልተፈጠረ ተረጋግቶ መለሰ የፈንጂ አምካኙ መሀንዲስ፡፡ የፎቶ ካሜራ ባለሙያው ግን መረጋጋት አልቻለም፡፡ ‹‹እኛ ረግጠነው አልፈን እንዴት ሳይፈነዳ ቀረ ?›› ሲል ጠየቀ ‹‹ይሄ እኮ ፀረ ተሸከርካሪ ፈንጂ ስለሆነ ነዋ ›› አለ የፈንጂ አምካኝ መሀንዲሱ ከተቀበረበት መሬት አልወጣ ብሎ የሚያታግለውን ፈንጂ ለማውጣት እየታገለ ‹‹ምን ማለት ነው ?››  ሲል ጠየቀ ግራ የተጋባው የፎቶ ካሜራ ጋዜጠኛው ‹አየህ ወንድሜ ፀረ- ተሸከርካሪ ፈንጂ የሚፈነዳው ከ80 ኪ.ግ. በላይ ክብደት ሲጫነው ብቻ ነው ፤  በአብዛኛው በዚህ ላይ ተረማምዳችሁ ያለፋችሁት በሙሉ ክብደታችሁ ከዚያ በታች ስለሆነ ይሆናል›› በማለት ፀረ ተሸከርካሪው ፈንጂው ሳይፈነዳ የቀረበትን ምክንያት ለማስረዳት ሞከረ፡፡ ግዙፉ የፎቶ ካሜራ ባለሙያ አሁን የሰማውን ማብራሪያ የሚያምንበት ዐቅም አጣ

‹‹እኔ እኮ ሰማንያ ስድስት ኪ.ግ. ነኝ›› በማለት በድንጋጤ ሊወድቅ ተንገዳገደ፡፡ ፈንጂ አምካኝ መሀንዲሱም በድንጋጤ ስራውን አቁሞ ሊወድቅ የተንገዳገደውን ግዙፍ ሰው መደገፍ ያዘ፡፡ ‹‹አዎ ምናልባት አንተ ይህቺን ነጥብ ሙሉ ለሙሉ አልረገጥካት ይሆናል እንጂ ይህ ሁሉ ጋዜጠኛ እዚህ ቦታ ላይ ሊሰዋ ይችል ነበር›› አለው፡፡ ግዙፉ የፎቶግራፍ ባለሙያ በድንጋጤ ሊያነሳ ያሰበውን ፎቶ ሳያነሳ ወደ ባልደረቦቹ ተመለሰ፡፡ ጉድ ጉድ እያለ የሰማውን ሁሉ ለባልደረቦቹ አካፈለ፡፡ አሁን የድንጋጤ ማህበርተኞቹ በረከቱ፡፡ እዚያ የተሰበሰበው ጋዜጠኛ በሙሉ ይበልጥ ያስደነገጠው ከሞት የተረፈበት አጋጣሚ አይደለም፡፡ ያን የፈንጂ ወረዳ እንዴት ተሸግረው እንደሚመለሱ ሲያስቡት እንጂ፡፡

ሣሙኤል ቀኑን በማስታወስ እዚያ የተሰበሰቡትን ባልደረቦቹን በሙሉ አረጋጋ፡፡  እናቱ ዳቦ ጋግረው፤ ሳሙኤልን አሸክመው አምስት ኪሎ ሜትር ተጉዘው የሚዘክሩትን የሌንጫው ሚካኤልን አስታወሰ፡፡ ባህራንን ከሞት ያሻገረው ቅዱስ ሚካኤል አሻገራቸው፡፡ እሱና ጓ ደኞቹ ሞትን ድል አድርገው ያንን አስፈሪ የፈንጂ ወረዳ ለሁለተኛ ጊዜ በተዓምር ተሻገሩት፡፡ ሰኔ 12 የሚካኤል ቀን፡፡ በጣም የሚደንቀው ደግሞ ያንን ተዐምር ከሁሉ ቀድሞ ያስተዋለው ግዙፉ የፕሬስ ድርጅት ፎቶ ጋዜጠኛ ስሙ ክንፈ ሚካኤል ነው፡፡ የሳሙኤል ቀጣይ የህይወት ገጽ ወደየት ያመራ ይሆን በክፍል 3 ይጠብቁን

የምርመራ ጋዜጠኝነት -አይናችን-ወርቃማው ዘመን

ሣሙኤል በጋዜጠኝነት ሕይወቱ በተለይም በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ እውቅናና ዝና ያተረፈለትን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመሸለም የበቃበትን የምርመራ ጋዜጠኝነት (Investigative Journalism) ሥራን የጀመረው ከጦር ግንባር መልስ ነው፡፡ ሣሙኤል ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን የተቀላቀለበት ወቅት ‹‹ወርቃማው የቴሌቪዥን ዘመን›› በመባል ይታወሳል፡፡

ይህ ወቅት ኢቲቪ አንድም ሶሎሜ ታደሰንና አሰፋ በቀለን በመሰሉ በጋዜጠኝነት ሙያ በቂ ልምድና እውቀት ባላቸው የስራ ሀላፊዎች ይመራ የነበረበት ወቅት በመሆኑ፤ ሁለትም ‹‹ዓይናችን፤ ስኬት፤ አውደ ሰብ፤ ትኩረት›› በመባል የሚታወቁና በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ አዳዲስ ፕሮግራሞች የተጀመሩበትና የፕሮግራሞቹ አዘጋጅ ጋዜጠኞችም ከዚያ በፊት የማይታወቅ የሙያ ነፃነት ያገኙበት ጊዜ ስለነበር ‹‹ወርቃማው የቴሌቪዥን ዘመን›› በመባል ይታወሳል፡፡

ሣሙኤል ከሬዲዮ እንደተዛወረ ‹‹አይናችን›› ፕሮግራም ላይ ተመድበሀል ሲባል በቀላሉ አልተቀበለውም፡፡ ሆኖም አንድም በዩኒቨርሲቲው ቆይታው የቀሰመው የህግ እውቀት ሁለትም በተፈጥሮው ተግዳሮትን ለመጋፈጥ ያለው ዝንባሌ እርሾ ሆነውት በርካታ ተወዳጅ ፕሮግራሞችን መስራት ችሏል፡፡ የተለያዩ ፈታኝ አጋጣሚዎችንም አሳልፏል፡፡

የቄራው ህንጻ

ሣሙኤል ለመጀመሪያ ጊዜ በዐይናችን ፕሮግራም ላይ ያቀረበው ቄራ አካባቢ በግብር ዕዳ በሀራጅ እንዲሸጥ የተወሰነበትን ትልቅ ዘመናዊ ህንፃ በ3 ሚሊዮን ብር የተሸጠበትን የጨረታ አሻጥር በተመለከተ ያቀረበው ዘገባ ነበር፡፡ ህንፃው ከሀገር እንዲወጡ የተደረጉ አንድ ኤርትራዊ ንብረት ነው፡፡ ግለሰቡ ከሀገር ሲወጡ ያልከፈሉት የመንግስት ግብር አለ በሚል ተገቢውን የጨረታ ስርዓት ሳይከተል ከፍተኛ ገንዘብ ሊያወጣ የሚችል ዘመናዊ ህንፃ እንዴት በሦስት ሚሊዮን ተሸጠ የሚል ነበር፡፡ ዘገባው አየር ላይ ከዋለ በኋላ ጨረታው ተሰርዘ፡፡

ያለአግባብ መሬታቸውን የተነጠቁ የባሌ ኢንቨስተሮችን ጉዳይን የሚመለከተውና ‹‹እውን ሶሻሊዝም በባሌ›› በሚል ርዕስ ባቀረበው የምርመራ ዘገባ ምክንያት የተነጠቀው መሬታቸው ለባለሀብቱ ሊመለስ ችሏል፡፡ በግድያ ወንጀል የተጠረጠረው የጅማ ፖሊስ፤  በሦስት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር ተሸጠ የተባለው የደሴ ህንፃ፤ፍርድ ቤት በዋስ የለቀቃቸው የሸኖ ነዋሪ ፖሊስ የፍርድ ቤት ትእዛዝን ያልፈፀመበት ምክንያት፤የአሰላ ሆስፒታል የቤተዘመድ ቤት የተባለበት አሰራር፤ በተደራጀና በተራቀቀ ሀይል የሚመራው የኮንትሮባንድ ንግድ፤ ለዓመታት ያለአግባብ የተዘጉ መንገዶችን ያስከፈተበት (ሀይሌ ሮጦ፤ሠሜ ተገልብጦ፤ሣሚ አፋጦ መንገድ ተሰየመላቸው ተብሎ- በዘላለም ኩራባቸው የተቀለደበት)፤ ቤታቸው ተቃጥሎባቸው የነበሩ የመርካቶ አሜሪካን ግቢ ነዋሪዎች ለነሱ የተሰራው ቤት ለዓመታት ተቆልፎበት ባዶውን እየኖረ ከ10 ዓመት በላይ በአዳራሽ የኖሩት ምስኪኖች ህይወት የተዳሰሰበት የምርመራ ዘገባዎች ሣሙኤልን ዝነኛ ለመሆንና ለመሸለምም ካበቁት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

1993 የህወሀት ክፍፍል 

1993 ዓ.ም. የነበረው የህወሀት ክፍፍል በሣሙኤል የምርመራ ጋዜጠኝነት ህይወት ውስጥ የተለየ ትዝታን ጥሎ አልፏል፡፡ በክፍፍሉ የቤተ መንግስት ቡድን ተብሎ የሚታወቀውን የነመለስ ጎራ ተፃርረው የቆሙት በነስዬ አብረሀም የሚመሩት ‹‹የአንጃው›› ቡድን አባላት ነበሩ፡፡ በነመለስ የሚመራው የቤተመንግስት ቡድን በክፍፍሉ አሸናፊ ሆኖ ከወጣ በኋላ የአንጃው ቡድን አባላትና ደጋፊዎችን ሰበብ አስባብ እየፈለገና እየለጠፈ ማሰር፤ከስልጣናቸው ማባረር ጀመረ፡፡ የዚህ እርምጃ ሰለባ ከሆኑት መካከል የባሌ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩት ባለስልጣን አንዱ ነበሩ፡፡ እኝህን ባለስልጣን ለማሰር ምክንያት ሲፈለግ የአርሶ አደሮች መብት የማስከበር አጀንዳ ተቀረፀ፡፡

በዚህም ቀደም ሲል በክልሉ ተለምነውና ተጋብዘው በህጋዊ መንገድ የእርሻ መሬት የተሰጣቸው ባለሀብቶች ለስብሰባ ከያሉበት ተጠርተው፤ በአንድ አዳራሽ ውስጥ እንዲሰበሰቡ ተደርገው አርሶ አደርን አፈናቅላችኋል ተብለው ከዛሬ ጀምሮ መሬታችሁ ተወርሷል ተባሉ፡፡ በወቅቱ የደረሰባቸውን በደል አስመልክቶ ቃለ- ምልልስ ከተደረገላቸው ባለሀብቶች አንዱ ‹‹ባሌ ላይ ሶሻሊዝም ታውጃል›› በማለት ምሬታቸውን ይገልፃሉ፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያ የፕሮግራምን ርዕስ ከቃለ ምልልስ ከሚገኝ አገላለፅ ላይ መውሰድ ተመራጭ በመሆኑ ሣሙኤልም ለዝግጅቱ ‹‹እውን ባሌ ላይ ሶሻሊዝም ታውጇል?›› የሚል ርዕስ ሰጠው፡፡ የምርመራ ዘገባው ባለሀብቶቹ መሬት የተረከቡበትን ህጋዊ ሂደትና የተነጠቁበትን የጉልበት አሰራር ያጋለጠ ነበር፡፡ ይህ ፕሮግራም ለተከታታይ ሣምንት አየር ላይ ከዋለ በኋላ ባለሀብቶቹ መፍትሄ አገኙ፡፡

የሚገርመው ግን ለባለሀብቶቹ መሬት መነጠቅ ምክንያት የሆኑትና ከአንጃው ጎራ ተሰልፈው የነበሩትና በወቅቱ ‹‹የጦስ ዶሮ›› የሚል ስም የተሰጣቸው የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በቁጥጥር ስር ከነበሩበት እስር ቤት አምልጠው ኬንያ ገቡ ተባለ፡፡ ከዚያ ወዲህ ባለሀብቶቹንም ማሳደዱ ቆመ የህወሀት ክፍፍል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዜና ዘገባም ላይ ጫና ሲያሳድር ተስተውሏል፡፡ ከክፍፍሉ ጋር በተያያዘ ከዚያ በፊት ሲታሙበት የቆየውን የሙስና ወንጀል አግዝፎ በማቅረብ ስዬ አብረሀምና ቤተሰቦቹ ለእስር ይዳረጋሉ፡፡

የነስዬን የፍ/ቤት ውሎ ከሣሙኤል የተሻለ የህግ ግንዛቤ አለው በሚል ምክንያት በየጊዜው እየተከታተለ እንዲዘግብ በቋሚነት ተመደበ፡፡ በዚህ ምክንያት የዜና ክፍል ባልደረቦቹን የሙያ እገዛ የሚሰጥበት እድል ተፈጠረ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን የዕለቱ ዜና ተረኛ ዋና አዘጋጅ ስለሺ ሽብሩ ስለነበር ከሣሙኤልም ጋር የቅርብ ወዳጆች ናቸውና ከትግርኛ ክፍል በአማርኛ የተተረጎመና እንኳንስ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ለሚያክል ትልቅ የመረጃ ሠጪ ተቋምና ለመንደር ወሬ የማይመጥን መቀሌ ከተማ ላይ የተጠናቀረ አንድ አርቲ ቡርቲ ዘለፋ የሞላበት ሀሜት ‹‹ዜና›› ተብሎ ይመጣል፡፡ ስለሺ ቋቅ እያለው በግሉ አነበበው፡፡ ስሜቱን መቆጣጠር ሲያቅተው እንካ እስኪ ኤዲት አድርገው ይልና ለሣሙኤል ይሰጠዋል፡፡

ሣሙኤል ለማንበብ ሞከረ መጨረስ ግን አልቻለም፡፡ ማንበቡን አቋረጠና ዘገባውን ወደ አማርኛ ተርጉሞ ያመጣውን የትግርኛ ክፍል ባልደረባ ‹‹ይሄ እኮ ዜና ሳይሆን የባለጌ ስድብ ነው›› ይለዋል፡፡ ‹‹አንተ ምን አገባህ›› በማለት ሊያስፈራራው ሞከረ፡፡ ‹‹ታግለን ሰጥተናችኋል የምትሉንን ዴሞክራሲ ሳትታገል ልትነጥቀኝ አትሞክር፤ እንኳን እኔ አንተም ከትግርኛ ክፍል መጥተህ ማዘዝ እየቃጣህ ነው›› በማለት አላገጠበት፡፡ በዚህ የተናደደው የትግርኛ ክፍል ባልደረባ ዜናው መተላለፋ አለበት እንዳይቀር ብሎ ቀጭን ትእዛዝ አስተላልፎ ሄደ ሰውዬው ስለሺ ሽብሩ ነው ማንንም አይፈራ

‹‹እንግዲያው አንተ የአማርኛ ዜና ክፍል ሀላፊ ስትሆን ታስተላልፈዋለህ›› ይልና ከዘገባው ጋር የሰጠውን ቪዲዮ መሳቢያው ውስጥ ይቆልፍበታል፡፡ ያኔ ‹‹ለመሆኑ ቪዲዮም አለው እንዴ?›› ሲል ጠየቀ ሣሙኤል፡፡ ‹‹ካዲያ!›› አለ ስለሺ አዎ የማለት የሱ ቅላፄ ናት፡፡ ‹‹ለምን አናየውም›› በማለት ሣሙኤል ቪዲዮውን ይዞ ከሦስተኛ ፎቅ ሁለተኛ ፎቅ ወረደ ቪዲዮ የሚታይበት ኤዲቲንግ ክፍል፡፡

በነገራችን ላይ የህወሀት ክፍፍል የትግራይ ፖለቲካ ልሂቃንን ለሁለት በከፈለበት ማግስት ኢዴፓ መቀሌ ላይ አፄ ዮሀንስ አዳራሽ ውስጥ ህዝባዊ ስብሰባ ይጠራል፡፡ በቤተ መንግስቱ የህወሀት ቡድን የሴራ ፖለቲካ የተከፋ የመቀሌ ህዝብ አዳራሹን ከአፍ እስከ ገደቡ ሞልቶታል፡፡ ውስጥ ቦታ አልበቃ ብሎ ደጅ የተኮለኮለውም ህዝብ እጅግ በጣም ብዙ ነው፡፡

በቤተመንግስቱ የህወሀት ቡድን ላይ የማይወርድ የውግዘት ናዳ፤ ያልተሰማ የተቃውሞ ዓይነት የለም፡፡ ይህን ይዘው ነበር የትግርኛ ክፍል ባልደረቦች ‹‹የተሰበሰቡት ፀረ ሠላም ሀይሎች ያደራጇቸው አደገኛ ቦዘኔዎች ናቸው›› የሚልና የስድብ ዓይነት የተዥጎደጎደበት ዘለፋን አጭቀው ዜና ብለው ያመጡት፡፡ ቪዲዮውን ካየው በኋላ ‹‹ይህን ያህል ብዛት ያለው አዳራሽ ሙሉ አደገኛ ቦዘኔ መቀሌ ውስጥ ካለ ሕወሀት ዜና ማሰራት ሳይሆን ስልጣን መልቀቅ ነው ያለበት›› አለ ሣሙኤል፡፡ ስለሺም በሀሳቡ ተስማማ፡፡

የትግርኛ ክፍል አሸርጋጆች ‹‹ተዋሪድና›› አሉ፡፡ ከስለሺ በላይ ሣሙኤል ላይ ፎከሩ ‹‹ዋጋህን ታገኛለህ›› በማለት፡፡ በማግስቱ ሣሙኤል ያለወትሮው ከማንም ቀድሞ ማልዶ ቢሮ ገባ፤ የተደገሰለትን ዋጋ በጠዋት ለመቀበል ጓጉቶ፡፡ የሚገርመው ግን የትግርኛ ክፍል አሸርጋጆች ቀድመውት ም/ሥራ አስኪያጁ አሰፋ በቀለ ቢሮ ገብተው ሴራ እየጉነጎኑለት ነበር፡፡ በእነርሱ ቤት አሰፋ ያሉትን ብቻ ሰምቶ ዋጋውን ይሰጠዋል ብለው ገምተው ነበር፡፡ ነፍሱን ይማረውና አሰፋ ግን ነገሮችን በሙያ መስፈርት ብቻ  የሚያይ ሰው ነበረ፡፡

ማምሻውን ጀምረው እረፍት ቢነሱት በሌሊት ገብቶ በትግርኛ የተዘጋጀውን ዘገባ ተመልክቶ ስለነሱ ሳያፍር አልቀረም፡፡ አንድ ነገር ብቻ ማረጋገጥ ፈልጓል፡፡ ሣሙኤል የኢዴፖ አባል ነው በሚል የቀረበለትን ክስ መመርመር፡፡ ደውሎ ጠራው ሣሙኤልም በቅርብ ነበርና ፈጥኖ ሄደ፡፡ ‹‹ኢዴፓ መቀሌ ላይ ይህን ያህል አባላት አሉት እንዴ?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ‹‹እንኳንስ ይህን ያህል አባላት ደጋፊዎችም እንዳሉት እጠራጠራለሁ›› ይለዋል፡፡ ‹‹ካዲያ ያን ያህል አዳራሽ ሙሉ ህዝብ እንዴት ሊሰበስብ ቻለ?›› ጠየቀ አሰፋ፡፡ ‹‹የድርጅቱ አባልም ደጋፊም ባለመሆኔ እንዴት ሊሰበስብ እንደቻለ እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም፤ ከሁኔታዎች ተነስቼ ለእውነት የቀረበ ግምቴን ግን ልነግርህ እችላለሁ›› አለ ሣሙኤል፡፡ ‹‹እስኪ ንገረኝ›› አሰፋ መለሰ፡፡ ‹‹በአዳራሹ የተሰበሰበው ህዝብ የኢዴፓ አባላት ወይም ደጋፊዎች አለመሆናቸውን መገመት አያዳግትም፡፡ ከግምት በላይ መናገር የሚቻለው ግን የህወሀት ተቃዋሚ መሆናቸውንና አደገኛ ቦዘኔዎች አለመሆናቸውን ነው፡፡

በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት በሚያውቀው ‹‹ሰይጣን›› የተከፋ ህዝብ ብሶቱን የሚያሰማበትን መድረክ አብዝቶ ስለሚሻ የማያውቀው ‹‹መልዐክ›› ይህን እድል ካመቻቸለት ይጠቀምበታል፡፡ በዚያ አዳራሽ የተሰበሰበው ህዝብም በዚህ ስነ አመክንዮ የተሰበሰበ ይመስለኛል፡፡ ከዚያ በተረፈ አንድ አዳራሽ ሙሉ ህዝብ የአደገኛ ቦዘኔ ስብስብ ነው ብሎ ዜና መስራት ከማንም በላይ ህወሀትን ከማዋረድ የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ ለትግራይ ህዝብም አይመጥንም፡፡›› በማለት ይመልስለታል፡፡ አሰፋ ከዚህ በኋላ ሣሙኤልን የሚሞግትበት ምክንያት አልነበረውም ‹‹ሌላ ጊዜ እናወራለን›› ብሎ አሰናበተው፡፡ ከዚያ በኋላ ‹‹ዋጋህን ታገኛታለህ›› ብለው ከፎከሩበት የትግርኛ ክፍል ባልደረቦች ጋር የተነጋገሩትን አያውቅም፡፡

የስዬ አብረሀ ችሎትን አልዘግብም

በዚያው ሰሞን ስዬ አብረሀ የዋስትና መብት ተፈቀደለት፡፡ እሱና ቤተሰቡ በደስታ ተቃቅፈው ከችሎት አዳራሽ እንደወጡ ደጅ የሚጠብቃቸው ፖሊስ ስዬን በድጋሜ አሰረው፡፡ ዜናውን ለኢቲቪ ለመዘገብ በስፍራው የተገኘው ሣሙኤል የሆነውን ሁሉ ከተከታተለ በኋላ ቢሮው ተመልሶ ‹‹የነስዬ አብረሀምን የክስ መዝገብ የመረመረው ችሎት በዛሬው ውሎው ስዬ አብርሀም በዋስትና እንዲለቀቁ ትእዛዝ ሰጠ፤ ፖሊስ በሌላ ወንጀል እጠረጥራቸዋለሁ በማለት ሳይፈታቸው ድጋሜ አሰራቸው›› የሚል መሪ (lead) ዘገባ ያለው ሚዛናዊ የሚመስል ዜና ዘገበ፡፡ የትግርኛ ክፍል ባልደረቦች ፎከሩ፡፡ ይሄ ዜና እንዳይተላለፍ በማለት አዘዙ፡፡ ‹‹ምን አገባችሁ ?›› አላቸው ሣሙኤል፡፡ አሁን ግን እንደዚህ ቀደሙ ሊገዳደራቸው አልቻለም፡፡ እንደሚያገባቸው አሳዩት፡፡ ሣሙኤል ያጠናቀረው ዜና እንዲቀር ተደረገና ኢዜአ የላከው ዜና ተላለፈ፡፡ ሣሙኤል ‹‹ሁለተኛ የስዬ አብረሀ ችሎት ላይ ተገኝቼ ዜና አልሰራም›› አለ፡፡ ‹‹ልስራስ ብትል ማን ይመድበሀል›› ተባለ፡፡ በሱ ቦታ ሌላ ሰው መመደብ ተጀመረ፡፡

የበረከት ስልጠና -1996 

1996 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በረከት ስምዖን ሣሙኤልን ጨምሮ ከተለያዩ የመንግስትና የፓርቲ  ሚዲያ ተቋማት የተሰባሰቡ ከ40 በላይ ጋዜጠኞችን ደብረ ዘይት ስራ አመራር ኢንስቲቲዩት ሰብስቦ የፓርቲውን ፖሊሲና ስትራቴጂ በማጥመቅ ስራ ላይ ተጠምዷል፡፡ በየዕለቱ ጧት ጧት ዋናው የስልጠና መርሀ- ግብር ከመጀመሩ በፊት መረጃ መለዋወጥ እየተባለ በሚዲያው ዙሪያ ከህዝቡ የሚደመጡ አስተያየቶች እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡ እንደ ግምገማም፤ መሆኑ ነው፡፡ የደብረዘይቱ ስልጠና አይሉት ግምገማ ከመጠራቱ በፊት የአይናችን ፕሮግራም  ዝግጅት ከአምቦ ነዋሪዎች በደረሰው ጥቆማ መሠረት የአምቦ ኢትዮጵያ ሆቴልን ሽያጭ አስመልክቶ በተለይም የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የተከተለውን ብልሹ አሰራር አስመልክቶ ሣሙኤል አንድ የምርመራ ዘገባ ይሰራል፡፡

በዘገባው ላይ የኤጀንሲውን ምላሽ ለማካተት ቢፈለግም የኤጀንሲው የስራ ሀላፊዎች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ማካተት አልተቻለም፡፡ ምላሽ መስጠት ፈቃደኛ ካልሆኑ በተገኘው መረጃ ዘገባው እንደሚተላለፍ በደብዳቤ ይገለፅላቸው ተባለና ደብዳቤው ተጻፈ፡፡ ኤጀንሲው ግን ምላሹን ከመስጠት ይልቅ ሥራ አስኪያጇ ኢቲቪ ድረስ መጥተው ምን እንደተነጋገሩ አይታወቅም ፕሮግራሙን አስቆሙት፡፡ በሌላ በኩል የአምቦ ህዝብ ፕሮግራሙን በጉጉት እየተጠባበቀ ነበር፡፡ ረጅም እጃቸውን በኢቲቪ ላይ እየዘረጉ የፈለጉት ፕሮግራም እንዲተላለፍ ያልፈለጉት እንዲቀር የማድረግ አቅም የነበራቸው ጉምቱ ባለስልጣን ፕሮግራሙ እንዳይተላለፍ የሰጡት ቀጭን ትእዛዝ አልበቃ ብሏቸው ፕሮግራሙን ያስቀሩት እነሣሙኤል ጉቦ ተቀብለውበት ነው የሚል አሉባልታ በስፋት እንዲወራ አደረጉ፡፡

በዚህ ከተከፉት የአምቦ ነዋሪዎች አንዱ የነበረው አትሌት ፊጣ ባይሳ ጋዜጠኞች በበረከት ፊት እየተገመገሙ ነው መባልን ሲሰማ ከዕለታት በአንዱ ቀን አመሻሽ ላይ ደብረዘይት ይገኝና የስብሰባው ተካፋይ የነበረውን ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤን ስራዬ ብሎ ፈልጎ ያገኘዋል፡፡ እህል ውሀ ሲቀማምሱ ያመሻሉ፡፡ የአምቦ ህዝብ በዓይናችን ፕሮግራም ዝግጅት ከፍል በተለይም በሣሙኤል ፍቅሬ ላይ በእጅጉን ማዘኑንና ያዘነበትን ምክንያትም ያጫውተውና ይሄ ጉዳይ በረከት ጆሮ እንዲደርስ በጠዋቱ መድረክ ላይ ደምሴ እንዲያነሳው አደራ ይጥልበታል፡፡ ነፍሱን ይማረውና አደራው የከበደው ደምሴ ይህን ጉዳይ እንዴት አድርጎ እንደሚያነሳውም ብቻ ሳይሆን ሣሙኤልን በዚያ ሁሉ ጋዜጠኛ ፊት ማሳጣት፤ ጉምቱው ባለስልጣን በሚመራው መድረክ ላይ ማጋለጥ ሆኖ ተሰማውና ከበደው፡፡ ቢቸግረው አንድ ዘዴ ዘየደ፡፡

አስቀድሞ ጉዳዩን ለሣሙኤል ማማከር፡፡ ጊዜው መሸትሸት ቢልም የስልጠናው ተሳታፊዎች በሙሉ እዚያው ስለሚያድሩ ሣሙኤልን ማግኘት አልከበደውም፡፡ ከእሸቱ ገለቱ ጋር ተጋርተው የሚያድሩበትን የመኝታ ክፍል በውድቅት ሌሊት አንኳኳ፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛ በዚያ ሰዓት እነሱን የፈለገበትን ምክንያት ባለማወቃቸው ደነገጡ፡፡ ከእነርሱ በላይ የደነገጠውና ለመደንገጡም ምክንያት የነበረው ደምሴ በዚያን ምሽት የሰማውን ሁሉ አጫወታቸው፡፡ ሣሙኤል ‹‹ይሄ ነው እንዴ እንቅልፍ የነሳህ?  እኔ እኮ የለመድኩት ነው›› በማለት አጣጣለበት፡፡ ‹፣ምን ማለትህ ነው ? በረከት ባለበት ስብሰባ ላይ እንዳቀርብላቸው እኮ ነው የነገሩኝ›› ይለዋል፡፡

‹‹አቅርበዋ ጥሩ ነው›› አለ ሣሙኤል፡፡ ‹‹አትቀየመኝም ?›› ሲል ጠየቀ ደምሴ፡፡ ‹‹ባታቀርበው ነው የምቀይምህ፤ አሁን ደህና እደር›› በማለት አሰናብቶት ተኛ ፡፡ ደምሴ ግን ጆሮውን ማመን አቅቶታል፡፡ አይነጋ የለም ነጋ፡፡ ሌሊት  በሞቅታ የሰማውን ማመን አቅቶት ማልዶ በመነሳት ሣሙኤልን አገኘው፡፡ ‹‹አቅርበው ነው ያልከኝ?›› ሲል በድጋሚ ጠየቀው፡፡ ‹‹አይ ባታቀርበው እጣላሀለሁ ነው ያልኩህ›› አለው፡፡ ስብሰባው ተጀመረ፡፡ በረከትም እንደ ልማዱ መረጃ ማነፍነፍ ጀመረ፡፡ ደምሴ እጁን አወጣ ‹‹በዓይናችን ፕሮግራም ላይ ትላንት የሰማሁት ቅሬታ የሚገርም ነው በማለት ጀመረና ሣሙኤልም አቅርበው ብለኸኛል አይደለም ? በማለት ፊቱን ወደ ሣሙኤል አዙሮ ማረጋገጫ ሲጠይቅ በአዳራሹ የተሰበሰበው ጋዜጠኛ በሣቅ ሞተ፡፡ ሣሙኤል ግን አንገቱን በአዎንታ በመነቅነቅ ይሁንታውን አረጋገጠ፡፡

ደምሴ ማምሻውን ከፊጣ ባይሳ የሰማውን የአምቦ ህዝብ ቅሬታ ዘከዘከው፡፡  ተሰብሳቢው በአግራሞት ያዳመጠው መረጃ ለበረከት ቁብ የሰጠው አይመስልም፡፡ ጭራሽ እንደቀላል ነገር ‹‹ሣሙኤል አስተያየት መስጠት ከፈለገ ይችላል ካልሆነ ግን የዛሬውን ፕሮግራማችንን እንቀጥል›› አለ፡፡ ሣሙኤል ይሄ ጉዳይ በርካታ የሙያ አጋሮቹ በተሰበሰቡበት መድረክ ላይ በመነሳቱ ደስ ብሎታል፡፡ በበርካታ ተመሳሳይ አጋጣሚዎች እጀ ረጃጅሞቹ ፕሮግራም እንዳይተላለፍ የሚያሳድሩትን ጫናና ጣልቃ ገብነት ለማስገንዘብ የሚያስችለውን አጋጣሚ ሊጠቀምበት ተዘጋጅቷል፡፡ በሱ አማካኝነት ከተዘጋጁት ፕሮግራሞች መካከል አየር ላይ እንዳይውሉ የተደረጉት በርካታ መሆናቸውንና ያገዳቸውንም ከዘረዘረ በኋላ የአምቦው ፕሮግራምም እስፍራው ድረስ ተኪዶ ህዝቡ የሰጠው ኢንተርቪው፤ መረጃና ማስረጃ ተጠናቅሮ አየር ላይ ሊውል ቀን በተቆረጠበት ዕለት የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ ቴሌቪዥን ድረስ መጥተው ከቢሮዬ አስጠርተው እንዳይተላለፍ አሉኝ፡፡

እርሳቸው እኔን የማዘዝ ስልጣን እንደሌላቸው ነግሬአቸው ቢሮዬ ተመልሼ ስራዬን ቀጠልኩ፡፡ ከሠዓት በኋላ የማጠናቀቂያውን ስራ እየሰራሁ አሰፋ ያለሁበት ቦታ መጥቶ ይህ ፕሮግራም እንዳይተላለፍ አለኝ ሳይተላለፍ ቀረ፤ የሚያሳዝነው ግን ፕሮግራሙን በከፍተኛ ጉጉት ሲጠባበቅ የነበረው የአምቦ ህዝብ በምን ምክንያት እንደቆመ እንኳን የሚያውቅበት እድል የለም›› በማለት ዘለግ ያለ ቅሬታ አዘል ምላሽ ሠጠ፡፡ በረከት አስመሳይ ፊቱን እየቋጠረና እየፈታ ካስጨረሰው በኋላ የስብሰባው ተካፋይ የነበረውን አሰፋን ‹‹አንተ ነህ እንዴ ያስቆምከው ?›› ሲል ጠቀው፡፡ ‹‹አዎን›. ሲል መለሰ አሰፋ ነፍሱን በገነት ያኑራት፡፡ ‹‹ለምን ?›› ሲል ጠየቀ በረከት፡፡ ‹‹ምክንያቱን ባልናገር እመርጣለሁ በሥራ አስኪያጅነት ስልጣኔ ያስቆምኩት ግን እኔ ነኝ›› አለ፡፡ በረከት ደነፋ፡፡ ‹‹ክርስቲና ፕራይቬታይዜሽን ባለስልጣንን እንድትመራ እንጂ ቴለቪዥን እየመጣች ፕሮግራም ይሂድ አይሂድ ብሎ የማዘዝ ስልጣን ማን ሰጣት?›› አለ፡፡ እሷ ነች ያስቆመችው ለማለት መሆኑ ነው፡፡

የስብሰባው ተሳታፊዎችን በእጅጉን ያስደመመው ግን ነፍሱን ይማረውና የአሰፋ በቀለ ቅንነት ነበር፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ምድረ ባለስልጣን ቢችል የበታቹን ሠራተኛ አጋፍጦ ይረማመድበታል፤ ባይችል መረጃው የለኝም እናጣራዋለን የሚል የተድበሰበሰ መልስ ይሰጣል እንጂ እውነቱን ተናግሮ እራሱን አሳልፎ በመስጠት ሌላውን ነፃ አያወጣም፡፡ በኋላ ላይ ይህ መረጃ በረከት ፊት እንዲቀርብ ብዙ የደከመው አትሌት ፊጣ ባይሳ በመድረኩ ላይ የሆነውን ሁሉ ሲሰማ ሣሙኤልን ይቅርታ ጠየቀው፡፡ 

የደብረዘይቱ ስልጠና አብቅቶ አዲስ አበባ እንደተመለሱ ከዕለታት በአንዱ ቀን ጠዋት ላይ ሣሙኤል አሰፋ ጋር ይሄድና ‹‹ያንን ፕሮግራም ልስራው?›› ሲል ይጠይቀዋል፡፡ አሰፋም ‹‹እስኪ በረከትን አማክረው›› ይለዋል፡፡ ሣሙኤል በምላሹ ግራ እንደተጋባ ከአሰፋ ቢሮ ሲወጣ ድንገት ኮሪደር ላይ ከበረከት ጋር ይገናኛሉ፡፡ ሠላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ‹‹ያንን ፕሮግራም ልሰራው ነው›› ይለዋል፡፡ ‹‹እንዳትሰራው!›› የሚል ቁጣ የተቀላቀለበት ምላሽ ይሰጠዋል፡፡ አሁን ፕሮግራሙን ያስቆመው እጀ ረጅም ማን እንደሆነ ገባው፡፡ ከሠዓት በኋላ ከዓይናችን ፕሮግራም መነሳቱንና የትኩረት ፕሮግራም አዘጋጅ ሆኖ መመደቡን የሚገልፅ ደብዳቤ ደረሰው፡፡ ሣሙኤል ብዙም አልተከፋም፡፡

የትም ቦታ ቢመደብ መስራት እንደሚችል ለማሳየት ቆርጦ ተነሳ፡፡ እንዳሰበውም ተሳካለት፡፡ ይብስ ብለው ምንም ምክንያት ሳይጠቅሱ አሁንም ሌላ ፕሮግራም ላይ እንዲመደብ አስደረጉት፡፡ አሁን ትእግስቱ አለቀ፡፡ ኢቲቪን ከነአካቴው ለመልቀቅ ወሰነ፡፡ የባሰ እንዳይተናኮሉት በመፍራት በዘዴ ሹልክ ማለት ነበር የፈለገው፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ቀጠሮ ያሲዝና በረከት ቢሮ ይገባል፡፡ ትልቅ ዶሴ በእጁ ይዟል፡፡ ‹‹አቶ በረከት እኔ የማንም ፓርቲ አባል አይደለሁም፡፡ ከመሬት እያነሱ የሚለጥፉብኝ ሁሉ ሀሰት ነው፡፡ ኢቲቪ ቆይቼ ሀገሬን ለተጨማሪ ጥቂት ዓመታት ባገለግል ደስ ይለኝ ነበር፡፡በሁለት ምክንያት ይህን ማሳካት አልችልም፡፡ አንደኛው ከባንክ ተበድሬ ቤት ሠርቻለሁ፡፡

በየወሩ ስምንት ሺህ አምስት መቶ ብር እዳ መክፈል ይጠበቅብኛል፡፡ እኔ አሁን ኢቲቪ የሚከፍለኝ ጥቅል ደመዎዜ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር ነው፤ ሁለተኛ እንግሊዝ ሀገር የትምህርት እድል አግኝቻለሁ ትምህርቴን እየተማርኩ በትርፍ ጊዜዬም እየሰራሁ ቤቴንም እዚህ አከራይቼ እዳዬን መክፈል እችላለሁ ስለዚህ ስራ ልለቅ ነው ›› ይለውና በእጁ የያዘውን ዶሴ ገልጦ እፊት ለፊቱ በመዘርጋት ያሳየዋል፡፡ በወቅቱ አራት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር ከባንክ የተበደረበትን የብድር ውል እያሳየው፡፡ በረከት አቀርቅሮ ውሉን እያነበበ ቀና ሳይል አንገቱን እየነቀነቀ ‹‹ ከባንክ ተበድረህ ነው እንዴ ቤት የሰራኸው ?›› አለው፡፡ ሣሙኤል ምንም መልስ አልሰጠም፡፡ በሆዱ ‹‹ከየት አምጥቶ ሰራ ነው ያሉህ ?›› አለ፡፡ በረከት ፈይሉን ከደነና እየመለሰለት ‹‹መልቀቅም ያለመልቀቅም ያንተ ውሳኔ ነው›› ብሎ አሰናበተው፡፡ ሣሙኤል አመስግኖ ከቢሮው ወጣ፡፡ ከዚህ በኋላ ግልገል ካድሬዎቹ ምንም እንደማያመጡ እርግጠኛ ሆነ፡፡ የካቲት 1/1997 ዓ.ም ሣሙኤል አጭር ደብዳቤ ፃፈ፡፡

‹‹ከመጋቢት 1/1997 ዓ.ም ጀምሮ ስራዬን እለቃለሁ›› የሚል፡፡ ሌላ ዝባዝንኬ የለውም፡፡ በኢቲቪ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ታሪክ ከዚህ ያነሰ አጭር ደብዳቤ የለም፡፡ ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ብርሀን ሀይሉ ተናደደ፡፡ ‹‹የምን ንቀት ነው?›› ሲል ተቆጣ፡፡ በፀሀፊው በኩል ‹‹ደብዳቤውን አስተካክሎ ይፃፍ›› ሲል መልዕክት ላከ፡፡ መልስ አልሰጠም፡፡ ጓደኞቹ ‹‹ለምን አታስተካክልም?›› ብለው ሊመክሩት ሞከሩ፡፡ ሣሙኤል አልሰማቸውም ‹‹በገዛ ፈቃዴ ሥራ ለመልቀቅ ህግ የጣለብኝ ዋና ግዴታ ስራውን እንደምለቅ ከአንድ ወር በፊት በማስታወቅ ማስጠንቀቂያ መስጠት ብቻ ነው፡፡ የፃፍኩት ደብዳቤ ይህን ይገልፃል በቃ›› አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ዋና ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ሣይመለስ ደብዳቤውንም ሳያስተካክል ከኢቲቪ ጋር ተለያዩ፡፡   

ሣሙኤል ኢትዮጵያ ሬድዮ እያለ ጀምሮ በቀድሞዋ ባለቤቱ ስም የከፈተው ‹‹ዲና ማስታወቂያ ኢንተርፕራይዝ›› የተሰኘ የማስታወቂያ ድርጅት ነበረው፡፡ በዚህ ድርጅት አማካኝነት በ1990 ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት (ያኔ ኤፍ ኤም አልተጀመረም) የአየር ሰዓት እየገዛ ከሬዲዮ ጋዜጠኛ ከእሸቱ ገለቱ፤ ዘመድኩን ተክሌ፤ ሺበሺ ዓለማየሁ ጋር በመሆን ‹‹የዐውዳዓመት ስጦታ›› የተሰኘ ፕሮግራም ያዘጋጅ ነበር፡፡ ፕሮግራሙ ተወዳጅ በመሆኑ የሣሙኤልም ቅልጥፍና ተጨምሮበት በርካታ ድርጅቶች ስፖንሰር ያደርጉት ነበር፡፡ እንደውም በአንድ ወቅት የመጣለት የስፖንሰር ብዛት ከአየር ሠዓቱ ለማስታወቂያ ከተፈቀደው ሠዓት በላይ ይሆንበትና ቢጨንቀው በወቅቱ ሌላ ፕሮግራም ያዘጋጅ ለነበረው ለቢኒያም ከበደ ለምኖ እንደሰጠው ያስታውሳል፡፡

ሣሙኤል ከኢቲቪ ከለቀቀም በኋላ ያኔ ትርፍ ስራ ይሰራበት የነበረውን ድርጅት ‹‹ዲናሣም ፕሮሞሽን›› በሚል መጠሪያ በአዲስ መልክ አደራጅቶ በግሉ በርካታ የዶክመንተሪ ፊልሞችን ሰርቷል፡፡ በ2002 ዓ.ም አካባቢ ከፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ጋር በመተባበር ‹‹የፍትህ ካስማ›› የተሰኘ በህግ ነክ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ልዩ የቴሌቪዝን ፕሮግራም ጀመረ፡፡ አማኑኤል በቀለ አሳምሮ ያቀናበረለትን ‹‹ይሁን የበላይ፤ ህገ መንግስቱ›› የተሰኘ የፕሮግራሙን መሪ ሙዚቃ (jngel) ድርሰትና የውዝዋዜ (choreograpy) ቀንብሩንም ያዘጋጀው ራሱ ነበር፡፡ በሚድያው አካባቢ በሚሰራቸው ሥራዎች የሚሳካለትን ያክል ሳንካና እንቅፋት የማያጣው ሣሙኤል ከኢቲቪ የስራ ሀላፊዎች ጋር ይጋጭና ፕሮግራሙ ለአስራ አንድ ተከታታይ ሣምንታት ከተላለፈ በኋላ እንዲቆም ይደረግና ተመሣሳይ ይዘትና የፕሮግራም ቅርጽ (formate) ያለው የተባባሪ አዘጋጅ ፕሮግራም እንዲተካው ይደረጋል፡፡

ሣሙኤል በብዕር ስሙ የሰላ ትችት የሚያቀርብባቸውን ፅሁፎቹን ቁም ነገር መፅሄትን ጨምሮ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ ከማቀረብ ውጪ የሚድያው ተሳትፎ ቀዝቅዞ ነበር፡፡ሣሙኤል እንደጋዜጠኝነቱ እውቅናና ዝናን ያተረፈለት ባይሆንም በጥብቅና እንዲሁም በንግድና ኢንቨስትመንት መስክም ተሳትፏል፡፡ በተለይም ደብረዘይት ላይ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንቨስት በማድረግ በዶሮና በወተት ስራ መስክ ተሰማርቷል፡፡ እንዲያም ሆኖ በየትኛውም አጋጣሚ ማንነቱን ሲገልፅ በፍቅር የወደቀለትን የጋዜጠኝነት ሙያውን መጠሪያ ማንጠልጠያ ማድረግን ይመርጣል፡፡ራሱን ሲያስተዋውቅም ሣሙኤል ፍቅሬ – ጋዜጠኛ፤ የህግ አማካሪና ጠበቃ ማለትን ያዘወትራል፡፡

ሣሙኤል በአሁኑ ሰዓት ከጥብቅና ስራው ጎን ለጎን ከEthio FM 107.8 ጋር በመተባበር ዘወትር ማክሰኞ ከ4፡30 ጀምሮ የሚቀርብ ‹‹የቸገረን ነገር›› የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም አለው፡፡ በተጨማሪም ከድሮ ወዳጆቹና ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ‹‹ኢትዮ ዋርካ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን አክሲዮን ማህበር›› (ዋርካ ሚድያ)ን ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር በመመስረትና የቦርድ አባልም በመሆን በሚድያው ላይ አንዳች ለውጥ እንዲመጣ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡

በጎ አድራጎት 

ሣሙኤል በመኖሪያ አካባቢው በማህበራዊ ተሳትፎው ለህብረተሰቡ ቅርብ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በቅርቡ የተማሪዎች የምገባ ስርዓት ከመጀመሩ ከአምስት ዓመት በፊት ሣሙኤል በአካባቢው የሚገኘው የህብር የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ደሀ ተማሪዎች መካከል 160 የሚሆኑት የቁርስና ምሳ ምግብ እንዲያገኙና እስከዛሬም የዚህ መርሀ-ግብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋፅፆ አበርክቷል፡፡ ሣሙኤል ደግሶ እንደማብላትና የቸገረውን እንደመርዳት የሚያረካው የለም፡፡ እየረዳ ያስተማራቸው ወጣቶች በርካታ ናቸው፡፡ በዓል በመጣ ቁጥር ገጠር ገንዘብ የሚልክላቸውም ብዙ ናቸው፡፡ በየዓመቱ ልደቱን የሚያከብረው በሚኖርበት ዋና ከተማ ደግሶ፤ ኬክ ቆርሶ አይደለም፡፡ ይልቁኑም የተወለደበት አካባቢ ገጠር ድረስ እየሄደ አርዶ ድሆችን በማብላትና ስጋ በማደል ነው፡፡

አብዝቶ የሚወዳትንና ‹‹ልደትዬ›› እያለ የሚጠራትን የግንቦት ልደታን የሚዘክረውም ደሆችን በማብላት ነው፡፡ በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ በዋነኝነት ማህበርተኞቼ የሚላቸውንና የአካባቢውን ቆሻሻ በማስወገድ ስራ ላይ የተሰማሩ ከ26 ያላነሱ የፅዳት ሰራተኞችን (አብዛኛዎቹ ሴቶች ናችው) በሬ አርዶ ከማብላት በተጨማሪ በልተው የተረፋቸውን 26 ቦታ መድቦ በላስቲክ ቋጥሮ በማከፋፈል ይታወቃል፡፡ በጣም የሚደንቀው ደግሞ በኮረና ምክንያት ላለፉት 2 አመታት እንደወትሮው እቤቱ ማብላት ቢያቋረጥም አርዶ 26 ቦታ መድቦ በላስቲክ ቋጥሮ ማከፋፈሉን አላቋረጠም፡፡

ቤተሰባዊ ህይወት  

ሣሙኤል ባለትዳርና የሁለት ሴቶችና የ3 ወንዶች ልጆች እንዲሁም የአንድ ሴት የልጅ ልጅ አባት ሲሆን ከአምስት ልጆቹ የወለዳቸው አራቱ ናቸው፡፡ ከአብራኩ ክፋይ ልጆቹ እኩል የሚወደውንና የሚሳሳለትን የመጀመሪያ ወንድ ልጁን የመድሀኒ ዓለም አደራ ነው ይለዋል፡፡ ‹‹የሚያሳድገው ልጅ›› ነው ሲሉትም ይከፋዋል፡፡ ለልጆቹ ያለው ፍቅር ወደር የለውም፡፡ ‹‹ከድንግል አማላጅነት፤ ከገብርኤልና ከሚካኤል ተራዳኢነት፤ ከመድሀኒዓለም ቸርነትና በረከት ቀጥሎ የምኮራውም የምመካውም በልጆቼ ነው›› ይላል፡፡ አሜሪካና እንግሊዝ ያሉትን ሁለቱን ታላላቅ ሴቶች ልጆቹን  እየጠቀሰ ‹‹ሁለቱ ልጆቼ ነዋሪነታቸው ከአትላንቲክ ወዲያ ማዶና ወዲህ ማዶ ነው›› ይላል በኩራት፡፡ ሣሙኤል የተወለደው በመድሀኒ ዓለም ዕለት ጥቅምት 27-1958 ዓ.ም በመሆኑ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም 55ኛ ዓመት የልደት በዓሉን አክብሯል፡፡  

ማጠቃለያ

ሣሙኤል ፍቅሬ፣ በሚድያው ዘርፍ በቆየባቸው 29 አመታት በብዙ መንገዶች አልፏል፡፡ እንደጋዜጠኛ ህዝብ ማወቅ ያለበትን ለማሳወቅ፣ ያለ አንዳች ፍርሀት በድፍረት የአቅሙን ያህል ጥረት ያደረገ ጋዜጠኛ ነው፡፡  የሚፈልገውን ለማግኘት እምን ድረስ እንደሚሄድም አይተናል፡፡ ገና በታዳጊነቱ መነገድ ፈለገ ነገደ፡፡ ደግሞ መማር ሲያሰኘው ተማረ፡፡ ዩኒቨርሲቲ መግባት ሲሻ በ23 አመቱ ግቢን ተቀላቀለ፡፡ ህግ ተማረ-የእውቀት አድማሱን አሰፋ፡፡ እንዲህ እያለ በአይናችን ፕሮግራም የሚችለውን ያህል ሰራ፡፡ እናም በ1994 የመገናኛ ብዙሀን ሽልማትን ከእጁ አስገባ፡፡  ይህ በ6500 ቃላት ወይም በ20 ገጽ የቀረበ የሣሙኤል ታሪክ  ይሁን እንጂ የአብዛኛው የሚድያ ባለሙያን ሽራፊ ታሪክ የሚያነሳሳ ነው፡፡ ስለ ሙያው ማጥናት ከተፈለገ ጋዜጠኛው የሚያልፍበትን  መንገድ ማወቁ የሚጠቅመው እዚህ ጋር ነው፡፡

የሣሙኤል ፍቅሬ ታሪክም ከዚህ አንጻር ከታየ የአንድ ጋዜጠኛን ህይወት በደምሳሳውም ቢሆን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ይመስለናል፡፡  ሣሙኤል በሙያው ውስጥ ሳለ ከሞት የተረፈባቸው ጊዜያት አሉ፡፡ ይህን  ስለ ሣሙኤል ፍቅሬ የሚያወሳ የዊኪፒዲያ ታሪክ ስናቀርብና እና እንዲነበብ ስንወስን የሚያስተምረው ታላቅ ቁምነገር ስላለ ነው፡፡ መጪው ትውልድ ይህን ታሪክ እንዲያውቅ በደማቅ ብእር ከትበን አኑረነዋል፡፡ ለሣሙኤልም  መልካሙን ሁሉ እንመኛለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *