ማንያዘዋል እንደሻው

ማንያዘዋል እንደሻው

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል የቴአትር ባለሙያ ፤ አዘጋጅ እና መምህር ማንያዘዋል እንደሻው አንዱ ነው፡፡ ማንያዘዋል የቴአትር ትምህርት ክፍል የመጀመሪያዎቹን ምሩቃን ሲያስመርቅ ከተመረቁት አንዱ ነው፡፡ ላለፉት 40 አመታት በመምህርነት እና በቴአትር አዘጋጅነት ያገለገለው ማንያዘዋል በአሁኑ ሰአት የብሄራዊ ቴአትር ስራ አስኪያጅ ነው፡፡ ሳምራዊት ተወልደ የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው ሰንዳዋለች፡፡

ብዙዎች ማኔ ሲሉ ይጠሩታል፤ የቴአትር አዘጋጅነት ደግሞ መክሊቱ ነው። ታላቅ ወንድሙ ስዩም ተፈራ ማንያዘዋል እንዳሻው ሆኖ ስሙ እንዳሻው ያልሆን ትሁት እና ታዛዥ ከዓመጽ የጸዳ ሰው ነው ሲል ይመሰክርለታል። ተፈሪ ዓለሙ፦ « 40 ዓመታትን ያስቆጠረ ጓደኝነት አለን፤ አብረን ኖረናል፤ ማንያዘዋል የአደባባይ ሰው አይደለም፤ እሱ ያዘጋጀው ቴአትር ተመርቆ መድረክ ላይ ወጥቶ ሰላምታ መስጠትም ሆነ መታየት አይፈልግም፤ እንደ ተዋናይ ተዋጥቶልኝ የሰራሁዋቸው ሥራዎች ከማንያዘዋል ጋር ያሉትን ነው። » ማንያዘዋል እንደሻው ተወልዶ ያደገው መዲናችን አዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ ነው፤ ከመንታ እህቱ የኔወርቅ እንደሻው ጋር የእናታቸውን ጡት በጋራ ጠብተው አድገዋል። የትውልድ ጊዜውም በ1950 መሆኑ ነው፡፡ ማሙዬ እና ማሚቱ ደግሞ የልጅነት መጠራሪያ ስማችው ነው።

ማኔ በልጅነቱ ብስክሌት በጣም ይወድ ነበር፤እናታቸው በልጅነት እድሜያቸው የምትነግራቸው ተረት ተረት ታሪክን የመውደድ ስሜት አሳድሮብኛል ፤ወደ መድረክ ደግሞ የመራኝ ወንድሜ ነው ይላል። መታየት የማይወድ፤ ደግ፤ ለሰው አሳቢነቱ ከልጅነት ጀምሮ ያደገበት መሆኑን መንታ እህቱ የኔወርቅ እንደሻው ትናገራለች። በልጅነቱ በጣም ጎበዝ ተማሪ ከመሆኑ የተነሳ የተማሪነት ጊዜው ላይ ሁለት ሁለት ክፍል አልፎ ነበር የተማረው።

የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ዳግማዊ ምንሊክ ተምሯል። ከ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርቱን ተከታትሎ ፤ የመጀመሪያው የቴአትር ተማሪም ነበር። ወደ ጀርመን ሀገር ተጉዞም የቴአትር ትምህርቱን አሳድጓል። በህይወቱ በጣም ከሚወዳችው ጊዜያቶች ውስጥ አንዱ በትምህርት ያሳለፈው ጊዜ እንደሆነ ይናገራል። ስራን የጀመረው የቀድሞ መምህሩን ሮበርት ማክላረንን እየረዳ ነበር፤ በተለይ ስለ ዝግጅት ትምህርት ቤት ካገኘሁት እውቀት በላይ ከእርሳቸው ጋር ስሰራ ያገኘሁት ብዙ ነው ይላል። በዚያው የመምህርነት ስራን ቀጥሎ እያስተማረ መማሩን ቀጠለ።

የመንግስቱ ለማ ስራ የሆነውን ዳንዲ ጨቡዴ ዩንቨርሲቲ ሆኖ ያዘጋጀው የመጀመሪያ ስራው ነው። ዳግማዊ ዓመለወርቅ ፈይሳ የስራ ባልደረባ እና የቀድሞ ተማሪ፦ «አካዳሚሺያን ነው፤ በዝግጅት እና ድራማ ላይ ጥልቅ የሆነ እውቀት አለው፤ ይህ ደግሞ የንባቡ ውጤት ነው፤ የተግባር ሰው ነው።
የወጣትነት ዘመኑ ላይ ከደርግ የፖለቲካ ስርዓት ጋር ተያይዞ የልጅነት ህይወቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሮበታል። የሚመለከታቸው ነገሮች “ የህይወት ትርጉሙ ምንድነው?” የሚል ጥያቄን በመፍጠሩ የተለያዩ የቴአትር መፅሀፍትን ማንበብ ጀመረ፣ በአብዛኛው ጊዜ ይወደው የነበረው መጽሐፍ waiting for Godot የሚለውን ነበር። በዚህ እና በሌሎችም ምክንያቶች Theatre of the absurd እሳቤን መከተል ጀመረ፣ ስራዎቹም ላይ ይህ አስተሳሰብ ይንፀባረቃል። የዚህ ማሳያዎቹ ደግሞ የብሩክታዊት ስጦታ፣ እንግዳ፣ እምዬ ብረቷ ማሳያዎች ናቸው። በጊዜ ሂደትም ይህ እሳቤ ከሌላው አፃፃፍ የተሻለ ምርጫው ሆነ።

ትወናም ይወድ የነበረ ቢሆንም ግን ሊገፋበት አልቻለም፣ የአባተ መኩሪያ ዝግጅት የሆነው የቴዎድሮስ ቴአትር ላይ ተጫውቷል፣ አንዳንዴ የራሱ የዝግጅት ስራዎች ላይ የተዋናይ ችግር አጋጥሞት ከቀረ ተክቶ ይጫወታል እንጂ ነፃነት ያሳጣኛል ይላል። አሁን ላይ በመሃል የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ላይ የራሱን ስም እና ስራ ይዞ እየተወነ ይገኛል። ከቴአትር ውጪ ሌላ ህይወት የለኝም የሚለው ማንያዘዋል በርካታ ቴአትሮችን ፅፎ ፣ተርጉሞ አዘጋጅቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል፣ ባለ ካባ እና ባለ ዳባ፣ ንጉስ አርማህ፣እንግዳ፣ የፍቅር ማዕበል፣የመስቀል ወፍ፣ የብሩክታዊት ስጦታ እና እምዬ ብረቷ ጥቂቶቹ ናቸው። ከፊልም ደግሞ አባትየው እና ዴዝዴሞናን ማንሳት ይቻላል።

የስዕል፣ የሙዚቃ እና በአጠቃላይ ያጥበብ አድናቂ ነው። እንግዳ ቴአትር በእንግሊዝኛ ቋንቋ ታትሞለታል። ከዚህ ቀደም በወጣትነቱ እና አሁን ላይ ለ 2ኛ ጊዜ ታላቁ ብሄራዊ ቴአትርን በስራ አስኪያጅነት እየመራ ነው። በስራዎቹ ሁለት ጊዜ በዝግጅት ተሸልሟል፣ በአባትየው ፊልምም ሽልማት አግኝቷል፣ world copy right association እንዲሁ ሽልማት ሰጥቶታል። ሰዎችን ማገዝ የሚወድ፣ ደግ፣ ጎበዝ አዳማጭ፣ ዘመናዊ አስተሳሰብ ያለው፣ግልፅ እና የዋህ ሰው መሆኑን ወዳጆቹ ሁሉ የመሰከሩለት ድንቅ የቴአትር አዘጋጅ ነው።

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ማንያዘዋል እንደሻው ለሙያው የኖረ መሆኑን ብዙዎች በሙሉ አንደበት ይመሰክሩለታል፡፡ በተለይ ደግሞ ቴአትርን ጥንቅቅ አድርጎ በማዘጋጀት ማንያዘዋል ተክኖበታል፡፡ ብዙዎች ይህ የዝግጅት ችሎታውን ያደንቁለታል ብቻ ሳይሆን አንዳች ቁምነገር መቅሰማቸውን ይናገራሉ፡፡ ማንያዘዋልም ቢሆን አቅሙን በዝግጅት ብቻ ሳይሆን በድርሰት እና በትርጉም ለማሳየት ትልቅ ጥረት አድርጓል፡፡ በአስተማሪነቱም ቢሆን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከ25 አመት በላይ በመቆየት ብዙዎች ቴአትርን በእውቀት እንዲሰሩት አድርጓል፡፡ ማንያዘዋል ከዚህም በላይ ሊጻፍለት የሚገባ በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ የተለየ አሻራ ካኖሩት ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡ ማንያዘዋል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳለ ከሮበርት ማክላራን የቀሰመው እውቀት አስተሳሰቡን እንደቀየረለት ያስረዳል፡፡ ለእርሳቸውም ያለውን አድናቆት ይገልጻል፡፡ ማንያዘዋል ከዚህም በላይ ብእር አንስተን ልንጽፍለት የሚገባ ሰው ነው፡፡ ብዙ ለመታየት የማይጓጓው ማኔ ስራውን ብቻ መስራት ርካታ ይሰጠዋል፡፡ ስለ ሀገራችን ቴአትር ስናነሳ ማንያዘዋልን ልንረሳ አንችልም፡፡ እንደ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንደ ማንያዘዋል አይነት ሰዎች ታሪካቸው በወጉ ተጽፎ መቀመጥ አለበት፡፡ ያለፉበት መንገድ ለአዲሱ ትውልድ እንዲተርፍ ማስተማር እና ማካፈል አለባቸው፡፡ መዝገበ-አእምሮ የስነዳ ፕሮጀክት ደግሞ ለዚህ ሆነኛ አማራጭ እየሆነ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *