ሙሉዓለም ታደሠ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ መዝገበ-አእምሮ (የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ) ፕሮጀክቱ ለአገር የሠሩ ሰዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ታሪክ በዲጂታል ሚድያዎች፣ በመጽሐፍ፣ በድምፅ ትረካና በሌሎችም መንገዶች እየቀረበ እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት 4 ዓመታት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ የ423 ሰዎችን የሕይወትና የሥራ ታሪክ ለመሰነድ የቻልን ሲሆን 600 ገፅ ባላቸው ሁለት የተለያዩ መጽሐፎች ላይም ታሪኮቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድርገናል።

ቅፅ 3 መዝገበ አእምሮ ከ20 በላይ ዘርፎች ይኖሩታል። በኪነጥበብና ትወና ዘርፍ ባለፉት 35 ዓመታት አሻራ ካኖሩት እና ታሪካቸውን ከምንሰንድላቸው መካካል አርቲስት ሙሉዓለም ታደሠ ትጠቀሳለች። ሙሉዓለም በመድረክ ቴአትርና በፊልም አቅሟን ያስመሰከረች፣ በማስታወቂያ ሥራና በመድረክ መሪነት ያገለገለች ባለሙያ ናት። የሬድዮ ድራማዎች እና ትረካዎች ላይ ሠርታለች። በዳይሬክተርነትም ችሎታዋን ያስመሰከረች ናት።ሙሉዓለም ተወዳጅ ሚድያ የሚሠራቸውን የህይወት ታሪክ ስነዳ ሥራዎችን የምታከብርና በሥራውም የምታምን ሲሆን የእርሷም የሕይወት ታሪክ እንዲሰነድ ፈቃዷን ሰጥታናለች። ይህን ታሪክ ስናሰናዳ ትልቁን ትብብር ያደረገልንን ወዳጃችንን ሚካኤል ታምሬን ማመስገን እንወዳለን። የሙሉዓለምን የሕይወት ታሪክ ዕዝራ እጅጉ እና ሂላሪያ ተስፋዬ እንደሚከተለው ሰንደውታል።

ትውልድና እድገቷ ሐረር ነው። በዚያው በሐረር ያሳደጓት ደግሞ መነኩሴዋ የእናቷ አክስት ናቸው፥ ሙሉዓለም ታደሠ። በልጅነቷና በአዳጊ እድሜዋ፣ የተሰጣትን የጥበብ ጸጋ ለይታ ያወቀች አይመስልም። እንዲያም ሆኖ ግን በተማረችባቸው ትምህርት ቤቶች በሥነጽሑፍ፣ ስፖርት፣ ቴአትር፣ ሙዚቃና በመሳሰሉት ሁሉ ተሳታፊ ናት።

ሙሉዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በአቡነ እንድርያስ እንዲሁም ኹለተኛ ደረጃ (9 እስከ 12) ትምህርቷን መተሓራ ስኳር ፋብሪካ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረች። በዚህ መካከል ነው፣ እንደዋዛ ወዲያ ወዲህ የምትልበትና እረፍት የነሳችው የተለያየ የጥበብ ሥራ ተሳትፎዋ አብቦ፣ በድፍን ሀገር ደምቃ የምትታይ ኮከብ ለመሆን ጉዞዋ የጀመረው።

መጽሐፍ ማንበብና ፊልም ማየት አብዝታ ትወድድ የነበረችው ሙሉዓለም፣ ትዳር የመሠረተችው ገና በልጅነት ነበር፣ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች። ታድያ የጥበብ ፍቅሯንና በትምህርት ቤት አጥር ተከልሎ የነበረ ለእርሷ ያልታያትን ኪናዊ ችሎታዋን የትዳር አጋሯ አስተውሎት ኖሯል።

እናም አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ፣ እርሷ ወደ አዲስ አበባ ባቀናች ወቅት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበብ መምህራን መተሓራ ተገኙ፥ የአጭር ጊዜ የቴአትር ሥልጠና ሊሰጡ። ምንም እንኳ ሙሉዓለም በሰዓቱ አዲስ አበባ የነበረች ቢሆንም፣ ባለቤቷ ግን ስሟን ከሠልጣኞች ዝርዝር እንዲካተት አስመዘገበ። ሙሉዓለም ከሄደችበት ስትመለስ፥ የቴአትር ሥልጠና ተቀበላት። እናም የቴአትር ትምህርት ጋር በመተሓራ ስኳር ፋብሪካ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዋወቀች።

በሰዓቱ የቴአትር ሥልጠናውን ይሰጣቸው የነበረው መምህራቸው የቴአተር አዘጋጅና ጸሐፊ አስፋው አጽማት ነበር። ይህም ሥልጠና ታድያ በ1983 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ሲጠናቀቅ፣ እርሷን ጨምሮ ተስፋዬ ገብረሃና፣ ቴዎድሮስ ተስፋዬ እና ሰሎሞን ሙላት አንድ ላይ ለቴአትር ሙያተኛነት ተቀጠሩ።

ለሥራ ቅጥር የመጀመሪያ መድረክ ላይ የፈተናት ጌታቸው አብዲ ነበር። እናም ከቅጥር በፊት፣ እንደ ማሟሻ የመጀመሪያ ትወናዋን ከአንጋፋው የቴአትር ባለሞያ ዓለሙ ገብረአብ ጋር “ጭላንጭል” የተሰኘ ቴአትር ላይ ተወነች። ይህ ቴአትር የደረጀ በቀለ (የሕያው ፍቅር መጽሐፍ ተርጓሚ) ነበር።

ሙሉዓለም በዚህ ቴአትር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ የወጣችበትን ያንን ጊዜ መለስ ብላ ስታስታውስ፣ “ቴአትሩ አጭር ቢሆንም፣ አዳራሹ ሙሉ ነበር። ሙዚቃ በድምጽ ማጉያ ከቀረበ በኋላ ነው እኛ ቴአትር ለማቅረብ የገባነው፣ ያለ ድምጽ ማጉያ። ሙዚቃ ለለመደ ጆሮ ቀጥሎ ቴአትር ሲገባ ቀላል አልነበረም።” ስትል ትገልጸዋለች።

ከቅጥሩ መጠናቀቅ በኋላ ‘ውጫሌ 17’ የተሰኘው የታምራት ገበየሁ ቴአትር ላይ፣ ከሌሎች በሰዓቱ ከቴአትር ቤቱ ሥራ ከጀመሩ ተዋናዮች ጋር አጃቢ በመሆን ሠርታለች። ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ነው እንግዲህ፣ 20 ዓመታትን የዘለቀው የብሔራዊ ቴአትር ቆይታዋ አንድ ብሎ የጀመረው።

በ1984 ዓ.ም በሹመት ብሔራዊ ቴአትርን የተቀላቀለው ጸሐፌ ተውኔት ማንያዘዋል እንደሻው፣ ሙሉዓለምን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚያ ወቅት መድረክ ላይ ልምምድ ስታደርግ እንዳያት ያስታውሳል። የተሰጣትን ገጸ- ባህርይ በሰውነት፣ በድምጽ እና በጭንቅላቷም የምትተረጉም፣ በእንግሊዝኛው ‘One of a kind’ የምትባል የሴት ተዋናያት ቁንጮ ናት ይላታል።

ከዚያ በኋላ ሙሉዓለም በትልልቅና ቢያንስ ሁለትና ሦስት ዓመት መድረክ ላይ በሚቆዩ ቴአትሮች ደመቀች፣ የቴአትሮቹም ድምቀት ሆነች። “በኋላ በ1985 ዓ.ም የሠራሁት ከሕዝብ ጋር ያስተዋወቀኝ ‘የሌሊት እርግቦች’ የሚለው፣ ተፈሪ ዓለሙ የተረጎመውና ጌትነት እንየው ያዘጋጀው ሥራ ነው። ከዚያ በዓመቱ ‘የጫጉላ ሽርሽር’ የሚል የተፈሪ ዓለሙን ትርጉም ይዘን ኩራባቸው ደነቀ፣ ተፈሪ ዓለሙ፣ ጀማነሽ ሰሎሞን እና እኔ ሆነን አሜሪካ ሄድን።” ብላለች።

የትወና ሙያ ችሎታና ብቃቷን ከዚያ በላይ ማስመስከር አልተጠበቀባትም። ቀጥላ በሃይማኖት ዓለሙ በተዘጋጀው ‘ዋዜማ’ የተሰኘ ቴአትር ላይ ሠራች። ‘ያለአቻ ጋብቻ’ ተከተለ፥ ቀጥሎ ደግሞ ‘ሐምሌት’ መጣ።

ማንያዘዋል እንደሻው‘ዋዜማ’ የተሰኘው ቴአትር ላይ ሙሉዓለምን እንዲህ ያስታውሳታል፥ “አስቂኝ/ኮሜዲ ዘውግ ያለው ቴአትር ነው። ከአንጋፋና ትላልቅ የቴአትር ባለሞያዎች ጋር ነበር የሠራችው። እኩል መቆም የግድ ያስፈልግ ነበር። ያንን በብቃት ተወጣችው። እዚያ ላይ ፍጥነቷ እና የኮሜዲ ስሜት የፈጠረችበት መንገድ ልዩ ነበር።”

ከዚያ በኋላ ሙሉዓለም በቁጥር ከሃምሳ በላይ ለሚሆኑ፣ እያንዳንዳቸው ሲጠቀሱ ግን ከተመለከተው የአእምሮ መዝገብ የማይጠፋ የቴአትር ሥራዎች ላይ ድንቅ ትወናዋን አሳየች። ከእነዚያም የአመጻ ልጆች፣ ነጻ ወንጀለኞች፣ ርጉም ሐዋርያ፣ የሌሊት እርግቦች፣ ከአድማስ ባሻገር፣ የቬነሱ ነጋዴ፣ አዙሪት፣ ባለካባ ባለዳባ፣ ነጻ ወንጀለኞች፣ የአመጻ ልጆች፣ ውበትን ፍለጋ፣ ኪሊዮፓትራ ተጠቃሽ ናቸው።

ታዋቂ የሆኑትና ከሁሉም በላይ ጎልተው የሚነሱት ንጉሥ አርማህ እና ውበትን ፍለጋ የተሰኙትም ሳይጠቀሱ አይቀሩም። እነዚህ ሥራዎች በ1994 ዓ.ም በተሰጠው ብሔራዊ ሽልማት ላይ እውቅናና ሽልማት ያስገኟት ሥራዎች ናቸው።

ሙሉዓለም ታደሠ የቴአትር ባለሞያ ብቻ ግን አይደለችም። የፊልምና የሬድዮ ድራማ፣ ማስታወቂያ እና ትረካ፥ ከዚያም አልፎ በማስታወቂያ እና ፊልም ዳይሬክቲንግ እና ፕሮድዩስ በማድረግ ሠርታለች።

እንደውም የማስታወቂያ ባለሞያነቷ ከቴአትር ባለሞያነቷ ጋር እኩያ ነው። “ማስታወቂያ ሥራን ከትያትሩ እኩል ነው የጀመርኹት። የመጀመሪያ ብሔራዊ ቴአትር ስቀጠር ጋሽ ውብሸት ወርቃለማኹ ዐየኝ። ከእርሱም ጋር የሎተሪ ማስታወቂያ ሠራሁ። እንደውም ሕዝብ ከቴአትሩ በፊት ያወቀኝ በማስታወቂያ ነው። ከዚያ ቀጥሎ የአምቦ ውሃ ማስታወቂያ ሠራኹ፥ እንደዚያ እያለ ቀጠለ።” ስትል ታስታውሳለች። ከዚያ ቀጥላም ከሦስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የማስታወቂያ ሥራዎችን ሠርታለች።

በማስታወቂያ ሥራ አሁን ድረስ በዘለቀ አብሮነት አብራው የሠራችው የሥራ ባልደረባዋ ሠራዊት ፍቅሬ፣ ከ28 ዓመታት ገደማ በፊት የአዋሽ ባንክ ማስታወቂያን ለመሥራት ሲገናኙ ትውውቃቸው እንደሚጀምር ያስታውሳል። ለሥራው ያላትን ፍቅርና ክብርም አድንቆ፣ ምን ያህል የተመልካችን ቀልብ የሚስቡ ሥራዎች ይሠሩ እንደነበርና፣ ሥራውም ከመስፋፋቱ የተነሳ በጋራ ድርጅት መሥርተው እንደነበርም ያነሳል።

ሙሉዓለም ምንም የማይወጣላቸው በተመልካች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ የማስታወቂያ ሥራዎችን ብቻ ደግሞ አልነበረም የምትሠራው። በጎን ፊልም ሠርታለች። የመጀመሪያ በቴሌቭዥኝ የቀረበ የፊልም ሥራዋ በ1985 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ለዕይታ የቀረበ ‘ቃል’ የተሰኘ ፊልም ነበር። ቀጥላም ‘የነቀዘች ሕይወት’ የተሰኘው ፊልም ላይ ተሳትፋለች።

በፊልም ሥራ የበለጠ የደመቀችው ታድያ ያለእረፍት ካገለገለችበት ከብሔራዊ ቴአትር 20 ዓመታት ቆይታ በኋላ የመጨረሻው ሥራዋ የሆነውን ‘ኪሊዮፓትራ’ ሠርታ መልቀቂያዋን ስታስገባ ነው። ምንም እንኳ እረፍት የማድረግ ሐሳብ ይዛ የነበረ ቢሆንም፣ ሥራዎችን መርጣና ተጠንቅቃ የምትሠራው ሙሉዓለም፣ በሰዓቱ የቀረበላትን ‘ሰው ለሰው’ የተሰኘውን ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ መግፋት አልፈለገችም።

ጎን ለጎን እንደ የነቀዘች ሕይወት፣ ስውር ችሎት፣ ስጋ ያጣ ነፍስ፣ አቦጊዳ፣ ቶክሲዶ፣ የሌባው ልጅ፣ ግራና ቀኝ፣ ጥቁርና ነጭ፣ እና ውበትን ፍለጋ (ከቴአትር የተመለሰ) የሚሉና ሌሎች በርካታ ፊልሞችን እየሠራች፣ ለአራት ዓመታት በቆየው ሰው ለሰው ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ላይ ደምቃ ቆየች። ከዚያም የተወሰነ ጊዜ እረፍት ከወሰደች በኋላ ‘እረኛዬ’ በተሰኘው ሌላ ተወዳጅ የቴሌቭዥን ድራማ ላይ ተገኝታለች። ‘አቦጊዳ’ የተሰኘ ፊልም ዳይሬክተርና ፕሮድዩሰርም ሆና ሠርታለች። በዚሁ ፊልም ላይ ደራሲና ተዋናይም ነበረች።

ከዚህ ሁሉ ባሻገር መድረክ በመምራት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ናት። ‘አንድ ብር ለአንድ ወገን’ ከሚለው መርሃ ግብር ጀምሮ የተለያዩ ሀገራዊና ግዙፍ መድረኮችን እንዲሁ በነጻ ጭምር በመምራት አገልግላለች። በሙያዋ በነጻ አገልግሎት የሰጠችባቸው መድረኮችም ከቁጥር በላይ ናቸው። ከዲኬቲ ኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከግሩም ዘነበ ጋር የመራቻቸውን በርካታ መድረኮች አትዘነጋም።

ከእነዚህ አለፍ ሲባል ደግሞ፥ በሬድዮ ድራማም አለችበትም። በብዛት ባይሆንም በተወሰኑ የሬድዮ ድራማዎች መሳተፏን የምታነሳው ሙሉዓለም፣ በቅርብ የሠራችበትንና በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ይቀርብ የነበረውን ‘ወፌ ቆመች’ የተሰኘ የመዓዛ ወርቁ የሬድዮ ድራማ አንዱ መሆኑን ጠቅሳለች።

ሙሉዓለም ሁለገብ የምትባል የጥበብ ባለሞያ ናት። እንዲያም ሆኖ እርሷ ከሁሉ አብልጣ የምትወድደው ትወናን ነው። “በጣም የምወደው፣ የሚያስደስተኝም ትወና ነው። ዳይሬክቲንግ ላይ ችሎታ አለኝ ብዬ አምናለሁ፣ ግን ጭንቀት አልችልም፥ እሱ ያስቸግረኛል።” ትላለች። ከዚህ ባለፈ በሬድዮ የመጽሐፍ ትረካም ‘ሕያው ፍቅር’ የተሰኘውን መጽሐፍ በመተረክ (ከተፈሪ ዓለሙ ጋር) ጀምራ የቶልስቶይ የሆነውን ‘አና ካሪና’ን (ከዓለማየሁ ታደሰ ጋር) እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ መጽሐፍትን በሬድዮ ትረካ አቅርባለች።

አሁን ደግሞ በአዲስ ሙያ ብቅ ብላለች፣ ይኸውም የቲቪ ሆስት ነው። ‘እሁድ ቤት’ በተሰኘ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥኝ በሚቀርብ ሳምንታዊ መሰናዶ ላይ፣ የተለያዩ አንጋፋና ባለሞያ የሆኑ ሰዎችን በመዘየር፣ ከተዋናይ ሚካኤል ታምሩ ጋር በጋራ በመሆን በቴሌቭዥን መስኮቶቻችን ትታያለች። ከዚህም በተጨማሪ ‘ዞሮ መግቢያዬ’ በተሰኘ በኢቢኤስ እየታየ ባለ ተከታታይ ፊልም ላይ እየሠራች ትገኛለች።

ተዋናይት እመቤት ወልደገብርኤል ስለ ሙሉዓለም ስትናገር፣ ‘የመድረኳ ንግሥት ናት’ ትላታለች። እርግጥም በቴአትር መድረክ ነግሣበት ኖራለች። አልፋም በማስታወቂያና በፊልም ደምቃ፣ ኮከብ ሴት ሆና ትታያለች።

በኢትዮጵያ የጥበብ ዘርፍ በትወና ብዙ እርሷን አርአያ አድርገው የሚከተሉ ወጣቶች አሉ። ከእነዚያ መካከል የሆነችው ተዋናይት ማህደር አሰፋ እንደ ሙያ መምህርት ብቻ ሳይሆን እንደ ጓደኛዋም እንደምታያት ትናገራለች። በበኩሏም ‘ሰው ለሰው’ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ላይ ለትወና እንድትመረጥ (ካስት እንድትደረግ) ያደረገችው ሙሉዓለም መሆኗን አስታውሳ፣ ለሙያውና ለጊዜ ካላት ክብር ጨምሮ አብራት በሠራችበት ወቅት ከሙሉዓለም በብዙ እንደተማረች ትናገራለች።

ሙሉዓለም በነጻ፣ ሙያዊ አገልግሎቷን ከሰጠችባቸውና ለዚያው የእውቅና የምስክር ወረቀት ካገኘችባቸው ባሻገር፥ ከተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) ጋር ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ (በጊዜው ኮሌጅ) እውቅና አግኝታለች። በቴአትር ምርጥ ተዋናይት በመባል የክብር ዲፕሎማ፣ በ’ሰው ለሰው’ ምርጥ ሴት ተዋናይት፣ በ‘ቶክሲዶ’ በጉማ አዋርድ ምርጥ ረዳት ተዋናይት፣ በ’እረኛዬ’ በምርጥ ፊልም በአሜሪካ ኢምፓክት አዋርድ እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች የተለያዩ ሽልማቶችን ተቀብላለች።

ይህ የሙሉዓለም ታሪክ ዛሬ ጥቅምት 15 2018 ሙሉዓለም ታደሰ ለተወዳጅ ሚድያ የሰጠችውን መረጃ መሠረት በማድረግ የቀረበ ነው። አስፋላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ፕላትፎርሞችና በህትመት የሚሰነድ ይሆናል። የመጣጥፉ ባለቤትም ተወዳጅ ሚድያ ሲሆን ፅሁፉን ሲያጋሩ ምንጭ እንዲጠቅሱ የአእምሯዊ ንብረት ህግ ያስገድዳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *