መታሰቢያ ሸዋዬ ይልማ
ጤና ይስጥልኝ አሁን ታላቅ ፊልም ይጀምራል
መታሰቢያ ሸዋዬ ይልማ ፤ በንቁ የኮሚኒኬሽን ሰውነቷ ትታወቃለች፡፡ ጉዞ ማድረግ ከፍ ያለ ደስታን ይሰጣታል፡፡ ያልተሞከረ ነገር መከወን ደግሞ ይበልጥ ያረካታል፡፡ ባለፉት 20 አመታት ከሚድያው ሳትርቅ ቆይታለች፡፡
ትውልድ እና ቤተሰብ
መታሰቢያ ሸዋዬ ይልማ (መቲ) የአባቷ ይልማ ወልደሰንበት እና የእናቷ ሸዋዬ ዱጋ የመጀመሪያ ልጅ ስትሆን የተወለደችው በድሬደዋ ከተማ የካቲት 4 ቀን 1971ዓ/ም ነው፡፡ አባቷ አቶ ይልማ ኢትዮጵያ በወቅቱ ከነበሯት ጥቂት ቢራ ጠማቂዎች መካከል አንዱ ስለነበሩ በእርሳቸው የስራ ፀባይ ምክንያት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የመኖር አጋጣሚ ኖራት፡፡አንድ አመት ሲሞላት አዲስ አበባ መጥተው ለአንድ አመት ከኖሩ በኋላ በሁለት አመቷ ደግሞ ወደ አስመራ አቅንተዋል፡፡ መቲ ሁለት ወንድሞች እና አንድ እህት አላት፡፡
ትምህርት
መቲ ትምህርት የጀመረችው በ3 ዓመቷ አስመራ በሚገኝ ደናግል ካፑቺኒ በተባለ መዋእለ ህፃናት ውስጥ ነበር፡፡ በመቀጠል የአንደኛ ክፍል ትምህርቷን በባህረ ነጋሽ፣ ሁለተኛ ክፍልን በፊላንድ ሚሽን ተምራለች፡፡ በ7 ዓመቷ አዲስ አበባ በመምጣት ጉለሌ አካባቢ በሚገኘው አዲስ አበባ ትምህርት ቤት ሦስተኛ ክፍል ተማረች፡፡ ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ አስራ ሁለተኛ ከፍል የተማረችው ቀድሞ መጠሪያው አሜሪካን ሚሽን፣ በመቀጠል የህይወት ብርሀን አሁን ደግሞ ቤተል መካነ እየሱስ ትምህርት ቤት በሚባለው የሴቶች ብቻ ትምህርት ቤት ነው፡፡ 12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀች ባገኘችው ውጤት የገባችው አዲስ አበባ ኮሜርሻል ኮሌጅ (በተለምዶ ኮሜርስ የሚባለው) ሲሆን የተመደበችውም ባንኪንግና ፋይናንስ እንድትማር ትምህርቱን አቋርጣ የእንግሊዝኛ ስነ-ጽሁፍ ፟(መማር ጀመረች፡፡ ማንበብና ፅሁፎችን መጫጫር ስለምትወድ ትምህርቱን በጣም ወደደችው፡፡ ሁለት አመት ከተማረች በኃላ በሶስተኛው አመት ከአንድ መምህሯ የቀረበላትን የወሲብ ጥያቄ አልቀበልም በማለቷ መምህሩ ውጤቷን አበላሸባት፡፡
ለማታ ትምህርት ክፍልና ለዲፓርትመንት ኃላፊዎች ክስ አቀረበች፡፡ ውጤቷ መበላሸቱ ሳያንስ የደረሰባትን በደል የነገረቻቸው የዩኒቨርስቲው ኃላፊዎች ግን መፍትሄ እንደሌላቸው፣ ይልቁኑ መፍትሄው ከመምህሩ ጋር ተስማምታ ውጤቷን ማስተካክል ብቻ እንደሆነ ነግረው አሰናበቷት፡፡ በዚህም ምክንያት የዩኒቨርስቲ ትምህርቷን አቋረጠች፡፡ ቢሆንም የተለያዩ ጋዜጠኝነት፣ የተግባቦት፣ የፕሮዳክሽን፣ የአመራርና የኢንተርፕረነርሽፕ ስልጠናዎችንና በርካታ አጫጭር ኮርሶችን በመውሰድ እውቀቷንና ክህሎቷን አዳብራለች፡፡ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ስራ የተዘጋበትን ወቅት የተለያዩ የኦንላይን ኮርሶችን በመውሰድ እውቀት ለመጨመር ተጠቅማበታለች፡፡
ሚዲያ
መቲ ሚድያ ላይ የመስራት ፍላጎቷ የመጣው 1986 ዓ/ም የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያለች በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መተላለፍ የጀመረውን አፍሪካ ጆርናል የተባለ ፕሮግራም ተመልክታ ነበር፡፡ በ1991 ዓ/ም የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የፕሮግራም አስተዋዋቂዎች እፈልጋለሁ ብሎ ያወጣውን ማስታወቂያ አይታ አመለከተች፡፡ በመቶዎች ከሚቆጠሩ አመልካቾች መካከል በፈታኞቹ አይን ውስጥ ቀልጣፋዋ መቲ ሸዋዬ ይልማ ገባች፡፡ የቃል፣ የፅሁፍ እና የንባብ ፈተና ካለፉት 7 ሰዎች አንዷ ሆነች፡፡ ታህሳስ 1991 ዓ/ም በ19 ዓመቷ ስራ ጀመረች፡፡ በነበራት ትጋት ቀድሞ ስክሪን ላይ የመታየት ዕድሉን አገኘች፡፡ በቆይታዋ በተለይ ሰው ልብ ውስጥ መግባት የቻለችው ቅዳሜ ምሽት የሚተላለፈውን በየሳምንቱን ታላቅ ፊልም ተመልካች አምሽቶ ስለሚጠብቀው በቂ መረጃ እንዲኖረው አስቀድማ የፊልሙን አይነትና ይዘት፣ ተዋንያኑንና ዳይሬክተሩ በማሳወቅ አምሽቶ የሚጠብቅ ከሆነ እንዲጠብቅ ማየት ካልፈለገ ከጥበቃ እንዲገላገል በማድረጓ ነበር፡፡ በጊዜው በአዲስ ቴክኖሎጂ ፕሮግራሞችን በፅሁፍ ማስተዋወቅ ሲጀመር የእነመቲ ስራ ቆመ፡፡ ተቋሙ በአማራጭነት ዜና እንድታነብ እድሉን ቢሰጣትም መቲ ዜና የማንበብ ፍላጎት ስላልነበራት በዛው አቆመች፡፡
ከኢቲቪ በኋላ ሚዲያ ላይ የተመለሰችው ጋዜጣ ላይ በመጻፍ ነበር፡፡ ታይም አውት አዲስ የተሰኘች አርብ እለት የምትወጣ ሳምንታዊ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ላይ ማህበራዊ፣ ወቅታዊና ስነጥበባዊ ጉዳዮች ላይ ለሁለት ዓመት ያህል ፅፋለች፡፡ ከዛ በኋላ ግን ለጥቂት አመታት ከሚዲያ ርቃ በተለያዩ ሀገር በቀልና አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በኮሚዩኒኬሽንና ሚዲያ ግንኙነት ባለሙያነት አገልግላለች፡፡ በ2000 ዓ.ም የቴሌቭዥን አማራጭ ብዙም ስላልነበረ ሬዲዮ ላይ ለመስራት ወስና ወደ ሸገር ሬዲዮ በመሄድ የአየር ሰዓት እንዲሰጧት ጠየቀች፡፡ መልሳቸው ሬድዮ ላይ ልምድም ስምም ስለሌለሽ ስም ገንብተሸ ነይ የሚል ነበር፡፡ ከማን ጋር ብትሰራ ሬዲዮ ላይ በፍጥነት ስም እንደምትገነባ ማሰብ ጀመረች፡፡
በሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች ማለትም በሚወዱትም በማይወዱትም ዘንድ በጣም ተደማጭ ስለነበረ፣ ሌሎች አዘጋጆችና አቅራቢዎች አብረውት እንዲሰሩ እድል ስለሚሰጥ፣ እንዲሁም አብረውት ለሚሰሩ ፈጠራቸውን ተጠቅመው የራሳቸውን ቀለም ሳይለቁ የራሳቸውን ሃሳብ እንዲያንጸባርቁ ስለሚፈቅድ ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር ለመስራት ወሰነች፡፡ በጊዜው ኤፍኤም 97.1 ላይ አዲስ ዜማ በሚል ርእስ ይሰራ የነበረው ሰይፉ ጋር በመሄድ አብራው ለመስራት ጠየቀችው፡፡ በደስታ ተቀብሏት አብረው መስራት እንደጀመሩ ትናገራለች፡፡ እንዳሰበችውም በቶሎ ስም ገነባች፣ ስራውንም ወደደችወ፡፡
ለ5 ወራት አብረው ከሰሩ በኃላ ተደማጭነት ማግኘቷን በማሰብ ወደሸገር ተመልሳ የአየር ሰዓቱን ጥያቄ ደግማ አቀረበች፡፡ “አሁን የአየር ሰአት እንሰጥሻለን ግን ሰይፉንም ይዘሽ ነይ” ተባለች፡፡
ሰይፉን አነጋግራው በደንብ ካሰቡበት በኋላ ወደ ሸገር ኤፍኤም በመሄድ በጋራ ታድያስ አዲስ ብለው የሰየሙትን ፕሮግራም ጀመሩ፡፡ መቲ ታዲያስ አዲስ ላይ ለ3 ዓመት ያህል ከሰይፉ ጋር ሰራች ፡፡ በመቀጠል መቲ ወደ አፍሮ ኤፍኤም 105∙3 በመሄድ ‹‹ኢን ኤንድ አራውንድ ዊዝ መቲ.›› የተሰኘ በእንግሊዝኛ የመረጃና የመዝናኛ ፕሮግራም ጀመረች፡፡ ለ5 አመታት ያህል ፕሮግራሙቆይቷል፡፡ የእንግሊዝኛውን መሰናዶው አፍሮ ኤፍኤም 105∙3 ላይ እያዘጋጀች ፋና ኤፍኤም 98∙1 ላይ ደግሞ ከፍሰሐ አለማየሁ ጋር በጋራ የጉዞ ፕሮግራም ማዘጋጀትና ማቅረብ ጀመረች፡፡ ሃዋሪ የጉዞ ፕሮግራም በሳምንት ሁለት ቀን በሀገር ውስጥና በውጪ የቢዝነስና የግል ጉዞ ላይ ያተኮሩ መረጃዎችንና ጥቆማዎችን በመስጠት ለ2 ዓመት ተኩል ተላለፈ፡፡ ነገር ግን የጉዞ ፕሮግራም በድምፅ ብቻ ከባድ ስለሆነና እይታን ስለሚፈልግ መቲና ፍሰሐ የጉዞ ፕሮግራሙን ከፋና ሬዲዮ ጋር በመነጋገር አቆሙት፡፡ በዚህ መሀል መቲ ወደ ሲይሸልስ በመሄድ በጋዜጣ ሪፖርተርነት ሰርታለች፡፡
ከሲይሸልስ ከተመለሰች በኋላ የጉዞ ፕሮግራሟን ቴሌቭዥን ላይ ለማቅረብ ስታስብ ኤልቲቪ የተባለ ጣቢያ ሊከፈት ዝግጅት ላይ በመሆኑ ስለአላማው ለባለሙያዎች ለማስተዋወቅ የተዘጋጀው መርሃግብር ላይ ተጋበዘች፡፡ በመቀጠል ”እንሂድ ከመቲ ጋር” የሚለውን የጉዞ ፕሮግራም ማዘጋጀት ጀመረች፡፡ “እንሂድ ከመቲ ጋር” ኢትዮጵያ ያሏትን ታሪካዊ እና የተፈጥሮ መስህቦችንና የኢትዮጵያውያንን ሰፊ ባህልና ትውፊቶችን ለማስተዋውቅ ያለመ ፕሮግራም ሲሆን አቀራረቡም ኤክስፒሬንሽያል/ ልምድ ማካፈል/ የተባለው አይነት ነው፡፡ መቲ የምትጎበኛቸው አካባቢዎች ላይ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ተመሳስላ በመኖርና የነሱን ባህል በመከተል፣ ድፍረት የሚጠይቁ ድርጊቶች ላይ በመሳተፍ፣ እንዲሁም መረጃዎችን በመስጠት ተመልካቾቿ ጉዞን የህይወታቸው አካል እንዲያደርጉ ማበረታታት ነው፡፡
ከኤልቲቪ በኋላ መቲ ኩዊንደም ሚዲያ የተባለ የሚዲያ ፕሮዳክሽን ድርጅት ከፈተች፡፡ ኩዊንደም ሚዲያ 360 ግራውንድ ከሚባል የቴክኖሎጂ ተቋም ጋር በጋራ “ሜዳ ሺ” የተባለ በቀጥታ ሥርጭት የሚተላለፍና ጥያቄዎችን ሜዳ ቻት በሚባል መተግበሪያ የሚመልሱበት የጨዋታ ፕሮግራም በሰኔ 2011 ዓ/ም በፋና ቴሌቭዥን ላይ አስተዋወቀ፡፡ መቲም የሜዳ ሺ አዘጋጅና አቅራቢ ሆነች፡፡
ከሚዲያ ውጪ ስራ
ኢቲቪ እየሰራች የመጀመሪያ የሙሉ ጊዜ ስራዋ ሸራተን ሆቴል የሚገኘው የቡክ ወርልድ ቅርንጫፍ ነበር፡፡ በስኩል ኦፍ ቱሞሮና በከበደ ሚካኤል አካዳሚ ህፃናትን አስተምራለች፡፡ በተለያዩ ሀገር በቀልና አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ እንዲሁም በግል ድርጅቶች ውስጥ በኮምዩኒኬሽንና ሚዲያ ግንኙነት ባለሙያነት አገልግላለች፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ ህፃናት አድን ድርጅት (Save The Children USA)፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት፣ The US Government Center for Disease Control in Ethiopia ፣ የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ሴክሬታርያት፣ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት (UNHCR) የኢትዮጵያ ቢሮ, UNESCO እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
መድረክ
የመድረክ ስራዎችን የጀመረችው ሴቭ ዘ ችልድረን በነበረችበት ወቅት ነበር፡፡ በድርጅቱ የሚዘጋጁ ትልልቅ ሁነቶችን እንድታስተባብርና እንድትመራ አለቃዋ ትገፋፋት ነበር፡፡ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንድትሰጥ በሮች እንደተከፈተላት እና በሚዘጋጁት ሁነቶችን በመምራት ከመድረክ ጋር የመላመድ እድሉን አገኘች፡፡ መቲ በሴቭ ዘ ችልድረን ቆይታዋ የሙያ እናቷንና ሜንተሯን ወርቅነሽ መኮንን እንዳገኘች እና ከእርሷ ብዙ እንደተማረች፣ አመራርንና ጠንካራ የስራ ባህልን ከአለቃዋ እንደወረሰች ትናገራለች፡፡
ንባብና መፅሃፍት
መቲ ከልጆች ወደ አዋቂ ንባብ የተሸጋገረችው 5ኛ ክፍል ሆና “ወይ አዲስ አበባ” በተሰኘው የአውግቸው ተረፈ መፅሀፍ ነበር፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ሳትጨርስ ክመቶ በላይ ልብወለድ መፅሃፍትን ማንበቧን መዝግባለች፡፡ በዚህም የተነሳ ከልጅነቷ ጀምሮ መፅሀፍ መፃፍና ማሳተም ትመኝ ስለነበር 25 አመት ሳይሞላት የመጀመሪያ መፅሃፏን ለማሳተም ወሰነች፡፡ ባሰበችው መሰረት ከ25ኛ አመት ልደቷ በፊት 25 የእንግሊዝኛ ግጥሞችን የያዘች መድብል The Gateway በጥር 1996 ዓ/ም አሳተመች፡፡
ሰርቫይቨር አፍሪካ ኢን ፓናማ
በዲኤስቲቪ የኤምኔት ጣቢያ ላይ የቀረበው ሰርቫይቨር አፍሪካ የተሰኘው ፓን አፍሪካዊ የቴሌቪዥን ሪያሊቲ ሾው ላይ የኛዋ መቲ በፈረንጆቹ 2006 ዓ/ም ኢትዮጵያን የወከለች ብቸኛዋ ሴት ሆናለች፡፡ ሰርቫይቨር ሰዎች የተለያዩ የአካላዊና አዕምሯዊ ፈተናዎችን ተቋቁመው እንዴት እንደሚያልፉ የሚያሳይ የቲቪ ፕሮግራም ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሪያሊቲ ሾው መቲ የፓናማ ደሴቶች ላይ ለ21 ቀናት ከባድ የሆኑ ፈተናዎችን ተቋቁማ ከ12 ተወዳዳሪዎች መካክል አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡
ኪሊማንጃሮ
ተራራ መውጣት፣ ረጅም የእግር ጉዞ፣ ዋናና ኤሮቢክስ ስፖርት የምትወደው መቲ በ31 አመቷ ራስ ዳሽንን በወጣች ጊዜ 40 አመት ሳይሞላኝ ኪሊማንጃሮን እወጣለሁ ብላ ለራሷ ቃል ገባች፡፡ ከወራት አካላዊ ዝግጅት በኋላ 40ኛ የልደት በአሏን ከማክበሯ ጥቂት ሳምንታት በፊት በአፍሪካ ትልቁ የሆነውን ኪሊማንጃሮ ተራራ ጫፍ ኡሁሩ ላይ በመድረስ በድል ተወጥታዋለች፡፡ ኪሊማንጃሮን መውጣት እንዴት እንደነበር ስትጠየቅ “ከልጅ መውለድ ምጥ አይተናነስም” ትላለች፡፡
የህይወት ቁም ነገር እና ፍልስፍና
መቲ ሸዋዬ ይልማ “ለኔ ወላጆቼ መሰረቴ፣ ምሰሶዬ፣ ካስማዬና ጣራዬ ናቸው” ትላለች፡፡ መልካም ነገሮቿ ሁሉ የቤተሰቧ፣ ጥፋቶቿ ደሞ የራሷ እንደሆኑ መቲ ትናገራለች፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ወላጆቿን ያለ አድልኦ ስለምትወዳቸው ስሟ ላይ የእናቷ ስም አለመኖሩ ይቆጫት ነበር፡፡ ታዲያ በ1993 ዓ/ም ጋዜጣ ላይ በምትፅፍበት ወቅት “የእናቴ ስም በኔና በአባቴ ስም መሀል ይግባ” ብላ ጠየቀች፡፡ ስሟ መርዘሙ ያሳሰባቸው ኤዲተሮች አይሆንም ብለው ቢከራከሩም በመጨረሻ መታሰቢያ የሚለው ስም ለመዝገብ ብቻ ቀርቶ “መቲ ሸዋዬ ይልማ” በሚለው ተስማምተው ሁላችንም በዚሁ ልናውቃት ችለናል፡፡
መቲ የአንዲት ሴት ልጅ እናት ነች፡፡
መቲ እራሷን የምትጠራው የህይወት ዘመን የህይወት ተማሪ ብላ ነው (Lifetime Student of Life) ለመቲ አንድ የሚደረስበትና በቃ የሚባልበት ስኬት ብሎ ነገር የለም፡፡ በየጊዜው ትንንሽ ስኬቶች ቢኖሩንም ለቀጣዩ መሰረት ነው የሚሆኑት ትላለች፡፡ የህይወትን ጉዞ ፎቅ እንደመገንባት ነው የምትመለከተው፡፡ ለሷ የዛሬ ጣሪያዋ የነገ ወለሏ ነው፡፡ መቃብሬ ነው የመጨረሻ ጣሪያዬ ብላ ታስባለች፡፡
በዚህ ጉዞዋ ውስጥ ታዲያ ህይወት የምትሰጣትን እድሎች በፀጋ ተቀብላ፣ የምትወስዳቸውን እርምጃዎች አስባበት በምልዓት ለመኖር ትተጋለች፡፡ መቲ ጠያቂ ናት፡፡ ማወቅ የምትፈልገው ነገር ካለ ያለ አንዳች ፍርሀት ትጠይቃለች፡፡ በዛው ልክ ታዳምጣለች፡፡ ለመግባባት ቁልፉ ማደመጥና እንደሌላው ሰው ሆኖ ሁኔታውን ለመገንዘብ መሞከር ነው ብላ ታምናለች፡፡