መምህር መሠረት አበጀ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡

ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ፡የሥነ ፅሁፍ  መምህር  መሠረት  አበጀ አንዱ ነው። መምህሩ በ ብዙ ተማሪዎች የሚወደድና የሚከበር ሲሆን በተለይ  ለሥነ ፅሁፍ  ባለው ጥልቅ  ፍቅር ይታወቃል ።  መምህር መሠረት ላለፉት  36 ዓመታት አዲስ አበባ  ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በልዩ ልዩ የዕውቀት  ማዕከላት ያስተማረ ሲሆን የህይወት ታሪኩንምእንድንሰንደው ስለፈቀደ  እናመሠግናለን። ቤርሳቤህ  ጌቴ ታሪኩን እንደሚከተለው ሰንዳዋለች።

ትውልድ እና ልጅነት

ጎጃሜ መባል ልቡን ትርር ያሰኘዋል። ታድያ ከንቱ ስሜት ተጠናውቶት አይምሰላችሁ። የበቀለበት፣ መገኛው፣ በጫካው ተሽሎክሉኮ፣ በሜዳው ቦርቆ፣ ሰፈር ጭቃ አቡክቶ፣ በወንዙ ዋኝቶ፣ አጋም፣ እንጆርይ፣ እንኮዩን በልቶ  ያደገበት ነውና እሚናፍቅውን የዛፍ ቅጠሉን ጠረን፣ የልካምድሩን ትዝታ ስለሚያስታውሰው እንጅ። ትውልድና እድገቱ ጎጃም፣ ቆላ-ደጋ-ዳሞት አውራጃ፣ ፍኖተሰላም  ነው። ጎጃምን “ምድረ-ገነት ነውኮ! ሰው፣ መሬቱ፣ ደኑ፣ እርሻው፣ ቡቃያው፣ የንፋሱ ሽውታ… ተልብ እማይጠፋ ውብ አገር ነው” ሲል ያሞካሸዋል፡፡ 

መሰረት አበጀ ኑሮውን አዲስ አበባ ካደረገበት ግዜ አንስቶ የከተሜነት ሂወት ሲያታክተውና ረፍት ሲያሳጣው፣ ፋታ ሲያምረው የሚመርጠው ያችኑ የልጅነቱን ስፍራ ነው። ምንም እንኩዋን የልጅነት አይምሮው ውስጥ ያለችውን ቦታ ያገኛታል ማለት ባይሆንም፣ በዘመን ለውጥ ውስጥ እንዳለችም ቢሆን፣ በሚናፍቀው ቀየ ውስጥ ተዘመድ ጎረቤቱ ተቀላቅሎ ማውጋት ተንፈስ ያረገዋል እና ይነቃቃል፡፡ 

የስነ ፅሁፍ  ዝንባሌ 

መሰረት እና ስነጽሁፍን ያስተሳሰረው ያው መገኛው ነው ማለት ይቻላል። ጎጃምን የተረት፣ የግጥም፣ የዜማ አውድማ አርጎ ይስለዋል። በለሊት ተነስተው ወደጎቻ እሚገሰግሱ እንጨት ለቃሚወች “ሆርዬ‘ርዬ ሆርየው መላ…” እሚለውን እንጉርጉሮ አይነት ዜማ እያወረዱ በደጁ ሲተምሙ፣ እረኛው፣ ገበሬው “ሆይ በሬ ሆይ…” ሲል፣ ሰፈርም በስራ የተጠመዱ ሁሉ፣ ሲቆሉ፣ ሲፈጩ እሚያቀነቅኑትን ዜማ ፣ እሚተርቱትን ሲሰማ አድጓል፡፡ የቅኔ እና ስነቃል ምንጭ በሆነ ህብረተሰብ መሀል አድጎ ወትሮስ ስነጽሁፍ እንዴት ሊርቀው ይችላል? 

እድሜው ለትምህርት ደርሶ ፊደል ከቆጠረ በሁዋላ፣ ንባብ ለመለማመድና ለመውደድም መሰረት የሆኑለት በሱ ዘመን ለመጀመሪያ ደረጃ ተማሪወች እንዲያገለግሉ በጥንቃቄ የተሰናዱት መፃህፍት -ለማ በገበያ፣ አረንጓዴው ጓደኛየ፣ ተረቶቻችሁ፣ የእንስሳት አገልግሎት፣ ተንኮለኛው ከበደ፣ ሶስተኛው የንባብ መፅሀፌ፣ ታሪክና ምሳሌ… ነበሩ፡፡ ተክፍል ክፍል ሲራመድም፣ መምህራን ግጥም ሸምድደው በክፍል ልጆቻቸው ፊት እንዲያነበንቡ፣ በተመረጡ ርእሶች ላይ ክርክር እንዲያካሂዱ የውድድር መንፈስ የሚቀሰቅስ አውድ ይፈጥሩላቸው ነበር። ከዚህ አልፎም ፍቅር እስከ መቃብርንና መሰል ረዥም ልብወለድ ድርሰቶችን እያነበቡ እንዲወያዩ እድል እየተፈጠረላቸው  ተኮትኩተዋልና እኒህ እድሎች ታደገበት አውድ ጋር ተደማምረው ስነጽሁፍና መሰረት ለመወዳጀታቸው ብርቱ መሰረት ጥለውለታል፡፡

በመሰረቱ መሰረት የ2ኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ፣ የሳይንስ ተማሪ ነበረና በዚሁ እንደሚገፋ ነበር የሚያስበው። ባዮሎጂ እና ኬሚትሪ የሚወዳቸው የትምህርት አይነቶች ነበሩ። በተለይ ባዮሎጂ ያስደስተው ነበር! አስራአንደኛና አስራሁለተኛ ሳለ የባዮሎጅ ችሎታውን ለክፍሉ ተማሪወች ለማሳየት፣ ሳይጠይቁትንኩዋ ስእሎችን እየሳለ ያስረዳ እንዳልነበር፣ የማትሪክ ውጤቱ ሲ ሁኖ ቁጭ አለ። ምርጫ አርጎ ሊያጠናው በሚመኘው ትምርት ሲ ማግኘቱ ‘ምናባቱ!’ አሰኘው። ፊቱን ከሳይንስ አዞረ። እንኳንም አዞረ! ወደሌላው ዝንባሌው ወደአርት ይቀላቀል ዘንድ ጥሩ ሰበብ ሆነለታ!

 ዩኒቨርሲቲ እና የማስተማር  ፍቅር 

እናም በ1975 ዩኒቨርስቲ ሲመደብ፣ ውሳኔው ትያትር መማር ነበር። ሆኖም የተመደበበት አስመራ ዩኒቨርሲቲ  የትያትር ትምህርት ክፍል አልነበረውምና ለትያትር የቀረበ ትምህርትና የስራ መስክ  ‘ስነፅሁፍና መምህርነት ናቸው’ ብሎ፣ ይህንኑ አጥንቶ መምህር ሆኖ ወጣ፡፡

መሰረት ለመምህርነት የተፈጠረ ይመስለዋል። ለሙያው ፍቅር አለው፤ ወዶት የተሰማራበት ስራ በመሆኑም ሲያስተምር ፍቅሩን ያጋባል፡፡ “መምህርነት ትወና፣ ክፍል መድረክ ነው፣ ተማሪወች ደሞ ተሳታፊም ታዳሚም ናቸው” ይላል። የደስታው ምንጭ ተማሪወቹን ማስደመም ነው። “ትምርት አዲስ ነገር የማወቅ/የመረዳት ሂደት ስለሆነ ያስደስታል፤ የኔም ግብ ተማሪወችን ማስደሰት ነው” በሚል መርህ ክፍሉን ሂወት ስለሚነዛበት፣ ክፍለ-ግዜው ሁሌም አጥሮ ነው ሚቀር። በቅጡ ይዘጋጃል። “ይህን የማረገው ግዴታየ ስለሆነ ብቻ አደለም፣ ለራሴ ደስታ ስለሚሰጠኝ ነው። ተማሪወቸን ባግባቡ ለመቃኘትና ለማስደነቅ ማንበብ፣ ዘመን ያፈራቸው ስልቶችን ማወቅና ትኩረታቸውን በሚገዛ አቀራረብ ማጋራት ያሻል። መምህርነት ቢቻል አራያ መሆኛንጅ ለደመወዝ የሚገቡበት የስራ መስክ አደለም። ብርቅ ሙያ ነው!” ሲል ይገልፀዋል። በሌላ መስክ መሰማራት አስቦ አያውቅም። 

ትዳር እና ቤተሰብ 

ትዳር የመያዝ መሻት አልነበረውም ምክንያቱም ወላጅ እናቱ እሱንና እህቶቹን በብዙ ድካም አሳድገው፣ ሊደግፉዋቸው ሲደርሱ ግን በሞት ስለተለዩዋቸው፣ ‘ያ ሁሉ መስዋእትነት ለዚሁ ነው? ሂወት ትንሽ ፋታና ተልጆች ጋር ጨዋታ እንዴት ይነፍጋል?’ አሰኝቶትና ሲለፉ ኑሮ ማለፍ ብቻ ሁኖ ታይቶት፣ ከዚ በላይም ተናቱ ያስተዋለውን ‘ሁሉንም ለልጆቸ’ እያሉ መቀነትን አጥብቆ፣ አላፊነትን ተሸክሞ፣ ፈተናው ለመጋፈጥ የናቴ ጥኑ መንፈስ የለኝም። ስለዚህ ቤተሰብ ብሎ ሀሳብ ቅም አይለውም ነበር። ነገር ግን ቆይቶ፣ ተልጅነቱ አንስቶ ይወዳት የነበረችቱንና አብራው የተማረችቱን ተናኘን አ.አ ታገኛት በሁዋላ ስሜቱ ለዘበ… ያም ሁኖ ለጋብቻ ዘግይተዋል። ትዳር የመሰረቱ የፍቅር ግንኙነታቸው አስራሁለተኛ አመቱን ሲይዝ ነው። ዛሬ ወልደው ከብደው ይኖራሉ። ለጉዋኞቹ ሁሉ ቅርብ ጉዋደኛ የሆነችለት፣ እነሱም በጣም የሚወዱዋት አጋሩ ናት፡፡ 

አንቲገን ውስጥ ንጉሱ “ንጉስነት እንጀራየ ነው” እንደሚለው፣ “ማንበብ እንጀራየ፣ ሙያየ ደስታየም ነው” እሚለው መሰረት፣ ባለቤቱን ተናኘን “ሳንሱር ክፍሌ ናት” ይላታል። የሚገዛቸውን መፃህፍት አስቀድሞ የሚሰጣት ለሱዋ ነው። አንብባ አስተያየት አክላ፣ “ይሄ ምርጥ ነው፣ ይኸኛው ምንም አይል፣ ይሄ… እንጃ” እያለች ቅድሚያ ማግኘት ያለባቸውን ተራ በማስያዝ ዋና ሚና ትጫወታለች።

የሚያደንቃቸው ደራሲዎች

ድርሰቶቻቸውን የሚያደንቅላቸው ብዙ ፀሀፊወች ቢኖሩም፣ ቆየት ካሉት ውስጥ ለሀዲስ አለማየሁን፣ በአሉ፣ ስብሀት፣ ገብረክርስቶስ ያለው አመለካከት ፈጽሞ ይለያል። ሀዲስና በአሉ ለሀገር ግስጋሴ ትምርት፣ ሰላም፣ ልዩነት ሲከሰትም የሰከነ ንግግርና እርቅ ለሁላችንም የሚበጅ መፍትሄ መሆኑን በመንግስት አካላት፣ በፖለቲከኞችና በህዝቡም ልቦና እንዲሰርፅ፣ በፅሁፎቻቸው ደጋግመው የጮሁ፣ ባለራእይ ደራስያን መሆናቸውን ከልቡ ያምናል። “ዳሩ የኢትዮጵያ ደራስያን አድማጭ ቀርቶ ሰሚ የላቸውም” ሲልም ያማርራል። 

ስነፅሁፍ በሀገራችን ያለውን እድገት በተመለከተ ስንጠይቀውም “ስነፅሁፍ አላደገም ማለት አይቻልም ምክንያቱም በየዘመኑ በርካታ ጎበዝ ወጣት ደራሲያን ፈርተዋል፣ አሁንም አሉ። ነገር ግን አንድ ደራሲ ምንም አይነት የኑሮ ጫና ሳያሳስበው እንዲጽፍ የደራሲያን አምባ ከፍቶ ሀሳባቸውን ያለገደብ እንዲያፈሱ እድል ሳይፈጠርላቸው ወደደራሲ ጣት መቀሰር አይገባም! የታተሙት መች በቅጡ ተነበቡና ነው?! ርግጥ ያሳተመ ሁሉ ደራሲ ሊባል አይችልም። ጥራዝ እንጅ ሌላ ሊባሉ እማይበቁ ህትመቶች ገበያውን እየሞሉት ነው። 

የፀሀፊነት መሰረቱ ጥሩ አንባቢነት ነው። የተረክ ችሎታ፣ ገጠመኝን የመተንተንና የማደራጀት፣ በማራኪ ቁዋንቁዋ የመግለፅ ክህሎት ተየትም አይመጣም – ተብዙ ንባብ አልያም ተአትኩሮ አድማጭነት ብቻ!! አሁን ተሆነ ግን አይምሮን በንባብ ሳያጠግቡ፣ ምናልባትም ምንም ሳያነቡ መቸክቸክ ነውር መሆኑ እየቀረ ይመስላል። ሁሉም አቁዋራጭ አሳዳጅ ሆነ። ብቻ ይሄ ብልጣብልጥነት ላይሞሮ ስራ አያግዝም፤ እንዲያውም አይወድቁ አወዳደቅ ያስወድቃል! ስልቱ የግዜው ብሂል ቢሆንም፣ ዋናው ችግር ተትምህርት ቤቶቻችን፣ ተመምህራን፣ ተወላጆች ራስ አይወርድም! 

ለልደት ቀን ስጦታ መፅሀፍ ጨርሶ ትዝ እማይላቸው፣ ኬክ በማጉረፍ ውድድር የሚጠመዱ ቤተሰቦችና ቤተዘመዶች ታመት አመት እየተባዙ ነው። ያውም ለተኮረጀ ልማድ! ምራባውያኑ በኛ በከተሜ ተብየወች ልደት አከባበር ግዝፈት ሲደነቁ ማየት ሊያሳፍር ይገባል!! ከበርቻቻ ልጆቻችንን ቢያመክንንጅ ሌላ ውለታ የለውም። ልደት ትምርት ቤት ውስጥም ይከበራል። ታይታ ነግሶብን! እንዲህ እያረግን ስለስነፅሁፍና ትውልድ እድገትም ሆነ የወደፊት እጣ ማውራት ይችግራል!!

One thought on “መምህር መሠረት አበጀ

  1. መምህር መሠረት አበጀ ጎበዝ አስተዋይ ጥበበኛ ነዉ እረጅም እድሜ ተመኘሁለት!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *