መላኩ ብርሃኑ ተስፋዬ

መላኩ ብርሃኑ ተስፋዬ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያው መላኩ ብርሃኑ ከ20 ዓመታት በላይ በብሮድካስትና ህትመት ሚዲያ ላይ የሰራ ጋዜጠኛ ነው። ከፖሊስ ራዲዮና ቴሌቪዠን እስከ አርትስ ቲቪ ፣ ከዕለታዊ አዲስ ጋዜጣ እስከ አዲስ-ጉዳይ መጽሔት ባሉ ከ11 ያላነሱ የግልና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ላይ በተለያዩ የጋዜጠኝነትና  የሀላፊነት እርከኖች አገልግሏል።

ጥንስስ 

የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ‹‹ኦሎምፒያ›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በትንሳዔ ብርሃን እና በቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተከታተለው መላኩ ብርሃኑ ከልጅነት ጀምሮ ላዘነበለበት የስነ-ጽሁፍ ፍቅር የተሸነፈው በጊዜ ነው።

ከእድሜው ብስለት በላይ የሆኑትን የዘመኑን ታላላቅ የልብወለድ መጽሃፍት ማንበብ የጀመረው የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለ ነው። ይህ ከፍ ያለ የንባብ ፍቅርና ከዚህ ጋር ተያይዞ እየዳበረ የመጣ  የስነጽሁፍ ችሎታ ጋዜጠኝነትን ራዕዩ አድርጎ እንዲያድግ ምክንያት ሆኖታል። የትምህርት ቤቶቹ ሚኒ ሚዲያዎች ጋዜጠኝነትን ሀ ብሎ የጀመረባቸው ስፍራዎች ነበሩ።የጋዜጠኝነት አለምመላኩ በመደበኛ ሚዲያ ላይ መስራት የጀመረው ከትምህርት ቤት እንደወጣ ለፖሊስና ርምጃው ጋዜጣ እንዲሁም ለፖሊስና ህብረተሰብ የራዲዮና ቴሌቪዠን ፕሮግራሞች በወንጀል ዘገባ ዘርፍ  የአዲስ አበባ ሪፖርተር በመሆን ነው ። በመቀጠልም ከህዝብ ጋር በሰፊው ያስተዋወቀውን “አዲስ ፖሊስ” የተሰኘ የቴሌቪዠን ፕሮግራም በመጀመር ከባልደረቦቹ ጋር በቀድሞው ኢቲቪ 2፣ በዛሬው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ላይ በሳምንት ሁለት ቀን እያዘጋጀ ማቅረብ ጀመረ።

መላኩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እስኪቀላቀል ድረስ በፖሊስ መገናኛ ብዙሃን ላይ እስከዋና አዘጋጅነት በደረሰ እርከን ዘለግ ላለ ጊዜ አገልግሏል።

ሙያን በትምህርት መደገፍ

መላኩ ከፖሊስ ኮሌጅ የጋዜጠኝነትና ህዝብ ግንኙነት ኮርስ ፣ እንዲሁም ከበርካታ አጭርና ረጅም የሙያው ስልጠናዎች ባሻገር ጋዜጠኝነትን በኮሌጅ ፕሮግራም ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከታተለው በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ነው። ዩኒቲ በሃገሪቱ የመጀመሪያ የነበረውን School of Journalism and Communications ከፍቶ ጋዜጠኝነትን በዲፕሎማ መርሃግብር መስጠት ሲጀምር ተማሪ ከነበሩ በርካታ የዛሬ ታዋቂ ጋዜጠኞች መካከል መላኩ አንዱ ነበር።

በ1997 ዓ.ም የ3 ዓመቱን የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ቆይታ በማዕረግ ተመራቂነት አጠናቀቀ።መላኩ የዚያን ጊዜውን የዩኒቲ የትምህርት ዘመን “የህይወት ዘመኔ የሙያ መሰረት” ብሎ ይጠራዋል። በከፍተኛ ጥንቃቄ በተቀረጸ ካሪኩለም ፣ ከአሜሪካ በሚመጡ ተጋባዠ ሌክቸረሮች እና በታዋቂ የሙያው አንጋፋ ሰዎች ይሰጥ የነበረው ትምህርት ለመላኩ የሙያ ህይወት ትልቅ ግብዓት ሆኗል።

መላኩ ዩኒቲን የተሰናበተበት 1997 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ከፍቶ ጋዜጠኝነትን በዲግሪ ፕሮግራም መስጠት የጀመረበት ጊዜ ነበር። ጊዜ ሳያጠፋ ወደዚያው በማቅናት  በብሮድካስት ጆርናሊዝም ዘርፍ በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። የመጀመሪያ ዲግሪውን ከሰራ በኋላ ከአንድ አመት በላይ ከትምህርት ርቆ መቆየት አልቻለም። ቀጣዩ የትምህርት ጉዞው “ሲኪም ማኒፓል ዪኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክኖሎጂካል ሳይንስስ” ከተባለ የህንድ ዩኒቨርሲቲ ጋር አገናኘው። በዚያም ጆርናሊዝም እና ማስ ኮሙኒኬሽንን ሜጀር አድርጎ በኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ልዩ ሙያ (specialization) የማስተርስ ኦፍ አርትስ ዲግሪውን ተቀብሏል።

መላኩ ከኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ መደበኛ ትምህርቶቹ ባሻገር ከጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽንስ ጋር የተያያዙ ከ25 የሚበልጡ አጫጭርና ረጃጅም የሰርተፍኬት ፕሮግራም ስልጠናዎችን በውጭ ሃገራትና በሃገር ውስጥ ተከታትሎ አጠናቋል ።

መላኩና መገናኛ ብዙሃን

ከጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽንስ ውጪ ምንም ሰርቼ አላውቅም የሚለው መላኩ የእድሜውን እኩሌታ ለሚልቁ አመታት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ላይ አገልግሏል።

በፖሊስ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ከሪፖርተርነት እስከዋና አዘጋጅነት በደረሱ መደቦች ላይ ፣ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ እና በ ‘ኢቲቪ-2’ ላይ በአምድ ጽሁፍ አዘጋጅነትና እና በወንጀል ዘገባዎች አቅራቢነት ለዘጠን አመታት አገልግሏል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ከተቀላቀለ በኋላም በዜና አገልግሎቱ ከዜና ኤዲተርነት እስከ ፕሮግራም ፕሮዳክሽን ሃላፊነት በደረሱ የጋዜጠኝነት ሙያ መደቦች ላይ ለሰባት አመታት ያህል ሰርቷል። 

“የጋዜጠኝነት ህይወቴን ሳስብ እኔን ጨምሮ በርካቶችን ላፈራው ኢዜአ ልዩ ከበሬታ እና ከፍ ያለ ፍቅር አለኝ” ይላል መላኩ።መላኩ በመደበኛነት ተቀጥሮ ይሰራባቸው ከነበሩት ሚዲያዎች ባሻገር በፍሪላንስ በርካታ ጋዜጦች ላይ ሰርቷል። ጦማር ፣ ዘ ፕሬስ እና ዕለታዊ አዲስ፣ ሮዝ እና አዲስ ጉዳይ የተሰኙት የያኔው ዘመን ታዋቂ ጋዜጦችና መጽሄቶች መላኩ ከአምደኝነት እስከ ማኔጂንግ ኤዲተርነት የሰራባቸው የነጻው ፕሬስ ውጤቶች ናቸው።

መላኩ በነዚህ የህትመት ውጤቶች ላይ በብዕር ስም ይጽፋቸው የነበሩ በማህበራዊና የወንጀል ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አርቲክሎች   በርካታ አንባቢዎችን አፍርቷል። የሸዋጌጥ ተካልኝ፣ መላከብርሃን ተስፋይ ፣ በመጨረሻም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ “ኮከብ አሳየ” የሚሉት የብዕር ስሞች የመላኩ ጽሁፎች ሲጻፉባቸው የኖሩ የብዕር ስሞች ነበሩ።

ታላቁ የሙያ አበርክቶ-  “አዲስ -ጉዳይ”

መላኩ “በህይወቴ ትልቅ ቦታ የምሰጠው የሙያ አበርክቶዬ የአዲስ ጉዳይ መጽሄት ቆይታዬ ነው” ይላል።

“አዲስ ጉዳይ” በኢትዮጵያ የህትመት ሚዲያ ኢንደስትሪ ታሪክ የራሱ ቀለም መፍጠር የቻለ፣ የተቀናጀ የባለሙያ ስብጥር እና ድርጅታዊ መዋቅር ላይ የተመሰረተ፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሙሉ ቀለም በየሳምንቱ ታትሞ ለንባብ በመብቃት ቀዳሚ የሆነ እና ከፍተኛ አንባቢ የነበረው መጽሄት ነበር። በጊዜው ከነበረው አስተዳደር ጋር ሙያዊ ነጻነቱን ብቻ መከታ አድርጎ ፊት ለፊት በመጋፈጥ ከሚዲያ የሚጠበቀውን ለህዝብ እና ለእውነት ብቻ የመቆም የሞራል ልዕልና በተግባር ያሳየ ፣ በዚህም የፈጠረው ከፍ ያለ ተጽዕኖ በመንግስት ያልተወደደለት እና በመጨረሻም በአሳታሚ ድርጅቱ ላይ ፍትህ ሚኒስቴር ክስ እንዲመሰርትበት ተደርጎ ከህትመት የወጣ የዘመኑ ምርጥ የሚዲያ ውጤት ነበር።

መላኩ በዚህ መጽሄት ላይ ከምስረታው እስከ ተዘጋበት ጊዜ ድረስ በማኔጂንግ ኤዲተርነት አገልግሏል።  መላኩ የዚህ መጽሄት አሳታሚ የነበረውን ባልደረባውን እንዳልካቸው ተስፋዬን “ያልተነገረለት የኢትዮጵያ የግል ፕሬስ መሃንዲስ” ይለዋል ። ዘመኑን ከህትመት ሚዲያ ውጤቶች ጋር ያሳለፈውና  በይዘት ፈጠራና ቅርጽ ማስያዝ ተጠቃሽ ስም ያለው እንዳልካቸው አዲስ ጉዳይ መጽሄትን ማሳተም ሲጀምር ነው መላኩ ቋሚ ስራውን ለቅቆ ሙሉ ጊዜውን ይህንን መጽሄት በመምራት ላይ ያደረገው።

መላኩ አዲስ ጉዳይን ተወዳጅ ካደረጉት ፣ የበሰለ የጋዜጠኝነት እውቀት ካላቸውና ለውጥ ማምጣት ከቻሉ ጽሁፎቻቸው ጋር አሁን ድረስ ከሚጠቀሱት ጋዜጠኞችና ጸሃፊያን ጋር በጋራ የሰራባቸውን አመታት ‘በጋዜጠኝነት ሙያዬ በፍጹም ነጻነትና ለእውነት ብቻ በመቆም ለሃገሬና ለህዝብ የድርሻዬን ተወጣሁ ከምልባቸው ጊዜዎች ሁሉ ጊዜ ነበር ” በማለት ይገልጸዋል። የዚህ መጽሄት የሽፋን ታሪክ (Cover story) የሚጻፍበትንና በዋናነት የፖለቲካ ጉዳዮች የሚስተናገዱበትን “ዐቢይ ጉዳይ” አምድ ኤዲት ከማድረግ እና ከመጻፍ ጀምሮ የመላኩድርሻ የላቀ ነው።

የታፈኑ እውነቶች፣ ፍቅርና ወንጀል፣ ቢዝነስቴይመንት፣ ትዳር እና ፍቅር፣ ማንን እንማ እና ሌሎችም አምዶች ሁሉ መላኩ በባለቤትነት የሚሰራቸው ነበሩ። ለአራት ዓመታት ሳይቋረጥ ከ100 በላይ እትሞችን ለንባብ ያበቃው አዲስ ጉዳይ መጽሄት በመንግስት ተጽዕኖና ክስ ሳቢያ በ 2007 ዓ.ም መጨረሻ ከህትመት ሲወጣና “የኔ የምንጊዜም የኔ ምርጥ ሰው ” የሚለውን የመጽሄቱ አሳታሚ እንዳልካቸው ተስፋዬን ጨምሮ ሁሉም አባላቶቹ ለስደት ሲዳረጉ “ያኔ በሃገሬ የፕሬስ ነጻነት ተስፋ ቆረጥኩ” ይላል መላኩ።

ባልደረቦቹ ሲሰደዱ ለስራ ጉዳይ ውጭ ሃገር የነበረው መላኩ ሲመለስ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ። “ከጋዜጠኝነት እረፍት ወስጄ ፊቴን ወደኮሚዩኒኬሽን ስራዎች አዞርኩ፣ ለጥቂት ዓመታት ሚዲያ ላይ በመደበኛነት መስራትም አቆምኩ፣ ሙሉ በሙሉ መተው ግን ከበደኝ” ይላል። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ግዮን በተባለ መጽሄት ላይ በፍሪላንስ ለመጽሄቱ የሽፋን ታሪክ የሚሆኑ የፖለቲካ ትንታኔዎችን መጻፍ ጀመረ።  መላኩ ስለአዲስ ጉዳይ ባልደረቦቹ ሲናገር “በጋዜጠኝነትም ፣ በቋሚ አምደኝነትም፣ በደጋፊ የስራ መደቦችም አዲስ ጉዳይን ያገለገሉ ሁሉ ዛሬ ባይነገርላቸውም ቅሉ አንድ ቀን ግን የሚዲያ ታሪክ የሚዘክርላቸው አበርክቶዎቻቸውን ትተው አልፈዋል” ይላል ።

ለቅቆ የማይለቅ የሙያ ፍቅር

መላኩ በዘመኑ በፕሬስ ላይ በነበረው ጫና እና ምቹ ያልሆነ ከባቢ ሳቢያ ጋዜጠኝነትን በመደበኛነት ከመስራት ለሶስት አመታት ያህል ቢርቅም ኢህአዴግ ሲፈርስና የለውጥ ጭላንጭሎች መታየት ሲጀምሩ ያንን ተከትሎ ካንሰራራው የሚዲያ ተስፋ ጋር አብሮ ብቅ አለ።

በጓደኞቹ ጉትጎታና ጥሪ  በአንድ ተቋም ሲያገለግልበት ከነበረው የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ስራ አስኪያጅነት ለቅቆ ከመስከረም 2019 ጀምሮ የአፍሪካ ሬይነሰንስ ቴሌቪዠን ሰርቪስን (አርትስ ቲቪን) በዜና ክፍል ሃላፊነት ተቀላቀለ። በዚያ የቴሌቪዠን ጣቢያ እስከ ዋና የኦፕሬሽን ሃላፊነት በደረሰ የሚዲያ መሪነት ቦታ አገልግሏል። በሄደበት ሁሉ አሻራውን ሳያሳርፍ የማይወጣው መላኩ በአርትስ ቲቪ ቆይታውም በብዙሃን ዘንድ ተወዳጅ የነበረውን “ዐቢይ ጉዳይ” የተሰኘ የቴሌቪዠን የውይይት ፕሮግራም ቀርጾ ለሶስት አመታት ያህል ሲያዘጋጅና ሲያቀርብ ቆይቷል።

“ዐቢይ ጉዳይ” ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበሩት የአዲስ ጉዳይ መጽሄት የፖለቲካ ትንተናዎች ይስተናገዱበት የነበረ ዐምድ ስም ሲሆን መላኩ ለቴሌቪዠን ፕሮግራሙ ይህንን ስም የሰጠውም በርግጥም ለውጥ ማምጣት የሚችሉ የፖለቲካ ውይይቶች እንዲካሄዱበት በማሰብ እንደነበር ይናገራል። መላኩ ‘በዐቢይ ጉዳይ’ ዝግጅቱ የሃገራችንን የፖለቲካ እና ማህበራዊ ዲስኮርስ ባህሎች ወደውይይት እና መግባባት ባህል ለማምጣት ሙያው የሚጠይቀውን ሃላፊነት በሚገባ ተወጥቶበታል። 

የመጽሐፍን ፍቅር በመጽሐፍ

በመጽሐፍ መላኩ በ2009 ዓ.ም “ፍቅርና ወንጀል” የተሰኘ አንድ መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል። የበርካታ መጽሃፍት አርትዖቶችንም ሰርቷል።ወደፊት ለማሳተም ካቀዳቸው ውስጥም የሁለት መጽሃፍት ረቂቆች በእጁ እንዳሉ ይናገራል። የሙያው ትሩፋቶች   መላኩ ከጋዜጠኝነት ሙያው ጋር በተያያዘ ለዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች፣ ስልጠናዎችና ጥናታዊ ጉብኝቶች 11 ወደሚጠጉ የአፍሪካ፣የአውሮፓ፣ የመካከለኛውና የሩቅ ምስራቅ ሃገራት ተጉዟል።

ቤተሰብና ህይወት

መላኩ ባለትዳርና የልጆች አባት ነው። ከወይዘሮ ሊዲያ ተስፋዬ ጋር በ 2001ዓ.ም ትዳር መስርቶ ሰንፔር መላኩ (ናኒ) ፣ ሚካኤል መላኩ እና አሜን መላኩ የተባሉ ሶስት ልጆችን አፍርቷል። ዛሬም ከሙያዬ አልራቅኩም የሚለው መላኩ “እግዚአብሄር ቢያድለኝ ቀሪው ዘመኔ በኮሚዩኒኬሽን ሙያ ለውጥ ለማምጣት የምተጋበት፣ በጋዜጠኝነት ሙያም በመምህርነት ትውልድ የምቀርጽበት ዘመን ይሆናል” ይላል ።

መላኩን ብዙዎች ለእናቱ ባለው ፍቅር ያውቁታል።  ቀጥሎ ያለው ጽሁፍ መላኩ “የህይወቴና የዛሬ ማንነቴ መሰረት” ለሚላቸው እናቱ የፃፈው ማስታወሻ  ነው

ይህንን ከላይ ያነበባችሁትን ታናሽ ሰው በጥርሷ አንጠልጥላ አሳድጋ ለዚህ ማንነቱ  ያበቃች ጀግና እናት ደግሞ አለች።የኋላዕሸት ገብረስላሴ ዘነበ። ጣፋጭ ስሟ በኔ አፍ ሁሌ ይክበር። ውለታዋም በቃላቶቼ ያለስስት ይመስገን !! 
እማዬ… የኔ የዘመኔ ማበቻ ካስማ። የህይወት መንገዴ  መመሪያ መጽሃፍ። የፍልስፍናዬ ውል …ስለእውነትና ሃቅ፣ ስለቀናነትና ትግል፣ ስለአሸናፊነትና አመስጋኝነት…ስለዚህ ሁሉ ላለኝ ምልከታ ሚዛኔ፣ የዝንተአለም ኗሪ ማንጸሪያዬ ነበረች። …እማዬ  አንብቤ ቀርቶ ገልጬ  የማልጨርሳት መጽሃፌ…በዘመናት ኑሮ የማይሞላ ትዝታዬ  ማከማቻ ጎተራ። ልጅነት በወጣትነት ስር አልፎ፣ ወጣትነት ወደአዋቂነት ሊሻገር እስኪሞካክር በኖርኩበት ዘመን ሁሉ ከስሯና ከጠረኗ ሳልላቀቅ ያደግኹባት አድባሬ ነበረች የኔ እናት።

መሰብሰቢያ ዋርካዬ  … ከሃሳብ ግርታ መሸሻዬ፣ ከህይወት ግርግር መጠለያዬ፣ ከቃጠሎ ማረፊያዬ፣ ከድካምና ዝለት መታደሻ ጥላዬ ነበረች እማዬ። ያቺ ጀግና …ጨረቃ በጉብዝናዋ የምትቀናባት፣ ጸሃይ በጉልበቷ የምትገረምባት…ሌሊት ተነስታ ሌሊት የምትተኛ አይታክቴ አይደክሜ እናቴ…ዛሬ ከአለች ወደነበረች ሄደች። አካሏ ከጎኔ…ደርባባ ቁመናዋ ከአይኔ ርቆ በስንዝር መሬት ተከተተ። አጠገቤ ስትሆን ትከሻዬን የምታከብድ ማዕረጌ…በሰው ፊት ቆሜ ስናገር ፊቴ ድቅን የምትል ሞገሴ !… ተሸንፋ ሄደች።

የማታምነውን የሁልጊዜ ህጻኗን …እኔን ለኔ ለብቻዬ ጥላኝ..ከራሴ ጋር ለክርክርና ድካም፣ ለዝምታና ጥሞና አስረክባኝ። “ጠንክር…ሁሌ አብሮ መኖር የለም…መደገፊያህን አብጅ” ብላ እንዴት መኖር እንደምችል ልትፈትን ጥላኝ ሄደች። ያለሷ መኖር ባዶነት መሆኑን እያወቀች…ከአይንና መንፈሴ እንደማትጠፋ እያወቀች …ግን …ሄደች። መንፈሷ  አይዞህ ይለኛል።ብርታቷ በርታ ይለኛል። ለእኔ የከፈለችው ዋጋ ለእሷ ደምቀህ ኑር ይለኛል። ህያውነቷ…አሁንም ከኔ ጋር ያለች መሆኗ በጥቂትም ቢሆን ያጽናናኛል። አትጨክንምና ዛሬም ከላይ እያየችኝ ለኔው ትባትል ይሆናል። ልሆንላት እንደምትፈልገው እየሆንኩላት እኖራለሁ።

ቃሌን ሰጥቻታለሁ። እማዬ አልሞተችም ብዬ ለራሴ ነግሬ በሌለችበት እየተጓዝኩ አለሁ። የርሷ ልጅ…የምኮራባት ልጇ ነኝ። ዘለዐዘለም በኔ ንገሺ እማ!…ስምሽ አሁንም በአፌ ሞልቷል። እወድሻለሁ ማለት ለኔ ትርጉም ያጣል። ህይወቴ ነሽ ይገልጽሽ ከሆነ…እኔን ራሴን ነሽ እማይዬ …ባለሽበት ደስ እንዲልሽ …እንደወትሮሽ ፈገግ እንድትይ…ለብቻሽም ቢሆን እንድታወጊ እመኛለሁ…ሁሌም እየሰማሁሽ ነውና …ሁሌም እያየሁሽ ነውና …አንቺ ካለሽልኝ ምንም የምፈልገው ነገር የለምና .. በውስጤ ተደላድለሽ ኑሪ። ጸሎትሽ እስከዘመኔ ዳርቻ….ምርቃትሽ ዘመኔን አልፌውም ቢሆን ሁሌም አብረውኝ ናቸው።  እጅግ መግለጽ በማይችለው ፍቅር …ልጅሽ መላ’ዬ አብዝቶ ይወድሻል ።  አልሞትሽም !!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *