ሕይወት ታደሰ

ሕይወት ታደሰ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡

በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ህይወት ታደሰ አንዷ ናት፡፡ ህይወት ከ19 አመት በፊት ህግ ብትመረቅም ነፍሷ ግን ለኪነጥበብ አደላ፡፡ ከሰሞኑ በኢቲቪ የሚታየው ግራና ቀኝ ድራማ መነሻው የሀማ ቱማ የእንግሊዝኛ ድርሰት ሲሆን ይህንን ድርሰት የዛሬ 6 አመት በ2007 በአማርኛ ተርጉማ ነበር፡፡ የግራና ቀኝ ፕሮዲዩሰሮችም መነሻ መጽሀፋቸው የህይወት የአማርኛ ትርጉም ነው፡፡ ህይወት የአዳም ረታ ስራዎችንም ወደ እንግሊዝኛ የመለሰች ሲሆን በታላቅ ርካታ ውስጥ ሆና ይህን ስራ እያከናወነች ስለመሆኑ ትናገራለች፡፡ እዝራ እጅጉ ከባለታሪኳ የተገኙ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ የህይወት ታሪኳን እንደሚከተለው ሰንዶታል፡፡

ትውልድ እና ትምህርት

ሕይወት ታደሰ ከወላጆቿ ከአቶ ታደሰ ኃይለማሪያም እና ከወ/ሮ ወጋየሁ ታደሰ፤ በባሌ ክፍለሀገር በሮቤ ከተማ በ1973 ዓም ተወለደች። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን አንደኛ እና ሁለተኛ ክፍልን በሮቤ ከተማ በሚገኘው ‘ድል በትግል’ ትምህርት ቤት ከተከታተለች በኋላ፤ በ1980 ዓ.ም ቤተሰቡ ወደ አዲስ አበባ ለመኖር መጣ። በመሆኑም ሕይወት እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ የተማረችው አዲስ አበባ በሚገኘው የሲስተርሺያን ሞናስተሪ ማሪያም ፅዮን ትምህርት ቤት ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በሠላም የሕፃናት መንደር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላ ጨርሳለች። የመጀመሪያ ዲግሪዋን በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ1996 ዓም፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ አሁንም በሕግ ከአምስተርዳም ዩኒቨርስቲ በ1999 ዓም አግኝታለች።

ህግ ትምህርት -ስነጽሁፍ

ሕይወት በትምህርት በሕግ ሙያ ብትሠለጥንም በፍላጎት ግን ወደ ሥነ-ጽሁፍ እና ኪነት ታዘነብላለች። ወላጆችዋ ሁለቱም መጻህፍትን አፍቃሪዎች በመሆናቸው በርካታ መጻህፍትን ይሰበስቡ የነበረ ከመሆኑም በላይ እናቷ ወ/ሮ ወጋየሁ በቤተሰቡ ዘንድ በገጣሚነትም ይታወቃሉ። በዚህም ከልጅነቷ ጀምሮ ለንባብ ባህልና ለሥነ-ጽሁፍ ጣዕም እንግዳ አልነበረችም። በትምህርት ቤትም መጻህፍትን አንብቦ ግምገማ ከማሰናዳት ጀምሮ ተውኔቶችን አዘጋጅቶ ለተማሪ እና ወላጆች የማቅረብ እንቅስቃሴዎች የነበሩ በመሆናቸው፤ በእነዚህ ውስጥ እየተሳተፈች ነው ያደገችው። እንደዚሁም ከእህቶቿ ጋር በልጅነታቸው አጫጭር ተውኔቶችን(ጭውውቶችን) ደርሰው በማዘጋጀት ወላጆቻቸውን ያዝናኑ ነበር። በሥነ-ጽሁፍ፣ በቋንቋ እና በትርጉም ረገድ ያደረባትን ፍቅር በተመለከተ፤ ሕይወት በልጅነቷ በ1980ዎቹ እና በ1990ዎቹ ያነበበቻቸው የጉምቱ ኢትዮጵያውያን ደራሲያን እና ተርጓሚዎች መጻህፍት፤ ተጽእኖ እንዳሳደሩባት ታምናለች። በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋም ቢሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ውስጥ በሚገኘው የባህል ማዕከል ውስጥ በሳምንት አንድ ቀን በሚካሄደው የግጥም ምሽት ላይ ግጥሞች እና የግጥም ትርጉሞችን በማቅረብ አስደምጣለች።

“የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”

በተመረቀችበት የሕግ ሙያ እና ከዚሁ ጋር ተያያዥ በሆኑ የሙያ መስኮች ውስጥ ለዐሥር ዓመት አካባቢ ተሠማርታ ስትሠራ ከቆየች በኋላ አንድ ቀን ያነበበችውን መጽሀፍ ግን አንብባ ብቻ ልትተወው አልፈቀደችም። የመጽሀፉ ርዕስ The Case of the Socialist Witchdoctor ሲሆን፤ ሀማ ቱማ በተሰኘ ኢትዮጵያዊ ደራሲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈ፤ በደርግ ዘመን የተከናወኑ ሁነቶችን በፖለቲካዊ ስላቅ ስልት የሚቃኝ መጽሀፍ ነው። ሕይወት ይህንን መጽሀፍ “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ በመተርጎም በ2009 ዓ.ም ለንባብ አብቅታለች። በትርጉሙ ውስጥ በመጽሀፉ ውስጥ የተጠቀሱ አንባቢያን ግር ሊያሰኙ የሚችሉ፤ ለአንባቢ ተገቢ የሆነ ተጨማሪ መረጃ ሊያቀብሉ የሚችሉ፤ ወይም አንባቢው ካላወቃቸው የታሪኩን ፍሰት በሚገባ እንዳይረዳ ሊያደርጉ ይችላሉ ብላ ያመነችባቸውን ጉዳዮች የተመለከቱ የግርጌ ማስታወሻዎችን በመጨመር አሳትማዋለች። መጽሀፉ በአንባብያን ዘንድ ከፍ ያለ ተቀባይነት ከማግኘቱም ባሻገር በ Rusty Town እና በኢትዮጵያ ቴሌቪዝን ትብብር፤ “ግራ ቀኝ” በሚል ርዕስ ወደ ቴሌቪዥን ድራማነት ተቀይሮ ከግንቦት 19 ቀን 2015 ዓም ጀምሮ ለስርጭት በቅቷል። በ2014 ዓ.ም ደግሞ መጽሃፉ በሮማናት አሳታሚ በኩል ለሁለተኛ ጊዜ ታትሟል።

ድርሰቶችን ወደ እንግሊዝኛ መመለስ

ከዚህ መጽሀፍ ትርጉም በኋላ ሕይወት በተሠማራችበት የሥነ-ጽሁፍ ዘርፍ ለራሷም ደስታ ለወገንም ይሁን ለሀገር ጥቅም የተሻለ የሚሆነው በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፉ መጻህፍትን ወደ አማርኛ መመለስ ብቻ ሳይሆን፤ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ ኢትዮጵያዊ ሥራዎችንም ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ በመመለስ ዓለም ከሥነ-ጽሁፋችን ለዛ ጋር የሚተዋወቅበትን እና የሚለማመድበትን ሥራ መሥራት እንደሆነ አመነች።

በመቀጠል ሕይወት ወትሮም የልብ ፍላጎቷ በሆነው የሥነ-ጽሁፍ መስክ ሙሉ በሙሉ ለመሠማራት የቅጥር ሥራን ለመተው ወሰነች። በዚሁ መሠረት በሕይወት ተፈራ Mine To Win ተብሎ የተጻፈውን የእንግሊዝኛ መጽሀፍ “ኀሠሣ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተረጎመች። ይህንን መጽሀፍ በመተርጎም ሂደት ውስጥ ትርጉሙ የመጽሃፉ ታሪክ በተዋቀረበት ወደኋላ ራቅ ያለ ዘመን ውስጥ ይነገር የነበረውን የአማርኛ ቋንቋ ለዛ በጥሩ ሁኔታ እንዲላበስ ያደረገችው ጥረት በአንባብያን ዘንድ ጥሩ አቀባበልን አስገኝቷል። መጽሀፉ ውስጥ የሚገኘው ዋና ገፀ-ባህሪይ ታሪኩን ልክ እርሱ በኖረበት በ19ኛው መቶ ክፍለ- ዘመን የገጠር አማርኛ መተረኩ ትርጉሙን ለጊዜው እና ለቦታው እውነተኛ (authentic) የሆነ አሰኝቶታል።

ከ “ኀሠሣ” በኋላ ሕይወት በዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ የተጻፉ ሁለት መጻህፍትን ደግሞ ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ ተርጉማለች። እነዚህ ሁለት የዮርዳኖስ መጻህፍት በዋነኛነት ኢትዮጵያውያን ዜጎች በእግር ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲፈልሱ ከዚህ እስከደቡብ አፍሪካ ባሉ ሀገራት ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ውጣ ውረድ እንዲሁም እዚያ ከደረሱ በኋላ የሚቆያቸውን ከባድ ሕይወት ገጽታ የሚዳስሱ ናቸው። ሕይወት “መንገደኛ” የተባለውን የዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ መጽሀፍ “Wayfarers” በሚል ርዕስ፤ “እላፊ” የተባለውን ደግሞ “Way Further” በሚል ርዕስ ወደ እንግሊዘኛ የመለሰች ሲሆን፤ የመጀመሪያው ማለትም “Wayfarers” በ2010 ዓም ታትሞ ለንባብ በቅቷል።

ሕይወት የትርጉም ሥራ ጉዞዋን በመቀጠል በበድሉ ዋቅጅራ(PhD) “እውነት ማለት የኔ ልጅ” በሚል ርዕስ የተጻፈውን ግጥም “Truth, my Child” በሚል ርዕስ ወደ እንግሊዘኛ ተርጉማ በ2010 ዓም PN Review በተሰኘ የTime መጽሔት የሥነጥበብ ክፍንፍ በሆነ ሕትመት ላይ፣ ገጣሚው ራሱ ባሳተመው “የወይራ ሥር ጸሎት” በተሰኘ መድብል ውስጥ እንዲሁም The Songs We Learn from Trees በተባለ የኢትዮጵያውያን ገጣሚያን ሥራዎች ስብስብስ ውስጥ ታትሟል። ከእነዚህ በኋላ ሕይወት አከታትላ የበድሉ ዋቅጅራን ሌሎች 12 ግጥሞችም እና “ያልተከፈለ ስለት” የተባለን አጭር ታሪክ ወደ እንግሊዘኛ ተርጉማ የአርትኦት ሂደትን አልፈው እስኪታተሙ በመጠባበቅ ላይ ነች። እንደዚሁም የእንዳለጌታን ሶስት ግጥሞች፣ አንድ አጭር ታሪክ እና አንድ ተውኔት ወደ እንግሊዘኛ ተርጉማለች።

ከእነዚህ በተጨማሪ በደራሲ አዳም ረታ ከተደረሱ ሶስት መጻህፍት ውስጥ “አለጋና ምስር”፣ “ትይዩ” እንዲሁም “ኩሳንኩስ” የተባሉ አጫጭር ታሪኮችን ወደ እንግሊዘኛ የተረጎመች ሲሆን፤ እነዚህም ህትመትን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። እንደዚሁም ከ1960ዎቹ አቢዮት ጋር በሚገናኙ ታሪካዊ ሁነቶች ሳቢያ ሁለት ትውልዱ ስለሚናወጥበት ቤተሰብ መጻፍ የጀመረችው ረጅም ታሪክ ጠቀስ ልቦለድም ሕይወት ወደፊት ለንባብ ለማብቃት ከምትሻቸው ሥራዎቿ መካከል ነው።

በአሁኑ ጊዜ የአዳም ረታን “መረቅ” እንዲሁም የበድሉ ዋቅጅራን “የማይጻፍ ገድል” የተሰኙ መጻህፍት ወደ እንግሊዘኛ በመተርጎም ሂደት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፤ ከእነዚህ በተጨማሪም በDStvው ‘አቦል’ ቻናል ላይ ከግንቦት 20/2015 ዓም ጀምሮ እየተላለፈ ለሚገኘው “አፋፍ” የተሰኘ የቴሌቪዥን ድራማ ስክሪፕቶችን ትጽፋለች። አልፎ አልፎም Translators Without Borders በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለተለያዩ አካላት የሚሠራቸውን የአማርኛ ትርጉሞች ጥራት በማረጋገጥ ረገድ በገምጋሚነት ትሠራለች።

በተለይ በአሁኑ ጊዜ ሕይወት የዓለምን ሥነጽሁፍ ወደ ሀገር ውስጥ ቋንቋ፤ በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የተደረሱ የሥነጽሁፍ ሥራዎችን ደግሞ ወደተቀረው ዓለም የማድረስን አላማ በተመለከተ፤ በዋናነት ከገጣሚ ሮማን ተወልደ እና ከተርጓሚ ቤተልሔም አትፊልድ ጋር በመሆን፤ ከአማርኛ እና እንግሊዘኛ በተጨማሪ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ሥነጽሁፍን ከሚከውኑ ባለሙያዎች ጋር “የኢትዮጵያ የሥነጽሁፍ ተርጓሚያን ማኅበር”ን ለማቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች።

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ስለ ህይወት

ከህይወት ታደሰ ጋር ለመጀመሪያ ግዜ በስነፅሁፍ ዝግጅት ላይ የተዋወቁ ሲሆን የዶ/ርን በድሉን ጨምሮ የተለያዩ ሰዎችን መፅሃፍት በትርጉም ሰርታለች። ህይወት ከተረጎመቻቸው የዶ/ር የፅሁፍ ሥራዎች መሃል ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ ያልተከፈለ ስለት እና ሌሎችም ይገኙበታል።

ተርጎሚ ለመሆን የስነ-ጽሁፍ ሰው መሆን የሚያስፈልግ ሲሆን ለዚህም ህይወት በስራዋ ስኬታማ መሆን ችላለች። ትርጉሞችን በሁለቱም ቋንቋ በአማርኛም ሆነ በኢንግሊዘኛ ትሰራለች። በኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ በትርጉም ስራዋ ስኬትን የተቀናጀች ሰው መሆንዋን ዶ/ር በድሉ ይመሰክራሉ ።ኢትዮጵያዊ ይዘት ያላቸውን የፅሁፍ ስራዎችን በትርጉም በኢንግሊዘኛ መፃፉ አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ነው። ምክንያቱም በአለም አቀፍ መፅሃፍት ቤቶች ሆነ በአፍሪካን ሥነ-ፅሁፍ ውስጥም ኢትዮጵያዊ ይዘት ያላቸው መፅሃፍቶች የሉም ። ለዚህም ትርጉም እና የትርጉም ስራዎች መሰረታዊ እና ብቸኛው መንገዶች ናቸው። ህይወት ከትርጉም በተጨማሪ የመፃፍ ብቃት ስላላት የራሷን ወጥ ስራ ብትሰራ መልካም እንደሆነ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ይናገራሉ።

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አእምሮ የቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቀበት ነው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በመዝገበ-አእምሮ የባለታሪኮች ስነዳ ፕሮጀክቱ እስካሁን ሲሰራ በቆየው መሰረት በሀገራችን ልዩ ልዩ ሙያዎች ለውጥ ያመጡ እና በትጋታቸው ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ተስፋ አላቸው ብሎ የሚያምንባቸውን ግለሰቦች ታሪክ በመሰነድ ትጋትና ጥረታቸውን ለትውልድ ማስተላለፍ አላማው መሆኑ የሚታወቅ ነው። በመሆኑም ዛሬ ያቀረብናት ባለታሪክ ህይወት ታደሰም የዚሁ አላማ አካል ሆና አግኝተናታል። ህይወት ከልጅነቷ ጀምሮ ለስነ-ፅሁፍ ያላት ቅርበት እና የኪነጥበብ ፍላጎቷ በአንድ ተዳምረው ያላትን የቋንቋ እውቀት ተጠቅማ በሀገሯ ሰዎች የተፃፉ ድንቅ የስነ-ፅሁፍ ስራዎች ለአለም እንዲደርስ እየተጋች ያለች እና የሀገራችንን ስነ-ጽሁፍ ለአለም በማስተዋወቅ ረገድ የራሷን አሻራ ለማሳረፍ እየተጋች የምትገኝ ብርቱ ባለሙያ ናት። እንዲህ አይነት ልታይ ሳይሉ ጠቃሚ ተግባር እያከናወኑ ያሉ ሰዎችን ወደ መድረኩ ማምጣት ቀዳሚ ግባችን ነው፡፡ በተለይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየጻፉ ኢትዮጵያን ለቀሪው አለም ቅርብ ለሚያደርጉ ሰዎች ልዩ ከበሬታ አለን፡፡ ህይወት ታደሰም በሙሉ ሰአት የድርሰት ስራዋን ለማከናወን ቆርጣለች-ይህም የሚያስመሰግናት፡፡ ከግማሽ ክፍለ-ዘመን በኋላ ይህ ታሪክ በዛኛው ትውልድ ሲነበብ የሚነግረው ብዙ ነገር አለ፡፡ ዘመንን የማሳየት አቅም አለው፡፡ ለወደፊት የሰነቀቻቸውን እቅዶቿን ተመልክተን የህይወት ታደሰ ጥረት በመዝገበ-አእምሮ የአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ ተሰንዶ ሊቀመጥ ይገባዋል የሚል አቋም ላይ ደርሰናል። በዚህም መሰረት ይህ ጽሁፍ ዛሬ ነሀሴ 24 2015 በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች ተቀመጠ፡፡