ሊሴ ገብረማሪያምን 70ኛ አመት

ተወዳጅ የሚድያና የኮሚኒኬሽን አገልግሎት›› የሊሴ ገብረማሪያምን 70ኛ አመት ምክንያት በማድረግ ይህን ጽሁፍ አቅርቦአል፡፡ አዘጋጅና አቅራቢ እዝራ እጅጉ 0911416678
ሊሴ ገብረማሪያም ተማሪ ቤት የዛሬ 70 አመት በ1940 የተመሰረተ የእውቀት ቤት ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ከ1‚800 በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ የሚገኘው ሊሴ በርካታ ብቁ ተማሪዎችን ስለማፍራቱ ይነገራል፡፡ በፈረንሳይና በኢትዮጵያ መንግስት የጋራ ትብብርና አንድነት የሚመራው ሊሴ ከጥቁር አንበሳ ተማሪ ቤት አካባቢ ይገኛል፡፡ ከአንደኛ እስከ 13ኛ ክፍል ድረስ የማስተማር ግብ ያለው ሊሴ የ70 አመት ታሪክ ያለው የእውቀት ቤት ነው፡፡
ሊሴ ገብረማሪያም ከመከፈቱ ቀደም ብሎ ማለትም ከ1940 በፊት የፈረንሳይና የኢትዮጵያ ግንኙነት በምን አይነት መንገድ እያደገ እንደመጣ መመልከት እንችላለን፡፡በቀዳሚነት የሀገራችንና የፈረንሳይ ግንኙነት ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረው ምኒሊክ በ1897 የባቡር ጣቢያ ለመጀመር ከፈረንሳይ ጋር ስምምነት ባደረጉበት ጊዜ ነበር፡፡ከ10 አመት በሁዋላ ማለትም በ1907 በአሊያንስ ፍራንሴስ የፈረንሳይኛ ትምህርት ማስተማር ይጀመራል፡፡ ቦታውም አሁን አሊያንስ ፍራንሴስ የሚገኝበት ቦታ ነበር፡፡ በ1910 ደግሞ መነሻውን ድሬዳዋ ያደረገ የካቶሊክ ተማሪ ቤቶች ምስረታ ስለነበር ይህም ለሊሴ ገብረማሪያም መመስረት ትልቅ ሚና አበርክቶአል፡፡ ልክ በ1917 በሀገራችን የባቡር መንገድ ስራውን ጨርሶ ሲጀመር የፈረንሳይ መንግስትም እገዛ ነበረበትና ይበልጥ የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ሊጠናከር ቻለ፡፡ ከተማሪ ቤቱ ያገኘሁት መረጃ እንደሚያስረዳው በ1947 ተማሪ ቤቱ ሳይመረቅ ነገር ግን 15 ተማሪዎችን ተቀብሎ ይመዘግባል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች አብዛኛዎቹ ከአሊያንስ ፍራንሴስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የመጡ ነበሩ፡፡ ሊሴ በ1948 በመደበኛነት 144 ተማሪዎችን ይዞ ማስተማር ጀመረ፡፡ ከ4 አመት በሁዋላ ማለትም በ1952 ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ሊሴ ተማሪ ቤት በመገኘት የምረቃ ስርአቱን አከናወኑ፡፡ በወቅቱ ሊሴ ሲጀመር ቦታው አሁን ጥቁር አንበሳ ያለበት ስፍራ ነበር፡፡ በ1961 በእኛ ቀመር ደግሞ በ1953 የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኦፍ አፍሪካ በአዲስ አበባ ሲከፈት ለሊሴ ገብረማሪያም ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ቻለ፡፡ በተለይም ፈረንሳይኛን ለማስፋፋት ትልቅ ሚና ነበረው፡፡


በ1966 በእኛ ደግሞ በ1958 የዛን ወቅት የፈረንሳይ መሪ የነበሩት ደጎል ስራዬ ብለው ሊሴን ጎበኙ፡፡ በወቅቱም ፈረንሳይና ሀገራችን የሁለትዮሽ ስምምነት አደረጉ፡፡ ደጎል በ1953 ማለትም ተማሪ ቤቱ በተመሰረተ በ5አመቱ ሊሴን እግረ-መንገዳቸውን ጎብኝተው ነበር፡፡ በዛው አመት ነበር የመጀመሪያዎቹ ሊሴ ባካሎሪያ ያጠናቀቁ ወጣቶች የተመረቁት ፡፡ ባካሎሪያ ማለትም ከ1-13 ያለውን ክፍል ተምረው የጨረሱ ማለት ነው፡፡ እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የሊሴ ምሩቃን ዶክተር ብርሀኑ አበበ፣ ዶክተር ኤፍሬም አስፋው ፣ ዮሀንስ ካሳ ፣ኢኛስ ካሎስ ነበሩ፡፡
በ1973 የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፖምፒዱ ሊሴን ከመጎብኘቱ ሌላ የተማሪ ቤቱን የተሰሩ አዳዲስ ህንጻዎች ሊመርቅ ችሎአል፡፡ ደርግ በ1974 ወይም በ1966 በኛ ፣ሲመጣ በሊሴ ተማሪ ቤት ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ ሳይደርስ ቀረ፡፡ ነገር ግን የተማሪ ቤቱ የማስተማር ስልት ሙሉ በሙሉ የሀገራችንን የትምህርት ስርአት የተከተለ ነበር፡፡ ከ1976-1983 ባሉት አመታት ሊሴ የአዳሪ ተማሪ ቤቱን ዘጋው፡፡ ነገር ግን ሊሴ ‹‹ሀ›› ብሎ ማስተማር ከጀመረበት ከ1948-1976 የአዳሪ ተማሪዎችን ነበር ይቀበል የነበረው፡፡ በ1991 ወይም በዕኛ ቀመር በ1983 የመንግስት ለውጥ ሲደረግ ሊሴ በራሱ የትምህርት ካሪኩለም መመራት ጀመረ፡፡ በ1997 ደግሞ ሊሴ ገብረማሪያም የተመሰረተበትን 50ኛ አመት አከበረ፡፡

በአሁኑ ሰአት 70ኛ አመቱን በማክበር ላይ የሚገኘው ሊሴ ገብረማሪያም በርካታ ታዋቂ ሰዎችን ለማፍራት የቻለ የትምህር ተቁዋም ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የስፖርት ሊቅ የሆኑት ፍቅሩ ኪዳኔ እንዲሁም በርካታ የታሪክ መጽሀፎችን ያቀረቡት አምባሳደር ዘውዴ ረታ የተማሩት በሊሴ ገብረማሪያም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሊሴ ጥራት ያለውን ትምህርት በመስጠትና በተለይም ለተማሪዎች ባህር ማዶ በሚገኙ አለምአቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ የትምህርት እድል በመስጠት ይታወቃል፡፡ አንድ ተማሪ ከ1-4 ከሆነ ሙሉ የትምህርት መሳሪያዎች ከሊሴ ተሙዋልቶለት በአመት 78‚000 ብር ወይም በወር 6‚500 ብር ይከፍላል፡፡ ከ5ኛ ክፍል -6 ከሆነ ደግሞ በአመት 38‚000 ብር ሲከፍል ይህም በወር 3‚166 ብር መሆኑ ነው፡፡ ከ7-10 ያሉ ተማሪዎች ብር 42000 ሲከፍሉ ከ11-13 ክፍል ያሉ ተማሪዎች በአመት 43000 ብር ይከፍላሉ፡፡ ሊሴ ገብረማሪያም ከዛሬ 70 አመት ቀደም ብሎ ሲመሰረት በአመት 60 ብር የሚያስከፍል ሲሆን በ1960 ዎቹ ይህ ክፍያ ወደ 180 ብር ሊያድግ ችሎአል፡፡ ውድ የዚህ ጽሁፍ ታዳሚያን ስለ ሊሴ የሚያስረዱ ወይም ካቀረብነው ሀሳብ ጋር አብረው የሚሄዱ ምስሎችንና ቪድዮዎችን አካተናል፡፡ ይህን ስራ እንድንሰራ ለረዳችን ለወዳጃችን አዜብ ወርቁ ታላቅ ምስጋና ይሁን፡፡


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *