ማክሰኞ ህዳር 18 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰአት ጀምሮ በተካሄደው የእውቅና ፕሮግራም ላይ የፀሐይ አሳታሚ መስራች ኤልያስ ወንድሙ እና ባለቤቱ ድምፃዊት ቤቲ ጂ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
ለባዊ ኢንተርናሽናል አካዳሚ ባዘጋጀው የእውቅና ፕሮግራም ፀሐይ አሳታሚ 25ኛ አመቱን ማክበሩን ተከትሎ አድናቆት ተቸሮታል፡፡ እንዲሁም ፀሐይ አሳታሚ ከ250 በላይ መፅሐፍትን በማሳተሙ ለአፍሪካ እና ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ ውሏል ተብሏል፡፡
የአካዳሚው የአንደኛ እና የ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች በመሰናዶው ላይ ታድመው በዘመናቸው ታሪክ ሊሰሩ እንደሚገባ እና የትውልድ ሽግግር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም ተነግሯል። አሳታሚው ኤልያስም ለተማሪዎቹ ልምዱን ያጋራ ሲሆን ያመነበትን ጉዳይ ይዞ እስከመጨረሻው በጽናት በመቀጠሉ ስኬታማ ለመሆን እንደቻለ ተናግሯል ።በንግግሩም ” ተስፋ መቁረጥ የለባችሁም ያመናችሁበት ነገር ካለ ማሳካት የሚባለው ነገር ቀላል ነው።” የሚል ሀሳብ ሰንዝሮ ነበር።
ባለቤቱ ቤቲ ጂም በበኩሏ ‘አንድን ስራ ለማሳካት በፅናት መስራት እንደሚገባ እንዲሁም ባለቤቷ ለዚህ እንደ ጥሩ ምሳሌ መሆን እንደሚችል አስታውቃለች።
የለባዊ ኢንተርናሽናል አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ፓኖስ ሀዘንድሪያስ በእለቱ ባደረጉት ንግግር፣ ኤልያስ ወንድሙን ከአሜሪካን ሀገር ጀምሮ እንደሚያውቁት ገልፀው በተለይ ፈጽሞ የህትመት ብርሀን ያላዩ የአፍሪካውያን ሥራዎችን፤ የምርምር ጆርናሎችን ኤልያስ በማሳተሙ ልናከብረው ይገባል ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም፣ ዶክተር አሉላ ፓንክረስት የአባቱ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት መጽሀፎች በፀሐይ አሳታሚ ለመታተም በመቻላቸው የተሰማቸውን ኩራትና ደስታ ገልጸዋል፡፡
‹‹ተማሪዎች ከታላላቆች ስኬት አንዳች እውቀት ሊቀስሙ ይገባል›› በሚል መነሻ ሀሳብ የተዘጋጀው ይህ መርሀ- ግብር ላይ ተማሪዎች የሙዚቃ ዝግጅት ያቀረቡ ሲሆን የሙዚቃ መምህሩ ሙዚቀኛ ቴዎድሮስ አክሊሉም ከተማሪዎቹ ጋር በመሆን ስራውን አቅርቧል፡፡
በዚህ የእውቅና ስነ-ስርአት ላይ ስለ ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት በአለም አቀፍ ደረጃ በምርምር ሥራቸው እውቅና ያተረፉ ምሁራን ምስክርነት የሰጡበት አጭር ዘጋቢ ፊልምም ለዕታ በቅቷል፡፡ በዚህ ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ሀሳባቸውን ከሰነዘሩት መሀልም የናይጄሪያው የስነ-ጽሁፍ ኖቤል አሸናፊ ወሌ ሶይንካ ይገኝበታል፡፡
እንደሚታወቀው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምኒኬሽን በመዝገበ- አዕምሮ ቅፅ ሁለት ላይ የኤልያስ ወንድሙን የህይወት ታሪክ በቅርቡ በሚወጣው የባለታሪኮች ስብስብ ውስጥ እንደሚያካትት ይታወቃል። ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽንም በተደረገለት ግብዣ በእውቅና አሰጣጥ ስነስርአቱ ላይ ታድሞ ነበር፡፡