ህይወት ተፈራ

የሕይወት ብርቱ ሕይወት

ህይወት ተፈራ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ሥራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡

ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ? የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡

ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 185 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር የፊልም ሰዎች ታሪክን አሰባስበናል። በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከሚሰነድላቸው መካከል ደራሲ ህይወት ተፈራ ትጠቀሳለች።

ህይወት ተፈራ የኢህአፓውን ጉምቱ ጌታቸው ማሩን የትግል ያልሆነ መልኩን ታውቀው ነበር እና፤ የተማሪዎች ንቅናቄ መሪው እጇን ይዞ ወደ ፍቅር ሲመራት አይታው ነበርና፤ ማርክሲስት ሌኒኒስትን ብቻ ሳይሆን ፍቅርንም አስጠንቷት ነበርና፤ ከፖለቲካ ሰውነቱ በላይ ሰዎኛ ሰውነቱን ዳሳው ነበርና… ሞቱ ያንገበግባታል። ገዳዮቹን ማወቋ፣ ከሞቱ በኋላ ሞቱ መዳፈኑን ማየቷ ደግሞ የመንገብገቧን መጠን ከፍ ያደርግባታል።

እናም ስለጌታቸው አንድ ወዳጁን ስታወራ ያላትን ይዛ መጽሐፍ ጻፈች:- “It remains a paradox to me that someone who believed so strongly in negotiation has been killed” ፈረንጅና አፉን በግርድፉ ወደ አማርኛ ስንመልሰው “የሃሳብ ልዩነቶችን በውይይትና ንግግር እንፍታ እያለ ወገቡን ይዞ የሚከራከር ሰው መገደሉ እስከዛሬ ድረስ ግራ ያጋባል።” እንደማለት ይሆናል።

የጌታቸውን ሌላኛውን መልክ ያየችው፤ ለራሴ ከራሴ የተረከብኩትን ሃላፊነት ስለጌታቸው ማሩ መጽሐፍ በመጻፍ ህሊናየን አሳረፍኩ ያለችው… ሕይወት ተፈራ ናት።

አስቀድማ በእንግሊዝኛ “Tower in the sky” ብላ የፃፈችውን ጌታነህ አንተነህ ወደ አማርኛ “ማማ በሰማይ” ብሎ መልሶታል። መጽሐፉ ስለጌታቸው ይሰማት የነበረውን መንገብገብ ያስታገሰ የፍቅርም የአብዮትም መጽሐፍ ነው።

ሕይወት ተፈራ ስለልጅነቷ፣ በአብዮት ውስጥ ስላለፈ ወጣትነቷና ከጌታቸው በኋላ ስላሳለፈችው የእስር ቤት እና የባህር ማዶ ሕይወት ከተወዳጅ ሚዲያ ጋር ቆይታ አድርጋለች። እዝራ እጅጉና አማረ ደገፋው እንደሚከተለው አሰናድተውታል።

እናቷ ጠንፍየለሽ ደምሴም አባቷ ተፈራ ምንዳም ፍቅርን ብቻ ሳይሆን ንባብን ይጋሩ ነበርና ሕይወት ገና በሕይወቷ ማለዳ ነበር ንባብን ሙጥኝ ያለችው። በመኮንን እንዳልካቸው የተጻፈውን “ፀሐይ መስፍን”ን ስታነብ ገና የ3ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች።

ሀረር ከተማ የነበራት የልጅነት ጊዜ ማራኪ እንደነበር ለማስረዳት በጊዜው የነበሩ የልጅነት ጨዋታዎችን ሁሉ ልቅም አድርጋ እንደተጫወተች ትናገራለች።

ከጨዋታው መሳ ለመሳ ንባቧንም አልተወች፤ ቤት የጀመረ መጽሐፍትን የማገላበጥ ልምዷ ትምህርት ቤት ድረስ ተከትሏት ሄዶ የቤተ መጽሐፍት አስነባቢዎች የሚመርጡላትን መጽሐፍ ደጋግማ አንብባለች።

እዚያው ሀረር መድኃኔዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እየተማረች አባቷ የገለጡላትን የእንግሊዝኛ መጽሐፍት ድንቅፍ ሳትል አንብባለች።

እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1965 ዓ.ም የያኔው ቀኃስ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን ተቀላቀለች። ወቅቱ ተማሪዎች ከፍተኛ ንቅናቄ የሚያደርጉበት ስለነበር… በሁለተኛው መንፈቅ ዓመት መጀመሪያ የጥናት ክበብ ቀጥሎ የፓርቲ አባል ሆነች። አሁን ንባቧ ማክሲስታዊ ሆነ። 1966 ዓ.ም ሲሆን ደግሞ አብዮቱ ፈንድቶ ትምህርት ተቋረጠ።

ትምህርት ከመቋረጡ ቀድሞ ከጓደኞቿ ጋር የያዘችውን የስለሶሻሊዝም ጥናት ይመራ ዘንድ አንድ ሰው ተዋወቀች። የያኔው ቀኃስ የአሁኑ የካቲት 12 ሆስፒታል ፊት ለፊት ያገኘችውና እድሜው በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የሆነ ደንገርገር ያለ ዓይን አፋር ወጣት – ጌታቸው ማሩ።

ስለ ታሪካዊና ዲያሌክቲካዊ ቁስ አካልነት፣ ስለመሬት ከበርቴዎች ሥርዓት እና ስለሌሎችም በማጥናታቸው እግረ መንገድ ፍቅርም አጥንተዋል። ፍቅራቸው ግን ድብቅ ነበር፤ ከጎረቤትና ከቤተሰብ ሳይሆን ካገናኛቸው ፓርቲ የተደበቀ ፍቅር።

እንደልባቸው ባይሆንም እንደሁኔታዎች ምቹነት ትግሉንም ፍቅሩንም ሲመሩት ዓመታትን ኑረው 1969 ዓ.ም ሲገባ እንቅፋት ገጠማቸው – ትልቅ እንቅፋት፤ ጌታቸው ማሩ በገዛ ጓዶቹ ተገደለ።

ሕይወት ሞቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሰማ የተሰማትን በመጽሐፏ “የስሜት ህዋሳቶቼ ሁሉ የከዱኝ መሰለኝ።” ብላ ለመግለጽ ሞክራለች። የመጨረሻዋ ቅፅበቱንም እያሰበች ራሷን በጥያቄዎች አጨናንቃለች፦ “ከመሞቱ በፊት ስላሳለፈው ጊዜ ለማወቅ ተመኘሁ። ለመሆኑ በጥይት ሲመታ ምን ተሰምቶት ይሆን? ምን ብሎ ይሆን? ስለኔ አስቦ ይሆን? በመጨረሻ ያሰበው ነገር ምን ይሆን? ምን ያለ ጨካኝ ዓለም ነው? ደርግ ገድሎት ቢሆን፣ ሐዘኔ ይቀንስ ይሆን? የተገደለውስ ለምንድን ነው? የሰዎችን ሕይወት እናድን ስላለ?”

የጌታቸው ሞት እያንገበገባት፣ እርሷም ከፖለቲካው ተነካክታለችና ሞትን እየሸሸች አንድ ዓመት ሙሉ አዳሯ ከቤት ውጭ ኑሮዋ የድብብቆሽ ነበር። በቀጣዩ ዓመት(1970 ዓ.ም)የካቲት ወር ላይ በቁጥጥር ስር ውላ 15 ዓመታት ተፈርዶባት ከርቼሌ ገባች። ከከርቼሌ እየተወሰደ ሰው ስለማይገደል እና ፍርደኛ ስለሆነች አብዮታዊ እርምጃ እንደማይወሰድባት ተስፋ ነበራት። በእስር ቆይታዋ ቀንሳው የነበረ ንባቧን አበረታች፣ ፍቅሯንም ህልሟንም የነጠቃት ፖለቲካን እርም አለች፣ ከንባቧ እና ፖለቲካን ከመርገም አረፍ ስትል ስለጌታቸው ለመፃፍ ሞካከረች፤ ያለችበት እስር ቤት ሲፈተሽ ግን የፃፈችውን አውጥታ ጣለች።

ከእስር ቤት እየተወሰዱ የሚገደሉ ስለነበሩ እርሷ ከዛ በማምለጧ ፈጣሪዋን እያመሰገነች ደሞ አብረዋት የነበሩ ጓደኞቿ ሲፈቱ አልቅሳ እየሸኘች 8 ዓመት ከ4 ወር ከፍርግርግ ብረቶች ጀርባ ካሳለፈች በኋላ ሰኔ 1978 ዓ.ም በምህረት ተፈታች።

በ1979 ዓ.ም መስከረም ላይ ተመልሳ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገባች። አመጽና አብዮት ይከተልሽ የተባለች ይመስል እግሯ ግቢውን በረገጠ በጥቂት ወራት ውስጥ የርሃብን ጨምሮ ተማሪዎች ከፍ ያለ አድማ አደረጉ። ‘ከእስር ተፈተው የመጡት ናቸው የአድማው መሪዎች’ የሚል ሹክሹክታ ሲሰማ የሕይወት ቤተሰቦች ስለሐይወት ሰጉ። ድጋሜ ልጃቸው እስር የሚቀማቸው ወይ ሞት የሚነጥቃቸው መሰላቸው፤ እናም መላ ዘየዱ።

መላቸው ባህር የተሻገረ መፍትሔን ይዞ መጣ። ሕይወት ባትፈልግም ጣልያን ሀገር ወዳለች እህቷ ተላከች።

ለዜጎቿ ምቹ ትሆናለች ብላ በወጣትነቷ የታገለችላትን ሀገር፣ ጓዶቿ ጋር ሁና ያለመችላትን ግዛት፣ አክብራ ያፈቀረችውን ብርቱ እንደዘበት ያጣችባትን መንደር ትታ ጣልያን ደረሰች።

ሁለት ዓመታትን በዚያ ከቆየች በኋላ ወደ ካናዳ አቀናች። በካናዳ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ኮኦርዲኔተር ሆና “ፒፕል ቱ ፒፕል ካናዳ” የተባለ ድርጅት ውስጥ ለዓመታት አገልግላለች። “ሴንተር ፎር ውሜን” የተባለ ድርጅትም ውስጥ 2 ዓመታት ከጥናት ጋር የተያያዙ ስራዎችን ሰርታለች። ቀጥላ በዚያው በካናዳ በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ በጥሩ ክፍያ መስራት ጀመረች።

ሁለት አስርታትን በተሻገረ የባህር ማዶ ኑሮዋ ስለጌታቸው ምንም ምንም ሳይል መቆየቱ ያንገበግባታል፤ ራሷ ራሷን ስለእርሱ አንድ መጽሐፍ መጻፍ አለብኝ የሚል ግዴታ ውስጥ ከታም ቆይታለች።

በትምህርት ቤት ቆይታዋ ከመጻፍ ጋር የተያያዙ ኮርሶቿ ላይ ከፍ ያለ ውጤት ማምጣቷ፣ ከመምህሮቿ የበርች አስተያየት መቀበሏ፣ ለ9 ወር ከፍላ 3 ወር ብቻ በተማረችው የሥነ ጽሑፍ የርቀት ትምህርት አቅሟን መፈተሿ እና የልጅነት የንባብ ፍቅሯ ተዳምረው ግዴታዋን ልትወጣ ብዕሯን ይዛ ተቀመጠች… ከዓመታት በኋላ ከተቀመጠችበት ስትነሳ “Tower in the sky” የሚል መጽሐፍ እጇ ላይ ነበር።

ከ26 ዓመታት በኋላ ጠቅልላ ወደ ሀገራ ከገባች እና “Tower in the sky” መጽሐፏ ይዞት የመጣውን ግብረ መልስ አስተውላ “ለካ መጻፍ የምፈልገው ነገር ነው” ብላ በዚያው በፈረንጅ አፍ “Mine to win” የሚል ጥናትን ያካተተ የልቦለድ ዘውግ ያለው መጽሐፍ ደገመች።

‘ምነው በእንግሊዝኛ ብቻ’ ያሏትን ተችዎች አፍ ለማዘጋት በሚመስል መልኩ “ምንትዋብ” የሚል ታሪካዊ ልቦለድን ሰለሰች፤ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጭምር በፌስቡክ ገፃቸው “ደገኛ መጽሐፍ ጽፈሻልና እናመሰግንሻለን” አሏት።

ጥሩ ክፍያዋን ትታ ወደ ሀገሯ የገባችው ሕይወት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ እና የኢትዮጵያ ሴቶች ጤና ማህበር ውስጥ ስትሰራ የቆየች ቢሆንም የሙሉ ጊዜ ደራሲ የመሆን ህልም አላት። በቅርቡም አራተኛ መጽሐፏን ለአንባቢያን ለማድረስ ዝግጅት ላይ ናት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *