ፍቅሩ ካሳ

ፍቅሩ ካሳ

ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በፊልም ፤ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እናስተዋውቃለን፡፡ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ5 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ የምንጀመረው ከሬድዮ ድራማ ዘርፍ ሲሆን ታሪኩ የሚቀርብለትም ሰው ፍቅሩ ካሳ ነው፡፡

እነሆ! ፍቅሩ ካሳ!

የተወለደው መንዝ እና ግሼ ውስጥ ነው፡፡ በ7 ዓመቱ ወደ ጎጃም ፓዌ ሰፈራ ጣቢያ ውስጥ በመሄድ ኖሯል፡፡ቤተሰቦቹ መምህራን (የከተማ ገበሬዎችም) ስለሆኑ በተለያዩ ቦታዎች የመኖር እድልን አግኝቷል፡፡ ቻግኒ፣ሸዋሮቢት፣ሃዋሳ፣ደብረዘይት፣አዲስ አበባ የኖረባቸው ቦታዎች ሲሆኑ አዲስ አበባ ውስጥም ከ25 ዓመት በላይ ኖሯል፡፡

በትምህርት አለምም እጅግ ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች አንዱ የነበረ ሲሆን 8ኛ እና 6ኛ ክፍሎችን ከ99 ፐርሰንት በላይ በማምጣት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያን / ማትሪክን/ ደግሞ በሶሻል ሳይንስ ዘርፍ 3.8 በማምጣት ለከፍተኛ ትምህርት የበቃ ነው፡፡ በአዲስ አበበ በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም በቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ውስጥ ሰቃይ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከከል ቀዳሚው ነው፡፡

ፍቅሩ ካሳ ተጫዋች ነገሮችን ቀለል አድርጎ በመኖር የሚታወቅ ሲሆን ወጣቶችን በማገዝ በመርዳት እና በመቅረብም ይታወቃል፡፡ አሁን ባለትዳር እና የ3 ወንድ ልጆች አባትም ነው፡፡ ፍቅሩ ካሳ መዝናኛን እና ትምህርትን ማዕከል በአደረጉ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ግልጋሎት ሰጥቷል፡፡ በ1992 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ቴአትር ጥበባት ከተመረቀ ጀምሮ በተለያዩ መንግስታዊና እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ማህበራዊ እሴቶቻቸውን የጠበቁ ጥበባዊና ትምህርታዊ ስራዎችን ለ20 ዓመታት ለማህበረሰቡ ሲያበረክት የቆየ ባለሙያ ነው፡፡

ለረጅም አመታት በተለያዩ የፈጠራ ስራ፣ በምርምር እና ጥናት በሁሉም የሚዲያ ውጤቶች ውስጥ በጋዜጠኝነት፣ በቴአትር እና ስነ ጽሁፍ ባለሙያነት፣ በህጻናት ኪነጥበብ ስራዎች በአዘጋጅነት፣ እና በአስተባባሪነት፣ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲን ጨምሮ በተለያዩ የስነ ጥበብ ኮሌጆች በሬድዮ ድራማ ፣ በተውኔት ጽሁፍ እና በህጻናት ድራማ ላይ በአስተማሪነት እና በኪነ-ጥበብ ሂስ ላይ ሲሰራ የቆየ ባለሙያ ነው፡፡

በሜጋ ኪነ ጥበባት፣ በሀገር ፍቅር፣ በህጻናት እና ወጣቶች ቴአትር ቤት፣በጆን ሆፕኪንስ ዩንቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ፣ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በቋሚነት ሰርቷል፡፡ ለስምንት አመታትም በተናጠልና በጋራ በመሆን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክት በሆኑት የባህሪ ለውጥ አምጪ ተከታታይ የህትመት ድራማዎች / serial print drama – comic books ላይ በደራሲነት፣ በፕሮዳክሽን አስተባባሪነት፣በግራፊክስ ስራዎች ውስጥ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ከስራዎቹም ውስጥ ለመከላከያ ሰራዊት “ ጥቋቁር ነብሮች” ን፣ ለፌደራል ፖሊስ “ ተወርዋሪ ከዋክብት” ን፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “ life 101” ለእያንዳንዳቸው ከ30 በላይ ክፍል ተከታታይ ድራማዎችን በደራሲነት ሰርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዚሁ መስሪያ ቤት የዋቆ ልጆች 13 ክፍል የሬድዮ ድራማ በደራሲነት፣ የህይወት ምርጫ ሙሉ የህትመት መጽሃፍ ትርጉምም ሰርቷል፡፡

ከዚህ መስሪያ ቤት ጋር በጋራ በመሆን ከቼክ ፕራግ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የቪዥዋል ስቶሪ ቴሊንግ ስልጠናዎችን ከመውሰዱም በላይ ከጆንሆፕኪንስ ዩንቨርሰቲ የሚሰጡ ሙሉ የኮሚዩኒኬሽን ትምህርቶችን በኢትዮጵያ ተከታትሏል፡፡ በዚህ ስልጠና ታግዞም ድራማዎችን በመስራት የጤና ትምህርቶች በድራማ ታግዘው ኢትዮጵያዊያን ተጠቃሚ እንደሆኑ የማይናቅ አገልግሎትን ሰጥቷል፡፡


“ገመና 2 “ ተከታታይ የተሌቪዥን ድራማን ሙሉ መዋቅሩን እና ታሪኩን ከመጻፍም በላይ እስከ 30 ክፍል በደራሲነት፣ 33 ክፍል አሸንክታብ ተከተታይ የሬድዩ ድራማ በፋና ሬድዮ፣ ከ40 በላይ ወጥ እና ትርጉም ተውኔቶችን በሸገር የቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም ላይ ጽፈዋል፡፡ እነዚህ ድራማዎች በወቅቱ ድራማ አድማጭ ለሆኑ ግለሰቦች አጅግ መሳጭ፣ በፈጠራ የታገዙ እንደነበሩ የሚረሱ አይደሉም፡፡

ሽፍንፍን የሬድዮ ድራማን ለ52 ክፍል በፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት በአዘጋጅነትና በደራሲነት፣26 ክፍል የሬድዮ ድራማ ለጄ ኤስ አይ ኢትዮጵያ በጋራ ደራሲነት ፣ 70 ከፍል ማለፊያ ድራማን በአዘጋጅነት፣ 36 ክፍል አዙሪት የተባሉ የፋና ፕሮዳክሽኖችን በአዘጋጂነት፣ የደጉ ልጆች 30 ክፍል ድራማ ለአማራ ብዙሃን መገናኛ፣ ለአይ ኦ ኤም 2 የሙሉ ጊዜ የመድረክ ድራማዎችን፣ ለህጻናት እና ወጣቶች ቴአትር ቤት የሙሉ ጊዜ የወጣቶች የመድረክ ድራማ፣ ለአላይቭ ኤንድ ትራይቭ “ማወቅ ደጉ” የተሰኘ አንድ ቪድዮ ፊለም በደራሲነት ፣ ለሴቭ ችልደረን “አሸንክታብ” ቪድዮ ፊልም በደራሲነት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አምስት የቲቪ ድራማዎችን በአዘጋጅነት እና በደራሲነት ፣ ለአዲስ አበባ መስተዳደር ከ10 በላይ አጫጭር ድራማዎችን በደራሲነት እና በአዘጋጅነት፣ ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ደግሞ ከ10 በላይ የማስተማሪያ የቪድዮ ፊልሞችን በማስተካከል ፣ የመድረክ ድራማዎችን የሬድዮ ተውኔቶችን በመጻፍ፣ በማዘጋጀት እና በማስተባበር ልምድ ያካበተ ባለሙያ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በመጽሄቶች እና በጋዜጦች ላይ የምርምር ጽሁፎችን በማቅረብ ሲሰራ የቆየ ባለሙያ ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት በፋና ብሮድካስቲነግ ኮርፖራት በድራማ ጸሀፊነት፣ አዘጋጅነት፣ ገምጋሚነት እና በመዝናኛ ረዳት ዋና ፕሮግራም አዘጋጅነት ( ፋና ቀለማት ፣ ፋና ላምሮት እና ፋና ክዋክብት) በመስራት ላይ ሲሆኑ አሁን እየተላለፉ የሚገኙ የቅዳሜ፣ የእሁድና የማስተማሪያ ድራማዎችን ደግሞ በአዘጋጅነት እና በአስተባባሪነት እየሰራ ይገኛል፡፡

በፋና ሬድዬ እየተላለፈ የሚገኘውን ጀንበር የሬድዮ ድራማን በአዘጋጅነት እና በታሪክ አርታኢነትም ይሰራል፡፡
በእዚህ በፋና ውስጥም የስራ መሪ ሲሆን በተለይ ጀማሪ ፕሮግራም ሰሪዎች ፈጣሪ እና አሳቢ እንዲሆኑ፣ የተሻለ ፕሮግራሞች እንዲያቀርቡ በማስተማር በመርዳት እና ልጆቹ ክርኤቲቭ እንዲሆኑ የማይናቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

ፍቅሩ ካሳ ከዚህ በላይ በጣም የበዙ ስራዎቸን የሰራ ቢሆንም ከእነዚህ መካከል ለዛሬ ይሄንን አቅርቤላችኋለሁ፡፡ ስራዎቹን እና ታሪኩን ያገኘሁት ከሲቪው ላይ መሆኑን ማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡
እዝራ እጅጉ! ( ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *