ጥላሁን ጉግሳ መንገሻ

Tilahun Gugssa Photo

ጥላሁን ጉግሳ መንገሻ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 150 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ጥላሁን ጉግሳ መንገሻ ነው፡፡

ጥላሁን በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ኢንደስትሪ ውስጥ የበኩሉን አበርክቶ በማድረግ ላይ ይገኛል።በተለይ ለልጆችና ለታዳጊዎች መንገድ ጠራጊ ነው።የገንዘብ ክፍያ ሳያስጨንቀው ከአፍንጮ በር መርካቶ በእግር ለዚያውም በራብ አንጀት ተመላልሷል። ለጥበብ ብሎ ትምህርቱን አቋርጧል ፡፡ ወድቋል ደግሞም ተነስቷል፡፡ ዛሬ ግን ከተሳካላቸው ሆኗል። አንጋፋው ተዋናይ ፣ ደራሲ : ዳይሬክተርና የማስታወቂያው ባለሞያ ጥላሁን ጉግሳ መንገሻ። የሙያ ታሪኩ ለአዲሱ ትውልድ አስተማሪ ሆኖ በመገኘቱ የህይወት ታሪኩ በእዝራ እጅጉ እና በዘቢብ ሁሴን ተሰንዷል፡፡

ውልደትና እድገት

አቶ ጉግሣ መንገሻና ወ/ሮ ባንቺ ገብሬ ካፈሯቸው ስድስት ልጆች መካከል አንዱ ነው።በ1949 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ‹‹አፍንጮ በር›› የቀድሞ ሳሙና ፋብሪካ የነበረበት አካባቢ ተወልዷል። ታላቁ የጥበብ ሰው ጥላሁን ጉግሳ መንገሻ። ጥላሁን፣ የመጀመሪያ ትምህርቱን እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ በወይዘሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ ትምህርት ቤት ተምሯል። በዚያም በጥሩ ውጤት ሚኒስትሪን ማለፍ ችሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ፣በወልድያ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃን በመነን ትምህርት ቤቶች ተምሯል።

የትያትር ፍቅር

ጥላሁን ጉግሣ ገና በልጅነቱ ወደ ትምህርት ገበታው ሳይገባ፣ ስለትያትር ምንነት በውል ሳይረዳ ነበር በጨወታዎቹ ውስጥ ትያትርን መለማመድ የጀመረው። የ3ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የወላጆች ቀን ሲከበር በዘመኑ በትምህርት ቤቱ የመዝሙር መምህር በነበሩት በአርቲስት መላኩ አሻግሬ የተዘጋጀ ትያትር ከፍ ባሉ ተማሪዎች መድረክ ላይ ሲተወን መመልከቱ ለትያትር ይበልጥ ልቡ እየቀረበና ቀንና ማታ እርሱን ብቻ እንዲያስብ አድርጎት ነበር። በዚሁ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለም ክፍል ከክፍል በሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች የተመለከተውን በግጥም መልክ በመዘገብ ለክፍል ጓደኞቹ ያቀርብ ነበር። የ6ኛ ክፍል ሚኒስትሪን ወስዶ በነበረበት የክረምት ወራት አንድ የልቦለድ ይዘት ያለው መፅሃፍና ወደ ሶስት አጫጭር የትያትር ፅሁፎችን መፃፍ ችሏል። ፅሁፎቹ በዘመኑ በነበረው ሳንሱር ተይዘውበታል።

ጥላሁን በዚህ ወቅት የነበረውን ጉጉት መቼም አይዘነጋውም። በልጅነቱ የወለዳቸው የበኩር ፅሁፎቹ ታትመውና ለመድረክ በቅተው ማየት ተመኝቶ በተፈሪ መኮንን የአማርኛ መምህር ለነበሩት ለየኔታ አሰፋ ገ/ መስቀል ( አሰፋ ሳይንሱ) አንብበው አስተያየት እንዲሰጡት ቢሰጣቸውም ስርዝ ድልዝ የሞላው ሆኖ ለህትመት ሳይደርስ ቀርቷል። ምንም እንኳን የፃፋቸው ፅሁፎች ለፍሬ ሳይበቁ ቢቀሩም መነሻ ሆነውታል። ጥላሁን ጉግሳ በዚህ ዘመን የተለከፈበት የትያትር ፍቅር አሁንም ድረስ አንዳች እንኳ ሳይቀንስ አብሮት ይኖራል።

በቀበሌ ኪነት ውስጥ

ጥላሁን ጉግሣ ትምህርቱን አቋርጦ ነበር በወጣት ማህበር በተደራጀ የቀበሌ ኪነት ውስጥ የገባው። ከቀይ ሽብር በኋላ በዚሁ በቀበሌ ኪነት ውስጥ እያለ አርቲስት መላኩ አሻግሬ በእንግዳነት በተገኙበት አንድ ድራማን ሰርቶ በጣም ስለወደዱለት ተጨማሪ ስራን እንደሚያሰራቸው ቃል ገባላቸው። ” የቆሰለች ስጋ” በአርቲስት መላኩ አሻግሬ የተደረሰ ትያትር ሲሆን ጥላሁን ለ4 ሰዓት የትወና ብቃቱን ያሳየበት ቴአትር ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዘመኑ ፕሮፌሽናል የተባሉ የሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ቋሚ ተቀጣሪዎች የነበሩት እነ ዘነበች ታደሠ( ጭራ ቀረሽ) ግርማዬ መኮንን የሺ ተክለወልድ አበራ ደስታ(ጆሮ) እና ሌሎችም ይህንኑ ትያትር ይለማመዱት ነበር።

ጥላሁንም በመላኩ አሻግሬ ጋባዥነት በተደጋጋሚ በሃገር ፍቅር ቤት እየተገኘ ልምምዳቸውን የመመልከት አጋጣሚ ነበረው፡፡ ከእለታት በአንዱ ቀን ታዲያ ከፕሮፌሽናሎቹ መካከል አንዱ ባለመገኘቱ የእርሱን ቦታ ሸፍኖ የመጫወት እድል ገጠመው። የመድረክ አያያዙ በተለይ ደግሞ ነጎድጎዳማው ድምፁ በዳይሬክተሩም ሆነ በደራሲው ተወደደለት። “የቆሰለች ስጋ” የጥላሁን ጉግሳ መንገሻ የመጀመሪያውና ታሪክ የማይሽረው ፕሮፌሽናል የመድረክ ስራው ሆኖ ተመዘገበ።

ራስ ትያትር (የከፍታው ዘመን)

ጥላሁን በራስ ትያትር ውስጥ ለ16 ዓመታት ያክል አገልግሏል። ከ1973 እስከ 1989 መጨረሻ ድረስ ። በዚህ የትያትር ቤት ቆይታው የጋሽ ተስፋዬ አበበ( ፋዘር)ድርሰት የሆነውን “ቀዩ መነፅር”ን ጨምሮ “አራት ለአንድ” : “የቴዎድሮስ እንባ” : “ሁለት ክፍል ግብዢያ” :”የሆቴሏ እመቤት”: “መንጠቆ”: “አሻራ”: “ስውር ሰይፍ”: “የመሀን ቱርፋት”: “የቁርጥ ቀን”: “መንገደኞች”: “የደም ባለሳምንት”: “የሰው ሰው “እና ሌሎችንም ወደ 40 የሚጠጉ ስራዎችን በመሪ ተዋናይነት ለመድረክ ያበቃ ሲሆን “የሰው ሰውን” ከተዋናይነት በተጨማሪ በዳይሬክተርነት ተሳትፎበታል።

በዘመኑ ለትያትር ተዋንያን ይከፈል የነበረው ደመዎዝ 230 ብር ቢሆንም ጥላሁን ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ ጥሩ ተከፋይ የሚባል ደረጃ ውስጥ የነበረና ከደመወዙ በተጨማሪ እንደማበረታቻ የኪስ ገንዘብ ይሰጠዋል። ከደበበ እሸቱ ጀምሮ ተስፋዬ ለማ፣ ሳህሉ አሰፋ ፣ ይገዙ ደስታ ራስ ትያትርን በስራ አስኪያጅነት በመሩበት ዘመን ሁሉ ጥላሁን ጉግሳ መንገሻ መድረክ ላይ አለ። ከሀላፊዎቹ ጋርም መልካም ግንኙነትና ጥሩ ቅርበትም ነበረው። ለእነዚህ የስራ መሪዎችም ትልቅ አክብሮት እንዳለው ይናገራል፡፡

መንጠቆ

“መንጠቆ” ጥላሁን ከሰራቸው በርካታ ስራዎች መካከል እጅግ የገነነበትና በብዙሀኑ ዘንድ እንዲታወቅ ያደረገውና በ1976 ዓ.ም ለእይታ የበቃ የመድረክ ተውኔት ሲሆን በኋላም ከመድረክ አልፎ ወደ ቴሌቪዥን የሄደ ስራ ነው። “መንጠቆ ” ከመድረክ ወርዶ በፊልም ተቀርፆ በቴሌቪዥን መታየት ቢጀምርም በ1996 ግን መልሶ ወደ መድረክ ሄዷል።

“መንጠቆ” የሞሊየር ድርሰት ሲሆን ወደ አማረኛ የመለሠው ደግሞ ደራሱ ሙላቱ ገብሩ ነበር። ጥላሁን ጉግሳ መንገሻ ፣ አይናለም ተስፋዬና ሃና ተረፈ ጥሩ አድርገው ተጫውተውታል። በዘመኑ አንድ ትያትር በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን ተወዳጁ “መንጠቆ ” ግን በሳምንት ሶስት ቀን ለተከታታይ አንድ ዓመት ያህል ተመልካቹ ሳይቀንስና ገቢው ሳይጓደል የመታየት እድል ነበረው። “መንጠቆ” ዛሬም ድረስ ጥላሁን የሚወደውና በተመለከተው ቁጥር የሚስቅበት ዘመን የማይሽረው ስራው ነው።

Tilahun Gugssa Photo

የማስታወቂያው ዓለም

ጥላሁን ጉግሣ መንገሻ ከመድረክ ተዋናይነት፣ ከደራሲነትና ከዳይሬክተርነት ባሻገር የተጨበጨበለት የማስታወቂያ ባለሙያም ነው። በኢትዮጵያ የማስታወቂያ ታሪክ ውስጥ ከአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ” አንበሳ የማስታወቂያ ድርጅት” ቀጥሎ ከዛሬ 29 ዓመት በፊት በ1986 ዓ.ም ሁለተኛው ህጋዊ ፈቃድ አውጥቶ መንቀሳቀስ የቻለ ሰው ነው። የመጀመሪያ የማስታወቂያ ስራውን የሰራው በአቶ ውብሸት ወርቃለማው ጋባዥነት ሲሆን ከዚህ በኋላም የዘፋኞችን የካሴት ማስታወቂያዎችና ሌሎችንም አልፎ አልፎ ይሰራ ነበር። ጥላሁን በሃገራችን ውስጥ ዛሬም ድረስ ማስታወቂያን ጥሩ አድርገው ከሚሰሩ ሰዎች መካከል ተወዳዳሪ ነው። ጥላሁን የሁለት ታላላቅ ባለሙያዎች ውጤት ነው ( በማስታወቂያው ዓለም የጋሽ ውብሸት ወርቃለማሁ እና በትያትሩ ዓለም የጋሽ መላኩ አሻግሬ) እነኝህን ሰዎች ዘወትር የሚያከብራቸውና የሚያመሠግናቸው ሲሆን ዛሬ ለደረሰበት ስኬት እጁን ይዘው እውቀትን የለገሱት አስተማሪዎቹ ነበሩ፡፡

ቤቶች

ድንቅ በሆነ አተዋወን ፣ በበሰለ የመድረክ አያያዙና በሚያስገመግም መረዋ ድምፁ የሚታወቀው ጥላሁን ጉግሣ መንገሻ “ቤቶች” የተሰኘ በኢትዮጵያ ቴሌቪዠን አሁንም ድረስ የሚተላለፍ ተከታታይ ሲትኮምን ለህዝብ እንካችሁ ብሏል። “ቤቶች” መታየት የጀመረው በ2004 ዓ.ም ሲሆን ወደ አስራ አንድ (11) ዓመታትን አስቆጥሯል። ጥላሁን በቤቶች ድራማ ላይ በተዋናይነት ከመሳተፉ በዘለለ ከክፍል አንድ ጀምሮ የበርካታ ክፍሎችን ድርሰት ያዘጋጀውም ሆነ ዳይሬክት ያደረገው እራሱ ነው። በዘመኑ ተከታታይ የቴሌቪዠን ድራማን ለመጀመር ለተዋንያኑም ለተመልካቹም ሆነ ለጣቢያው ያልተለመደና አዲስ ስራ በመሆኑ እጅግ ፈታኝ ነበር። ይህም በቶሎ ሰዎች ጋር እንዳይደርስ አድርጎት ቆይቷል። ዛሬ ግን “ቤቶች በብዙሃኑ ተወዶ እና ተመርጦ የሚታይ እያዝናና የሚያስተምር ቆንጆ ስራ ነው።

ዳግም ወደ ትምህርት

ጥላሁን ትምህርቱን አቋርጦ ለተጠራበት ጥበብ ደፋ ቀና ሲል ዘመናት ቢነጉዱም ትምህርት እድሜ አይገድበውምና ዝቅ ብሎ ተምሮ በጥሩ ውጤት ማትሪክን ዳግም መፈተን ችሏል። በዘመኑ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት 241 ቢሆንም ጥላሁን ግን 370 በማምጣት በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ምደባ ተደርጎለታል። ጥላሁን፣ የመማር ፍላጎቱ ትያትር ነበርና በ2003 ዓም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኤክስቴንሽን መርሀ- ግብር ትያትሪካል አርትን ማጥናት ጀመረ ።ጥላሁን ከዚህ ጊዜ በኋላ ወደ ትምህርቱ ዓለም የተመለሰው ለወረቀት ሳይሆን አዲስ ነገርን ወደ ህይወቱ ለመጨመርና ትወና በትምህርት ሲታገዝ የተሻለ ይሆናል ብሎ በማመኑ ነውና ሲማር ትያትርን እንደሚያውቅ ሰው እንደአንጋፋና ታዋቂ ሆኖ ሳይሆን እንደ አዲስ ተማሪ ሰዓቱን አክብሮ ለመምህራን ዝቅ ብሎ ታዞ ነበር። በ2007 ዓም የመጀመሪያ ዲግሪውን በጥሩ ነጥብ መያዝ የቻለው ጥላሁን ሁለተኛ ዲግሪውን በሚቀጥለው ዓመት ለመያዝ በትምህርት ላይ ይገኛል።

ጥላሁን ጉግሣ መንገሻ በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ኢንደስትሪ ውስጥ የበኩሉን አበርክቶ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን በተለይ ለልጆችና ለታዳጊዎች መንገድ ጠራጊ ነው። አዳዲስ ስራዎችን በአዳዲስ ልጆች ይዞ በመምጣት ላይ የሚመሰከርለት ነው። እርሱ ዛሬ ለደረሰበት ክብር እንዲበቃ ያደረጉትና ከባዶ አንስተው እጁን ይዘው ያወጡት አንጋፋ ባለሙያዎች ነበሩና በተራው አቅሙ ኖሯቸው ግን የተደበቁ የማይታወቁና ላልታዩ ታዳጊዎችና ህፃናት እድል በመስጠት በጥበብ ቤት እንዲያድጉ ህዝብ እንዲያውቃቸውና የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩ በማድረግ ብዙ ሰርቷል ። ወደፊትም ህልም አለው።

ጥላሁን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በልጆች ፕሮግራምና በመዝናኛው ቻናል በቅርቡ ለእይታ የበቃ እድሜያቸው ከ5-12 ለሆኑ የታዳጊ ልጆች የትወና ውድድር አዘጋጅቶልናል። ዛሬም ስለታዳጊዎች ያስባል። ዛሬም ከመላው ኢትዮጵያ ተገኝተው የተሰባሰቡ ኪነጥበብን የሚረከቡና የሚያሳድጉ ህፃናትና ታዳጊዎች በውስጣቸው ያለውን አቅምና ችሎታ እንዲያወጡ ድልድይ በመሆን ላይ ይገኛል። “ኢትዮጵያን ስላገለገሉ ፤ ኢትዮጵያ ታመሰግንዎታለች” በሚለው የሽልማት ፕሮግራም ላይ አንጋፋው አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ በሙያቸው ለአገራቸው ላበረከቱት አስተዋፅዎ በጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር አብይ አህመድ(ዶ/ር) እጅ ሽልማት ከተበረከተላቸው የጥበብ ሰዎች መካከል አንዱ ነው።

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ጥላሁን ጉግሳ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ብቅ ካሉ የኪነጥበብ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ይህ ዘመን ብዙ ሊነገርለት የሚገባ በርካታ የጥበብ እንቅስቃሴዎች የታዩበት በመሆኑ አንዳንዶች ወርቃማው ዘመን ይሉታል፡፡ ጥላሁን በዚህ ዘመን ብዙ ዋጋ ከፍሎ ዛሬም ሙያውን ወዶ እያገለገለ ይገኛል፡፡ 40 አመት በላይ በጽናት መቆም አርአያ የሚያሰኝ ነው፡፡ ታዲያ ጥላሁን በትወና ብቻ አይወሰንም እግዚአብሄር የሰጠውን ድምጽ ለማስታወቂያ ተጠቅሞበታል፡፡ የቴአትር ሙያ ላይ ብቻ ተደግፎ ህይወትን መግፋት አዳጋች በመሆኑ ጥላሁን ከ29 አመት በፊት ማስታወቂያ በማንበብ ራሱንም ሆነ ቤተሰቡን ሲያስተዳድር ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያ አንዱ ታሪክ ነው፡፡ በሰዎች ታሪክ ዘመን፤ የወቅቱ ሁኔታዎች ብሎም አስተሳሰብን ማየት ይቻላል፡፡

በእኛ ጥናት የ1970ዎቹና እና የ1980ዎቹ ብሎም 1990ዎቹ ወርቆች በአግባቡ ከትልቅ ሳጥን ውስጥ እንዲቀመጡ አልተደረገም፡፡ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ግን በዝርዝር ስራቸው አይቀመጥም፡፡ በይሉኝታ የሚሸበቡት ሲደበቁ ታሪካቸው ተረስቶ ይቀርና የት አሉ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በሀገራችን የሰነድ አያያዛችን ደካማ ብቻ ሳይሆን ሰነዱ ራሱ የለም፡፡ በመሆኑም የሰው ታሪክ የሀገር ታሪክ ነውና በጥላሁን ዘመን የነበሩ ሰዎችን እያሰባሰብን ታሪካቸውን ከወርቃማው መዝገብ ላይ እያሳፈርን እንገኛለን፡፡ ጥላሁን ለትውልዱ ብዙ ያስተምራል፡፡ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችም ላይ በአርት ሚኒስትሪ ውስጥ በመግባት ወንጌል እንዲዳረስ አድርጓል፡፡ መንፈሳዊ ድራማዎችን በመስራትም ሰዎች ወደ እግዚአብሄር መንግስት እንዲመጡ የተቻለውን ጥሯል፡፡ እንግዲህ ባለሙያ ማለት ሁለገብ ነውና ጥላሁን ሁሉን አቀፍ በሆነው የኪነጥበብ እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያኖረ ነው፡፡ በዚህ ስራው እንዲቀጥል ደግሞ ይህን ታሪካዊ ሰነድ ለትውልዱ አስቀምጠናል፡፡ ዛሬ የሚሰራው በጎ የጥበብ ስራ የነገው ትውልድ የሚቀበለው ነውና ጥላሁን ለዚህ አስተዋጽኦ ልናከብረው እንወዳለን፡፡ ነጮች በዘመናዊ መንገድ መጥተው ቀድመውን ታሪኩን ሳይጽፉት እኛ ሰንደነዋል፡፡ ይህ ጽሁፍ በእዝራ እጅጉ እና በዘቢባ ሁሴን የተጻፈ ሲሆን ዛሬ ሀሙስ ሀምሌ 27 2015 በተወዳጅ ሚድያ ዲጂታል ሚድያዎች ለመሰነድ የበቃ ነው፡፡ አስፈላጊ መሻሻሎች የሚደረግበት ይሆናል፡፡

One thought on “ጥላሁን ጉግሳ መንገሻ

  1. በጣም አስተማሪ ታሪክ ነው።
    እኛ የአሁኑ ትውልድ ገንዘብ ልናደርገው የሚገባ ትልቅ የህይወት ልምድ አካፈልከን ተባረክ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *