ጌትነት እንየው

ጌትነት እንየው

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬ 310 ሰዎችን እያፈላለግን የሰነድን ሲሆን በዚህ ስራችንም ጠንክረን ቀጥለንበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ በማለት አምና በ2014 ታሪኮቹን አሳትመን ያሳራጨን ሲሆን ብዙዎችም ማመሳከሪያ መጽሀፍ እያደረጉት ነው፡፡ ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ ምን ታሪክ አለኝ የሚሉ ሰዎችን እያሳመንን አስገራሚ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን እያወጣን እያከበርን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ በህይወት እያለ ታሪኩ የማይሰነድ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፡፡ በዚህ አያያዛችን በመቀጠል መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ በዚህ ጥራዝ የህይወት ታሪካቸው ከተካተተላቸው መካከል ጸሀፌ-ተውኔትና ተዋናይ ጌትነት እንየው ነው፡፡ ጌትነት ባለፉት 40 አመታት በሙያው ትልቅ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

ጌትነት እንየው ባለ ብዙ መልክ የጥበብ ስብእና ያለው ነው። ተውኔት ይፅፋል፣ ያዘጋጃል፣ ይተውናል። ግጥም ይፅፋል ።ደግሞም ደራሲ ነው።ለሃገራችን የኪነ ጥበብ ጉዞ ሁለገብ አስተዋፅኦ ከሚያበረክቱ የሀገራችን ከያኒዎች መካከል አንዱና ግንባር ቀደም ነው። ብዙዎች የቃላት ሃብት አለው ይሉታል። ቴአትርን ማዘመን ፤ ለቴአትር ህይወት መስጠትን ደግሞ ተክኖበታል። ታላቁ ባለቅኔ ጌትነት እንየው። የህይወት ታሪኩን እዝራ እጅጉ እና ዘቢባ ሁሴን ሰንደውታል፡፡

ውልደትና እድገት

ጌትነት እንየው ከጎጃም ምድር የፈለቀ ጠቢብ ነው።ወላጆቹ አርሶ አደሮች እርሱም የገበሬ ልጅ ነው። በደብረማርቆስ ከተማ አብማ ማርያም በምትባል መንደር በ1950 ዓ.ም ተወልዷል። ጌትነት ያደገው ከታላቅ እህቱ እና ከባለቤቷ ጋር ደብረማርቆስ ከተማ ሲሆን በ1964 ዓ.ም የእህቱ ባል በስራ ምክንያት ወደ ጅማ ሲዘዋወር ጌትነትም ከእህቱና ከባለቤቷ ጋር ወደ አባጅፋር ሃገር ጂማ ተጓዘ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በጎጃም፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በጅማ ተምሯል።ገና በለጋ እድሜው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለ የተጠናወተው የኪነ-ጥበብ አባዜ በጅማም አብሮት ነበር።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

ጌትነት ትምህርቱን አጠናቆም በጥሩ ውጤት ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ችሏል። በ1971 አ.ም የመጀመሪያ ምርጫው የሆነውን የትያትር ጥበብን ማጥናት ቀጠለ። በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም የግቢውን ባህል ማዕከል እንደርሱ በሚገባ የተጠቀመበት አልነበረም። ባህል ማዕከል ራሱን የሚፈትሽበት እና ራሱን የቀረፀበት ትወናን በማንያዘዋል እንዳሻው “በጠልፎ በኪሴ” ዝግጅት የጀመረበት የራሱንም የመጀመሪያ ተውኔት “ስንብትን” አዘጋጅቶ ለመድረክ ያበቃበት ባለውለታው ስፍራ ነበር።

ጌትነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲማር ዘወትር ኬኔዲ ላይብረሪ እየገባ በርካታ መፅሃፍትን ያነብ ነበር። አባኮስትር የተጠነሰሰው ያኔ ነው። አባኮስትር የካቲት መፅሄትን ሲያነብ ያገኘውና የተሳበበት ሀሳብን ያነሳበት ስራው ነበር።

ጌትነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ትምህርቱን በ1974 . ተመርቆ ወጥቶ በ1975 ዓም ለተመረቁ ተማሪዎች የመመረቂያ እለት ስለ እናት ፣ ስለ ሃገር፣ ስለማገልገል የሚሰብክ መዝሙርን አዘጋጅቶ ነበር። ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወዲያው በዝና እንጂ በውል በማያውቀው ብሄራዊ ትያትር ቤት ገብቶ ህልሙን እውን ማድረግ ጀመረ። በብሄራዊ ትያትር በነበረው ቆይታም ከተመልካች አእምሮ ውስጥ በጉልህ የተጻፉ ስራውን ማቅረብ ችሏል፡፡

ጌትነት ጎበዝ ገጣሚም ነው። ግጥምን የሚያነብበት መንገድ ከማንም ጋር የማይመሳሰል የራሱ ዜማ ያለው ፣ ወኔውና ስሜቱ ከነድምፀቱ እጅግ የሚማርክና የሚነዝር ነው ።

አበርክቶዎች

የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ዋርካ !ታላቁ ከያኒ ፀሐፊ ተውኔት ጌትነት እንየው በቴአትር ድርሰት ፣ በዝግጅት ፣ በትወና እና በገጣሚነት ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ በርካታ ጥንቅቅ ያሉ ስራዎችን ያበረከተ ፣ ሥነ – ሥርዓት ሞልቶ የተረፈው ጨዋ ፣ ስራዎቹ በፍቅር የሚታዩለት ፣ የኪነጥበብ ታላቅ ሰው ነው። ከስራዎቹ ውስጥ ፦

“ውበትን_ፍለጋ “

ይህ የጌትነት እንየው ድንቅ ተውኔት ሲሆን ግሩም አድርጎ ፅፎት ድንቅ አድርጎም አዘጋጅቶታል። ይኼ ቴአትር የመድረክ ዕይታው ሲጠናቀቅ ወደፊልም ተቀይሮም ተሰርቷል። ወደፊልም ሲቀየር ጌትነት እንየው የመሪ ተዋናዩን ” ይገረሙ ” የተሰኘውን ገፀ ባህሪ ወክሎ ተውኗል። ቴዎድሮስ ተስፋዬም ፊልሙን ዳይሬክት አድርጎለታል።

“ውበትን ፍለጋ” ጌትነት ከሰባት አመት በላይ የለፋበትና ውጤት ያገኘበት ተወዳጅ ተውኔት ነበር ። የኔ የሚለው እምነትና ማንነቱም የተንፀባረቀበት ስራ ነበር። የአፃፃፍ ቴክኒኩ ከመምህሩ መንግስቱ ለማ ያገኘውን እውቀትም ተግባራዊ ያደረገበት ነው።

“በላይ_ዘለቀ” (አባኮስትር)

ይህን ቴአትር ጌትነት መድረክ ላይ ሲተውነው : በሚያስገመግም ድምፁ መድረኩ ላይ ጎብለል ጎብለል እያለ ሲምነሸነሽበትና ሲሞላው እጅግ ድንቅ ነው። ጌትነት እንየው በላይ ዘለቀን ሲተውን ጥላሁን ገሰሰን በፍቅር ያንበረከከ በስራው ያሳመነ እና ያስጨበጨበ ሰው ነበር። ጥላሁን ገሰሰ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ መድረክ ላይ የተመለከተው ሁሉ እጅግ የተደመመበት ታላቅ ስራ ነበር።

” የእግዜር_ጣት”

ጌትነት እንየው የፃፈው ትያትር ሲሆን በዚህ ተውኔት ላይ ተስፋዬ ገ/ሃና ፣ አበባየሁ ታደሰ ፣ ስናፍቅሽ ተስፋዬ ፣ ህንፀተ ታደሰ እና ሱራፌል ወንድሙ ድንቅ ትወናቸውን አሳይተውበታል። የድራማው ዋና ጭብጥ እግዚአብሔር ከፃፈው ውጪ ምንም ነገር ሊፈፀም አይችልም የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍና ድንቅ አስተማሪ ቴአትር ነው።

“የቴዎድሮስ_ራዕይ”

“ወይ_አዲስ_አበባ”

ይህ በ1996 ዓም የብሄራዊ ትያትር ቤት ለእድሳት ተዘግቶ ሲከፈት በአዲስ ስራ መከፈት አለበት ተብሎ በመታሰቡ በርካታ ተዋንያን የተሳተፉበት በጌትነት የተዘጋጀ ስራ ነው ።

ተውኔቱ የአፄ ሀይለስላሴን ፣ የደርግንና የኢህአዴግን የሶስቱንም መንግስታት የአገዛዝ ዘመን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሙዚቃዊ ድራማ ሲሆን ጌትነት ፅፎና አዘጋጅቶ ከጨረሰ በኋላ ለዕይታ ሊበቃ በነበረበት ሰዓት በጊዜው መድረክ ላይ እንዳይታይ ቀጭን ትዕዛዝ ተላልፎ ታግዶበታል።

ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ለእይታ የበቁ አጫጭርና የሙሉ ግዜ ተውኔቶች

  • ስንብት አአዩ የባህል ማዕከል1974
  • የግርማ ቀላቢት በብሄራዊ ትያትር ቤት ለእይታ የቀረበ 1974
  • እንቁላል በብሄራዊ ትያትር ቤት እና በአሜሪካን ሀገር ለእይታ የቀረበ 1978-81
  • (final moment) እንግሊዘኛ ሲሆን ወደ አማርኛ ሲመለስ “እውነተኛ ቅፅበት ” በብሄራዊ ትያትር ቤት: ካሜሮንና ስዊዲን ሃገር ለእይታ የቀረበ
  • ዲሞቴራፒ በብሄራዊ ትያትር ቤት ለእይታ የቀረበ 1985
  • ሃምሳ አመት ስንት ነው? በአ.አ ዩኒቨርሲቲ (50ኛ ዓመት ክብረ በዓል

ጌትነት ከተወነባቸው ቴአትሮች መካከል ፦

  • ባለካባ እና ባለዳባ ፣ አሉላ አባነጋ ፣ ነፃ ወንጀለኞች ፣የቬኑሱ ነጋዴ ፣
  • የእጮኛው ሚዜ ፣ አንድ ጡት ፣ ውጫሌ አስራሰባት ፣ እርጉም ሀዋርያ እና ሐምሌት ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።

በዝግጅት ከተሳተፈባቸው ተውኔቶች ውስጥ ፦

  • የለሊት እርግቦች ፣ የእግዜር ጣት ፣ ውበትን ፍለጋ ፣ ምስጢረኞቹ ፣ ሕንደኬ ፣የቴዎድሮስ ራዕይ ፣ አዙሪት ፣ አባትየው ( ትርጉም ተውኔት ) አዲስ ፀሐይ እና
  • እቴጌ ጣይቱ ጀግና አዘጋጅ መሆኑን ያስመሰከረበት ስራዎቹ ሲሆኑ እነዚህንና ሌሎች ያልተካተቱ ቴአትሮች ላይ በመሪ ተዋናይነት በብቃት ተውኗል።

ጌትነት እንየው ከመድረክ ቲአትሮች በተጨማሪ ብዛት ያላቸው አጫጭር ልብ ወለዶችን፣ አጫጭር የሬዲዮና የቴሌቪዥን ሥራዎችን ለህዝብ አበርክቷል፣

  • “ላይመለስ”፣ “ዲሞቴራፒ”፣ “የቅርብ ሩቅ” እና ለ13 ተከታታይ ሳምንታት የቀረበው፣ “ጥንዶቹ” የተሰኙ የሬዲዮ ድራማዎች በብዙኃን የሬዲዮ ተደራሲያን ዘንድ እንዲታወቅ አድርጎታል::

ከእነዚህ ውስጥ “ላይመለስ” እና “የቅርብ ሩቅ” በሚል ርዕስ የሚታወቁት ድራማዎች በአገራችን ተከስቶ በነበረው ረሀብ ላይ የሚያጠነጥኑ ሥራዎች ሲሆኑ፣ በተለይ “ላይመለስ” የሚለው ሥራ በሬዲዮ ከመቅረቡ በፊት በቴሌቪዥን መታየቱ ይታወሳል፡፡

ጌትነት በሬዲዮ የመጻሕፍት ዓለም ፕሮግራም ላይ የሰርቅ ዳንኤልን፣ “ቆንጆዎቹ”ን ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ መተረኩም ይታወቃል፡፡ የአተራረክ ስልቱ እጅግ በጣም ማራኪ በመሆኑ በጊዜው ከፍተኛ እውቅናን አስገኝቶለት ነበር፡፡ በርካታ የሙዚቃ ግጥሞችን ለሙዚቀኞች እንካችሁም ብሏል።

ጌትነት ለሀገሩ ያለው ፍቅር ልዩ ነው፡፡ በጥበባቸው ለህዝብ ከሚደርሱ ተዋንያን መካከል አንዱ ነው። ኢትዮጵያን በብእሩ አሞካሽቷታል። በነጎድጎዳማ ድምፁ አነብንቦላታል። በወኔ ገልጿታል። ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሄ ብሎ በግጥሞቹ ተንፍሶልናል። አስቆናል። ደግሞም አስለቅሶናል።

ምስጋናና ሽልማት

ጸሐፌ- ተውኔት፣ ገጣሚ፣ ተዋናይ እና አዘጋጅ ጌትነት እንየው ለጥበብ ላበረከተው አስተዋጽዖ በርካታ የእውቅና ምስጋናን ተችሮበታል፡፡ የአማራ ክልል ባህልና ኪነ-ጥበብ ፌስቲቫል “ለባህልና ኪነ-ጥበብ እድገት” ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆኖ የክብር የእውቅና ሽልማት ሰጥቷታል።

በ1991 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሥነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙኃን የሽልማት ድርጅት በቲአትር የረዥም ጊዜ አገልግሎት ተሸላሚም ነበር።

ጌትነት ከቲአትር ሙያ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ውጪ ወደ ተለያዩ የዓለም ሃገራት የተዟዟረ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ኬንያና ካሜሮን፣ ከአውሮፓ ስዊድንን፣ ከአሜሪካ የተለያዩ ስቴቶችን ጎብኝቷል፡፡ ወደ ቻይናም አቅንቶ የቲአትር ስልጠና ወስዶ ተመልሷል።

መዝጊያ

ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ጌትነት እንየው ዛሬም የሙያ ክብሩን እንደጠበቀ ያለ ግሩም የኪነጥበብ ሰው ነው፡፡ በትወና ክህሎቱ፤ በድርሰት እና በዝግጅት ብቃቱ ብዙ ባለሙያዎች መስክረውለታል፡፡ ስለ 1970ዎቹ አጋማሽ የሀገራችን የቴአትር ታሪክ ስናወሳ ጌትነት በዛን ዘመን ብቅ ካሉት አንዱ ነው፡፡ ጌትነት ከ1975 ጀምሮ ላለፉት 40 አመታት በጽናት ሙያው ላይ የቆየ ነው፡፡ ለዚህ ጽናቱ ልናመሰግነው ግድ ይላል፡፡ የህይወት ታሪኩንም በዚህ መልኩ የሰነድነው የጽናት ተምሳሌትነቱን ለማሳየት ነው፡፡ ስለ ጌትነት ታዳሚያንም ልዩ ፍቅር እንዳላቸው አስተውለናል፡፡ በተለይ የቴዎድሮስ ራእይ ላይ ሲተውን ሙሉ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ ታዲያ ጌትነት ከትወና እና ከዝግጅት ባሻገር ጎበዝ ገጣሚነቱም ተመስክሮለታል፡፡ እኛም ለአዲሱ ትውልድ አርአያ የሚሆን ስንል ታሪኩን ሰንደናል፡፡