ዶክተር አክሊሉ ሀብቴን የማመስገን ስነ-ስርአት ሊደረግ ነው

በሀገራችን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ1943 አ.ም ሲጀመር ከመጀመሪያዎች 13 የዲግሪ ምሩቃን አንዱ ለሆኑት ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ ማክሰኞ ታህሳስ 2 2016 አ.ም የእውቅና ስነ-ስርአት ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከለባዊ ኢንተርናሽናል አካዳሚ ጋር የእውቅና ስነ-ስርአቱን ያዘጋጁ ሲሆን የ94 አመት የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት ዶክተር አክሊሉ ሀብቴም ከእነ ቤተሰቦቻቸው በመርሀ-ግብሩ ላይ ይታደማሉ፡፡

በተፈሪ መኮንን ት/ቤት የአንደኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ ዪኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከፈት ከገቡትና ከተመረቁት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ በ1946 አ.ም ከተመረቁ በኋላም ወደ ካናዳ እና አሜሪከ በማቅናት በኤጁኬሽን እስከ ፒኤችዲ ድረስ ለመማር የቻሉ ናቸው፡፡

ዶክተር አክሊሉ ሙሉ ህይወታቸውን ሀገራቸውን ያገለገሉት በትምህርት ዘርፍ ሲሆን በተመረቁበት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲም ከመምህርነት እስከ ፕሬዚዳንትነት ለማገልገል የቻሉ ናቸው፡፡

ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ፣ ከ1946-1966 ከተማሪነት እስከ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ ሲሆን የ1966ቱ ለውጥ ከመጣም በኋላ የባህል የስፖርትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ሰርተዋል፡፡

በመቀጠልም ወደ አለም ባንክ በማቅናት በባንኩ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ኢትዮጵያዊ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር በመሆን ሙያዊ አደራቸውን ተወጥተዋል፡፡ አከታትለውም በዩኒሴፍ የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው እስከ እስከ 1987 አ.ም የጡረታ ዘመናቸው ድረስ እውቀታቸውን ሳይቆጥቡ አገልግለዋል ፡፡

ዶክተር አክሊሉ ‹‹የቀዳማዊ ሀይለስለሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ የከፍተኛ ትምህርት መቋቋምና መስፋፋት ጉዞ በኢትዮጵያ›› በሚል ርእስ በ600 ገጽ የተሰናዳ መጽሀፍ ያሳተሙ ሲሆን በብዙዎች ዘንድም ለመደነቅ የበቃ መጽሀፍ ነው፡፡

ማክሰኞ ታህሳስ 2 2016 ከቀኑ 7 ሰአት በለባዊ ኢንተርናሽናል አከዳሚ በሚደረገው የእውቅና ስነስርአት የለባዊ ኢንተርናሽናል ተማሪዎችና የተጋበዙ እንግዶች በታሙበት ልዩ ልዩ አዝናኝ እና አስተማሪ መሰናዶዎች ይቀርባሉ፡፡

የዚህ መሰናዶ የሀሳብ አመንጪ እና ስራውን በአጭር ጊዜ እውን እንዲሆን ያደረገው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሲሆን በዶክተር አክሊሉ የተጻፈውንም መጽሀፍ ወደ ድምጽ በመቀየር ከ 4 ወር በኋላ ተርኮና ፕሮዲዩስ አድርጎ እንደሚያቀርበው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ ኦድዮ ስራም ሆነ የእውቅና ስነስርአቱ ከዶክተር አክሊሉ ቤተሰቦች ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን በእውቅና ስነ-ስርአቱም እለት ዶክተር አክሊሉ መልእክት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *