ደረጄ አያሌው ሞላ

ደረጄ አያሌው ሞላ

ህልም-ትጋት-ጽናት እና ውጣ ውረድ በደረጀ ህይወት

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡

ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡

ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ አሁን ታሪኩ የሚዘከርለት ሰው ደረጀ አያሌው ሞላ ሲሆን በሚድያ ዘርፍና በሬድዮ ድራማ ዘርፍ የራሱን አሻራ ያኖረ ሰው ነው፡፡

ትውልድ ፤ ልጅነትና ትምህርት

ደረጄ አያሌው ሞላ ከአባቱ አቶ አያሌው ሞላ እና ከእናቱ ወ/ሮ ዝባብ ደምሴ ህዳር 21/1969 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ ከ22 ማዞሪያ ወረድ ብሎ ቀድሞ ቀበሌ 13 ኋላ ‘ቺቺኒያ’ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ተወለደ። የአካባቢው ወጣቶች በእግርኳስ ፍቅር ያበዱ ነበሩ፤ ክረምት ከበጋ የማይቋረጥ የእግርኳስ ውድድር ነበር፤ከዛ ባለፈ ከአጎራባች ቀበሌ ጎረምሶች ጋር በቡድን ጠብ መቆራቆስ የተዘወተረ ነበር።45 ዓመታትን በአብሮነት ከዘለቀው ትዳራቸው አራት ልጆች ላፈሩት ወላጆቹ 3ኛ ልጅ የሆነው ደረጄ አብዛኛውን የልጅነት ጊዜውን እንደ አብሮ አደጎቹ በጨዋታና በትምህርት አሳልፏል።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ካዛንቺስ በሚገኘው የቀድሞ አስፋ ወሰን /ምስራቅ ጎህ/አንደኛ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትሏል።በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበረው የላቀ የትምህርት አቀባበል ችሎታ ሳቢያ አንደኛና ሶስተኛ ክፍልን በግማሽ አመት በመጨረስ/በጊዜው በነበረው አሰራር መሰረት ደብል መትቶ/ነበር ያለፈው።በጊዜው ብዙዎችን ባስገረመ ፍጥነት የአስራ ሁለት ዓመት ታዳጊ ሳለ የቀለምና የሙያ ትምህርት ወደሚሰጥበት ወደ ምስራቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ገባ።በአራት አመታት የሀይስኩል ቆይታው የውዴታ ግዴታ ሆኖበት የቀለም ትምህርቱንና የቴክኒክና ሙያ ስልጠናውን ቢከታተልም ፍላጎቱ ወደስነፅሁፍ በማድላቱ በቀለም ትምህርቱ ላይ መዘናጋት አመጣ፤በአንፃሩ በት/ቤቱ ሚኒ ሚዲያና የስነፅሁፍ ክበብ ውስጥ የነበረው ተሳትፎና በግቢው ማህበረሰብ ዘንድ የነበረው ተቀባይነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጣ።

በሀይስኩል ቆይታው በጣም ከሚወደው የስነ-ፅሁፍ ተሳትፎ ሊያርቀው የነበረውን የቁመት ችግር እንዴት ታግሎ እንዳሸነፈው ፈፅሞ አይዘነጋውም። ብላቴናው ወደመድረክ በወጣ ቁጥር ለሌሎቹ/ለረጃጅሞቹ/ የተዘጋጀው የማንበቢያ ሳጥን ቁመቱን ስለሚውጠው ከማንበቢያ ሳጥኑ ውጭ ለመቆም ይገደድ ነበር።በቁመቱ ማጠር ሳቢያ የወረቀት ማስቀመጫ ካለውና ዘና ብሎ ለማንበብ ከሚመቸው ሳጥን ውጭ መሀል መድረክ ላይ በአንድ እጁ ማይክራፎን በሌላ እጁ የሚገለጥ ወረቀት ይዞ አንዴ ወረቀቱ አንዴ ማይክራፎን እየወደቀበት እየተደነባበረ በማንበቡና የዳኝነት ነጥብ እየተቀነሰበት አንደኝነትን በማጣቱ በተደጋጋሚ በንዴትና በዕልህ መድረክ ላይ አልቅሶአል ።

ከዕለታት ባንዱ እለት ግን ትልቅ ሽልማት በሚያስገኝ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ሲዘጋጅ ለራሱ አንድ ቃል ገባ።ከሻይቤት ያመጣውን የለስላሳ ሳጥን ከማንበቢያ ሳጥኑ ስር አስቀምጦ ላዩ ላይ በመቆም አዘጋጆችና ታዳሚዎች እየሳቁበት ግጥሙን እያቀረበ የውድድሩን ሶስት ዙሮች ካለፈ በኋላ በመጨረሻው/በፍፃሜው/ውድድር ላይ ሌላ አቀራረብ ይዞ ወደ መድረክ ወጣ። ያዘጋጀውን ባለ3 ገፅ ወቅታዊና አገራዊ ግጥም በቃሉ ሸምድዶ በከፍተኛ የራስ መተማመን ስሜት በመድረኩ ላይ እየተንጎራደደ በትወናዊ አቀራረብ ግጥሙን አቀረበ።በአንደኝነት አሸንፎ ተሸለመ።በዚያ አጋጣሚ የመፃፍ ብቻ ሳይሆን የመተወን ተሰጥኦም በውስጡ እንዳለ ተገነዘበ

አፍላነትና ራስን የመቻል ትግል

ደረጄ አያሌው ፤ ተፈጥሮ የቸረችውን ከአዳዲስ ነገሮች ጋር ፈጥኖ የመተዋወቅና ራሱን የማብቃት ክህሎት የተገነዘበው በማለዳ ነው።በአነሰተኛ ደመወዝ የሚተዳደሩትን ወላጆቹን በሁሉ ነገር ከማስቸገር ለመላቀቅ ቁርጠኛ አቋም በመያዝ በስራና በገቢ ራሱን ለመቻል የመፍጨርጨርን ትግል የጀመረውም ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ነው። ከአብሮአደጎቹ ጋር ቡሄ ጨፍሮ ባገኛት ሳንቲም ቀለምና ብሩሽ ገዝቶ ራሱ የሰራውን የእንጨት ሳጥን/ሊስትሮ ዕቃ/በመሸከም በክረምት ወራት ጫማ እየጠረገ በጋው ላይ የትምህርት መሳሪያዎቹን ወጭ በመሸፈን ‹‹ሀ..›› ብሎ የጀመረውን የስራ ዓለም በበጋው ጊዜም የቀን ትምህርቱን እየተማረ ማታ ማታ ቤት ለቤት እየሄደ ተማሪዎችን በማስጠናት የኪስ ገንዘብ በመያዝ አጠናክሮታል።

በጊዜው የእድሜ አቻዎቹ ደፍረው ያልሞከሩትን የመኪና ማሽከርከር ስልጠና ተከታትሎ በአስራ ስምንት ዓመቱ መንጃ ፍቃድ በማውጣት ሰፈርውስጥ ባለ አነስተኛ ዳቦ መጋገሪያ በሹፍርና ተቀጥሮ ወፍ ሳይንጫጫ በግፊ በምትነሳና አሮጌ ቮልስዋገን መኪና ትኩስ ዳቦ ጭኖ በየሱቁ እያዞረ ሸጧል፤የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቆ በመልቀቂያ ፈተና /በማትሪክ/ የሚፈለገውን ነጥብ ማምጣት ባልቻለ ጊዜም በሆቴል መስተንግዶ ሙያ አጭር ስልጠና ወስዶ በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ በዘመኑ ስመ-ጥር በነበረው ‘ኮንራድ’ ሆቴል ለአንድ አመት ተኩል በአስተናጋጅነት ሰርቷል።በ‘አዲስ ብሎኬትና የወለል ንጣፍ ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥም በቀን ሰራተኝነት ተቀጥሮ አገልግሏል።

ከኑሮ ዱብ ዱብ በሚተርፈው የዕረፍት ሰዓትም ከስነፅሁፍ ጋር የጀመረውን ወዳጅነት አጠናክሮ ቀጥሏል። ያገኘውን እየሰራ ከሚያገኛት ፈረንካ ላይ የልቦለድ መፃህፍትን ይሸምታል፤እንደሱ የንባብ ፍቅር ካላቸው አብሮአደጎቹ ጋር በልዋጭም በውሰትም መፃህፍትን እያፈራረቀ ከምሽት እስከ እኩለ ሌሊት በፍቅር ያነባል /’በቃህ ተኛ ዓይንህን ያምሃል’ ተብሎ በወላጆቹ ቁጣና ተግሳፅ ከመፅሀፍ የሚላቀቅበት ጊዜም ነበር/ያ ጊዜ ከማንበብ ጎን ለጎን ለራሱና ለአብሮ አደጎቹ መልሶ መላልሶ የሚያነባቸው አጫጭር ልቦለዶች ግጥሞች እና ጭውውቶችን የመፃፍ ዝንባሌውን ማሳየት፤የብዕር ስራዎቹን ይዞ ወደብዙሀን መድረኮች ብቅ ማለትም ጀመረ።አጭር ልብ-ወለድና ጭውውቶችን በኢትዮጽያ ሬዲዮ (ቅዳሜ መዝናኛ) ለለገዳዲ/ትምህርት በሬዲዮ/(ዕሁድ ጠዋት)፤በብስራተ ወንጌል ሬዲዮ (አርብ ምሽት) ፕሮግራሞች ላይ ማቅረብና በድምፅም መሳተፍ ጀመረ።

ትምህርት

በመጀመሪያው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ወደዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ አጥጋቢ ውጤት ባለማምጣቱ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ቆይቶ በቀጣዩ አመት ፈተናውን በግል በመውሰድና ውጤቱን በማሻሻል

  • በ1989 ዓ/ም ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በአማርኛ ቋንቋና በስነፅሁፍ በዲፕሎማ
  • በ2006 ዓ/ም ከአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በ ኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በአድቫንስድ ዲፕሎማ ተመርቋል።
  • የሙያ ስልጠናዎች
  • ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ኢ-መደበኛ የተሰጥኦና ክህሎት ማጠናከሪያ አጫጭር ኮርሶችንም ተከታትሏል።ለአብነት የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፦
  • በ1986 ዓ/ም በክልል 14 ባህልና ስፖርት ቢሮ የቴአትርና የስነ-ፅሁፍ ስልጠና
  • በ1995 ዓ/ም በሬዲዮ ፋና የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅነት ስልጠና
  • በ1997 ዓ/ም በዩኤንዲፒ ማህበረሰብ አቀፍ ራዲዮ አዘጋጅነት ስልጠና
  • በ2003 ዓ/ም በሲፒዩ ኮሌጅ መሰረታዊ የኮምፒዩተር ፕሮግራም አጠቃቀም ስልጠና
  • በ2012 ዓ/ም በሮይተርስ ከፍተኛ የራዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅነት የአሰልጣኞች ስልጠና እና ሌሎች የሙያ ስልጠናዎችን ተከታትሎ በአጥጋቢ ውጤት አጠናቋል።

አገር አቀፍ የስነ-ፅሁፍ ውድድሮችና ሽልማቶች

  • 1990ዓ/ም ኢትዮጽያ ሬዲዮ የዘመን መለወጫ የግጥም ውድድር 2ኛ ደረጃ አሸናፊ
  • 1991ዓ/ም በባህል/ሚ/ር የሴቶች ጉዳይ መምሪያ የድራማ ፅሁፍ ውድድር 1ኛ ደረጃ አሸናፊ
  • በ2000 ዓ/ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም ፅ/ቤት የግጥም ውድድር 1ኛ ደረጃ አሸናፊ

ግለ – ባህሪና ፍልስፍና

ደረጄ አያሌው ‘በራስ ዓለም የመኖርን ‘በራስ ባህር የመዋኘትን ’ ግለ ዕምነት የህይወቱ መርህ ያደረገ ሰው ነው።በቀላሉ ተግባቢ ቀልደኛና ተጫዋች የሚሰማውን ለመናገር የማያመነታ፤ያመነበትን ለማድረግ የማያወላዳ በጣም ግልፅ የግንባር ስጋ የሚባል ዓይነት ሰው ነው።ከፍተኛ በራስ የመተማመን ስሜት አለው።በተሰማራበት የስራ መስክ ሁሉ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በትጋት ይሰራል።

ለግጥምና ለሙዚቃ የተለየ ፍቅር ያለው የኪነ-ጥበብ አድናቂም ነው። ‘የግል ዕምነትና የህይወት ፍልስፍናዬን በመቅረፅ በኩል የጎላ ድርሻ አላቸው፤ከሞት በቀር ምንም ላያፈርሳቸው በውሰጤ ተተክለዋል’ የሚላቸው ሶስት ሀውልቶች እንዳሉትም ይናገራል። እነርሱም (1)ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ዝባብ ደምሴ/ረሂሙ አላህ/(2)አጎቱ ሰዒድ መሀመድ/ረሂሙ አላህ/ እና (3)የማትሞተው የፍቅር ከተማ ሀረር ናቸው!

የሬዲዮ ድራማ

ከልጅነት እስከ ዕውቀት ለሬዲዮ ያለው ፍቅር የተለየ ነው።በባትሪ ድንጋይ የምትሰራውን የአባቱን ፊሊፕስ ራዲዮ /ብርቅዬን/ሳይፈቀድለት መንካት መነካካት የተሸፋፈነችበትን የጨርቅ ልብስ እያወላለቀ ጣቢያ ማዙዋዙዋር ብዙ ጊዜ የተገረፈበት ግን ደሞ እርም ብሎ ሊተወው ያልቻለ ጥፋቱ ነበር።በወላጆቹ ዓይን ጥፋት የሆነው ራዲዮ መነካካት ለእርሱ ሱሱ ነበርና በቁጣም በዱላም አልተመለሰም።የኢትዮጽያ ሬዲዮን በተለይ / ለወጣቶች ከመፃህፍት ዓለም ቅዳሜ መዝናኛ እና ፖሊስና ህብረተሰብን /የማድመጥ ጉጉቱ የዘወትረ ራቡም ጥሙም ነበር።

ወቅታዊ መረጃዎችን በተለይም ደሞ ወንጀል ነክ ታሪኮችን የመከታተል ፍላጎቱም ከፍተኛ ስለነበር በየአስራአምስት ቀኑ የሚወጣውን የፖሊስና ህብረተሰብ ጋዜጣ የመግዛት ልምድ ለነበረው ጎረቤቱ በመታዘዝ በእግሩ ካዛንቺስ ድረስ እየሄደ ጋዜጣውን በመግዛት ገዠው አንብቦ ሲጨርስ እየተዋሰ ያነብ ነበር።

‘ሬዲዮ ፋና’ ከተመሰረተ ከአምስት ዐመታት በኃላ /በ1992 ዓ/ም/ጭውውትና ድራማን ለመሳሰሉት የመዝናኛ ፕሮግራሞቹ ተጨማሪ ተሳታፊዎችን ሲመለምል ደረጄ አያሌው ከ ራዲዮ ድራማ ፀሀፊያን አንዱ ሆኖ ‘ፋና’ን ተቀላቀለ። ከዛን ጊዜ ጀምሮ በፋና ውስጥ በቆየባቸው አስራ አራት አመታት ቅዳሜ ረፋድ ላይ የተደመጡ ከ25 ያላነሱ ድራማዎችን አበርክቶአል።

ለአብነትም፦ የስምዖን ቀኖች’ ‘ያልተፃፈው መንገደኛ’ ‘የዲያቢሎስ ጭስ’ ‘ጥቁርና ነጭ’ ‘እንደገና’ ‘መልክ የለሽ አባት’ ‘አፈር ለምኔ’’ ን የመሳሰሉት አጭር-ተከታታይ ድራማዎችና ፤‘መሃል ቤት’ ‘እኛን ነው ማየት’ እና ‘ቺርስ’ የተሰኙት ረጅም-ተከታታይ ድራማዎች ተጠቃሽ ናቸው።ከዛም ባለፈ በየበዓላቱ የተደመጡ በርካታ የአውዳመትና ፤በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጁ ትምህርታዊ ጭውውቶችን በመፃፍ በማዘጋጀትና በመተወን ጣቢያውና አድማጮች የማይዘነጉትን ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

ለኢትዮጽያ ሬዲዮ የቅዳሜ ከሰዓት መዝናኛ ፕሮግራምም በ2007ዓ/ም እና በ2009 ዓ/ም ‘ህልሞች’ እና ‘ሰንሰለት’ የተሰኙ ሁለት ረጃጅም /እያንዳንዳቸው ለአንድ ዓመት/ለ52 ሳምንታት/የተደመጡ ድራማዎች አበርክቷል።

ጥቂት የፊልም ድርሰቶችንም ፅፏል።እስካሁን ለዕይታ የበቃው ግን‘ውበት ለፈተና’ የተሰኘው ፊልም ብቻ ነው። በህትመት በኩልም ሁለት መፃህፍት ፅፎ ለንባብ አብቅቷል። የመጀመሪያውና በ2001 ዓ/ም የታተመው ‘መሀልየ መሀልይ ዘ ቺቺኒያ’ የተሰኘው መፅሀፉ ’ቺቺኒያ’ እየተባለ የሚጠራውን የትውልድ ሰፈሩን አስገራሚ አስደንጋጭ አሳዛኝና አስተዛዛቢ የመሸታ የዳንኪራና የዝሙት ገመናዎችን ፈልፍሎ ያወጣበት የእውነተኛ ታሪኮች ስብስብ ሲሆን በበርካታ አንባቢያን ልቦና ውስጥ ትልቅ አሻራ አሳርፎ ያለፈ መፅሀፍ ነው። ሁለተኛውና በከተሜው ህይወትና አኗኗር ላይ አዲስ ዘይቤ በፈጠረው የኮንዶሚኒየም ቤትና መኖሪያ መንደሮች ውስጥ ለውስጥ የሚከናወነውን ሽፍንፍን የገመና መጋረጃ ገላልጦ ያሳየበትና በ2009 ዓ/ም ለንባብ የበቃው ‘መሀልየ መሃልይ ዘ ኮንዶሚኒየም’ /‘ጎጆና ቆንጆ’ የተሰኘው መፅሀፉ ነው።

ጋዜጠኝነት

ብዙዎች በልጅነታቸው ለመሆን የተመኙትና የማታ ማታ ሆነው የተገኙበት ሙያ አልተገናኝቶም ሆኖባቸዋል።ደረጄ አያሌው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ‘ስሙኝ ስሙኝ’ ማለትና ግድግዳ ላይ የተለጠፈ ጋዜጣ ርዕስ እየመራረጠ በራዲዮ የሚሰማቸውን አንባቢዎችን ድምፅ እያስመሰለ ጮክ ብሎ ማንበብ ያዘወትር ነበር።የማለዳ ህልሙም ጋዜጠኛ መሆን ነበር።

ጊዜው 1993 ዓ/ም ነበር።አንድ ዕለት ሳያስበው ከሬዲዮ ፋና አማርኛ ክፍል ሀላፊ ቢሮ ተደውሎ ‹‹ትፈለጋለህ›› ተባለ፤ ፈራ ተባ እያለ ወደ ተጠራበት ቢሮ ገባ።

አለቃው ጌታቸው ሀይሉ ብዙ ነገር አውርቶታል፤ደረጄ ግን በደስታ ስካር ናላው ዞሮ ስለነበር ጌታቸው ካወራው ውስጥ የሚያስታውሰው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ‘የመስራት አቅምህን ገምግመን ውጤታማ እንደምትሆን በማመን ከዛሬ ጀምሮ በጋዜጠኝነት ቀጥረንሀል’ የሚለውን ንግግር ብቻ! የቅጥር ደብዳቤው እጁ ላይ ከደረሰ በኋላም ዓይኑን ማመን አቅቶት ነበር፤ የሰራ መደብ ጀማሪ ሪፖርተር፤ደሞዝ 595 ብር! የልጅነት ህልሙን መፍቻ ቁልፍ በእጁ መጨበጡ ‘ጋዜጠኛ’ መባሉ..ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ፈጠረበት! ዲፕሎም የለ ዲግሪ የለ የስራ ልምድ የለ ትችላለህ ብሎ በማመን ብቻ በጊዜው የኮሌጅ ምሩቆች የሚያገኙት የስራ መደብና ደሞዝ ተሰጥቶት በፋና ስራ ጀመረ፤ፋና ጋዜጠኛውን ደረጄን ፈጠረው።

በፋና ሬዲዮ ከጀማሪ ሪፖርተርነት እስከ አዘጋጅነት በሰራባቸው የአስራ አራት ዓመታት ቆይታው በፖሊስ ፤በህግና ፍትህ፤በቤተሰብ ሰዓት፤በሬዲዮ መፅሄት ፤በፍቅር ሰዓትና በሌሎች ተወዳጅና ተደማጭ ፕሮግራሞች ላይ በአዘጋጅነትና በአቅራቢነት ሰርቷል።አዳዲስና ጆሮገብ የራዲዮ ፕሮግራም ፎርማቶችን በመቅረፅ ፋናን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀዳሚና ተመራጭ ሬዲዮ ያደረጉት አመራርና ባለሙያዎች ድምር አቅም የታየበትንና በሀገራችን የሬዲዮ ፕሮግራም ታሪክ ሁለትና ሶስት አድማጮች በቀጥታ ስልክ መስመር ገብተው የሚወያዩበትን ‘እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ?’ የተሰኘ አዲስና ፈር ቀዳጅ /phone in discussion & debate/ ፕሮግራም በማስተዋወቅና የመጀመሪያው አወያይ በመሆን ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ አበርክቷል።

በ1997 ዓ/ም ሀገራዊ ምርጫ ማግስት በወቅታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ደረጄና የፋና ስራ አመራር አካላት መጣጣም ባለመቻላቸው ከፍተኛ ጫና ደርሶበታል፤ስራውን ለቆ በሞያሌ በኩል ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ ተሰዶ ነበር፤ከሁለት ወራት በኋላ ግን በሁኔታዎች አስገዳጅነት ወደአዲስ አበባ ተመልሶ በግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ እየሰራ ከእጅ ወደአፍ በሚባል ገቢ ልጁን ለማሳደግ ከኑሮ ጋር መራራ ትግል ታግሏል።

በጊዜው በሳልና ተነባቢ የነበረው የ ‘እምቢልታ’ ጋዜጣ ም/ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል።ቃልኪዳን እና ሮዳስ መፅሄቶች ላይ በአዘጋጅነት አገልግሏል። የጊዜውን ተወዳጅ ተከታታይ ፊልሞች ታሪክ በአማርኛ እየተረጎመ አስነብቧል። በተለያዩ የወንጀል ክሶች ተከሷል፤ታስሯል።የወቅቱን የአገዛዝ ፖለቲካ በመቃወሙና፤ለሹማምንቱ ጎንበስ ቀንጠስ ባለማለቱ መስራት እየቻለ እንዳይሰራ ተደርጓል፤ ከህፃን ልጁ ጋር ለራብ ለጥማት እስከመዳረግ ድረስ ብዙ ፈተና ገጥሞታል።ግፍና በደሉ ያበቃለት በ2003 ዓ/ም ዳግም ወደፋና ተመልሶ እንዲሰራ ተጠይቆ ከተስማማና ወደስራው ከተመለሰ በኋላ ነው።

ከመጋቢት 2009 ዓ/ም ጀምሮ በራሱ ፈቃድ ሬዲዮ ፋናን ለቋል። ለአጭር ጊዜ በብስራት ኤፍ ኤም ከፍተኛ ፕሮግራም አዘጋጅ እንዲሁም በአሀዱ ራዲዮ የዜና ኤዲተር ሆኖ ከሰራ በኋላ ከጥቅምት 2011 ዓ/ም ጀምሮ አንጋፋውን የኢትዮጽያ ሬዲዮ በመቀላቀል የአማርኛ መዝናኛ ፕሮግራም ከፍተኛ አዘጋጅ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።በተጓዳኝ የድራማ ድርሰትና ሌሎች የስነ-ፅሁፍ ስራዎቹን መስራቱንም አጠናክሮ ቀጥሏል።

ደረጄ አያሌው ከቀድሞ የፍቅር ህይወቱ የበኩር ልጁን ወልዶ ከተለያየ በኋላ በ2007 ዓ/ም ከወ/ሮ ትዕግስት አየለ ጋር ከመሰረተው ትዳር ሁለት ልጆችን በማፍራት የሶስት ሴት ልጆች አባት ሆኗል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *