ከተመሰረተ 25 አመት ያስቆጠረው እና እስከ ዛሬ ከ 200 በላይ መጽሀፎችን ያሳተመው ጸሀይ አሳታሚ በትናትናው እለት ታላላቅ እንግዶች በታደሙበት በሎስ አንጀለስ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡
የአሳታሚ ድርጅቱ መስራች እና ባለቤት ኤሊያስ ወንድሙም ይህ እውቅና ለእኔ ሳይሆን የኢትዮጵያ ገጽታ የሚቀይር ነው ሲል ለተወዳጅ ሚድያ ሀሳቡን ሰጥቷል፡፡ ታላላቅ የሎስ አንጀለስ ከተማ ታዋቂ ሰዎችና የከተማዋ ከፍተኛ ባለስልጣናት በታደሙበት በተከናወነው በዚህ ስነ-ስርአት ኤሊያስ ወንድሙ ብቸኛው አፍሪካዊ የመጽሀፍ አሳታሚ የሚል ትልቅ ሙገሳ አግኝቷል፡፡
ኤሊያስ ወንድሙ ሀገር ቤት ሳለ የእውቀት በር የተሰኘ የመጽሀፍ መድብር ውስጥ በልጅነቱ መገኘቱ ለንባብ ታላቅ ፍቅር እንዳደረበት ይናገራል፡፡ በመቀጠልም ኤሊያስ በ1980ዎቹ አጋማሽ ይወጡ በነበሩ የህትመት ውጤቶች ላይ መሳተፉን ይናገራል፡፡ በሂደትም የዛሬ 29 አመት በ1986 ወደ ባህር ማዶ አቅንቶ ከ 4 አመት በኋላ በ1990 ጸሀይ አሳታሚን ጀመረ ፡፡
ኤሊያስ ወንድሙ ለሀገሩ ትልቅ ፍቅር ያለው የኢትዮጵያ ታሪክ ለአለም መነገር አለበት ብሎ ያምን ስለነበር ካሳተማቸው መጽሀፎች አብዛኛዎቹ በእንግሊዝኛ ለህትመት የበቁ ነበሩ፡፡ እርሱ እንደሚናገረው መጽሀፍን አሳትሞ ሀብታም መሆን ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡ ነገር ግን የሀገርን ያልተነገረ ታሪክ ለማሳየት እና ትርክቶችንም በትክክለኛው መንገድ ለማቅረብ ጸሀይ አሳታሚ የበኩሉን ትልቅ አሻራ በማኖር ላይ ይገኛል ብሎናል፡፡
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በቅርቡ በሚያሳትመው መዝገበ-አእምሮ መጽሀፍ ላይ የኤሊያስን ታሪክ የምናካትት ሲሆን እንደ ወትሮውም በቅርቡ የኤሊያስን ታሪክ ይዘን እንቀርባለን፡፡