ተሾመ ብርሀኑ ከማል

ተሾመ ብርሀኑ ከማል

የሀገር ባለውለታ

ከንባብ ከምርምር ከጽሁፍ ያልተለዩት ደራሲ ተሾመ ብርሀኑ ከማል እንደጋሽ ተሾመ አይነት ታታሪ ሰው ካወቃችሁ ንገሩን፡፡ አቶ ተሾመ ብርሀኑ በድርሰት እና ስነጽሁፍ ዘርፍ ከ45 አመት በላይ  የደከሙ ለወጣቱ አርአያ የሚሆኑ  ባለውለታ ናቸው፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የደራሲ ተሾመ ብርሀኑ ከማልን ታሪክ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡ 

ትውልድና ልጅነት 

ተሾመ ብርሃኑ ከማል አደም፣ ሐሙስ ግንቦት 16 ቀን 1943፣ ከቀኑ 11፡00 በቀድሞው ሰሜን ወሎ በዋግ አውራጃ ዋና ከተማ፣  በአያቱ በባዩሽ ዓብዱራህማን ኽያሩ ቤት ተወለደ፡፡ አያቱ ቤት የተወለደው እናቱ የሐሙስ (ኸሚስ) ቂጣ የሚሆን ስንዴ  ልትፈጭ ሄዳ ሲሆን አያቱ የመጀመሪያ ስሙን ‹‹አወቀ›› ብላ አወጣችለት፡፡ ሆኖም ከእርሷ በስተቀር ሌላ ሰው ጠርቶት  አያውቅም፡፡  አባቱ  ‹‹ሐሚድ  ነው  የምለው›› ብሎ  ስም  አወጣለት፡፡  ሆኖም  ከእርሱ  በስተቀር  በዚያ  ስም  የሚጠራው  አልነበረም፡፡

‹‹ሙሐመድ ኑር ብርሃኑ›› ተብሎ እንዲጠራም አደረገች፡፡ በዚህ ስም  በዘመዶቹም፣ በጓደኞቹም ታወቀ፡፡ ለ18  ዓመታት ያህልም ተጠራበት፡፡  ሙሐመድ ኑር ብርሃኑ ተብሎ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቋል፡፡  ቁርዓን ቤትም ቀርቷል፡፡   ከ18  ዓመት  ዕድሜው  በኋላ  ግን  ስሙን  ተሾመ  ብርሃኑ  ብሎ  ቀየረ፡፡  ሆኖም  በዚህም  ምክንያት  ሙስሊም  ዘመዶቹ   ሙሐመድ ኑር ብርሃኑ እያሉ ሲጠሩት በትምህርትና በሥራ ዓለም የሚያውቁት ግን ተሾመ ብርሃኑ ብለው ይጠሩታል፡፡ ሁሉም  ህጋዊ ሰነዶቸ በተሾመ ብርሃኑ ስም የሰፈሩ ናቸው፡፡

ተረት እየሰሙ ቂጣ መብላት 

ተሾመ ብርሃኑ የህጻንነት ዕድሜውን ያሳለፈው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነበር፡ ከሁሉ አስቀድሞ አባቱና እናቱ እርሱ የአራት  ወይም  የአምስት  ዓመት  ልጅ  ሆነው  ተፋቱ፡፡  ሥራ  ያልነበራት  እናቱ  (ወርቂያ  አሕመድ)  የትልቁ  ትልቅ  ወንድሙን  (ዓብዱራሕማን ብርሃኑ) እና ትልቅ እህቱ (ሳዕዲያ ብርሃኑን) ጨምራ ለማሳደግ ጥጥ እየፈተለች ነጠላና ኩታ አሠርታ በመሸጥ   በብቸኝነት ማሳደግ ጀመረች፡፡ ቀጥላም ቅመማ ቅመም እየያዘች ወደ ገበያ በመውጣት መቸርቸር ጀመረች፡፡ ከዚያ ጋር  ድርም ጥለትም፣ የኮዳና የነሐስ ቀለበትና ሌሎች ጌጦችም ትሸጥ ነበር፡፡ ያኔ ካፒታሏ ከ10 ብር አይበልጥም ነበር፡፡ ነገር ግን  እህል ርካሽ ስለነበር ሁለት ብርም ሦስት ብርም ብታተርፍ ለሳምንት ቀለብ ባይበቃም ተቸግሮ ይበቃ ነበር፡፡ ቅርስ እፍኝ  ቆሎ፣ ምሳ እሩብ እንጀራ፣ ራት ሩብ እንጀራ ወይ ቂጣ ከተገኘ በቂ ነበር፡፡

ራት እፍኝ የአተር ቆሎ ሊሆን ይችላል፡፡ እርሱም  ከሌለ ከሌለ ተረት እያወሩ እንቅልፍ እንዲወስድ የማድረግ ዘዴም ነበር፡፡ያኔ አተር በኪሎ አሥር አምስት ሳንቲም ቢሸጥና  ለሳምንት የሚበቃ ቢሆንም አስር ሳንቲም ማግኘት ቀላል አልነበረም፡፡ እንቁላል በአምስት ሳንቲም ቢሸጥም በአመት አንድ ጊዜ  ወይም ሁለት ጊዜ ካልሆነ አይገኝም፡፡ ዶሮማ አሥር ወይም አሥራ አምስት ሳንቲም ቢሆንም አይታሰብም፡፡ ሲጀመር ወንድ በሌለበት  ዶሮ አይታረድም፡፡ ከዚያ ላይ በአካባቢው ርሃብ የሚከሰተው በየጊዜው ነው፡፡ አንበጣ በየዓመቱ እየመጣ እህሉን ያጠፋዋል፡፡  ስለዚህ ከሚያዚያና ግንቦት ጀምሮ እስከ ሐምሌ ድረስ ርሃብ ነው፡፡ በሐምሌ ወር እንዲደርስ የተተከለው ጎመን፣ በቆሎ፣ ዱባ፣  የጫካ ሥራ ሥር ካልደረሰ የከፋ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ በሽታ ይበዛል፡፡ ጎመን፣ በቆሎ፣ ዱባ፣ ከደረሰ ግን የሩብ ሩብ በሆነች  እንጀራ ጎመንም፣ ዱባም ሊበላ ይችላል፡፡ በቆሎም ደርሶም ሳይደርስም ሊበላ ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት በየዓመቱ ብዙ  ህጻናትና ሽማግሌዎች ያልቃሉ፡፡ እንደ ተሾመ ብርሃኑ ያሉት የተረፉት እደጉ ቢላቸው ነው ማለት ይቻላል፡፡

ብልሁ ብርሀኑ-ትምህርት የበራለት ጊዜ 

በመሠረቱ፣ ተሾመ ብርሃኑ ከማል ከህጻንነቱ ጀምሮ ብልጥና ትምህርት በቀላሉ ይቀበላሉ ተብለው ከሚነገርላቸው ህጻናት  መካከል አንዱ ነበር፡፡ ስለዚህም በቁርዐን ቤትም ይሁን በዘመናዊ ትምህርት ቤት ትምህርት የመቀበልና የማንበብ አቅሙ ጥሩ  ነበር፡፡ ብዙ ሰዎችም እንደሽማግሌ እንጂ እንደ ህጻን አያዩትም ነበር፡፡ አያቶቹ ሳይቀሩ ምክር ይጠይቁት ነበር፡፡ የእናቱ መካሪ  እርሱነው፡፡ ከአሥራ አምስት እስከ አስራ ሰባት ባለው ዕድሜው የአንድ ሳምንት የእግር መንገድ እየተጓዘ ከእናቱ ጋር  ለመሸቀጥ መክሮ ነበር፡፡

በአካባው ከሚገኙት ሳምንታዊ ገበያዎች ሮብ ገበያን፣ አስ ከተማን፣ ቆብዝባን፣ ደሃናን ሸቀጣ ሸቀጥ  ዘርግቶ ነግዶባቸዋል፡፡ የተጠቀሰውን ችግር ሁሉ ተቋቁሞ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን  ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ በቀድሞው በየነ መርዕድ (አሁን እድገት በህብረት) አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ  የስምንተኛ ክፍልን፣ በቀድሞው አስፋው ወሰን ትምህርት ቤት (አሁን ምሥራቅ አጠቃላይ) የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን፣  የመጀመሪያ  ዲግሪውን  በአዲስ  አበባ  ዩኒቨርሲቲ  አጠናቀቀ፡፡  በሌሎች  የትምህርት  ተቋማትም፣  ጆርናሊዝምን፣  ህዝብ  ግንኙነትን፣ ፕሮቶኮልን፣ ማኔጅመንትን፣ አጥንቶ ከሰርቲፊኬት እስከ ዲፕሎም ደረጃ ያሉትን ትምህርቶች ቀስሟል፡፡

የሙያ ጅማሮ-ዜና ተቀብሎ ማሰራጨት

ተሾመ  ብርሃኑ  ከማል  ከልጅነት  ዕድሜው  ጀምሮ  የስነ-ጽሑፍና  የጋዜጠኝነት  ዝንባሌ  እንደነበረው  የአንደኛ ደረጃ  ተማሪ  ከነበረበት  ጊዜ  አሳይቷል፡፡  በተማረባቸው  ትምህርት  ቤቶችም  የስነ-ጽሑፍና  የጋዜጠኝነት  ክበብ  አባል  በመሆን  ተማሪዎች  እንዲያነቡት በቦርድ የሚለጠፍ ጽሑፍ በማበርከት፣ በጥዋት ሰልፍ  ዜና በማቅረብ ይታወቅ ነበር፡፡ ስለሆነም ገና የዩኒቨርሲቲ  አንደኛ ተማሪ በነበረበት ጊዜ (በ1970) በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የዓለም አቀፍ መምሪያ በማታው ሺፍት ከልዩ ልዩ የዜና  ምንጮች  (ከሬውተር፣  ከአዣን  ፍራንስ  ፕሬስ፣  ከሴቴካ፣  ወዘተ)  በቴሌክስ  ይመጡ  የነበሩትን  ዜናዎች  በመቀበልና  ለሚመለከታቸው ክፍሎች በማስራጨት ለአንድ ዓመት በኮንትራት ሠርቷል፡፡

1971 ጉዞ ወደ ኢቲቪ እና ሌሎች

ከ1971 ጀምሮ እስከ 1976 ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ፣ እንዲሁም ፕሮግራም  መሪና አስተባባሪ በመሆን፣ የወጣቶች ፕሮግራም አዘጋጅ አቅራቢ በመሆን፣ እንደዚሁም ልዩ ልዩ ዜናዎችንና ሪፖርታዦችን  በመሥራት አገልግሏል፡፡ ከ1976­1980 ባለው ጊዜ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ህጻናት አምባ ህዝብ ግንኙነት፣ የፍቼ ተሐድሶ ፕሮጀክት ህዝብ ግንኙነት፣ የራሱ የሚኒስቴሩ መሥሪያ ቤት በአባልነትና በኃላፊነት  ሠርቷል፡፡ 

ከ1980­-1983  የብሔራዊ  ቁጥጥር  ኮሚቴ  የህዝብ  ግንኙነት  ረዳት  በመሆን  አገልግሏል፡፡  ከ1983­-1987  ድረስ  በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት የፕሬስ ክፍል ኃላፊ ሆኖ ሠርቷል፡፡ በዚህ ጊዜም የምክር ቤቱ ቃለ-  ጉባኤዎች በደንብ እንዲቀመጡ፣ መገናኛ ብዙሃን እንዲያውቋቸውና እያንዳንዱ መደበኛና አስቸኳይ ስብሰባ በምን ጉዳይ ላይ  እንደተወያየና ውሳኔ እንደሰጠ ጠቃሚ መረጃ አጠናክሮ በአዲስ ዘመን ጋዜጣና በሌሎችም እንዲታወቁ አድርጓል፡፡

ከ1987­-1992  በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ አዘጋጅ በመሆን፣ እንዲሁም የሰንደቅ መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር በመሆን  ሠርቷል፡፡ ከ1992­1994 በኢትዮጵያ ጤናና ስነ-ምግብ ኢንስቲትዩት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ ከ1992-­2004 በኢትዮጵያ ንግድ  መርከብ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ በመሆን አገልግሏል፡፡ 

የጥናትና ምርምር ሥራዎች

ተሾመ ብርሃኑ ከማል፣ በልዩ ልዩ የህትመት ሥራዎች (ለምሳሌ በአዲስ ዘመን፣ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ በሪፖርተርና ካፒታል  ጋዜጦች፣ በየካቲት፣ በሙዳይ፣ በአፍሪካ ቀንድ፣ በእፎይታ መጽሔቶች) ለንባብ ካበረከታቸው ሥራዎች አብዛኛዎቹ በጥናትና  ምርምር ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ከሥራዎቹ አንዳቸውንም እንኳን ቢሆን ልዩ ልዩ መረጃዎችን ሳያነብ ወይም ዕውቀቱ  ያላቸውን ባለሙያዎች ሳያነጋግር እንዳልጻፈ ሥራዎቹ ራሳቸው ይመሠክራሉ፡፡ በጋዜጣና በመጽሔቶች ከጻፋቸው 2000 ያህል  ሥራዎች በተጨማሪ በሀገር ውስጥና በውጭ አገር ስብሰባዎች ያቀረባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ስለጋዜጠኝነት፣  ስለህዝብ ግንኙነት፣ ስለፕሮቶኮልና ኮሙዩኒኬሽን፣ ስለኢትዮጵያውያን ሴት ጸሐፍትና ጋዜጠኞች፣ ስለሃይማኖታዊ መቻቻል፣  ስለጥንታዊ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ፣ ስለኢስላማዊ ረቂቅና ተጨባጭ ቅርሶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ተሾመ ብርሃኑ ከማል 30 ያህል መጻህፍት ለኅትመት ያበቃ ሲሆን እነርሱም 14 ያህል የሕጻናት  ( የተረት አባት፣ አንዲት  ትንቸልና ቀጭኔ፣ ደረቶ፣ የተረት አባት ባለ አረንጓዴ ጥለት፣ የተረት አባት ባለ ቀይ ጥለት፣ ደረቶ፣  እሱባለውና የገነት ወፍ፣  ጎራዴ ያገባችው  ልዕልት፣ ዓለሚቱ ማንን ታግባ፣ መርከበኞቹ፣ አስራ ሁለቱ ልዕልቶች፣ የኤዞፕ ተረቶች  አንደኛ፣  64 ቱ የኤዞፕ  ተረቶችና  4 ምርጥ የዓለማችን ተረቶች ፣ ሠዓዳ ና ሌሎች አስደናቂ ተረቶች ፣ የኔዎቹ ተረቶች )፣ አራት የጠቅላላ ዕውቀት ( የሕልም ኢንሳይክሎፒዲያ፣ የዓለማችን ታላላቅ ሰዎችና ጥቅሶቻቸው፣ መቻቻል፣ ንግሥት ፉራ ( ፎክሎር ) ፣ ንግሥት ፉራ ( በፎክሎር ላይ የተመሰረተ ልቦለድ ) ፣ ሰባት የታሪክ መጻሕፍት ( ኢማም አሕመድ ኢብራሂም፣ የሰላም ፍኖት ለኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች አንድነት፣ ኮናባ የተደበቀች የዓለም ቅርስ፣ የዓፋር ታሪክ ­ከሌሎች ምሁራን ጋር በመ ሆን የተጻፈ፣ ሌላው የኢትዮጵያ የታሪክ ገጽታ፣ የሐረር ዐሚሮች፣ ሐረሪ ለምን ህጋዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ አግኝታ ክልል ሆነች ? ­ ከሐረሪ ባህል፣ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር፣ ) ሁለት የትርጉም መጻህፍት  ( የካሚላ ጊብስ የቅዱሳን ከተማ በሚል ርዕስ ለፒኤችዲ  ማሟያ የጻፈችው፣ አቪሻይ ቤን ዶር ኢሚሬት፣ ኢጅፕት፣ ኢትዮጵያ በሚል ርእስ ለፒኤችዲ ማሟያ የጻፈው­ ­ከሐረሪ ባህል፣  ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር )

ለመድረክ የበቁ ተውኔቶች

ዲምቱ በከተማ (ብሔራዊ ትያትር የታየ የህጻናት ትያትር)፣ የማታላቅሰው ህጻን (አዲስ አበባ ዩቨርሲቲ ባህል ማዕከል የታየ)፣  ከራስህ ጋር ታረቅ (የቴሌቪዥን ድራማ)፣ ምስክርነት (የቴሌቪዥን ድራማ)፣ ጠፍሪ (የቴሌቪዥን ድራማ)

የታተሙ ጥናቶችና ምርምሮች

Ancient Marine transport and trade route of Ethiopia,   Ship construction in ancient Ethiopia Dialogue African Forum (Editor and Translator) Dire Shekh Hussien  The History of Ethiopian Shipping Lines  The importance of Hizmet movement in the process of peace building in Ethiopia የውጭ ሀገር ጉብኝት

ሐምሌ 1972፣ በጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ተደርጎ በነበረው 32ኛው ዓለም አቀፍ ሳመር ካምፕ ተካፋይ ለመሆን ፣ ከሰኔ  1 ቀን እስከ ሰኔ 14 ቀን 1972 በኢጣሊያ /በተለይም በቶስካና ክፍለ ሀገር ኮሎዲ ኢንተርናሽናል (የአፍንጮ ቀን) ለመካፈል ፣  ህዳር 8 ቀን 1972 ኬንያ ለአፍሪካ አቀፍ ህጻናትና ወጣቶች ሬዲዮና ቴሌቪዥን ኮንፈረንስ፣ 1993 ኬንያ ለህዝብ ግንኙነትና  ፕሮቶኮል ስልጠና ለመውሰድ፣ 26/9/98­ሰኔ 11 ቀን 1998 ከጅቡቲ ­ ሙምባይ ጉዞ በመርከብ፣ ከጥር 22 ቀን አስከ ጥር 24  ቀን ኒውደልሂ በተካሄደው የኢቨስትመንት ሲምፖዚየም ኢትዮጵያ ንግድ መርከብን ወክሎ ለመገኘት፣ ሰኔ 26 ቀን 1999  ኢትዮጵያ ንግድ መርከብን ወክሎ በርበራ መጓዝ፣ ጥቅምት 14 ቀን 2005 ዋሺንግተን ዲሲ በዓለም ሰላም ግንባታ ጉባኤ  ለመገኘትና ኢትዮጵያን የሚመለከት ጥናታዊ ጽሑፍ በዓለም አቀፍ መድረክ ለማቅረብ፡፡

ሽልማቶችና ምስክር ወረቀቶች

በሐረሪ ክልል መሠረታዊ የጋዜጠኝነትና የህዝብ ግንኙነት ስልጠና በመስጠት፣ በአማራ ክልል ጋዜጠኝነትና የጋዜጠኝነት  ስነምግባር እንዲሁም የፊቸር አጻጻፍ ስልጠና በመስጠት፣ በኢትዮጵያ ፕሬስ አጀንሲ መሠረታዊ የጆርናሊዝም ትምህርት በመስጠት፣ በትፍላሜ አማተር ጋዜጠኞች ማህበር ስለጋዜጣ ሜክአፕ ስልጠና በመስጠት፣ በጳውሎስ ኞኞ አማተር ጋዜጠኞች  ማህበር መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ስልጠና በመስጠት፣ በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር እንቅስቃሴ ተካፋይ በመሆን፣  በሠርቶ አደር ጋዜጣ አምስተኛ ዓመት የስነ ጽሑፍ ተሸላሚ በመሆን የተገኙ ናቸው፡፡

ተሾመ ብርሃኑ ከማል በርካታ ለህትመት የተዘጋጁ ሥራዎች ሲኖሩት ከነዚህም ውስጥ ስድስቱ ‹‹ጋዜጣና ጋዜጠኝነት፣ ዓረብኛ  ስነጽሑፍ በኢትዮጵያ፣ የሁሉም ሥራዎቹ ቢብሊዮ ግራፊ፣ የሃይማኖት ችግሮች በኢትዮጵያ፣ የውጭ አገር ጉዞዬ ማስታወሻ፣  የበደኖና የወተር ጭፍጨፋ  ድብቅ ታሪክ፣ የአረካ ጭፍጨፋ ድብቅ ታሪክ፣ ከ1983­20013 በኢትዮጵያ የደረሱ ፍጅቶች›› የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ማጠቃለያ …. በአሁኑ ሰአት የ70 አመት ሰው የሆኑት ደራሲ ተሾመ ብርሀኑ ይህን ዊኪፒዲያ ታሪክ ስንጽፍ አንተ ያልናቸው ለወጣት የሚቀርቡ፣ እውቀት ለመለገስ የማይሰስቱ ስለሆኑ ነው  እንጂ ባህላችን እንደሚፈቅደው አንቱታ የሚገባቸው በስራቸው እና በምግባራቸው የተከበሩ  ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ጋሽ ተሾመ የራሳቸውን ስራ በወጉ ጠብቆ በማቆየት ያምናሉ፡፡ ባለፉት አመታት ስንት ጽሁፍ እንደጻፉ በየትኞቹ ህትመቶች አሻራቸው እንዳለ በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ከእነ ቁጥሩ በሰንጠረዥ አድርገው የሚያነበው ሰው በቀላሉ ሊረዳው በሚችለው መንገድ ግልጽ አድርገው አስቀምጠውታል፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆችም  በ60 ገጽ የቀረበውን ዝርዝር ቢቢሊዮግራፊ በጥንቃቄ ተመልክተዋል፡፡

ለመጪው ትውልድ የሚያስብ ስራዬ ብሎ ይህን ያደርጋል፡፡ አቶ ተሾመ ዛሬም ከንባብ አልራቁም፡፡ በስራ መወጠሩ በእድሜ አልገታም፡፡ መጻፍ ፤ ማንበብ ፤ መማር ዋና የህይወታቸው መርህ እንደሆነ ይዘልቃል፡፡ አብረዋቸው የሰሩ በሳል የሚድያ የድርሰት ሰው መሆናቸውን በሙሉ አፍ ይመሰክራሉ፡፡ እኒህ ታላቅ ሰው ለመታየት ብሎም ራሳቸውን ለማሳወቅ ሳይሆን ስራቸውን ቶሎ አጠናቀው ለንባብ ለማብቃት ይጣደፋሉ፡፡ ብዙም ያልነገረላቸው አቶ ተሾመ ዛሬም ይመሰገናሉ፡፡ ተተኪው ትውልድ ማን መሆናቸውን እንዲያውቅ ይህን አጭር ግለ-ታሪካቸውን ዛሬ ሰኔ 13 2013 ከታሪክ መዝገብ ላይ እንዲሰፍር እነሆ ብለናል፡፡ መልካም ተመኘን ለጋሽ ተሾመ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *