ስንዱ ኃይሌ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በቅርቡ ክምችተ-አእምሮ / ኢንሳይክሎፒዲያ / በሚል ርእስ የሚድያ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎችን ታሪክ በጠንካራ ሽፋን መጽሀፍ አሳትሞ ያስመርቃል፡፡ ታሪካቸው በመጽሀፉ ውስጥ ከሚሰነድላቸው አሻራ ካኖሩ የሚድያ ሰዎች አንዷ ስንዱ ሀይሌ ናት፡፡ ስንዱ በህትመት ጋዜጠኝነት በተለይ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ሰንበት ለልጆች የተሰኘውን አምድ በማዘጋጀት መጪው ትውልድን የማነጽ ስራ ላይ ጉልህ ተግባር አከናውናለች፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረችበት ወቅት የ “Prose and Fiction” መምህሯ የነበረችው መምህርት ኦልጋ ያዝቤክ፣ የመንፈቀ ዓመቱን የጥናት ወረቀት ውጤቷን ካየች በኃላ “ሙያሽ ምንድነው?” ብላ ትጠይቃታለች። “ጋዜጠኝነት” ስትል ትመልሳለች። “ይገርማል! ብዙ ጋዜጠኛ ተማሪዎች አሉኝ ፤ ለመሆኑ ሥነ ጽሁፉ ነው ወደ ጋዜጠኝነቱ የሚስባችሁ? ወይስ ጋዜጠኝነቱ ወደ ሥነ ጽሁፍ?” አሁንም ጥያቄ። የተማሪዋ ምላሽም“እኔን፣ ሥነ ጽሁፉ ነው ወደ ጋዜጠኝነቱ የመራኝ” የሚል ነበር።
ስንዱ ኃይሌ፣ ከልጅነቷ ጀምሮ ለሥነ ጽሁፍ፣ ለስዕልና ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር ነበራት። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችበት የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ደግሞ ይህ ፍቅሯ እንዲጎለብት አስተዋጽኦ አድርጎላታል።
ከትምህርት ቤቱ ግቢ ጋር ተያይዞ የተገነባው የሥዕልትምህርት ቤት የሽቦ አጥር ላይ እየተንጠላጠለች ሰዓሊያኑ ሸራቸውን ወጥረው የሚስሉትን የሥዕል ሥራና ቅርጻ ቅርጽ ማየት ያረካት ነበር ፤ ዝቅ ብሎ ደግሞ ከዳግማዊ ምኒልክ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚፈልቀው የሙዚቃ መሣሪያ ድምጽ ቀልቧን ይገዛት ነበር። በሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ገብታ ለጥቂት ጊዜያት በኳየርነት የተሳተፈች ሲሆን የሙዚቃ መሣሪያም ማጥናት ጀምራ ነበር – አልገፋችበትም እንጂ።
ስንዱ፣ ከእናቷ ከወይዘሮ ስንቅነሽ ገብረየስና ከአባቷ ከአቶ ኃይሉ አባይ በአዲስ አበባ ከተማ ቄስ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ1959 ዓ. ም. ተወለደች። አራት ልጆቻቸውን ያለአባት ላሳደጉት እናቷ ስንዱ የመጨረሻ ልጅ ናት።
ከሥነ- ጽሁፍ ወደ ጋዜጠኝነት
1983 ዓ. ም. የክረምት ወራት መግቢያ ነበር። አራት ኪሎ “ጆሊባር” ስር በሚገኘውና በማስታወቂያ በሚጨናነቀው ግንብ ላይ የወቅቱ የአዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢ ባሕልና ስፖርት መምሪያ፣ የሥነ ጽሁፍና የቴአትር ፍቅር ያላቸውን ወጣቶች ተቀብሎ እንደሚያሰለጥን የሚገልጸውን ማስታወቂያ ስንዱ ታነባለች። ዕድሉን ተጠቅማም ለሁለት ወራት ከ15 ቀናት የሚሰጠውን የሥነ- ጽሁፍ መሠረታዊ ሥልጠናን ቀሰመች። መምህሩ አቶ አበበ ኬሪ፣ ሠልጣኞቹ የቀሰሙትን እውቀት የበለጠ እንዲያዳብሩ በክበብ እንዲደራጁ እድሉን በማመቻቸቱ ወጣቶቹ ፍካት ወጣት ደራሲያን ክበብን መሠረቱ። ክበቡ ሲመሠረት የመመሥረቻ ደንቡን ፈርመው ለቢሮው ካስገቡት አምስት ወጣቶች ውስጥ አንዷ ሴት ስንዱ ነበረች። የክበቡ ቆይታዋም በሥነ- ጽሁፉ ዘርፍ ያላትን የዕውቀት አድማስ ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎላታል።
ስንዱ፣ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተለያዩ መጣጥፎችን መላክ ጀመረች ። ጽሁፎቿ ታትመውም ለአንባቢያን መድረስ ጀመሩ። በ1987 ዓ. ም. አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባወጣው ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ በመወዳደርም በፍሪላንስ ተቀጠረች። ከጥቂት ወራት በኋላም “ትዝታ” የሚል ዓምድ የማዘጋጀት እድሉን በማግኘቷ ለአገራቸው በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ ያደረጉ ባለሙያዎችን ትዝታ ለአንባቢያን ማቅረብ ጀመረች። ከእነዚህም ውስጥ የአባባ ተስፋዬ ሳህሉ “ሲኞር ፖርቾሌ” በሚል ርእስ የቀረበው ትዝታ ይታወሳል። የአባባ ተስፋዬ ይህ ድንቅ ትዝታ፣ በአምስት ዓመቱ የጠላት ወረራ ወቅት የልጅነታቸውን አስገራሚ ታሪክንና ምንም የሕክምና እውቀት ሳይኖረው በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሕመምተኞችን መርፌ ይወጋ ስለነበረው “ሲኞር ፖርቾሌ” ያወሳል፤ ጣልያናዊው መርፌ መውጋቱ አልበቃ ብሎት በካዛንቺስ አካባቢ በስሙ ክሊኒክ መክፈቱም ታሪኩን አስደናቂ አድርጎታል።
ሌላው አንጋፋው የእውቀት አባትና የፊደል ገበታ መሥራች፣ ቀኛዝማች ተስፋ ገብረስላሴ (ዘብሔረ ቡልጋ) በዚያው በጠላት አምስት ዓመታት ውስጥ በአርበኝነት ቆይታቸው በቅርበት ከሚያውቁት ታሪክ በመነሳት እስካሁን አገሪቱ ተቀብላ ከምታከብራቸው ብሔራዊ በዓላት ውስጥ፣ አንዱ በዓል ላይ የተዛባ ታሪክ እንዳለ የገለጹበት አስደንጋጭ ቃለ ምልልስ ይታወሳል። በወቅቱ ይህን ታሪክ የጻፉ ጸሐፊዎችም እንደ እርሳቸው ያሉ የዓይን እማኞችን ሳይጠይቁ የተሳሳተ የታሪክ መሠረትን መጻፋቸው ትክክል ባለመሆኑ ኮንነዋል። ጽሁፉን ሚዛናዊ ለማድረግ ምላሽ እንዲሰጡ የተጠየቁት ታሪክ ጸሐፊዎች ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አልነበሩም፤ የአንዱ ታዋቂ ታሪክ ጸሐፊም መልስ አጭር ነበር፣ “በአሁን ሰዓት ይህን ማንሳት ለምን አስፈለገ?” የሚል።
ስንዱ፣ በአዲስ ዘመን ቆይታዋ የተለያዩ ዓምዶችን ያዘጋጀች ሲሆን በተለይ ለብዙ ዓመታት በሠራችባቸው “ሰንበት ለልጆች” እና “እንግዳችን” በተባሉ አምዶቿ ትታወቃለች። በሰንበት ለልጆች ዓምድ ላይ ታቀርባቸው የነበሩ የተለያዩ ዝግጅቶች፣ ልጆችን ከአንባቢነት አልፎ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደረገ ነበር። ከእነዚህም ውስጥ ልጆች የሚልኳቸው ደብዳቤዎችን ከእነእጅጽሁፋቸው ለህትመት እንዲበቁ በማድረግ ሥራቸውን ታበረታታ ነበር። በደብዳቤዎቻቸውም ላይ ጽሁፎቻቸውን ሲጀምሩ “እትዬ ስንዱ” የሚል የአክብሮት አጠራር ስለሚጠቀሙ ይህን ስም ተውሰው የሚጠሯትም ነበሩ። የላቀ የፈጠራ ሥራ ያላቸውና በትምህርታቸው ውጤታማ የሆኑትን ልጆች ቃለ- ምልልስ በማድረግ፣ አንጋፋና ታዋቂ ባለሙያዎችን በአርአያነት በማስተዋወቅ፣ የውጭ አገር ተረቶችን በመተርጎም፣ የዓለም ዓቀፍ የሕጻናት መብቶች ድንጋጌዎችን በምስልና በካርቱን አስደግፎ በማስተዋወቅ፣ ልጆች ዓምዱን በጉጉት እንዲጠብቁት ከሚያደርጉ ዝግጅቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ነበሩ። ስለዚህም በአዲስ አበባም ሆነ ጋዜጣው በሚሰራጭባቸው ክልሎች ከሚገኙ ልጆች በርካታ ደብዳቤዎችና የስልክ ጥሪዎች ይደርሷት ነበር። በዚህ አምድ ላይ ከልጆች በተጨማሪ አዋቂዎችም ጽሁፍ በመላክ ተሳትፎ አድርገዋል።
“እንግዳችን” በተሰኘው ዓምድም ላይ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊና ሰብዓዊ ተግባራት የተሠማሩ፣ ለአገራቸውና ለማኅበረሰቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ የተመረጡ ባለሙያዎችን የሕይወት ተሞክሮና ውጤታማ ሥራቸውን በስፋት አቅርባለች። በወቅቱ በሕይወት የነበሩና በአገሪቱ በተለያየ ሙያ ጀማሪ የነበሩ ባለሙያዎችን በዚሁ ዓምድ ላይ አስተናግዳለች ።እነዚህን ሁለት ዓምዶች እያዘጋጀችም በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት ለሁለት ዓመታት በሕትመት ጋዜጠኝነት የቀን ትምህርቷን ተከታትላለች።
ስንዱ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስትቀጠር ደሞዟ 230 ብር ቢሆንም ለሙያው ከፍተኛ ፍቅር ስለነበራት ሥራዋን የምታከናውነው በደስታ ነበር። ለመስክ ሥራ በተለያዩ ክልሎች ስትሰማራ የምሠራው ለሚከፈለኝና ለተመደብኩበት ሥራ ብቻ ነው ሳትል በጋዜጣው ላይ ለነበሩ ለተለያዩ አምዶች የሚሆኑ ሥራዎችን አሰባስባ ትመለስ ነበር። የሌሊት የእንቅልፍ ሰዓቷን በመጠቀምም ጽሁፎቿን አቀናብራ ለየአምዱ አዘጋጆች ታስረክብ ነበር። በተጨማሪም በ1990ዎቹ መጀመሪያ የሰኞ ጋዜጣ ሕትመት ሲጀመር ጋዜጣውን ለማዘጋጀት ከተመደቡት ጋዜጠኞች ውስጥ አንዷ ነበረች ።
የግል ሥራ
በ2002 ዓም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከለቀቀች በኋላ “እኛ’ በሚል ርዕስ ሲተላለፍ በነበረው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በፕሮግራም አስተዋዋቂነትና አዘጋጅነት ሠርታለች። በዚያው ዓመት “እጹብ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች” የሚል፣ በሚዲያና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያትኩር የራሷን የሚዲያ ተቋም አቋቋመች። በሚዲያው ዘርፍ፣ በኮንስትራክሽን ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ “ኮንስትራክሽን ካፌ” የተሰኘ ፕሮግራሟን፣ መጀመሪያ በፋና ሬድዮ፣ ቀጥሎም በዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የአየር ሰዓት በመውሰድ ለአምስት ዓመታት ሠርታለች። ፕሮግራሙ፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በእውቀት እንዲመራ፣ በዘርፉ ያሉ የተለያዩ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን የሚያካፍሉበት፣ በዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮች እየተዳሰሱ መፍትሄዎች የሚቀርቡበት፣ በግንባታ ቦታዎች በመገኘት የኮንስትራክሽን ደህንነትና ጤንነት ስጋት ተጋላጮች ችግሮቻቸውን የሚዳስሱበት፣ የጥንት የኮንስትራክሽን ታሪክ በበገና የሚተረክበት፣ “ጎጆ ዲዛይን” በሚል ርእስ ታዋቂ ሰዎች ስለ ቤታቸው ዲዛይን የሚያወጉብት፣ በየሳምንቱ ከነጋዴዎች መረጃን በመሰብሰብ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች የኮንስትራክሽን እቃዎች የዋጋ ዝርዝር የሚቀርቡብት ነበር። እጹብ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን፣ በተጓዳኝም የተለያዩ የመጽሔት ሥራዎች፣ የመድረከ ዝግጅቶች፣ ማስታወቂያዎች፣ ዘጋቢ ፊልሞችና የተለያዩ የመድረክ ዝግጅቶችን አከናውኗል።
የሥነ ጽሁፍ
አጫጭር ልቦለዶችና ግጥሞች የመጻፍ ዝንባሌ ያላት ስንዱ፣ አጫጭር ልቦለዶቿ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለሕትመት የበቁ ሲሆን ፍካት ደራሲያን ክበብ ባሳተመው “ዜማ” በተባለው የአጭር ልቦለድ መድብል ውስጥም ተሳትፋለች ። በተጨማሪም “ሺረጋ ኃይሌና ሕይወቱ” በሚል ከጓደኛዋ ጋዜጠኛ ጽጌ ዓይናለም ጋር በመሆን የግል ሕይወት ታሪክ መጽሐፍ አዘጋጅተዋል። አሁንም እጆቿ ላይ የህትመት ጊዜያቸውን የሚጠብቁ የተለያዩ የሥነ ጽሁፍ ሥራዎች ይገኛሉ ።
ትምህርት
ስንዱ፣ በሕትመት ጋዜጠኝነት ዲፕሎማዋን በመገናኛ ብዙኃን ማሰልጠኛ ተቋም፣ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍ አግኝታለች። ከሁለት ሴት ልጆቿ ጋር ኑሮዋን በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገችው ስንዱ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ጤናው ዘርፍ በሚያስገባው መንገድ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ።
የመዝጊያ
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የኢንሳይክሎፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ ስንዱ ሀይሌ በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ወደ ጋዜጠኝነቱና ወደ ስነ-ጽሁፉ አለም በመግባት ብእር ከወረቀት ያዋሀደች ባለሙያ ናት፡፡ ስንዱ፣ በተለይ አንጋፎችን አቅፎ በያዘው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ከታላላቆች ልምድ እየቀሰመች የራሷንም አቅም ሳትቆጥብ እያወጣች ስታገለግል ቆይታለች፡፡ ለህጻናት ስነ-ጽሁፍ ፤ ለህጻናት አምዶችና ፤ ለህጻናት የሬድዮና የቲቪ መሰናዶ ብዙም ትኩረት በማይሰጥበት በዛን ወቅት ስንዱ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የልጆች አምድን በፍቅር ስታዘጋጅ ኖራለች፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የልጆች አምድ ዝግጅት ላይ የራሳቸውን አሻራ ካኖሩ ኢትዮጵያውያን አንዷ ያደርጋታል፡፡ ኢትዮጵያ በአንድ ሰው ብቻ አልተገነባችም፡፡ ሁሉም በየግላቸው በሚያዋጡት መሰረት ሀገር ትሰራለች፡፡ ይህን የግለ-ታሪክ መዝገበ-አእምሮ ወይም ኢንሳይክሎፒዲያ አሻራ ላኖሩ ሰዎች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ግለ-ታሪኩ ለትወልድ የሚሻገር ስለሆነ አንዱ የሌላውን ልምድ ሲቀስም እርሱ ደግሞ አሻሽሎ የራሱን ጉልህ አሻራ ያኖራል፡፡ይህ እንዲሳካም የስንዱን አጭር ግለ-ታሪክ ሰንደዋል፡፡/ ይህ ግለ-ታሪክ ከባለ ታሪኳ የተገኙ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ የተጻፈ ነው፡፡