ቢንያም ነገሱ

ቢንያም ነገሱ

ጊዜው የዛሬ 10 ዓመት ነበር። በአንድ በኩል ፋና ላይ ተቀጥሬ ስሠራ በሌላ ደግሞ ተወዳጅ ሚድያን እመራ ነበር ። እና ስለ ኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች እና ታሪክ የት ሄጄ ልተንፍስ? የሚል ጭንቅ ውስጥ በገባሁት ሰዓት ከቢኒ ጋር ተዋወቅን ። ዕድል ሰጠኝ። አሁን የጀመርኩት የህይወት ታሪክ ፕሮጀክት መልክ ለፍሬ የበቃው ድሬ ቲዩብ መሥራት ከጀመርኩ በኋላ ነው። ገራሚ ገራሚ ትዝታዎች ነበሩኝ። እንደ ተሾመ ታደሠ ፣ በንቲ አበራ andafta media መሥራች ፣ ዓይነት ሰዎችን ተዋውቄአለሁ። በ2008 ላይ ስሜነህ ጌታነህ በሚለው የብዕር ስሜ ቢኒን ኢንተርቪው አድርጌው ነበር ። እነሆ።

ቃለምልልስ ፦ በዚህ አምድ ለሌሎች አርአያ የሆኑ ሰዎች ይቀርባሉ ።

ከቢንያም ነገሱ ጋር የተደረገ ቆይታ በ2008 የተደረገ ኢንተርቪው

<<2ነጥብ 5 ሚልዮን የፌስ ቡክ ደንበኛ ማፍራታችን ያበረታታናል>>

ቢንያም ነገሱ፦ የድሬቲዩብ መስራች ሲሆን ድረገጹን ከጀመረ 8 አመት አልፎታል ። በአሁኑ ሰአት በሃገራችን ካሉ ድረ ገጾች ግንባር ቀደም የሆነው ድሬ ቲዩብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን ለማፍራት የቻለ ነው ፤፤ ከድሬቲዩብ መስራች ወጣት ቢንያም ነገሱ ጋር ስሜነህ ጌታነህ አጭር ቆይታ አድርጎ ነበር

ምን አዲስ ፦ድሬ ቲዩብ ድረ ገጽ ከተመሰረተ 8 አመቱን አስቆጥሮአል። 8 አመቱ እንዴት አለፈ?

ቢንያም ነገሱ ፦ ድሬ ቲዩብ በ 7 አመት ጊዜ ውስጥ የራሱን የእድገት ደረጃዎች አሳልፎአል ። ድሬ ቲዩብን ተፈላጊ ያደረጉት ቀዳሚዎቹ በባህር ማዶ ያሉ ትውልደ ኢትዮዽያውያን ናቸው። እነርሱ ስለሃገራቸው ማወቅ የሚፈልጉትን ቀለል ባለ መልኩ ማግኘት አዳጋች ይሆንባቸው ነበር። እናም ድሬ ቲዩብ ይህን ክፍተት በተሙዋላ መልኩ ለመሙላት ተነሳስቶ ነበር። ፊልም እና ሙዚቃ ለምሳሌ ማግኘት ለእነርሱ ቀላል አልነበረም። ድሬ ቲዩብ ይህን ችግር ለመፍታት በበቂ ሁኔታ ተንቀሳቅሶአል ። በፍጥነት የማደጋችን ሚስጢር ይህ ነው።

እኔ ስጀምረው ያኔ ሰዎች የሀገር ውስጥ ሙዚቃዎችን ያለአንዳች ልፋት በአንድ ቦታ ያገኙ ነበር። ሲጀመር በዜሮ ነበር የተጀመረው። ብዙም ፋይናንስ አልነበረንም። ድሬ ቲዩብ እንደድርጅት ከመመስረቱ አስቀድሞ በግሌ ነበር እሰራ የነበረው። በተቻለ አቅም በመጀመሪያዎቹ ጊዜያቶች አድማስ ዩኒቨርሲቲ ሳስተምር ከማገኛት ደመወዝ እየወሰድኩ ድሬቲዩብን ለማሳደግ እጠቀምበት ነበር። በዛን ወቅት ለዌብሳይት ትልቅ ፍላጎት አሳይቼ ነበር። እናም እንዲህ እንዲህ እያለ ድሬ ቲዩብ 7 አመት ላይ መድረስ ችሎአል።

ምን አዲስ ፦ ድሬቲዩብን ስትመሰርት የነበረውን ሁኔታ እስቲ በደንብ አጫውተኝ።

ቢንያም፦ ድሬ ቲዩብን ስመሰርት በአድማስ ዩኒቨርሲቲ የሀርጌሳ ቅርንጫፍ የአይቲ መምህር ነበርኩ። ያኔ አንድ ኮምፒውተር እኔና ጠረጴዛ ብቻ ነበርን። በዚህ ሁኔታ ነበር ቤቴ ውስጥ ቀለል ባለመንገድ የጀመርኩት። ያን ጊዜ ሃርጌሳ የነበረው አድማስ ዩኒቨርሲቲ ዌብ ሳይት አልነበረውም። ለዩኒቨርሲቲው ድረገጽ መስራት ችያለሁ። በወቅቱ በቀላሉ የማገኛቸው ሙዚቃዎችን በመጫን ነበር ስራውን የጀመርኩት። የጎብኚዎች ቁጥር በቀን ከ30 ሰው በላይ አይበልጥም ነበር። ያኔ ዩቲዩብ ላይ የተለያዩ ሙዚቃዎች ይጫኑ ነበር። ሆኖም ለማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር። አንድ ሰው የኢትዮዽያን ሙዚቃ ቢፈልግ ዩቲዩብ ላይ ቀለል ባለ መልኩ ሊያገኝ አይችልም። ሰዎች በራሳቸው ተነስተው ዩቲዩብ ላይ የሚጭኑትን ይዘት በቀላሉ እንዲገኝ አድርጎ ማስቀመጥ ነበር የእኔ ትልቁ ስራ።

ምን አዲስ ፦ ቢንያም አይቲ ነበር የተማርከው አይደል?
ቢንያም፦ በድሬደዋ ቴክኒክና ሙያ አይቲ ነበር የተማርኩት። ከዚያም ከቴክኒክ እና ሙያ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ ሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ተማሩ የሚል ሃሳብ ቀርቦልን ነበር። በዛን ወቅት ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሶፍትዌር እና የሃርድዌር ምህንድስናን እንማር ዘንድ አማራጭ ተሰጥቶን ነበር። ከ1እስከ 3 የወጣን ልጆች እዛው ትምህርት ቤት መምህር እንድንሆን ተደረገ። የስራ እድል ተፈጠረልን ማለት ነው ። ደስም አለን ። ስለዚህ ጠዋት እያስተማርን ማታ በኤክስቴንሽን ሃሮማያ ሶፍትዌርን እንማር ነበር። ቢዝነሶችንም እንሰራ ነበር። በጊዜውም ለድሬደዋ ሃይስኩል ዌብሳይት ሰርተንላቸው ነበር። የድሬደዋ ከንቲባም ለስራው አድናቆታቸውን ሰጡ። ከዛም የድሬደዋ ከተማን ዌብ ሳይት ለመስራት ቻልኩ ። ይህ ዌብሳይት የድሬደዋ ከተማን ታሪክ የያዘ ፣ የድሬደዋን የመስህብ ቦታዎችን በደንብ አድርጎ የሚያሳይ ነበር። ከዚህ በሁዋላ የዌብሳይት ልማት የሚባለው ነገር እየሳበኝ መጣ።

ምን አዲስ ፦ ድሬቲዩብ ፣ ከ2000 እስከ 2002 ባሉት ጊዜያት ብዙ ፈተናዎችን አልፎ ነበር። በሰዎችም ዘንድ መታወቅ የጀመረው ከ 2002 በኋላ እንደሆነ ይታወቃል።ከ2002 በኋላስ?

ቢንያም ፦ ከስራው ገቢ እንዲገኝ ማድረግ ነበረብኝ ። ህጋዊ ማድረግም ግድ ነበር። ከ2002 በኋላ ራሱን የቻለ ይዘት ፈጥረን ነበር። እኔን ጨምሮ 3 ሰዎች አብረውኝ መስራት ጀመሩ። ከዚያ ድሬ ቲዩብ መታወቅ ጀመረ።

ምን አዲስ፦ ብዙ ሰዎች ድሬ ቲዩብ ገቢው ምንድነው እያሉ ይጠይቃሉ። እስቲ ንገረን።

ቢንያም፦ በአብዛኛው የዌብ ሳይትን ቢዝነስን ሊወስን የሚችለው ጎብኚው ነው። በውጭው አለም ፣ በአፍሪካ እንደ ጋና ፣ ናይጄሪያ ባሉ ሀገራትም ድርጅቶች ዌብ ሳይት ላይ ማስታወቂያ ማስነገር ለምደዋል። የእኔ ተጠቃሚዎች በአብዛኛው ከአሜሪካ ነበሩ። ያ ዳያስፖራ የእኔ ዌብሳይት ላይ ሲመጣ ድርጅቶች ደግሞ ለእነዛ ሰዎች ማስታወቂያቸውን ማሳየት ይሻሉ። ጎግል ደግሞ ይህንን ይሰራል ። እኔ ከጎግል ጋር የራሴ ስምምነት አለኝ ። ጎግል ለእኔ ማስታወቂያያመጣልኛል ።ስለዚህ ጎግል የራሱን ኮሚሽን ይወስድና ቀሪውን ክፍያ ለእኔ ይከፍላል። ከአሜሪካ ቁጭ ብለህ ድሬቲዩብን ስትከፍት የሚመጣው ማስታወቂያ አሜሪካ ላሉ የሚሆን ነው። ከኢትዮዽያ ስትከፍት ደግሞ ለኢትዮዽያ የሚሆን ማስታወቂያ አለ ።ሲስተሙ በመጠኑ የተወሳሰበ ቢመስልም ግን የሚሰራበት ነው። ብዙ ድርጅቶች ድረገጽ ላይ ማስታወቂያ ማስነገር አልለመዱም ። ጋዜጣላይ ማውጣት ነው የለመዱት ።ድሬ ቲዩብ በሳምንት ብቻ እስከ 4 ሚልዮን ተጠቃሚዎች ጋር ይደርሳል ። ወደ ጋዜጣ ስትመጣ ግን በአሁኑ ሰአት ከ10,000 በላይ ቅጂ በሳምንት የሚያሳትም የለም ። በአሁኑ ሰአት ድሬ ቲዩብ ከቴሌቪዢን ጋር ይፎካከራል ። እንዲያውም በጎብኚ ብዛት ከሃገር ውጭ እንበልጣቸዋለን ።

ምን አዲስ፦ ድሬቲዩብን የሚያስተዳድረው ሪፍሬሽ ሚዲያ ሲጀመር ለ 3 ሰዎች የስራ እድል ፈጥሮ ነበር ፤፤ አሁንስ?
ቢንያም ፦በአጠቃላይ 25 ሲሆኑ 9 ያህሉ ቢሮ ውስጥ የሚሰሩ ናቸው።

ምን አዲስ ፦የድሬ ቲዩብ አዋርድ ዋና አላማው ምንድነው?
ቢንያም፦በኪነጥበብ ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በተለይ ትልቅ ሚና አበርክተው ያልታወቁትን ማድነቅ ነው አላማችን ።በ2006 ይህን አድርገናል ። ዘንድሮም ይሄው ነው ሀሳባችን ።

ምን አዲስ፦ የድሬ ቲዩብ የፌስ ቡክ ገጽ ብዙ ጎብኚዎች እንዳሉት ይታወቃል። ብዙ አስተማሪ ጽሁፎችም ይስተናገዱበታል። እስቲ ስለ ድሬ ቲዩብ የፌስ ቡክ ገጽ እንጨዋወት ።

ቢንያም ፦ ሰው ፌስቡክ ላይ በጣም ተጠቃሚ መሆን ጀምሮአል ። ሰዎች ፌስቡክ ላይ ሲገቡ ፎቶግራፍ ከማየት በዘለለ ለምን መረጃ አያገኙም? በሚል ነው ፌስ ቡክን የጀመርነው ።በ2002 ግድም ነበር የጀመርነው ።በአሁኑም ሰአት ትጉህ የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ወደ 1ነጥብ 7 ሚልዮን ተጠግተዋል ። ያንን ታሳቢ አድርገን ነው የምንሰራው ። ፌስቡክ ይህን በማድረጋችን የሚከፍለን ክፍያ አይኖርም። ሆኖም ሰዎች ወደዋናው የድሬ ቲዩብ ድረገጽ እንዲገቡ ያስችላቸዋል ። በአጠቃላይ ለህብረተሰቡ አንድ ነገር ለማበርከት እናስባለን ። በፌስቡክ ጥሩ መረጃ እንዲገኝ ነው ዋናው አላማችን ። 1ነጥብ 7 ሚልዮን የፌስ ቡክ ደንበኛ ማፍራታችን ያበረታታናል ።የፌስቡክ ገጻችን የማናውቃቸውን ጸሃፊዎች አስተዋውቆናል ።

ምን አዲስ፦ለወጣቱ ምን ትመክራለህ ?

ቢንያም ፦ ሰው ከመደበኛ ትምህርት ውጭ ስኬታማ መሆን ይችላል ።ማንበብ ነው እኔን የለወጠኝ ። ስለዚህ ወጣቱ ያነብ ዘንድ ነው የምመክረው ፤፤
ምን አዲስ ፦ አመሰግናለሁ ፤፤
ቢንያም ፦ እኔምአመሰግናለሁ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *