ሠራዊት ፍቅሬ
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን፣ በሚድያ እና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በህዝብ ዘንድ የማይረሱ ባለሙያዎችን ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
እስከ ዛሬ 310 ሰዎችን ኣፈላልገን ታሪካቸውን ሰንደናል፤ ለወደፊትም በዚህ ስራችን ጠንክረን እንቀጥላለን፡፡ በ 2014 “የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ” በማለት ታሪኮችን ዳገስ ያለ ጥራዝ የወጣውን መጽሃፍ አሳትመን ያሰራጨን ሲሆን፤ ባለታሪኮቹን ጨምሮ፤ ብዙ ሰዎች ማጣቀሻ ሰንድ እያደረጉ እንደሚጠቀሙበት መረጃ አለን። በዚህም ተበረታትተናል።
ድርጅታችን የህይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረጉ የበርካታዎችን ቤት እያንኳኳ “ምን ታሪክ አለኝና?” የሚሉና ታሪካቸው በስፋት ተደራሽ ያልነረ፤ ያልተዘመረላቸው ሰዎችን፤ የህይወት ገጽ እያስነበብን እንገኛለን፡፡ የእኛን መስፈርት ያሟሉ እንጂ የበርካታ ባለመልካም ተሞክሮ ዜጎችን ታሪኮችን መሰነዳችንን እንቀጥልበታለን፡፡ በህይወት የማይገኙትን አበርክቶም ለማስነበብ የተቻለንን እናደርጋለን፤ ምክንያቱም የግለሰብ ታሪክ ከግለሰቡ ባለፈ የሀገር ታሪክ ነው ብለን ስለምናምን፡፡ መዝገበ-አእምሮ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ ቅጽ 2 በቅርቡ ታትሞ ለንባብ ይበቃል፡፡ 200 የሚድያ ፤ የስነ-ጽሁፍ የቴአትር እና የፊልም ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ጥራዝ ብዙ ቁምነገር ይገበያሉ፡፡ ከባለታሪኮቹ መካከል ሠራዊት ፍቅሬ አንዱ ነው። ሠራዊት ሁለገብ የጥበብ ሰው ሲሆን በቴአትር ፣በሬድዬ ድራማ በፊልምና በማስታወቂያ ሥራዎቹ ይታወቃል። ለዛ ባለው ጽሁፍና ንግግሩም ይታወቃል ። ዕዝራ እጅጉ እና አይናለም ሀድራ የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው ሰንደውታል።
እድገትና ትምህርት
ወደ 30 አመታት ገደማ በኪነጥበብ ውስጥ ያሳለፈው ተዋናይና የማስታወቂያ ባለሙያ ሰራዊት ፍቅሬ ትውልድና እድገቱ እዚሁ አዲስ አበባ በተለምዶው ካዛንችስ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው። አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ የመዘጋጃ ቤት የሂሳብ ሹም ከነበሩት አባቱ ከአቶ ፍቅሬ ምህርካና ከእናቱ ከወ/ሮ በለጥሻቸው ማመጫ በ1957 ዓ.ም መስከረም 17 ቀን ተወለደ። የመጀመሪ ደረጃ ትምህርቱን በአስፋው ወሰን 1ኛና መለስተኛ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የ2ተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በምስራቅ አጠቃላይ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቀው።
የኪነጥበብ ዝንባሌው መታየት የጀመረው በትምህርት ቤት ቆይታው ነው። በተለይ በአማርኛ ክፍለ ጊዜ መምህራኑ መጻህፍቶች ይተርኩ ነበር ተማሪዎችም እንዲተርኩ ይደረግ ነበር። በተጨማሪም ጭውውቶች ፣ግጥሞችና መጣጥፎች ይቀርቡ ነበርና ሰራዊት ንቁ ተሳትፎ ነበረው።ከሰፈሩ ልጆች ጋር ያቋቋሙት ሃራምቤ ቡድን ላይም ኳስ ከመጫወት ባለፈ ሰራዊት ፍቅሬ ዘገባ ይሰራ ነበር፤ መጣጥፎችንም አዘጋጅቶ በማቅረብ ይታወቃል።
ብሄራዊ ውትድርና
በደርግ የአገዛዝ ዘመን ወጣቶቸ ጦርሜዳ በመዝመት የዜግነት ሃላፊነታቸውን የመወጣት ግዴታ ይጣልባቸው ነበር። ዘማቾች በወቅቱ የኢትዮጲያ የበኩር ልጆች እንዲሁም ብቁ ዜጎጅ እየተባሉ ይሞገሱ ይበረታቱም ነበር።ሰራዊትም ተራው ደርሶ 12ተኛ ክፍል ካጠናቀቀ በኋላ በ1977 ዓ.ም ብሄራዊ ውትድርና ዘመተ። በወቅቱ አርቲስት አስረስ በቀለም ነበር። በደማቅ ስነስርአት ተመርቀው ተሸኙና ታጠቅ ጦር ሰፈር ጦላይ ገቡ ለስልጠና።
በስልጠና ቆይታቸው በየብርጌዱ የኪነጥበብ ቡድን ተቋቁሞ ነበርና የነሰራዊት ብርጌድ በቲያትርም በሙዚቃም ጥሩ ተሳትፎ ነበረው።በኋላም ከየብርጌዱ ተውጣጥተው በማዕከል ደረጃ አንድ የኪነጥበብ ቡድን ሲመሰረት ሰራዊትና ጓደኞቹ ተመርጠው ቡድኑን ተቀላቀሉ። ቡድኑ ለግቢው ማህበረሰብ አጫጭር ጭውውቶች፣ መነባንብ ሙዚቃና ሌሎች የኪነ ጥበብ ስራዎችን ያቀርብ ነበር። የ6 ወራት የውትድርና ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ ሁሉም ወደ ግንባር ሲዘምት ዋናው የኪነጥበብ ቡድን አባላት እዛው እንዲቆዩና በዘርፉ እንዲያገለግሉ ሲደረግ ሰራዊት ፍቅሬም የቲትርና ስነጽሁፍ ክፍል ተጠሪ ሆኖ ማገልገል ጀመረ።
ዘማቾች 6 ወራት በስልጠና ከቆዩ በኋላ 2 አመታት ማገልገል ይጠበቅባቸው ነበርና ሰራዊትና አጋሮቹ ለ2 አመት ከ6 ወር ሌላም 3 ወር ባጋጣሚ ተጨምሮ 2 ዓመት ከ9 ወር አገልግለው የብቁ ዜጋ መታወቂያቸውን ተረከቡ። ግዳጃቸውን ጨርሰው ሊመለሱ ሲሉ በሲቪል እንቅጠራችሁ ቆዩ የሚል ጥያቄ ቢቀርብላቸውም እነሰራዊት መመለሱን መርጠው ወደ መኖሪቸው ተመለሱ። ተመላሾቹ በጋራ በመሆን የቲያትር ቡድን አቋቋሙ። እነሰራዊት በቡድኑ ውስጥ ጥሩ ዝግጅት በማድረግ አጫጭር ጭውውቶችን በየትምህርት ቤቶች እየዞሩ አቅርበዋል።
አፍለኛው የቲያትር ቡድንና ሌሎች ስራዎች
የአፍለኛው የቲትር ቡድን ምስረታ ወደ 1983 ዓ.ም ይወስደናል። ሰራዊት ፍቅሬ፣ ሰለሞን አለሙ፣ድርብ ወርቅ ሰይፉ፣አዜብ ወርቁና ፍሬህይወት መለሰ በጋራ በመሆን ነው ቡድኑን ያቋቋሙት።የቡድኑ አባላት የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ተወዳጅ ስራዎቻቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል ። ከቲያትር ቡድኑ ተሳትፎው ባሻገር ሰራዊት ፍቅሬ በለገዳዲ የሬዲዮ ጣቢያ የሬዲዮ ድራማ ይሰራ ነበር። በጣቢያው ይተላላፍ የነበረ ከማስታወሻ ደብተራችን የተሰኘ ዝግጅትንም ያቀርብ ነበር ቲትሮችም ሲመጡ ይሰራ ነበር። በቲያትር ረገድ ከከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን ከዳንኪራው ጀርባን፣ ፍራሽ ሜዳን፣የከርቸሌው ዘፋኝንና ሌሎች ስራዎችን ለመድረክ አብቅቷል።
ሰራዊት ፍቅሬ በሰፊው ከህዝብ ጋር የተዋወቀው በኢትዮጲያ ሬድዮ ይተላለፍ በነበረው “ሸምጋይ” ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ነው።ሰራዊት ፍቅሬ በድራማው በህዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ መሆን የቻሉትን አብዬ ዘርጋውን ወክሎ ይጫወት ነበር። ድራማው በ5 ክፍል ሲጠናቀቅ በህዝቡ ብርቱ ጥያቄ ተራዝሞ እንደገና ለ1 አመት ከ6 ወር ገደማ እንዲሄድ ተደርጓል። በሬዲዮ ተሳትፎው የኢትዮጲያ ቤተሰብ መምሪና ሌሎች ማህበራዊ ስራ ላይ በተለይም ጤና ላይ ያተኮሩ ድርጅቶች ስፖንሰር የሚያደርጓቸውን በርካታ አስተማሪ ጭውውቶች ሰርቷል።
አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ በፊልም ስራም አሻራውን አሳርፏል። ዳግማዊት ፣ ሰማያዊ ፈረስ፣ሰካራሙ ፖስታ፣ ሄሮሺማ፣ ይፈለጋልና ወርቅ በወርቅ ስሙ የተጠራባቸው ፊልሞች ናቸው። በማስታወቂያ ኢንደስትሪውም መጀመሪያ በሰራዊትና ሙላለም ፕሮሞሽን በኋላ በሰራዊት መልቲ ሚዲያ ሰው ልብ የገቡ በርካታ ማስታወቂዎችን ሰርቷል። በዚህ ዘርፍም የራሱን መልክ ማሳረፍ ችሏል።
ልዩ ሽልማት
አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ በስራው ካስመዘገበው ውጤት በተጨማሪ በእምነት ዘንድም ባደረገው አስተዋጽኦ እንደ እምነቱ ስርአት ሽልማት ተበርክቶለታል።
ለደብረ መንክራት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ባረከተው አስተዋጽዎ የገዳሙ የበላይ ጠባቂና የወላይታ ሃገረ ስብከት ሊቀጳጳስ እንዲሁም የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ ይስሃቅ “በኩረ ጥበባት ”ብለው ሰይመውታል። የወላይታ ባህልን መሰረት ያደረጉ ሌሎች ሽልማቶችም ተበርክተውለታል።የአቢሲኒያ ሽልማትንም ከእጁ ያስገባ ነው። ሠራዊት ከባለቤቱ ሮማን አየለ ጋር ጋብቻ መስርቶ 2 ልጆችን ወልዷል ።