ሀሊማ ዑስማን

 ሀሊማ ዑስማን

የአፋን ኦሮሞ ምርጥ ሴት ጋዜጠኛ

ሀሊማ በአፋን ኦሮሞ ጋዜጠኝነት ውስጥ ከ30 አመት በላይ የሰራች፤ በመዝናኛ እና በማህበራዊ ፕሮግራሞች ላይ ድንቅ አቅሟን የፈተሸችና አሻራ ኖረች ናት፡፡ ፊልድ እየሄደችም በትጋት ሙያዋን ያስከበረች ናት፡፡ ሀዊ የተሰኘውን ታዋቂ ልቦለድም ተርካለች፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንደ ሀሊማ አይነት ሰዎች ታሪካቸው  ሊሰነድ ይገባል ብሎ ስለሚያምን እነሆ ሀሊማን ይዘን ብቅ ብለናል፡፡    

ትውልድ እና ልጅነት

ከአባቷ ሀጅ ዑስማን መሐመድ ከእናቷ ከወ/ሮ ራህመቴ መሐመድ በ1954 ዓ/ም በወለጋ ክ/ሀገር ደምቢ ዶሎ ከተማ ተወለደች። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በደምቢ ዶሎ ከተማ የኦሊቃ ድንግል ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃን  በአሜሪካ ሚሽን በተልምዶ ቤቴል ኢቫንጀሊካል ትምህርት ቤት ተማረች። በሁለተኛ ደረጃ መልቀቅያ ፈተና በተለያዩ ምክንያቶች ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት ስላልመጣላት ድጋሚ በግል ተፈታኝ ሆና ባመጣችው ውጤት በአ/አ ንግድ ሥራ ኮሌጅ የማታ ትምህርት ክፍል በሂሣብ መዝገብ አያያዝ በሰርተፊኬት ተመረቀች።

ስራ ፍለጋ

ከሁለት ዓመት የኮሌጅ ቆይታዋ በኋላም በተመረቀችበት ሙያ ሥራ መፈለግ በጊዜው አንዱና ፈታኙ ወቅት ነበር፡፡ ሆኖም በትዕግስትና ማስታወቂያዎችን በመከታተል ቆየች። በሁለት ክፍት የስራ ቦታዎች ላይም ተወዳድራ ሥራ የማግኘት ዕድል ቢገጥማትም  ሥራው ከአ/አ ውጪ በመሆኑ

  1. ኛ በወቅቱ ከቤተሰብ ተለይታ ዘመድ ጋር መኖር በራሱ ከብዷት ብቻዋን መቋቋም የምትችል ስላልመስላት  መወሰን አልቻልችም ነበር።
  2. ኛ ቤተሰቦቿም ብቻዋን የትም እንዳትንቀሳቀስ ስላሳሰቧት ላለመሄድ ወስና ያገኘቻቸውን ዕድል ለማሳለፍ   ተገደደደች። ዋናው አላማዋ አ/አ ውስጥ ሥራን ፈልጎ ማግኘት ስለሆነ ተስፋ ባለ መቁረጥ ለተለያዩ መ/ቤቶች CV በመበተን አንዱ የሥራ መፈለጊያ ዘዴ አድርጋ ወደ አ/አ ንግድ ም/ቤት አመራች።

ፍቃደኛ ከሆንሽ መጀመር ትችያለሽ

ያኔ የነበረውን ሁኔታ ሀሊማ ስታስታውስ :‹‹….ከአስተዳድር ቢሮው የተሰጠኝ ምላሽ በሥራው ፍላጎት እንዳለኝ ከተጠየኩኝ በኋላ  በተማርሺው ሙያ ሌሎች ከኮሌጁ ለመጡ ተማሪዎች ልምምድ እየሰጠን ነው፡ እና ፍቃደኛ ከሆንሽ መጀመር ትችያለሽ የሚል ነበር። የም/ቤቱ አስተዳዳሪ ምላሽ በደምዎዝ የተቀጠርኩ ያህል ደስታን አጎናጸፈኝ። አ/አ ሥራ አገኘሁ የሚል ሞራልም ሰጠኝ፡፡ አመስግኜ ልምምዱን ጀመርኩ።›› ትላለች ትዝታዋን ስታወጋን፡፡

ሀሊማ ፤በመጀመሪያው 3 ወራት በትጋት ከሠራች በኋላ እስከ መቼ በነፃ እሠራለሁ የሚል ሀሳብ ውስጧ ይመላለስ ጀመረ፡፡  በተጓዳኝም  ሌሎች የስራ ዕድሎችን ለመሞከር ወሰነኩ። ከስድስት ወር ነፃ የስራ ልምምድ  በኋላም ካናዳ ከሚኖር ዘመዷ ጋር እየተጻጻፈች ከቻለ ከሃገር እንዲያስወጣት ጠየቀች፡፡በአረብ ሃገር በኩል መሞከር እንዳለባት  አሳወቃት፡፡ ብዙ  ቢሞክርላትም የሚሳካ አልሆነም፡፡

እድልን መሞከር 

ሀሊማ የአረብ ሀገሩ አልሳካ ሲል ደግሞ ወደ ሌላ እድል መዞሯን ትናገራለች፡፡ ‹‹…..የሁለተኛ ዕድል ሙከራዬ አ/አ ት/ት መገናኛ   ጊዜያዊ ሥራ እንደወጣ ሰማሁ፡፡ ወደዚያው አቀናሁ። በዳታ ለቀማ እና ሪከርድ ክፍል በወጣው ቦታ ላይ ተወዳድሬ አለፍኩ፡፡ ወዲያውም በጊዜያዊነት ሥራ ጀመርኩ። በዚሁ ድርጅት ውስጥ ለጥቂት ጊዜያት ሰራሁ፡፡ ድርጅቱ ለገዳዲ ሬድዮ ጣቢያ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በተለያዩ ቋንቋዎች በሚተላለፉ የትምህርት በሬድዮ ፕሮግራም የአፋን ኦሮሞ ስክሪፕት በትርፍ ጊዜ እንዳነብ ተፈቀደልኝ።  

እንግዲህ ለዛሬው የጋዜጠኝነት ሙያዬ መሠረት የሆነኝ  ይህ ድርጅት ነው፡፡   በትምህርት በሬድዮ ፕሮግራሙ ላይ የተዘጋጀውን ፕሮግራም ለማንበብ ብቻ ነበር። ሆኖም ግን ዝግጅቱን አስተማሪ እና አዝናኝ በሆነ መልኩ ለአድማጭ በጥሩ ሁኔታ በማቅረብ ጥሩ የሚባል ተቀባይነትን አገኘሁ። እስክሪቱን ሳነብ የነበረኝ ክፍያ በአንድ እስክሪፕት ማለትም ከ 20 እስክ 30 ደቂቃ ፕሮግራም ከ10ብር ያነሰ ነበር። ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ከዳታ ለቀማው ጎን ለጎን የስክሪፕት ማንበቡንም ሥራ እያከናወንኩ በ1978ዓ/ም መጨረሻ አካባቢ ያለኝን የሥራ ልምዶችና የትምህርት ብቃት ይዤ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር የፕሮግራም ክፍል አመራሁ።›› ስትል ሀሊማ ከለገዳዲ ሬድዮ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ያደረገችውን ሽግግር ትናገራለች፡፡

ኢትዮጵያ ሬድዮ

በወቅቱ የፕሮግራም ክፍል ሃላፊ ለነበሩት ለአቶ ታደሰ ሙሉነህ ማመልከቻዋን አቀረበች፡፡ እርሳቸውም ወደ አፋን ኦሮሞ ዝግጅት ክፍል መሩላት። በዚያንጊዜ የዝግጅት ክፍሉ አስተባባሪ የነበሩት አቶ ኩማ ኤደኤ ማመልከቻየን አይተዉ በለገዳዲ ሬድዮ ጣቢያ የማቀርበውን ዝግጅት  እንደሚከታተሉት እና ለሬድዮ የሚመጥን ጥሩ ድምፅ እንዳላት ገለጹላት፡፡ በቦታው ማስታወቂያ ሲወጣም ተከታትላ እንድትወዳደር መከሯት።

በተባለችው መሠረት ተመላልሳ ስትጠይቅ ከቆየች በኋላ በትርፍ ሰዓት ሥራ እንድትሠራ ተፈቀዶላት የአንድ እስክሪፕት ንባብ ለገዳዲ ሲከፈላት በነበረው  ሂሳብ ተስማምታ ስራውን  ጀመረች። በወቅቱ ክፍያው አነስተኛ በመሆኑ የሥራ ባልደረቦቿ ለተለያዩ ፕሮግራሞች የሚቀርቡ ዝግጅቶችን እስክሪፕቶች እንድታነብ እና ክፍያው ከፍ እንዲልላት ይረዷት ነበር። ባጠቃላይ ድምጿም ከሣምንት እስከ ሣምንት ከአየር ላይ አይጠፋም ነበር። በዚህም ያዳበረችው ልምድና የሙያ ፍቅር ተደማምሮ  ሁለገብ ሠራተኛ  እንድትሆን ረዳት፡፡

ሀሊማ የዛን ጊዜ የስራ ውድድሩን በተመለከተና አጠቃላይ በአፋን ኦሮም ዝግጅት ክፍል ስለነበራት ቆይታ ስታነሳ ይህን አካፍላናለች፡፡ ‹‹…ከተወሰኑ ወራት በኋላ ፍሪላንስ ሠራተኛ ለመቅጠር በወጣው ማስታወቂያ  መሠረት ለአማርኛ፣ ለትግረኛ እና ለኦሮምኛ ክፍል ተወዳድረን ተቀጠርን። በወቅቱ ከተቀጠርነው ሰዎች መካከል ለአማርኛ ክፍል በልሁ ተረፈ፣ ለትግርኛ ትርሃስ እንዲሁም ለኦሮምኛ ክፍል እኔ ሐሊማ ዑስማን ነበርን። በእኛ ጊዜ መሆኑን እርግጠኛ ባልሆንም እነ ዓለምነህ ዋሴ፣ ዋጋዬ በቀለ፣ ቡርትካን ሐረገወይንን ጨምሮ ፍሪላንሰሮች ነበርን፡፡  ለጊዜው ያላስታወስኳቸው ሌሎችም በርካቶች ነበሩ። የፍሪላንስ ጋዜጠኞች እንባል እንጂ እኛ ግን ሙሉ ጊዜያችንን በጋዜጠኝነት ሥራ ላይ ነበርን። በዚሁ ሁኔታ ከሶስት ወይንም ከአራት ዐመታት በኋላ በ1983 ዓ/ም ሰኔ ወር በኢትዮጵያ ሬድዮ በቋሚ ሠራተኝነት ተቀጠርኩ። በሪፖርተርነት የተጀመረው የጋዜጠኝነት ሙያዬ እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት ክፍሉን በምክትል ቢሮ አስተባባሪነት በመምራት በኢትዮጲያ ሬድዮ የአፋን ኦሮሞ ዝግጅት ክፍል ከ1979 እስከ 1983 ለአራት ዓመታት በፍሪላንሰርነት ከ1983 እስከ 2009 ደግሞ በቋሚ ሠራተኛነት ካገለገልኩ በኋላ በ2009 ዓ/ም ጡረታዬን አስከብሬ በገዛ ፈቃዴ ሥራዬን ለቀቀኩ። ‹‹ ስትል ትዝታዋን አጫውታናለች፡፡

በወቅቱ በአፋን ኦሮም ቋንቋ አድማጭ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን እና ታዋቂነትን ካጎናፀፏት ፕሮግራሞች ውስጥ የእሁድ መዝናኛ፣ የጤና ፕሮግራም፣ የግብርና ፕሮግራም፣ እንዲሁም የዜና እና ውቅታዊ ዝግጅቶች ዋነኞቹ ናቸው።  ፕሮግራሞቹንም በማዘጋጀት በማቀናበር እና በኤዲቲንግ ሥራ ላይ ለረጀም አመታት  ሠርታለች። በመጀመሪያዎቹ የጋዜጠኝነት ሥራዎቿ ላይ በእሁድ መዝናኛ ላይ የሠራቻቸው ሥራዎች በጣም የማትረሳቸውና በጋዜጠኝነት ሕይወት ውስጥ እንድትቆይ ካደረጓት ፕሮግራሞች አንዱ ነው። በዚህ ፕሮግራም ውስጥ ከሚዘጋጁት የተለያዩ መሰናዶዎች  አንዱ የአጫጭር እና ረጅም ድራማ ለአድማጮቻችን የሚቀርብበት ነበር። በክፍሉ አዘጋጆች እና ከተለያዩ አድማጮቻችን የሚቀርቡት ድራማዎች እና ትረካዎች ላይ በድምፅም ፕሮግራሙን አቀናብራ ለጆሮ በሚጥም መልኩ በማቅረብም በኩል የጎላ አስተዋፅዎ ነበራት።   በአዘጋጅና ደራሲ ኢሳያስ ሆርዶፋ የተጻፈውን ሀዊ መጽሐፍ በሬድዮ በተላለፈው ድራማ ላይ የሀዊን ገፀ ባህሪ በመተወን ለተከታታይ ሣምንታት በማቅረብ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፋበታለች። በቅርቡም  ለ ኦንላይን ኦድዮ መጽህፍም የተረከችው ሀሊማ ነበረች፡፡

የእሁድ ፕሮግራም

ዝግጅትን በተመለከተ ከአንጋፋ የዝግጅት ክፍሉ ጋዜጠኞች  የሚዘጋጁ ጽሑፎችን በማቀናበርና ስክሪፕቱን በማንበብ አጭጭር የሬድዮ ስከሪፕቶችን በመዳፍ  እና በተለያዩ የትርጉም ስራዎች ላይም  የጎላ ተሳትፎ ነበራት። በሌላ በኩል በማህበራዊ ዘርፍ በሃገራችን የተከሰተውን የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት እና ቁጥጥር ሥራ ላይ መንግስት በመርህ ደረጃ ያስቀመጠው ዕቅድ ላይ በመመርኮዝ የኤች አይ ቪ ኤድስ ተኮር ትምህርትን በጤና ፕሮግራም ላይ ብቻ ሣይሆን በክፍሉ በሚዘጋጁ የተለያዩ ፕሮግራሞች በአጫጭር ጭውውቶች መልክ የተለያዩ ቃለ ምልልሶችን በመሥራት እና ባለሙያዎችን በማካተት ጥሩ አስተዋፅኦ አበርክታለች። የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት እና ቁጥጥር ሥራ ላይ በዝግጅት ክፍሉ የተሰጠው የአየር ሽፋን እና የተገኘው የባህሪይ ለውጥ እንዲሁም ችግሮቹ ላይ በመመርኮዝ የመጀመሪያ ድግሪ መመረቂያ ጽሑፏን አቅርባም ጥሩ ውጤት ማግኘት ችላለች።

ሀሊማ አሁንም የስራ ዘመኗን መተረክ ጀምራለች‹‹………..የዜና እና ወቅታዊ ዝግጅት ላይ በጣም ማስታወስ እና መግለፅ የሚፈለገው ነገር የአፋን ኦሮሞ ዝግጅት የዜና እወጃ የማለዳው ሰአት አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ ማንኛውም ዜና አቅራቢ እንደ ከባድ ችግር የሚያነሳው ነው። ለማለዳው የዜና እወጃ ሌሊት 9 ሰዓት ከእንቅልፍ ተነስቶ ከተለያዩ የዜና አውታሮቸ የተገኙ  ዜናዎችን ተርጉሞ ማዘጋጀት እጀግ ፈታኝ ሥራ ነበር።

ሆኖም ግን እኔም እንደ አንድ ጋዜጠኛ ችግሩን ተቋቁሜ በሠራሁባቸው ጊዜያት አንድም ቀን የሰዓት ክፍተት ሳይኖርብኝ መወጣቴን እንደ ትልቅ ድል እቆጥረዋለሁ። በዚህ ወቅት እንደገጠመኝ የማስታውሰው ነገር ቢኖር የማታ ዜና ተረኛ አንባቢ ሆኜ ማለዳ ገቢም እኔው ነበርኩ፡፡

እና ሰርቪስ እቤቴ እንዳደረሰኝ በቂ እንቅልፍ ለማግኘት በቶሎ ተኛሁ። ታድያ ሌሊት 6 ሰዐት ላይ የማለዳው ሰርቪስ የመጣ መስሎኝ ከእንቅልፌ ባንኜ በፍጥነት ሰርቪስ ለመጠበቅ ስወጣ ጭር ያለ ውድቅት ሌሊት ነበር። በድንጋጤ ወደ ቤት ተመልሼ ሰዓት ስመለከት ከሌሊቱ 6፡30 ይላል። ተመልሼ ለመተኛት ስላልቻልኩ ሰርቪሱ እስኪመጣ ጠብቄ በዛው ሄድኩ። እኔ ተረኛ ማለዳ ገቢ በሆንኩባቸው ቀናት ቤተሰቤም ጭምር ከእኔ ጋር እየባነኑ ማደር ፈታኙ ጊዜ ነበር። በተለይ ይህች እኩለ ሌሊት ሮጬ የወጣሁብትን ቀን አልረሳውም።›› በማለት አጫውታናለች፡፡

በፊልድ ሥራ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች ተዘዋውራ ከሠራቻቸው ሥራዎች ዋነኞቹ

  • በ2002 በሃገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የምርጫ ዘገባ በቄለም ወለጋ የተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች ላይ በመዘዋወር ዘገባ አጠናክራለች።
  • ለበዓል ዝግጅት ክፍሉ በስፖንሰር ዝግጅት በሚሠራው ሥራ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ቦረና ዞን ቡሌሆራ ከተማ እንዲሁም በአርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች  ነቀምት ግምቢና ሽዋ አካባቢን በመዘዋወር ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፕሮግራሞችን ለማጠናከር ችላለች።

ለድምፅ ቀረፃ ፊልድ ይዘው የሚወጡት 25 ኪሎግራም የሚመዝነው (ኡኸር) የሚባለው የድምፅ መቅረጫን ዛሬ ላይ ሆና ስታስበው ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባው ያስብላታል። በአጠቃላይ የፊልድ ሥራ ላይ ከተለያዩ የሲቪል ሠራተኞችና እና ከሕብረተሰቡም ብዙ ትምህርት ይዛ ትመለስ ነበር። በአንፃሩም ብዙ ችግሮችንም ተጋፍጣ የወጣችበትንም አላማ አሳክታ የተመለስችበት ወቅትም ነበር። እንደ ምሳሌ በአንድ ወቅት ወደ ኢሉባቡር ዞን የግብርና ፕሮግራም ለማሰባሰብ ወጥታ የቢሮ ኃላፊው ቀድመው ለተለያዩ ጋዜጠኞች ቃለ ምልልስ እንደ ሰጡና ለሀሊማ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ገለፁላት። ሀሊማም ተስፋ ባለመቁረጥ ተመላልሳ ስትጠይቃቸዉ  ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ጭራሽ ዜናውን ግዥኝ የሚል ህሳብ አመጡ፡፡  ከብዙ ልመና በኋላ  ፈቃደኛ ሆኑና ፕሮግራሙን ይዛ ወጣች።  ሌላ አንድ ችግር በፈልድ ላይ የምታነሳው ተደራራቢ ነገሮቸ ሲከስቱ ከተማ ውስጥ አልጋ  አጥታ የተንከራተተችበትን ጊዜያቶችን ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *